Wednesday, October 1, 2014

“ጌታዬ ሆይ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ቢሆን ይህ ነገር ሁሉ ስለምን ደረሰብን?» /መሳ.6÷13/ባለፈው መልእክታችን የእግዚአብሔር ቤት ወዴት ነው? የሚል መልእክት ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ በዓይነቱ ተመሳሳይ የሆነ መልእክት ደግሞ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ሥር እናስነብቦታለን፡፡ የባለፈው ጽሑፋችን ከአንድ ትዝብት ተነሥቶ የእግዚአብሔር ቤት ወዴት ነው? ወይም በእውነት እግዚአብሔር ከኛ ጋር ነው? በሚል ሐሳብ ላይ አጠንጥኗል፡፡ በመጠኑም ቢሆን ቤተ ክርስቲያናችን ያለችበትን ሁኔታ ለማየት የቻልን ሲሆን ወቅታዊው የቤታችን ጉዳይም ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነም ተመልክተናል፡፡ እንደ አንድ መንፈሳዊ ተቋምም የቃሉን ቱንቢ ተጠቅመናል፡፡ የፈተሽንበትም መንገድ ማዕከል ያደረገው ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ከእነዚህ መጻሕፍት ጋር የሚስማሙትን በትውፊት የተቀበልናቸውን እግዚአብሔራዊ ቃል መሠረት አድርገን ነው፡፡ የተወደዳችሁ አንባቢዎችም ካሻችው  አማራጭ መንገድ ተከትላቸው እንድትመረምሩና ፍለጋ እንድታካሄዱ የእግዚአብሔር ቤት ወዴት ነው? በሚል ፍለጋውን ለናንተ ትተናል፡፡ የዛሬ አሳባችን ተመሳስሎና ታሪክ ጠቅሶ ዘመነ መሳፍንትን በማስቃኘት  በሌላ ሙግት ይቀጥላል፡፡
የዘመነ መሳፍንት ታሪካዊ ዳራ
“ጌታዬ ሆይ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ቢሆን ይህ ነገር ሁሉ ስለምን ደረሰብን?” ይላል ጌዴዎን በመጽሐፈ መሳፍንት ምዕራፍ 6÷13፤ የጥያቄው መነሻ ለጌዴዎን የተገለጠለት መልአክ ይህን የእግዚአብሔር ባሪያ “ብቻህን አይደለህም እግዚአብሔር ካንተ ጋር ነው” በማለት ላረጋገጠበት ንግግር የቀረበ የይግባኝ ጥያቄ ነው፡፡
ነገሩ ወዲህ ነው! የእግዚአብሔር ባለመዋል አብርሃም በዘፍጥረት ምዕራፍ 12÷1-3 እንደምንመለከተው በጌታው ተስፋ ላይ ሲተከል ሕዝብ ሆኖ ተባርኮ እንደሚባርክ፣ በዓለም ሁሉ ሰፍቶ በረከቱ ከእርሱ ተርፎ አሕዛብን ሁሉ አትረፍርፎ እንደሚጎበኝ ከተነገረው ቃል የተነሣ በእምነት እንደ ሆነለት በመቁጠር በሩቁ አይቶ ተስማምቷል፡፡ ሆኖም ኪዳኑን ለማጽናት ተስፋውን ለማጉላት ጌታ ተመልሶ በዘፍጥረት 15÷18 ሲገናኘውና ሲያረጋግጥለት እንመለከታለን፡፡ ሆኖም ግን በተገባለት ተስፋ መሠረት የአሞራውያን፣ የከነዓናውያን፣ የኢያቡሳውያን እንዲሁም የሌሎች ጽዋ እስኪሞላ መጠበቅ ነበረበት፡፡ አብርሃምና ዘሮቹ ርስታቸውን ለመውረስ ረጅም ጊዜ ተጣለባቸው፡፡ ጊዜውም የዋዛ አይደለም ከ430 ዓመት በላይ እንጂ፤ (በክርስቶስ በኩል የሚሆነው የተስፋ ፍጻሜ እንደተጠበቀ ሆኖ) ልብ ላልነው ምን ያህል አድካሚ እንደሚሆን ለመገመት አያዳግትም፡፡

