Sunday, March 2, 2014

አባ እስጢፋኖስ ዘጉንዳጉንዲና ተከታዮቹ ስለ ማርያም የሚያምኑት ምን ነበረ?

ከመምህር አዲስ
አባ እስጢፋኖስና ተከታዮቹ እስካሁን ድረስ መነጋገሪያ ሆነው እንደቀጠሉ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ምናልባትም በፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የተተረጐመው በሕግ አምላክ መጽሐፍ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ፀረ ማርያም እየተባሉ ይጠሩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ለዚህም በአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን በተደረሰው ተአምረ ማርያምና እርሱን በመሰሉ እንደማህሌተ ጽጌ ባሉ የዚያ ዘመን ድርሰቶች የእነዚህ ቅዱሳን ስም እንዲጠፋ ተደርጓል፡፡ ከዚህ የተነሣ ለደቂቀ እስጢፋኖስ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የነበረው አመለካከት በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ አስተምህሮ የተቃኘ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የእነዚህ ቅዱሳን ገድል ታትሞ ሲወጣ የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ አስተምህሮ ብቻ ሲናኝበት የነበረው መድረክ መልእክቱን እንዲቀይር ተገድዷል፡፡ በዚህ አቅጣጫ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ አንዳንዶች ደቂቀ እስጢፋኖስ ለማርያም የነበራቸው አመለካከት አሁን በኦርቶዶክስ እንዳለው ነው በማለት የእነርሱ እንቅስቃሴ የተሐድሶ እንቅስቃሴ አይደለም ለማለት እየጣሩ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ከደቂቀ እስጢፋኖስ ገድሎች ውስጥ አንዳንድ ነጥቦችን እየነቀሱ በማውጣት ፀረ ማርያም አለመሆናቸውን ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ደቂቀ እስጢፋኖስ ስለማርያም ያምኑ የነበረው ምን እንደሆነ እነዚህ ወገኖች ቆንጽለው የሚጠቅሱትን ብቻ ሳይሆን ሳይጠቅሱ የሚያልፉትንና በገድላቸው የተጻፈውን ሁሉ መመርመር ያስፈልጋል፡፡

        በቅድሚያ ደቂቀ እስጢፋኖስ በአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘንድ “ፀረ ማርያም” ተብለው መፈረጃቸውን ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም የሆነው ተኣምረ ማርያምን ወደ ገዳማቸው ስላላስገቡና ለማርያም ሥዕል አንሰግድም ስላሉ ነው፡፡ ተአምረ ማርያምን ወደገዳማችን አናስገባም ያሉትም መጽሐፉ ብዙ ኃጢአት የሰሩትን ማርያም አማልዳ አስማረቻቸው ስለሚል መነኮሳቶቻችን ይህን ካነበቡ በቀና ምግባር መኖራቸውን ትተው ንዝህላል ይሆናሉ ብለው ስለሰጉ ነው፡፡ (ደቂቀ እስጢፋኖስ በሕግ አምላክ ገጽ 128)፡፡ እንደተባለውም ሰው እንደፈለገው ኖሮ ተአምረ ማርያም እንደሚሰብከው ለድሃ በማርያም ስም በመመጽወትና በመሳሰሉት ስራዎች ሁሉ በማርያም ምልጃ የሚድን ከሆነ በወንጌል ማመን፣ እንደወንጌሉ ቃል መኖር ወይም ሰፊውን የኃጢአት መንገድ ትቶ በጠባቡ የጽድቅ መንገድ መጓዝ ቦታ ስለሌላቸው መንግስተ ሰማያት የድል ነሺዎች ስፍራ ሳይሆን የቀልድ ቦታ ነው የሚሆነው፡፡ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ሥራም ከንቱ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ተአምረ ማርያም በደቂቀ እስጢፋኖስ ዘንድ ተቀባይነት ማጣቱ ትክክለኛ ክርስቲያናዊ እርምጃ ነው፡፡ ለዚህም ነው “ዘሰይብል አፈቅረኪ ወኢያፈቅር  ተአምረኪ ክርስቲያናዊ ኢክርስቱን ውእቱ አይሁዳዊ ወሰርጸ እስጢፋ ሐሳዊ” ትርጉም “አንቺን እወድሻለሁ እያለ ክርስቲያናዊ የሆነ ተአምርሽን የሚጠላ እርሱ ክርስቲያን ሳይሆን አይሁዳዊና የዚያ የእስጢፋኖስ  ተከታይ ነው፡፡” ተብሎ አባ እስጢፋኖስ በማሕሌተ ጽጌ የተወቀሰው፡፡ 

        በአባ እስጢፋኖስ ገድል ውስጥ “ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፥ ቅዱሱ (አባ እስጢፋኖስ) ከሁሉም የመጀመሪያዋ በሆነችው በመንፈሳዊ ትንሳኤ ውስጥ ሆኖ ቅድስት ድንግል ማርያምንም እስኪያያትና ቃሏን እስኪሰማ ድረስ የተመሰገነች ሰማያዊት ምሥጢር በራእይ የሚያይ ሆነ፡፡” ተብሎ የተጻፈ ቃል አለ (ገጽ 69)፡፡ ይህን በተመለከተ ፕሮፌሰር ጌታቸው በሰጡት የግርጌ ማስታወሻው ላይ “አባ እስጢፋኖስና ተከታዮቻቸው ይከሰሱበት የነበረው አንዱና ዋናው ቅድስት ማርያምን አያከብሩም እየተባሉ ነበረ” ብለዋል፡፡ ይህም የሚጠቁመን እዚህ ስፍራ ላይ የማርያምን ስምና እርሷን በራእይ ማየት የሚለውን ሐሣብ የገድሉ ጸሀፊ ያገባው በማርያም ላይ የሚነሣባቸውን ክስ ለማስተባበል ይመስላል፡፡  

