Sunday, November 30, 2014

ማኅበረ ቅዱሳንን ክርስቲያናዊ ብራዘር ሁድ የሚያሰኙ ማስረጃዎችና መመሳሰሎች!ምንጭ፡- ደጀ ብርሃን
ሙስሊም ብራዘር ሁድ ወይም የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር የተባለው ድርጅት 1928 / በግብጽ ተመሠረተ። ከሰማንያ ዐመታት በኋላ በጄኔራል አልሲሲ መንግሥት በአሸባሪነት ተፈርጆ ድምጥማጡ እስኪጠፋ ድረስ 70 ሀገሮች ውስጥ ቅርንጫፎቹን ከፍቶ በዘመናዊና ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች፤ በገበያ ማዕከላት፤ በንግድ ሱቆች፤ በማከፋፈያ ድርጅቶች፤ በሚዲያ ተቋማት ወዘተ የሀብት ማግበስበሻ መንገዶች እየተሳተፈ ክንዱን በማፈርጠም ለእንቅስቃሴው የሚጠቅመውን የገንዘብ ምንጭ ሲፈጥር ቆይቷል። ይህ የግብጹ ሙስሊም ብራዘር ሁድ በዐረብ ሀገራት ውስጥ ተመሳሳይ የሙስሊም ወንድማማች ማኅበራትን በማደራጀትና በማሰልጠን መንግሥታቱን ሲያስጨንቅ የቆየ ሲሆን አሁንም እያስጨነቀ ይገኛል።

የሙስሊም ብራዘር ሁድ ለተባለው ሃይማኖታዊ-ፖለቲካዊ ድርጅት ዋነኛ ተቀባይነት ማግኘት ዋናው ምክንያት የሆነው በእስላሙ ሕብረተሰብ ውስጥ ቶሎ ሰርጾ እንዲገባ የሚያካሂደው ሃይማኖታዊ አስተምህሮቱና  ለዚህ እምነት መክፈል የሚገባውን ዋጋ ሁሉ በመክፈል ከአላህ ዘንድ የሚከፈለውን ምንዳ ለመቀበል ቶሎ መሽቀዳደም ተገቢ መሆኑን አበክሮ በመስበኩ የተነሳ ነው።

1/
የሙስሊም ብራዘር ሁድ መዋቅራዊ እንቅስቃሴ 

 
ሙስሊም ብራዘር ሁድ መዋቅሩ በሀገሪቱ የመንግሥት ሲቪላዊ መዋቅር ደረጃ የተዘረጋ ነው። ይህም ከማዕከላዊ ቢሮው ተነስቶ አባል በሆኑ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ውስጥ በሰንሰለት የተያያዘ ነው። ቤተሰባዊውን የአባልነት ማኅበር «ኡስራ» ይሉታል። አንድ «ኡስራ» አምስት አባላት ሲኖሩት ከአምስት በላይ ከሆነ በሁለተኛ የኡስራ ስያሜ ደረጃ ይዋቀራል። በቤተሰቡ ያሉትን ኡስራዎች የሚመራ ደግሞ የቤተሰቡ አባል የሆነ በእስልምና ሃይማኖቱ የበሰለና የብራዘር ሁድ አስተምህሮት በደንብ የገባውን ሰው የቤተሰቡ ጉባዔ ይመርጠውና «ናቂብ» ተብሎ ይሰየማል። ይህ «ናቂብ» የተባለው ሰው የቤተሰቡ አባላት በእስልምናው ደንብ ዘወትር ስለመንቀሳቀሱ ይቆጣጠረዋል፤ ያስተምረዋል፤ ይነግረዋል። ያልተመለሰውን በማኅበረሰቡ ደረጃ ለተቀመጠውና ከፍ ላለው ሃይማኖታዊ መሪ ያቀርበዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ስለእስልምናው የሚደረግ እርምጃ በመሆኑ በደስታ ከሚቀበል በስተቀር ማንም በተቃውሞ አያንገራግርም፤ ሊያንገራግርም አይችልም። ምክንያቱም ጸረ እስልምና እንደሆኑ ራሳቸውን አስገዝተዋልና። በዚህ ዓይነት አደረጃጀት የሙስሊም ወንድማማቾች ማኅበር ከላይ ወደታችና ከታች ወደላይ የተሳሰረ መዋቅር አለው።