      ይህ ታሪክና ተስፋ ቀጥሎ በይስሓቅ አልፎ ዘመን ተሻግሮ በያዕቆብ ዘመን ታድሶ ግብጽ አገር ገባ (ዘፍ.46÷1)፡፡ በአሣር፣ በጭንቅና በግፍ የተባለው ዘመን መላ፡፡ ይህ ግን በዋዛ የተደረሰ ዘመን አይደለም፤ ብዙ እስራኤላውያን ዋጋ ከፍለውበታል፤ ብርቱ እምነትም ታክሎበታል፡፡ የሕዝቡ ጭቆና ሲበረታ ጩኽትም ወደ ላይ ወደ አምላክ በደረሰ ጊዜ “እግዚአብሔርም አለ በግብጽ ያለውን  የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ…. ከግብፃውያን እጅ አድናቸው ዘንድ….  ወተትና ማር ወደምታፈስሰው አገር ወደ ሰፊዪቱና ወደ መልካሚቱ አገር ወደ ከነዓናውያንም ወደ ኬጢያውያንም፣ … ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ” (ዘፀ.3÷7-12)፡፡ በዚህ መሠረት ወደ ነፃ መሬት ሊያወጣቸው ወደደ፡፡ እንዳለውም አደረገው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን አሕዛብም ይሁኑ ሕዝቡ ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ ምክንያቱም የጌታ ቀን ሳያስቡት ደርሷልና፡፡ ሐሳቡን ለማስፈጸም ሲነሣ ማንም አያቆመውምና፤ ውጊያውና ዘመቻው በሠራዊት ጌታ ይመራ ስለነበር ሁሉ በጊዜው ተከናውኗል፡፡ ጉዞውም በተለያዩ ምክንያቶች አርባ ዓመታትን ፈጅቷል፡፡
ለዚህ ዋና ምክንያት የሕዝቡ አለመታዘዝ፣ አለማመንና የእግዚአብሔር ፍርድ ነው፡፡ ከሠላሳ አንድ መንግሥታትና ነገሥታት ጋር ጦር ገጥመዋል፤ በተዋጊው ጌታ ድል ነሥተዋል፡፡ አሕዛብና አማልክቶቻቸው ተሸንፈዋል፣ ተዋርደዋልም! ለእስራኤልና ለአምላኳ ተንበርክከዋል፡፡ እግዚአብሔርም በአሕዛብ አማልክት መካከል ብቸኛ ልዩና የተፈራ አምላክ እንደሆነ እራሱን ገልጧል፤ የአሕዛብንም የግፍ ጽዋ ተበቅሎበታል፡፡ በዓለም ሁሉ ታይቶ ተሰምቶም በማይታወቅ መልኩ እግዚአብሔር በትከሻው እስራኤልን ተሸክሞ እንደ ንስር በክንፎቹ ከልሎ መድረስ ከሚገባቸው አድርሷቸዋል፤ ምንም እንኳ በስህተታቸው የከፈሉት ዋጋ ቢኖርም፡፡ ሌላው ጉዞው  ከማይዘነጋቸው መካከል የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሙሴና ኢያሱ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ (የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ልትማርባቸው ይገባል ባለ ራእይ መሪዎች ናቸውና፡፡ የሚያሳዝነው የኛ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለምን እንደሚኖሩ የወደፊቱን ማሰብ አይፈልጉም፤ ለውጥ አምጪ እቅድም ማቀድ አያስቡም፤ ደግሞም የላቸውም፡፡ በርግጥ እንዲህ ለማሰብና ለመሥራት መጀመሪያ ለክርስቶስ ራስን