        ደቂቀ እስጢፋኖስ ውዳሴ ማርያምንና አንቀጸ ብርሃንን ይደግሙ እንደነበር፣ ምስለ ፍቁር ወልዳ የተሰኘውን የማርያምን ሥዕል በየመጽሐፎቻቸው ስለው እንደተገኙ ፕሮፌሰር ጌታቸው ገልጸዋል (ገጽ 30)፡፡ ከዚህም በቀር ደቂቀ እስጢፋኖስ ታስረው በንጉሡ ሰፈር እየተጠበቁ ሳለ የጸሎት ሰዓት ደርሶ እንደተለመደው የጸለዩ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በጸሎታቸው ውስጥ “የአምላክ እናት ሆይ በምሕረትሽ ጥላ ሥር ተደግፈናል በጭንቃችን ጊዜ ልመናችንን አትናቂ” ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ በዚህም በዙሪያቸው የነበሩና የንጉሡ አስተምህሮ ደጋፊዎች በፊት ስለማርያም ይጠረጥሯቸው ስለነበር በዚህ ጸሎታቸው ተደንቀዋል (ገጽ 140)፡፡ ለአንዳንዶች እነዚህና የመሳሰሉት ነገሮች ደቂቀ እስጢፋኖስ የተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጆች አልነበሩም እንዲሉ አድርገዋቸዋል፡፡

        በቅድሚያ ደቂቀ እስጢፋኖስን መመዘን ያለብን በዘመናቸው ይዘው በተነሡት የተሐድሶ ሐሳብ እንጂ አሁን በሚታየው የተሐድሶ እንቅስቃሴ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ደቂቀ እስጢፋኖስ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረታቸውና የሁሉም ነገር መለኪያ አድርገው መንቀሳቀሳቸው ትልቁ እውነት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሌላ መጨመር እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡ ለምሳሌ አቡነ በርተሎሜዎስ በንጉሡ ፊት ቀርቦ በሰጠው ምስክርነት “ሥርዐት አሟላለሁ እያልህ እንደዚህ የምትጥረው ለምንድነው? በጽዋ ውስጥ ያለ ጐደሎ ውሃን ውሃ ይሞሉበታል፤ ከሙሉው ላይ ቢጨምሩበት ግን ይፈስሳል፡፡ አሁን የሐዋርያትና የነቢያት ሥርዐት ሙሉ ሆኖ ሳለ በላዩ የምትጨምርበት ምንድነው?” ብሎታል (ገጽ 123 እንዲሁም ገጽ 112)፡፡ ከዚህም ምስክርነት የምንረዳው ለእነርሱ መሠረታቸው “የእግዚአብሔር መጻሕፍት” የሚሏቸው ብሉያትና ሐዲሳት ናቸው (ገጽ 199)፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ የሚጠብቋቸው ሥርዓቶችና ልማዶች መኖራቸውም እውነት ነው፡፡  እንዲህ ያደርጉ የነበረው ግን በአንድ በኩል እነዚያ ሥርዓቶች ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር የማይጋጩ መሆናቸውን በዘመናቸው በነበራቸው አመለካከት መዝነው ይመስላል፡፡ እያንዳንዱን ሥርዓትም ለመቀበልና ለመጠበቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ይፈልጉለታል፡፡ ለምሳሌ ደቂቀ እስጢፋኖስ ታቦቶች ነበሯቸው፤ “የእግዚአብሔር ታቦቶች” ብለውም ነበር የሚጠሯቸው (ገጽ 257፣ 284፣ 305፣ 307፣ 308፣ 311)፡፡ ይሁን እንጂ ለታቦት እየሰገዱ ዛሬ እንደሚደረገው ታቦትን አያመልኩም ነበር፡፡ አቡነ ዕዝራ ከታቦቶች ጋር በመጣ ጊዜ “ለእግዚአብሔር ሰገዱ፡፡ [እርሱን/ዕዝራን] እጅ ነሱት፡፡ ስብሐት ለደረሰው ለእግዚአብሔር ስብሐት እናደርስለታለን” አሉ፡፡  … ዳዊት እንደ ዘፈነ ከታቦቱ ፊት ዘፈኑ፡፡” የሚል በገድላቸው ውስጥ ተጽፏል (ገጽ 311)፡፡ ነገር ግን  በዚህ መንገድ ለታቦት ሕጋዊነትን የሰጡት ብሉይ ኪዳን የሚለውን መሠረት አድርገውና ሐዲስ ኪዳን ስለታቦት የሚለውን ባለማስተዋል ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ ሌሎችንም ነገሮች ያደርጉ የነበረው በዚህ እሳቤ መሆኑ ሊታወቅ ግድ ነው፡፡ እንዲህ ስለሆነ ግን ደቂቀ እስጢፋኖስ የተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጆች አይደሉም ማለት አይቻልም፡፡ እጅግ በርካታ ጉዳዮች እነርሱን የተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጆች ያሰኟቸዋልና፡፡ ለዛሬው በማርያም ላይ ስለነበራቸው አቋም እንመልከት፡፡

        ከላይ የተጠቀሱትንና ከማርያም ጋር የተያያዙትን ጉዳዮች ሲፈጽሙ ማርያምን በማክበር እንጂ በማምለክ መንፈስ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ምስለ ፍቁር ወልዳ የተሰኘውን ሥዕል ቢስሉም ከመሳል ያለፈ ለሥዕሉ ስግደት ሲያቀርቡ አናይም፡፡ ሥእል የሰው እጅ ሥራ መሆኑን የተገነዘቡበት ሁኔታ ጎላ ያለ ነው፡፡ እንዲያውም ከአፄ ዘርአ ያዕቆብ ጋር ያጣላቸውም “በሥዕሏ ፊት ስገዱ” የሚለው በተአምረ ማርያም ውስጥ የሰፈረው የንጉሡ አዋጅ ነው፡፡ በአንድ ወቅት አንዱ የማርያምን ሥዕል ቢያሳያቸው የሥዕሉን ሁኔታ አድንቀው የሰው እጅ ሥራ ነው ማለታቸው ተጽፏል (ገጽ 30-31)፡፡

