Tuesday, November 11, 2014

ቅዱስ ሲኖዶስ በደቡብ አፍሪካ ለምትገኘው የኢትዮጵያ ቤ/ን ትኩረት ሊሰጥ ይገባዋል

Read in PDF

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ*
የኢትዮጵያ ቤ/ን ጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት ቤ/ን መሆኗ ይታወቃል፡፡ የክርስትና ሃይማኖት በእስራኤልና በአካባቢው ገና ብዙም ባልተስፋፋበት በ፩ኛው መቶ ክ/ዘመን በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማካኝነት ወንጌልን የተቀበለችው የኢትዮጵያ ቤ/ን በዓለም አቀፍ የክርስትና መድረክ ያላት ስፍራ ልዩ ነው፡፡ የክርስትናን ሃይማኖትን ያጠኑ የታሪክና የሥነ መለኮት ምሁራን የዳጎሱ ድርሳናትም የኢትዮጵያ ቤ/ን በአኅጉረ አፍሪካ የክርስትና እምነት መስፋፋት ሂደት ውስጥ ቀደምትና ልዩ ታሪክ ያላት ሐዋርያዊትና ጥንታዊት ቤ/ን መሆኗንም አስረግጠው ጽፈዋል፡፡
በአፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በካረቢያንና በጃሜይካ በሚገኙ ሕዝቦች ዘንድ የነጻነት ተምሳሌትና የተስፋ ምድር ተደርጋ የምትወሰደው የኢትዮጵያ ቤ/ን በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ አሁንም ድረስ ልዩ ክብርና ስፍራ ያላት ናት፡፡ በወንጌል ስብከት ስም የምዕራባውያን ቅኝ ገዢዎች የባህል ወረራ ያልነካት፣ ለበርካታ ዘመናት ብሉይን ከሐዲስ አስማምታ፣ የክርስትና ሃይማኖትን አስተምህሮ፣ መንፈሳዊ ሥርዓት፣ ባህልና ትውፊት ጠብቃ የቆየች፣ ሐዋርያዊት ትክክለኛ፣ ቀደምት አፍሪካዊት እናት ቤ/ን (Genuine, Independent African Mother Church) በሚል ክብር የሚጠሯት፣ የሚያሞኳሽዋት ናት፡፡
ይህችውን ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት የሆነች የምዕራብ ባህል ያልበረዛት፣ አፍሪካዊት እናት ቤ/ን በሚል ቅፅል የምትሞካሸውን የኢትዮጵያ ቤ/ን ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ተልዕኮ ታሪኳን ጠለቅ ብለን ስናጠና፣ ስንፈትሽ ግን ቤተ ክርስቲያናችን የታሪኳንና የዕድሜዋን ያህል በተስፋ፣ በጉጉትና በናፍቆት ለሚጠብቋት አፍሪካውያንና ጥቁር ሕዝቦች ወንጌልን በመስበክ ረገድ ሐዋርያዊና መንፈሳዊ ግዴታዋን በሚገባ ተወጥታለች ብለን ለማለት የሚያስደፍሩን የታሪክ ሰነዶች እምብዛም አይገኙም፡፡
እንደውም በወንጌል ስብከት ስም በአውሮፓውያን ቅኝ ገዢ ኃይሎች በአፍሪካውያን ላይ ያደረሱትን ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ሰብአዊ ቀውስን ያጠኑ አንዳንድ አፍሪካ አሜሪካውያን ምሁራንና ሊቃውንት ደፈር ብለው፡- ‹‹የኢትዮጵያ ቤ/ን ከሁሉ የዓለም ሕዝቦች አስቀድማ የተቀበለችውን የወንጌል አደራ ለአፍሪካውያን ባለመስጠቷ በክርስትና ስብከት ስም ለመጡ አውሮፓውያን ቅኝ ገዢዎች በር በመክፈት ተባብራለች፡፡›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡

ይህ የአፍሪካውያንና የአፍሪካ አሜሪካውያን ምሁራን ሙግት የተጋነነ ቢመስልም አንዳንች እውነታ የለውም ለማለት ግን የምንችል አይመስለኝም፡፡ በእርግጥ ከመጀመሪያው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ እስከ መካከለኛው መቶ ክ/ዘመን ድረስ ያለውን የኢትዮጵያ ቤ/ን ታሪክን በጨረፍታ ስንመለከት ከዚህ ምሁራዊ ሙግት ውጭ ነው፡፡ ወደ ዝርዝር አሳቦችና ታሪካዊ ማስረጃዎች ውስጥ ለመግባት በዚህ ጽሑፌ ላነሳው ካሰብኩት ዐቢይ ርእሰ ጉዳይ ብዙም እንዳይርቀኝ ስል በዚሁ ልግታው፡፡
ግና እዚሁ አሳቤ ላይ አንድ ቁም ነገር ግን አስረግጬ ላልፍ እፈልጋለኹ፡፡ ቤተ ክርስትያናችን በዓለም አቀፍ መድረክ ካላት ክብርና ረጅም ታሪክ አንፃር ልንቆጭበት የሚገባ ነገር አለ፡፡ ይኸውም ለሺሕ ዘመናት በሕገ ልቦና፣ በሕገ ኦሪት፣ ከዛም በሕግ ወንጌል ጸንታ የቆየች፣ የራሷ የኾነ ቋንቋና ፊደል ያላት፣ ዜማን ከእነምልክቱ ለዓለም ያስተዋወቀች፣ ሰማያዊ የኾነ የአምልኮ ሥርዓት፣ ጠንካራ መንፈሳዊ ባህልና ትውፊት ያላት ቤ/ን፤ ግን እንደው ለመሆኑ እነዚህ መንፈሳዊ ሀብቶቿና ቅርሶቿ በየትኞቹ አፍሪካ አገራትና ሕዝቦች መካከል መንፈሳዊ አሻራውን ትቷል ብለን ብንጠይቅ ምላሹ አሳፋሪ ነው የሚሆነው፡፡
እናም የአሁኑ የቤተ ክርስቲያናችን ወጣት ትውልድ፣ መንፈሳዊ መሪዎችና አገልጋዮች ለዚህ የዘመናት የአፍሪካውያን ጥያቄ፣ ክስና ሙግት መልስ መስጠት ግዴታችንም ኃላፊነታችንም መሆን ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይህን ተጠየቅ መሠረት በማድረግም በዚህ አጭር ጹሑፌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን ሐዋርያዊ ተልዕኮና በደቡብ አፍሪካ ባለችው የኢትዮጵያ ቤ/ን ዙሪያ ከታሪካችንና ቤተ ክርስቲያናችን ካለችበት ነባራዊው ኹኔታ በመነሳት ጥቂት ነገሮችን ለማንሳት ወደድኹ፡፡
በመግቢያዬ እንደጠቀስኩት የኢትዮጵያ ቤ/ን በዓለም አቀፉ የክርስትና ሃይማኖት መድረክ ካላት የረጅም ዘመን ታሪክና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋ የተነሣ በተለይ በአፍሪካውያን ሕዝቦች መካከል የነጻነት ተምሳሌት ተደርጋ የምትቆጠር ጥንታዊትና ቀደምት አፍሪካዊት እናት ቤ/ን ናት፡፡ ከዚህ ታሪካዊ ሐቅ ጋር ተያይዞም የኢትዮጵያ ቤ/ን በደቡብ አፍሪካ ለየት ያለ ጅማሬና ታሪክ ያላት መንፈሳዊ ተቋም ናት፡፡
ከአፍሪካውያን ጥቁር ሕዝቦች የፀረ-ባርነት፣ የቅኝ ግዛትና የፀረ-አፓርታይድ መራራ ትግል ጋር በእጅጉ ተቆራኝታ የምትነሣው የኢትዮጵያ ቤ/ን በደቡብ አፍሪካውያን ጥቁር ሕዝቦችና የነጻነት ፋኖዎች በኾኑት በኔልሰን ማንዴላና የትግል አጋሮቻቸው ልብ ውስጥ ልዩ ስፍራ፣ ልዩ ክብር ያላት መንፈሳዊ ተቋማት ናት፡፡ ይህን የኢትዮጵያ ቤ/ን በደቡብ አፍሪካ በአጠቃላም በአፍሪካና በመላው በጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህል፣ ማንነትና ክብር ውስጥ ያላትን ጉልህ ድርሻ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዛዳንት የኾኑት ታምቦ እምቤኪ እንዲህ ገልጸውታል፡-
The Ethiopian Church would serve as the authentic African church a repository of the aspirations of all Africans for freedom and respect for their cultures, their identity and their dignity. It was therefore not by accident that the independent African churches, called themselves the Ethiopian Church.
