Tuesday, September 9, 2014

በአዲሱ ዓመት በአዲስ ሕይወት እንመላለስ

https://drive.google.com/file/d/0B2hMej2gZy_lRkRHeVQ2bVh3WlE/edit?usp=sharing 


አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ያለፈውን ዓመት አሮጌ ብሎ መሸኘት፣ በዓመቱ የተከናወኑ ብርቱና ደካማ ጎኖቻችንን መፈተሽ፣ በአዲሱ ዓመት የለውጥ ሐሳቦችን ይዞ ብቅ ማለቱ የተለመደ ነው፡፡ ይህ እንደባህል ከመያዙ በስተቀር በውሳኔያችን የምንጸናና እንዳቀድነው በአዲሱ ዓመት በአዲስ መንገድ የምንመላለስ ግን ጥቂቶች ነን፡፡ አብዛኛዎቻችን ከአዲሱ ዓመት ላይ ጥቂት ቀናት እንደተነሱ ወደ አሮጌው ዓመት ኑሯችን እንመለሳለን፡፡ አዲስ ያልነው ዓመትም ወዲያው ማርጀት ይጀምራል፡፡ ታዲያ ከአሮጌው ማንነት ለመውጣትና በአዲሱ ማንነት ለመመላለስ መፍትሔው ምን ይሆን?

አዲስ ሕይወትን ለመጀመር መነሻው አዲስ ዓመት ሊሆን አይችልም፡፡ አዲስ ዓመት አዲስ ሕይወትን ለመጀመር ሊያነሳሳ እንደሚችል ግን መናገር ይቻላል፡፡ ታዲያ በአዲስ ሕይወት ለመመላለስ መነሻው ምን ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፡፡ አሮጌው ነገር አልፏል፡፡ እነሆ ሁሉም አዲስ ሆኗል፡፡” (2ቆሮ. 5፡17) ይላል፡፡ የአዲስ ሕይወት መሠረቱና መነሻው ይኸው ነው፡፡ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት መሆን፡፡

ሰው በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት እስኪሆን ድረስ በአሮጌው ማንነቱ ነው ያለው፡፡ በዚህ ማንነት ደግሞ ሃይማኖተኛ ነኝ ቢልም እንኳን ምድራዊ እንጂ ሰማያዊ መሆን አይቻልም፡፡ ምድራዊ ስኬት እንጂ መንፈሳዊ ፍሬ ማፍራት አይቻልም፡፡ ሥጋዊና ዓለማዊ ሰው እንጂ መንፈሳዊ ሰው መሆንም አይቻልም፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት መሆን የማያስፈልገው ሰው የለም ማለት ነው፡፡ ሰው በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ካልሆነ አሮጌ ነው፡፡ ፍጥረታዊ ሰው ነው፡፡ በአዳማዊ ማንነቱ የሚገኝም ነው፡፡ በዚህ ማንነት ያለ ሰው ደግሞ እግዚአብሔርን አላወቀም፡፡ በክርስቶስ ሞት የተከናወነውን የኃጢአቱን ስርየት በእምነት አልተቀበለም፡፡ በክርስቶሰ የቤዛነት ስራ አላመነምና የእግዚአብሄር ቁጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም፡፡ ሰው ከዚህ አሮጌ ማንነት መውጣት የሚችለው በአዲስ ዓመት ሳይሆን በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት በመሆን ነው፡፡

ሰው ስም ያለው የትልቅ ሃይማኖት ተከታይ ስለሆነ አዲስ ፍጥረት ነው ማለት አይደለም፡፡ ልዩ ልዩ የሃይማኖት ስርኣቶችን ስለፈጸመም አዲስ ፍጥረት ሊሆን አይችልም፡፡ አዲስ ፍጥረትነት በክርስቶሰ በመሆን ብቻ የሚገኝ እውነተኛ የሕይወት ለውጥ ነው፡፡ ሰው በክርስቶስ የሚሆነው ወይም በእርሱ አምኖና ራሱን ለክርስቶስ አስረክቦ እርሱን በእውነተኛ ልብ ሲከተለው ነው፡፡ ይህም በቅዱስ ወንጌል እንደሚሰበከው በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት ሰው የክርስቶስ ቤዛነት የእርሱ እንደሆነ፣ ኃጢአቱ እንደተሰረየ ከኩነኔ ነጻ እንደወጣና የዘላለማዊ ሕይወት ባለቤት እንደሆነ አምኖ ሲቀበል የሚገኝ አዲስ ሕይወት ነው፡፡ በዚህ ጊዜ “በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም” (ሮሜ 8፡1) ሲል ቃሉ የሰጠው የተረጋገጠ ተስፋ በሚያምነው ሰው ሕይወት ውስጥ እውን ይሆናል፡፡ ያኔ ነው ከአሮጌው ማንነት ወደ አዲሱ ማንነት ተሸጋገርን ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር የምንችለው፡፡

በአዲሱ ዓመት አሮጌው ሕይወት በቃኝ፤ በአዲስ ሕይወት መመላለስ አለብኝ ያልን ስንቶቻችን እንሆን? ስንቶቻችንስ እንዲህና እንዲያ ለማድረግ ወስነናል? አንድ እውነት አለ፤ ሰው በኃይሉ አይበረታም ተብሎ እንደተጻፈው (1ሳሙ. 2፥9) በራሳችን ውሳኔ ብቻ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት አንችልም፡፡ በአሮጌው ማንነት እስካለን ድረስ ኃጢአት ያደከመን የኃጢአት ደካሞች ነን፡፡ የኃጢአት ሸክም የከበደው ደግሞ ይህን ሸክሙን ሳያወርድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ መንፈሳዊ ፍሬ የሌለው ከንቱ ድካም ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ወደእኔ ኑ የሚለውን የጌታን ድምፅ ሰምቶ ወደእርሱ በእምነት መቅረብና የኃጢአትን ሸክም ማራገፍ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም የእርሱን ቀላል ሸክምና ልዝብ ቀንበር ተሸክሞ በደስታ መመለስና በዚሁ ደስታና ሰላም ውስጥ መኖር ነው፡፡      


1 comment: