Saturday, February 28, 2015

ቤተ ክርስቲያን በአደጋ ክበብ ውስጥ (ክፍል ሁለት)                      Read in PDF            

                                                     ከዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
በክፍል አንድ ላይ ቤተክርሰቲያን እንዴት ወደ አደጋ ክበቡ እንደገባች የሚጠቁም ጽሁፍ አቅርቤ ነበር፡፡ እናት ቤተክርሰቲያን ትታደስ ብለን የተነሳን ሰዎች የቤተክርስቲያኒቱ ችግሮችን መጠቆማችን እንግዳ ነገር ሊሆን አይችልም፡፡ አይገባምም፡፡ በጽሁፉ ላይ የተሰጡትን የተለያዩ አስተያየቶች ለመመልከት ችያለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ምክንያታቻውና መነሻ ሀሳባቸው የማይታወቅ ስድቦች ብቻ ናቸው፡፡ የተጻፈውን ጽሁፍ በሰለጠነ መንገድ በምክንያት ከመሞገት ይልቅ በመንደር ቋንቋ እንዲህና እንዲያ ተብያለሁ፡፡ የሆነው ሆኖ ግን ቤተክርስቲያን በአደጋ ክበብ ውስጥ የሆነችበትን ሀሳብ ሳስቀምጥ ዋነኛ ምክንያት አድርጌ ያነሳሁት እግዚአብሔርን ብቻ አለማምለካችን የሚለውን ሀሳብ ነው፡፡ አሁንም እሱን ማብራራት እቀጥላሁ፡፡ አሁንም አስተያየታችሁን በሰለጠነ መንገድ በምክንያት እንድትገልጡልኝ በፍቅር አሳስባለሁ፡፡ መልካም ንባብ  
1.1.       ጥንቈላ
   የእግዚአብሔርን እውነተኛ አስተማሪነት (ኢሳ.30፥20) አለመቀበል  ፤ በትምህርቱም አለመጽናት የሐሰት መመህራን ትምህርት ሾልኮ ለመግባት ሠፊ በር ይከፍታል፡፡ (2ጴጥ.2፥1) በቤተ ክርስቲያናችን እንደቤተ ክርስቲያናችን የመጻህፍት ጽህፈት ቀኖና መሠረት በቀለማት አጊጦ ከሚባዙትና ከቤተ ክርስቲያኒቱ መጻህፍት ጋር ታትሞ እኩል በየመጻህፍት መደብሩ ከሚሸጡት መጻህፍት መካከል አንዱ አውደ ነገሥት የሚባለው የጥንቈላ መጽሐፍ ነው፡፡ መሥተፋቅር ፣ አስማት የሚደግሙ ፣ ሞራ ገላጮች ፣ መናፍስት ጠሪ ፣ ሙታን ሳቢዎች … እና ሌሎችም የጥንቈላ ሥራዎች ሁሉም ለማለት ሊያስደፍር በሚችል መልኩ የሚከናወነው ከደብተራ እስከካህናት ባሉት የቤተ ክርስቲያኑቱ አገልጋዮች ነው፡፡
   ጥንቈላ የሥጋ ሥራና (ገላ.5፥20) ከእግዚአብሔር ሃሳብና ፈቃድ ውጪ መንፈሳዊ ኃይልና መገለጥን የሚፈለግበት መንገድ ነው፡፡ እግዚአብሔር ጠንቋይንም አስጠንቋይንም አብዝቶ ይቃወማል፡፡ እስራኤል በጠንቋዮች መንገድ እንዳይሄዱ አስጠንቅቋቸዋል ፤ እንዲያጠፏቸውም ነግሯቸዋል፡፡ (ዘጸ.22፥18 ፤ ዘሌ.20፥27) ሐዋርያት የክርስቶስን ወንጌል ለብዙዎች ከመሠከሩ በኋላ ከጥንቈላና አስማተኝነት የተመለሱትን አማኞች ይገለገሉበት የነበረውንም ዕቃ እንዲያቃጥሉ አድርገዋል፡፡ ለጥንቆላ ሥራ አገልግሎት ይሰጠው የነበረው ማናቸውም ነገር ሲቃጠልና ሲወድም ተቀይሮ ለመንፈሳዊ ሥራ ሲውል አልታየም፡፡ (ሐዋ.19፥19)

     የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ የገዛ “ወንድሞቹና የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ያደረጉበትን የድግምትና የጥንቈላ” ሥራ ፈጽሞ አይረሳውም፡፡ ጥንቁልና ዛሬ በብዙ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና አማኞች በተለይም ጠበል በሚያጠምቁ አገልጋዮች ዘንድ የማንክደው የአደባባይ እውነት ነው፡፡ ጠንቋዮቹም የልብ ልብ ተሰምቷቸው በሚጠነቁሉበት ቤት “ቅዱሳት ስዕላትን” ከመስቀል አልፈው ፤ በግልጥ በብዙ ድጋፍና ተቀባይነት አብያተ ክርስቲያናትን ሲያንጹ  ይታያሉ፡፡ በተለይ ደግሞ በየዓመቱ ግንቦት አንድ በየአድባሩና በየወንዛ ወንዙ የእንሰሳት መሥዋዕት የሚያቀርቡ ካህናት እንዳሉ ስንሰማ ምን ሊሰማን እንደሚችል ለመረዳት ያዳግታል፡፡ የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ በአንድ አመት ግንቦት አንድ የሚደረገውን ካህናት የተሳተፉበትን የጣዖት አምልኮ እርድ በመቃወሙና በዚህ ዙርያ በማስተማሩ ምክንያት የደረሰበትን የግድያ ሙከራ መቼውም አይረሳውም፡፡ 
   ቤተ ክርስቲያን በመካከሏ ካሉት መጻህፍት ጀምሮ እስከአገልጋይ ጠንቋይና አስጠንቋይ አማኞቿ ግልጥና ቁርጥ ያለ ነገር ማስቀመጥና እንዲህ የሚያደርጉትን ሰዎች ያለማወላወል የንስሐ ዕድል ሰጥታ ካልተመለሱ ለብዙዎች ሳይሆን ለአንድ ሰው እንኳ መሰናክል እንዳይሆኑ ለመጠንቀቅ (ማቴ.18፥6) ስትል ከመካከልዋ ልትለይ ይገባታል፡፡
1.2.    ዘረኝነት

