Friday, September 26, 2014

ከብዙዎች ልብ የጠፋውን መስቀል ማን ይፈልገው?

Read in PDF

በየዓመቱ የደመራ በዓል ይከበራል፡፡ በዓሉ የሚከበረው በትውፊታዊው ትረካ መሠረት አይሁድ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ተአምራት እየሰራ ስላስቸገራቸው ጉድፍ መጣያ አድርገውት ለብዙ መቶ ዓመታት ከቆየና የተራራ ክምር ከሆነ በኋላ በንግስት እሌኒ አማካይነት ከተቀበረበት መውጣቱ ስለሚዘከርበት ነው፡፡ ይህ ታሪክ እውነተኛ መሆኑ ግን በጣም አጠራጣሪ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ በተለይም ይህ ታሪክ ሊዘከርበት በሚገባው በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ይህ ጉዳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ፈጽሞ አለመወሳቱ ሲሆን፣ ሐዋርያትም ዛሬ ብዙዎች እንደሚሉት የመስቀል ቅርጽን ይዘው ወይም እያማተቡ ምንም ሲያደርጉ አይታይም፡፡ ይህም የሚያሳየው የመስቀልን ቅርጽ መጠቀምም ሆነ ማማተብ በሐዋርያት ዘመን የሌለና በኋላ ዘመን ምናልባትም ከቈስጠንጢኖስ ዘመን ወዲህ የተጀመረ ልማድ እንደሆነ ነው፡፡


በሐዋርያት ስራ ውስጥ እንደምናነበው አይሁድን ያስቸገራቸው የኢየሱስ ስም ሃያልነትና ፈዋሽነት እንጂ ዕፀ መስቀሉ አልነበረም፡፡ ሐዋርያት መመኪያ የእግዚአብሔር ኃይል እያሉ የጠሩት መስቀል ጌታችንንና መድሃኒታችን ኢየሱስ የተቀበለውን መከራ እንጂ የተሰቀለበትን እጸ መስቀል አልነበረም፡፡ ታዲያ የኢየሱስን ስም ሃያልነትና የመከራውን ስፍራ እንዲቀማ የተደረገው የእፀ መስቀል መቀበርና በንግሥት እሌኒ ከተቀበረበት የመውጣት ታሪክ ደራሲ ማን ይሆን?

Tuesday, September 23, 2014

የኦክላንድ ደብረ ሰላም ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን እና የመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ልዩነት በይቅርታ ተደመደመ።

 Read in PDF
ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ በመጨረሻም ቢሆን መልካም ታሪክ እየሰሩ ነው። በየሄደቡት ሁሉ የበድልኋችሁ ይቅር በሉኝ በማለት ማንኛውንም ተቀይሚያለሁ ያለውን ሁሉ እየታረቁ ነው።
  የኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ያስተዳደር በደል ደረሰብን በማለት ባቀረቡት ጩኸት የሚሰማቸው በመታጣቱ ከመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተለይተው የራሳቸውን ቤተ ክርስቲያን ማቋቋማቸውና በብፁእ አቡነ መልከ ጼዴቅ መወገዛቸው ይታወሳል። ቅዱስ ፓትርያርኩና ሌሎች አንዳንድ ጳጳሳት እንዲሁም ሰባክያነ ወንጌል ውግዙቱን አንቀበልም በማለት ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር ቁመው ቆይተዋል። ይህን ሁኔታ እንደ ልዩ መግቢያ በመጠቀም ጠቡን ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ እና ወደ አቡነ መልከ ጼዴቅ ከፍ በማድረግ ከጠቡ የሚገኘውን ፍርፋሪ በኮፌዳቸው ሊለቅሙ ያሰፈሰፉ ሰዎችም ነበሩ። በተለይም በአስታራቂ ኮሚቴው ከተካተቱት አባላት ውስጥ የዳላሱና የሎስአንጀለሱ ዋና ተጠቃሽ ናቸው። 

አንዳንድ የቦርድ ኮሚቴ ነን የሚሉ የፖለቲካና የልዩ ጥቅም ኃይሎችም ከጠቡ ተጠቃሚ ለመሆን ሲሯሯጡ ነበር። የብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅን ጠንካራ ወዳጆች ሰባክያነ ወንጌልን በዚህ እያያይዞ መምታት ዋና ተግባራቸው አድርገው ያላሉትን አሉ ያላደረጉትን አደረጉ በማለት ከአቡነ መልከ ጼዴቅ ለይተዋቸው ነበር። ይህን ልዩነት ወደ ሕዝብ ለማውረድ ታስቦም ጽሑፍ ተዘጋጅቶ በጥምቀት በዓል ላይ ሊበተን ሲል እግዚአብሔር ቀድሞ ወጥመዱን አክቸፈው። የታሰበው የጠብ እቅድ ተበላሽቶ ወደ ሰላም እርቅና ፍቅር ተለወጠ አባቶች እርስ በርስ ይቅርታ ተጠያየቁ ጽሑፉን ያዘጋጀው ሰው ኮፒ አድርጎ ሲመጣ ሰላም ወርዶ አገኘው በቁጣ ተሞልቶ ፊቱ ላይ ይታወቅበት ነበር ይላሉ ታዛቢዎች። ምእመናኑ እልል አሉ ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን እያሉ እግዚአብሔርን በመዝሙር አከበሩ። የጠላታችን ቢሆንም ጊዜው፤ ዛሬም እኛው ነን የምናሸንፈው ነገም እኛው ነን የምናሸንፈው። ተብሎ ተዘመረ።