Wednesday, November 26, 2014

የሃና ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረትን የሚሻ ነው

Read in PDF

በቅርቡ የተከሠተው አስደንጋጭም ዘግናኝም ከሰብኣዊ ፍጡር ፈጽሞ የማይጠበቀውና በሀገራችን የሥነምግባር ዝቅጠት የቱን ያህል እየወረደ መምጣቱን የሚያመለክተው የ16 ዓመቷ ተማሪ የሐና ላላንጎ በአምስት ጎረምሶች በተደጋጋሚ መደፈርና ታዳጊዋን ለኅልፈተ ሕይወት ማዳረጉ የማንኛውንም ሰብኣዊ ፍጡር ልብ ያደማና ወደየት እያመራን ነው ያሰኘ ክሥተት ሆኗል፡፡ በታዳጊዋ ላይ የደረሰው ይህ ዘግናኝ ድርጊት መልካም የሚባሉ ኢትዮጵያዊ እሴቶች ምን ያህል እየተሸረሸሩና በሴቶች ላይ እየተፈጸመ  ያለው ጾታዊ ጥቃት ምን ያህል በዓይነትም በመጠንም በአፈጻጸምም እየከፋ መሄዱን አመላካች ነው፡፡ እህታችን ሀና ከትምህርት ቤትዋ ወደ መኖሪያ ቤትዋ ለመሄድ ከተሳፈረችበት ታክሲ ታግታ ህይወትዋ እስኪጠፋ ድረስ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል የተፈጸመባት መኆኑን ማወቅና ማሰብ ለማንም ህሊና ላለው ፍጡር በጣም የሚያስደነግጥ የሚያሳዝንና የሚያሥቆጣም እውነት ነው፡፡
ሀና ለምን ተደፈረች? ምን አይነት ሰብዓዊ ፍጡር ነው የ16 ዓመት ልጅን እንደ እንስሳ ተሰብስቦ የሚደፍረው? ሀገሪቱ የነበሯት እና ህብረተሰቡ በተለምዶ የሚቀበላቸው የሥነ ምግባር ህጎች የት ሄዱ? ሰብዓዊነቱስ እንዴት ጠፋ? የክርስቲያን ደሴት በምትባል ሀገር፣ ክርስቲያን ታዳጊ ወጣት፣ ምናልባትም “ክርስቲያን” ነን በሚሉ ሰዎች እንዴት ልትደፈር ቻለች?  እነዚህ ጥያቄዎች የግድ መልስ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ናቸው። አሁንም ቢሆን ስለ ሀና መደፈር እና ሞት ግልጽ ያለው እውነት አለመውጣቱና የወንጀሉ መፈጸሚያ ቦታ ነው የተባለው ሺሻ ቤት አለመዘጋቱ ከፍተኛ ግርምትን የሚፈጥር ጉዳይ ሆኗል። ሺሻ ቤቱን ለመዝጋትና የሺሻ ቤቱን ባለቤት በወንጀል ለመጠየቅ መንግስት ከዚህ በላይ ምን ይፈልግ ነበር? የሚያሰኝም ሆኗል። ህብረተሰቡም እንዲህ ያለው ወንጀል ፈጽሞ ፈጽሞ እንዳይደገም ከከንፈር መምጠጥ ባለፈ እያደረገ ያለው ነገር ባለመኖሩ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው። 

Wednesday, November 19, 2014

የእግዚአብሔርን ዝማሬዎች ለሌላ የሰጡ “ዘማሪዎች” ምን ይባሉ?

read in PDF

ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሣሣኝ ከሳምንታት በፊት አባ ሰላማ ላይ የወጣውና በዘማሪ ታዴዎስ ዝማሬዎች ላይ የቀረበው መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጎ የተሰጠው እጅግ መልካምና ሚዛናዊ ሒስ ሲሆን እኔም ታዴዎስን ጨምሮ የእግዚአብሔርን ዝማሬዎች ለሌላ በመስጠት እግዚአብሔርን እያሳዘኑ የሚገኙ የጥቂት ዘማሪዎችን ዝማሬዎች ይዘት በመጠኑ ለመዳደስ ነው፡፡ ከእነዚህ ዘማሪዎች መካከል የታዴዎስን የአዜብ ከበደንና የእንግዳወርቅ በቀለን አንዳንድ ዝማሬዎችን እንመልከት፡፡

ዘማሪ ታዴዎስ
ይህ ዘማሪ የአንኮበርን ፖለቲካ ያራምዳሉ ከሚባሉት የማቅ ክንፎች አንዱ እንደሆነ ከሚዘምርላቸው “ቅዱሳን” አንጻር መመልከት ይቻላል፡፡ መዝሙሩ በአብዛኛው በሸዋ የተወለዱና “ቅዱሳን” የተባሉ ሰዎችን የሚያሞጋግስና የሚያመልክ ነው፡፡ ታዴዎስ ከዘመረላቸው የሸዋ “ቅዱሳን” መካከል እጨጌ ተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ አንዱ ናቸው፡፡ ስለእርሳቸው ሲዘመር ምንጭ አድርጎ የተጠቀመው ገድለ ተክለሃይማኖትን ሲሆን ገድሉ ፈጽሞ ተኣማኒ ያልሆነውንና እንደ ዮሐንስ አድማሱ ያሉ ሊቃውንት በግጥማቸው “ሰይጣን ሠለጠነ” ብለው የተሳለቁበትን፣ ብዙዎችም ተረት ተረት የሚሉትን የፈጠራ ድርሰት ነው፡፡ የዮሐንስ አድማሱ ግጥም እነሆ!
ሰይጣን ሰለጠን፣
ቀንዶቹን ነቃቅሎ
ጭራውንም ቆርጦ
ከሰው ልጆች ጋር አንድነት ተቀምጦ
ሊኖር ነው ጨምቶ
ከሰው ልጆች ጋር ሊጋባ ተጫጭቶ።
ሰይጣን ሰለጠነ፤
ዘመናዊ ሆነ
ፊደል ቆጠረና ዳዊትም ደገመ
በስመ አብ ብሎ ውዳሴ ማርያምን
አንቀጸ ብርሃን መልካመልኩን ሁሉ
አጠና ፈጠመ።
ከዚህም በኋላ ጾም ጸሎት ጀመረ
በመጨረሻውም አቡን ተክሌ አጥምቀው
ክርስትና አነሱት።
ግና ተቸገረ
እንዲያው በየዕለቱ
ጨርሶ አላወቀም ለማን እንደሆነ ጾምና ጸሎቱ
ቢጨንቀው ጊዜና ቆይቶ ሰንብቶ
ክርስቲያን የሆነ አንድ ሰው አግኝቶ
ተወዳጀውና ብሶቱን ነገረው ሁሉንም ዘርዝሮ፣
በጣፈጠ ቋንቋ በውነት አሳምሮ።
አትቸገርአለው ክርስቲያን ወዳጁ አጽንናው መልሶ
ሰይጣኑ ካሰበው አለመጠን ብሶ፣
ይህስ ቀላል ነገር ችግርም የለው
እንደኛው ክርስቲያን ሆንክ ማለት ነው።

Monday, November 17, 2014

ግብረ ሰዶማዊነትና የእኛ ዘመን አገልጋዮች

 ምንጭ፡-ደጀ ብርሃን
(ግብረ ሰዶማዊነት በአስደንጋጭ ሁኔታ በሀገራችን እየተስፋፋ ይገኛል። በኅጻናት መብት ረገጣ ዙሪያ የሚሰሩ ሰዎች እንደሚናገሩት በአዲስ አበባ ከተማ ወደ ሆስፒታል ተደፍረው ከሚመጡ ኅጻናት መካከል የወንዱ ቁጥር ከሴቶቹ እኩል እየሆነ ነው። ይህ ወሬ ለክርስቲያኖች ሩቅ ነው ብለን ስናስብ የነበረ ቢሆንም በቤተክርስቲያን በግልጽ የሚሰማ ጉዳይ ሆኗል። እነ አባ እገሌ እነ ዲያቆን እገሌ እየተባለም የሚጠሩ ሰዎችን መስማት እንግዳ መሆኑ አብቅቷል። ይህ በሀገር ውስጥም በውጭም ባለችው ቤተክርስቲያን እኩል የሚሰማ እና የሚያስደነግጥ ጉዳይ እየሆነ ነው። በፕሮቴስታንቱም አለም ቢሆን ያለው ችግር ተመሳሳይ ነው።
በቤተክርስቲያናችን እንዲህ ያለ ችግር መስማታችን የበለጠ ልባችንን ያደማዋል። እንደዚህ አይነቱ ወሬ የመጨረሻው ዘመን ላይ ለመሆናችን ትክክለኛው ማሳያ ነው። በአሜሪካ እና በአውሮፓ መብት ሆኖ የጸደቀው እና በአደባባይ እስከ ማጋባት የደረሰው ግብረ ሰዶማዊነትን በመቃወም ቤተክርስቲያን የበኩልዋን ድርሻ ስላልተወጣች ነው። በኛም ሀገር ዝም ከተባለ እና ስለ እነ እገሌ እንዴት ይወራል? በማለት በዝምታ የሚታለፍ ከሆነ የሚያስከትለው ችግር እየከፋ ይመጣል። ለዛሬው በደጀ ብርሃን ብሎግ ላይ የወጣውን ይህንን ጽሁፍ እንድታነቡት እንጋብዛለን።)
    ( ከአቤኔዘር ተክሉ )
       
