Thursday, January 29, 2015

አስተያየት መቀበል የተሳናቸው ጳጳሳት መጨረሻቸው ምን ይሆናል?የዘንድሮው የጥቅምት ወር ሲኖዶስ ከወሰናቸው ውሳኔዎች መካከል አንዱ በተራ ቁጥር 19 ላይ ተይዞ በነበረው አጀንዳ ውስጥ በሥርዋፅ የገባውና ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በቅርቡ ያሳተመው “ስማችሁ የለም” የሚለው መጽሐፍ ጉዳይ እንደሚገኝበት በቅርብ ጊዜ ከወጣ አንድ ጽሑፍ ላይ ሳነብ እጅግ ነው የተገረምኩት፡፡ ሲኖዶሱ እጅግ ወርዶና ተዋርዶ “ ‘ስማችሁ የለም’ የሚለው በዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተጻፈው መጽሐፍ በሊቃውንት ጉባኤ ታይቶና ተመርምሮ መልስ እንዲዘጋጅለት ሲል በአንድ ድምጽ ተስማምቶ ወስኗል፡፡” ሲል የቃለ ጉባኤው ውሳኔ ያስረዳል፡፡ ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር ማለት እንዳለብኝ በጣም ተሰምቶኛል፡፡ ለግንዛቤ እንዲረዳ “ስማችሁ የለም” በሚል ርእስ የቀረበውን የዲ/ን ዳንኤል ክብረትን ጽሑፍ ቀጥሎ ላቅርብ፡፡ ከዚያ ወደ ጽሑፌ አገባለሁ፡፡ስማችሁ የለም
በሰማያዊው ዙፋን ዘንድ አንድ ውሳኔ ተላለፈ፡፡ «እነዚህ የኢትዮጵያ ሰዎች ሃይማኖተኞች ናቸው፡፡ ስለዚህም ዓለም ከማለፉ በፊት አስቀድመው ተጠርተው ዋጋቸውን ሊቀበሉ ይገባል» የሚል፡፡ አንድ ሊቀ መልአክ እልፍ አእላፍ መላእክትን አስከትሎ ከሰማይ ሲወርድ ታየ፡፡ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሰዎችንም ሁሉ ለሰማያዊ ፍርድ ሰበሰባቸው፡፡

ወዲያውኑ በመንግሥተ ሰማያት በር ላይ ሁለት ዓይነት ሰልፎች ታዩ፡፡ አንደኛው ሰልፍ ረዥም፤ ሌላኛው ሰልፍ ግን አጭር ነበር፡፡ ረዥሙ ሰልፍ ባለበት ቦታ ገበሬዎች፣ ወዛደሮች፣ የዕለት ሥራ ሠራተኞች፣ እናቶች፣ አባቶች፣ ሕፃናት፣ ሊስትሮዎች፣ የቤት ሠራተኞች፣ ሾፌሮች፣ መሐንዲሶች፣ ሐኪሞች፣ አስተማሪዎች፤ ማን ያልተሰለፈ አለ፡፡ ከጥቂቶቹ በቀር ብዙዎቹ መንግሥተ ሰማያት የመግቢያ ካርድ ማግኘት ቻሉ፡፡

ይህንን ሁኔታ ሲመለከቱ በአጭሩ ሰልፍ በኩል የተሰለፉት የልብ ልብ ተሰማቸው፡፡ መጀመርያውኑ ለብቻቸው ሰልፍ የሠሩት ከሕዝብ ጋር ላለመደባለቅ እና ላለመምታታት ብለው ነበር፡፡ እንዴት ሲያስተምሩት፣ ሲያስመልኩት፣ ሲያስሰግዱት፣ ሲያሳልሙት፣ ከኖሩት ሕዝብ ጋር አብረው ይሰለፋሉ? መጀመርያ ነገር እነርሱ ያስተማሩት ሕዝብ መንግሥተ ሰማያት ከገባ እነርሱ የማይገቡበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ወደፊትም ቢሆን በመንግሥተ ሰማያት ለየት ያለ የክብር ቦታ ሊጠብቃቸው ስለሚችል ለየት ብለው መሰለፋቸው ተገቢ ነው፡፡ ይህንን እያሰቡ እና እያወሩ እያለ አንድ መልአክ ወደ እነርሱ ሰልፍ መጣ፡፡

ተሰላፊዎቹ በኩራት ገልመጥ ገልመጥ አሉ፡፡ እንዲያውም «ከመካከላችን ማን ይሆን ቀድሞ የሚገባው» የሚለው ነገር ሊያጨቃጭቃቸው ነበር፡፡ አንዳንዶች በተከታዮቻቸው ብዛት፣ አንዳንዶች በነበራቸው መንፈሳዊ ሥልጣን፣ አንዳንዶች ባገኙት የካሴት እና የመጽሐፍ ገቢ፣ ሌሎችም በሕዝቡ ዘንድ በነበራቸው ተደናቂነት፣ የቀሩትም ደግሞ በንግግር እና በድምጽ ችሎታቸው እየተማመኑ እኔ እበልጣለሁ እኔ እቀድማለሁ ሲባባሉ መልአኩ «እናንተ እነማን ናችሁየሚል ያልተጠበቀ ጥያቄ ጠየቃቸው፡፡


ሁሉም መልአክነቱን ተጠራጠሩት፡፡ አገር ያከበራቸውን፣ ሕዝብ ያረገደላቸውን፣ እነርሱን ለማየት እና ለመንካት አዳሜ የተንጋጋላቸውን፣ በየፖስተሩ፣ በየካሴቱ፣ በየመጽሐፉ፣ በየመጽሔቱ «ታዋቂው» እየተባሉ ሲቀርቡ የኖሩትን፤ ሰይጣን ያወጣሉ፣ መንፈስ ይሞላሉ፣ ጠበል ያፈልቃሉ፣ እየተባሉ ሲያርዱ ሲያንቀጠቅጡ የኖሩትን፤ ሲዘምሩና ሲያስተምሩ ወፍ ያወርዳሉ የተባሉትን፤ ገንዘብ ከፍሎ መንፈሳዊ ቦታ ተሳልሞ ለመምጣት ሕዝብ ቢሮአቸውን ደጅ ሲጠናቸው የኖሩትን እነዚህን ጉምቱ ጉምቱ ሰዎች የማያውቅ መልአክ እንዴት ሊኖር ቻለ? ተጠራጠሩ፡፡

