Friday, May 30, 2014

በአቡነ ጳውሎስ ላይ ሲፈጸም የቆየው የሊቃነ ጳጳሳቱ አድማና የማኅበረ ቅዱሳን ጣልቃ ገብነት በአቡነ ማትያስ ላይም ቀጥሏል!

Read in PDF

ምንጭ፡- ደጀ ብርሃን
ከሊቃነ ጳጳሳቱ ግማሾቹ የራሳቸውን የጉባዔ ላይ የድምጽ ጡንቻ በማፈርጠም ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ከሚመስሏቸው ጋር የመቀናጀት ጠባያቸው ከምንኩስና ጀምሮ የተዋረሳቸው እንጂ ድንገት የተከሰተባቸው ዐመል አይደለም። ገሚሶቹ ሊቃነ ጳጳሳት ደግሞ ከዚህ ፈርጣማና  ጠንካራ የቡድን  አቅም መፍጠር ከቻሉት ጋር መለጠፍ የሚፈልጉት አንድም ብቻቸውን መዝለቅ እንደማይችሉ ስለሚያውቁ፤ በሌላ መልኩም ሊመጣ ይችላል ከሚሉት ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ከመፈለግ ራስን የማዳን ዘዴ የተነሳ ነው። ጥቂቶች ቢሆኑም አንዳንዶቹ ደግሞ ያልሆነ ንትርክና ጭቅጭቅ እንዲነሳ የማይፈልጉ፤ ዝም ብለው በመመልከት ታዛቢ የሚመስሉ በእድሜ የገፉ ሲሆኑ በጣት የሚቆጠሩት ደግሞ ስለቤተክርስቲያን የሚገዳቸው ነገር ግን ድምጻቸው ብዙም የማይሰማላቸው ናቸው።

 የቡድን ኃይል መፍጠር የቻሉት አብዛኛዎቹ ሊቃነ ጳጳሳት የወጣትነት ዐመል ብዙም ያልራቃቸው፤ በቂ ኃብት ማከማቸት የቻሉ፤ ለተሸከሙት ማዕርግ ሳይሆን ለስምና ለዝና የሚጨነቁ በተለይም ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ንክኪ ያላቸው ናቸው። እነዚህኞቹ ለቤተ ክርስቲያን የሚታይ፤ የሚጨበጥ፤ ለትውልድ የሚተላለፍ ቋሚ ቅርስና ሀብት መፍጠር ያልቻሉ ነገር ግን በምላስ የሰለጠኑ፤ እምቢተኝነትና ቡድንተኝነት እውቀት የሚመስላቸው ናቸው። ቤተክርስቲያን መታመስ የጀመረችው እነዚህኞቹ ቅዱስ ወደተባለው ሲኖዶስ የመቀላቀል እድል ካጋጠማቸው በኋላ ነው።  ማኅበረ ቅዱሳንም ከሀገር ቤት እስከ ውጪ ሀገር ድረስ በቤተ ክርስቲያኒቱ መልክና ቁመና ስሩን የሰደደው በእነዚህኞቹ ጀርባ ታዝሎና ተንጠላጥሎ ነው።

Tuesday, May 27, 2014

ይድረስ ለእሕታችን ዘማሪት ፋንቱ ወልዴ

Read in PDF

የአምላካችን የክርስቶስ ሰላም ይድረስሽ! በእግዚአብሔር መንግሥት የተጠራነው መጀመሪያ ለመዳን ነው ከዚያም እርሱንና የፈቃዱን ምሥጢር በማወቅ እንድናገለግለው ነው። አገልግሎት ሰው ሲያደርግ አይተን የምናደርገው፣ ለከንቱ ውዳሴ ወይም ለጥቅምና ለዝና የምናደርገው ነገር አይደለም። እግዚአብሔር ስላደረገልን መልካም ነገር የምንሰጠው ምላሽ ነው እንጂ። ስለዚህ አስቀድመን እርሱን ማወቅ ይገባናል። ጥሪው ሲደርሰን ደግሞ እሺ ብለን ባሰማራን እና በወሰነልን ሁኔታ በፍርሐትና በመንቀጥቀጥ ልናገለግለው ይገባል።
  የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያስጠነቅቀን ማንም ተነሥቶ አስተማሪ ወይም ተናጋሪ እንዳይሆን ነው። "ወንድሞች ሆይ ከእናንተ ብዙዎች አስተማሪዎች አይሁኑ የባሰውን ፍርድ እንድንቀበል ታውቃላችሁና‚ ይላል ያዕ 3፥1። በሌላ ሥፍራም "ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር የሚያገለግልም ቢሆን እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል ክብርና ሥልጣን እስከ ዘለዓለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ‚ ይላል 1ጴጥ 4፥11። በዚህ ቃል መሠረት ሁሉም አስተማሪ ሊሆን አይችልም ካስተማረም እንደ እግዚአብሔር ቃል ብቻ መሆን አለበት፤ እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ የሚለውን ቃል እናስተውለው። 

Friday, May 23, 2014

“የኮሌጁ ችግር “ረቡዕ ስለማይጾም ነው” ያለው አዲሱ አሜሪካዊ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን ከኮሌጁ ተሰናበተ

Read in PDF

  • በፎርጅድ ማስረጃ ሲማር የተገኘው አንድ የማቅ አባል ተማሪም ተባሯል
ማኅበረ ቅዱሳን በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ያለውን ፍላጎት ለማስጠበቅ በተለመደ ስልቱ አስርጎ ያስገባውና በከፍተኛ ደመወዝ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን ሆኖ እንዲሠራ የተመደበው ቀሲስ ኸርበርት ጎርደን የተባለው ግለሰብ ከኮሌጁ መሰናበቱ ተሰማ፡፡ ይህ በዜግነት አሜሪካዊ፣ በእምነት ካቶሊካዊ፣ በሚስቱ ደግሞ ማህበረ ቅዱሳን የሆነው ግለሰብ ማኅበረ ቅዱሳን የሰጠውን ተልዐኮ በአግባቡ ሳይወጣና የአራት ወር ደሞዙን ሳይበላ በቋሚ ሲኖዶስ ትእዛዝና እርሱም ማመልከቻ በመፃፍ የተሰናበተ መሆኑ ታውቋል፡፡
የሚገርመው ነገር የኮሌጁ አንዱና ዋና ችግር ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑ እየታወቀ ለማቅ ያደረው ግለሰቡ ግን የኮሌጁ ችግር ረቡዕና ዓርብ ስለማይጾም ነው ማለቱ ለብዙዎች አስገራሚ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ምክንያቱም በትምህርትና በጥናት ላይ ያሉ ሰዎች እንዲጾሙ መገደድ የሌለባቸው መሆኑ በእስራ ምእቱ መጽሐፍ ላይ የተገለጸ ሆኖ እያለ ማቅ ግን መጽሐፉንም ይህን ማሻሻያ ባለመቀበልና መጽሐፉም እንዳይሠራጭ በመቀስቀስ ሲሰራ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በተለይም በደብረ ማርቆስ ይህ መጽሐፍ ኑፋቄ አለበትና እንዳትገዙ እያለ ሲቀሰቅስ እንደነበር ምንጮቻችን ይናገራሉ። ምንም እንኳ ፆም አስፈላጊ ቢሆንም ለአንድ ዲን ነኝ ለሚል ሰው የማይመጥን ሐሳብ አንስቶ የኮሌጁን ትልልቅ ችግሮች በአርብ ሮብ ጾም ለመሸፈን መሞከሩ ብዙዎችን ሲያሳዝን የቆየ ድርጊት ነው፡፡ ይሁንና በእነዚሁ ቀናት ማለት ረቡዕ ማመልከቻ አስገብቶ አርብ መሰናበቱ በነገሩ ግጥምጥሞሽ ብዙዎች ተገርመዋል፡፡ ማቆች ግን እንደ ተአምር ሳይቆጥሩት እንደማይቀር ብዙዎች ይገምታሉ፡፡