ይህ ቤተ ክርስቲያናችን በደቡብ አፍሪካውያን፣ በአፍሪካ አሜሪካውያንና በአጠቃላይ በጥቁር ሕዝቦችና ነጻነታቸውን በሚያፈቅሩ የሰው ልጆች መካከል የነበራትና፣ ያላት የከበረ ታሪክ ለአገራችን ኢትዮጵያም ልዩ ክብርን እንድትጎናጸፍ አድርጓታል፡፡ እናም የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮ፣ መንፈሳዊ ሀብቶቿና ቅርሶቿ ለሕዝቦች የእርስ በርስ ግንኙነት፣ የአገራት የባህል ልውውጥ፣ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የራሱ የኾነ ትልቅ ድርሻን ማበርከቱ ግልጽ ነው፡፡
በደቡብ አፍሪካ የምትገኘው የኢትዮጵያ ቤ/ን ታሪካዊ መነሻ በ፲፱ኛው መቶ ክ/ዘመን መጨረሻ ገደማ የተቀጣጠለው ፀረ-ባርነትና የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ በዚሁ ክ/ዘመን በ፲፰፻፹፰ ዓ.ም ዓለምን ሁሉ ያስደመመውና ከአድማስ አድማስ የናኘው የዐድዋ ድል፣ በቅኝ ግዛት ሥር ለሚማቅቁ ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል ትልቅ መነሳሳትንና ወኔን ፈጥሮላቸው ነበር፡፡
የዐድዋው ግንባር ዐፄ ምኒልክ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ሣይሉና ሳይለዩ ኹሉም ኢትዮጵያዊ ወገናቸውንና ነጻነቱን የሚያፈቅርና የሚያከብር ታላቅ ሕዝባቸውን ያስከተቱበት ዘመቻ ነበር፡፡ በዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ መነኮሳትና ታቦታቱም ጭምር ሳይቀር በተሳተፉበት ዘመቻ የተገኘው የዐድዋ ድል መላውን አውሮፓን በኸፍረት አንገት ያስደፋ፣ አሳፋሪ ሽንፈት ነበር፡፡
በተጨማሪም የዐድዋው ድል በግዙፉ ፍልስጤማዊ ጦረኛ በጎልያድ የተመሰለችው የሮማ ካቶሊካዊት ቤ/ን በእረኛውና በብላቴናው ዳዊት በተመሰለችው የኢትዮጵያ ቤ/ን ወንጭፍ ተመትታ የተሸነፈችበት ድል ተደርጎ ነበር የተቆጠረው፡፡ ይህች ነጻነታቸውን ከሚያፈቅሩና ለሰው ልጆች ኹሉ ከፈጣሪ የተሰጣቸውን ፍጹም ነጻነት የምታከብርና የምትጠብቅ የኢትዮጵያ ቤ/ን ለደቡብ አፍሪካ የነጻነት ፋኖዎች ወኔ፣ የክብርና የኩራት ምንጭ ኾና አግልግላለች፡፡
የኢትዮጵያ ቤ/ን በደቡብ አፍሪካ ምድር ዕውን የመኾን የታሪክ ውሉም ከዚሁ ቤተ ክርስቲያናችን በአገራችን ሕዝቦች የነጻት ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ ከነበራት ጉልህና ስፍራና ታሪካዊ ድርሻ የሚመዘዝ ነው፡፡
በደቡብ አፍሪካ የዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት መገርሠሥ በኋላ በአሜሪካና በካረቢያን ሊቀ ጳጳስ የነበሩት ነፍሰ ኄር ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በደቡብ አፍሪካ ኦርቶዶክሳዊት ቤ/ን እና በኢትዮጵያ እናት ቤ/ን ግንኙነት መካከል ታሪካዊ ሊባል የሚችል የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠ፡፡ ከዛም በመቀጠል ነፍሰ ኄር ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስና ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አባቶች በ፲፱፻፺ዎቹ መጨረሻ ገደማ በደቡብ አፍሪካ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በኹለቱ አገራት በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የእናትና ልጅ ግንኙነትን ዕውን አደረገው፡፡
በወቅቱም አቡነ ጳውሎስ በደቡብ አፍሪካዊቷ የወደብ ከተማ በፖርት ኤልዛቤት በሚገኘው የደቡብ አፍሪካውያኑ ቅዱስ መስቀል ኦርቶዶክስ ቤ/ን ተገኝተው ቀድሰው ካቆረቡ በኋላ ባስተላለፉት መንፈሳዊ መልእክታቸውና የወንጌል ስብከታቸውም፡-