«ለምንድን ነው ለብቻ ሰልፍ የሠራችሁት? ለምን ከሕዝቡ ጋር አልተሰለፋችሁምመልአኩ ይበልጥ የሚገርም ጥያቄ አመጣ፡፡ ተሰላፊዎቹ እርስ በርሳቸው ተያዩ፡፡ ከመካከል አንድ በነገሩ የተበሳጨ ሰባኪ «እንዴት እንደዚህ ያለ ጥያቄ በዚህ በመንግሥተ ሰማያት በር ላይ እንጠየቃለን፤ እስካሁንም ተሰልፈን መቆየት አልነበረብንም፡፡ እኛን ለመሆኑ የማያውቅ አለ? ስንት ሕዝብ ያስከተልን ሰባክያን፤ ስንት ሕዝብ የፈወስን አጥማቂዎች፣ ስንት ሕዝብ ያስመለክን አስመላኪዎች፣ ስንቱን ያስረገድን ዘማሪዎች፤ ስንቱን የታደግን ፈዋሾች፣ ስንቱን የመራን የእምነት መሪዎች፤ ስንቱን በባዶ እግሩ ያስኬድን ባሕታውያን፤ ስንቱን ለገዳም ያበቃን መነኮሳት፤ ሕዝብ ተሰብስቦ የሾመን «ሐዋርያት» እንዴት እነማን ናችሁ ተብለን እንጠየቃለንሁሉም በጭብጨባ ደገፉት፡፡

መልአኩ «መልካም፤ የስም ዝርዝሩን ላምጣውና ስማችሁ እዚያ ውስጥ ካለ ትገባላችሁ» ብሎ አንድ ትልቅ ሰማያዊ መዝገብ ይዞ መጣ፡፡ «እኛ ካልተጻፍን እና የኛ ስም ከሌለ ታድያ የማን ስም በዚህ መዝገብ ውስጥ ሊኖር ነው፡፡ ይኼው እኛ የማናውቀው ሰው ሁሉ እየገባ አይደለም እንዴአለ አንድ አስመላኪ በንዴት፡፡ «ልክ ነህ፤ እናንተ የማታውቁት፣ ፈጣሪ ግን የሚያውቀው፤ እናንተንም የማያውቅ ፈጣሪውን ግን የሚያውቅ ብዙ ሕዝብ አለ ወዳጄ» አለው መልአኩ መዝገቡን እየገለጠ፡፡

«የሁላችሁንም ስም ማስታወስ ስለምችል ሁላችሁም ስማችሁን ንገሩኝ» አላቸው፡፡ ከወዲህ ወዲያ እየተንጫጩ ስማቸውን ከነማዕረጋቸው ነገሩት፡፡ መልአኩ ከፊቱ ላይ የኀዘንም የመገረምም ገጽታ ይነበብበታል፡፡ ቀስ እያለ የስም ዝርዝሩን ያይና ገጹን ይገልጣል፤ ያይና ገጹን ይገልጣል፤ ያያል፣ ገጹን ደግሞ ይገልጣል፡፡ ብዙ ገጾችን ገለጠ፣ ገለጠ፣ገለጠ፤ ማንንም ግን አልጠራም፡፡ ከዚያ ይባስ ብሎ የመጨረሻውን የመዝገቡን ሽፋን ከቀኝ ወደ ግራ መልሶ ከደነው፡፡ «ምንም ማድረግ አይቻልም፤ የማናችሁም ስም መዝገቡ ላይ የለም» ብሎ መልአኩ በኀዘን ሲናገር «ምንየሚል የድንጋጤ ኅብረ ድምጽ ተሰማ፡፡ «የማናችሁም ስም ወደ መንግሥተ ሰማያት ከሚገቡት ሰዎች ዝርዝር ውስጥ የለም» አለ መልአኩ በድጋሜ፡፡

«ሊሆን አይችልም» «የተሳሳተ መዝገብ ይዘህ መጥተህ እንዳይሆን» «ወደ ሲዖል የሚገቡትን መዝገብ ይሆናል በስሕተት ያመጣህው» «እኛኮ አገልጋዮች ነን፤ የከበረ ስም እና ዝና ያለን፤ ስንኖርም፣ መድረክ ላይ ስንቀመጥም፣ ድሮም ልዩ ነን፤ የኛ መዝገብ ልዩ መሆን አለበት» «እስኪ ሌላ መልአክ ጥራ» ብቻ ሁሉም የመሰለውን በንዴት እና በድንጋጤ ይሰነዝር ጀመር፡፡ ሌሎች መላእክትም ሌሎች ዓይነት መዝገቦችን ይዘው መጥተው እያገላበጡ ፈለጉ፡፡ የነዚያ «የከበሩ አገልጋዮች» ስም ግን ሊገኝ አልቻለም፡፡

«እኛኮ የታወቅን ነን» አሉ አንድ አጥማቂ፡፡ «ሕዝብማ ያውቃችሁ ይሆናል መዝገብ ግን አያውቃችሁም» አላቸው መልአኩ፡፡ «እንዴት እኮ እንዴት? » አሉ በዋና ከተማዋ ታዋቂ የነበሩ ፓስተር፡፡ «ሊሆን አይችልም፤ ፈጽሞ ሊሆን አይችልም» አሉ አንድ ሼሕ፡፡ «የዚህን ምክንያት ማወቅ ትፈልጋላችሁ? » አለ አንዱ መልአክ፡፡ «አዎ» የሚል ኅብረ ድምጽ ተሰማ፡፡

«ምክንያቱኮ ቀላል ነው፡፡ ሌሎችን መንፈሳዊ እንዲሆኑ ታስተምሩ ነበር እንጂ እናንተ መንፈሳውያን አልነበራችሁም፡፡ እናንተ ድራማ ስትሠሩ ነውኮ የኖራችሁት፡፡ መድረክ ላይ ወጥታችሁ መንፈሳዊ ድራማ ትሠሩ ነበር፡፡ ልብሳችሁ፣ንግግራችሁ፣ የእጅ አጣጣላችሁ፣ ጸሎታችሁ፣ የተዋናይ ነበርኮ፡፡ የማትሆኑትን ነበር ስታስተምሩ የነበራችሁት፡፡

ለመሆኑ ለሕዝቡ የምታስተምሩትና እናንተ የምትመሩበት የሃይማኖት መጽሐፍ አንድ ነው? ወይስ ይለያያልእናንተ የምድር ቤታችሁን በብዙ ብሮች እየገነባችሁ ሰዎች ግን ቤታቸውን ረስተው የሰማዩን ቤት ብቻ እንዲያስቡ ታስተምሩ ነበር፤ ሕዝቡን ስጡ ስጡ እያላችሁ እናንተ ግን አምጡ አምጡ ትላላችሁ፡፡ ሕዝቡን በባዶ እግሩ እያስኬዳ ችሁ እናንተ የሚሊዮኖች መኪና ትነዱ ነበር፤ ሕዝቡን እያስጾማችሁ፣ እናንተ ግን ጮማ ትቆርጡ ነበር፤ ታስተምሩት የነበረውኮ ያጠናችሁትን ቃለ ተውኔት እንጂ የምታምኑ በትን እና የምትኖሩትን አይደለም፡፡ እናንተኮ ግብር የማትከፍሉ ነጋድያን ነበራችሁ፡፡ እናንተ ከገዳም ወደ ከተማ ትገባላችሁ፤ ሰውን ግን ከከተማ ወደ ገዳም ትወስዳላችሁ፡፡

