Tuesday, July 8, 2014

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ውለታ የዘነጋው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የ፶ ዓመታት ጉዞው ዝክር

Read in PDF

በፍቅር ለይኩን
፲፭ኛው (አሥራ አምስተኛው) ዓለም አቀፉ ኢትዮጵያ ጥናት ኮንፈረስ ከዐሥራ አንድ ዓመት በፊት በአውሮፓዊቷ አገር በጀርመን ሀምቡርግ ከተማ ከሰኔ ፲፬-፲፰ ፲፻፺፭ ዓ.ም. ነበር የተካሔደው፡፡ በወቅቱም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍል መምህርትና ተመራማሪ የኾኑት አጋረደች ጀማነህ የተባሉ ኢትዮጵያዊት ምሁር የኢትዮጵያ ጥናት ልደቱን ያገኘበትን ልዩ አጋጣሚውን በመጥቀስ ‹‹አባ ጎርጎርዮስን የኢትዮጵያ ጥናት አባት›› በሚል ርእስ ዘክረውት ነበር፡፡
የቋንቋና የሥነ ጽሑፍ ምሁሯ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ የኾኑትን የአባ ጎርጎርዮስ ዘመካነ ሥላሴና የጀርመናዊውን ምሁርና አጥኚ ሂዮብ/ኢዮብ ሉዶልፍ ከ፬፻ ዓመታት ገደማ በፊት በ፲፯ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢጣሊያዊቷ ጥንታዊትና ታሪካዊት ከተማ በሮም የተገናኙበት ልዩ የታሪክ አጋጣሚ በሥልጣኔና በጥበብ እጅጉን ልቃ በሔደችው በአውሮፓ ምድር ለኢትዮጵያ ጥናት ጅማሬ ትልቅ መሠረት ጥሎ እንዳለፈ በዚሁ ጽሑፋቸው በአጭሩ ለመዳሰስ ሞክረዋል፡፡

ኢትዮጵያ- ጎንደር መካነ ሥላሴ፣ ኢጣሊያ- ሮም ከተማ፣ ከዚያም ጀርመን- ኑርምበርግ፡፡ እነዚህ አገሮች በ፲፯ኛው መቶ ክ/ዘ ተጠንስሶ እስከ ዛሬ ድረስ ለዘለቀው ኢትዮጵያ ጥናት መሠረት የኾኑ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጎርጎርዮስ ዘመካነ ሥላሴ በስደት ወደ ኢጣሊያ ሮም ከተማ በማምራታቸው የእውቀት ጥማት ከአገሩ ጀርመን ካመጣው ሂዮብ ሉዶልፍ ጋር በሮም ተገናኙ፡፡ እነዚህ የሁለት አገር ባዕዳን ቋንቋዎቻቸውን፣ የየአገራቸውን ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖት እርስ በርሳቸው ተማማሩ፡፡
በቆይታቸውም አባ ጎርጎርዮስ ጀርመንኛን፣ ሉዶልፍ ደግሞ ግዕዝን በሚገባ ተካኑ፡፡ የእነዚህ የሁለት አገራት ሊቃውንት ይህ ግንኙነታቸው ውሎ አድሮ ደግሞ ሌላ ውጤትን አሰገኘ፤ ይኸውም ጀርመናዊው ሉዶልፍ ወደ አገሩ ተመልሶ በምድረ አውሮፓ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያን ጥናት ለመመሥረት በቃ፡፡ ይኼ ግንኙነታቸው መሠረቱ ጠንካራ ስለነበር የኢትዮጵያ ጥናት ግንባታው ዘለቄታን አግኝቶ ይኸው እስከአሁን ዘመን ድረስ ሊዘልቅ በቅቷል፡፡ በዘመናችንም በአውሮፓ በሚገኙ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎችና አካዳሚያዎች የኢትዮጵያ ጥናት በዋና ትምህርት ክፍለ ደረጃ፣ ወይም በአፍሪካ ጥናት ሥር አሊያም ደግሞ በምሥራቅ አገሮች (Oriental Studies) ሥር ይሰጣል፡፡
በእርግጥ የኢትዮጵያ ጥናት በተቋምና በተደራጀ ኹኔታ በአውሮፓ ልደቱ ይበሰር እንጂ ስለ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ገናና ሥልጣኔ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ቅርስ … ወዘተ ጥናት የተጀመረው በ፲፯ኛው ክ/ዘ ጀምሮ ነበር ብሎ መደምደም የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ለዚህም ተጨባጭ መረጃዎችንና በርካታ መከራከሪያ የሚሆኑን የታሪክ ድርሳናትን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለአብነትም አባ ጎርጎርዮስ ወደ ሮማ ምድር ከመምጣታቸው ከመቶ አምሳ ዓመታት ገደማ በፊት በ፲፭ኛው መቶ ክ/ዘ በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ከዴር ሱልጣን ገዳምና ከኢትዮጵያ ተሰደው በሮማ ይኖሩ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ዘንድ የግዕዝ ቋንቋን የተማሩና እንዲሁም በኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ሃይማኖት፣ ታሪክና ባህል ከመመሰጣቸውና ከመገረማቸው የተነሣ ሰፊ ጥናት ያደረጉ አውሮጳውያን ምሁራን፣ የሃይማኖት ሊቃውንትና አሳሾች እንደነበሩ የታሪክ መዛግብት ይመስክራሉ፡፡
እ.ኤ.አ. በ1960 ‹‹An Outline of the Development of Ethiopian Topography in Europe›› በሚል ርእስ ጥናታቸውን ያስነበቡት ሆላንዳዊው ምሁር ዶ/ር ኤች. ኤፍ. ዊጂንማን በአውሮፓ ምድር በመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ የግዕዝ ፊደላት በደቻዊው ሠዓሊና ቀራጺ ኤርኸርት ቫን ሪዊች በእንጨት ላይ ተቀርጸው መተዋወቃቸውን በዚህ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ይፋ አድርገዋል፡፡
ዶ/ር ዊጂንማን በዚሁ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ከሙስሊም ተስፋፊዎች የገጠማቸውን ወረራ የሚመክቱበት የጦር መሣሪያ ዕርዳታ እንዲልኩላቸው ወደ አውሮፓ ምድር መልእክተኞቻቸውን ልከው እንደነበርና በተመሳሳይም ንጉሡ በዘመነ መንግሥታቸው ከዴር ሱልጣን ገዳም ሁለት ኢትዮጵያውያን መነኮሳትን ልዑክ አድርገው በ፲፬፻፴፪ ዓ.ም. በኢጣሊያ ፍሎረንስ ከተማ በተካኼደው የሃይማኖት ጉባኤ ላይ እንዲሳተፉ መላካቸውን ይገልጻሉ፡፡
የዶ/ር ዊንጅማን ጥናት እንደሚያትተው ኢትዮጵያውያኑ መነኮሳት ከሮማ ካቶሊክ ቀሳውስትና ሊቃውንት ጋር በነበራቸው ግንኙነት የተነሣ ከታላቁ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል አቅራቢያ የሚገኘውን የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ንን ሮማውያኑ ካቶሊኮች ለኢትዮጵያውያን መነኮሳትና የመንፈሳዊ ተጓዦች ቤተ አምልኮና ማረፊያ እንዲሆናቸው በስጦታ ተሠጥቷቸው ነበር፡፡ ይህ የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ንም እስከ ፲፰ኛው መቶ ክ/ዘ መገባደጃ ድረስ የኢትዮጵያውያን መነኮሳትና ተጓዦች ማረፊያ እንደሆነ ቆይቷል፡፡
በ፲፯ኛው መቶ ክ/ዘ አባ ጎርጎርዮስና ጀርመናዊው ሂዮብ ሉዶልፍ በሮማ ከተማ ከመገናኘታቸው አስቀድሞም በሮማ በሚገኘው በቅዱስ እስጢፋኖስ በነበሩ የኢትዮጵያ ቤ/ን መነኮሳትና መናኒያን ጋር ተገናኝቶ ስለግዕዝ ቋንቋ ለማወቅ ጥልቅ ፍላጎትን ያሳየው በሮም ከተማ ይኖር የነበረው ጀርመናዊው ቄስ ጆን ፖትከን ነበር፡፡
ይህ ሰው በ፲፭፻፲፩ ዓ.ም. በኢየሩሳሌም በነበረው ቆይታው በዴር ሱልጣን ገዳም ከኢትዮጵያውያን መነኮሳትና ሊቃውንት ጋር ተገናኝቶ እንደነበር በጉዞ ማስታወሻው ላይ ጠቅሶታል፡፡  ጀርመናዊ ቄስ ፖትከን በሮም ቆይታው ከዴር ሱልጣን ገዳም መጥተው በሮም ይኖሩ ከነበሩት አባ ቶማስ ወልደ ሳሙኤል ከተባሉ መናኒ መነኩሴ የግዕዝን ቋንቋ በሚገባ ማጥናት ችሎ ነበር፡፡
ከአባ ቶማስ ዘንድ የግዕዝን ቋንቋ ያጠናው ቄስ ፖትከን በ፲፭፻፲፫ ዓ.ም. በአውሮፓ ምድር በግዕዝ ቋንቋ የመጀመሪያውን መዝሙረ ዳዊትን ከመኃልየ መኀልይ ዘሰለሞን ጋር በአንድነት አድርጎ አሳትሞ እንደነበር ካፒቴን ማሪዮ ዳ. ሌኦኔሳ የተባለ አጥኚ በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም. ባሳተመው ‹‹ሳንቶ እስቴፋኖ ማጊዮሬ ዴግሊ አቢሲኒያ ኤ ለ ሬላዚዮኒ ሮማኖ ኢትዮጲቼ›› በሚለው መጽሐፉ ገልጾታል፡፡ በጀርመን ኮለኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ን አገልጋይ የሆነው ቄስ ፖትከን ከሮም ወደ አገሩ ጀርመን ከተመለሰ በኋላም መዝሙረ ዳዊትን በግዕዝ፣ በሂብሪው፣ በላቲንና በግሪክ ቋንቋ በአንድነት አድርጎ አሳትሞት ነበር፡፡
