Tuesday, February 24, 2015

የትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ዓዲግራት ሀገረ ስብከት ምእመናን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ላይ ላቀረብነው አቤቱታ ፍትሕ አጣን ይላሉ

Read in PDF 

የትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ዓዲግራት ሀገረ ስብከት ምእመናን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ላይ ላቀረብነው አቤቱታ ፍትሕ አጣን ይላሉ
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በዚህ ብሎግ ላይ ምንጮችን ጠቅሰንና ሰነዶችን አባሪ አድርገን በትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ዓዲግራት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአባ መቃርዮስ እየተፈጸመ ያለውን ሙስናና ብልሹ አሠራር ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ በጊዜው ለብሎጋችን ጭፍን ጥላቻ ያላቸው ሰዎች እንደተመለደው ሐሰት ነው እያሉ ለማስተባበል በመሞከር አስተያየት ሲሰጡ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ የዜናውን እውነተኛነት ግን ዜና ቤተክርስቲያንም ስላረጋገጠልን ያን የተሳሳተ አስተያየት ሲሰጡ የነበሩ ሰዎች አሁን አቋማቸውን ሊለወጡ እንደሚችሉ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ዜናው በዜና ቤተ ክርስቲያን ላይ የወጣው ችግሩ እስካሁን ሰሚ ባለማግኘቱና ባለመቀረፉ፣ እየተባባሰም በመሄዱ በአዲግራት ከተማ የሚገኙ የስድስቱ አድባራት አስተዳዳሪዎች ፊርማና የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ማህተም ያረፈበትን ደብዳቤ ዜና ቤተክርስቲያን ጋዜጣ በታኅሣሥና ጥር ወር እትሙ አውጥቶታል፡፡ ጋዜጣው “አቤት ባዮቹ በቃልና በጽሑፍ ያቀረቡልን ነገር ግን እኛ ለቤተ ክርስቲያን ክብር ስንል የዘለልናቸው ሌሎች የክስ ነጥቦችም አሉ፡፡” በማለት ከደብዳቤው ውስጥ ሳያትም ያስቀራቸው የክስ ነጥቦች መኖራቸውን ጠቅሷል፡፡
ይሁን እንጂ የቤተ ክርስቲያን ክብር የሚጠበቀው ነውርን በመሸፈን ሳይሆን ወደብርሃን በማምጣትና ንስሐ እንዲገባበት፣ አስተዳደራዊ የእርምት እርምጃም እንዲወሰድበት በማድረግ ይመስለናል፡፡ እንዲህ ካልሆነ ብዙዎች እንዲህ ካለው ስሕተት አይማሩም፤ እንዲያውም ሕገወጥ ሆኖ መኖር ሕጋዊነት እየመሰላቸው በጥፋታቸው ይገፉበታል፡፡ የሚታየውም እውነታ ይህ ነው፡፡ በእርግጥ ቤተ ክርስቲያኗ ጳጳሳት የቱንም ዓይነት ጥፋት ቢያጠፉ የማይከሰሱባትና ከሕግ በላይ የሆኑባት ስለሆነች ጋዜጣው የክስ ነጥቦቹን ቢያወጣም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በቤተክህነቱ በኩል የሚለወጥ ነገር ይኖራል ማለት አይቻልም፤ ምናልባት በአዘጋጆቹ ላይ ጥቃት ሊሰነዘርባቸው፣ ከእንጀራቸው ሊፈናቀሉ ይችላሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ግን እግዚአብሔር በፍርዱ ሲገለጥ አንድ ቀን መለወጡ አይቀርም፡፡ ለሁሉም የጋዜጣውን ጽሑፍ ከዚህ ቀጥሎ አቅርበነዋል፡፡    
የትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ዓዲግራት ሀገረ ስብከት ምእመናን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ላቀረብነው አቤቱታ ፍትሕ አጣን ይላሉ
ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለሁለተኛ ጊዜ አጣሪ ኮሚቴ ልኮ ውጤቱ እየተጠበቀ ነው
የትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ዓዲግራት ሀገረ ስብከት ምእመናን ተወካዮች ነን ያሉና አለአግባብ ከሥራ ታግደናል ደመወዛችን ተይዞ ብናል ከክህነት ማዕረጋችን ታግደናል ወዘተ የሚሉ ምእመናን ካህናትና ዲያቆናት በተለይ ለዜና ቤተ ክርስቲያን በሰጡት መግለጫ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ በምእመናንና በካህናት ላይ እያደረሱት ያለ አስተዳደራዊ በደልና እየተከተሉት ያለ የሙስና አሠራር ተጣርቶ መፍትሔ እንዲሰጠን ከጠየቅን የቆየን ቢሆንም እስከ አሁን መፍትሔና ምላሽ ባለማግኘታችን ጉዳዩ ከአቅማችን በላይ ሆኖብናል በማለት አስረድተውናል፡
                  የምእመናን ተወካይ መሆናቸውን በዓዲግራት ከተማ የሚገኙ የስድስቱ አድባራት አስተዳዳሪዎች ፊርማና የሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ማኅተም ያረፈበት “ለሚመለከተው ሁሉ” በሚል ርእስ መስከረም 4 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም የተሰጠ የውክልና ሥልጣን ማሳያ ደብዳቤ አሳይተውን ኮፒውንም ሰጥተውናል እነዚህም ተወካዮች፡-
መልአከ ብርሃናት ገ/እግዚአብሔር በረሀ
መምህር ስባጋዲስ ተስፋይ
አቶ ኃይሉ በረሀ
ዳያቆን ክፍሎም ገ/ዮሐንስ
መምህር ብርሃነ ገብረ ዮሐንስ ናቸው፡፡

