Sunday, December 14, 2014

ንቡረ እድ ኤልያስና ማኅበረ ቅዱሳን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው

“እመሰ አማን ጽድቀ ትነቡ ወርትዐ ትኴንኑ ደቂቀ እጓለ እመሕያው እስመ በልብክሙ ኀጢአተ ትገብሩ በዲበ ምድር”
ትርጉም፡- በእውነት ጽድቅን ብትናገሩስ፥ የሰው ልጆች ሆይ፥ በቅን ትፈርዳላችሁ፡፡ በልባችሁ በምድር ላይ ኃጢአትን ትሠራላችሁና፥ እጆቻችሁም ግፍን ይታታሉና።” መዝ. 57፥1-2
አበው ሲተርቱ <<ምላጭ ቢታመም በምን ሊበጡ ቄስ ቢያጠፋ በምን ሊቆጡ>> ይላሉ፡፡ በአገራችን በባህልም ሆነ በእምነት ለቄስ (ለካህን) ያለው ግምት በጣም ከፍ ያለና ለእግዚአብሔርም በጣም የቀረበ ነው፣ የእግዚአብሔርን መንገድ ያውቃል ተብሎ ስለሚታመን አያጠፋም፣ አይገሰጽም፣ አይከሰስም ይባላል፡፡ እውነትነትም አለው፡፡ ምክንያቱም ካህን መካሪ፣ የተጣሉትን አስታራቂ፣ ያጠፉትን ተቆጪ፣ እንዲህ ዓይነቱን ክፉ ሥራ እግዚአብሔር አይወድም፣ እንዲህ ዓይነቱን መልካም ሥራ ደግሞ እግዚአብሔር ይወዳል እያለ ይገስጻል፣ ያስተምራል፡፡
በዚህ ሐሣብ የተነሣነው የካህን ሥራ ምን እንደሆነ እንደአዲስ ትምህርት ለማስተማር ሳይሆን ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘና ንቡረ እድ ኤልያስ ከአንድ እንደእርሳቸው ካለ ምሁር የማይጠበቅ አሳፋሪ ድርጊት ሲፈጽሙ እየታዘብን ስለሆነና ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የቤተክርስቲያንን ክብር የሚነካ፣ እውነተኞችን የሚጎዳና ሙሰኞችን የሚጠቅም ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን በተጨባጭ ማስረጃ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ለማሳየት በማሰብ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ቅዱስ ፓትርያርኩ በፈቃደ እግዚአብሔር ፓትርያርክ ሆነው ከተሾሙ ወዲህ አጥብቀው ሙስናን ሲቃወሙትና ሲጸየፉት አስቸኳይ መፍትሄ እንደሚያስፈልገውም በሚዲያና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተሰበሰቡ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ፊት እያነሱ በተለያየ ጊዜ ሲያወግዙት ነበር፡፡ ቅዱስነታቸው በታሪክ ሙስናን በአደባባይ ከልባቸው የተጸየፉና ሁነኛ ሰው ባያገኙም የተዋጉ የመጀመሪያው አባት ናቸው ብንል ማጋነን ወይም መዋሸት አይሆንም፡፡ ነገር ግን በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣል እንደሚባለው ንቡረ እድ ኤልያስን የመሰሉ ሁለት ባሕርይ ያላቸው ሰዎች የቅዱስ ፓትርያርኩን ሙስናን የማስወገድ ራእይ ገና ከጅምሩ እያኮላሹት ይገኛል፡፡ ንቡረ እድ ኤልያስ መንፈሳዊም ዓለማዊም ገጸ ባሕርይ ተላብሰው በሚያታልለው አንደበታቸው የመንግሥት ባለሥልጣን ሲያገኙ ለሕዝብና ለቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ እርሳቸው ብቻ እንደ ሆኑ አስመስለው ሲታዩ፣ ቤተክህነት ውስጥ በተግባር ግን ፀረ ቤተክርስቲያን ተግባር ሲፈጽሙ ይታያል፣ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ሚናቸው ስላልለየ ወዳጅ ሲሏቸው ጠላት ሆነው የሚገኙበት አጋጣሚ ያይያል፡፡

