Sunday, July 20, 2014

የእግዚአብሔር ቤት ወዴት ነው?

Read in PDF

በርዕሱ የቀረበው ጥያቄ በዝርዝር ጉዳዮች ውስጥ የሚመለስ ቢሆንም እንኳ፤ በአጭሩ መልስ ሰጥቶ ለማለፍ የእግዚአብሔር ቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመለክበትና የሚከበርበት የእርሱ ሥፍራ ነው፡፡ የጌታችን ሰላም፣ ጽድቅና ፍትሕ የሚገዛበት እርሱ የእግዚአብሔር ቤት ነው፡፡ ቅሉም ቦታውና ሥፍራው በመንፈስና በእውነት እርሱን ማምለክ ነው፡፡ ክርስቲያናዊ እሳቤውም ይኸው ነው  (ዮሐ. 4÷24)፡፡
የእግዚአብሔር ቤት ወዴት ነው የሚለው ጥያቄ መነሻ በየጊዜው በቤተ ክርስቲያን የምናያቸው ሁከትና ግርግሮች ቅጥ ማጣታቸው ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ሰው በአምላኬ ቤት ልረፍ ብሎ የሚሄድበት፣ ሰላምና እረፍት የሚገኝባቸው አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና አድባራት አሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ሲጀመር ለሰው እረፍት ሊሆን የሚችል ቃለ እግዚአብሔርና ስርዓተ ክርስትና በካህናት አንደበት  ስለማይደመጥ በሕይወታቸውም ስለማይታይ እረፍትና ሰላም ከየት ይገኛል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የውርደትና የሐፍረት ማቅ ከለበሰች ጊዜ የለውም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ከጌታዋ ጉያ ወጥታ ከሲኖዶስ እስከ አጥቢያ ድረስ  ከሐዋርያትና ከነቢያት መሠረት ውጪ ከክርስቶስ ባልተቀበለችው ልማድ፣ ባህልና አስተምህሮ እየተመራች ትገኛለች፡፡ መሪዎቿ በግድ ጠምዝዘው ከክርስቶስ ፍቅር አውጥተው በፊታቸው መልካም መስሎ እንደታያቸው የሚመርዋት ምድራዊ ተቋም ሆናለች፡፡
ልብ ብለን ከተመለከትን ቤተ ክርስቲያን ሊኖራት ከሚገባ መሠረታዊ መልክ አንፃር የመሪዎቿንና የተከታዮቿን ሕይወት ስንገመግም ፍጹም መተላለፍ ተፈጥሯል፡፡ የዘመኑ ተከታይም ቢሆን በክርስቶስና በመሪዎች ብሎም በቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ልዩነትና አንድነት ለይቶ ለማወቅ ብዙም ፍላጐት አይታይበትም፡፡ እውነትን ከመረዳት ይልቅ የስሕተት አስተምህሮ አጃቢ ሆኖ ወደፊት ቀጥሏል፡፡ ይህን ሁሉ በጥልቀት ስናስብ የእግዚአብሔር ቤት ወዴት አለ ብቻ ሳይሆን የሚያስብለው በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቆመን እግዚአብሔር ወዴት አለ እንድንል እንገደዳለን፡፡ “አለህ እንዳልል እንዲህ ይደረጋል የለህም እንዳልል መሽቶ ይነጋል” እንደተባለው የዚህ አባባል ባለቤት ፍትህ ጐድሎ አይተው ይሆናል፤ በእውነት በዚህች ተቋም እግዚአብሔር አለ ብሎ ለመናገር መድፈር ነገሩን ከባድ ያደርገዋል፡፡ ቅዱሱና ጻድቁ ጌታ የሚሆነዉን እያየ ዝም የሚል ይመስላቸዋል? እራሱን ከእኛ ለይቶ ከሆነስ? ምክንያቱም በኦሪቱ ዘመን ሕዝቅኤል በራዕይ እንዳየው ጌታ በምስራቅ ደጅ ወጥቶ ሲሄድ እንመለከታለን፡፡ ካህናቱና ሥርዓቱ ቢኖሩም እርሱ ግን አልነበረም፡፡ በታናሽዋ እስያ የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ሁኔታም ይህን ያስረዳናል፡፡ እግዚአብሔርም ቤቱም በኛ ዘንድ አለ በመካከላችን ነው ብለን ለመናገር ምን ድፍረት አለን? የምናየው የምንሰማው ነገር በአንድ በክርስትና ስም ከተቋቋመ መንፈሳዊ ተቋም የሚታይ ሳይሆን ሥርአተ አልበኝነት ከነገሰበት መሪ ካጣ አገር የሚወጣ ነው፡፡  