እርስ በርሳችሁ እንደ ውሻ እየተናከሳችሁ ለማስተማር እና ለመዘመር ሲሆን፣ ለማስመለክና ለማሰገድ ሲሆን፣ የአዞ እንባ እያነባችሁ መድረክ ላይ ትወጣላችሁ፡፡ እርስ በርሳችሁ ከበርሊን ግንብ የጠነከረ የመለያያ ግንብ እየገነባችሁ ሕዝቡን ግን አንድ ሁኑ፣ ተስማሙ፣ ታቻቻሉ እያላችሁ ታስተምራላችሁ፡፡ ለመሆኑ ይህ ሁሉ ፓስተር፣ ሰባኪ፣ ዘማሪ፣ መነኩሴ፣ ባሕታዊ፣ ዑላማ፣ አሰጋጅ፣ አስመላኪ፣ የእምነት አባት፣ እያላት ነው ኢትዮጵያ እንዲህ ስሟ በድህነት እና በጦርነት የሚነሣውሙስና እና የዘመድ አሠራር፣ ጠባብነት እና ዘረኛነት፣ ስግብግብነት እና ማጭበርበር፤ ክፋት እና ምቀኛነት የበዛው ይኼ ሁሉ አገልጋይ እያላት ነውለመሆኑ እናንተ ባትኖሩ ኖሮ ይህች ሀገር ከዚህስ የከፋስ ምን ትሆን ነበር?

ለመሆኑ ተከፋፍላችሁ፣ ተከፋፍላችሁ፣ ተከፋፍላችሁ መጨረሻችሁ ምንድን ነውለመሆኑ አንድ ባትሆኑ እንኳን ለመግባባት፤ ለመገነዛዘብ፤ ቢያንስ ላለመጠላላት፤ ቢያንስ በጠላትነት ላለመተያየት፤ ላለመወጋገዝ፤ ላለመነቃቀፍ አስባችሁበት ታውቃላችሁ? የሀገራችሁ ፖለቲከኞች እንኳን የሥነ ምግባር ደንብ ይኑረን ሲሉ እናንተ ለመሆኑ የሥነ ምግባር ደንብ አላችሁሻማ ሲበራ ዋናው ጨለማ ከሻማው ሥር ነው የሚገኘው፡፡ ሌላውን ታበራና ሻማዋ ለራሷ ጨለማ ትሆናለች፡፡ እናንተስ? በየቤተ እምነታችሁ ያለውን ችግር መቼ ፈታችሁ ነው ሕዝብ እናስተምራለን የምትሉትለናንተ ሁልጊዜ ጠላታችሁ ሌላ እምነት የሚከተለው ብቻ ነውለራሳችሁ ግን ከራሳችሁ በላይ ጠላት የለውም፡፡ ሕዝቡኮ አንዳችሁ ሌላውን ስትተቹ፤ አንዳችሁ በሌላው ስትሳለቁ፤ አንዳችሁ በሌላው ላይ ነጥብ ስታስቆጥሩ፤ አንዳችሁ የሌላውን ኃጢአት ስትዘረዝሩ መስማት ሰልችቶት ነበር፡፡

«ታድያ እኛ ያስተማርነው ሕዝብ እንዴት ጸደቀ? » የሚል አንድ ድምጽ ተሰማ፡፡

«ሕዝቡማ ምን ያድርግ በምትናገሩት እናንተ አልተጠቀማችሁም እንጂ ሕዝቡማ ተጠቀመበት፡፡ ሕዝቡማ በሁለት መንገድ ተጠቀመ፡፡ እናንተን እያየ «እንደነዚህ ከመሆን አድነን» በማለቱ ተጠቀመ፤ የምትሉትን እየመዘነ በማድረጉም ተጠቀመ፡፡ እንደ እናንተ ቢሆን ኖሮማ ማን ይተርፍ ነበር፤ አጫርሳችሁት ነበርኮ፡፡ የዚህ ሕዝብ ጉብዝናው ይሄ አይደል እንዴ፤ ሙዙን ልጦ መብላቱ፡፡ ሲገዛው ከነልጣጩ ነው፤ ሲበላው ግን ልጦ ነው፡፡ የእናንተንም ትምህርት የሰማው መላጥ ያለበትን ልጦ እየጣለ ነው፡፡

እናንተ ለዚህች ሀገር መድኃኒት ነበራችሁ፡፡ ነገር ግን ጊዜው እንዳለፈበት መድኃኒት በሽታዎቿ ሆናችሁ፡፡ የሚከተል እንጂ የሚድን፤ የሚያደንቅ እንጂ የሚለወጥ፤ የሚያወቅ እንጂ የሚሠራ፣ የሚመስል እንጂ የሚሆን መች አፈራችሁሕዝቡን የናንተ ተከታይ አድርጋችሁት ቀራችሁ፡፡ ያንን ጠባያችሁን ይዛችሁ እዚህ ከገባችሁ ደግሞ የገባውን ታስወጡታላቸሁ ተብሎ ይፈራል፡፡

የሚያለቅሱ ድምጾች እየበረከቱ መጡ፤ አንገታቸውን ያቀረቀሩት ብዙዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹን ፀፀቱ ያንገበግባቸው ነበር፡፡ ሌሎቹም ራሳቸውን ጠሉት፡፡

«አሁን ምንድን ነው የሚሻለን» አሉ አንድ ፓስተር፡፡

«የዚህን መልስ እኔ መስጠት አልችልም፤ ፈጣሪዬን ጠይቄ መምጣት አለብኝ» አለና መልአኩ ትቷቸው ሄደ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ሲመለስ እንዲህ የሚል መልስ ይዞ ነበር፡፡

«አንድ እድል ይሰጣችሁ፡፡ ትስተካከሉ እንደሆነ አንድ እድል ይሰጣችሁ፡፡ ሕዝቡን ተውትና ራሳችሁን አስተካክሉት፤ ያኔ ሕዝቡ በራሱ ጊዜ ይስተካከላል»

ድንገት ሁሉም መሬት ላይ ተገኙ፡፡ እነሆ አሁን በየቤተ እምነቱ ያሉት በዚህ መንገድ የተመለሱት ናቸው፡፡

ጳጳሳቱ “ስማችሁ የለም” በሚል ርእስ የቀረበው ይህ ጽሑፍ ምናቸውን ነክቶ ይሆን የቤተ ክርስቲያንን ሃይማኖታዊ ጉዳዮች እንዲያይ፣ እንዲመረምርና ለውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ የተሠየመውን የሊቃውንት ጉባኤ እንደግል ተላላኪ በመቁጠር ምላሽ ይስጥልን ለማለት የተነሣሡት? ለእንዲህ ዓይነቱ ራስን መመልከቻና ማስተካከያ ጽሑፍ ምላሽ ለመስጠት መነሣት በራሱ ትክክለኛ ነገር ነወይ? ከጳጳሳትስ ይህ ይጠበቃል ወይ?