 ስለግብረ ሰዶማዊነት በሁለት የተለያዩ ክፍሎች መጻፌና በሁለቱ ክፍሎችም ለጊዜው የነበረኝን ሃሳብ ማጠቃለሌን አልዘነጋውም፡፡ ነገር ግን አሁንም ግብረ ሰዶማዊነት የቤተ ክርስቲያንን ቅድስና ከማርከስ፤ ምድራችንን ለከፋ ጉስቁልናና ርኩሰት አሳልፎ ከመስጠት ያላቆመ ፍጹም ወደመስፋፋት የሄደ ክፉ ርኩሰት ነውና ዳግም ይህንን ርዕስ ማንሳት አስፈልጎኛል፡፡ ለዚህ እውነታ ብዙ የቅርብ ጊዜ ማሳያ ብቻ ማንሳቱ በቂ ይመስለኛል፡፡
    ድርጊቱ የተፈጸመው በምስራቁ የሃገራችን ክፍል ነው፡፡ የሠላሳ ሁለት አመት አጐት የአራት አመት የወንድም ልጁን በእረኝነት ሥፍራ በመሄድ ጫት እንዲቅም ያግባባዋል፡፡ ህጻኑ እንቢ ቢልም ያስገድደዋል፡፡ ጫት እንዲቅም ካስገደደው በኋላ ልጁ ራሱን መቆጣጠር ሲያቅተው ልጁን የግብረ ሰዶም ጥቃት ይፈጽምበታል፡፡ የልጁ የሰገራ ማውጫ ሙሉ ለሙሉ ይቀዳዳል፡፡ ከሆዱ የወጣው የውስጠኛው የሰገራው ክፍል ሙሉ ለሙሉ የልጁን ጠረን ይለውጠዋል፡፡ ልጁ ፍጹም ራሱን ስቶ ሲወድቅ ከወደቀበት ቦታ ተሸክሞት ከወላጆቹ ጓሮ አምጥቶ ጥሎት ይሰወራል፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የልጁ ህይወት ያልፋል፡፡

Thursday, November 13, 2014

ቤተ ሙስና የሆነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአቡነ ቀሌምንጦስ ይለወጥ ይሆን? ወይስ…

Read in PDF

በአገራችን ተወዳዳሪ ያልተገኘለትና ጠያቂም ተጠያቂም የሌለበት ቤተ ሙስና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በዚያ፣ ለቤተክርስቲያን እድገት ሳይሆን በቤተክህነት ትምህርት ብዙ ደክመው ሥራ ፍለጋ ደጅ ከሚጠኑና በልዩ ልዩ ምክንያት (ደኅና አድርገው ለመብላትም ጭምር ሊሆን ይችላል ምክንያቱ) ወደተሻለ ደብር መዛወር ከሚፈልጉ ሥራ ፈላጊዎች ወንድሞቻቸው ላይ ጉቦ በመቀበል ለመበልጸግ ተግተው የሚሠሩ ጥቂት ስግብግብ ሹማምንት አሉ፡፡ 
ሥራ ፍለጋ ደጅ በመጥናት ላይ ያሉና በር ከፍቶ የሚያስገባቸው እንኳን ስላላገኙ በሀገረ ስብከቱ በር ላይ በሥራ ቀናት የሚኮለኮሉ፣ በቤተክህነት ትምህርት ብዙ ደክመው ቤተክህነቱ ያልተቀበላቸው ተምረው እንዳልተማሩ የሆኑ ሊቃውንት ጊዜ በሰጣቸው ጨዋዎች እየተጉላሉ በዚያ አሉ፡፡ በችሎታቸው ሳይሆን በጉቦ ጥሩ ገቢ ባለበት ደብር ውስጥ ዳጎስ ያለውን ገቢ በሚያስገባ ጥሩ የሥራ መደብ ለመመደብ በበሩ ሳይሆን በጓሮ በር የሚገቡ ወደፊት ለመዝረፍ ዛሬ ጉቦ የሚሰጡ ከንቱዎችም በዚያ አሉ፡፡ ደግሞም እንደ ሎጥ በዐመፀኞች መካከል ጻድቅ ነፍሳቸውን አስጨንቀው የሚኖሩ እንደ ሀገረ ስብከቱ ዋና ጸሐፊ እንደ ቀሲስ ኃይሉ ያሉ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረባቸው ጥቂት ታማኞችም በዚያ አሉ፡፡