እነዚህ የምእመናን ተወካዮችና የሀገረ ስብከቱን የሙስና አሠራር በመቃወማችን ከሥራና ከደመወዝ ታገድን ከሚሉ ሃያ ስድስት ካህናትና ዲያቆናት መካከል አምስቱ ቢሮአችን ድረስ መጥተው እንደነገሩን በሀገረ ስብከቱ የተከሰተው ችግር እንዲፈታ ለሚመለከታቸው አካለት አመልክተዋል፡፡ ለአብነት ያህል ይህንን ችግር በተመለከተ ለብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀደማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቀ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ባለፈው ዓመት ማለትም ሚያዝ 17 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም ማመልከታቸውን በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡
ምእመናኒ ለቅዱስ ፓትርያርኩ በጻፉትና ደረሰብን ያሉትን በደል በዝርዝር ካረቀቡዋቸው 16 ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ፡-
ሀ. ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የእህታቸውን ልጆች በሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ግቢ ድል ባለ ሰርግ ደግሰው ከመዳራቸውም በላይ የእታቸውን ልጅ ባል የሆኑትን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የእህታቸው ልጅን ሒሳብ ሹም አድርገው ሹመዋል፤ በዚህ የተነሣ የባንክ ሒሳቡን የሚንቀሳቀሰው (ቼክ የሚፈረመው) በብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የእህት ልጃቸው ባል በሆኑት ሥራ አስኪያጅና እና በእህታቸው ልጅ በመሆኑ አሠራሩ ሆን ተብሎ ለሙስና አሠራር ተመቻቸ መሆኑ፤
ለ. የወረዳ ሊቀ ካህናትና የደብር አለቆች የሚሾሙት በአስተዳደርና በችሎታ ብቃት እየተመዘኑ ሳይሆን በዝምድና እና በልዩ ቀረቤታ ከመሆኑም በላይ ማዕረግ የሚሰጠው በነፍስ ወከፍ ብር 7ዐዐ       (ሰባት መቶ ብር) እየተከፈለ መሆኑንና ይህ አሠራር ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ሕግ ውጭ መሆኑ፤
ሐ. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው መሠረት ለድቁና እና ክህነት ማዕርግ የሚከፈል ክፍያ የሌለ መሆኑ የታወቀ ሆኖ እያለ ብፁዕነታቸው ይህንን በመተው ለቅድስናና ዲቁና ማዕርግ በነፍስ ወከፍ ብር 5ዐ (ሃምሳ ብር) ማስከፈላቸው ሳያንሰ ሒሳቡ የሚሰበስቡበት መንገድ ሕጋዊ አሠራር ያልተከተለ መሆኑ፤
