Saturday, December 13, 2014

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን በዘወርት

Read in PDF

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በማኅበረ ቅዱሳን የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ክፍል ሓላፊ የሆኑት ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ከጥቂት ወራት በፊት በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣና በማኅበረ ቅዱሳን ድረ ገጽ ላይ በተከታታይ ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዘወርት›› በሚል ዐቢይ ርእስ ያቀረቡትን ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ተከታትያለኹ፡፡ ዶ/ር መርሻ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓለም የክርስትና መድረክ የነበራትንና አሁንም ያላትን ልዩ ስፍራና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን በተመለከተ ያቀረቡት ታሪክ ዳሰስ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ለዚህ ጽሑፍ ዐቢይ ምክንያት ኾኖኛል፡፡
ዶ/ር መርሻ የኢትዮጵያ ቤ/ን የክርስትና እምብርት ከሆነችው ከእስራኤል ጋር ከዘመነ አበውና ከሕገ ኦሪት ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን ዘመን ድረስ ስለነበራት ሦስት ሺህ ዘመናትን ስላስቆጠረው ረጅም ታሪኳ፣ ክርስትያናዊ ጉዞዋና ዓለም አቀፍ ግንኙነቷን አጠር ባለ መልኩ ለመግለጽ ሞክረዋል፡፡ ዲያቆን መርሻ በዚሁ ጥናታዊ ጽሑፋቸውም የኢትዮጵያ ቤ/ን በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአሜሪካና በካረቢያን ለረጅም ዓመታት የቆየውን መንፈሳዊ አገልግሎቷን ሐዋርያዊ ተልዕኮዋን ተንትነዋል፡፡

ዶ/ር መርሻ በዚህ ጥናታዊ ጽሑፋቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከውጩ ዓለም ጋር ስለነበራት በርካታ ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት፣ ሐዋርያዊ ተልዕኮዋንና አገልግሎቶቿን በተመለከተ ያላነሷቸውን አንዳንድ ነጥቦችን በዚህ ጽሑፌ ለመዳሰስ ነው የዚህች አጭር ጥናታዊ ጽሑፍ ዓላማ፡፡
 ለዚሁ አጭር ጥናታዊ ጽሑፍ በታሪካዊ መረጃነትና ምንጭነት ከተጠቀምኩባቸው የጥናት ድርሳናት መካከልም የኢጣሊያዊው ምሁርና የታሪክ ተመራማሪ ኤነሪኮ ቼሩሊ፣ The Two Ethiopian Tales on the Christian of Cyprus በሚል ርእስ ያቀረበው የጥናት ወረቀት አንዱና ዋንኛው ነው፡፡ ይህ የቼሩሊ ጥናታዊ ጽሑፍ የኢትዮጵያ ቤ/ን ከዋክብት የሆኑ አባቶችና ሊቃውንቶች ከውጩ የክርስቲያን ዓለም ጋር ረጅም ዘመንን ያሰቆጠረ ግንኙነት እንደነበራቸው የሚያረጋግጥልን ነው፡፡ 
