Friday, January 9, 2015

ዕጹብ የገና ስጦታ፡- ‹‹ሰላም በምድር ይሁን፣ ለሰው ልጆችም በጎ ፈቃድ!››በዲ/ን ተረፈ ወርቁ
የሰላም ጉዳይ፣ የሰላም ወሬ የፍጥረት ሁሉ ናፍቆት ነው ብል ብዙም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ ሰላም ማለት የግጭት፣ የብጥብጥ፣ አሊያም የጦርነት አለመኖር ብቻ አይደለም ይላሉ የሥነ ልቦና ምሁራን፡፡ ሰላም በጦርነት፣ በጫጫታ፣ በኹከት፣ በመናወጥና በማይመች ሁኔታ ውስጥም ሆኖ እርጋታን፣ ውሳጣዊ ጸጥታን መላበስም ጭምር ነው ሲሉ መንፈሳዊ አንድምታ ያለው ትርጓሜ ይሰጡታል፡፡
በእርግጥም በነጋ ጠባ፣ የጦርነትና የእልቂት፣ የሥቃይ፣ የጩኸትና የጣር ድምጽ በሚሰማባት ዓለማችን፣ የሽብር ሥጋት ክፉኛ በሚንጣት ምድር ላይ እየኖርን ውስጣዊ የሆነ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም የማይናወጥና የማይደፈርስ ሰላም ይኖርን ዘንድ የግድ ይላል፡፡
እንዲህ ዓይነቱ ሰላም ምንጩ ከላይ፣ መገኛውም ሰማያዊና መለኮታዊ ነው ሲሉ የሃይማኖት ሊቃውንትና ምሁራን ከቅዱሳት መጽሐፍት ጠቅስው ያስረዳሉ፣ ይተነትናሉ፡፡ ዓለማውያኑንም ሆኑ በፈጣሪ መኖር የሚያምኑ ምሁራን ስለ ሰላም ምንጭ ያላቸው ትንታኔ ቢለያይም በአንድ ነገር አጥብቀው ይስማማሉ፡፡ እርሱም ሰላም ለሰው ልጆች ሁሉ አስፈላጊና መሰረታዊ መሆኑን!!

ሰላም ሰው ልጆች፣ ለፍጥረታት ኹሉ የዕለት ተዕለት ጥያቄ ከመሆኑ የተነሣ ለዓለማችን ሰላም ሲባል የተቋቋመውና ዋና ጽሕፈት ቤቱን በኒው ዮርክ አሜሪካ ያደረገው የመንግሥታቱ ድርጅትም በጽ/ቤቱ ፊት ለፊት ሰላምንና ስለ ሰላም የሚያዘክር አንድ ግዙፍ ሀውልት ቆሞ አለ፡፡ ይህ ሀውልትም አንድ ጎልማሳ፣ ጎበዝ ሰይፉን ወደ ምርት መሣሪያ ለመቀየር በመዶሻ ሲቀጠቅጥ የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ ሀውልትም ስርም የተቀረፀው ጽሑፍም እንዲህ ይነበባል፡-
"They shall beat their swords into ploughshares, and their spears into pruning hooks: nation shall not lift up sword against nation, neither shall they learn war any more.” “ስይፋቸውን ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፣ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሳም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም፡፡" (ኢሳ. ፪፣፬)፡፡
ግና አሳዛኙ እውነታ ጦርነትን እናውግዛለን የሚሉ የመንግሥታቱ ድርጅቱ ምስራቾችና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው ልእለ ኃያላኑ ሀገራት ሌሎች ሕዝቦች እርስ በርሳቸው የሚተላለቁበትን መሳሪያ በማምረትና በመሽጥ ተወዳዳሪ ያልተገኘላቸው መሆናቸው ነው፡፡ እነዚሁ አገራት ከፍተኛ በጀታቸውም የሚውለው ለጦር መሳሪያ ግዢና ምርት ነው፡፡ በአፋቸው ሰላም ሰላም ቢሉም በልባቸው ውስጥ ብርቱ ሰልፍና የጥፋት ሰይፍ እንዳለ በተግባራቸው እየገለጹ ነው፡፡
ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ፡- ". . . የሕዝቤን ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ ሰላም ሳይሆን፦ ሰላም ሰላም ይላሉ።" በማለት እንደተነበየው ስለ ዓለምና የሰው ልጆች ኹሉ ሰላም አብዝተው የሚጮኹ፣ አብዝተው የሚሰብኩ እነርሱ ራሳቸው የጦርነትንና የእልቂት ድግስን ደግስው ምድሪቱን የጭንቀትና የጣር ምድር እያደረጓት እንዳለን ብዙ ማስረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለአብነትም በኃያላኑ አገራት የኒኩሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት የመሆን ሕልም ዕውን መሆን በሌሎች እኛስ ከማን እናሳለን በሚሉ አገራት መካከል የፈጠረው ሥጋትና የኒኩሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት የመሆን ሩጫ ውድድር የሚነግረን ዘግናኝ ሐቅ ቢኖር በዓለማችን ላይ የተጋረጠውን ግዙፍ የሆነ የጦርነት አደጋ ነው፡፡ በየዕለቱ ከመገናኛ ብዙኃን እንደምንሰማውም በአገራት መካከል ያለው የጦር አውርድ ወሬና ዝግጅት የሰው ልጆችን የዕለት ተዕለት ኑሮ የሥጋትና ጭንቀት እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በዚህ በዛሬው ጽሑፌ ስለ ሰላም ጉዳይ ጥቂት ለማለት የወደድኩት በአንድ ምክንያት ነው፡፡ ይኸውም በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ መንፈሳዊና ባህላዊ ዝግጅቶች የሚከበረው፣ የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል/ገና ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም የተሰበከበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ ሰው ከአምላኩ፣ ሰው ከተፈጥሮ፣ ሰው ከራሱ ጋር ጠብ ውስጥ የነበረበት የጨለማ ዘመን ተሽሮ በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ለሰው ልጆች ኹሉ ሰላም የምስራች ተብሎ በመሰበኩ ነው፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት/የገና በዓል ለእኛ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ታላቅ የሆነ መንፈሳዊና ባህላዊ አንድምታ ያለው ትልቅ በዓል ነው፡፡ የበዓሉ መንፈሳዊ ምስጢር እንደ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናችን አባቶቻችን አስተምህሮ ከሰው ልጆች በኃጢት መውደቅ በኋላ፣ የልጅነት ክብሩንና ጸጋውን የተገፈፈውን የሰው ልጅ ወደቀደመ ክብሩ ለመመለስ ‹‹አምላክ ሰው የሆነበት፣ ሰውም አምላክ የሆነበት›› ድንቅና ዕጹብ የሆነ ሰማያዊ ምስጢር የተገለጸበት በዓል እንደሆነ ያትታሉ፡፡
ይህን ሰው አምላክ፣ አምላክም ሰው የሆነበትን ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊ ምስጢር የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት አባቶች እንዲህ ሲሉ ያመሰጥሩታል፡- ‹‹እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ የሰውን ልጅ ያዳነበት ወይም ሰውን ለማዳን አምላክ ሰው የሆነበት ጥበብ እጅግ ይጠልቃል፣ ይረቃል፣ ይሰፋልም፡፡›› ሲሉ በአድናቆትና በመገረም ይተርኩታል፡፡ የአገረ ብሕንሳው የቤተ ክርስቲያን አባት አባ ሕርያቆስም፣ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ቅዳሴው፡-
… ከአባቱ አጠገብ ሳይለይ ቃል ወደ አንቺ መጣ፡፡ ሳይወሰን ፀነሽው በላይ ሳይጎድል በታችም ሳይጨመር በማኅፀነሽ ተወሰነ፡፡ … ድንግል ሆይ እሳተ መለኮት በሆድሽ ባደረ ጊዜ ፊቱ እሳት፣ ልብሱ እሳት፣ ቀሚሱ እሳት ነው፡፡ እንደምን አላቃጠለሽ፣ ሰባት የእሳት ነበልባል መጋረጅ በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተዘጋጀ፣ ወዴትስ ተጋረደ ከጎንሽ በቀኝ ነውን፣ ወይስ ከጎንሽ በግራ ነውን፣ ትንሽ አካል ስትሆኝ፡፡ የሚያንጸባርቅ ነደ እሳት የሚከበው ኪሩቤል የተሸከሙት ዙፋን በሆድሽ ውስጥ ወዴት ተዘጋጀ፣ ወዴትስ ተተከለ፣ ታናሽ ሙሽራ ስትሆኚ፡፡ በማለት የኢየሱስ ክርስቶስን ሰው የመሆን ምስጢር አድንቋል፡፡
