Thursday, July 24, 2014

ሐሰትን ሲናገር ከእራሱ ይናገራል፥ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና። ዮሐ.8:44

Read in PDF

ይነብብ ሐሰተ እምዚአሁ…….ወአቡሃ ለሐሰት

ከጥዑመ ልሳን ፈረደ!
ይኽ ቃል በሰዎች ዘንድ በጣም የተለመደና ሰዎች በቦታውም ያለቦታውም የሚጠቀሙት ነው። ቃሉ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ሲሆን የተነገረው በክፉ መንፈስ ተሞልተው ሐሰትን ይዘሩ ለነበሩ አይሁድ ነው። ዛሬ ዛሬ ሐሰት የጊዜው ፋሺን በሆነበት ዘመን ሐሰትን መዝራት ለብዙዎች ኃጢአት የማይመስልበት ጊዜ ነው። ምክንያቱም በዚህ ዘመን ሐሰት እንደ ነውር የሚታይበት ሳይሆን ሐሰት ጥበብ፤ ሌላውን ማጥቂያ መሣሪያ፤ የሰውን ልብ መግዣና ስውር ደባን ወደሰዎች አእምሮ ለማስገባት ዓይነተኛ ዘዴ ሆኖ የሚታይበት ዘመን ስለሆነ። ሐሰት ያልሆነውንና ያልተደረገውን ነገር ከራስ አፍልቆ መናገር ብቻ ሳይሆን ዋና ዓላማው በጀርባ ላለው ስውር ደባ የኋላ መግቢያ በር ነው።

በነ “ሐራ” መንደር ሐሰት መናገር በጣም ቀላል ሲሆን የዕለት ዕለት ሞያዊ ተግባርም ነው። ማቅ የቆሻሻ መድፊያ አድርጎ ያቆማት “ሐራ” በየጊዜው በሬ ወለደ ወሬን ታስነብበናለች። ምን አልባት አንባቢ በሐራ ዘንድ ሐሰትን መዝራት ምን አዲስ ነገር አለው? ምንስ ያስደንቃል? ሊል ይችላል። እርግጥ ነው አዲስ ነገር ሆኖብን ሳይሆን አያውቅብንም ተብሎ እየተዋሸና እየተወናበደ ያለው ወገን እንዲነቃ ብለን እንጂ ሐሰት ለሐራ መነሻና መድረሻ መሆኑን እኛም አሳምረን እናውቃለን።

Sunday, July 20, 2014

የእግዚአብሔር ቤት ወዴት ነው?