ማስገዛትና በሙሉ ልብ ለመዳናችን የከፈለውን ዋጋ ለእኔ ነው ብሎ ማመን፣ ክርስቲያናዊ አስተምህሮን ጠንቅቆ ማወቅ፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ምሳሌ መሆን፣ መጠራት፣ ከልብ ለአገር ለወገን ይልቁን ለክርስቶስ ወንጌል ዓላማ መቆርቆር ይጠይቃል፡፡ ግን  ይህ ሁሉ የለም፡፡ እንዲህ እንዲሆኑ የማይፈቅደው ጌታ ቤቱን ለወንበዴዎች እስከ ጊዜው ትቶላቸዋል፡፡)፡፡ በምድረ በዳው ጉዞ አሮንና ካህናቱ የነገድ አለቆችም ደግሞ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በተጨማሪም ሥርዓተ ክህነት፣ የመቅደስ አገልግሎቱ፣ መገናኛ ድንኳኑ በተጨማሪም ሕጉ መሠረታዊ የሞራል ልዕልና እና ከጌታ ጋር የመገናኛ መስመሮች ናቸው፡፡ በሙሴ አርባ ዓመት የተመራው ሕዝብ ከዮርዳኖስ ወዲያ ማዶ ቢዘገይም ከአምስት ዓመት እልህ አስጨራሽ የመውረስና ወደ ከነዓን የመግባት የእግዚአብሔር ጦርነት በኋላ ሕዝቡ የተጠራበትን ርስት በተዋጊው ጌታ ወርሰዋል፤ እንደሚገባቸውም ተካፍለዋል፡፡ ቅብብሎሹ እንደቀጠለ ነው ማለት ነው፡፡
ዘመነ መሳፍንት
ለክርስቶስ ምሳሌ (ጥላ) ከሚሆነው ከኢያሱ በኋላ እስራኤል መራር ዘመን ተሻግራለች፤ ይህም ወደ 480 ዓመት ይገመታል፡፡ የመሳፍንት ዘመን በሚል ይታወቃል፡፡ በዚህ ዘመን ከላይ ካየነው መልካም የተስፋና የመውረስ ዘመን የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ልዩ የሚያደርገው ከእግዚአብሔር አሳብ በተቃራኒ መቆማቸው ነው፡፡ በመጽሐፈ መሳፍንት ምዕራፍ 2÷10 ላይ እንዲህ ይነበባል ከዘመን በኋላ እግዚአብሔር ለእስራኤል ያደረገውን የማያውቅ ትውልድ ተነሣ” ይለናል እግዚአብሔር ያን ሁሉ ካደረገ በኋላ፡፡ ከዚህ የተነሣ የሚያደርጉትንና የሚሆኑትን ሊያውቁት አልቻሉም፤ ሰው ሁሉ ወደገዛ ፈቃዱ አዘነበለ፡፡ በተለይ የዚህን ዘመን ታሪክ የዘገበው መጽሐፈ መሳፍንት ደግሞ ደጋግሞ ሳቱ ለጣዖታት ተንበረከኩ ይለናል፡፡ ከዚህ የተነሣ ከርስታቸው መካከል በርትተው ያላስለቀቁአቸው አሕዛብ  እየተነሡ ይገዙአቸዋል ያስገብሩአቸዋል፡፡ (የሁልጊዜ የእስራኤልን ውድቀትና ችግር ልብ ይሏል) በዚህ ብቻ ሳያበቃ አማልክቶቻቸውን ተላምደው ከነርሱ ጋር በአምልኮተ ጣዖት ተጠምደው እናያቸዋለን፡፡ ይህን ተከትሎ ከአምላካቸው ጋር ተፋቱ፣ የተናቁና የተተዉ ሆኑ፡፡ (የዛሬው የኛ አምሳያ ሆኑ ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን ትታ የክርስትና ትምህርት ባልሆነ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆነ በተረታተረት ትምህርት ተጠምዳለች፡፡ ከፊሉን ክርስቲያናዊ ትምህርት ይዛ ሌላውን ጥላ ከነቢያትና ከሐዋርያት ትምህርት ኮብልላለች፡፡ የሕዝባችንም ሕይወት በመንፈሳዊና ቁሳዊ ጉስቁልና ውስጥ ይገኛል፡፡ ወየው ማን በነገራት….)