በቅድሚያ እንዲህ ዓይነት ሒሳዊ ጽሑፎች ራስን ለመመልከትና ለማስተካከል የሚረዱ በመሆናቸው በዚህ ጽሑፉ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ሊመሰገን ይገባል እንጂ ምላሽ ይሰጠው የሚልና ቅዱስ ሲኖዶስን የሚያነጋግር አጀንዳ መሆን አልነበረበትም፡፡ ማነጋገር ካለበትም ብዙዎቻችን ዲ/ን ዳንኤል እንደ ጻፈው ነንና ራሳችንን እንዴት እናየዋለን? እነዚህን የምንመራቸው ምእመናን የታዘቧቸውን የሕይወታችንን መሠረታዊ ችግሮች እንዴት ማስተካከልና ለመንጋው ምሳሌ መሆን እንችላለን? ተብሎ በአዎንታዊነቱ ተወስዶ መነጋገር ነበረባቸው፡፡ ራሳቸውን ለማስተካከል ያልታደሉትና በሹመት ያገኙትን ብፅዕናና ቅድስና በኑሮ ወይም በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ባፈሩት ፍሬ እንዳገኙት ብፅዕናና ቅድስና የቆጠሩት ጳጳሳት ግን እኛ ብፁዓን አባቶች እንዴት እንዲህ እንባላለን በሚል በዓለም እንኳ ተደርጎ የማይታወቀውን ራስን ንጹሕ አድርጎ የማቅረብ አዝማሚያ ነው ያሳዩት፡፡ በዓለም ፖለቲከኞች በተለይም ሥልጣን ላይ በወጡት በየጊዜው በየጋዜጣውና በየመጽሔቱ ልዩ ልዩ ትችቶች የግለሰቦች ስም እየተጠቀሰ ጭምር ይጻፋል፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ ፖለቲከኞች እንዴት እንዲህ እንባላለን በሚል ምላሽ ይሰጥልን ሲሉ አይታይም፡፡ እንዲህ ያለው አስተያየት ራሳቸውን እንዲመለከቱና ስሕተታቸውን እንዲያርሙ በቀጣይም ከስሕተት እንዲጠበቁ የሚያደርጋቸው ስለሆነ በአዎንታዊነቱ ነው የሚወስዱት፡፡ 

የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በዘመናቸው ስማቸው እየተጠቀሰ ልዩ ልዩ ፎቷቸው ጭምር እየተለጠፈ በርካታ ነገር ሲጻፍባቸው የከሰሱትም ሆነ የወቀሱት ጋዜጠኛ ስለ መኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ይህ የሚያሳየው ሰዎች በነጻነት አስተያየታቸውን መስጠት የሚችሉ መሆናቸውንና አስተያየቱ የሚሰጠን ሰዎች ደግሞ አስተያየቱን ተቀብለን ራሳችንን ማስተካከል ያለብን መሆኑን ነው፡፡ አሁን ያሉት የሲኖዶስ አባላት ግን ለዲ/ን ዳንኤል ክብረት ጽሑፍ ምላሽ ለመስጠት የተነሳሱት ታዲያ ለምን ይሆን? ዳንኤል የጻፈው እነርሱ ያልሆኑትን ነውን? ደግሞም የጻፈው የኦርቶዶክስ ጳጳሳትን ብቻ ጠቅሶ ሳይሆን የሁሉንም ሃይማኖት መሪዎችና ግንባር ቀደሞችን አስመልክቶ ነው፡፡ ሌሎቹ ሒሳቸውን ውጠው ዝም ያሉበትን ጉዳይ የእኛዎቹ አባቶች ምላሽ ይሰጥልን ማለታቸው፣ ጳጳሳቶቻችን በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዴት ባሉ ጳጳሳት እየተመራች እንዳለች ጭምር የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱን ውድቀት ያመለክታል፡፡

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የጻፈው ሃይማኖታዊ ነገርን አይደለም፡፡ ግለሰቦችን የተመለከተ ነው፡፡ በዚያ ላይ በስም የጠቀሰው አንድም ጳጳስ የለም፡፡ ታዲያ የቀረበውን ሂስ በተመለከተ የሲኖዶስ አባላት አጀንዳ አድርገው ሲወያዩበት እንዴት ይህን አላስተዋሉም? እንዴትስ አላፈሩም? ጵጵስናን ከሕግ በላይ መሆኛና ያለመከሰስና ያለመወቀስ መብትን መጎናጸፊያ አድርገው ስለወሰዱት፣ በሌላም በኩል የቤተክርስቲያንን አገልጋዮች በትንሹም በትልቁም በሚረባውም በማይረባውም ሃይማኖታዊ በሆነውም ባልሆነውም ማውገዣ ሥልጣን አድርገው እንደሚጠቀሙበት አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ሐቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ በዚህ በሠለጠነ ዘመን እጅግ የወረደ ማንነት ያላቸው ተራ ሰዎች የሚሠሩት ተራና ወራዳ ተግባር እንጂ በሃይማኖት መሪዎች ደረጃ ከቶም የማይታሰብ ነው፡፡

የሊቃውንት ጉባኤ ምላሽ የሚሰጥበት ምክንያትስ ምንድን ነው? የሲኖዶስ አባላት ብዙ ጊዜ ሃይማኖታዊውን ጉዳይ ሃይማኖታዊ ካልሆነው ሌላ ጉዳይ ጋር የማደበላለቅ ሁኔታ ይታይባቸዋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የእነርሱ ስም በዚህ መንገድ ቢተች ነገሩ እንዴት ሃይማኖታዊ ይሆናል? ትልቁ መጠየቅ ያለበት ጉዳይ እነርሱ እንደተጻፈው ናቸው? ወይስ አይደሉም? የሚለው ነው፡፡ ምላሹን ደግሞ እነርሱ ሳይሆኑ የሚመለከታቸው ሕዝብ ነው መስጠት ያለበት፡፡ ዲ/ን ዳንኤልም በዚህ መንገድ ነው ትዝብቱን ያሰፈረው፡፡ እነርሱ እንደ ተጻፈው አለመሆናቸውን ማሳየት ያለባቸው ተላላኪያቸው ላደረጉት የሊቃውንት ጉባኤ መልስ እንዲያዘጋጅ ትእዛዝ በመስጠት ሳይሆን ሕዝቡን በትክክል እየመሩትና እያሰማሩት መሆናቸውን በተጨባጭ በማሳየት ነው፡፡ መልስ ይሰጥልን ማለታቸው በራሱ ትክክል አለመሆናቸውን እንጂ እውነተኛነታቸውን አያሳይም፡፡ ይህም ጳጳሳቶቻችን በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ቤተክርስቲያን የምትመራውም እንዲህ ባሉ አባቶች መሆኑ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ ጋኖች ሁሉ ዐልቀው ምንቸቶች ጋን በሆኑበት ዘመን ላይ እንደምንገኝም ያመላክታል፡፡ ለማንኛውም የዳንኤል ምናባዊ ጽሑፍ ጳጳሳቱን ያስቆጣቸውና ምላሽ እንዲሰጥላቸው ግድ ያላቸው የጽሑፍ ክፍል ምን ይሆን? የሚለውን በሙሉ ሳይሆን በመጠኑ ለመመልከት እንሞክር፡፡