ይህ ሰው ፲፭፻፳፬ ዓ.ም. ሲሞት በእርሱ እግር በመተካት የግዕዝን ቋንቋ ጥናት በአውሮፓ ምድር እንዲቀጥል ካደረጉት መካከል ዕውቁ ሂዩማኒስት ጆናስ ሬዩችሊን እና ጆናስ ትሪቴሚዩስ ይጠቅሳሉ፡፡ እንግዲህ በአውሮፓ ምድር የግዕዝን ቋንቋ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና ቅርስና እንዲሁም የኢትዮጵያን ቤ/ን ታሪክ፣ ዶግማና ቀኖና በማጥናት ረገድ ከጀርመናዊው ሂዮብ ሉዶልፍና አባ ጎርጎርዮስ አስቀድሞ የተጀመረ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ምንም እንኳን የኢትዮጵያን ጥናት በተደራጀና በተቋም ደረጃ በማስጀመር ረገድ ስማቸው ቀድሞ የሚነሳው የጎንደሩ አባ ጎርጎርዮስ ዘመካነ ሥላሴና ሂዮብ ሉዶልፍ ቢሆኑም፡፡ 
ከዚሁ የኢትዮጵያ ጥናት ጅማሬና መስፋፋት ጋር ተያይዞም በአውሮፓ ምድር ‹‹የካህኑና ንጉሡ ዮሐንስ አገር›› ተብላ ለረጅም ዓመታት በምናባቸው የቆየችውን ኢትዮጵያ በአውሮፓ ምድር በሚገባ እንድትታወቅና እንድትጠና በማድረግ ረገድ ፖርቹጋላውያን ትልቅ ሚና ነበራቸው ማለት ይቻላል፡፡ ፖርቹጋላውያን አሳሾችና የሃይማኖት ሰባኪዎችና ሊቃውንቶች ኢትዮጵያን በማወቅና በማስተዋወቅ ረገድ የነበራቸውን ቀዳሚ ሚና በተመለከተ አንድ ሁለት የታሪክ ማስረጃዎችን ልጥቀስ፡፡
ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዓፄ ልብነ ድንግል የአዳል ገዢና የጦር አዝማች ከሆነውና በተለምዶ ግራኝ አሕመድ እየተባለ ከሚጠራው የጦር ኃይል ጋር በገቡበት ጦርነት ዕርዳታን ፈልገው ወደ ፖርቹጋል ንጉሥ መልእክተኞችን ልከው ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል ጸጋ ዘአብ ከተባለው ሊቅና ከንጉሡ መልእክተኛ ጋር በሊዝበን ከተማ የተገናኘው ታዋቂው ሂዩማኒስትና ሚሽነሪ ዳሚያኑስ ጆኤስ ከጸጋ ዘአብ ጋር ያደረጉትን ሃይማኖታዊ ውይይት በተመለከተ ያወጣው መጽሐፍም በአውሮፓ በነበሩ በተሐድሶ አራማጆችና በአናባፕቲስቶች ዘንድ ትልቅ ዕውቅናን እና ዝናን ለማትረፍ ችሎ ነበር፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላም ፍራንስሲኮ አልቫሬዝ በ፲፭፻፲፫-፲፭፻፳ ዓ.ም. በኢትዮጵያ የነበረውን ቆይታውን በተመለከተ በ፲፭፻፴፪ ዓ.ም. በሊዝበን ከተማ ‹‹የካህኑና የንጉሡ ዮሐንስ አገር ኢትዮጵያ›› በሚል ርእስ በፖርቹጊዝ ቋንቋ ያሳተመው ዳጎስ ያለ የጉዞ ማስታወሻ መጽሐፍ በአውሮፓ ምድር ስለ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ውበትና ሀብት፣ ስለ ሕዝቦቿም ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ቅርስ… ወዘተ. በሰፊው ለማወቅ ለሚፈልጉ ምዕራባውያን ሁሉ ትልቅ ጉጉትንና መነቃቃትን የፈጠረ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
በዚህ ሁሉ ረጅሙ የአገራችን የታሪክ ጉዞ ውስጥ እጅግ በጥቂቱ ለመጥቀስ የሞከርኳቸው የታሪክ ማስረጃዎችና ዋቢዎች አንድ የሚነግሩን እውነታ አለ፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያን ለተቀረው ዓለም በማሳወቅና እንዲሁም በምዕራቡ ዓለም የኢትዮጵያ ጥናት ልደት እንዲበስር በማድረግ ረገድ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ሊቃውንቶቿ ሊዘነጉ የማይገባቸው ታላቅ ባለ ውለታ መሆናቸው ነው፡፡