አባ ሕርያቆስ በዚሁ በእመቤታችን ቅዳሴው፡- ‹‹ኃያል ወልድን ለሰው ልጆች፣ ለፍጥረቱ ያለው ፍቅር ከዙፋኑ እንደሳበውና እስከሞትም እንዳበቀው፤›› ይተርክልናል፡፡ ይህ አባት በዚህ ድርሳኑም፡- ‹‹የማይደፈር ግሩም ነው፣ በእኛ ዘንድ ግን ትሑት ነው፣ የማይገኝ ልዑል ነው፣ በእኛ ዘንድ ግን አርዓያ ግብርን ነሣ፣ የማይዳሰስ እሳት ነው፣ እኛ ግን አየነው፣ ዳሰስነውም ከእርሱም ጋር በላን፣ ጠጣን፡፡›› ሲል እግዚአብሔር ከእመቤታችን ከድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ ዘመድ እንደሆነን አመስጥሯል፡፡
ለዚህም ነው የአገራችን አዝማሪ በዘለሰኛ ድንቅ ዜማው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው በመሆኑ ለእኛ ለሰው ልጆች የቅርብ፣ የሥጋ ዘመድ እንደሆነን በማመስጠር እንዲህ የተቀኘው፡-
አብን ተወውና ንገረው ለወልድ
ጥሎ አይጥልምና የሥጋ ዘመድ፡፡
አስቀድሞም ከክርስቶስ ልደት በፊት ፯፻ ዓ.ዓ. ገደማ የኖረው ‹‹ደረቅ አዲስን ተናጋሪ›› ተብሎ በቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ዘንድ የሚጠራው ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስም፡-
‹‹እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድም ልጅም ትወልዳለች፣ ስሙንም ኢየሱስ/አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች … ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ ሰላም አለቃ ይባላል፡፡›› ብሎ እንደተናገረ በይሁዳ ቤተ ልሔም የተወለደው ‹‹ኢየሱስ የሰላም አለቃ›› መሆኑን ተናግሯል፣ ሰብኳል፣ መስክሯልም፡፡ በይሁዳ ቤተልሔም የክርስቶስ ኢየሱስ መወለድን ተከትሎ መላእክት ከእረኞች ጋር በአንድነት ሆነው ስለ ሰላም መዘመራቸውን ሐኪሙና ታሪክ ጸሐፊው ወንጌላዊው ሉቃስ ደግሞ እንዲህ በወንጌሉ ዘግቦታል፡-
‹‹እነሆም፣ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፣ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፡፡ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ፡፡ መልአኩም እንዲህ አላቸው፡- እነሆ ለሕዝብ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፣ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ የሆነ ጌታ ተወልዶላችኋልና፡፡ … ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ፡፡ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን፣ ሰላምም በምድር፣ ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ፡፡››