በእኔ እምነት የመጀመሪያው ነጥብ በምናባዊ ጽሑፉ ጳጳሳቱ በዚህ ምድር ትልቅ ስምና ስፍራ ይዘው ወደገነት የማይገቡ ሆነው መቅረባቸው ይመስለኛል፡፡ የጳጳሳቱን ብቻ ያነሣሁት በዚህ ጉዳይ ላይ ሂሳቸውን አልውጥ ብለው ያስቸገሩት እነርሱ ስለሆኑ ነው፡፡ በርግጥም ጳጳሳቱ አሁን በሚታየውና በሚሰማው መንገድ ኖረው መንግሥተ ሰማያት የሚገቡ ከሆነ አስገራሚ ነገር ነው የሚሆነው፡፡ ጌታ በወንጌል ስለጻፎችና ፈሪሳውያን እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።” (ማቴ 23፥13) ሲል የተናገረው ዛሬ በጳጳሳት ካልተተረጐመ በማን ሊተረጎም ነው? መንግሥተ ሰማያት እንደ እነርሱ ላሉት ሰዎች ቦታ ካላት በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ማመን፣ በእርሱ አምኖ ራስን አስጨንቆና አስጠብቦ ጽድቅን ለማድረግና ከኀጢአት ለመራቅ በሚደረገው ተጋድሎ ውስጥ ማለፍም አያስፈልግም፡፡ እንዲያውም ገበናን በልብሰ ጵጵስና ሸፍኖ ኃጢአትን እንደልብ እያደረጉ፣ የቤተ ክርስቲያንን ሀብትና ንብረት እየዘረፉና እያባከኑ በቅምጥልነት መኖር፣ ዘረኛነትን ማስፋፋት የወደዱትን መሾምና የጠሉትን መሻር፣ ለመከራና ለእንግልትም መዳረግ ሌላውም ተዘርዝሮ የማያልቅ አያሌ ግፍና መከራ የሚፈጽሙ ሰዎች ናቸው፡፡ ፈራጅ እርሱ አምላካችን በመሆኑ ፍርዱን ለእርሱ መተው ቢገባም የሚታየውን ኑሯቸውንና ሕይወታቸውን ለተመለከተ ግን ዳንኤል እንዳለው ብዙዎቹ በሰዎች እንጂ በሰማያዊው መዝገብ የማይታወቁ መሆናቸውን ለመገመት አይከብድም፡፡

ሌላው ጳጳሳቱን ያስቆጣው ነጥብ ነው የምለው “ ሌሎችን መንፈሳዊ እንዲሆኑ ታስተምሩ ነበር እንጂ እናንተ መንፈሳውያን አልነበራችሁም፡፡ እናንተ ድራማ ስትሠሩ ነውኮ የኖራችሁት፡፡ መድረክ ላይ ወጥታችሁ መንፈሳዊ ድራማ ትሠሩ ነበር፡፡ ልብሳችሁ፣ ንግግራችሁ፣ የእጅ አጣጣላችሁ፣ ጸሎታችሁ፣ የተዋናይ ነበርኮ፡፡ የማትሆኑትን ነበር ስታስተምሩ የነበራችሁት፡፡” የሚለው ይመስለኛል፡፡ ታዲያ ይህ ሐሳብ ምን ሐሠት አለበት፡፡ ለዓለም ሞተናል ያሉት ጳጳሳት ከማንም በላይ በዓለማዊነት የሚኖሩና በዚህም ወደር ያልተገኘላቸው አይደሉምን? ከዚህ በላይ ድራማ ምን አለ! መንኩሰናል ጰጵሰናል ብለው በልብሰ ጵጵስና ውስጥ ቅድስናቸውን ጥለው ከዓለማዊ በባሰ ሕይወት የሚገኙት ጳጳሳት በርካታ አይደሉምን? ከዚህ በላይ ድራማ ምን አለ! ታዲያ መንግሥተ ሰማያት የጵጵስና ገጸ ባሕርይን ለብሰው ሲተውኑ የኖሩት የሚገቡባት ሳትሆን እውነተኛ ጳጳሳት ሆነው የተገኙ የሚወርሷት ርስት አይደለችምን? ስለዚህ ጳጳሳት ሆይ በአደባባይ የሚታይና ከማንም ስውር ያልሆነውን ገበናችሁን ለመሸፈን አትሞክሩ፤ ከዚያ ይልቅ እባካችሁ ራሳችሁን ተመልከቱ! ሒሳችሁን ዋጡና የተጨመረላችሁን ቀሪ የንስሐ ዘመን መንፈሳዊ ፍሬ አፍሩበት፡፡ አሊያ አንድ ቀን ትጠሩና በእውነተኛውና ልታታልሉት በማትችሉት ዳኛ ፊት ትቆማላችሁ፤ ያን ጊዜ ምላሻችሁ ምን ይሆን? ዳንኤል በምናባዊ ጽሑፉ እንዳስነበበን ክርክር ያለ እንዳይመስላችሁ፡፡ አስፈሪ የሆነው ፍርድ ግን አለ፤ ብዙ ከተሰጠው ብዙ ይፈለጋልና ብዙም ያጠፋ ብዙ ይገረፋልና ለሁሉም ብዙ ዕዳ አለባችሁና ዕዳችሁን በንስሐ ዛሬ ብታወራርዱና ለንስሐ የሚገባ ፍሬን ብታፈሩ ያ መልካም ነው፡፡ አታምኑበትም እንጂ የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአት ሁሉ ያነጻችኋል፡፡ ስለዚህ ንጹሕ ነን የሚለውን ክርክራችሁን አቁሙና ራሳችሁን ተመልከቱ፤ የት እንዳለችሁ አስቡ፤ ንስሐ ግቡ፤ ጵጵስና ትልቅ እዳ እንጂ ወደ መንግሥተ ሰማያት የመግቢያ ካርድ አይደለምና ራሳችሁን አታታልሉ፡፡