‹‹… የአፓርታይድ ዘረኛ መንግሥት ቅዱስ ወንጌል በአንድ መንፈስ ያስተሳሰራቸው ሕዝቦች እንዳይገናኙ የጋረደው ፅልመታዊ መጋረጃ ተነሥቷል፣ ከአሁን ወዲያ ቤተ ክርስቲያናችን ቤተ ክርስቲያናችሁ፣ ሕዝባችንም ሕዝባችሁ፣ ታሪካችንም ታሪካችሁ ነው …!›› በማለት ነበር የወንጌል ቃል እውነት ያስተሳሰራቸውን የኹለቱ አብያተ ክርስቲያናትን የእናትና ልጅ ግንኙነትን ያበሰሩት፡፡
አቡነ ጳውሎስ በተጨማሪም ከደቡብ አፍሪካውያኑ መካከል በርካታ ካህናትና ዲያቆናት በመሾም በኹለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የተጀመረው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ትልቅ ሚናን ተጫውተዋል፡፡ ከእነዚህ ካህናት መካከልም በአቡነ ጳውሎስ ግብዣ በኢትዮጵያ ተገኝተው የከተራንና የጥምቀትን በዓል አብረውን እንዲያከብሩ፣ በአገሪቱ ታላቅ ገደማትና አድባራት በመጓዝም የቤተ ክርስቲያናችንን ጥንታዊ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህልና ትውፊት በማየት ለሕዝባቸው በሚገባ እንዲያስተምሩ ዕድል አመቻችተውላቸውም ነበር፡፡ በተጨማሪም ሦስት የቤ/ቱ መምህራን በደቡብ አፍሪካ የስድስት ወራት ቆይታ በማድረግ ለደቡብ አፍሪካውያኑ ኦርቶዶክሳውያን ሥልጠናም ሰጥተው ነበር፡፡
 በመቀጠልም የዛን ጊዜው ቆሞስ አባ ገብርኤል የአሁኑ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ፣ የመላው አፍሪካ ሊቀ ጳጳስና የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ምክትል ፕሬዝዳንት ወደ ደቡብ አፍሪካ ተሹመው መምጣት በደቡብ አፍሪካ ምድር፣ የአገር ቤቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እናት ቤ/ን ህልውና እና ሐዋርያ ተልዕኮዋን ዕውን እንዲኾን አደረገው፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያኒቷ ምስረታና ሐዋርያዊ አገልግሎትም ለኦርቶዶክሳውያን ኢትዮጵያውያንና ደቡብ አፍሪካውያን ታላቅ የምስራች ነበር፡፡
በ፲፱፻፺ዎቹ ጆሐንስበርግ ከተማ የተጀመረው የቤተ ክርስቲያናችን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ተስፋፍቶ ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ምድር አምስት አብያተ ክርስቲያናት፣ በርካታ ጉባኤያትና እንዲሁም በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ከኢየሩሳሌም ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ውጭ ኹሉተኛ የኾነውን ገዳም በደቡብ አፍሪካዊቷ የሊጅስትሌቲቭ ከተማ በብሉምፎንቴን ለማቋቋም ተችሏል፡፡ ይህን አገልግሎት በማስፋፋት ረገድ ከቤ/ቱ መንፈሳዊ አባቶች፣ መሪዎችና አገልጋዮች ባሻገርም ኢትዮጵያውያንና ደቡብ አፍሪካውያን ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ትልቅ ተሳትፎና ድርሻ ነበራቸው፤ አሁንም አላቸው፡፡
ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያናችን በአፍሪካ ምድር ቀደምት፣ ሐዋርያዊትና እናት ቤ/ን ተብላ የምትጠራውን ያህል ባለፉትም ሆነ በአሁን ዘመን ለአፍሪካውያን ሕዝቦች የሚጠበቅባትን ያህል ተገቢ የሆነ አገልግሎት እየሰጠች ነው ብሎ ለማለት አያስደፍርም፡፡