ምንም እንኳ በየደብሩ፣ በየአጥቢያው፣ በየገደማቱና በየተቋማቱ፤ እሰጥ አገባው የተለመደ ቢሆንም ለዚህ ጽሑፍ መነሻችን ሰኔ 29 ቀን 2006 ዓ.ም በደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል፣ በየአድባራቱ እየተዘዋወሩ በሚያውኩት በሥራ ፈቶችና በቤተ ክርስቲያን መሪዎች መካከል የሚሠሩትን ድራማዎች መመልከታችን  ነው፡፡ በእርግጥ በሌሊት እዚያ የተገኘነው አምላካችንን ለመመልከት ነበር፡፡ አለመታደል ሆኖብን የናፈቅነውን አምላክችንን ሳይሆን አምላካችን በቤቱ ባይተዋር ተደርጎ ለቆ እንደሄደ ተመለከትንና አዘንን፡፡ በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ቆም ብለን እንዘን፣ እንቆዝም፣ እንብሰልሰል ብንል ገደብ የለሽ የምናዝንባው ጉዳዮች አሉ፡፡ ከምንኰራበት ይልቅ የምናፍርበት ነገር በዝቶና ጎልቶ ይታያል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተቋም ናት ስንል በዓለም ካሉ ለሰው ጥቅም ከተመሠረቱ ተቋማት የምትጋራው ጥቂቱን ነገር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በሰው ፈቃድና ልምምድ ላይ ተመሥርታ የምትተዳደር አይደለችም፡፡ “የክርስቶስ አካል ናት” ማለት ቃላትን ለማሳመር ሳይሆን ባለቤቷ ክርስቶስ ነው የሚለውን እውነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለንበት ዘመን ፍትህ በማጉደል፣ ሥርዓት አልበኝነትን በማስፈን ከመንፈሳዊውም ከዓለሙም የአሠራር ሥርዓት በማፈንገጥ ቤተ ክርስቲያን ግንባር ቀደም ለመሆኗ ብዙ ማስረጃ ማቅረበ በተቻለ ነበር፤ ከአብራክዋ የተወለዱም በመንግስት ተቋሟትና በልዩ ልዩ ሓላፊነት የሚገኙ ስመ ኦርቶዶክሳውያን ይህን መንገድ እየሄዱ ለመሆኑ ማረጋገጫ ማቅረብ አያስፈልግም፡፡ አንድ ሊቅ ያለውን ያስታውሰናል፡፡ “አንድ አገር የዳበረ ባህል ከሌለው ውጤቱ ረብሻ፣ ሕገ ወጥነትና ሥርዓት አልበኝነት ይሆናል” ቤተ ክርስቲያን ለዚህ አባባል ማሳያ ናት፡፡ በአስተምህሮ ከክርስትና እውነተኛ ትምህርት ማፈንገጧ ብቻ ሳይሆን የምታፈራውም ትውልድ የሚዳኝበት መንፈሳዊ ልዕልና አለመኖር ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ክርስትና አምኖ ከክርስቶስ መወለድ፣ ከኀጢአት በሽታ መዳን፣ አዲስ ሰው መሆን፣ የመንፈስ ፍሬ ማፍራት ነው፡፡ በኛ ቤተ ክርስቲያን ስለ መዳን ያለንን አስተምህሮ ከመነሻው አበላሽተን ስለምንነሳ ጨንግፎ የሚጀምር ትምህርት ውጤቱንም እያየነው ነው፤ የከሰረ ትውልድ ውስጥ እንዳክራለን፤ እራስን አለማወቅ ደግሞ ይህንኑ በቀን ብርሃን አስክዶናል፡፡