ይህ ለሺህ ዘመናት በሱባኤ፣ በታላቅ ናፍቆትና ጉጉት ‹‹ይወርዳል፣ ይወለዳል›› ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የመሢሑ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ፣ አምላክ ሰው፣ ሰው አምላክ መሆኑ ለሰው ልጆች ኹሉ ታላቅ የምስራች ነው፡፡ የአጥቢያ ንጋት ከዋክብትም ከሰማይ መላእክት ሠራዊቶችና ከእረኞች ጋር በአንድነት መዘመራቸውንና ይህን ዕጹብ ድንቅ የሆነ ዘላለማዊ ደስታ ለመካፈል በይሁዳ ቤተልሔም ከትመው እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳናል፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ዕለት ሌሊት መንጋቸውን በሜዳ አሰማርተው ለነበሩ የይሁዳ እረኞች መላእክት በታላቅ ደስታ ውስጥ ሆነው ‹‹ሰላም በምድር ይሁን፣ ለሰውም በጎ ፈቃድ!!›› በሚል ታላቅ ሰማያዊ ዝማሬ ይህን ዘላለማዊና ፍጹም ሰላም ለሰው ልጆች ኹሉ አብስረዋል፡፡ በዚህ ታላቅና ዘላለማዊ እውነት መሠረትም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት/የገና በዓል በአገራችን በኢትዮጵያ በታላቅ ደማቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓትና ባህላዊ ዝግጅቶች በድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ወይም ገና በአገራችን ኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለውን መንፈሳዊና ባህላዊ አካባበሩን በተመለከተ ለዛሬ እምብዛም የምለው ነገር አይኖረኝም፡፡ ግና የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ለሰው ልጆች ኹሉ ሰላምና ፍቅር የተሰበከበት ታላቅ ዕለት መሆኑን በተመለከተ፣ ስለ ሰላም ባነሳሁት ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ጥቂት አሳቦችን ልጨምር፡፡
ይህን ጽሑፍ ሳዘጋጅ ከኹለት ዓመት በፊት በአፍሪካ ቀንድ ባሉ አገራት ያሉ ሃይማኖት አባቶች ሰላምን በማስፈን፣ ግጭቶችን በመፍታት፣ በአፍሪካ ቀንድና በአጠቃላይ በአፍሪካና በመላው ዓለም ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት እንዲሰፍን ያላቸው ሚና ምንድን ነው በሚል የተደረገ ኮንፈረንስ ትዝ አለኝ፡፡ እነዚሁ ከኢጋድ አባላተ አገራት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ‹‹IGAD Countries Religions Leaders Consultation on the Welfare of the Region›› በሚል መሪ ቃል የተካኼደ አኅጉራዊ ኮንፈረንስ ነበር፡፡
በዚህ በኬንያ ናይሮቢ በተደረገው ጉባዔ ላይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ን የመላው አፍሪካ ሊቀ ጳጳስ የኾኑት ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ፣ ‹‹Peace and the Human Race›› በሚል ርእስ ለጉባኤው ያቀረቡትን የጥናት ወረቀት ለማንበብ ዕድሉን አግኝቼ ነበር፡፡
ብፁዕነታቸው በዚሁ የጥናት ወረቀታቸው፡- ‹‹… ቤተ ክርስቲያን በዚህ ምድር ላይ ዋንኛ ተልዕኮዋ የሰላም አለቃ የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን መስበክ፣ በሰላም ማጣት፣ በግጭት፣ በጦርነት በምትታመሰው ምድር፣ በኹከትና በሽብር ሥጋት ለሚናጠው ዓለማችን ሰላምና ፍቅር የሞላበትን ቅዱስ ወንጌል፣ የምስራቹን ቃል ለሰው ልጆች ኹሉ ማዳረስ…፡፡›› እንደሆነ ይኸው የጥናት ወረቀታቸው ያትታል፡፡