ንቡረ እዱ አሁን እያደረጉት ያለው ተግባር ፓትርያርኩን የሚያስነቅፍና አንገት የሚያስደፋ እንደሆነ ለማንም ግልጽ እየሆነ ነው፡፡ በቅርቡ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ካህናትና የቢሮ ሰራተኞች መካከል ለተፈጠረው ውዝግብና በቢሮ ሰራተኞች ስለተፈጸመው የዘረፋ ወንጀል እውነቱን እያወቁና እየተረዱ ለዘራፊዎቹ ወግነው በመቆማቸውና ጠበቃ በመሆናቸው ታሪካዊ ስህተት ፈጽመዋል፡፡ ይባስ ብለውም የተገለጠውን እውነት /ሐቅ/ አይተውና ተመልክተው ንስሀ እንደመግባት ሌላ ትልቅ ጥፋት እየሠሩ ነው፡፡ ይኸውም ከእርሳቸው ይልቅ ለኅሊናውና ለቤተ እግዚአብሔር ቀናኢ ሆኖ የተገኘውንና በእድሜ ልጃቸው የሚሆነውን መ/ር ሙሴ ታደሰ የተባለውን ወጣት ምሁርና ታማኝ አገልጋይ እግዚአብሔር ያሳድግህ እድሜ ይስጥህ በማለት ፈንታ ከሙሰኞች ጋር በማበር እርሱን ከሃላፊነቱ ለማስወገድ ጉድጓድ እየማሱለት መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በቅርቡ ወደ ቅዱስነታቸው የገቡትንና በገዳማቸው እየተፈጸመ ስላለው ዝርፊያ አቤት ያሉትን የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ካህናትን እኔ እንዳይገቡ ከልክዬ ሳለ እግሬ ወጣ እንዳለ አስገብቶ አቤት እንዲሉ ያደረገው እርሱ ነው በሚል ነው፡፡ በእነዚህ ካህናት የተጀመረው ሙስናን የማጋለጥና ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የማስፈን ሕጋዊ እንቅስቃሴ ወደሌሎች አድባራትና ገዳማት ሳይዛመት አዳፍኖ ለማስቀረትና ቅዱስ ፓትርያርኩ በገዳሙ የጀመሩትን ፍትህ የማስፈን እንቅስቃሴ ወደሌሎች እንዳይዘረጉ ለማድረግም ነው፡፡
ብዙ ግፍና በደል ደርሶባቸው አቤት የሚሉበት ያጡትን፣ የፍትሕ ያለህ እያሉ የሚጮኹትንና እንደንቡረ እድ ኤልያስ በሩን ይዘው አላስገባ ያሏቸውን ግፉዓንን እያስገባ ያለው መ/ር ሙሴ ስለሆነ፣ ይህ ደግሞ ለሙሰኞች የሙስና በሩን የሚዘጋ አሠራር ስለሆነባቸው ካህናት በዚህ መንገድ አቤት እንዳይሉ ወደዚያ የሚያቀርባቸውን መ/ር ሙሴን ነገር ሰርቶ ከዚያ ማስነሳት የሰሞኑ የንቡረ እድና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ትልቅ አጀንዳ ሆኗል፡፡ በሙስና በተበከሉ አድባራት ውስጥ የተሾሙና በቢሮ የሚሠሩ ሙሰኞች በንቡረ እድ ኤልያስ መሰርይ ምክር ምክንያት አድማ የመቱ መሆናቸውን በቅርበት የምንከታተል ሲሆን ንቡረ እድ አይዟችሁ ስላሏቸው መ/ር ሙሴን ከቦታው ለማስነሳት ፒቲሽን እየተፈራረሙ መሆናቸውን ከአንደበታቸው እየሰማን ነው፡፡ ለመሆኑ በዚህ ተግባራቸው በማኅበረ ቅዱሳንና በንቡረ እድ መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው? ማኅበረ ቅዱሳንን እየተቃወምነው ያለነው እኮ በሚያሳየው ሁለት ባህርይ ምክንያት ነው፡፡ ላይ ላዩን ለተመለከተው የሃይማኖት ተቋም ነኝ፣ ለቤተክርስቲያን የቆምኩኝ ነኝ ሲል ይሰማል፡፡ በሌላኛው ገጽታው ግን ፖለቲከኛ፣ አሻጥረኛ ነጋዴ (ተገቢውን ግብር እንኳ ሳይከፍል በቤተ ክርስቲያን ስም የሚነገድ)፣ ከምንም በላይ ደግሞ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ሲል ሙሰኛ ከሆኑ የአንዳንድ አድባራት አለቆች ደጋፊዎቹ ጋር ተሞዳሙዶ የሚኖርና ቤተክርስቲያን ስትዘረፍ ዝም ብሎ የሚመለከት አድር ባይ፣ እርሱን በተቃወሙት ላይ ግን ሐሠተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ የሚከፍት ግብዝ ማኅበር ስለሆነ ነው፡፡ ንቡረ እድ ኤልያስም በአንድ ወገን ማኅበረ ቅዱሳንን እየተዋጋሁ ነው እያሉ ሲምሉ ሲገዘቱ በሌላ በኩል ግን በጉቦ ፍርድን እያጣመሙ በሙስና ተዘፍቀው የሚኖሩ መሆናቸው ከማኅበረ ቅዱሳን የተለዩ አያደርጋቸውም፡፡