ለነገራችን መነሻ ወደ ሆነን ደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል ስናመራ ምንም እንኳ መነሻ ይሁነን እንጂ ሁሉንም ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያናችንን ሁኔታ ይወክላል፡፡ የዚህ ደብር ልዩ መለያ የወንጌል ማዕከልነት ሳይሆን “ልዩ ሐብት” ማካበቱ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ልዩ ልዩ ቡድኖችና ማኅበራት ብሎም የቤተ ክህነት አመራር ይህን ሥፍራ “ቤዝ” አድርጐ ለመንቀሳቀስ የማይፈለግ በነርሱ አባባል ከርፋፋ ካህን ከሆነ ነው፡፡ የአካባቢው ምዕመናን በምን መልኩ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባ አለመታደል ሆኖ ደንብም ሥርዓትም የለም፡፡  ቢሆን ቢሆን በቤተ ክርስቲያኒቱ የሚተዳደር ወላጅ ያጡ ሕጻናት ጧሪ ያጡ አረጋዊያን፣ ኑሮ ያዳገታቸው የሚያገግሙበት ሥፍራ ቢሆን ምንኛ በታደልን ነበር፤ ዓላማ የሌለው ገንዘብ ድሮም ዘራፊ መግዣ ነው፡፡ አርቀን እናስብ ከተባለ ደግሞ አሁን የሚታየውን ብልሹነት ሊያስተካክል የሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ቢቋቋም፣ የልዩ ልዩ ሙያ ትምህርት ቤት እና መሰል የሆኑ በነጻ ማህበረ ምዕመናኑን በቀጥታ የሚያሳትፍ ነገር ቢኖር እሰየው ያስብለን ነበር፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ቡድኖች ተደራጅተውም ይሁን ተሹመው ሲመጡ፤ ሕንፃ ሠራን አገሩን ዓለማን ነው የሚሉት ጥቅሙ የማን እንደሆነ ባይታወቅም፡፡ ምክንያቱም ለንግድ ውድድር የተሰራ እንጂ በቀላል ወጪ ምእመናንን ለመጥቀም (Community Enterprises) የተሰሩ ናቸው ለማለት ይከብዳል፡፡
ኡራኤል ባለ ሐብት ደብር ነው መባሉ የቦታውን ታሪክ ከማበላሸት ውጪ ምንም አይፈይድም፡፡ እውነቱን ለመናገር የቦታው ቋሚ ታሪክ ወደ ፊትም የግጭት የንጥቂያ የሥርዓት አልበኝነት ወሬ የሚሰማበት ቦታ ነው፡፡ እስከወዲያኛው ባንመኝም በወንጌል ቤተ ክርስቲያኒቱ እስካልተዳኘች ይህ ክፉ ሁኔታ ይቀጥላል፡፡ እንግዲህ ከላይ እንዳስቀመጥነው የግጭትና የልዩ ኃይሎች ዓይን እንዲያርፍበት ሆኗል፡፡ በደብሩም የሚታየው አሠራር ብስለት የተሞላበት ይህን ጉዳይ በዘላቂው የሚፈታ ሳይሆን  ግጭት የሚያወናጭፉ ወጣቶችና ቡድኖች ለእለት ጉርስ የሚፋጁበት ሆኖ ይታያል፡፡
በባለፈው እሁድ ሰኔ 29 ቀን 2006 ዓ.ም በተለመደው ሁኔታ ለደብሩ ዐዲስ አለቃ መምጣቱን ለማስተዋወቅ በተደረገው እንቅስቃሴ በዚህ ደብር በሌሎችም ዘንድ እንደተለመደው ተራ ተርታ የሆነ ኢ-ክርስቲያናዊ ሥራ መመልከት ችለናል፡፡ በቅርብ ጊዜ እንደ ልማድ የተያዘ አዲስ አለቃ ከአንድ ሥፍራ ተቀይሮ ሲመጣ አጀብ የሚያሰኝ መንግሥታዊ የሚመስል እጀባና አቀባበል ይደረጋል፡፡ ይህን ሥርዓት አሟልተው ቀድሞ ከሣሪስ አቦ የነበሩ አዲሱ አለቃ ማለት ነው፤ ሌሊት ወደ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን ሲደርሱ ልብሰ ተክህኖ በለበሱ የደብሩ አገልጋዮች (ካህናት) ደማቅ አቀባበል ተደርጐላቸው ገቡ፤ ሰዓቱ ሲደርስም ቅዳሴ ቀድሰው እኛም አስቀድሰን ወደ አውደ ምህረት ለሕዝብ ሊተዋወቁና የሹመት ደብዳቤያቸው