Tuesday, January 6, 2015

“ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና።” ሉቃ. 2፥11እንኳን ለጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ እንላለን፡፡ ይህን የደስታ መግለጫ መልእክት ለውድ የአባ ሰላማ ብሎግ አንባቢዎች ስናስተላልፍ መልእክታችን በባህላዊ መንገድ ለሚከበረው የገና በዓል እንኳን አደረሳችሁ ከማለት ያለፈ መሆኑን ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ መልእክታችን እንኳን ክርስቶስ ተወለደላችሁ፡፡ ክርስቶስ በመወለዱ እንኳን ደስ አላችሁ ወደሚለው ያዘነበለ ነው፡፡

እንደ ክርስቲያን በዚህ በዓለ ልደት የደስታችን ምክንያቱ የክርስቶስ መወለድ እንጂ ሌላ ሊሆን አይገባውም፡፡ ክርስቶስ በተስፋ ሲጠበቅ የነበረው ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድናቸው መድኃኒት መሆኑ በመልአኩ በኩል በዚያች ሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ ለነበሩ እረኞች ተበሥሯል፡፡ ብሥራቱ ለእረኞቹ የጠላለፈ ቢሆንም ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለሕዝቡ ሁሉ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤” እንዳለ መልአኩ፡፡
የተወለደው ክርስቶስ ጌታ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው የሚያድን፣ ሰውንና እግዚአብሔርን በሞቱ የሚያስታርቅ፣ በኃጢአት ምክንያት በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የገባውን ጥል የሚያስወግድ ብቸኛ ሊቀ ካህናትና መሥዋዕት ነው፡፡ በዓለ ልደቱን በየዓመቱ ስናከብር ይህን እውነት ማእከል አድርገን ካልሆነ ግን እንደ ከሰርን ነው የሚቆጠረው፡፡ ስለዚህ በበዓለ ልደቱ የተነገረው የምሥራች ወደ ውስጣችን ዘልቆ ሊገባ፣ የተወለደው ክርስቶስ መድኃኒታችን፣ ጌታችንና አምልካችን መሆኑን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ማመን ይገባናል፡፡ በእርሱ መምጣትና ሰው ሆኖ መወለድ የልብ ዕረፍትና ሰላም ሊሰማንም ይገባል፡፡ እነዚህ ነገሮች ለእያንዳንዳችን ካልደረሱልንና “የክርስቶስ በዓለ ልደት” በሚል ብቻ በዓሉን በመብልና በመጠጥ ፌሽታ ብቻ የምናከብር ከሆነ ግን የክርስቶስ መወለድ ለእኛ ምንም ትርጉም አይኖረውም፡፡ መልአኩ ካበሠረን ብሥራት በእጅጉ ተራርቀናልና ስለዚህ ልናስብበት ይገባል፡፡