        አንዱ የሚያስገርመው ነገር በገድላቸው ውስጥ እንደተጻፈው ስለ ማርያም ካልተጠየቁ በቀር በራሳቸው ተነሣስተው ሲናገሩም ኾነ በትምህርታቸው ሲገልጹ አለመታየታቸው ነው፡፡ ስግደትንም በሚመለከት ለእግዚአብሔር ብቻ ነው እንጂ ለሌላ ለማንም አንሰግድም ብለው ነበር፡፡ ለማርያም ስገዱ ሲባሉ እንኳ፥ “ለልጇ ስንሰግድ እዚያው እናገኛታለን” የሚል ጥበብ የተሞላ የማምለጫ ምላሽ ነበር የሚሰጡት እንጂ ዛሬ ሰዎች ለስግደት ደረጃ አውጥተውለት የአምልኮትና የጸጋ ወይም የአክብሮት በሚል ለፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ለፍጡራን እንደሚሰግዱ ደቂቀ እስጢፋኖስ አልሰገዱም፤ በመጀመሪያ አንሰግድም ብለዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ተገርፈዋል (ገጽ 146፡147)፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዚያ ዘመን የነበረው ጳጳስ እንዲያወግዛቸው አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ባዘዘው ጊዜ ጳጳሱ ስለ ሃይማኖታቸው መረመራቸው፡፡ ሃይማኖታቸው የጸና ምግባራቸው የቀና መሆኑን ሲረዳም “ታዲያ ለማርያም ለምን አትሰግዱም?” ሰል ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም፥ “ካሁን በፊት ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ እሰግዳለሁ ሲባል እንጂ ለማርያም እሰግዳለሁ ሲባል አላገኘንም” አሉት፡፡ ይህም በቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ በሌሎች የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ለማርያም ስለ መስገድ የተጻፈ ነገር አለመኖሩን የሚያመለከት መከራከሪያቸው ነው፡፡ ጳጳሱ ግን፥ “ዕውቀት የሌላቸው ናቸው እንጂ ዕውቀት ያላቸው አያቃልሏችሁም፤ ስለዚህ ማርያምን ከሐዲዎች ይሏችኋል፡፡ ለማርያም ባትሰግዱ ስሕተት አይሆንባችሁም፤ ብትሰግዱ ኃጢአት አይሆንባችሁም፡፡ የሞታችሁ ምክንያት ለማርያም ስለ መስገድ አይሁን፤ ለንጉሥ ባለመስገድና የመምህራችሁን ስም ባለመስደብ እንጂ ለማርያም ባለመስገድ አይሁን፡፡ በዚህ ብትሞቱ ጥሩ ይሆንላችኋል፡፡ አሁንም ኑ አብረን እንስገድ አላቸው፡፡” ቅዱሳኑም የጳጳሱን ቃል ተቀብለው ከቤተ ክርስቲያን ገብተው ለማርያም አብረው ሰግደዋል፡፡  

ጳጳሱ እንዲህ ያደረገው ቅዱሳኑን ከውግዘትና ከመከራ ለማዳን ነበር፡፡ “ለማርያም ባትሰግዱ ስሕተት አይሆንባችሁም፤ ብትሰግዱ ኃጢአት አይሆንባችሁም፡፡ የሞታችሁ ምክንያት ለማርያም ስለ መስገድ አይሁን፤ ለንጉሥ ባለመስገድና የመምህራችሁን ስም ባለመስደብ እንጂ ለማርያም ባለመስገድ አይሁን፡፡” የሚለው የጳጳሱ አስተያየትና ምክር በቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ቢመሰረት ኖሮ “ካሁን በፊት ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ እሰግዳለሁ ሲባል እንጂ ለማርያም እሰግዳለሁ ሲባል አላገኘንም” ሲሉት ስገዱ የሚል ማስረጃ ባቀረበላቸው ነበር፡፡ ስለሌለው ግን የግል አስተያየቱን እውነትም ሐሰትም የተቀላቀለበት ምላሽ ሰጣቸው፡፡ “ለማርያም ባትሰግዱ ስሕተት አይሆንባችሁም” የሚለው እውነትነት አለው፡፡ “(ለማርያም) ብትሰግዱ ኃጢአት አይሆንባችሁም” የሚለው ግን ሐሰት ነው፡፡ ጌታ ከእርሱ በቀር ለሌላ እንዳንሰግድ ያዘዘውን ትእዛዝ በተንኮል የሚሽር ነውና፡፡ እውነትና ሐሰት ሲደባለቅ ደግሞ ውጤቱ ሐሰት ነው፡፡

እነርሱም ስግደትን በተመለከተ የሚሰሙት የእግዚአብሔርን ቃል እንጂ የሠዎችን ልምምድ እንዳልሆነ የገለጹበት አጋጣሚ አለ፡፡ ስግደትን በተመለከተ የቀደሙት ሰዎች ለሰዎች ሰግደዋል፤ ለምሳሌ አብርሃም ለዔሞር ልጆች፣ ያዕቆብ ለኤሳው ሰግዷል፡፡ ታዲያ አንተ ልታደርገው የኮራህበት ምክንያት ምንድነው? ተብሎ ሲጠየቅ የሰጠው ምላሽ የሚከተለው ነበር፡፡ “ምንድነው ይህ ብዙዎች አድርገዉታል በማለት የነገር ድካም? ከብዙዎች አድራጎት ይልቅ ሰማይና ምድር ያልፋል፤ ቃሌ ግን አያልፍም ያለው የእግዚአብሔር ቃል ምስከራ ይበልጣል፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ በኦሪት ለሱ ብቻ ካልሆነ ለሌላ እንዳንሰግድ በቃሉ አዞናል፡፡ በሐዲስ ኪዳን ደግሞ በሥራው ግልጽ አድርጎ አሳይቶናል፡፡ እንደዚያ አድርገን ፈለጉን እንድንከተል አዝዞናል፡፡ አሁንም ለሕግ መገዛት ከቻልክ ለእኛም ላንተም (ሕግ በወሰነው) ይሁነን፡፡ እንደዚህ እንዲሆን ካልፈቀድክ ራሱ ጌታ ‘አንድ ባሪያ ለኹለት ጌቶች መገዛት አይችልም’ ብሏል፡፡ እኛ ራሳችንን ለቅድስት ሥላሴ አስገዝተናል፡፡ ስለዚህ ለሌላ መገዛት አንችልም፡፡” (ገጽ 109፡ 185-86)፡፡