Monday, September 15, 2014

በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ስር የሚመራው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ አስራ ሁለተኛ አመታዊ ጉባኤ ተካሄደ

Read in PDF

በሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ስር የሚመራው የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ አስራ ሁለተኛ አመታዊ ጉባኤ “ራእይ ያለው ትውልድ” በሚል መሪ ቃል በደብረ ቅዱሳን ተከለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን በኦታዋ ካናዳ ተካሄደ፡፡ እንደፈረንጆች አቆጣጠር ከAugust 29 – August 31, 2014 ለሶስት ቀናት የተካሄደው አመታዊ መደበኛ ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ የተከናወነ ሲሆን ከካናዳ እና ከተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች ከ150 በላይ ተሳታፊዎች 21 የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትንና ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በመወከል ተገኝተዋል።

ጉባኤው በሊቀ ካህናት ምሳሌ እንግዳ የቅዱስ ሲኖዶስ የውጭ ጉዳይ ተጠሪ ጸሎት የተጀመረ ሲሆን ራእይ ያለው ትውልድ በሚለው መሪ ቃል ሥር ልዩ ልዩ ትምህርቶች በተለያዩ መምህራን የተሰጡ ሲሆን በዚሁ መሠረት፦
·        ዓላማ፤ ጥሪና ራዕይ - በቀሲስ ዘገብርኤል አለማየሁ
·        ራእይ በመጽሐፍ ቅዱስ - በቆሞስ አባ መላኩ ታከለ
·        የሕይወት ራዕይ - በቀሲስ መላኩ ተረፈ
·        ራዕይ ለቤተክርስትያን - በቀሲስ መላኩ ተረፈ
·        ራዕይ ለኢትዮጵያ - በአባ ገብረሥላሴ ጥበቡ
·        ራዕይ ለአለም - በቀሲስ ዘገብርኤል አለማየሁ ተሰጥተዋል፡፡
የጉባኤው ተሳታፊዎችም በመምህራን የተሰጠውን ትምህርት በበለጠ ከሕይወታቸው ጋር ማዛመድ እንዲችሉ የሚረዳና ከተመረጡት የትምህርት እርእስት ጋር የሚሄዱ ተግባራዊ መልመጃዎች ቀርበዋል። ከዚህ በተጨማሪም በየክልል ጉባኤ ላይ የየቤተክርስቲያኑ ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በህብረት ሆነው በተመደበላቸው የትምህርት ርዕስ ላይ የቀረፁትን ስምንት ራዕዮች በክልሉ ተወካዮች በኩል አቅርበዋል።

Tuesday, September 9, 2014

በአዲሱ ዓመት በአዲስ ሕይወት እንመላለስ

https://drive.google.com/file/d/0B2hMej2gZy_lRkRHeVQ2bVh3WlE/edit?usp=sharing 


አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ያለፈውን ዓመት አሮጌ ብሎ መሸኘት፣ በዓመቱ የተከናወኑ ብርቱና ደካማ ጎኖቻችንን መፈተሽ፣ በአዲሱ ዓመት የለውጥ ሐሳቦችን ይዞ ብቅ ማለቱ የተለመደ ነው፡፡ ይህ እንደባህል ከመያዙ በስተቀር በውሳኔያችን የምንጸናና እንዳቀድነው በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንገድ የምንመላለስ ግን ጥቂቶች ነን፡፡ አብዛኛዎቻችን ከአዲሱ ዓመት ላይ ጥቂት ቀናት እንደተነሱ ወደ አሮጌው ዓመት ኑሯችን እንመለሳለን፡፡ አዲስ ያልነው ዓመትም ወዲያው ማርጀት ይጀምራል፡፡ ታዲያ ከአሮጌው ማንነት ለመውጣትና በአዲሱ ማንነት ለመመላለስ መፍትሔው ምን ይሆን?

አዲስ ሕይወትን ለመጀመር መነሻው አዲስ ዓመት ሊሆን አይችልም፡፡ አዲስ ዓመት አዲስ ሕይወትን ለመጀመር ሊያነሳሳ እንደሚችል ግን መናገር ይቻላል፡፡ ታዲያ በአዲስ ሕይወት ለመመላለስ መነሻው ምን ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፡፡ አሮጌው ነገር አልፏል፡፡ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኗል፡፡” (2ቆሮ. 5፡17) ይላል፡፡ የአዲስ ሕይወት መሠረቱና መነሻው ይኸው ነው፡፡ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት መሆን፡፡

Saturday, September 6, 2014

"በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ” 1ጴጥ 4፥13

Read in PDF

ይድረስ በናይጀሪያ፣ በቻይና፣ በኢራቅ፣ በሶሪያ፣ በግብጽ፣ በፓኪስታን፣ በሳውዲ አረቢያና በሶማሊያ ለምትገኙ ክርስቲያኖች።
እኛ በኢትዮጵያ የምንገኝ ክርስቲያን ወንድሞቻችሁ ነን። ሁላችን የአንድ አባት ልጆች ነን፣ በተለያየ አመለካከት ስሕተትም ይሁን ትክክል ይሁን እንለያይ እንጂ ሁላችንም በሚመጣው የክርስቶስ መንግሥት እንገናኛለን "በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና” ተብሎ እንደተጻፈ የክርስቶስ የመስቀሉ ሥራ ሁላችንንም ከነድክመታችን በአብ ዘንድ ያገናኛናል። መከራ የሚያሳዩአችሁም በክርስቶስ የፍርድ ወንበር ፊት ይቀርባሉ። እናንተ የክርስቶስ አካል ናችሁ እኛም የክርስቶስ አካል ነን። ስለዚህ የናንተ መከራ እኛንም ይሰማናል። የአካላችን አንዱ ክፍል ናችሁና ሕመሙ የጋራችን ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሕመሙ ይሰማዋል እስጢፋኖስ መከራ ሲቀበል ከዙፋኑ ብድግ ብሎ ቆሞ እንደታየ ዛሬም በእናንተ መከራ ጊዜ ዝም ብሎ የተቀመጠ እንዳይመሳላችሁ። ስለስሙ ያቀራባችሁትን የተወደደ መስዋእታችሁን ለመቀበል ቆሞላችኋል።
 አይዟችሁ በርቱ የተስፋችን ፍጻሜ እየቀረበ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ ሊመጣ ዓለም የማያውቀው የልጅነት ክብራችን ሊገለጥ እየተቃረበ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ "ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ስቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ። የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጥባበቃልና።” ብሎ እንዳስተማረን እግዚአብሔር ስለ ስሙ የተቀበላችሁትን መከራ ዘለዓለማዊ ደስታ አድርጎ ይለውጥላችኋል። 

Wednesday, September 3, 2014

ይድረስ ለዘማሪ ታዴዎስ ግርማ።እግዚአብሔር ታላቅ ነው ነገር ግን ማንንም አይንቅም መዝ 51፥17፤
ኃያል ነው ግን በጣም ታጋሽ ነው ኢዮ 36፥5።
ስሜን በከንቱ አትጥራ በማለት ክብሩን የተናገረው አምላካችን ዘፍ 20፥4 እንዲህ በድፍረት የምንዘባበትበት አይደለም። ለመዘመር ያነሣሣን ምንድር ነው? እግዚብሔርን ስላወቅነው? ወይስ በሌላ ስሜት? መዝሙር አምልኮ ነው እግዚአብሔር ስላደረገልን የምንሰጠው የደስታ ምላሽ ነው። ማርያም እሕተ ሙሴ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሙሴ አልዘመረችም ዘጸ 15፥1። እመ ሳሙኤል ሃና ለእግዚአብሔር ዘመረች 1ሳሙ 2፥1። ቅዱስ ዳዊት ለእግዚአብሔር ዘመረ። ድንግል ማርያም ለእግዚአብሔር ዘመረች ሉቃ 1፥47። በመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኛቸው ቅዱሳን ሁሉ ለእግዚአብሔር ብቻ እንቺ አንዱ ለሌላው ሲዘምር አናይም። እኔ እንደተማርኩት ቅዱስ ያሬድም ለእግዚአብሔር ብቻ ነው የዘመረው። የኋላ ሰዎች አዋልድ በሚል ጨመሩበት እንጂ። ቅዱሳንንም ሲያነሳ ተጋድሏቸውንና እሩጫቸውን መጨረሳቸውን በማድነቅ የእግዚአብሔር ክንድ እንዴት እንዳገዛቸው ይናገራል እንጂ እነርሱን ከጌታ በላይ አስቀምጦ የእርሱን ሥራ ለነርሱ አይሰጥም። መጽሐፍም "ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ፤ ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ እግዚአብሔር ለምድር ሁሉ ንጉሥ ነውና በማስተዋል ዘምሩ‚ በማለት ለማን መዘመር እንዳለብን ይነግረናል። መዝ 46፥6-7።


ይህን ማስታወሻ የጻፍኩልህ አንደኛ ዝማሬ ለጌታ መሆኑን ልነግርህ ሲሆን! በተጨማሪም አንተን ተከትሎ የተሳሳተውን ሕዝብ ወደ ትክክለኛው አምልኮ ለመመለስና አንተም ንስሐ እንድትገባ ለመምከር ነው። በዚህ ሃያ ዓመት ውስጥ የኢትዮጵያን ሕዝብና ቤተ ክርስቲያንን ከበደሉና ይቅርታ መጠየቅ ከሚገባቸው ሰዎች መካከል አንዱ አንተ መሆንህን ልነግርህ እወዳለሁ።