ልብ እንበል፤ በዓለ ልደቱን ስናስብ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን እጅግ ዝቅ አድርጎ የመጣው እኛን ለማክበርና ከወደቅንበት ለማንሣት ነው፡፡ ይህም ፍጻሜ ያገኘው ኃጢአታችንን ተሸክሞ በመሠዋት በተከናወነ የማዳን ሥራው አማካይነት ነው፡፡ በመወለዱ የተበሠረው ታላቅ ደስታና የምሥራች በመሰቀሉና በመሞቱ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱም ተፈጽሟል፡፡ ክርስቶስ ስለኃጢአታችን እንዳዳነን ካላመንንና እንደዳንን በእምነት ካልቆጠርን ልደቱን “ተወለደ” እያልን ብለን ብቻ በየዓመቱ ማክበራችን ትርጉም የለውም፡፡ የተወለደው መድኃኒት ነው ተብሎ እንደተነገረ መድኃኒትን ያደረገልን የእኛን ዕዳና በደል ተሸክሞ በመሞቱና ሞትን ድል አድርጎ በመነሣቱ ነውና የኃጢአት ዕዳችን ወደተከፈለበት መጽደቃችንም ወደታወጀበት ወደ ሞቱና ወደ ትንሣኤው መመልከትና ሞቱንና ትንሣኤውን ለእኛ እንደተደረገልን ማመንና መዳን አለብን፡፡ ልደቱ ይዞልን የመጣው የምሥራችም ይኸው ነውና፡፡     
በዓለ ልደቱን ስናስብ የምናመልከውም ሆነ የምናከብረው ሌላ አካል መኖር እንደሌለበት ከሰብአ ሰገል እንማራለን፡፡ ሰብአ ሰገል እንዳደረጉት ስጦታችንንም ሆነ ስግደታችንን ለተገባው፣ ጌታና መድኃኒት ለሆነው ለክርስቶስ ብቻ ነው ማቅረብ ያለብን፡፡ እንደሚታወቀው የተወለደውን ሕፃን ለማየትና እጅ መንሻን ለማቅረብ በኮከብ ተመርተው ከሩቅ ምሥራቅ የመጡት እነዚህ የጥበብ ሰዎች የኮከቡን በተወለደበት ስፍራ መቆም አይተው እጅግ ደስ አላቸው፡፡ ወደቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ጋር አዩት፡፡ ነገር ግን ለተወለደው ሕፃን ብቻ ወድቀው ሰገዱለት፡፡ ለእርሱም ብቻ ሰጥናቸውን ከፍተው ወርቅ ዕጣንና ከርቤም አቀረቡለት፡፡ ከዚህ ውጪ ተከፋፍሎ የማይቀርበውን ስግደት በአክብሮትና በጸጋ ስም ለእናቱ አላቀረቡም፤ ስጦታም አልሰጡም፡፡ “ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።” (ማቴ. 2፥11)፡፡ ስለዚህ በኹለንተናችን ወደክርስቶስ ብቻ መመልከት እርሱንም ብቻ ማሰብ፣ ለእርሱም ብቻ መዘመር፣ ለእርሱም ብቻ መገዛት አለብን፡፡
ይህ በዓለ ልደቱን ስናከብር ብቻ ሳይሆን በማንኛውም መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ላይ ልንከተለው የሚገባ አርኣያ ነው፡፡ መመለክ ያለበት እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሊሰገድለት የሚገባው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሊዘመርለት የሚገባው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ማኅሌት ሊቆምለት የሚገባው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሊቀደስ ሊወደስ የሚባው እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሊሰበክ የሚገባው እርሱ ብቻ ነው፡፡ የፍቅራችን መግለጫ የሆኑ ልዩ ልዩ መባዎች ሊቀርቡ የሚገባቸው በእርሱ ስም ብቻ ነው፡፡ እርሱ ብቻ ጌታ ነው፡፡ እርሱ ብቻ አዳኝ መድኃኒት ነው፡፡ ከእርሱ በቀር ሌላ የለም፡፡ ስለዚህ በክርስቶስ በዓለ ልደት ክርስቶስን ብቻ እናንግሥ፡፡ ሁሉን ለእርሱ ክብር ብቻ እናድርግ፡፡     
  መልካም በዓለ ልደት ይሁንላችሁ

2 comments:

 1. ብቻ
  የሚል ቃል ቢነገር መልካም ነበር
  ቃሉ እሙን ነው ምስክርነቱም ስለ ህፃኑ መሆኑ
  ክብር ለሚገባው ምስጋናም ሊቸረው ለሚገባው በእርሱ ክብር ለሆነው የተከለከለ አድርጎ ቃሉ ምስጢርን እንደሰነዘረ አድርጎ በዚህ መልኩ ማስረፅ ፍፁም
  አፅራረ ምልክታን አጉልቶብዎ ታይቶአል

  እባክ ዎ
  ስለ ክርስቶስ ኢየሱስ መመስከር መስበክ ፡ ክብር የሚገባውን መንደፍ መንቀፍም ማለት አይደለምና ይህን ድንቅ ምስክርነት
  በእውነትና በእርሱ መንፈሱ ይባርኩት ይባረኩበት