በተጨማሪም ‹‹… የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በቀደመው ታሪኳ በሰው ልጆች ኹሉ መካከል ሰላምና ፍቅር የተሞላ ግንኙነት እንዲኖር ያስተማረችና፣ ሌላው ቀርቶ በሃይማኖት የማይመስሏትን ከመካከለኛው ምሥራቅ በሃይማኖት ጠብ ምክንያት የተሰደዱ የነቢዩ መሐመድ ተከታዮችን ያለ ምንም ልዩነት በሰላም ተቀብላ ያስተናገደች፣ የወንጌልን እውነት የሆነውን ሰላምን፣ ፍቅርን በቃልም በተግባርም የሰበከች ቤተ ክርስቲያን መሆኗን፡፡›› ይኸው የብፁዕነታቸው የጥናት ወረቀት ይጠቁማል፡፡
ምንም እንኳን ይህ የደመቀና ግዙፍ ታሪክ ያላት፣ በሰው ልጆች ኹሉ መካከል ሰላምን የሰበከች ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ያለችበት እውነታው አሳዛኝና ተገላቢጦሽ ቢሆንም፡፡ ‹‹በሰላም ማሰሪያ የመንፈስ አንድነትን ለመጠበቅ ትጉ፡፡›› ተብሎ በወንጌል ቅዱስ ቃል የተጻፈላቸው አባቶቻችን እርስ በርሳቸው ተከፋፍለውና ተለያይተው እንኳን ለዓለም ቀርቶ ለራሳቸው የሚሆን ሰላም ጠፍቷቸው የመንግሥታትንና የፖለቲከኞችን ደጅ የሚጠኑ ወደመሆን የመሸጋገራቸው ነገር ልብን የሚሰብር መሆኑ ሳይዘነጋ፡፡
በሰው ልጆች መካከል ሰላም እንዲሰፍን ታላቅ ሚና ያላቸው ሃይማኖቶች፣ ስለ ሰላም፣ ዕርቅና ፍቅር ማስተማር ኃላፊነት ያለባቸው የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች በተቃራኒው የጠብ፣ የግጭትና የጦርነት መንሥኤ ሲሆኑ በታሪክ ደጋግመን አይተናል፣ በቁጭትም ታዝበናል፡፡ በመሠረቱ ግን የክርስትና የሃይማኖት ሐዋርያና ሊቀ ካህናት የሆነው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጻሕፍት እንደተጻፈው፡- ‹‹ድንቅ፣ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አምላክ፣ አባትና የሰላም አለቃ ነው፡፡››
ስለሆነም የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች የሆኑ ኹሉ የሰላም አብሳሪዎችና የምስራች ቃል ሰባኪዎች ናቸው፡፡ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ሌሊት መላእክትና የሰማይ ሰራዊት ከእረኞች ጋር በአንድነት ሆነው፡- ‹‹ሰላም በምድር ይሁን ለሰው ልጆችም በጎ ፈቃድ!›› የሚለውን የምስራች በዜማ እንዳወጁ ኹሉ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ልደት በዓልም በክርስቲያኖች ኹሉ ዘንድ ይኸው በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን ያገኘነው ታላቅ፣ ፍጹምና ዘላለማዊ ሰላም ነው ሊነገር፣ ሊወራ፣ ሊዜም የሚገባው፡፡ ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሙሉ ሰላምና ፍቅር የተሞላ የልደት በዓል እንዲሆን በመመኘት ልሰናበት፡፡
ሰላም! ሻሎም!

4 comments:

 1. awdelday. bebelahibet ende jib techohaleh. frekersiki!

  ReplyDelete
  Replies
  1. አንተ ደግሞ ማን ነህ? እውነትና ጥሩ ነገር የማይወድልህ ማፈሪያ

   Delete
 2. ድንቅ ጽሁፍ ነው

  ReplyDelete
 3. As I informed you with the past, Aba yacob x wife will have moved to Atlanta including to there kids. Her lawyer notify to our office sent a letter for Aba yacob to corporate DNA test. That is the base point to prove he is bio father of this kids. Abaselama , can you send secret jurnails to Atlanta.

  ReplyDelete