ሆኖም ጳጳሱ ነገሩን ያቀረበበት መንገድ ጥያቄ ከመጠየቅ ለማይቦዝነውና በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ የተመሰረተ ማስረጃ ለሚፈልገው የደቂቀ እስጢፋኖስ አእምሮ የተሻለ አሳማኝ ሆኖ የተቆጠረ ነጥብ ይመስላል፡፡ በሌላም በኩል ይህን ያላቸው ጳጳስ ስለሆነና በንግግሩ ለእነርሱ የወገነ ስለመሰለ ያቀረበላቸው ሐሣብ ምንም እንኳን የመረጃ እጥረት ያጋጠመው ቢሆንም ያልተጻፈን ነገር በህሊና ዳኝነት የመመልከት ሁኔታ ስለሚኖር በዚህ ምክንያት ተቀብለውት ይሆናል፡፡ ሆኖም በጳጳሱ ምክር ያደረጉትን ንጉሡ በቀና መንፈስ ስላልተመለከተው አልተቀበለውም (ገጽ 149፡151)፡፡

የደቂቀ እስጢፋኖስን የመጀመሪያ አቋም ኋለኞቹ ልጆቹ እየተዉ መሄዳቸውን ፕሮፌሰር ጌታቸው አብራርተዋል (ገጽ 31)፡፡ ሆኖም አንዳንዱ ሁኔታ በስልት የመጠቀም እንጂ ትተዋል የሚያሰኝ አይደለም ማለት ይቻላል ብዬ አስባለሁ፡፡ በአቡነ ዕዝራ ዘመን በማርያም ጕዳይ እንዳይከሰሱ በተለይ የአቡነ ዕዝራ ገድል ጸሀፊ በየጽሁፉ አንዳንድ ነገሮችን ሲጽፍ ማርያምንና እርሷን የሚመለከቱ ጕዳዮች ካጋጠሙት ያን እየጠቀሰ ነው የጻፈው፡፡ ለምሳሌ “.. በዚያ ጊዜ የማርያም ፍልሰታ ስለነበረ ስብሰባው ትልቅ ሆነ” ይላል (ገጽ 313)፡፡ ስለስብሰባው ታላቅነት ለመገልጽ ተነስቶ ሳለ የማርያም ፍልሰታን መጥቀሱ ለስልት ካልሆነ ሌላ ምን ሊባል ይችላል? በተጨማሪም አቡነ ዕዝራ ስለ ተቀበረበት ቀን “በሐምሌ 21 ቀን የማርያም በዓል ዕለት በሕይወቱ በተመኘበት መቃብር ቀበሩት” ይላል (ገጽ 214)፡፡ ሐምሌ 21 ማለት አይበቃም ነበር ወይ? ነገር ግን አሁንም በማርያም በዓል የሚል ሀረግ ደርቷል፡፡ የሐምሌ ማርያም ወርኃዊ እንጂ ዓመታዊ በዓል ስላይደለ ይህንንም ለስልት እንደተጠቀመበት መገመት ቀላል ነው፡፡ ይህንንም ሁኔታ ፕሮፌሰር ጌታቸው “ደራሲው ባጋጠመው ቁጥር ስለቅድስት ማርያም የሚታሙበትን ያስተባብላል፡፡” ሲሉ ገልጸዉታል (ገጽ 313)፡፡

አቡነ ዕዝራም እንዲህ ያደረገው በጥበብ ለመጠቀም እንጂ ማርያምን በተመለከተ የአፄ ዘርዓ ያዕቆብን አስተምህሮ በመቀበል አይመስልም፡፡ ይኸውም ሊታወቅ አቡነ ዕዝራ ከደብተሮች ጋር እንዲከራከር በተደረገ ጊዜ ደብተራዎቹ እስኪ በሰላመ ገብርኤልን ድገም አሉት፡፡ ጥበበኛው ዕዝራ ግን እነሱ ያላሰቡትን፥ ወበሳድስ ወርኅን (በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ ከሚለው ጀምሮ መልአኩም ከእርሷ ሄደ)” እስከሚለው ድረስ አለ፡፡ እነርሱም የአፄ ዘርዐ ያዕቆብን ድርሰት (በሰላመ ቅዱስ ገብርኤልን) ትቶ በሉቃስ ወንጌል የተጻፈውንና በጸሎት ዘዘወትር ተካቶ የሚገኘውን ክፍል ማለቱ ገረማቸው (ገጽ 300)፡፡

ይህም ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ እንደ ደረሰው የሚነገረውን በሰላመ ገብርኤልን ትቶ በሉቃስ ወንጌል 1፥26-38 ድረስ ያለውን ማንበቡ አቡነ ዕዝራ ስለ ማርያም መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት እንጂ ከዚያ ውጪ ባሉ ድርሰቶች ላይ ብዙም እንደማያተኩሩ ሊያመለክት ይችላል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ መመልከት የምንችለው አባ ዕዝራ በሰላመ ገብርኤልን ድገም ሲባል ወበሳድስ ወርኅን መድገሙ፣ ማርያምን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት ለማክበር እንጂ ከዚያ ውጪ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ መንገድ ማርያምን የሚያመልኩ አልነበሩም (ገጽ 300)፡፡ ታዲያ አሁን በአፄ ዘርዓ ያዕቆብ የተዘጋጀውንና እስከዛሬ የዘለቀውን ስለማርያም ያለውን የተሳሳተ አስተምህሮ ደቂቀ እስጢፋኖስ ተቀብለውታል እንዴት ይባላል?

12 comments:

 1. ብዙ ጊዜ እከታተላለሁ እጅግ በጣም ያስታውቅባችሀል ለማሳሳት ሆነ ብላችሁ እንደሆነ ያሁኑ ደግሞ ይገርማል ምን አይነት የተንኮል ምንፍቅና ነው የተጠናዎተህ ባክህ ያሳዝናል በውኑ በሰላመ ገብርኤል የሚለው ወንጌል ላይ የለም ? ዘለክ ወበሳድስ ያልከው

  ReplyDelete
 2. Abet indet yalachihu kifuwoch nachihu.Iski lib kalachiihu tirgum silelewu yepirotestantu lisan lay tsafu.tsom,mitswat,milja silemayawukut tsafu.Lehaymanot ketenesachihu.Inante inde Eli lijoch minamintewoch nachihu Igziabiherinina maderiyawun lemetsadebu af yeteseachihu yeaganint lijoch