Read in PDF

በርዕሱ የቀረበው ጥያቄ በዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ የሚመለስ ቢሆንም እንኳ፤ በአጭሩ መልስ ሰጥቶ ለማለፍ የእግዚአብሔር ቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመለክበትና የሚከበርበት የእርሱ ሥፍራ ነው፡፡ የጌታችን ሰላም፣ ጽድቅና ፍትሕ የሚገዛበት እርሱ የእግዚአብሔር ቤት ነው፡፡ ቅሉም ቦታውና ሥፍራው በመንፈስና በእውነት እርሱን ማምለክ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ እሳቤውም ይኸው ነው  (ዮሐ. 4÷24)፡፡
የእግዚአብሔር ቤት ወዴት ነው የሚለው ጥያቄ መነሻ በየጊዜው በቤተ ክርስቲያን የምናያቸው ሁከትና ግርግሮች ቅጥ ማጣታቸው ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ሰው በአምላኬ ቤት ልረፍ ብሎ የሚሄድበት፣ ሰላምና እረፍት የሚገኝባቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና አድባራት አሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ሲጀመር ለሰው እረፍት ሊሆን የሚችል ቃለ እግዚአብሔርና ስርዓተ ክርስትና በካህናት አንደበት  ስለማይደመጥ በሕይወታቸውም ስለማይታይ እረፍትና ሰላም ከየት ይገኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የውርደትና የሐፍረት ማቅ ከለበሰች ጊዜ የለውም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከጌታዋ ጉያ ወጥታ ከሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ድረስ  ከሐዋርያትና ከነቢያት መሠረት ውጪ ከክርስቶስ ባልተቀበለችው ልማድ፣ ባህልና አስተምህሮ እየተመራች ትገኛለች፡፡ መሪዎቿ በግድ ጠምዝዘው ከክርስቶስ ፍቅር አውጥተው በፊታቸው መልካም መስሎ እንደታያቸው የሚመርዋት ምድራዊ ተቋም ሆናለች፡፡
ልብ ብለን ከተመለከትን ቤተ ክርስቲያን ሊኖራት ከሚገባ መሠረታዊ መልክ አንፃር የመሪዎቿንና የተከታዮቿን ሕይወት ስንገመግም ፍጹም መተላለፍ ተፈጥሯል፡፡ የዘመኑ ተከታይም ቢሆን በክርስቶስና በመሪዎች ብሎም በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ልዩነትና አንድነት ለይቶ ለማወቅ ብዙም ፍላጐት አይታይበትም፡፡ እውነትን ከመረዳት ይልቅ የስሕተት አስተምህሮ አጃቢ ሆኖ ወደፊት ቀጥሏል፡፡ ይህን ሁሉ በጥልቀት ስናስብ የእግዚአብሔር ቤት ወዴት አለ ብቻ ሳይሆን የሚያስብለው በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቆመን እግዚአብሔር ወዴት አለ እንድንል እንገደዳለን፡፡ “አለህ እንዳልል እንዲህ ይደረጋል የለህም እንዳልል መሽቶ ይነጋል” እንደተባለው የዚህ አባባል ባለቤት ፍትህ ጐድሎ አይተው ይሆናል፤ በእውነት በዚህች ተቋም እግዚአብሔር አለ ብሎ ለመናገር መድፈር ነገሩን ከባድ ያደርገዋል፡፡ ቅዱሱና ጻድቁ ጌታ የሚሆነዉን እያየ ዝም የሚል ይመስላቸዋል? እራሱን ከእኛ ለይቶ ከሆነስ? ምክንያቱም በኦሪቱ ዘመን ሕዝቅኤል በራዕይ እንዳየው ጌታ በምስራቅ ደጅ ወጥቶ ሲሄድ እንመለከታለን፡፡ ካህናቱና ሥርዓቱ ቢኖሩም እርሱ ግን አልነበረም፡፡ በታናሽዋ እስያ የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ሁኔታም ይህን ያስረዳናል፡፡ እግዚአብሔርም ቤቱም በኛ ዘንድ አለ በመካከላችን ነው ብለን ለመናገር ምን ድፍረት አለን? የምናየው የምንሰማው ነገር በአንድ በክርስትና ስም ከተቋቋመ መንፈሳዊ ተቋም የሚታይ ሳይሆን ሥርአተ አልበኝነት ከነገሰበት መሪ ካጣ አገር የሚወጣ ነው፡፡  