መ. ሁሉም ነባር አብያተ ክርስቲያናት ጽላት (ታቦት )እንዳላቸው እየታወቀ በቤታቸው ታቦት ቀራጭ በማስቀመጥ አዲስ ታቦት አስቀርጻችሁ ብር  10,ዐዐዐ (ዐሥር ሺህ ብር) በመክፈል እንድታስገቡ በማለት ተቦታት እንዲቀየሩ ማድረግጋቸው፡፡ ለምሳሌ ከ65ዐ ዓመታት በላይ ዕደሜ ያለው የደብረ መንክራት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን በዚህ መልክ በግድ አዲስ ታቦት እንዲያስገባ ተደርጓል፡፡ በዚህ የተነሣ ነባሩ ጽላት በቦታው ይኑር አይኑር ስለማይታወቅ ድርጊቱ በምእመናንና ካህናት ዘንድ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ማድረጉ፤
ሠ. በቅርቡ “ልማት” በሚል ከሁሉመ የአሕጉረ ስብከቱ አብያተ ክርስቲያናተ ከ2,ዐዐዐ - 12,ዐዐዐ (ከሁለት ሺሕ እስከ ዐሥራ ሁለት ሺሕ )ብር በግዴታ ማስከፈላቸው፤
ረ. ብፁዕነታቸው የገንዘብ ምንጩ ባልታወቀ በአዲግሪት ከተማ ብቻ የሦስት መሬት(ቦታ)ባለቤት መሆናቸው፤
ሰ. ብፁዕ አቡነ ሙሴ በጥረታቸውና በምአመንና ዘንድ በነበራቸው ከፍተኛ ተቀባይነት ለአረጋውያንና ወላጅ ላጡ ዕጓለ ማውታ ሕፃናት ማሳደጊያ ብለው በጠየቁት መሠረት መንግሥት ለሀገረ ስብከቱ ሰጥቶት የነበረው 15ዐዐ (አንድ ሺህ አምስት መቶ)ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ በብፁዕነታቸው ድክመት ቦታው ለታሰበለት ሥራ ሊውል ባለመቻሉ መንግሥት መልሶ ሊወስደው መቻሉ የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡
አቤት ባዮቹ በቃልና በጽሑፍ ያቀረቡልን ነገር ግን እኛ ለቤተ ክርስቲያን ክብር ስንል የዘለልናቸው ሌሎች የክስ ነጥቦችም አሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገረ ስብከቱ በበኩሉ ከቀረቡበት “ክሶች” መካከል ከሥራ ተባረሩ የተባሉትን በተመለከተ ለአዲግራት ከተማ ወረዳ ጽ/ቤት በ9/1/2007 በቁጥር 23/2ዐዐ7 ከጻፈው ደብዳቤ ለማየት እንደቻልነው አቶ ተስፋይ በረሀ እና አቶ ይርጋዓለም ተስፋይ ከሰበካ ጉባኤ የሥራ ኃላፊነትና ከምእመንነት አባልነት እንዲሰረዙ 2. ቄስ  ኃ/ጊዮርጊስ ገ/ሚካኤለ ቄስ ኪዳነ ገብረ እና ዲ/ን ተስፋይ ግርማይ ከሰበካ ጉባኤ  የሥራ ኃላፊነት፤ ከሥራ አገልግሎትና ደመወዝ እንዲታገዱ የተደረገው የቤተ ክርስቲያኒቱ መተዳደሪያ ሕግ የሆነው ቃለ ዓዋዲና የቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያዎችና ትእዛዞች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመቃመዋቸው ነው፡፡
        መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የምእመናንና የካህናት ጥያቄዎችና አቤቱታ መነሻ በማድረግ በክልል ትግራይ መሥራቃዊ ዞን ሀገረ ስብከት ተፈጸሙ የተባሉ አስተዳደራዊ በደሎችና የገንዘብ ብክነት የሚያጣሩ ሁለት አባላት ያሉት ቡድን በመስከረም ወር 2ዐዐ7 ዓ.ም መጀመሪያ ወደ ሀገረ ስብከቱ ልኮ ነበር፡፡ ይሁንና ሁኔታውን እንዲያጣሩ የተላኩት ሊቀ ሥዬማን ገብረ መስቀል ዘርዑ እና ወ/ሮ ጽጌ መንገሻ ለአንድ ወር ያህል በማጣሪት ሥራ ላይ ቆይተው ያመጡት ምላሽ(ሪፖርት) በሚመለከተው አካል ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ከሁሉ የሚገርመው አንደ አቤቱታ አቅራቢዎች አባል ሁኔታውን ለማጣራት ወደ ቦታው ተልከው የነበሩ ስማቸው ከላይ የተጠቀሰው ሁሉ አጣሪዎች ለአንድ ወር ያህል ጊዜ በአዲግራት ከተማ ሲቆዩ አንድም ጊዜ ቅሬታ አቅራቢ ወገኖችን ሳያነጋግሩ ወደ አዲስ አበባ የመመለሳቸው ጉዳይ ነው፡፡