Tuesday, November 11, 2014

ቅዱስ ሲኖዶስ በደቡብ አፍሪካ ለምትገኘው የኢትዮጵያ ቤ/ን ትኩረት ሊሰጥ ይገባዋል

Read in PDF

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ*
የኢትዮጵያ ቤ/ን ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት ቤ/ን መሆኗ ይታወቃል፡፡ የክርስትና ሃይማኖት በእስራኤልና በአካባቢው ገና ብዙም ባልተስፋፋበት በ፩ኛው መቶ ክ/ዘመን በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማካኝነት ወንጌልን የተቀበለችው የኢትዮጵያ ቤ/ን በዓለም አቀፍ የክርስትና መድረክ ያላት ስፍራ ልዩ ነው፡፡ የክርስትናን ሃይማኖትን ያጠኑ የታሪክና የሥነ መለኮት ምሁራን የዳጎሱ ድርሳናትም የኢትዮጵያ ቤ/ን በአኅጉረ አፍሪካ የክርስትና እምነት መስፋፋት ሂደት ውስጥ ቀደምትና ልዩ ታሪክ ያላት ሐዋርያዊትና ጥንታዊት ቤ/ን መሆኗንም አስረግጠው ጽፈዋል፡፡
በአፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በካረቢያንና በጃሜይካ በሚገኙ ሕዝቦች ዘንድ የነጻነት ተምሳሌትና የተስፋ ምድር ተደርጋ የምትወሰደው የኢትዮጵያ ቤ/ን በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ አሁንም ድረስ ልዩ ክብርና ስፍራ ያላት ናት፡፡ በወንጌል ስብከት ስም የምዕራባውያን ቅኝ ገዢዎች የባህል ወረራ ያልነካት፣ ለበርካታ ዘመናት ብሉይን ከሐዲስ አስማምታ፣ የክርስትና ሃይማኖትን አስተምህሮ፣ መንፈሳዊ ሥርዓት፣ ባህልና ትውፊት ጠብቃ የቆየች፣ ሐዋርያዊት ትክክለኛ፣ ቀደምት አፍሪካዊት እናት ቤ/ን (Genuine, Independent African Mother Church) በሚል ክብር የሚጠሯት፣ የሚያሞኳሽዋት ናት፡፡
ይህችውን ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት የሆነች የምዕራብ ባህል ያልበረዛት፣ አፍሪካዊት እናት ቤ/ን በሚል ቅፅል የምትሞካሸውን የኢትዮጵያ ቤ/ን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ታሪኳን ጠለቅ ብለን ስናጠና፣ ስንፈትሽ ግን ቤተ ክርስቲያናችን የታሪኳንና የዕድሜዋን ያህል በተስፋ፣ በጉጉትና በናፍቆት ለሚጠብቋት አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦች ወንጌልን በመስበክ ረገድ ሐዋርያዊና መንፈሳዊ ግዴታዋን በሚገባ ተወጥታለች ብለን ለማለት የሚያስደፍሩን የታሪክ ሰነዶች እምብዛም አይገኙም፡፡
እንደውም በወንጌል ስብከት ስም በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢ ኃይሎች በአፍሪካውያን ላይ ያደረሱትን ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ሰብአዊ ቀውስን ያጠኑ አንዳንድ አፍሪካ አሜሪካውያን ምሁራንና ሊቃውንት ደፈር ብለው፡- ‹‹የኢትዮጵያ ቤ/ን ከሁሉ የዓለም ሕዝቦች አስቀድማ የተቀበለችውን የወንጌል አደራ ለአፍሪካውያን ባለመስጠቷ በክርስትና ስብከት ስም ለመጡ አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች በር በመክፈት ተባብራለች፡፡›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