ንቡረ እድ ኤልያስ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሙስና ምክንያት ጩኸት ስለበዛ ተነሥተው ወደ ጠቅላይ ቤተክህነት ከተዛወሩና የቅዱስ ፓትርያርኩ የቅርብ አማካሪ ከሆኑ ወዲህ የተቀመጡበትን ቦታ ለሙስና በማመቻቸት ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ ከሚገቡት መማለጃ በመቀበል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅነታቸው ዘመን የኖሩበትን ሙስና በጠቅላይ ቤተክህነትም እየደገሙት ይገኛሉ፡፡ ‹‹ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ›› እንዲሉ አበው፡፡ ለዚህ አንድ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ጉቦ የበላ ዓይን የታወረ ነውና የሰአሊተ ምህረት ማርያም ጸሐፊ የነበረው ውጪ ይሄዳል በሚል በመቶ ሺህ የሚቆጠር ብር የጠቅላይ ቤተክህነቱ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ማቴዎስና ንቡረ እድ ኤልያስ በየፊናቸው ጉቦ ስለበሉ ቅዱስ ፓትርያርኩን በማሳሳት ለአመክሮ በሚል ወጣ ያለ ቦታ እንዳይሰጠው በሚል አባቶችን አፈናቅለውና እንደአሮጌ ቁና አውጥተው በመጣል ለጸሐፊው ክብር ሲባል የእንጦጦ ኪዳነ ምህረትን አስተዳዳሪ ወደ ደብረ ብርሃን በማሳደድ የሰአሊተ ምህረትን አስተዳዳሪ ወደ እንጦጦ በማዛወር ትልቅ ስህተት ተፈጽሟል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በንቡረ እድ ኤልያስ መሰርይ አቀነባባሪነትና በአቡነ ማቴዎስ ክፋት፣ ተንኮለኛነትና ገንዘብ ወዳጅነት ነው፡፡ ዓይናቸው በጉቦ የታወረው እነዚህ ሰዎች ይህን አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት የፈጸሙት ለአንድ የቤተክርስቲያን ውስጥ ወንበዴ፣ አባቶችን የማያከብር፣ ያልተማረና የቤተክርስቲያንን ሀብት በመዝረፍ የበለጸገ ግለሰብን በህገወጥ መንገደ ለመጥቀምና እነርሱም ጠቀም ያለ ጉቦ ለመብላት ሲሉ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
በተለይ ንቡረ እድ ኤልያስ እየፈጸሙ ያለው ይህን መሰል ሙስናዊ ተግባር በቅዱስ ፓትርያርኩ ላይ ከፍተኛ የመንፈስ ስብራትን እንደሚያመጣ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያሉ ብልሽቶችን በጊዜው ማረም ካልተቻለ በኋላ የሚመጣውን ችግር መሸከም አስቸጋሪ ይሆናልና ቅዱስ ፓትርያርኩ አሁን በጀመሩት ከሁሉም ወገኖች ሰምቶና ነገሩን አጥርቶ ፍትህ የመስጠት ስራ መቀጠል እንዳለባቸው በታላቅ ትህትናና አክብሮት አስተያየት ስንሰጥ ቅዱስነታቸው ጉዳዩን እንደሚቀበሉት ምንም ጥርጥር የለንም፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረስብከት አድባራትና ገዳማት የምንገኝ ግፉዓን