ሌላው ጳጳሳቱን ያስቆጣው የሚመስለኝ “እናንተ የምድር ቤታችሁን በብዙ ብሮች እየገነባችሁ ሰዎች ግን ቤታቸውን ረስተው የሰማዩን ቤት ብቻ እንዲያስቡ ታስተምሩ ነበር፤ ሕዝቡን ስጡ ስጡ እያላችሁ እናንተ ግን አምጡ አምጡ ትላላችሁ፡፡ ሕዝቡን በባዶ እግሩ እያስኬዳ ችሁ እናንተ የሚሊዮኖች መኪና ትነዱ ነበር፤ ሕዝቡን እያስጾማችሁ፣ እናንተ ግን ጮማ ትቆርጡ ነበር፤ ታስተምሩት የነበረውኮ ያጠናችሁትን ቃለ ተውኔት እንጂ የምታምኑ በትን እና የምትኖሩትን አይደለም፡፡ እናንተኮ ግብር የማትከፍሉ ነጋድያን ነበራችሁ፡፡ እናንተ ከገዳም ወደ ከተማ ትገባላችሁ፤ ሰውን ግን ከከተማ ወደ ገዳም ትወስዳላችሁ፡፡” የሚለው የሰላ ትችት ነው፡፡ አሁን በዚህ ትችት ውስጥ ሐሰት የት አለ? ነገር ግን ለዓለም ሞቻለሁ ለሚል ጳጳስ እነዚህ ሁሉ የቅንጦት ነገሮች ተገቢ ነበሩን? በዚህ የተቀማጠለ ሁኔታ ውስጥ እየኖራችሁ ቅድሰናችሁን ትጠብቃላችሁ ብሎ ማን ሊያስብ ይችላል? አሁን ለዚህ አገር ላወቀው ፀሐይ ለሞቀው ኑሯችሁ ምን ማስተባበያ እንዲሰጥ ነው የፈለጋችሁት? መነኩሴ ጓዘ ቀላል እንዲሆን ህግ እያዘዘ እናንተ ግን በአንድም በሌላም መንገድ ከቤተክርስቲያን በወሰዳችሁት ገንዘብ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ ቪላዎችን እየገነባችሁ ስትሞቱ እንኳን ቤተክርስቲያን ወራሽ እንዳትሆን ለቤተሰቦቻችሁ ማውረስ የሚያስችላችሁን ሕግ በሲኖዶሳዊ ሥልጣናችሁ ስትደነግጉ ከቶ አላፈራችሁም እኮ! ለመሆኑ በድንግልና የመነኮስን ነን እናት አባታችንን እኅት ወንድማችንን ትተን ክርስቶስን ተከትለናል እያላችሁ ሀብትና ንብረታችሁን የምታወርሱት ዘመድ በየት በኩል አፈራችሁ? እናንተን እንዲህ እያንደላቀቀ የሚያኖራችሁን ሕዝብ በአግባቡ አልመራችሁትም፤ ሲባዝን አልፈለጋችሁትም፣ ሲሰበር አልጠገናችሁትም፤ ሲከሳ አላወፈራችሁትም፤ በለመለመው መስክ አላሰማራችሁትም፤ በእርሱ ከመጠቀም በቀር እርሱን አልጠቀማችሁትም፡፡ አይምሰላችሁ በዚህ አሳፋሪ ድርጊታችሁ ንስሐ ካልገባችሁ ስለበጎቹ ግድ የሚለው እውነተኛው የበጎች እረኛ የበጎቹን ደም ከእጃችሁ ይፈልገዋል፡፡ ያን ጊዜ ማስተባበያ መስጠት የለም፡፡ ስለዚህ ሂሱን ውጣችሁ ራሳችሁን ለማስተካከል ዛሬውኑ ተነሡ፡፡

ሌላው ጳጳሳቱን ሊያስቆጣ ይችላል ብዬ የማስበው ነጥብ “በየቤተ እምነታችሁ ያለውን ችግር መቼ ፈታችሁ ነው ሕዝብ እናስተምራለን የምትሉትለናንተ ሁልጊዜ ጠላታችሁ ሌላ እምነት የሚከተለው ብቻ ነውለራሳችሁ ግን ከራሳችሁ በላይ ጠላት የለውም፡፡ ሕዝቡኮ አንዳችሁ ሌላውን ስትተቹ፤ አንዳችሁ በሌላው ስትሳለቁ፤ አንዳችሁ በሌላው ላይ ነጥብ ስታስቆጥሩ፤ አንዳችሁ የሌላውን ኃጢአት ስትዘረዝሩ መስማት ሰልችቶት ነበር፡፡” የሚለው ነው፡፡ ይህም ሐሳብ ራሳችሁን ልትፈትሹበት የሚገባ ጠቃሚ ሐሳብ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በብዙ ውስብስብ ችግሮች ተጠላልፋ ትገኛለች፡፡ ለዚህ ሌሎች የቤተክርስቲያኒቱ አካላት የየራሳቸው ድርሻ ቢኖራቸውም ዋነኛው ተጠያቂዎች ግን እናንተው ናችሁ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከሕዝቡ በጣም ርቃችሁ ስለምትገኙ አገልጋዩንም ሆነ ሕዝቡን በሚገባ አላስተማራችሁትም፡፡ ለክብረ በዓላት እንደ መሶበወርቅ ተሸፋፍናችሁ ብቅ ብትሉም የሚረባና ለመዳኑ የሚጠቅመውን ነገር ሳታስተምሩት ሕይወት የማይገኝበትን ተረታተረቱን ተርታችሁለት፣ እርሱም ሲያልቅባችሁ ሌሎች እምነቶችን ወቅሳችሁና ከሳችሁ ነው ወንጌል ሰበክን የምትሉት፡፡ ይህ የየዋሁን ሕዝብ ትኩረት መሳቢያና አቅጣጫ ማስለወጫ ስልት  አድርጋችሁ የምትጠቀሙበት ያረጀ ዘዴያችሁ ነው፡፡