ቼሩሊ በኢየሩሳሌም ዴር ሱልጣን ይኖሩ የነበሩ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መነኮሳት አባቶችና መናኒያን ኢየሩሳሌም በእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በሆኑት በቱርኮች እጅ ከወደቀች በኋላ ከዴር ሱልጣን ገዳም የአውሮፓ ግዛት ወደሆነችው ወደ ቆጵሮስ ተሰደው ሃይማኖታቸውን፣ የአባቶቻቸውን ሥርዓትና ትውፊት ጠብቀው ለረጅም ዓመታት እንደኖሩ በዚሁ ጥናታዊ ጽሑፉ ያትታል፡፡
በዓለም ታሪክ እንደሚታወቀው የቱርክ ሱልጣን የሆነው ሳላዲን በ፲፪ኛው መቶ ክ/ዘመን በተቀናጀ ጦርነትና ወረራ መላው ፍልስጤምን፣ ኢየሩሳሌምንና እንዲሁም ቀይ ባሕር ዳርቻን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ችሎ ነበር፡፡ ታሪክ እንደሚነገረንም ክርስቲያኑ ዓለምም በሙስሊም እጅ የወደቀችውን ኢየሩሳሌምን ከዐረቦች ነፃ ለማውጣትም ለመቶ ዓመታት ያህል የዘለቀ የመስቀል ጦርነትን አካሒዷል፡፡
በአገራችንም ታሪክ ራሱን ‹‹የኢትዮጵያ ባል የቅድስቲቷ ምድር የኢሩሳሌም ውሽማ›› አድርጎ የሚቆጥረው የቋራው ካሣ፣ ዐፄ ቴዎድሮስም ለበርካታ ዓመታት በሙስሊም ቱርኮች እጅ የተያዘችው ቅድስት ምድር ኢየሩሳሌም ውስጥ ውስጡን ትበላው እንደነበርና በአውሮፓውያኑ የመሳሪያ ዕርዳታ ነጻ ሊያወጣት ትልቅ ሕልም እንደነበረው የአገራችን የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ ይህን የዐፄ ቴዎድሮስን ትልቅ ሕልም የተረዳ የአገራችን አዝማሪም እንዲህ ብሎ ማንጎራጎሩም አለምክንያት አልነበረም፡-
ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሣ ብሎ ስም፣
አርብ አርብ ይሸበራል ኢሩሳሌም፡፡
ኢየሩሳሌም በቱርኮች እጅ ከወደቀች በኋላ ሃይማኖታቸውን በነጻነት ማካኼድ ያልቻሉት ስደትና መከራ የበዛባቸው በዴር ሱልጣን ገዳም ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን መነኮሳትና አባቶች ከግብፃውያን አባቶችና መነኮሳት ጋር በመሆን በሜድትራኒያን ዳርቻ ወደምትገኘው ወደ ቆጵሮስ ደሴት ነበር የተሰደዱት፡፡ ኢትዮጵያውያኑ መነኮሳትና አባቶች በተሰደዱባት በቆጵሮስ ሃይማኖታቸውን፣ የአባቶቻቸውን ሥርዓትና ትውፊት ጠብቀው በማኅበር ለብዙ ዓመታት ይኖሩ እንደነበር የቼሩሊ ጥናት ያመለክታል፡፡
ቼሩሊ ለዚህ ጥናታዊ ጽሑፉ በመረጃነት የተጠቀመው በቫቲካን ቤተ መጻሕፍት የሚገኘውን ‹‹ቫቲካኑስ ኢትዮጲከስ›› በሚል በማይክሮ ፊልም ቁጥር MS. 272 የተመዘገበና በ፲፮ኛው መቶ ክ/ዘመን በኢትዮጵያውያን ሊቃውንቶች በተጻፈው ተኣምረ ማርያም መጽሐፍ ውስጥ የተካተተውን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቆጵሮስ ያደረገቻቸውን ኹለት ተኣምራቶችን የሚጠቅሰውን ንባብ መነሻ ያደርጋል፡፡ ኢጣሊያዊው የታሪክ ተመራማሪና ምሁር ኤነሪኮ ቼሩሊ ድንግል ማርያም በቆጵሮስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች ያደረገቻቸው እነዚህ ኹለት ተኣምራቶችን በኢትዮጵያውያኑ መነኮሳት/ሊቃውንት በተጻፈው ተኣምረ ማርያም ውስጥ እንዴት ሊያካትቱት ቻሉ ሲልም ይጠይቃል፡፡