Sunday, November 9, 2014

ስደተኛው ቅዱስ ሲኖዶስ አርባ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን በኮለምበስ ኦሓዮ አካሄደ።

Read in PDF

በጥሩ መንፈስ የተጠናቀቀ ነው የተባለው ጉባኤ በርካታ ካህናት እና ምእመናን የተገኙበት ጉባኤ ነበር ይባል እንጂ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች አነጋጋሪ ነበሩ።
  የመጀመሪያው የቅዱስ ፓትርያርኩ 25ኛ ዓመት በዓል አከባርን የተመለከተ ሲሆን በጥቅምት ውስጥ ሊከናወን ቀጠሮ ተይዞበት እያለ ይህን ጉዳይ እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች ምንም እንቅሥቃሴ ሳያደርጉ ቆይተው በመጨረሻ ፕሮግራሙ ተሰርዟል ብለው አስታወቀዋል። ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ሲጠየቁ የተድበሰበሰና ተንኮልን ያዘለ ሆኖ ተገኝቷል። ሲኖዶሱ ውስጥ የጠራ አላማ የሌላቸው ሰዎች አሁንም እየተሽሎከለኩ መሆኑን ግንዝቤ ተይዞበታል። ይህ ጉዳይ ብዙ ሰዎችን አሳዝኗል።

Thursday, November 6, 2014

ማኅበረ ቅዱሳንና ተላላኪዎቹ ጳጳሳት የቤተክርስቲያንን ችግር ሆነው የሚቀጥሉት እስከ መቼ ነው?

Read in PDF

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ መታመሷን ቀጥላለች፡፡ የሲኖዶስ ስብሰባ በመጣ ቁጥር ማኅበረ ቅዱሳን አጀንዳ ሆኖ መቅረቡ በጣም አነጋጋሪ ነው፡፡ ልዩ ልዩ ውሳኔዎች ቢወሰኑም ከቤተክርስቲያን ጥቅም አንጻር ሳይሆን የማኅበሩን ጥቅም የሚነካ መስሎ ከታየ በልዩ ልዩ መልክ ተፈጻሚ እንዳይሆን እጀ ሰፊውና እጀ ረጅሙ ማኅበረ ቅዱሳን ልዩ ልዩ የማዳከም ሥራዎችን በመሥራት ውሳኔዎቹ የወረቀት ላይ ነብር ሆነው ብቻ እንዲቀመጡ ያደርጋል፡፡ ቤተክርስቲያን በተለያዩ ጊዜዎች በማኅበረ ላይ የወሰነቻቸው ውሳኔዎችም ሳይፈጸሙ እንደገና ሌሎች ውሳኔዎች እየተላለፉ ከ2007ቱ የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ ደርሰናል፡፡ 
አሁንም የቀድሞው የማኅበሩ ተጠሪነት ጉዳይ ላይ የተላለፈው የሲኖዶስ ውሳኔ ተሽሮ ወደቀድሞው የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እንዲመለስና ተጠሪነቱ ለእርሱ እንዲሆን ወስኗል፡፡ ሲኖዶሱ ይህን ውሳኔ ሲወስን ምክንያቱ ምን ይሆን? ቀድሞ ከዚያ እንዲወጣና ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ቤተክህነት እንዲሆን ሲወስን ማኅበረ ቅዱሳን ትልቅ ማኅበር ስለሆነ በአንድ መምሪያ ሥር መሆኑ አይመጥነውም ተብሎ ነበር፡፡ አሁን ታዲያ ወደቀድሞው መምሪያ ሲወርድ ምን ምክንያት ተሰጥቶ ይሆን? ትልቅ የተባለው ማቅ ትንሽ ሆኖ ስለተገኘ ይሆን በመምሪያ ሥር ነው መሆን ያለበት ተብሎ እንደ ገና ወደ ቀድሞው ቦታው የተመለሰው? ወይስ ሌላ ምክንያት ይቀርብ ይሆን? ይህ ሲኖዶሱን የሕጻናተ አእምሮ ስብስብ የሚያሰኝና የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችም ክብደት የሌላቸው ተራና ምክንያታዊ ያልሆኑ እንደሚያደርጋቸው ምንም አጠራጣሪ አይደለም፡፡ 

Tuesday, November 4, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን ለአቡነ ቀሌምንጦስ መልካም የሥራ ዘመን የተመኘው ለምን ይሆን?