3 comments:

 1. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በላይ መኮንና ንቡረ እድ ኤልያስ በየፊናቸው ጉቦ ስለበሉ ቅዱስ ፓትርያርኩን በማሳሳት ለአመክሮ በሚል ወጣ ያለ ቦታ እንዳይሰጠው በሚል አባቶችን አፈናቅለውና ለጸሐፊው ክብር ሲባል የእንጦጦ ኪዳነ ምህረትን አስተዳዳሪ ወደ ደብረ ብርሃን በማሳደድ የሰአሊተ ምህረትን አስተዳዳሪ ወደ እንጦጦ በማዛወር ትልቅ ስህተት ተፈጽሟል፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በንቡረ እድ ኤልያስ መሰርይ አቀነባባሪነትና በበላይ መኮን ክፋት፣ ተንኮለኛነትና ገንዘብ ወዳጅነት ነው፡፡ ዓይናቸው በጉቦ የታወረው እነዚህ ሰዎች ይህን አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊት የፈጸሙት ለአንድ የቤተክርስቲያን ውስጥ ወንበዴ፣ አባቶችን የማያከብር፣ ያልተማረና የቤተክርስቲያንን ሀብት በመዝረፍ የበለጸገ ግለሰብን በህገወጥ መንገደ ለመጥቀምና እነርሱም ጠቀም ያለ ጉቦ ለመብላት ሲሉ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡

  ReplyDelete
 2. ብዙ ግፍና በደል ደርሶባቸው አቤት የሚሉበት
  ያጡትን፣ የፍትሕ ያለህ እያሉ የሚጮኹትንና እንደንቡረ እድ
  ኤልያስ በሩን ይዘው አላስገባ ያሏቸውን ግፉዓንን እያስገባ
  ያለው መ/ር ሙሴ ስለሆነ፣ ይህ ደግሞ ለሙሰኞች የሙስና
  በሩን የሚዘጋ አሠራር ስለሆነባቸው ካህናት በዚህ መንገድ
  አቤት እንዳይሉ ወደዚያ የሚያቀርባቸውን መ/ር ሙሴን ነገር
  ሰርቶ ከዚያ ማስነሳት የሰሞኑ የንቡረ እድና የጥቅም
  ተጋሪዎቻቸው ትልቅ አጀንዳ ሆኗል፡፡