ሊነበብ ሲወጡ የተለመደው የቤተ ክርስቲያን የክስረት፣ የውርደት፣ የጥል የክርክር ድራማ ተጀመረ፣ ምክንያታዊነትን ተከትለን ስንሄድ በደብሩ ያሉ ሃሳባቸውን ምክንያታዊነትን አያሟላም ማለት ይቻላል፡፡ ሙግታቸውም ከልፋት ያለፈ ምንም አያተርፍላቸውም፤ ለማን ለምን እንደሚቃወሙም አንዳንዶቹ አያውቁትም፡፡ ከኋላ መሪ ከሆኑት በስተቀር፤ ከተቃዋሚዎች ጀርባ የሚያንቀሳቀስ ስውር እጅ እንዳለ በግልፅ ይታያል፡፡ ቤተ ክህነቱም በግልጽ አሳቡን ማስረዳት አይፈልግም፡፡ «ሁለቱም ሥራ ከምፈታ ልጄን ላፋታ» የሚለውን መንገድ የተከተሉ ይመስላሉ፡፡
አንድ ሳይነቀፍ የማይታለፍ ጉዳይ ግን ከአንቀበልም ባዮች መካከል ማለታቸውን እንጂ ያሉትን የማያውቁ እንደ ሆኑ የሚያሳይ ነገር ተደምጧል፡፡ “በሲኖዶስ አንመራም የአቡነ ማቲያስ ደብዳቤ አያዘንም” የሚሉ አረፍተ ነገሮች ተወናጭፈዋል፡፡ ማናቸው ይህን አሳብ ሕዝብ እንዲያንጸባርቅላቸው የቀሰቀሱ! በቀጥታ ሲተረጐም የቤተ ክርስቲያን የበላይ በኛ ጉዳይ ምንም አያገባውም ወይም እውቅና አንሰጠውም የሚል ይመስላል ወይም ነው፡፡ በእርግጥ በማን ደብዳቤና ሥልጣን እንደሚታዘዙ አልገለጹልንም፡፡ ስለዚህ ገፋ አድርገን ካሰብን የተለያዩ ጭፍሮች ቤተ ክርስቲያንን ቅርጫ ለማድረግ አስበው የትጥቅ ትግልን ጀምረዋል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር በቦታው አልነበረም፡፡ መደማመጥ የለም፡፡ ሁሉም ዐውደ ምህረቱን ምኞታቸውን ለማሳካት ሲሉ ዐውደ ነገር አደረጉት! መቀባበል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የለም ማለት እግዚአብሔር ትቶን ሄዷል ማለት ነው፡፡ እግር ጭንቅላትን ማከክ የጀመረ ዕለት ነገሮች እያበቁ ነው ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሲባርክ መሪ ይሰጣል፡፡ መቀባበልን ያሰፍናል፡፡ አዙረን ካየን ደግሞ እግዚአብሔር የተጣላን እንደሆነ ይህን በተቃራኒ ይገለብጠዋል፡፡
ለነገሩ ይህን ደብር እንደማሳያ አነሳን እንጂ እግዚአብሔርን በቤቱ ካጣነው ሰንብተናል፡፡ በሲኖዶስ የምንሰማው ይህንኑ መለያየትና ጸብ ነው። በየአኅጉረ ስብከቶች ብንሄድ ያለው ነገር ያው ነው። አጥብያ አብያተ ክርስቲያኖቻችንን ብንዞር ገዳሞቻችንን ብንጎበኝ ጠቡና ውንብድናው ይብሳል እንጂ እግዚአብሔርን የምናገኝበት ቦታ አንድ እንኳ ለማግኘት አዳግቶናል፡፡ የተነሣንበትን ጥያቄ የሚመልስልን ማነው? ከቤቱ የተባረረው እግዚአብሔር የት ይገኛል? እኛ ወደ ቤተ ክርስቲያን የመጣነው ራሱን በሕያው ቃሉ የሚገልጠውንና የሚያምኑበትንም የሚያድነውን እግዚአብሔርን ፈልገን ነው፤ በአንዳንድ አጥቢያዎች ስብከተ ወንጌል እየተጠናከረ ቃሉ ሲሰበክና ጌታ በቃሉ መሰበክ በቤቱ መገለጥና መስራት ሲጀምር፣ ሰዎች ንስሓ ሲገቡ፣ እርስ በእርስ ይቅርታ ሲጠያየቁና መቀባበል ሲጀምሩ ሰላምም ሲሰፍን የማይወዱቱ ኹከተኞች ወዲያው በስውር አመራር እየሰጡ የሚቀሰቅሱት ሰባክያኑንና የስብከት ጉባዔውን በመቃወም አገልግሎቱ ይቁምልን የሚሉትን ያስነሣሉ፡፡ ምን አይነት ትውልድ ነው እግዚአብሔር ቤት መጥቶ ጌታን በቤቱ እንዳይሰራ የሚያስወጣ? እግዚአብሔር ፈቃዳችንን ስለሚያከብር ነው እንጂ በፍርዱና በቁጣው ከተገለጠ የሚባላ እሳት ነው፡፡