Read in PDF

በዘንድሮው የጥቅምት ሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ከተወሰኑት ውሳኔዎች አንዱ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እንዲሆኑ መወሰኑ ነው፡፡ ይህን ተከትሎ የማኅበረ ቅዱሳን ብሎግ የሆነችው ሐራ ከዚህ ቀደም «ብአዴን እና ደህንነቱ» እያለች ስማቸውን እንዳላጠፋች ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስን እንኳን ደስ አለዎት ለማለት የቀደማት የለም፡፡ ይህን ያደረገችው ስለቀድሞ ዘለፋዋ ይቅርታ ጠይቃ ሳይሆን አይኗን በጨው አጥባ ነው “ለብፁዕነታቸው ውጤታማ የሥራ ዘመን እንመኝላቸዋለን፡፡” ስትል ከሰሞኑ የጻፈችው፡፡ ከዚህ ቀደም January 21, 2013 ባወጣነው ዘገባ እንዲህ ብለን ነበር፣ ማኅበረ ቅዱሳን “የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀጳጳስ በሆኑት በብፁእ አቡነ ቀሌምንጦስ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ የከፈተ ሲሆን፣ በብሎጎቹ ላይ «ብአዴን እና ደህንነቱ» እያለ ስማቸውን በማጥፋቱ ብፁእነታቸው ማቅን «እኛ እኮ ከእኛ ጋር ተባብሮ ለቤተ ክርስቲያን ይሰራል ብለን ነው አርፎ የማይቀመጥ ከሆነ ሁለት መስመር ደብዳቤ ጽፈን እናዘጋዋለን» ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ማቅ የመምሪያው ሃላፊ ከነበሩት ከአባ ሠረቀ ብርሃን ጋር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ ገብቶ በነበረ ጊዜ አቡነ ቀሌምንጦስ ከማቅ ጎን ቆመው ለማቅ ከፍተኛ ድጋፍ የሰጡ ሲሆን ያኔ ማቅን በሚገባ ባለማወቅና ለቤተ ክርስቲያን የቆመ መስሏቸው ያን ድጋፍ እንዳደረጉ እየተናገሩ መሆኑን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡ አባ ሠረቀ ብርሃንን «እኛ እኮ የእርስዎን ትግል ሳናውቀው ነው ከማቅ ጎን የቆምነው» ብለው ባለፈው በሆነው ነገር ሁሉ መጸጸታቸውን ምንጮች ይናገራሉ፡፡”

Sunday, November 2, 2014

ማኅበረ ቅዱሳን ሶስተኛው ሲኖዶስ

Read in PDF

ቅዱስ ፓትርያርኩ በ33ተኛው አጠቃላይ የሰበካ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ማኅበረ ቅዱሳን ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ተገንጥሎ የራሱን ቤተክርስቲያን ለመክፈት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጠዋል። ቅዱስነታቸው መረጃ አለኝ በማለት የገለጡት እውነት ተግባራዊ ከሆነ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሦስት ሲኖዶሶች ሊኖሯት ነው ማለት ነው። ይህ ደግሞ የቤተክርስቲያኒቱ ህጋዊ ተጠሪ እኔ ነኝ እያሉ የሚወዛገቡትን የአገር ቤቱንና የውጪውን ሲኖዶስ የሚያስቆጣ ይሆናል። በእኛ እምነት ግን ማኅበሩ አሁንም ቢሆን ሦስተኛ ሲኖዶስ ነው የሚል አቋም ነው ያለን። ይህን በጥቂት ማስረጃዎች እናሳይ

አንዲት ቤተክርስቲያን ቤተክርስቲያን ከሚያሰኝዋት ነገሮች አንዱ አስራት በኩራት መቀበልዋ ነው። ማቅ ይኸው ድፍን ሃያ ዓመት አስራትና በኩራት እየተቀበለች ኖራለች። እንዲሁም ተሳስተሻል የሚሉዋትን ሁሉ ለራስዋ ባዘጋጀችው ልዩ ዶክትሪን አማካይነት “ተሀድሶ መናፍቅ” እያለች ነው። የተለየ የአባላት ምዝገባ የተለየ በአባልነት የመጠመቂያ ትምህርትም አላት። ቤተክርስቲያኒቱንና ጳጳሳቱን የምትፈልጋቸው የምታከብራቸው የምታሞግሳቸው እና የምትባርካቸው ከእርስዋ ጋር እስከተሞዳሞዱ ድረስ ብቻ ነው።