ምድያማውያን
በተለያዩ ዘመናት የበረቱ የጐረቤት አሕዛብ መንግሥታትና ሕዝቦች እስራኤልን ሲረግጡ ኖረዋል፤ በጌዴዎን ዘመን ተራው የምድያማውያን ሆነ፡፡ ምድያም ብዙ ኃያል የሚባል ሆኖ ሳይሆን ከዮርዳኖስ በስተምሥራቅ ያሉ ሕዝቦችን በማስተባበር እንደ ደራሽ ውሃ እየመጣ ይወራቸው ነበር፡፡ ለሰባት ዓመታትም ያህል ቡቃያቸውን ይረግጣል፣ ያጠፋል እንሰሳው አይቀር አዝመራው ሲፈልግ ዘርፎ ሲተርፈው አቃጥሎ ሲያስጨንቃቸው ቆየ፡፡ የዚህ ዘመን ሰው ጌዴዎን አንድ ነገር ያውቃል ከአማልክት ሁሉ በላይ የሆነ አምላክ የእርሱና የአባቶቹ አምላክ እንደ ሆነ፡፡ ነገር ግን በታሪክ ነው የሚያውቀው፡፡ እስራኤላውያን የግብፅ ስደተኛ የምድረ በዳ ተጓዦች በነበሩ ጊዜ አባቶቹ አምነውና በታላቅ ታምራት፣ በድንቅ ኤርትራን ተሻግረው እንደ መጡ ቤተሰቡ ያወጋዋል! ዛሬ ግን የለም፡፡ ጌዴዎን ያልተረዳው ነገር አለ፤ ልክ ዛሬ ዛሬ በኛም ምድር ሰዎች በቤተክርስቲያን መሰብሰባቸውን እንጂ እግዚአብሔር ይኑር ጥሎን ይሂድ በቃሉ እውነት ማረጋገጥ አንፈልግም፡፡ እግዚአብሔር በባህርይው ምን ያህል ነውርን፣ ኀጢአትን እንድሚጸየፍ አናስተውልም፡፡ ጌዴዎን ባይረዳውም  መጽሐፍ የሚለው “የእግዚአብሔር እጅ ትከፋባቸው ነበር” /መሳ.2÷15/  እስራኤል በእግዚአብሔር የቁጣ ክንድ ሥር ወደቀ፡፡ የጌዴዎን ንግግር ከእግዚአብሔር ጋር ተፋተናል ነው፡፡ እግዚአብሔርም የበኩሉን ይላል “ድምጼን አልሰማችሁም /መሳ. 6÷10/ ነገሩ ወዴት እየሄደ እንደሆነ ልብ በሉ! አንዳንዴ ይህ ዘመን የሚያሳየው ከመቼውም በላይ ሰዎች አምላካቸውን ያስቀየሙበት፤ አንዳንዶችም የርሱን አብሮነት የተጠራጠሩበትና ግራ የተጋቡበት ዘመን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኃጢአት ክፉኛ ሰውን ከአምላኩ የሚነጥልበት አእምሮን የሚይዝ ባላጋራ ነው፡፡ የሕዝብንም ልብ ያሸፍታል፡፡ ጌዴዎን ለመልአኩ አሳብ የሰጠው ምላሽ በርግጠኝነት እግዚአብሔር ትቶናል ነው፡፡ በርግጥ ልክ ነው፡፡ አምላክ አለኝ የሚል ሕዝብ መረን ሆኖ የአሕዛብ መላገጫና መጫወቻ ሲሆን ለምን አያስጠረጥርም? በኛም አገር የሚሆነውን በቤተክርስቲያን የሚፈጸመውን እብደትና ነውር ስናይ እግዚአብሔር ከኛ ጋር አለ እንዴ? ያስብላል፡፡ ምንም እንኳ መልአኩን ልኮ ካንተ ጋር ነኝ ይበል እንጂ ጌዴዎን እንዳለው ቀድሞ እግዚአብሔር ትቷቸው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ግን እግዚአብሔር ለማዳን ተነሥቷል ማለት ነው፡፡ ወደ ተናቀው ጌዴዎን እየገሰገሰ ነው፤ የሕዝቡም ምሬት ደርሶታል፤ የአሕዛብን የጭቆና ቀንበር ማየትም አንገሽግሾታል፤ የእስራኤል የነጻነት ቀን ለመድረሱ እግዚአብሔር ፍንጭ እየሰጠ ነው፡፡ ታናሹና የተናቀው ጌዴዎን መልእክት ደርሶታል፤ የምድያማውያን ፀሐይ እየሽቆለቆለች ነው፡፡ የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ የምትገለጥበት ቀኑ ደረሰ፡፡ እግዚአብሔር ሲመጣ በቦታው ሲገኝ መኖሩን ይገልጣል፡፡ እግዚአብሔር ያለበት ሥፍራ በእውነት የሚጣፍጥ ሕይወት፣ ቅድስና፣ ጽድቅ፣ ሰላምና ደስታ አለ፡፡ ከሁሉ በላይ በአዲስ ኪዳን የእነዚህ ሁሉ ማደሪያ ኢየሱስ አለ፡፡   
በዘመነ መሳፍንት  ውስጥ ወደ ራሳችን እንይ ???
በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ከሚታዩ መልካም ነገሮች ይልቅ እጅግ የሞላው የክፋት ሁሉ ሥር ነው፡፡ ከቤተ መንግሥት እስከ ቤተ ክህነት ከከተሜው እስከ ገጠሩ፤ ከሊቅ እስከ ደቂቅ በማይታመን ሁኔታ  ጽድቅና እውነትን ማቆሸሽ የተያዘበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ ወደዚህ አዘቅት ምን አወረደን ብሎ ማሰብም ነውር ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ከዚህ መንገድ እንመለስ ማለትም በሃይማኖት ለዋጪነት ስለሚያስፈርጅ፤ /ጌዴዎንም የጣዖት አምልኮን ማፈራረስ በተያያዘበት ጊዜ ያገባናል የሚሉ መሠዊያ ጠባቂዎች ተገዳድረውት ነበር፤ እውነተኛው አምላክ ከርሱ ጋር ሆነና አላሸነፉትም እንጂ፡፡/ እነሆ እንደ ጌዴዎን የኛም ጥያቄ “እግዚአብሔር ከኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ ለምን ደረሰብን እንላለን፣ እንጠይቃለን፡፡ እኮ ምን ሆነ የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችል ይሆናል፡፡ ያልሆነብን ምን አለ ለማለት እኛ ደግሞ እንገደዳለን፡፡
ይህን አሳብ ስንጽፍ እንደ አገር ወይስ እንደ ቤተክርስቲያን እናውራ የሚል ጥያቄ አጫረብን፡፡ ምክንያቱም ከልባችን ልንል የወደድነውን እስቲ ተመልከቱ መቼም የከፋ ድንቁርናና ጉስቁልና፣ እምነትና አስተሳሰብ የተጫነው ሕዝብ እንደ እኛ አለ ወይ? እነዚህን ሁሉ በዝርዝር ለማየት ሁለቱንም አዋሕደን እንመለከታለን፡፡ እንደ ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ትከሻችንን ሰብረዋል፡፡ ያልተሸከምነው ጉድ ያልተቃወስንበት ነገር አለ ብሎ መናገር ያስቸግራል፡፡ ሰው ሊኖር ከሚገባው ሥርዓትና ልክ እንዴት ዝቅ ባለ ነገር እንደምንመራ በሁላችንም ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ምክንያቱም እንደ ወገናችን ለረሀብ፣ ለስደት፣ ለውርደት፣ ለጦርነት፣ ለመከፋፈል፣ ለድኅነትና ለተስፋቢስነት አገር እንደሌለው በየአገሩ የተበተነ በዓለም ለመኖሩ ርግጠኛ አይደለንም፤ በተጋነነ ሁኔታ አንገት አስደፍቶናል፡፡ ባህላችንና እምነታችን እንዲህ አድርጐ  ቀርጾናል፡፡ ማረሚያም መታረሚያም ወግ የለንም፡፡ ከዚህ ጀርባ ቤተ ክርስቲያናችን ትልቅ ሚና ተጫዋች ናት፡፡ እውነቱን ለመናገር እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አገር በቀል ትልቅ ባለ እድል ቤተ ክርስቲያን በአፍሪካ ክፍለ አህጉር አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቤተ መንግሥት አንጋሽ፣ የሕዝቡ ባህል በያኒ ነበረች፤ ያሻትን ማድረግ ትችል እንደ ነበር በሁሉ ዘንድ ይታወቃል፡፡ ግን ምን ያደርጋል በዘመናት በተሸከመቻቸው ደባትራንና ኢ-ክርስቲያናዊ አስተምህሮ በተላበሱ አይሁዳዊ አይሉት አሕዛባዊ ልማድ፤ ክርስቲያናዊ እሴቶቻችንን ወደታች በመድፈቅ በሐዋርያት ያልተሰማ ያልተነገረ ሲያዩት ክርስቲያናዊ የሚመስል የስሕተት ትምህርት ተቸልሶባታል፡፡