ቼሩሊ ለዚህ ጥያቄ ራሱ መልስ ሲሰጥም ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ለረጅም ዓመታት በቆጵሮስ ደሴት ይኖሩ እንደነበርና ምናልባትም የመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውያን መነኮሳትና አባቶችም በ፲፪ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኢሩሳሌም በቱርኮች እጅ ስትወድቅ በሜድትራኒያን ዳርቻ ወደምትገኘው ወደ ቆጵሮስ ደሴት ከግብጻውያን መነኮሳት አባቶች ጋር ተሰደው ሳይመጡ እንዳልቀሩ ጽፏል፡፡
እነዚሁ በቆጵሮስ ደሴት ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያኑ መነኮሳት ለረጅም ዓመታት በግብፃውያን መንፈሳውያን አባቶች ሥር ይተዳደሩ እንደነበርና በ፲፭፻፷፬ ዓ.ም. ግን ኢትዮጵያውያኑ ማኅበረ መነኮሳት ለግሪካዊው መንፈሳዊ መሪና አባት ለሊቀ ጳጳስ አቡነ ፒየስ ፬ ባቀረቡት አቤቱታቸው ከኮፕት አባቶች አሥተዳደር ደስተኛ ባለመሆናቸው ከኮፕት መንፈሳዊ አባቶች ውጭ የሆነ የራሳቸውን ሌላ መንፈሳዊ መሪ፣ አባት/ሊቀ ጳጳስ ይሾምላቸው ዘንድ መጠየቃቸውን ይገልጻል፡፡
ከግብፃውያኑ አባቶች መንፈሳዊ አሥተዳደር ሥር ተለይተው በቆጵሮስ ዋና ወደብ ከተማ በሆነችው ኒቆሲያ ለበርካታ ዓመታት ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ብቻቸውን ራሳቸውን ችለው በማኅበር መኖር የጀመሩት ኢትዮጵውያኑ መነኮሳትና አባቶች በአገራቸው በተከታታይ በተከሰተው የግራኝ አህመድ ወረራና በኦሮሞ ሕዝብ ፍልሰት ምክንያት ከእናት ቤተ ክርስቲያናቸው ጋር ለብዙ ዓመታት ተለይተው እንደቆዩና ለመገናኘትም ቢፈልጉም እምብዛም ዕድሉ እንዳልነበራቸው የኤኔሪኮ ቼሩሊ ጥናት ይጠቁማል፡፡
ቢሆንም ግን ይላል ቼሩሊ፡- እነዚህ ኢትዮጵያውያን መነኮሳትና አባቶች ሃይማኖታቸውን፣ ሥርዓታቸውን ትውፊታቸውን ጠብቀውና አስጠብቀው ከመኖራቸውም በላይ በስደት በሚኖሩበት ዓለም የነበረውን መንፈሳዊ ሕይወትን በድርሰቶቻቸው ውስጥ በማካተት ከትበው እንዳስቀሩ በ፲፮ኛው መቶ ክ/ዘመን በኢትዮጵያውያን አባቶች የተጻፈውን ተኣምረ ማርያምን በዋቢነት በመጥቀስ ጽፏል፡፡ 
ይህን ቼሩሊ ኢትዮጵያውያኑ መነኮሳት በቆጵሮስ ይኖሩ እንደነበር የሚያትተውን ጥናታዊ ጽሑፉን የሚደግፍ ሌላ አንድ አውሮፓው ተጓዥ ምስክርነትን ደግሞ እዚህ ጋር ላንሳ፡፡ በ፲፭፻፲፮ ዓ.ም. ወደ ጥንታዊዎቹ የክርስትና ማዕክል ወደሆኑት ግሪክ፣ ሮምና መካከለኛው ምሥራቅ የተጓዘው ስፔናዊው ተጓዥ ዲኦጎ ሜሪዳ በሜድትራኒያንዋ ዳርቻ በምትገኘው በቆጵሮስ ዋና ከተማ ኒቆሲያ ኢትዮጵያውያን መነኮሳትንና አባቶችን ማግኘቱን በጉዞ ማስታወሻው ላይ አስፍሮታል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን መነኮሳትና አባቶች በአውሮፓ ምድር ስለነበራቸው መንፈሳዊ ሕይወት፣ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነትና አገልግሎትን በተመለከተ እ.ኤ.አ. በ1960 An Outline of the Development of Ethiopian Topography in Europe በሚል ርእስ ጥናታቸውን ያስነበቡት ሆላንዳዊው ምሁር ዶ/ር ኤች. ኤፍ. ዊጂንማን ጥናት እንደሚገልጸው፣ ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶችና ሊቃውንቶች ከ፲፭ኛው እስከ በ፲፰ኛው መቶ ክ/ዘመን አጋማሽ ድረስ ወደ አውሮፓ ምድር በግልና በማኅበር ይጓዙ እንደነበር በዚሁ ጥናታቸው ያትታሉ፡፡