  ReplyDelete
 3. ደቂቀ እስጢፋኖስን አባቶቻችሁ ለማድረግ ስትጥሩ እመለከታለሁ!!አይሆንም!!የእነሱ ልጆች አይደላችሁም!! “በቅሎ አባትሽ ማን ነው ቢሉዋት ፈረስ አጎቴ ነው አለች” የሚባለውን ያስተርትባችሁዋል!!የደቂቀ እስጢፋኖስና የዘርዓያዕቆብ ውዝግብ መንስኤው ጥርት ብሎ ያልታወቀ መሆኑ እንደተጠበቀ ነገር ግን እነሱ ከእናንተ በሚከተሉት ምክንያቶች ይለያሉ!!ልዘርዝራቸው…..
  (ሀ)የጉንዳጉንዲንና የአሲራ መቲራ ቅ/ድ/ማርያም ገዳማትን ጨምሮ የመሰረቱዋቸው ገዳማት በሙሉ በእመቤታችን ስም ናቸው፣በጻፉዋቸው መጻህፍትና ገድላት ሁሉ የምስለፍቁር ወልዳ ስዕል አለ፣ውዳሴማርያምና አንቀጸብርሃን ይደግማሉ!!ስለሆነም ለእናንተ ያላቻው የመንፈስ አባትነት ሩቅ ነው!!አትዛመዱም!!በነገራችን ላይ ደቂቀ እስጢፋኖስ በእመቤታችን አማላጅነት አንዳችም ጥርጣሬ የላቸውም!!አማላጅነቱዋን ያምናሉ!!
  (ለ)እናንተ የምታናንቁትን የምናኔ ህይወት በዘርዓያዕቆብ ዙሪያ ካሉት መነኮሳትም በላይ ማጥበቃቸው አንዱ ከንጉሱ ያላስማማቸው ምክንያት እንደሆነ ፕ/ር ጌታቸው ይገልጻሉ!!እናም እናንተን የእነሱ ልጆች ማለት የሚያስቀስፍ ውሸት ነው!!
  (ሐ)ደቂቀ እስጢፋኖስ ወደ ደቡብ ከተሰደዱ በሁዋላ ቤ/ክ ተክለው፣ታቦት አስገብተው የወንድሞቻቸውን ተዝካር ስለማውጣታቸው ታሪካቸው ይናገራል!!እናንተ ደግሞ ታቦትና ተዝካርን የሚቀበል ሰው አባቴ ለማለት ስትደፍሩ አናይም!!
  (መ)ለእመቤታችን ሊደረግ ስለሚገባው የጸጋ ስግደትም ንጉሡ ለእኔ ካልሰገዳችሁ ይላቸው ስለነበርና አቀራረቡም እልህ የተሞላበት ስለነበር አልፎ አልፎ አንሰግድም ሲሉ ቢሰማም ድርሰቶቻቸው ግን ይህን አያሳዩም!!ለምሳሌ አባ እስጢፋኖስ “በእንተ እግዝእትነ ድንግል ማርያም” በሚለው ድርሰቱ ገጽ 38 ላይ ….አንቺን ከፍ እናደርግሻለን በስብሐትና በውዳሴም(በአምልኮ አላለም)እንሰግድልሻለን…ይላታል!!ደቀመዝሙሩ አባ ዕዝራም በገድሉ ገጽ 294/5 እንደተጻፈው…ለማርያምና ለአንድ ልጁ መስቀል ስለመስገድ እኔ እሰግዳለሁ፣መምህሮቼም ይሰግዳሉ፣ምክንያቱም መጽሐፍ የጌታችን እግር በቆመበት ቦታ እንሰግዳለን(መዝ131ቁ7)ይላል.ቦታውም የማርያም ሆድ ነው…..ይልባችሁዋል!!እንግዲህ በተአምረ ማርያም ያን ያህል የተወቀሱት ደቂቀ እስጢፋኖስ ገድላቸውን በጻፉበት ወቅት አቁዋማቸውን ቀየሩ ወይስ ከመጀመሪያውም ንጉሡ ሀሳባቸውን በቅጡ ሳያዳምጥ ለግዝትና ለግዞት ዳረጋቸው የሚለው ዝርዝር ጥናት ይጠይቃል!!
  (ሠ)ነገር ግን በፕሮቴስታንት አስተምህሮ ላይ አንዳችም ነቁጥ ሳትጨምሩና ሳትቀንሱ ተሃድሶ የሚለውን ቃል ብቻ ከሰንደቁ በላይ የምታውለበልቡ አውለብላቢ ዘመነኞች ከደቂቀ እስጢፋኖስ ጋር አንዳችም ተዛምዶ እንደሌላችሁ ለመናገር የዐይነልቡና ንባብ አይጠይቅም!!ዐይነስጋችን በቂ ነው!!ልዩነታችሁ ከመታየትም የሚዳሰስ ስለሆነ!!እናንተ ሌላ፣ደቂቀ እስጢፋኖስ ሌላ!!ማሞ ሌላ፣መታወቂያው ሌላ እንዲሉ የመሀል አገር ሰዎች!!
  እናንተማ ወላዲተአምላክን ከውሃው እንጅ ከቡዋንቡዋው፣ከሽቶው እንጅ ከብልቃጡ ጉዳይ የለንም እንደምትሉዋት ሰማን!!አዘንን፣ተከዝን፣ተከፋን!!ባይገለጽላችሁ!!ባታስተውሉ!!ቡዋንቡዋ ውሃ የሚያልፍበት እንጅ የሚመነጭበት አይደለም፣ብልቃጥም ሽቶ የሚቀመጥበት እንጅ የሚቀመምበት አይደለም!!ጌታ ግን ከእመቤታችን ከስጋዋ ስጋ፣ከነፍሱዋ ነፍስ ነስቶ የህጻንነትን ሥርዓት ሳያፋልስ ተወለደ እንጅ እንዲያው እንደ ቡዋንቡዋ ውሃ ሳይነካካ-የራሱን አካል ብቻ ይዞ ሽው ብሎ አላለፈም!!ስለዚህ ምሳሌው የሚገባ አይደለም!!ህጹጽ ነው፣ጸያፍ ነው!!እንኩዋን የጌታ እናት በአመጻ የወለዱ እናቶችም ለልጆቻቸው ቡዋንቡዋ፣ብልቃጥ አይደሉም-እናት እንጅ!!9 ወር ተሸክሞ ከሚበላው በጥበበ እ/ር በህንብርቱ ለጽንሱ ምግብ እያቀበለ የሚወልድ ቡዋንቡዋም ሆነ ብልቃጥ ያለ ስለማይመስለኝ እባካችሁ በየመንገዱ ጌታን ተቀበሉ ለሚሉን ወገኖቻችሁ ይሄን ምሳሌ ቀይሩት በሉልን!!