ለዚህ ደግሞ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ቢኖሩም በዚህ አጭር መጣጥፍ ኹሉንም ችግሮችና ክፍተቶች ማንሳት የሚሞከር አይሆንም፡፡ ስለዚህም በደቡብ አፍሪካ የትምህርት ቆይታዬና አገልግሎቴ ያስተዋልኳቸውን ዐበይት ክፍቶችና ችግሮች ብቻ ላይ በማተኮር በመፍትሔ አሳቦቹ ላይ ትኩረት ማድረግ እንድንችል ጥቂት ነገሮችን ብቻ ልበል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን በደቡብ አፍሪካ ምድር ካላት ግዙፍ የሆነ ታሪካዊ መሠረትና ተቀባይነት አንፃር የስብከተ ወንጌል አገልግሎቷን ከራሷ ሕዝቦች አልፋ ሌሎች አፍሪካውያንና የዓለም ሕዝቦች በማዳረስ ረገድ ብዙ ርቀት መሔድ አልተቻላትም፡፡ ይኽም ቤተ ክርስቲያን ዋና ተልዕኮዋ የሆነውን የስብከተ ወንጌል ሥራ ቸል ማለቷ ዋንኛው ምክንያት ተደርጎ መጠቀስ የሚችል ይመስለኛል፡፡
ከዚህ እውነታ ጋርም ተያይዞ በዘመናችንም በቤተ ክርስቲያናችን የነገሠው ዘረኝነት፣ መከፋፈሉ፣ መለያየቱ፣ ሙስናው፣ የመንፈሳዊ ሕይወት እጦቱ፣ የሞራል ውድቀትና ድቀቱ የቤተ ክርስቲያኒቷን ሁለተናዊ መንፈሳዊ አገልግሎት ከድጡ ወደ ማጡ እያደረገው እንዳለም እያየን ነው፡፡
በተደጋጋሚ እንደታዘብነውም አባቶቻችንም በቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በተገናኙ ቁጥር አብዝቶ የሚያነጋግራቸው የጥቅማ ጥቅም፣ የአገረ ስብከት ቅየራ፣ ተደጋጋሚና የሆኑና ተግባራዊ መፍትሔ ያልተሰጣቸው በየዓመቱ እንደ አዲስ የሚነሡ የተንዛዙ አስተዳደራዊ ጉዳዮች/በደሎች ናቸው፡፡
በአንጻሩ ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ምን ያህል ሰው አምኖ ተጠመቀ፣ ምን ያህል መንፈሳዊ ት/ቤቶች፣ መንፈሳዊ የሥልጠና ተቋማትና ማዕከሎች ተቋቋመዋል፣ በቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ዕርቀ ሰላምን በማውረድ ረገድ ምን ያህል ሥራ ተሠራ በሚሉ ቅዱስ ሲኖዶሱ እንዲህ ዓይነቱን አንገብጋቢ አጀንዳ እንደ ዋና ርእሰ ጉዳዩ አድርጎ አንስቶ የተነጋገረበት ጊዜው ሩቅ እየሆነ ነው፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ሥራውን ዘንግቶም በሂደት የጠብ፣ የክርክርና የሙግት፣ የመወራረፊያ መድረክ እየሆነ መምጣቱን እየታዘብን ነው፡፡ በሰሞኑን የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ውዝግብ ባሻገርም ቅዱስ ፓትርያሪኩ ቤተ ክርስቲያናችን ባለፉት ዓመታት በሚሊዮን የሚቆጠር ምእመናኖቿን እንዳጣች፣ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማትም እየተዘጉ መሆናቸውን የገለጹበት አሳዛኝ ዜና የቤተ ክርስቲያን ዋና ተልዕኮ በሆነው በስብከተ ወንጌል አገልግሎትላይ ላጋጠማት ተግዳሮት ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ይኸው ተባብሶ የቀጠለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር በውጩ ዓለምም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥላውን እንዳጠላበት ግልጽ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በደቡብ አፍሪካ በምትገኘው ቤ/ን አገልግሎት ላይ ወዳሉ ክፍተቶችና ችግሮችም ስንመጣም ቅዱስ ሲኖዶስ በደቡብ አፍሪካ ቤ/ን በሚመደቡ አባቶች፣ አገልጋዮችና መምህራን ላይ ልዩ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ላነሳ እወዳለኹ፡፡
በደቡብ አፍሪካ በተደጋጋሚ የተላኩ መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል በአገሩ ቋንቋ አሊያም በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚገባ ለመግባባት ችግር ያለባቸው፣ ቤተ ክርስቲያናችን በአፍሪካ ሕዝቦች ዘንድ ያላትን ታሪካዊ መሠረትና ቁርኝት በሚገባ የማያውቁ፣ የሄዱበትን ሕዝብ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሥነ ልቦና ቀርበው ለማወቅ እምብዛም ማይጥሩ መሆናቸውን ነው የታዘብኩት፡፡