በአውሮፓ በተለይ ደግሞ የካቶሊክ ሃይማኖት ማዕከል ወደሆነችው ሮማ በተለያዩ ምክንያቶች የመጡ ኢትዮጵያውያኑ መነኮሳት ከሮማ ካቶሊክ ቀሳውስትና ሊቃውንት ጋር በነበራቸው ግንኙነት የተነሣ ጥሩ የሚባል ቅርርብና የሃይማኖታዊ ውይይትን መፍጠር ችለው እንደነበር ዶ/ር ዊንጅማን ያወሳሉ፡፡
ለአብነትም ያህል፡- ‹‹የኢትዮጵያ ጥናት አባት›› ተብሎ የሚጠራውን ጀርመናዊውን ሂዮብ ሉዶልፍን ግዕዝ ቋንቋንና ኢትዮጵያን ታሪክ በማስጠናት የኢትዮጵያ ጥናት በአውሮፓዊቷ የጀርመን ከተማ በኑረምበርግ እንዲጀመር መሠረቱን የጣሉት በሮም ከተማ ይኖሩ የነበሩት የቤተ ክርስቲያናችን ሊቅ አባ ጎርጎርዮስ ዘመካነ ሥላሴን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በሌላም በኩል ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዓፄ ልብነ ድንግል የአዳል ገዢና የጦር አዝማች ከሆነውና በተለምዶ ግራኝ አሕመድ እየተባለ ከሚጠራው የጦር ኃይል ጋር በገቡበት ጦርነት ዕርዳታን ፈልገው ወደ ፖርቹጋል ንጉሥ መልእክተኞችን ልከው ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከልም አባ ጸጋ ዘአብ ከተባለው ሊቅና ከንጉሡ መልእክተኛ ጋር በሊዝበን ከተማ የተገናኘው ታዋቂው ሂዩማኒስትና ሚሽነሪ ዳሚያኑስ ጆኤስ ከአባ ጸጋ ዘአብ ጋር ያደረጉትን ሃይማኖታዊ ውይይት በተመለከተ ያወጣው መጽሐፍም በአውሮፓ በነበሩ በተሐድሶ አራማጆችና በአናባፕቲስቶች ዘንድ ትልቅ ዕውቅናን እና ዝናን ለማትረፍ ችሎ ነበር፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላም ፍራንስሲኮ አልቫሬዝ በ፲፭፻፲፫-፲፭፻፳ ዓ.ም. በኢትዮጵያ የነበረውን ቆይታውን በተመለከተ በ፲፭፻፴፪ ዓ.ም. በሊዝበን ከተማ ‹‹የካህኑና የንጉሡ ዮሐንስ አገር ኢትዮጵያ›› በሚል ርእስ በፖርቹጊዝ ቋንቋ ያሳተመው ዳጎስ ያለ የጉዞ ማስታወሻ መጽሐፍ በአውሮፓ ምድር ስለ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ውበትና ሀብት፣ ስለ ሕዝቦቿም ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ቅርስ… ወዘተ. በሰፊው ለማወቅ ለሚፈልጉ ምዕራባውያን ሁሉ ትልቅ ጉጉትንና መነቃቃትን የፈጠረ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