Wednesday, July 16, 2014

ግብረ ሰዶማዊነት የጊዜው የቤተ ክርስቲያን ፈተና

ምንጭ፡- ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ብሎግ


የክርስቶስ ሙሽራ የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ስትኖር በልዩ ልዩ መከራ ውስጥ ታልፋለች፡፡ መከራዋ ከውጭ ከአጽራረ ወንጌል ሃይላት ብቻ ሳይሆን ከውስጥ ከራሷም የሚነሣ ነው፡፡ ከውስጥ ፈተናዎቿ መካከል አንዱ በአገልጋዮቿና በምእመናኗ ዘንድ የቅድስና መታጣት ነው። እግዚአብሔር እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም በኑሯችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ ሲል አዟል፡፡ ያለ ቅድስና እርሱን ማገልገል እንደማይቻል ግልጽ ጉዳይ ነው፡፡
ቅድስና ብዙ ነገር ነው። በጥቅሉ ቅድስና ከኃጢአት መራቅ እና ጽድቅን እያደረጉ መኖር ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ በዚህ ክፍል የምንመለከተው ግን ከጾታዊ ግንኙነት ጋር የተያያዘውን የቅድስና ጉድለት ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድ ቅድስና የሚባለው አንድ ወንድ በአንዲት ሴት ተወስኖ እግዚአብሔርን እያከበሩ ከእርሱ ጋር መኖር ነው፡፡ ከዚህ ውጭና ተቃራኒ በሆነ አኗኗር መመላለስ ማለትም ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸም ማንኛውም ጾታዊ ግንኙነት ሁሉ ርኩሰት ነው፡፡ ይልቁንም ከተፈጥሮ ባሕርይ ውጪ ወንድ ከወንድ ሴት ከሴት ጋር የሚፈጽሙት አስጸያፊ ድርጊት ሌላ ገላጭ ቃል ስለሌለ እንጂ ከርኩሰትም በላይ ነው፡፡
እግዚአብሔር ቅዱስ አምላክ ነው፡፡ ለቅድስናው ተስማሚ በሆነ አኗኗር እንድንኖርም ይፈልጋል፡፡ ጋብቻን ሲመሰርት ለአዳም ሔዋንን እንደፈጠረና ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚፈጠር ህብረት እንደሆነ ግልጽ ሆኗል፡፡ ሰው በኃጢአት ከወደቀ በኋ ግን ይህን የእግዚአብሔር ሐሳብ የሚፈጸምበትን ቅዱስ ሕብረት ጋብቻን ለማበላሸት በወንድና ሴት መካከል የዝሙት ሃጢአት እንዲፈጸም በማድረግ ጠላት ዲያብሎስ ሲሰራ ኖሯል፡፡ ከዚያም የጥፋቱን መጠንና ዐይነት በማስፋት ሰው ከተፈጥሮ ባሕርዩ ውጪ በሆነ መንገድ ከተመሳሳዩ ጾታ ጋር  አስነዋሪ ድርጊት እንዲፈጽም አደረገ፡፡ ይህም አስጸያፊ ርኩሰት የተጀመረው በቅርቡ ሳይሆን ጥንት ነው፡፡ 

Tuesday, July 8, 2014

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ውለታ የዘነጋው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የ፶ ዓመታት ጉዞው ዝክር

Read in PDF

በፍቅር ለይኩን
፲፭ኛው (አሥራ አምስተኛው) ዓለም አቀፉ ኢትዮጵያ ጥናት ኮንፈረስ ከዐሥራ አንድ ዓመት በፊት በአውሮፓዊቷ አገር በጀርመን ሀምቡርግ ከተማ ከሰኔ ፲፬-፲፰ ፲፻፺፭ ዓ.ም. ነበር የተካሔደው፡፡ በወቅቱም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል መምህርትና ተመራማሪ የኾኑት አጋረደች ጀማነህ የተባሉ ኢትዮጵያዊት ምሁር የኢትዮጵያ ጥናት ልደቱን ያገኘበትን ልዩ አጋጣሚውን በመጥቀስ ‹‹አባ ጎርጎርዮስን የኢትዮጵያ ጥናት አባት›› በሚል ርእስ ዘክረውት ነበር፡፡
የቋንቋና የሥነ ጽሑፍ ምሁሯ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ የኾኑትን የአባ ጎርጎርዮስ ዘመካነ ሥላሴና የጀርመናዊውን ምሁርና አጥኚ ሂዮብ/ኢዮብ ሉዶልፍ ከ፬፻ ዓመታት ገደማ በፊት በ፲፯ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢጣሊያዊቷ ጥንታዊትና ታሪካዊት ከተማ በሮም የተገናኙበት ልዩ የታሪክ አጋጣሚ በሥልጣኔና በጥበብ እጅጉን ልቃ በሔደችው በአውሮፓ ምድር ለኢትዮጵያ ጥናት ጅማሬ ትልቅ መሠረት ጥሎ እንዳለፈ በዚሁ ጽሑፋቸው በአጭሩ ለመዳሰስ ሞክረዋል፡፡