ቤተ ክህነት ውስጥ ብዙ ሙስናና ወንጀል እየተፈጸመ፣ ጥቂቶች የዓመፅን ትርፍ ያገኙ ዘንድ ብዙዎች ንጹሐንን እያንገላቱ መሆናቸውን እየሰማችሁና እያያችሁ፣ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት የጥቂቶች መክበሪያ መሆኑንም በሚገባ እያወቃችሁ ነገር ግን እናንተም ተቋዳሾች ስለሆናችሁ ምንም ዓይነት እርምጃ ባለመውሰዳችሁ ቤተክርስቲያን በሚያሳዝን ውድቀት ውስጥ ትገኛለች፡፡ እነዚህ ሁሉ ችግሮች እንዲወገዱና የቤተክርስቲያኗ መንፈሳዊ ጤንነት እንዲጠበቅ ቤተክርስቲያኗ በእግዚአብሔር ቃል መታደስ አለባት የሚለውን ጥያቄ ተቀብላችሁ ለቤተክርስቲያን በሚጠቅም መልኩ አዎንታዊ ምላሽ እንደመስጠት ተሐድሶን ጭራቅ አድርጋችሁ በመሳል ስትቃወሙት ትገኛላችሁ፡፡ የውስጥ ችግራችሁን ሸፋፍናችሁ የቤተክርስቲያን ስጋት ራሳችሁ መሆናችሁ እንዳይታወቅ ተሐድሶ የተባለው እንቅስቃሴ እንደሆነ አድርጋችሁ በስፋት ታስወራላችሁ፡፡ ለቤተክርስቲያን የሚበጀው እናንተ የያዛችሁት መንገድ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ዘመናት በልማድ የገቡትንና ሲሰራባቸው የኖሩትን እንደመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ያልሆኑትን ትምህርቶች፣ ሥርዓቶች፣ ልማዶችና ወጎች በእግዚአብሔር ቃል በማረምና በማሻሻል ቤተክርስቲያን እንድትታደስ ማድረግ ነው፡፡ በአንጻሩ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ለሚያስፋፉት አዋልድ መጻሕፍት የማያዳግም የማስተካከያ ርምጃ በመውሰድ እንዳለፈ ታሪካችን ብቻ እንዲታዩ አድርጎ ወደሙዚየም ማስገባት መፍትሔ ነው፡፡

አዋልድ ሙስናንና ብልሹ አሰራርን የሚያስፋፉት እንዴት ነው? የሚል ካለ በዐጭሩ መልስ ልስጥ፡፡ እንደሚታወቀው እነዚህ ልቦለድ ድርሰቶች ሰው እንዳሻው ኖሮ በቅዱሳን ስም ዝክር በመዘከሩና የተለያዩ ነገሮችን በመፈጸሙ እንደሚድን ተስፋ የሚሰጡ ናቸው፡፡ ይህ ስብከት ሕይወትን የሚቀይር ሳይሆን በኃጢአት እንድንገፋ የሚያበረታታ ነው፡፡ በላኤ ሰብ 78 ሰዎችን በልቶ በማርያም ስም በተዘከረው እፍኝ ውሃ የሚድን ከሆነ መንግስተ ሰማያት ውስጥ ሙስና አለ ብልሹ አሰራርም ሰፍኗል የሚያሰኝ ነው፡፡ ምክንያቱም ኃጢአትና በደል የሚወራረደው እንዲህ ባለው ርካሽ ተግባር ሳይሆን በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ነው፡፡ ነገር ግን ይህን እውነት ያልተረዳና የበላኤ ሰብን ታሪክ የሰማ ሰው ነገሩ እንዲህ ከሆነ እንዳሻኝ ልኑርና በማርያም ስም አንድ ነገር ላድርግ በማለት ኃጢአትን ለመሥራት መበረታታቱ አይቀርም፡፡ ሲኖዶሳችሁ እንዲህ ያለውን ልቦለድ ትምህርት ማረምና የቤተክርስቲያንን ስምና አገልግሎት መጠበቅ ሲገባው እየተሠራ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ ለቤተክርስቲያን መፍትሔ የሆነውን ተሐድሶን ከገፋችሁት ሳትታደሱ የምትቀሩት እናንተ ናችሁ እንጂ ሕዝቡ እየታደሰ መሄዱ አይቀርም፡፡ ይህን በምንም ተአምር ልትቀይሩት አትችሉም፡፡ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ከማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ደርሷልና፡፡ እንቅስቃሴው ቤተክርስቲያንን ጥሎ የሚሄድ ትውልድን ሳይሆን እዚያው ሆኖ ለቤተክርስቲያን መታደስ የሚተጋና የሚከፈለውን ዋጋ  የሚከፍል ትውልድን እየቀረጸ ነው፡፡ ስለዚህ የማያዋጣውን መንገድ ትታችሁ ወደሚያዋጣው መንገድ ብትመለሱና ስለተሐድሶዋ በተገቢው መንገድ ብትመክሩ እንቅስቃሴውንም እናንተው ብትዘውሩት ቤተክርስቲያን ከውድቀቷ ትነሣለች፡፡ ለብዙዎች በረከትም ትሆናለች፡፡ አሊያ በጀመረችው የቁልቁለት መንገድ ወደገደሉ መጣደፏ አይቀርም፡፡ ይህ ተራ ፕሮፓጋንዳ ሳይሆን እናንተም እያረጋገጣችሁት ያለ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ እንደሐዋርያው ቃል በልባችሁ መታደስ በመለወጥና ይህንን ዓለም ባለመመስል ቤተክርስቲያንን ከምትገኝበት ውስብስብ ችግር ነጻ ለማውጣት የችግሯ ሳይሆን የመፍትሔው አካል ትሆኑ ዘንድ ይገባል፡፡

በመጨረሻ ላይ ጳጳሳቱን አስቆጥቷል የምለውን ነጠብ ልጥቀስና ላብቃ ዳንኤል በምናባዊ ጽሑፉ ውስጥ ጳጳሳቱን እያነጋገረ ያለው መልአክ ሁሉም ሐዘንና ጸጸት ውስጥ መግባታቸውን አይቶ «አንድ እድል ይሰጣችሁ፡፡ ትስተካከሉ እንደሆነ አንድ እድል ይሰጣችሁ፡፡ ሕዝቡን ተውትና ራሳችሁን አስተካክሉት፤ ያኔ ሕዝቡ በራሱ ጊዜ ይስተካከላል» ያለው ጳጳሳቱን ሳያበሳጫቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም እኛ ብፁዓን ተብለን የምንጠራ የቤተክርስቲያን የበላይ አካል፣ ሕዝቡንም ማስተማርና መምራት ያለብን ሆነን ሳለ፣ ሕዝቡም አለቅጥ እያከበረንና እየተከተለን ሳለ እንዴት ተሳስታችኋልና ሕዝቡን ተስተካከሉ ማለታችሁን ትታችሁ ራሳችሁን አስተካክሉ እንባላለን ነው ነገሩ፡፡ እንዲህ የሚል ሰው መቼም ቢሆን ለመስተካከል ፈቃደኛ አይደለም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ጳጳሳቱ ከሥርዓቱ አንጻር ካልሆነ በስተቀር በሚሰማውና በሚታየው ማንነታቸው ሕዝቡን ለመምራትም ሆነ ለማስተማር ከሚችሉበት የሞራል ደረጃ ላይ ያሉ አይመስለኝም፡፡ ሕዝቡም የቤተክርስቲያኑን ወግ ለማክበርና ለመጠበቅ ብሎ እንጂ በእነርሱ ላይ የተፈጠረበት ጥያቄ ቀላል ነው ማለት አይደለም፡፡ ጳጳሳቱ ግን ይህ ሐቅ ተሸፋፍኖ ለምን አልቀረም? ለምን እንዲህ ተገልጦ ይጻፍብናል የሚል አቋም ነው የያዙት፡፡ በተሰጣቸው ዕድል ለመጠቀምና ራሳቸውን ለማስተካከል ፍላጎቱም ያላቸው አይመስልም፡፡ ታዲያ መጨረሻቸው ምን ይሆን?  እነርሱ የሚመሯት ቤተክርስቲያን ዕጣ ፈንታስ ምን ይሆን?