በተመሳሳይም ሌሎች የታሪክ ሰነዶችንና መዛግብቶችን ስንፈትሽም በእውቀታቸው፣ ጥበባቸውና በበሳል ፖለቲካዊ አስተዳደራቸው በአገራችን ታሪክ ወርቃማ ዘመንን በማስፈናቸው ‹‹ፍጹማዊ አገዛዝ/Absolute Monarchy›› የሚል ቅፅል ስም የተሰጣቸው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብም በ፲፬፻፴፪ ዓ.ም. በኢጣሊያዊቷ ፍሎረንስ ከተማ በተካኼደው የሃይማኖት ጉባኤ ላይ ኹለት ኢትዮጵያውያን መነኮሳትን እንዲሳተፉ ልዑካን አድርገው ልከው እንደነበር እነዚሁ የታሪክ ድርሳናት ይመስክራሉ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ መነኮሳትና ሊቃውንት ከአውሮፓውያን በተለይም ከሮማውያን ጋር በነበራቸው ግንኙነት የተነሳም ከታላቁ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል አቅራቢያ የሚገኘውን የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያንን ሮማውያኑ አባቶች ለኢትዮጵያውያን መነኮሳትና የመንፈሳዊ ተጓዦች ቤተ አምልኮና ማረፊያ እንዲሆናቸው በስጦታ አበርክተውላቸው እንደነበር የዶ/ር ዊንጅማን ጥናት ይገልጻል፡፡
ይህ የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ንም እስከ ፲፰ኛው መቶ ክ/ዘ መገባደጃ ድረስ የኢትዮጵያውያን መነኮሳትና ተጓዦች ቤተ አምልኮና ማረፊያ ሆኖ መቆየቱን ዶ/ር ዊንጅማን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ ከጥንት ጀምሮ የተጀመረውና መካከለኛው ምሥራቅንና አውሮፓን ማእከል ያደረገው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮና ከውጩ ዓለም ጋር የነበራት ግንኙነት ብዙ ዘመናትን ያስቆጠረ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
በዚህ በረጅም ዘመን ታሪኳ፣ በጥንታዊነቷና በገናና ሥልጣኔዋ የተነሳ በዓለማችን ከነበሩ ታላላቅ ሥልጣኔዎች መካከል የምትመደበው አገራችን ኢትዮጵያና ለዚህ ረጅም ታሪኳና ሥልጣኔዋ ዋንኛ አካል የሆነችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን የብዙዎችን የውጭ አገር ተጓዦችን፣ አሳሾችንና ተመራማሪዎችን ቀልብ ለመሳብ እንደቻለች በርካታ የአገር ውስጥና ውጭ አገራት የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓና ከመካከለኛው ምሥራቅ በሃይማኖት ምክንያት በደረሰባቸው ስደት፣ መከራና እንግልት የተነሳ ወደ እርሷ በእንግድነትና ለመጡ ሁሉ መጠለያ በመስጠት በፍቅርና በትሕትና ስታስተናገድ መቆየቷ በሰፊው ተጽፎላታል፡፡ እንኳን በእምነት ከሚመስሏት ከአኀት አብያት ክርስትያናት ቀርቶ ከዐረቢያ ምድር የመጡ የነቢዩ መሐመድን ተከታዮች ሁሉ ሳይቀር በሰላም ተቀብላ መጠለያ በመስጠትና በማስተናገድ ሕይወታቸውን ከጠላቶቻቸው ሰይፍ የታደገች መንፈሳዊ፣ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት መንፈሳዊ ተቋም ናት፡