  ReplyDelete
 2. እንክርዳድ አትርጩJanuary 13, 2015 at 10:33 PM

  የመሳት ድሪቶ ሲደራረት።
  ማንበብም ተችሏል፤ ጥቅሶችም ለመዳን ሳይሆን ሌላውን ለማደናገር ተጠቅሰዋል፤ እንደ መልካም ሰውም የእንሿን አደረሳችሁ መልክት ተላልፏል በውስጡ ገዳይ
  መርዝ ቢኖርበትም፤ ስለልደቱና በልደቱ ዕለትም
  የተከናወኑ ነገሮች ተዘርዝረዋል ሚስጥሩና የተከናወኑት
  ነገሮች መሠረታዊ መነሻቸው ምን እነደሆነ አልተገለጠምና
  አልተብራም እንጂ ምክንያቱም አነበቡት እንጂ አላወቁትምና ነው፤ ብቻ በዚህ የክህደትና የሰህተት ድሪቶ
  ብዙ የፊደል ዝብርቅርቅ ክምችቶች ታጭቀዋል። ለመሆኑ
  ሰባ ሰገል ከሩቅ ምስራቅ ተነስተው በዳዊት ከተማ በቤቴል ከከብቶች ግርግም የተገኙትና የተወለደውን ህፃኑን ከእናቱ
  ጋር የአዮትና ወድቀው ሰግደውም እጂ መንሻ ያቀረቡለት
  ከምን የተነሳ ነው? እናንተ የኦርቶዶክስ እምነት የሌላችሁ
  የክርስቶስ ቤተክርስቲያንም ጠላቶች ናችሁና
  አትመልሱትም። ምክንያቱም በአጭሩ ምንም አይነት
  የክርስቶስ ወንጌል እውቀት የላችሁምና ነው። መጽሐፍንና
  የእግዚአብሔርን ነገር አታስተውሉምና ትስታላችሁ
  እንደተባለው። ነገሩ ሰባ ሰገል በረሃ አቋርጠው ቤተልሔም የተገኙት አንደኛ የተነገረው ትንቢት ይፈፀም ዘንድ ነው። ሁለተኛ የአቀረቡለት መስዋትና የሰገዱለት ስግደትም ሁሉም ሚስጢርና ምሳሌነት አላቸው። እናንተ ግን በከንቱ የምትመፃደቁ ባዶ ግብዞች ናችሁና ያልተፃፈ ብቻ የሚል ቃል ተጠቅማችሁ ክዳችሁና ስታችሁ ለማሳት ዳክራችኋል። ይችን "ብቻ" ቃል ፈጥራችሁ ተጠቅማችሁ ሳነብ አንድ ጊዜ "አሴምብልስ ኦፍ ጎድ" የተባለ ጎተራ ወሎሰፈር መሔጃ በስተቀኝ ቁልቁለቱን ወርዶ ወንዙ አጠገብ የሚገኝ የኘሮቴስታንት አዳራሽ ይገኛል እናም በዚህ አዳራሽ በእርዳታ ስም የተታለሉና እዛ እርዳታ ለመቀበል ሲሉ ብቻ የሚሔዱ አንድ የቤተሰብ አባሎችን አውቃለሁ። ቤታቸው አንዴ ተገኝቸ ቀላል አማረኛ በሚል የታተመ የአዲስ ኪዳን መጽሐፍ ቅዱስ አየሁና አንስቸ ገልበጥ ገልበጥ እያደረግሁኝ መመልከት ጀመርኩ። ከዛም 1ኛጢሞ 2 ፤ 5ትን መመልከት ስጀምር አንድ እግዚአብሔር አለ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለ መካከለኛ የሆነ ደግሞ አንድ አለ… ይላል። እናም መካከል ከሚለው ፊትለፊት በቅንፍ " አማላጂ " የሚል ቃል ተጽፎ ተመልክቻለሁኝ። መናፍቃን ለክሄደታቸው ለመጠቀም የሌለን ቃላት ያስገባሉ ሚስጢሩን ወይም ትርጉሙን ጠይቆ ከመማርና ከማወቅ ። ለመሆኑ ይህ ብሎግ ሰባ ሰገል ለህፃኑ ብቻ እያለ የሚዘባርቀው ህፃኑ ብቻውን ነበር እንዴ የተኛውን? ካሉስ እንዴትና በየት በኩል?እጂ መንሻውንስ ለህፃኑ ብቻ ስትሉ ህኑ ወርቁን ሃብል ወይስ የእጁ ቀለበት ሊያደርገው ነውን? ብሩስ ምን አየነት ብር ነው ? የጌጥ ወይስ የመገበያያ ገንዘብ ነውን? የመገበያያ ነው ካለችሁ ምን ሊገዛበት ነው? የጌጥ ብር ነው ካላችሁ ደግሞ ምኑን ሊያጌጥበት ይሆን? ከርቤውንስ ምን ሊያደርገው ይሆን? ደግሞስ ቃል የተወለደው በምድር ላየ በስጦታ በልጽጎ በአለም ቁሳቁስ ሊያጌጥ ነውን? እናንት የጨለማ ሰራዊቶች የእውነት ጠላቶች ምን ይሆን የምትሉት? ድንግል ማርያም የካህኑ የዘካሪያስን ሚስት ቅድስ ኤልሳቤትን በጎበኘቻት ጊዜ የጌታየ እናት ወደኔ ትመጭ ዘንድ እንዴት ይሆናል አንች ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ ብላ አመሰገነቻት በማህፀኗም ያለው ዮሐንስ የድንግልን ድምጽ በሰማ ጊዜ በደስታ ዘለለ ነው ያለችው። ታዲያ ኤልሳቤት ያመሰገነቻችትን እናንተ ተከፋፍሎ የማይሰጥ እያላችሁ ክህደትና ስተትን ለምን ታራግባላችሁ? ለመሆኑ በማህፀኔ ያለው ጽንስ የሠላምታሽን ድምፅ በሰማ ጊዜ በደስታ ዘለለ ማለት ለእናንተ ምን ይሆን? ዘለለ ማለት በማህፀን ውስጥ እንጣጥ እንጣጥ አለ ማት ነውን ለእናንተ? ለእኛ ግን አባቶቻችን አመስጥረው ለአምላክ እናት በደስታ ሰገደ ማለት እንደሆነ አስተምረውናልና በደስታ የአክብሮት የፀጋ ስግደት ለድንግል ሰገደ ማለት ለው። ደግሞስ እራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን የፀጋ ስግደት መስገድ በእሱ ዘንድ የተወደደ ስለመሆኑ በራእይ ዮሐ 3፤ 9ኝ ላይ አይሁድ ሳይሆኑ አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማህበር አንዳንዶችን እሰጥሀለሁ እነሆ መጥተውም በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደወደድሁ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ ሲል አረጋግጧል። ሌላው የሚገርመው ልዮ ልዮ ስጦታዎቻችን ሁሉ ለሱ ብቻ ነው መሆን የሀ የለበት ይላል ይሔ ብሎግ። ምን ማለት ነው?እንዴትና የት? እሱ ወርዶ ይሆን በሻንጣ ሞልቶ ተሸክሞት የሚሔደው? ደግሞስ እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል ነው እኮ ያለው አምላካችን። ለነዚ ለአንዱ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል ነው እኮ ያለው። ወንጌሉ መነገርና ያለበት ሁሉ ለእሱ ብቻ ይባልልኛል። አይ ክህደት። አዎ ቅዱሳን የሀ የደረጉትም ሲነገር ክርስቶስ ነው የሚሰበከው። ክርስቶስ እንዲህ አለ ወንጌል በሚሰበክበት ሁሉ ይች ሴት ያደረገችው ይነገራል ብሎ ቅዱሳን ለክርስቶስ ቅዱሳን በክርስቶስ ያደረጉትና የሠሩት ወንጌል በሚነገርበት ሁሉ መናገር ተገቢ እንደሆነ ተረጋግጦልናል። ምክንያቱም ቅዱሳኑ ሲነሱ ክርስቶስ ይከብራልና ነው። ጭራሽ በባህላዊ መንገድ ተባለልኝ። ተቀጠለና እኛ ግን ከዛ በዘለለ ተባለና እራስ ተኮፈሰልኝ። አይ ግብዝነት፣ አይ አለመማር፣ አይ አለማውቅ፣ አይ ጨለምተኝነት። እግዚአብሔር በእውነት ልባችሁን ይመልሰው። ይሁዳን የተመኘው ሰላሳ ብር ምን ጠቀመው በሰላምታ ቀርቦ አምላኩን አሳልፎ ሰጥቶ ታንቆ ሞተ እንጂ። ለእናንተስ የነጮች ገንዘብ ከምድራዊ ደስታ ውጭ ምን ሊያተርፋችሁ ነው እንዲህ እውነትንና ክርስቶስን የምታሳድዱ? ምንስ ይጠቅማችኋልና ነው የእግዚአብሔርን ቃል የምታጣምሙና የምትሸቃቅጡ? የፈረንጆች የገና አከባበርስ በእናንተ እይታ እንዴት ይሆን?ለማንበብ አጓጓለሁ። ደግሞ የተዋህዶን የአምልኮት ሥርዓት እየጠቀሳችሁ ሰዓታቱ ፣ ኪዳኑ ፣ ቅዳሴው ለሱ ብቻ ብላችኋል። እምነት ስለሌላችሁ አልተገለጠላች አልተረዳችሁትም እንጂ ቤተክርስቲያናችን በሁሉ ነገሯ ክርስቶስን የምትሰብክ የክርስቶስ ናት። ለምሳሌ ቤተክርስቲያን ተሠርቶ በአንዱ ቅዱስ ስም ሲጠራ "በቤቴና በቅጥሬ የማይጠፋ የዘላለም መታሰቢያን እሰጣችኋለሁ" ያለውን ከመናገር ባለፈ በተግባር ትሰብካለች። እናንተ አላችሁ እንጂ ለሚጠፋ ለምድራዊ ድሎት የእግዚአብሔርን ቃል የምትሸቃቅጡ። ይሁዳ አምላኩን በሰላምታ አሳልፎ ሰጠው። እናንተ ደግሞ በእንሿን አደረሳችሁ እንክርዳድ ኩርንችታችሁን ትበትናላችሁ። አይ አለማወቅ። እግዚአብሔር ይቅር ይበላችሁ።

  ReplyDelete