በክርስቶስ ደም የተመሠረተው ውዱ ክርስትና በኢትዮጵያ ምድር እክል ገጥሞታል፡፡ ጣፋጩ ትምህርተ ወንጌል ውሃ ውሃ ብሏል፡፡ መንፈሳዊውም ይሁን ቁሳዊው ነገራችን ረብ የለሽ ሆኗል፡፡ እናቅና ቢሉት በሌላ ልምምድ ተሰናብቶ  ሌላ ዓለም ፈጥሯል፤ አዲሱም ትውልድ ነገሩን ሳይመረምር እራሱን ከዚህ ተራራ ላይ አጐናፍሮ በጨለማ ውስጥ ይገኛል፡፡ ይልቁን በትዕቢት መንፈስ ተረፈ አይሁድ  ኦርቶዶክስን ከፕሮቴስታንትና ከካቶሊክ ማወዳደር ነው ሥራቸው፡፡ ማወዳደሪያውም ውጫዊ በሆነ ባህል፣ ዜማ፣ ሥርዓትና መሰል ነገሮች ነው፡፡ ይህ አገራዊ ሊሆን ከቻለ እንጂ ክርስቶስ የመሠረታትን በዓለም ሁሉ ያለችውን አካሉን አንዲቱን ቤተ ክርስቲያን አይወክልም፡፡ ምክንያቱም አብያተ ክርስቲያናት የየራሳቸው ልምድ አላቸው፡፡ እርሱ ትርጉም የለሽ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን መለኪያዋ መሆን የሚገባው የነቢያትና የሐዋርያት አስተምሮ ነው፡፡ ጤናማ ከሆነች፣ በተንኮል አይኗ ካልታወረ በጥንተ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት እራሷን ብታይም ተመራጭ ሊሆን በቻለ ነበር፡፡ ግን ሳንታደል ቀረና አልሆነም፡፡ ቅሉም አብያተ ክርስቲያናትን ማወዳደር ትርጉም የለሽ ሥራ ነው፡፡ መለኪያው ቃሉ ነውና፡፡
እንደ ሚታወቀው በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያለችው ቤተ ክርስቲያናችን የ2000 ዓመት የዕድሜ ባለጠጋ ናት፡፡ ዕድሜዋ ባልከፋ፤ ተጠንቅቄ ታርሜ እራሴን ከስሁታን አስተማሪዎችና ከባህል ተጽዕኖ ጠብቂያለሁ ለማለት መሞከር ግን ነውርም ትዕቢትም ነው፡፡ ስሕተት አልባ ነኝ፣ ስንዱ እመቤት ነኝ ብሎ መሟገት የንቀት መንፈስ ነው፤ መጨረሻውም በጨለማ መጣል ነው፡፡ ለዚህ የሎዶቂያ ቤተ ክርስቲያን ማሳያ ናት (ራእ. 3÷14-22) እነዚህ ሁሉ ተደማምረው እውነቱን ሲያሳዩን እኛም እንዲህ ለማለት ወደድን፤ በእውነት እግዚአብሔር ከኛ ጋር አለ? ይሁንና አንዳንድ ወፈ ገዝቶች በትክክለኛው አቋም ላይ ነን የሚሉትን አምነን ብንቀበላቸው እየሆነ ያለውና የአገርና የቤተ ክርስቲያን ዘረፋ ብዙ ማሳያዎች ቢሆን አምላክ በሙሉ ልቡ የሚሠራበት ቤተ ክርስቲያንና አገር እንዲህ ነው? ለማለት እንገደዳለን፡፡ የጌዴዎን ጥርጥርም ይህን ያሳየናል፡፡ ብዙ ጊዜ በጣምራ እየቀረበ የሚያስቸግር ጉዳይ አለ ቤተ ክርስቲያን ተሳስታለች ሲባል ሞቼ እገኛለሁ ሊሆን አይችልም የሚሉ አሉ፡፡ ሕዝቡን፣ አስተምህሮውንና የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን መልክ መለየት አስፈላጊ ነው፡፡ በነፍስ ወከፍ ሁሉ ቢጠየቅ ኃጢአተኛ መሆናችንን አንክድም፡፡ ታዲያ ይህን ተከትሎ ለውድቀትና ለመጥፋት የተማርነውና የምናስተምረው ትምህርት መነሻ እንደ ሆነ ማንም መመርመር አይፈልግም፡፡ ሲጀምር ከሐዋርያት ያልተቀበልነው የስህተት አስተምህሮ ገብቶ እውነተኛውን አቆሽሻል ሲባል መቀበል ይከብደዋል፡፡ እውነቱን ለመናገር ብዙ ሰው ክርስትናን ሳይሆን የሚያውቀው ኦርቶዶክስ የሚባለውን ድርጅቱን ነው፤  ስሕተቱ ደግሞ ይህ ነው፡፡ ተከራካሪዎችም ለመከራከር የሚሞክሩት በክርስትና ወግ ሳይሆን በኦርቶዶክስ አስተምህሮ ላይ ቆመው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ትታደስ ሲባል ወደ እውነተኛ የክርስትና አስተምህሮ ትመለስ ማለት ነው፡፡ ሁለቱ መንገዳቸው ተለያይቷል፡፡ ኦርቶዶክሳዊነትን ማምለክ ከእውነተኛው ክርስትና ውጪ ያደርጋል፡፡ በወንጌል ትምህርት እንጂ በራስ ትምህርትና ልማድ ላይ መመሥረት ከእውነት ውጭ ያደርጋል፡፡ የራስን ባህል ይዞ ክርስቲያን መሆን በወንጌል መዶሻነት መስመር ይይዝ ይሆናል፡፡ ቁም ነገር ወደሆነው የአባቶች ትምህርት መግባት ግድ ይለናል፡፡ ክርስትናም በኛ የመዋጮ አስተምህሮ ላይ አይመሠረትም፡፡ በራሱ መገለጥ ላይ ነው የቆመ ነው እንጂ፡፡ ራስ ምታት የሆኑብን እነዚህ ሁሉ ውጥንቅጦች ናቸው፡፡ እግዚአብሔር በሌለበት አለ ብሎ መናገር ስሙን ማጥፋት ነው፡፡ የተሟላ ሥርዐት ስላለ እርሱ አለ ማለት አይደለም፡፡ እርሱ እኛ ለራሳችን አምሮት መወጫ የፈጠርነው ነው፡፡ እንዲህ ከሆነማ የሩቅ ምስራቅ እምነቶች ያማረ ሥርዓት አላቸው፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር በነርሱ ሥርዓት ውስጥ አለ ማለት ነው??? ለቀሪው መልእክት በቀጣይ እንመለሳለን፡፡
    

6 comments:

 1. I never read just like this . It has very strong idea. Thank you and God bless you. Please keep writing.

  ReplyDelete
 2. ayi mechakaw diyabilos lifa biloh

  ReplyDelete
 3. ጽሑፉ ጥሩ አቀራረቡም መልካም ነው። ዳሩ ግን የመሳፍንንቱ ጥቅስ አለኝታ የለሽ የዘመኑን ትውልድ
  ባዶ ያስቀረዋል (ዕንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ እናም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ)ይሆናል።
  God is in charge and All things are under His control. እርሱ ከፍጥረቱ ጋር ቢኖር ነው እንጂ ቢለየውማ ኖሮ እንደሰዶምና ገሞራ አመድ - ትቢያ ሆኖ በቀረ ነበር ይሁንና ይህን የመሰለ ጽሑፍ መንፈሳዊ ወኔ ቀስቃሽ ነውና ቢደጋገም አያስቀይምም።

  ReplyDelete
 4. ጽሑፉ ጥሩ አቀራረቡም መልካም ነው። ዳሩ ግን የመሳፍንንቱ ጥቅስ አለኝታ የለሽ የዘመኑን ትውልድ
  ባዶ ያስቀረዋል (ዕንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ እናም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ)ይሆናል።
  God is in charge and All things are under His control. እርሱ ከፍጥረቱ ጋር ቢኖር ነው እንጂ ቢለየውማ ኖሮ እንደሰዶምና ገሞራ አመድ - ትቢያ ሆኖ በቀረ ነበር ይሁንና ይህን የመሰለ ጽሑፍ መንፈሳዊ ወኔ ቀስቃሽ ነውና ቢደጋገም አያስቀይምም።

  ReplyDelete
 5. ጽሑፉ ጥሩ አቀራረቡም መልካም ነው። ዳሩ ግን የመሳፍንንቱ ጥቅስ፤ አለኝታ የለሽ የዘመኑን ትውልድ
  ባዶ ያስቀረዋል (ዕንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ እናም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ)ይሆናል።
  God is in charge and All things are under His control. እርሱ ከፍጥረቱ ጋር ቢኖር ነው እንጂ ቢለየውማ ኖሮ እንደሰዶምና ገሞራ አመድ - ትቢያ ሆኖ በቀረ ነበር ይሁንና ይህን የመሰለ ጽሑፍ መንፈሳዊ ወኔ ቀስቃሽ ነውና ቢደጋገም አያስቀይምም።

  ReplyDelete
 6. this is the best biblical analysis. The writer deserves appreciation for his excellent work and bold presentation of what was left-confused and never looked by any one here before.

  ReplyDelete