ወደ ኡራኤሉ ክስተት ስንመለስ የቦታው ትዕይንት ስድብ፣ ጫጫታ፣ ጩኸት ምን ለማለት እንደተፈለገ የማይገልጽ መዝሙርና ልቅሶ ነበር፡፡  ከኋላ ሆነው የሚመሩ በሕዝቡ የሚጠቀሙ እውር መሪዎች  እንዳሉ ትእይንቱ በግልጽ ያሳብቅ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ ርቀት መሄድ ለምን አስፈለገ? ከአንዳንዶች እንደሰማነው በስውር ክስተቱን የቀሰቀሰውና የሚመራው የአምስት ኪሎው ባለ ሕንጻው ማህበር እንደሆነ በርግጠኝነት ይናገራሉ፤ “እባካችሁ ይህ ባለ ሕንፃ ማኅበር ማነው ብለን ለመጠየቅ እናንተ እራሳችሁ ይህን የማታውቁ ማን ናችሁ” እንባላለን ብለን ስለፈራን ሰዎቹ በስሙ ስለማንነቱ ስለተግባቡ አንባቢዎቻችንም ያውቁታል በማለት ማንነቱን ሳናጣራ በጠሩበት ስሙ አስቀምጠነዋል፡፡ የአምስት ኪሎው ባለ ሕንፃው የተባለው ማኅበር የእርሱ ሕንፃ የቱ ነው ብለን አሰብንና “ለአባ ማትያስ ደብዳቤ አንታዘዝም” የሚል መፈክር ከሚቆመርበት ሕዝብ ስለሰማን ምንአልባት ፓትርያርኩ የሚኖሩበት የመንበረ ፓትርያርክ ሕንፃ ይገባኛል የሚል ተከራካሪ፣ አማፂ፣ ሽምቅ ተዋጊ ሳይኖር አይቀርም ብለን ገመትን፡፡ ይህን ስናስብ አንድ ነገር ይታወሰናል እርሱም ተረት ነው ተረት እንወድ የለ? አንድ የፍርድ ቤት ሹም ነው አሉ ከሥራው በራሱ ጥፋት በበላይ ከሹመቱ ይሻራል፡፡ የለመደው ሹመት  አላስቀምጠው ቢለው ወንዝ ወርዶ ውሃ ከሚቀዱ ሴቶች መካከል ገብቶ አሁን አንቺ ቅጂ አሁን አንተ ቅዳ ይል ጀመር ይባላል፡፡ ዳኝነት መስጠቱ  ነው፡፡ የሰው ክምችት የሆነው ማህበር የቀሰቀሰው አድማ ከሆነ እንደተባለው ዓላማ የለሽ የሆነ ስብስብ መዳረሻው ወደዚህ መውረድ ነው፡፡
በበላይ ኃላፊዎች የተላለፈው የሥራ ዝውውር  በጐም ይሁን መጥፎ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ሲባል ለጊዜው መቀበሉ የተሻለ ነው፡፡ በተንኮልም መንገድ ቢሄዱም በመጨረሻው ሰዓት በድል ያጠናቅቃሉ፡፡ በስውር አመፁን የሚመራው ቡድንም ይህን ያውቀዋል፤ በምእመናን ልጫወትና የዕድሌን ልሞክር ብሎ እንጂ፤ ምእመናንም እንዲህ ከመሰለ የቆማሪዎች ቁማር መጫወቻነት እራሳቸውን ሊያገሉ ይገባል፡፡ ይህን የምንለው ሳያውቁት ተገፍተው ለአመጽ የተባበሩትን ነው እንጂ የኋላ አውራዎቹን አይደለም፤ ለቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ መሪዎች አንገዛም፣ አንታዘዝም የሚያስብሉ እራሳቸውን ሲኖዶሱ ቦታ ላይ እንደተቀመጡ የሚያስቡ ሸማቂ ኃይሎች እንዲህ ያለው መንፈሳዊ ቅንነትና እውነት አይነካካቸውም፡፡ ሲጀመርም የቤተ ክርስቲያን አንድነት ለነርሱ ምንድነውና? በዚህ ዓይነት ሁኔታ መቀጠል እያደገ ሄዶ መበታተንን ያመጣል፡፡ ለተጨነቁ፣ ግራ ለገባቸው ክርስቶስ ኢየሱስን ማየት ለሚፈልጉ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ሥፍራ መሆን አልቻለችም፡፡ የእግዚአብሔር ቤት ብለንም  ልንጠራት አንችልም፡፡ የእግዚአብሔር ቤት ግን ወዴት ነው? ፊታችንን ወደ እግዚአብሔር እንመልስ ቅዱስ ቃሉን እናጥና እንመራበትም፡፡ የእስካሁኑ  ወደ ገደል የሚያወርድ እንዲህ የሚያባላ ነገ ቤተ ክርስቲያንን የሚያፈርስ አገርን የሚያጠፋ መጥፎ የሕይወት ጐዳና ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት ግን ወዴት ነው?