እናም በአብዛኛው የእነዚህ ሰባክያነ ወንጌል አገልግሎታቸው በዛ ላሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በአገሪኛ ቋንቋ ብቻ የተወሰነ እንጂ ደቡብ አፍሪካውያን የቤተ ክርስቲያናችንን አባላትና ሌሎች ስለ ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አገልግሎትና ታሪክ ማወቅ የሚፈልጉ የውጭ አገር ሰዎችን ማዕከል ሊያደርግ የቻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚችሉ ሆነው አልተገኙም፡፡
በእርግጥ በሊቀ ጳጳሱ በአቡነ ያዕቆብና በቤተ ክርስቲያናችን እያገለገሉ ከሚገኙ ደቡብ አፍሪካውያን ካህናትና ዲያቆናት ትብብር በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚደረግ የቅዳሴና የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አለ፡፡ በተጨማሪም በትምህርትና በተለያዩ የሥራ ጉዳዮች በደቡብ አፍሪካ ያሉ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመግባባት ክፍተትን በመሙላትና የቤተ ክርስቲያኒቱን በአፍሪካና በዓለም መድረክ ያላትን ልዩ ስፍራ፣ ጥንታዊ ታሪኳን፣ መንፈሳዊ ቅርሶቿንና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት፣ በተለያዩ መድረኮች የበኩላቸውን ጥረት ያደረጉ እንደነበር አስታውሳለኹ፡፡
ይሁን እንጂ ከአገልግሎቱ ስፋት አንጻር ይህ በቂ ሊሆን አይችልምና በቅጡ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይ በአገር ቤት ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያላትን ሐዋርያው አገልግሎት ምሉዕ ለማድረግ የተጠናከረ ሥራ ልትሠራ ይገባል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም ዋናው ተልዕኮውና ሥራው የሆነውን የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ዋናው አጀንዳው አድርጎ አጠናክሮ ሊይዘው ይገባል፡፡
ወንጌልን በተለያዩ አገሪኛም ሆነ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ሊሰብኩ የሚችሉ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስተዋውቁ የወንጌል መምህራንን በጥራትና በብዛት አሰልጥነው የሚያወጡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትንና የሥልጠና ማዕከሎችን መገንባትም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡
ከአርባ ሚሊዮን በላይ ምእመን ላላት ቤ/ን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የተገነባ አንድ ለእናቱ የሆነ የሥነ መለኮት ኮሌጅ ብቻ ባለቤት ሆኗ መቅረቷ የሚያሳፍር ብቻ ሳይሆን የሚያስቆጭም ጭምር ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ለቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮ የሚመጥን ደረጃውን የጠበቀ፣ የምርምርና የልቀት ማዕከል የሆነ የሥነ መለኮት ዩኒቨርሲቲ ማቋቋምን አጥብቆ ሊያስብበት ይገባዋል፡፡
በፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ዘመን መሠረቱ የተቀመጠው የማሕሌታዊው የቅዱስ ያሬድ የሥነ መለኮት ዩኒቨርሲቲ ጉዳይም ይኸው ‹‹ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም›› እንዲሉ ተነስቶ አያውቅም፡፡ ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ በትምህርትና በስብከተ ወንጌል ተልእኮ ላይ ሊጠናከር ይገባዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያንን ከዘረኞችና ከጎጠኞች፣ ከጥቅመኞች፣ ከሙሰኞች፣ ከአጭበርባሪዎችና የነጋዴዎች ምሽግ ከመሆን ሊታደጋት የሚችሉ የወንጌል አርበኞችን በሚገባ አስተምረውና አሰልጥነው የሚያሰማሩ መንፈሳዊ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና መምህራን በብዛትና በጥራት ያስፈልጉናል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶሱም እንደ ስሙ ቅዱስ የሆነ፣ ከፖለቲካና ከፖለቲከኞች አጀንዳ የጸዳ፣ የቅዱስ ወንጌል እውነት የሆነውን ፍቅርን፣ ሰላምንና ዕርቅን የሚሰብክ፣ መንፈሳዊ አባቶቻችንም ለእውነትና ለፍትሕ ድምፃቸው ከፍ ብሎ የሚሰማ የእውነት፣ የፍትሕ፣ የድሆችና የግፉአን ጠበቃ ሆነው እንዲቆሙ ነው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ፍላጎትም፣ ምኞትም!!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
*ዲ/ን ተረፈ ወርቁ፣ በደቡብ አፍሪካ ጆሐንስበርግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን፣ የደቡብና የምዕራብ አፍሪካ ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡

6 comments:

 1. አዛኝ መሳይ፡፡ አሁን ይህን ፅሁፍ ስለለጠፋች ኦርቶዶክሳዊያን ልትባሉና ልትሆኑ ነው? ሰይጣንመ አዳምንና ሔዋንን ወደሞት ሲወስዳቸው መልካም በሚመስልና አሳቢ መስሎ እንጂ ቅጠሏን ከበላችኹ ሞትን ትሞታላችኹ ብሎ አይደለም መከራ የጫነባቸው፡፡ እናም እናንተም ይኽን የሀሳብ
  ድግግሞሽ የበዛበትን ግራ አጋቢ ፅሁፍ በመለጠፈ
  ታማኒነትን ልታገኙ አትችሉም ፡፡ ማንነታችሁ
  በእሥከዛሬው ድርጊታችኹ ተጋልጧልና ነው፡፡
  ማንነታችሁም የክርስቶሥ ተቀዋሚዎች ስትሆኑ
  ግባችሁም አለማዊነትንና ሐሳዊ መሲሑን ማወጂ
  ነው፡፡ ደግሞ እናንተን ብሎ የምህራባውያንን ተግዳሮት
  ተች፡፡ ሌት ተቀን እንደ እባብ እየተሽሎከለካችኹ
  እውነትንና የክርስቶሥ የሆኑትን የምትዋጉትና
  የምታሳድዱት የምህራብያውያኑን እውነትንና ህይወትን
  የማጥፋት እንዲሁም ትውልዱ ማንነቱን አጥቶ
  ለሀገሩም ለማንነቱም ደንታቢሥ ሆኖ የነሱ ባሪያ
  እንዲሆን በተሰጣች ሚሽን አይደለምን? ይሁዳ
  ስለሽቶው ጌታን ሲሞግተው ድሆችን ተገን አድርጎ
  ነበርና እናንተም የኢትዩጲያ ኦርቶቶዶክሥ ተዋህዶ
  የክርስቶሥ ወንጌል አሥተምሮ፥ ሐይማኖታዊና
  መፅሐፍ ቅዱሳዊ ህጎቿና ሥርዓቷ ለሌሎች ሀገሮች
  እንዲዳረስና እንዲሰበክ ፅኑ ፍላጎት ያላችሁ
  በመምሠል ይሁዳ ለድሆች ያዘነና የተቆረቆረ መሥሎ
  ሽቶው ተሽጦ የሚደርሰውን ገንዘብ ለማግኘት
  በክርሥቶሥ ፊት ሆኑ ይህ ሽቶ ለምን ይባክናል ተሽጦ
  ለድሆች ይሆን ነበር ሲል በመርዝ የተለወሠ ቋንቋ
  እንደተናገር እናንተም ለክፉ ምኞታችሁ ማስፈፀሚ
  መሽሎኪ ለማግኘት መሆኑ ይታወቃል። እግዚአብሔር አጋልጧችኆልና አይሆንላችሁ። ንሥሀ ግቡ።

  ReplyDelete
 2. kkkkkkk! terefe! aba yaecon min aluh. lemin besimachew ayawetutim neber. melisugn maletachew aydel weche gud! motenatala!

  ReplyDelete
 3. be blessed bro. good job

  ReplyDelete