  ReplyDelete
 3. ትናንት የንቡርድ ወዳጆች ዛሬ ለምን ጠላት ሆናችሁ?December 16, 2014 at 7:19 AM

  ድሮ ድሮ የቤተክርስቲያን ቋንቋ የሆነውን የግዕዝ ቋንቋ ግፉዓን ባዮች በተግባር እውነትን ለመጣል በክፉ ተግባራቸው እውነትን ገፊዎች የሆኑትና አህዛ የብሎጉ ሠዎች ሌላ ትርጉምን ይሰጡት ነበር።ዛሬ ዛሬ ደግሞ ያ የድሮው አሥተሳሰባቸው ውሸት መሆኑ የተነቃባቸው ሲሆንና ግዕዝም የመግባቢ ቋንቋ የሚደመጥና የሚተረጎም በመሆኑ ሠሚሥላጡ ቋንቋውን ለመዳንና ለእውነት ሳይሆን ለተንኮላቸውና ለማስመሰያነት መጠቀም ይዘዋል። የተጠቀሠው ጥቅስ ቢያሥተውሉት እነሱን ነው የሚመለከተው። ምክንያቱም ይህ ብሎግና እንዲሁም ግብርአበሮቹ እንዲሁም ጽሑፎቹ ከእውነት የተጣሉ እውነትን የማይናገሩ የሀሰት አባት በላያቸው ነግሶ ሐሰትን የሚያውጁ ተሳዳቢዎች ሥም አጥፊወች ደም አፍሳሾችና መጣጮች ከሀዲዎች የዋጃቸውን ክርስቶስ የከዱ አሉባልታ አናፋሾች በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚዘሩ የመከባበር ጠላቶች የተማር ምናምን እያሉ በሥጋዊ ሀሣብ በቤተክርስቲያን አገልጋዮች ውሥጥ መከፋፈልን ለመፍጠር ሌት ተቀን የሚዳክሩ ማስተዋል የራቃቸው ሐሳባቸውና ምኞታቸው ምድራዊ የሆኑ ግብዞች የቅን ፍርድን የማያደርጉ ካለ እረፍት ወንጀልን የሚያደርጉ ከሳሾች በመሆናቸው ነው።ይገርማል የነ ግፉዓን ነን ባዮቹ ገፊዎች ምንም አይነት የኦርቶዶክስ እምነትና የወንጌል ትምህርት የሌላቸው ናቸው። ምክንያቱም በአሮጊቶች ተረት ወግ የተጠመዱ ምንም አይነትየመንፈሳዊነት ሽታ የሌለባቸው ሥለሆነ ነው። ለምሣሌ "ምላጭ ቢታመም በምን ሊበጡት ቄስ ቢያጠፋ በምን ሊቀጡት" አሉ አበው ሲሉ ተረትን ጥቅሥ አድርገው በማቅረብ አላዋቂነታቸውን አንፀባርቀዋል። ካህን ወይም ቄስ ካጠፍ በንስሐና በቀኖና ይቀጣል ጥፋቱ ይነገረዋል። ካህን ይከበራል ለተባለው አዎ ይከበራል። ምክንያቱም መንፈሳዊ አባቶች ናቸውና አባትህን አክብርም ተብሎ ተጽፏልና ። እንዲሁም የሚያገለግል በሁሉም ይከበራልና ነው። ምንም እንሿን የክርስቶስና የቤተክርሥቲያን አሳዳጆች ክፉ ሥራ ሁሉ የዕለት ተለት ተግባራቸው ቢሆንም በማህበረ ቅዱሳን ላይ የሚከፍቱት የደም ማፍሰስ ዘመቻ በጣም ያሥገርማልም ያሳዝናልም። ይህ ክፉ ብሎግና ፀሐፊዎቹ እጆቻቸው ማህበሩን ለማጥፋትና የአባላቶችን ደም ለመምጠጥ በውሸት መንፈስ ሽምጥ ይጋልባሉ። ይህ ሁሉ ተንኮል መንፈሳዊነት ሳይሆን አለማዊነት ጽድቅ ሳይሆን ሀጢያት ነው። በዚህ ብሎግ አንድም የወንጌል ትምህር ጽሑፍ ቀርቦቦት አያውቅም ከሠይጣናዊ የጽሑፍ መልክት ውጭ። ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ በአን ግለሠብ ምክንያት ጳጳሱ የመንፈስ ስብራት ሊገጥማቸው ይችላል መባሉ ነው። በርግጥ አካሔዳችሁ ሌላ ቢሆንም አንድ የቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አባትና መሪ በሥሩ ባለ አገልገይም ሆነ ግለሰብ ጥፋትም ሆነ ሥህተት የመንፈስ ስብራት የሚገጥማቸው ከሆነ መንፈሳዊ አባትም መሪም ናቸው ለማለት አሥቸጋሪ ነው። በእርግጥ በልጆቻቸው ሊያዝኑ ይችላሉ እንዳባትነታቸውና እንደቤተክርስቲያን መሪነታቸው ደግሞ ያጠፋውን መገሰፅና እንዲመለሥ መምከር እምቢ ያለውን ደግሞ በቤተክርሥቲያኒቷ ህግ መሠረት መለየት ነው። የቤተክርስቲያኒቷን አባት በመቅለሥለሥ በማባበልና አዛኝ ወዳጅ በመምሠል መግቢያ ፍለጋ የምትዳክሩትን አይሠሟችሁምና አተድከሙ መንፈስ ቅዱስ አባቶችንና ቤተክርስቲያንን ከመሠሪዎች የጥፋት የተንኮል አካሔድ ይጠብቃልና። በመጽሐፍ የተመረጡትን እንሿን እሥኪያሥቱ ታላላቅ ነገርን እንሿን ያደርጋሉ ተብሎ እንደተጻፈ እናንተም የቤተክርሥቲያኗን አባትና አገልጋዮችን ለማሳሳት አንዱን እያነሳችሁ አንዱን እየጣላችሁ ብዙ የጥፋት ተግባሮችን በመተግበር ቀጥላችኋል። እግዚአብሔር ይመልሳችሁ።

  ReplyDelete