እናም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አገራችን መጥተው በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እምነት፣ አስተምህሮ፣ ትውፊትና ሥርዓት በአባቶቻችን ተጋድሎ፣ ትዕግሥት፣ ጽናትና የወንጌል አርበኝነት ተስበው፣ አምላካችሁ አምላካችን፣ ሕዝባችሁ ሕዝባችን ብለው በአገራችን የቀሩ፣ ወንጌል ያስፋፉ፣ መጻሕፍትን የተረጎሙ፣ ታላላቅ ገዳማትን የገደሙ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ የስልጣን ማእረግ እስከሆነው የእጨጌነት ሥልጣን ድረስ የደረሱትን እንደ የመናዊው እጨጌ ዕንባቆምን ያሉትንና፣ የኢትዮጵ ቤ/ን የመጀመሪያው ጳጳስ የነበሩትን አባ ሰላማን/ከሳቴ ብርሃንን፣ ተሰዓቱ ቅዱሳንን፣ አባ ሰላማ ካልዕን፣ አቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስን ለአብነት ያህል ማንሳት ይቻላል፡፡
በአንጻሩም ደግሞ የቀደሙት የቤተ ክርስቲያናችን አባቶችና ሊቃውንቶች ወደ አፍሪካ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ፣ የመን፣ እስራኤልና አውሮፓ ድረስ በመጓዝ ለተቀረው ዓለም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና ሥርዓት፣ የአገራቸውን ታሪክ፣ ቋንቋና ባህል በማስተዋወቅ ረገድ በባዕድ ምድር የዘር፣ የቋንቋ፣ የባህል ልዩነት ሳያግዳቸው ትልቅ አስተዋጽኦን አድርገዋል፡፡
እንደዛሬው የቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ አባቶችና መሪዎች ከእውቀትና ከመንፈሳዊነት ዕድገት ተገድበውና ከሌላው ዓለም ተነጥለውና ተለይተው፣ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስ አንድነታቸውን ለመጠበቅ ተስኗቸው፣ እርስ በርሳችን በቋንቋ፣ በዘርና በፖለቲካ ተከፋፍለን እንኳን የውጩን ዓለም በወንጌል ቃል ለመማረክ ቀርቶ በስራችን ያሉትን መነጋዎች እንኳን በቅጡ ለማሰማራት ያልቻልንበት ደረጃ ከመድረሳችን በፊት የቀደሙት አባቶቻችን ከሕዝባቸው አልፈው ሌሎችን በመንፈሳዊ ሕይወታቸውና ሥርዓታቸው ለመማረክ የቻሉ፣ በባዕድ ምድር በአምልኮተ እግዚአብሔር ጸንተው የኖሩና እንደ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ የእውቀትና የመንፈሳዊ ጥበብ ራብና ጥማት እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ሳይቀር የሚያማስናቸው ትጉ፣ ጠንካራና መንፈሳዊ ዐርበኞ ነበሩ፡፡
እነዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶችና ሊቃውንት በሔዱበት የውጩ ዓለም ሁሉ ሃይማኖታቸውን በትጋት በመጠበቅ፣ ወንጌልን በመስበክ፣ የአገራቸውንና የሕዝባቸውን ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋና ቅርስ ለሌሎች በማስተዋወቅና በማስተማር በአፍሪካ፣ በአሜሪካ፣ በካረቢያንና በጃማይካ ዛሬም ድረስ የዘለቀ
በእግዚአብሔር የፍቅር ልዩ ቃል ኪዳን የተዋበው የኢትዮጵዊነት የአንድነት መንፈስ፣ የነጻነት ተጋድሎ ብሔራዊ ኩራት በልባቸውና በደማቸው ውስጥ ጸንቶ እንዲቆይ ይህን ትልቅ ሥራ፣ ይህን ሕያው ታሪክ ሠርተው አልፈዋል፤ እናም እነዚህ የቤተ ክርስቲያናችንን ከዋክብትና ታላላቅ ባለ ታሪኮችን ሁልጊዜም ልንዘክራቸው፣ ልናከብራቸው፣ በሥራቸውም ልናወድሳቸው ይገባል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