ታሪክ እንደሚመሰክረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰማያዊው፣ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋ ባሻገር በሰው ልጆች ሥልጣኔ ታሪክ ውስጥ ጉልህና ደማቅ አሻራን የተወች ናት፡፡ ቋንቋን ከነፊደሉ ያበረከተች፣ በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ኪነ-ጥበብ፣ ኪነ-ሕንፃ፣ ሥነ ጽሑፍወዘተ ውስጥ ግዙፍና ደማቅ አሻራ የነበራትና አሁንም ያላት ሃይማኖታዊ ተቋም ናት፡፡
ይህ ቤተ ክርስቲያኒቱ በኢትዮጵያ ግዙፍ ታሪክና ገናና ሥልጣኔ ውስጥ የነበራት ድርሻና ጉልህ ሚና በተለይም ደግሞ ካላት የረጅም ዘመናት ተጠብቆ የቆየ የሥነ ጽሑፍ ሀብት የተነሣ በሌላው ዓለም ዘንድ ከአድናቆት ባለፈ የብዙ ተመራማሪዎችንና አጥኚዎችን ቀልብ እንድትገዛ አስችሏታል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ፲፰ኛ ጊዜ የተካኼደው የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ጅማሬው ውሉ የሚመዘዘውም ከዚሁ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለአገራችን ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ለረጅም ዘመናት ጠብቃ ካቆየቻቸው ዕድሜ ጠገብ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶቿና ቅርሶቿ፣ ከጥንታዊው የግዕዝ ቋንቋዋና የሊቃውንቶቿ ትጋት፣ የጥበብና የእውቀት ጥማት የተነሣ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ይህ ረጅም ታሪክና ገናና ስም ያለው ግን ደግሞ ባለ ውለታውን የዘነጋ የሚመስለው የኢትዮጵያ ጥናት በአገራችን በኢትዮጵያ በተቋም ደረጃ የተመሠረተበትን ፶ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን በቅርቡ በተለያዩ ዝግጅቶች ማክበሩን ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተከታትለናል፡፡
በእርግጥ በዚህ ልንሰናበተው የሁለት ወራት ዕድሜ በቀረን በዚህ እያገባደድነው ባለው ዓመት የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ብቻ ሣይሆን የዚሁ ተቋም ወዳጅ፣ ዋና አጋርና ተቆርቋሪ የኾነው አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍልም የተቋቋመበትን ፶ ዓመት የልደት በዓሉን ከሞት አፋፍ ላይ ቆሞም ቢሆን በአልሞት ባይ ተጋዳይነትና ቁርጠኝነት ማክበሩ አይዘነጋም፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋምም ሆነ የታሪክ ትምህርት ክፍሉ በዓላቸውን ያከበሩበት ድባብ የተቀዛቀዘ፣ እምብዛም ሽፋን ያልተሰጠውና ድምቀት የጎደለው እንደነበር በወቅቱ ታዝበናል፤ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ይመስለኛል፡፡
በዘመነ ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ለማኝ እህል የተደበላለቀ ፍቺና ትርጓሜ እየተሰጠውና ከዚህም የተነሣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ትርጓሜ ክፉኛ አጣብቂኝ ውስጥ እየገባ እንዳለ ፈጽሞ የሚዘነጋ አይደለም፡፡
ከዚሁ ጋርም ከኢትዮጵያ የረጅም ዘመናት ታሪክና ሥልጣኔ እንዲሁም ከኢትዮጵያዊነት የአንድነትና ብሔራዊ ስሜትና መንፈስ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ታሪክና ቅርስ ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም በሥልጣን ላይ ባሉ ፖለቲከኞቻችን ዘንድ ከበጎው ይልቅ አብዝቶ አሉታዊ ታሪኳ ብቻ እየተነቀሰና እየተጋነነ የሚተረክላት፣ እምብዛም በበጎ ዓይን የማትታይና በትልቅ ጥያቄ ውስጥ ያለች ተቋም መሆኗን ያስታውሷል፡፡