  ReplyDelete
 4. ገድሉን ከተቀበልክ በምልዐት መቀበል እንጅ ለሀሳብህ የተስማማውን ትክክል ነው ያልተስማማህን ደግሞ ደራሲው የጨመረው ነው ማለት የሀሳብ አንካሳነት ያመላክታል!!ወይ ትፋው ወይ ዋጠው!!
  እንዴትም ብትጽፈው ደቂቀ እስጢፋኖስ ተሀድሶዎች አይደሉም!!ነባሩን ክርስትና እናድስ አላሉምና!!ከዐረብኛ ወደ ግዕዝ በተተረጎመው ተአምረማርያም ላይ በተለይ በመቅድሙና በበላኤሰብዕ ታሪክ ላይ ጥያቄ ማንሳታቸው እውነት ነው!!ነገር ግን አስቀድሞ የነበሩትን ስለእመቤታችን የቀረቡ ድርሰቶች ሲቃወሙ አልተሰሙም!!ነባሩ ስርዐተ-ቤ/ክርስቲያንም ሆነ ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮዎች እናንተ ዛሬ እንደምታቀነቅኑት ይታደሱ አላሉም!!አንተ በመሰለህ እየቆነጻጸልክ ለመተርጎም አትሞክር!!
  ተሀድሶ ናቸው ቢባል እንኩዋ የእነሱን ተሃድሶ ትክክል ነው ብሎ እንደውርስ ያለመቀበል መብታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በምንም መልኩ ስርአት-አልባ ከሆነው የዘመናችን የፕሮቴስታንት አቀንቃኝ ስመ -ተሀድሶ የአስተምህሮም የመንፈስም ዝምድና አላቸው ለማለት አይቻልም!!አትዛመዱም!!
  እንደ ድሮ የርስት ተከራካሪ ጫፍ ይዛችሁ ዝምድና ለመፈለግ አትጣሩ!!የግዕዝ ዘይቤ እናውቃለን ብሎ አጉል ማደናገር ደግም አይደል!!በዚያው በምናውቀው አሰረ-ሉተር ብትቀጥሉ ይሻላል!! እንጅ ባንዴ ከጀርመን ወደ ጉንዳጉንዲ በስመ ጥሪ ብቻ ስለመዳን የሚሰብከው አባታችሁ ሉተርም ይቀየማል!!ተራራውንስ ምን በወጣችሁ!!እዚችው….ሰፈር እጥፍ ብላችሁ መዳን ስትችሉ ከፋም ለማም ላመኑበት በእመቤታችን ስም ገዳም ገድመው፣ገድል ተጋድለው፣በዐት አጽንተው፣በጾም በምናኔ ካለፉ ሰዎች ጋር የሃይላንድ ውሃ እየጠጣችሁ በስመ ሰባኪ ስጋችሁን የምታደልቡ ዘመናውያን እጣ የላችሁም!!ስንተዋወቅ አንተላለቅ!!ክፉ አታናግሩን!!

  ReplyDelete
 5. Wonderful! Please continue in this way. Thank you very much and God bless you!

  ReplyDelete
 6. እንግባባ…ቃሉ ግልጽ ነው!!
  1. ከዛሬ ጀምሮ ትውልድ ሁሉ ብጽእት ይሉኛል!!!…..እንዴትም ቢተረጎም “በመገረም” የሚቆም አይደለም!!ያለፈውም፣ያለውም፣የሚመጣውም ትውልድ ያመሰግኑኛል ማለት ነው!!....ትውልድ ሁሉ….የሚለው ቃል ይሄን ይገልጻል!!
  2. ድርሰቱም ….ሰዐሊ ወጸልይ ለነ ምህረተ ሀበ ፍቁር ወልድኪ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመ ይስረይ ለነ ኃጣውኢነ- ኃጢአታችንን ይቅር ይለን ዘንድ ከጌታችን ከመድሀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ይቅርታና ምህረትን ለምኝልን…ከሚለው ቃል ውጭ ሙሉ ጸሎቱ በሉቃስ ወንጌል ምእራፍ 1ቁ 26 እስከ 56 ውስጥ የሚገኝ ቅ/ገብርኤልና ኤልሳቤጥ ለእመቤታችን ካቀረቡት ምስጋና የተወሰደ እንጅ እናንተ እንደምትሉት የንጉሥ ዘርዐያዕቆብ ድርሰት አይደለም!!
  3. የእሱ(የዘርዐያዕቆብ) ድርሰት ቢሆንማ ሁሌም እንደምንለው እመቤታችን የምትመሰገነው በኢትዮጵያ ብቻ ሆኖ ይቀር ነበር!!ግን አደለም!!የምስራቅ ኦርቶዶክሱም፣ካቶሊኩም፣ኦሪየንታሉም ከሉተር ልጆች በቀር አማናዊውን መድህን ያስገኘችውንና በመ/ቅዱስ ውስጥ በመልአክ ቃል ብጽእት ተብላ ከሴቶች ሁሉ ተለይታ የተጠራቸውን ወላዲተአምላክ ሰአሊ ለነ ቅድስት ሳይሉዋት አይውሉም!!የእሱዋ ምስጋና በሀገር ብቻ ሳይሆን በአህጉራትም የታወቀ ነው!ወንዝ ይሻገራል!!
  4. ስለ መላእክት በመዝ 102 ቁ 20…ባርክዎ ለእ/ር ኩልክሙ መላእክቲሁ-መላእክት ሁሉ እ/ርን ባርኩ…ተብሎ ተጽፎልሀል!!እና ቅ/ዳዊትን ያህል ነቢይና መዘምር መላእክትን እንዲህ በጸሎቱ ሲያናግራቸው ለጣኦት ምስጋ እያቀረበ ነበር ልትለን ነው???ባርክዎ ያለው ዳዊት ሰአሉ ለነ-ለምኑልን እንዳይል የትኛው ጥቅስ ነው የሚከለክለው??እስኪ ጨምረህ በመዝሙር 148 የተጻፈውን አንብበው!!መዝሙር 32 ቁ 1…..ተፈስሁ ጻድቃን በእ/ር-ጻድቃን በእ/ር ደስ ይበላችሁ…..ይላል ቅ/ዳዊት ያሉትን በሞተ ስጋ ከተለዩት ሳይለይ ነው…ደስ ይበላችሁ…የሚለው!!እኛም እሱን አብነት አድረገን ቅድስት ድንግል ማርያምን ደስ ይበልሽ ስንላት ልባችን ሀሴት ያደርጋል!!
  5. ደጋግሜ እንደምለው የሞቱ ቅዱሳንና መላእክት አያማልዱም የሚል የመጽሀፍ ቅዱስ ጥቅስ የለም!!ወፍራሞቹ ፓስተሮች ያማልዳሉ እየተባለ በክርስቶስ ህያው የሆኑት እነ ቅ/ጳውሎስ አያማልዱም ማለት የክርስቲያንን ሞት ከአረማዊ ሞት ለይቶ ካለማወቅ የተነሳ የሚመጣ አመለካከት ይመስለኛል!!
  ለማንኛውም ስለ እመቤታችን ምስጋና ስላነሳችሁ መዝሙረኛውን ደጋግሜ ብጠቅስም የልቤ ስላልደረሰ መመለሴ እንደማይቀር ገልጨ ሀሳቤን ልግታ!!
  ሰዐሊ ለነ ቅድስት!!!