6 comments:

 1. ዲ ተረፈ ጥሩ ታሪክ አስነብበከን ። ስለ ዘርኣ ያእቆብ ከተናገርከው በቀር ሌላውን ተቀብለንሃል። ዘርኣ ያእቆብ ጨለማን በኢትዮጵያ ያመጣ ክፉ ሰው ነው። በዚህ ሰሰው ጉዳይ ንስሃ እስካልገባን ድረስ ጨለማው ባገራችን ላይ አስከፊ ሆኖ ይቀጥላል። እናንተ ዘርአ ያእቆብን እየሰበካችሁ የጨለማውን ዘመን ልታስረዝሙ ትሞክራላችሁ። እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን በመስበክ ጨለማውን እናስወግዳለን። ሁሉም መገለጡ ስለማይቀር ከወዲሁ እግዚአብሔር ይመስገን።

  ReplyDelete
 2. ኸረ እናንተ ሰዎች ምነው ጤነኝነት ተሰማችሁ? እንዴ ማቅን መክሰስ ረሳችሁሳ? የሰም ማጥፋት፣የመዋሸት ልምዳችሁ ቀረሳ?

  ReplyDelete
 3. is it all about from 'aba selama' blog? who advised u to write the truth for the first time since this blog was opened. but i am sure you will not continue with this positive thing, you will come back with your nufake, hate, insult and critics to our mather church as usual.

  ReplyDelete
 4. aba selama stop preaching the Gospel and starts teret teret

  ReplyDelete
 5. ከወራት በኋላ ምን ፍለጋDecember 15, 2014 at 10:30 AM

  የዚህ ጽሑፍ ፀሐፊ በመግቢያው ዶክተር ዲያቆን መርሻ አለኸኝ ባቀረቡት "የኢትዮጽያ ቤተክርስቲያን በዘወትር" ጥናታዊ አጭር ጽሑፍ ላይ ለመጨመር ነው ይላል። የዲያቆን መርሻ አለኸኝ ጥናታዊ ጽሑፍም የቀረበው ከወራት በፊት እንደሆነ ይናገራል።ይቀጥልና ይህን ለመፃፍ የተነሳው ዲያቆን መርሻ ያልገለጧቸውን ለመጨመር እንደሆነ ዲያቆን ነይ ባዮ አቶ ተረፈ ይተርክልናል።እኔ በግሌ ከወራቶች ወይም እንደሱ አገላለጥ የዲያቆን መርሻ ጥናታዊ ጽሑፍ ከወጣ ከወራት በኋላ ያልተካተቱ ለመጨመር በሚል የተንኮል ስሌት አሁን ለመጻፍ ለምን አሥፈለገ?በጊዜው ለመርዳት ለመን አልፃፈም? ሌላው የአቶ ተረፈ ጽሑፍ እውነታ የጎደለውና ማምታታት የታጨቀበት ነው። ለምሰሣሌ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሐን ኢትዮጽያ መጥተው ሐይማኖታችሁ ሐይማኖቴ አምላካችሁ አምላኬ ብለው ተቀበሉ ሲል የሚያጠራጥርና ከትክክለኛው እውነታ የወጣ እውነት የሚመስል ግን ያልሆነ ታሪክ ጽፈዋል።እውነታው አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሀን የመጡት በአጭር ቋንቋ ለቤተክርስቲያን አባት ሆነው ወንጌልን ለማስፋፋት ከግብጽ መንበር ተሾመው የመጡ ናቸው።ሥለሌላ አባ ሰላማ ከሆነ የሚያወራው ለይቶ በግልጽ መጻፍ ይገባዋል።ከዚህ ተነስተን የሠውየውን አምታች ጠባብ ጠናታዊ ጽሑፍ ተብየ መቀበል አይቻልም ።

  ReplyDelete