በተጨማሪም ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ የምትሉት ለመሆኑ ‹‹ስለየትኛዋ ኢትዮጵያ ታሪክ ነው የምታወሩት?!›› የሚሉ ዘመነኞቻችን ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን፣ ክብሩንና ታሪኩን እንደመሰላቸውና እንዳሻቸው ይጽፉት፣ ያጽፉትና ይተረትሩት ከጀመሩ እነሆ ሁለት ዐሥር ዓመታትን አሳልፈናል፡፡ እናም ‹‹የኢትዮጵያ የምትባል አገር የ፻፶ ዓመት ታሪክ ብቻ ያላት አገር ናት፡፡›› ‹‹ኢትዮጵያ የምትባል አገርም ትናንትና ያልነበረች ከ፻ ዓመት በፊት ምኒልክና ነፍጠኛ ሠራዊቱ በሰይፍ እንደ ገል ቀጥቅጠው፣ እንደ ሰም አቅልጠውና አፍሰው ያበጃጇት፣ የሠሯት አገር ናት›› ከሚል ድምዳሜ ላይም ተደርሷል፡፡
ከዚህ የታሪክ ተፋልሶና ፈጽሞ የወረደ ተረት ተረት ጀምሮ አክሱማውያንና የአክሱምን ሥልጣኔ የአንድ ሕዝብና ብሔር ብቻ ገናና ሥልጣኔና ታሪክ ብቻ እንደሆነ አድርጎ በመቁጠር፣ ‹‹የአክሱም ሀውልት ለወላይታ ሕዝብ ምኑ ነው?!›› እስከሚል የዘለቀ ድፍረትና የታሪክ ውርዴ ውስጥ የተዘፈቅንበት ይህ የእኛው ዘመን ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ አንድነታችንና የትናንትና ግዙፍ ታሪካችንና ገናና ሥልጣኔያችን አፍን ሞልቶ መናገርም ሆነ መጻፍ ሌላ ስም የሚያሰጥ በጥርጣሬ ዓይን የሚያሰመለክት ርእሰ ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡
ከዚህ አሳፋሪ እውነታ ጋር በተያያዘም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የአምሳኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን ሲያከብር በአምሳ ዓመታት ጉዞ ውስጥ ለኢትዮጵያ ጥናት ጅማሬና ዕድገት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንቶች ያደረጉትን አስተዋጽኦ ወይም ውለታ በሚገባ ዘክሮታል ለማለት አልደፍርም፡፡
ለዚህ ምክንያት ይሆናል ብዬ የምለው ደግሞ ከላይ በአጭሩ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት፣ በሥልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግሥት ኢትዮጵያዊነትን፣ የኢትዮጵያን ታሪክና የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን እየተቸበትና እየፈረጀበት ያለው ብዥታ ያጠላበት ምልከታው የወለደው የተሳሳተ የታሪክ ዕይታው እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
በግልባጩም ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ መሪዎችና አባቶች ከነገሥታቱና ከገዢዎች ጋር የገቡበት ያለ አቻ የሆነ የፖለቲካ ጋብቻ የፈጠረው ጥምረትና የምድራዊ ሥልጣንና ምቾት ቤተ ክርስቲያኒቱ ልትወቀስበትም ሆነ ልትመሰገንበት በሚገባት ታሪኮቿንና ሥራዎቿን በተመለከተ ገዢዎችንና ፖለቲከኞችን በአደባባይ ሳይፈሩና ሳያፍሩ በቆራጥነት መልስ ሊሰጡላትና ሊሟገቱላት የሚችሉ የመንፈስ ልእልናን የተቀዳጁ፣ ለፍቅር፣ ለእውነትና ለፍትሕ የቆሙ አባቶችና መንፈሳዊ መሪዎች በዘመናችን ቁጥራቸው እጅጉን መመናመኑ ወይም መጥፋቱ ይመስለኛል፡፡
እንጂ ለኢትዮጵያ ጥናት ጅማሬ ብቻ አይደለም በአገራችን ለዘመናዊ ትምህርት ጅማሮና ዕድገት ትልቁን መሠረት የጣለች ቤተ ክርስቲያን በአገራችን ትልቅና አንጋፋ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ለሆኑት ለአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ባይተዋርና የበይ ተመልካች መሆን ወይም እንድትሆን መደረግ አልነበረባትም ነበር፡፡ 