  ReplyDelete
 7. the name that represents Aba Selama doesn't go with you... please try to call yourself Anti Christian Ze Bonke...And read bible with prayer and good spirit....don't complicate things...everything is understood...you are working to protest the Orthodox church...Ye awurewun menfes Ersu Geta Eyesus Kiristos Yiyazilin...Amen!!!

  ReplyDelete
 8. endihe new engi. bertulema abo

  ReplyDelete
 9. ስለድንግል ሲነሳ አላስቻለኝምና አርምሞየን ሰብሬ ተመለስኩ!!
  ደቂቀ እስጢፋኖስ ስለማርያም የሚያምኑት ይሄውልህ፡፡ በሰላመ ቅዱስንም ወበሳድስንም ተወው፡፡ ወደ ራስህ ሜዳ ወርጄ ራሱ አባ እስጢፋኖስ “በእንተ እግዝእትነ ድንግል ንጽህት ማርያም” በሚለው ድርሰቱ ያስቀመጠውን እጽፍልሀለሁ፡፡ ባለፈው በጨረፍታ አቅርቤው ነበር፡፡ ከገጽ 38 ጀምሮ ካለው ዘለግ አርጌ ልጥቀስ፡፡ ተከተለኝ!!
  ግእዙ… ንህነሰ ኢኮነ ጸላእያኒሃ ለማርያም…. ብሎ ነው የሚጀምረው ግን እሱን ብዙዎች አንባቢዎቻችን ለግእዝ ሩቅ ናቸው ብየ ስለምገምት አማርኛውን ብቻ እቀጥላለሁ፡፡ ጀመርኩ….ማለቴ አባ እስጢፋኖስ ስለእመቤታችን በ2ኛ መደብ አድርጎ ድርሰቱን ጀመረ….ይቀጥላል ተከተሉት….
  ….እኛ ከመጠራጠር የተነሳ ሰዎች እንደሚሉን የማርያም ጠላቶች አይደለንም፡፡ ቃላችንም አይደለም አይደለም አዎን አዎን ብቻ ነው፡፡ እኛ ፊታችንን እያማተብን የድንግል ማርያም አገልጋዮች ነን፤ባሮቹዋም ነን፤ፊታችንን በስላሴ ስም እያማተብን አበሳችንን የሚደመስስ ስለወለደችልን እንሰግድላታለን፡፡
  …..እንዲህ እያልን እመብርሃንን እናመሰግናታለን፡፡ አንቺን ከፍ እናደርግሻለን ፤በስብሐትና በውዳሴም እንሰግድልሻለን፡፡ ዓሳ ከውሃ ወጥቶ በየብስ ለመኖር እንዳይችል ነፍስ የተለየው ስጋም እንደማይንቀሳቀስ፣ከግንዱ የተቆረጠ እንጨትም እንደማያፈራና እንደሚደርቅ ክርስቶስን በወለደች ማርያም የማያምንም ከመጽሐፍ የተፋቀ(የተደመሰሰ) ነው፡፡
  …እግዝእትነ ማርያም የብርሃን እናት ናት፡፡ የህግና የኪዳንም ታቦት ናት፡፡ የወርቅ አርጋኖን ትባላለች፡፡ የሰሎሞን የወይን ቦታ እሱዋ ናት፡፡ ሮማን የብር አበባም ናት፡፡ የድንኩዋን ምሰሶ ናት፡፡ የቁርባን መሶብ ትባላለች፡፡ በዚህም መንገድ ለእሱዋ ልእልና ምስጋና ይገባል፡፡ እስከዘለዓለሙ አሜን፡፡
  …እምነታችን ይህ ነው፤ትውክልታችንም ይህ ነው፡፡ ከዚህ የተለየ እምነት የለንም፡፡ የመመኪያችን አክሊል እሱዋ ናትና፡፡ የንጽህናችን መሰረትም እሱዋ ናትና፡፡ የድህነታችንም ቀዳሚ እሱዋ ናትና፡፡ የምንኩስናችን መሰረት በእሱዋ የተመሰረተ ነው፣የክህነታችን ቅብዕ እሱ ናት፣የምንኩስናችን ሽልማት እሱዋ ናት፡፡ ስለዚህ ከምስጋና ጋር ስግደት ለእሱዋ ይገባል፡፡
  ….በእሱዋ ለቁስላችን መድኃኒት፣የወንጌል ጫማን ለእግራችን፣የክብር ቀለበት ለጣታችን፣የጥበብ ማህተም ለከንፈራችን፣ምስጋናን መቅሰም ለአንደበታችን አግኝተናል፡፡
  ….ከግብርናተ ሰይጣን የመውጣት እድልን በእሱዋ አገኘን፣ስለዚህ እንዲህ እያልን እናመሰግናታለን፡ የትምክህታችን አክሊል፣የድህነታችን ቅድምናና መጀመሪያ፣የንጽህናችን መሰረት በእውነት በማርያም ሆነ፡፡
  …ጥበብ ቤትን ሠራች፣በቤቱም ሰባት ምሰሶዎች አቆመች ብሉዋል፡፡ ጥበብ የተባለው ወልደ እግዚአብሄር ነው፣ቤት የተባለችውም ማርያም ናት፡፡ ሰባት ምሰሶዎችን በቤቱዋ አቆመች የተባሉት ሰባቱ የምስጢር ላእካን ናቸው….
  ጽሁፉ ባያልቅም እኔ ግን ጨረስኩ፡፡ ለማሳያ ያህል ረዘም አድርጌ ከጠቀስኩ በቂ መሰለኝ፡፡ ግን አንድ የሚገርመኝን ነገር ልንገራችሁ፡፡ ገድላቱን ሁሉ ተረት ተረት የሚሉን ወገኖች ለራሳቸው የሚጠቅም መስሎ በተሰማቸው ጊዜ ያጣጣሉትን ገድል ሳይቀር አቡዋራውን አራግፈው በማንሳት ለራሳቸው ስሜት በሚመች መልኩ ቢሆንም ገድል ጠቅሰው ለመከራከር መሞከራቸው ‘ወይ ጉድ’ ያሰኘኛል!!
  ከደቂቀ እስጠፋኖስ እንደማትመሳሰሉ ባለፈውም ብዙ ብየ ነበር፡፡ አሁንም anonymous ተብሎ ማን እንደለጠፈው ባላውቅም ከላይ ተቀምጡዋል፡፡ለምን ስሜ አልወጣም ብየ አልከፋም፡፡ወደ ጉዳየ ስመለስ፡ ቢያንስ የአባ እስጢፋኖስ ተከታዮች ቅዱሳኑን እንደሌላው ኦርቶዶክሳዊ ሁሉ የሚያከብሩና ገድላቸውንም ጽፈው፣ደጉሰው ለበረከትና ለምልጃ የሚጠቀሙበት ስለመሆኑ ገድላቸው ይመሰክራልና አሁንም የፕሮቴስታንት አዝማች ከሆናችሁት ከእናንተ ጋር ዝምድና እንደሌላቸው ከመግለጽ አንቦዝንም፡፡
  በበኩሌ ደቂቀ እስጢፋኖስን እንደ ሌሎች የሃይማኖቴ አባቶች አድርጌ ባልቀበላቸውም እናንተ የእኛ ናቸው ስትሉ ስሰማ ግን ያመኛል፡፡ በመንፈስ እንዳልወለዱዋችሁ የድርጊታችሁና የእምነታችሁ መለያየት ግልጽ፣ፍንትው ብሎ ስለሚታይ፡፡ አትመሳሰሉም!!
  በዚህ አጋጣሚ መምህር ሐዲስ ደቂቀ እስጢፋኖስ ከተሀድሶዎች የሚለዩባቸውንና እኔ ከዚህ በፊት ዘርዝሬ ያቀረብኩዋቸውን የልዩነት ነጥቦች ስላላስተባበሉዋቸው አንባቢ እንደ ሀቀኛ ማስረጃ ቆጥሮ ልዩነታቸውን እንደሚገነዘብ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡እነዚህኞቹ ከእነዛኞቹ ምንም ዝምድና የላቸው፡፡
  ገጻችሁ, እንደኔ እምነት, የኑፋቄ ቢሆንም ደጋግመን በስሙዋ “ስለእመብርሃን” ብለን ለተማርነው ወገኖች መድረክ ያልከለከላችሁንን አባ ሰላማዎች ደግሜ በኢ/ዊ ጨዋነት ላመስግን!!እግዚአብሄር ይስጥልኝ!!ይግለጽላችሁ!!ወደ አሚነ-ስላሴ ይመልሳችሁ!!