8 comments:

 1. Mk is the master mind of this .

  ReplyDelete
 2. I enjoyed your article "Where is God's house" or where can we find God? For me and many others, we find god in our home and in our heart, in our conversation and in our action, where we work and and where we dine, not in our Deber as it should be, as you have indicated the church podium has become instrument to spread their self interest, or to broadcast vengeful message towards others. Just to give you as an example, recently there was a funeral service in our church, and several priests and bishops happened to be in town and decided to attend this service. So one of the guest priest took the podium and overtly attack some persons with different view from himself, the message should have been strictly about the young lady whose life we were honoring. It is apauling how these preachers do not have guidelines what subject matter they could teach which should be stipulated in each churchs' bylaws, but no priests and deacons use the pulpit to say whatever they wish to transmit. so you ask "where is God" In my heart, I get his guidance everyday. You see I do not need permission to talk with God.I am his child.

  ReplyDelete
 3. Ekidachihu sayisaka silekere tekatelachihu ayidel yegna Menafikan! Wore bicha!!

  ReplyDelete
 4. አይ ማህበረ ቅዱሳን ብር ጠፋበት ስለዚህ ነደደ

  ReplyDelete
 5. እናንተ መናፍቃን መች ይሆን ቤትክርስትያንን የምትተዋት ማህበረቅዱሳንን በመወንጀል አይጸደቅም እኮ

  ReplyDelete
 6. Mk papasu alamawonenea ekedun selawekubet ayekebelachewom amese bersachewo lay yasnesal.

  ReplyDelete
 7. ለናንተ እምነት ማለት ፕሮቴስታንት መሆን ነው።አሳፋሪዎች ናችሁ ፕሮቴስታንት ለራሳቸው አንድ ላይ መቆም አቅታቸው 2000 ቦታ ተከፋፍለዋል መጀመርያ አንድ ሁኑ መናፍቃኖች።

  ReplyDelete
 8. Thank u and God bless u.

  ReplyDelete