በመጨረሻም ስለ ኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ጥቂት ነገሮችን በማለት አሳቤን ላጠቃል፡፡ ይህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኘው ታሪካዊ ተቋም በአገሪቱ አለ የሚባል አንጋፋና ከፍተኛ የምርምርና የጥናት ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡ የምርምርና የጥናት ተቋሙ እንደ ስሙ ሁሉ ለኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያን ለማወቅና ለማጥናት ለሚልጉ ሁሉ ተቀዳሚና ተመራጭ የምርምርና የጥናት ተቋም መሆኑም አሌ የማይባል ሐቅ ነው፡፡
ተቋሙ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ባደረገው ጉዞ በሥሩ ያሉት ቤተ መጻሕፍቱ፣ የኢትኖግራፊክ ቤተ መዘክሩ (Ethnographic/Anthropological Museum)፣ የምርምርና የጥናት ማዕከሉና ከዚሁ ጋር በተቀዳሚነት አብሮ የሚነሣው የኢትዮጵያ ጥናት ወዳጆች ማኅበር/SOFIES ለተቋሙ ትልቅ ክብርና ሞገሱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ደግሞ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ያለበት የቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሕንፃ ለተቋሙ ትልቅ ታሪክን፣ ልዩ ውበትንና ግርማን አጎናጽፎታል፡፡

3 comments:

 1. SELAME LE HULACHENE YEHUNE . SELE EYERUSALEM GEDAMACHEN SELE ABATUOCHACHN YETSFEU YASAZENALE . MENEW YEMAYEMELKTACHUNE BATENEKAKU . KE SAFCHU DEGMO BE HULUME BEKULE YALEWEN CHGER SEMTO METFE NEBER . LEMANGNAWEME YETEFETRE CHGER BENREME ABATUOCH BETSLOTE BETEHETNA EYKENAWENUTE NEW . LEMANGNWEME GEDAMU LE BETSU ABATCHEN KEFU HUNU AYDELEME ESACHUME ASCHEGARE SEBAYE BENOREBACHUME BE ASETEDADER BEKULE LEGZEW KE KIDUS SENUODOS WESANYE BEMETBKE LAYE NACHEW . GEN ADDIS YESRUTEME YASERTEM NEGER YELEME , YETEGEZAUME BETE MELEKOSATU LEFETEUO NEW LE WETET YABEKUTE , SELEZHE ENANTE BETEKERSETYANACHENEN , ABATUOCHACHENEN LE TELATE , LE SEDABYE ATESTUTBEN EBAKACHU.

  ReplyDelete
 2. Eski endezih mestaf yilmedibachihu.Ewunetin ketarik eyatakesu metsaf.

  ReplyDelete
 3. Woy Difret? Zares Legna Wetachihu aydel Enante Abaselamawoch.Kemeche aedih new degmo Mengistin Nekifachihu Metsaf Yejemerachihut???
  በዘመነ ኢህአዴግ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ለማኝ እህል የተደበላለቀ ፍቺና ትርጓሜ እየተሰጠውና ከዚህም የተነሣ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ትርጓሜ ክፉኛ አጣብቂኝ ውስጥ እየገባ እንዳለ ፈጽሞ የሚዘነጋ አይደለም፡፡.....‹‹የአክሱም ሀውልት ለወላይታ ሕዝብ ምኑ ነው?!››.....በሥልጣን ላይ ያለው የኢህአዴግ መንግሥት ኢትዮጵያዊነትን፣ የኢትዮጵያን ታሪክና የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን እየተቸበትና እየፈረጀበት ያለው ብዥታ ያጠላበት ምልከታው የወለደው የተሳሳተ የታሪክ ዕይታው እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

  ReplyDelete