  ReplyDelete
 10. አባ ሰላማዎች በርቱ ጊዜው የጌታ እውነት የሚገለጥበት ነውና፡፡ ጳውሎስ ከወንጌል አላፍርም እንዳለ ሁሉ አዎ ወንጌልን ለመግለጥ እንደርታ ሰውንም ከስህተት ለማዳን የማረዳን የታወነ ነውና በርቱ ድሮም እኮ ወንጌል በብዙ መስዋዕትነት ነው እዚህ የደረሰው ሀዋርያት እንገፋለን እንጂ አንወድቅም ብለዋል የእነሱ አምላክ የእኛም ነውና ይረዳናል፡፡ በርቱ ፀጋው በእምነት ከእናንተ ጋር ይሁን አሜን

  ReplyDelete
 11. አባ ሰላማዎች በርቱ ጊዜው የጌታ እውነት የሚገለጥበት ነውና፡፡ ጳውሎስ በወንጌል አላፍርም እንዳለ ሁሉ አዎ ወንጌልን ለመግለጥ እንበርታ ሰውንም ከስህተት ለማዳን የሚረዳን የታመነ ነውና በርቱ ድሮም እኮ ወንጌል በብዙ መስዋዕትነት ነው እዚህ የደረሰው ሀዋርያት እንገፋለን እንጂ አንወድቅም ብለዋል የእነሱ አምላክ የእኛም ነውና ይረዳናል፡፡ በርቱ ፀጋው በእምነት ከእናንተ ጋር ይሁን አሜን

  ReplyDelete
 12. ኢየሱስ ክርስቶስ የማደንና የመመለክ ሥልጠኑን ለእናቱ ማሪያምም ሆነ ለመላዕክት በውክልና አልሰጠም፤ማሪያምም በአንደበቷ እርሱን ስሙት ብላለች፤ ስዕሌን ስላችሁ ስገዱልኝ አላለችም፤ክርስቶስም ወላጅ እናቴ ስለሆነች አምልኳት አላለም። ማሪያም የአዳኛችን የኢየሱስ ክርስቶስ የሥጋ እናት በመሆኗ ይህንን የአምላክ ሥራ ስናደንቅ እንኖራለል፤ በዚህም ምክንያት እናከብራታለን እንጂ መለኮታዊ ኋይል እንዳላት አድርገን ካሰብን ተሳስተናል መጸሐፍ ቅዱሱ አላዘዘምና፤ አምልኮ ለአብ፤ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው።
  አባ ሰላማዎች:ሕዝቡ ለዘመናት ሳይረዳ የቆየውን ሃይመኖተ- ምስጥራት በማጋለጥ እየሰጣችሁ ላለው ትምህርት አደንቃችኋለሁ፤በርቱ እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርካችሁ!

  ReplyDelete