 4. ሀሳባችሁ ሁሉ እነሆ በጣም መልካምና እዉነቱን የተመረኮዘ ነው። ስለ እዉነት ስንናገር በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ሁነን መሆን አለበት። እዉነት ሁልግዜም እዉነት ነው። ነገር ግን እነ ማቅ በገንዘብ ካህናት አባቶቻችንን ስለ አሳወሩ እውነትን መናገርና ማየት አይችሉም። ይሁዳ አማላኩ ጋር ሆኖ ሳለ አምላኩን ማየት አልቻልም። ምክንያቱ ገንዘብ አይኑን አሳውሮት አምላኩን በ30 ዲናር ሽቶታል። ዉጤቱም ራሳን በራሱ በሰይጣን መንገድ ወስዶት ራሱን አጥፍቶዋል። ስለዚህ ጳጳሳትም ሆኑ ሌሎች ካህናት የማቅ ጥቅማጥቅም አንደበቶቻቸውን ስለ ዘጋ እዉነት መናገርና መስራት ተስኖዋቸው ይታያሉ። ዛሬ ለቤተ ክርስትያናችን ትልቅ ውድቀነተ ሆነ የተገኘው የሊቃነ ጳጳሳት ሀብት ማከማቸትና ባለ ትላልቅ ህንጻ ቤቶች መሆናቸው ምን ያህ መንፈሳዊ ህይወት እንደራቃቸው ነው በየመንደሩ የምወራውና የሚነገረው። ለመሆኑ ህዝባችን እስከ መቼ ነው ከህይወት ቃል ርቆና በጥላቸና በመለያየት የምኖረው? በአባቶችን መካከል የተፈጠረው ልዩነት እኮ ማህበር እናምልከ ወይንስ እግዚአብሔርን ? በዘመናችን ዓይነት እንድህ ዓይነት አስነዋር በነዋይ ፍላጎት እግዚአብሔርን የምያህል አምላክ ትተን ስለ ማህበር ነገር ቀንና ማት መወራቱ እጅግ አሳዛኝ ነው። ምን ያህል ከወንጌል ጋር እንዳትገናኘን ቃሉ በትክክል ሰርጾ ወደ ውስጣችን እንዳልገባና በልማድ ብቻ አምልኮት እየገለጽን መሆናችንን በግልጥ ያሳየናል። ድካም የበዛበት ህይወት ነዉ ያለነው።

  ReplyDelete
  Replies
  1. የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባአየሁሽ
   የእውነት መንፈስ ይህም የእግዚአብሔር መንፈስ የለባችሁምና ነገራችሁ፥ ጩኸታችሁ ሁሉ የተዘበራረቀ እርስበርሱ የሚጣረዝ ባዶ። ውድ አስታየት ሰጭ የተፃፈውን መልክት እንሿን ባልቀበለውም የተገነዘብከው ወይም ያነበብከው አይመስለኝም። ነገር ግን እንዲሁ የብሎጉ መሥራቾች ደጋፊ ወይም አባል ሥለሆንክ ብቻ እነሱን ያሥደሥትልኛል ያልከውን የተለመደውን ባዶ እውነት የለሽ የሠይጣን ክስኸን አንፀባረቅህ። የፃፍከውን አስተያየት ደግመኸ ብትመለከተው ሥለምን እንደፃፍክ የሚገባህ አይመስለኝም። እንዲሁ በማርገብገቢይ ወይም መሽረፍረፊት ከግራ ወደ ቀኝ እንሚውለበለብ የእሳት ነበልባ ከዛም ከዚህም ትዛክራለህ። ፈሪሳውያን እነሱ አዋኪ፥ ከሳሽ፥ አሳዳጅ፣ አሉባልተኛ ሆነው ሣለ ንፁሁን ክርሥቶሥ በየ አደባባዪ ይወነጅሉት ነበር። አንተም አስተያየት ሠጭና አለቆችህም ክፎዎች ሆናችሁ ሳለ ንፁሀንና በጎ አገልጋዮችን ትወነጂላላችሁ። ሥለመልካም ሠዎችና ማህበራታ መናገር ዝምብሎ የመጣ ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው። ለነገሩ አዉቆ የተኛ እንደሚባለው እናንተ መቸ ትሰሙና። የቃሉ ሙላትና የመንፈሥ ፍሬ የሌለባችሁ ናችሁና ሁልጊዜ ባዶ ውሸትን ታራግባላችሁ። የሞኝ ዘፈን ሁልጊዜ አበባአየሁሽ እንደተባለው ማህበረቅዱሳንን በጥላቻ ትራገማላችሁ። ከቤተክርሥቲያን፥ ከአባቶች፥ ከአገልጋዮችና ከማህበራት እራስ ወርዳች አታውቁም። ውድ አሥተያየት ሰጭ፤ አንተና መሠሎችህ ከእውነት ጋር ከመቆም ይልቅ ሁልጊዜ በፈረንጂ መዘውር እየጦዛችሁ ከቤተክርሥቲን እውነትን ከመሥማት ይልቅ ዛሬም እንደትናንቱ በነጭ የውሸት መንፈስ ፈረሥ እየተጋለባችሁ ሙሥና ሠጠ፥ሙሥና ተቀበሉ ወዘተ የዉሸት ክሶቻችሁን ምንም እንሿን ሠሚ የሌለው ከንቱ የቁራ ጩኸት ቢሆን በተደጋጋሚ ታራግባላችሁ። ወንድሚ በከንቱ ትርኪምርኪ አሉባልታ ውሥጥህን ከምታበክት የቃሉ ሙላት በውሥህ ይኖር ዘንድና ወደ እውነት እርሱም ክርሥቶሥ ነውና ትቀርብ ዘንድ ወደእውነተኞቹ አባቶችና አገልጋዮች ቀርበህ በየዋህነት ከግራቸው ሥር ቁጭ ብለህ ተማር።

   Delete
 5. አዛኝ መሳይ፡

  ReplyDelete