        በዚህና ሒሳብ ነክ በሆኑ ጉዳዮች “አጣርተን መጥተናል” ብለው ያቀረቡት ሪፖርት በቁጥጥር አገልግሎት መምሪያው ኃላፊ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቶ ውድቅ ሆኖአል፡፡ ይህንን አስመልክተው የመምሪያው ኃላፊ መምህር ኤርምያስ ተድላ ጥቅምት 21 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም ለመንበረ ፖትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቴት በጻፉት ማስታወሻ አጣርተው ውጤቱን እንዲያቀርቡ የተመደቡ ሁለቱ አጣሪዎች የቀረቡት ሪፖርት በርካታ ጉድለቶች ያሉቡት መሆኑን ነጥብ በነጥብ በመዘርዘር ካቀረቡ በኋላ በመጨረሻ፡- “የሒሳብ ምርመራውም ሆነ የአስተዳደር የማጣራት ሥራው በማስረጃ ያልተደገፈ ስለሆነና በጉድለት የተሞላ መሆኑን በመግለጽ ይህን መግለጫ ለውሳኔ አቅርበናል” ይላል፡፡
        በዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ቀደም ሲል ጉዳዩ ለማጣራት ወደ አዲግራት ሄደው የነበራትን ሊቀ ሥዩማን ገብረ መስቀልንና ወ/ሮ ጽጌን በጉዳዩ ዙርያ ለማነጋገር ሞክሮ በሁለቱም እምቢተኝነት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ይህም አጣሪዎች አንድም በሠሩት ሥራ አለመተማመናቸውን ሁለትም አጣርተን መጣን ያሉት ውጤት እውነትነት የሌለው መሆኑን ያሳያል የሚል ግምት እንድንይዝ አድርጎናል፡፡
        ቋሚ ሲኖዶስም የቁጥጥር መምሪያ ኃላፊ ሪፖርት መነሻ በማድረግ በጉዳዩ ዙሪያ ከተወያየና የቅሬታ አቅራቢዎችን አቤቱታ በግንባር ካዳመጠ በኋላ በዶክተር አባ ኃይለ ማርያም መለሰ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ሥራ አስኪያጅ የሚመራ፤ መምህር ኤርሚያስ ተድላ የቁጥጥር አገልግሎት መምሪያ ኃላፊና መልአከ ብርሃነ ፍስሐ ጌታነህ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ዋና ኃላፊን ያካተተ ቡድን ቦታው ደረስ በመላክ ሂደቱን በሚገባ አጥንተው የመጨረሻ የውሳኔ ሐሳቡ አንዲያቀርቡ በወሰነው መሠረት ቡድኑ ተልእኮውን ፈጽሞ ተመልሷል፡፡
        የሁለተኛው አጣሪ ቡድን የደረሰበት ውጤት ምን እንደሆነ ለጊዜው ባይደርሰንም በቀጣይ እትማችን የዚህ ኮሚቴ ሪፖርትና ቋሚ ሲኖዶስ የሚያስተላልፈውን ውሳኔ እንደዚሁም የትግራይ ምሥራቃዊ ዞን ዓዲግራት ሀገረ ስብከት የሚሰጠው ምላሽ ካለ አካትተን ይዘን ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡

12 comments:

 1. አባ ሰላማ ብሎግ የሚያወጣቸው ጽሑፎች የሚሸነቁጣቸው አንዳንዶች በብሎጉ ላይ የሥድብ ናዳ በማውረድ የተጻፈው ሁሉ ውሸት እያሉ በማስተባበል የብሎጉን ስም ለማጠልሸት እንደሚተጉ አውቃለሁና ከዚህ ቀደም ብሎጉ ላይ የወጣው ጽሑፍ በዜና ቤተክርስቲያን ላይ መውጣቱ ለብሎጉ ጽሑፎች ተአማኒነት ጥሩ ማስረጃ ነውና በርቱ፡፡ የሚያሳዝነው ግን ቤተክርስቲያኗ እንደእነዚህ ባሉ ጳጳሳት መመራቷ ነው፡፡ ቤተክርስቲያኒቱ እኮ የለችም ማለት ይቀላል፡፡

  ReplyDelete
 2. ውሻ ምን ኣገባት በእርሻ አንደተባለው እናንተስ በሰው ቤተክርስቲያን ምን አገባችሁ ስለነፓስተር ተከሰተ ብትዘግቡ ኣይሻልም

  ReplyDelete
 3. ቤተ ክርስቲያኗማ አለች ትኖራለች ሞራል ያለው አገልጋይ ነው የጠፋው

  ReplyDelete
 4. አቤቱ በክፋት የተሞላችሁ የ21ኛው ሺ አባቶች የእዚ የሚስኪን ሕዝብ
  እንባ የት ያደርሳችሁ ይሁን…

  ReplyDelete
 5. Turinafa Tultula.. What the hell do u have in our church? Talk about Your Protestant fathers ....

  ReplyDelete
 6. አይጣል ሁኔታዎች እየከፉ ሄዱ፤ ሁሉም ለገንዘብ ሰገዱ፤ ምናለ በጸጸት ቢገደዱ፤ ገሀነም ሳይወርዱ፤
  በሰዎች አንደበት በክፉ መነሳትም ዕኮ ገሀነም ነው፤ ያው ግን ለሚሰማው እንጂ ለማይሰማው እንዲያው ለእንዲያው!

  ReplyDelete
 7. አይጣል ሁኔታዎች እየከፉ ሄዱ፤ ሁሉም ለገንዘብ ሰገዱ፤ ምናለ በጸጸት ቢገደዱ፤ ገሀነም ሳይወርዱ፤
  በሰዎች አንደበት በክፉ መነሳትም ዕኮ ገሀነም ነው፤ ያው ግን ለሚሰማው እንጂ ለማይሰማው እንዲያው ለእንዲያው!

  ReplyDelete
 8. ተሳዳቢ አንደበትን ይዝጋልን የመሸነፍ ምልክት ነውና

  ReplyDelete
 9. አሌ ለክሙ ጸሐፍት ፈሪሳዊያን

  ReplyDelete
 10. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሙሰኞችና ዘረኞች ታጠረ ምን ይሻላል ጎበዝ።

  ReplyDelete
 11. i am the witness it is real

  ReplyDelete