ከሁሉም በላይ የሊቃውንት ጉባኤ ዳንኤል ክብረት ያጎደፈውን ስማቸውን ለማደስ የሚሰጥላቸውን መልስ በጉጉት መጠበቁ አይከፋም፡፡ ግን ምን ይል ይሆን? ይህን እውነተኛ ነገር እንዴት ብሎ ነው ሐሰት ነው በማለት የሚያስተባብለው? መቼስ አላስተባብልም አይል እንጀራም አይደል? ከኅሊና ጋር እየተካሰሱ መኖሩ ግን አይቀርም፡፡

ልዑል እግዚአብሔር የሚወቀስና ለንስሐ የተዘጋጀ ልብ ለጳጳሳቱ፣ ማስተዋሉንም ለሊቃውንቱ ያድልልን!   


መ/ር አዲስ      
    

15 comments:

 1. Is that Written by Memihir Addis or Memihir Tehadiso?
  I read your article with sincere attention up to the mid of the session. You were telling Right. But After a while, you got into your TEHADISO stuff.
  By the way, the objection during the Sinodos Meeting comes ONLY from "ABA" SEREKEBIRHAN and not from our Real Fathers. So do not advice our Real fathers to become TAHADISO and renew our Beloved Church as you see the impact of being TEHADISO is to think blindly and irresponsibly like SEREKEBIRHAN.........KESASHU SEITAN

  ReplyDelete
  Replies
  1. For your information. The people who attend the synod are only arch bishops(papasat) therefor you comment doesn't make sence because aba sereke is not a papas. So the question was by members of the holy synod. And I dont think deacon daniel was worried or need to be concerned about it since his comment or article is not religion. You are probably one of those people who identify someone as tehadeso when he/she has an openion that differs from you. So when the end comes since you are always judging someone with out having any knowledge what so ever. The angel will tell you, your name is not on the list.

   Delete
  2. ስማ እናን ተ ማቆች ትንሽ ቆይታችሁ አዳር እንዴት ነበር ስትባሉ ምን እንቅልፍ አለ አባ ሰረቀብርሃን እንቅልፍ እንዳላይ እየከለከሉኝ ሳትሉ አትቀሩም። አበ ሰረቀ ብርሃን መቼ የሲኖዶስ አባል ሆነው ነው ዳንኤልን ሲኖዶስ ላይ የሚቃወሙት? ትንሽ ጭንቅላትህን ብታሰራው ጥሩ ነው

   Delete
 2. ዳንኤል ክብረትም በተሐድሶነት ተጠረጠረ ማለት ነዉ? ገና ብዙ እንሰማለን፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ምን ችግር አለዉ ?ዳንኤል ከአባ ሰረቀብርሐን ይበልጣል እንዴ?

   Delete
  2. የዳንኤል ጽሑፍ በአባ ሰላማ ድረ ገጽ ስለወጣ ዳንኤልን በተሐድሶ ተጠረጠረ አያሰኝም ወንድሜ። ይልቅ ከተሐድሶም የሚጠቅም ጽሑፍ ብታገኝ አንተም ተጠቀምበት።

   Delete
  3. What is wrong if Daniel restructure himself and become a reformist (Tehadeso)? It does not mean that he became a monster! It shows how dynamic he is and a sharp eye to see what you guys could not see or do not want to see. You are not concerned about the generation that Our church is going to loose because of incredibly shameful practices.

   Delete
 3. Mr. Addis, I think you didn't get the message What Dn Daniel Wrote. It is not about the bishops. He mentioned to all religious leaders, including you. Have you seen yourself, where are you? Are you among the poor who belonged to Heaven or to those who are dividing people, disseminating false messages, etc...

  ReplyDelete
 4. ሞኝን አንድ ጊዜ ስደበው ሲሰደብ ይኖራል ዝም ነውጂ እንዴት መልስ ይሰጥ ይባላል
  ጸሓፊው ተርትም ይሁን ቁም ነገር የጻፈውን ጽፏል ለመሆኑ የነገር ርቢ ምን ይጠቅማል አዬ ጉድ!
  ባለም ላይ ስንት ያሀማኖት መሪ አለ ሁሉ ቢነሣ ምድር ቁና አትሆንም እንዴ ከተቻለ ርማት መልካም ነው
  ራስን ማረም ካልተቻለ እንዲያው ዝም ነው የሚያዋጣው።

  ReplyDelete
 5. ሞኝን አንድ ጊዜ ስደበው ሲሰደብ ይኖራል ዝም ነውጂ እንዴት መልስ ይሰጥ ይባላል
  ጸሓፊው ተርትም ይሁን ቁም ነገር የጻፈውን ጽፏል ለመሆኑ የነገር ርቢ ምን ይጠቅማል አዬ ጉድ!
  ባለም ላይ ስንት ያሀማኖት መሪ አለ ሁሉ ቢነሣ ምድር ቁና አትሆንም እንዴ ከተቻለ ርማት መልካም ነው
  ራስን ማረም ካልተቻለ እንዲያው ዝም ነው የሚያዋጣው።

  ReplyDelete
 6. የሃይማኖት መሪ ሚባል የለም የሃይማኖት አጨበርባሪ እንጅ
  ቀሚስ ና ፈረጅያ ክርቫት ና ኩፍያ (ቆብ) አድራጊው ሁሉ ሌባ ነው

  ReplyDelete
 7. http://www.diretube.com/voa-news/pastor-tekest-is-accused-of-sexually-assaulting-married-woman-video_f5561cce5.html

  ReplyDelete
 8. I think Daniel hit the nail on the head. The issue is the religious leaders mentioned in the article ( be it sebaki, pastor or shek) are leading the people in the wrong direction. As Lord Jesus said " If a blind leads a blind...".

  ReplyDelete
 9. Daniel go Jame looks like gangster.

  ReplyDelete