      ዘረኝነት የሚለውን ቃል ሶሻሊስታዊው “ማርክሳዊ ሌኒኒናዊ” መዝገበ ቃላት “ከቀለም ወይም ከዝርያ ልዩነት የተነሳ ራስን የተሻለ አድርጐ ማየትና ሲቻልም ማስገበር ማለት ነው፡፡ የዚህ ዓይነት የዘረኝነት ተግባርም በአንድ አገር ውስጥ ባሉ ልዩ ልዩ ጐሳዎች ፥ ነገዶች ወይንም ዝርያዎች መካከል ወይንም ደግሞ በዘር በቀለም ፣ በመሳሰሉትና በተለያዩ ምክንያቶች ላይ ተመርኩዞ ልዩነቶችን ልዩነቶችን በመፍጠር የአንድ ሐገር ሕዝብ በሌላው ሐገር ህዝብ ላይ ሊፈጽመው የሚችለው ነው፡፡” (የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት፤ አዲስ አበባ ፤ 1978 ፤ ኩራዝ ማተሚያ ድርጅት)
    ዘረኛ የሚለውን ቃል ደግሞ ኣማርኛ መዝገበ ቃላቱ ሲተረጉመው “ ሰዎችን በዘር ከፋፍሎ የሚያጋጭና በዘር ምክንያት ለአንዱ እያደላ፤ ሌላውን የሚጎዳ ፥ የዘረኝነትን አስተሳሰብን ፥አመለካከትን የሚያራምድ፡፡ በማለት ይተረጉመዋል፡፡ ( አማርኛ መዝገበ ቃላት ፤ የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ማርምር ማዕከል ፤ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ፤ የካቲት 1993 ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት፡፡ገጽ.437)
    ጌታ እንዳስተማረን በዘመን ፍጻሜ ከሚፈጸሙት ታላላቅ የትንቢት ቃላት መካከል አንዱ “ሕዝብ በሕዝብ ላይ … ይነሣልና” (ማቴ.24፥7) የሚለው ነው፡፡ ይህ ሕዝብ በሕዝብ ላይ የሚነሳበት አንዱና አስቀያሚ መንገድ ዘረኝነት ነው፡፡ ዘረኝነት ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን የሚክድ ፤ ሰዎች የሰዎች ልጆች ብቻ መሆናቸውን የሚያስረዳ መርዝ ፖለቲከኞች የሚዘሩት መንፈስን በካይ ዘር ነው፡፡ የጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ለኃጢአት መሥዋዕት የቀረበ ነው፡፡ ስለዚህም ክርስቶስ በሞቱ “ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅቶ  ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አድርጎናል”ና (ራዕ.5፥9-10) በሥጋችን እግዚአብሔርን ልናከብር ይገባናል፡፡ (1ቆሮ.6፥20)
     ዘረኝነት በሥጋ የራስን ነገድና ቋንቋ ተናጋሪን ፈልጎ የመግባባት መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ በራሱ ችግር አይኖርበት ይሆናል ፤ ነገር ግን ዘረኝነቱ የሚንጸባረቀውና ጎልቶ የሚወጣው “ከእኔ በላይ ሌላ ዘር የለም ፤ የእኔ ዘር ብቻ ነው ንጹሕ ፤ ሌላው ዘር ከእኔ በታች ነው ፤ እንደእኔ ዘር ታማኝ እንደእኔ ዘር ቆንጆ የለም ፤ የእኔን ዘር የእገሌ ዘር ጨቁኖታል፣ በድሎታልና የእገሌን ዘር ፈጽሞ አልወደውም ፤ የእኔ ዘር ካልሆነ በዚህ ሥፍራ ሌላ ሰው ሊቀጠር ፣ ሊሠራ ፣ ደመወዝ ሊያገኝ አይገባውም ፤ የእኔ ዘር …. የእኔ ዘር …. የእኔ ዘር … ” የሚለው ንግግር ምንጩ ወይም መንፈሱ ከእግዚአብሔር ፤ ከማይጠፋው ዘር ከተወለደ ማንነት የሚወጣ አይደለም፡፡
    ይህ ሥር የሰደደ ክፋት ናዚዎች አይሁዳውያንን እንዳይቀበሉና ለእስከመጨረሻው ለመጥላት ፤ ለመጨፍጨፍና ለጅምላ ግድያ ምክንያት ሲሆን ፣ ሩዋንዳ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በእኛ ዕድሜ አንድ ሚሊየን ገደማ የሚገመት ሕዝብ መጥረቢያና በገጀራ የመተላለቁ ምክንያት (የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችና አብያተ ክርስቲያናት ሳይቀሩ የተሳተፉበት) ምንጩና መነሻው የዘረኝነት መንገድ ነው፡፡ በዚህ መንገድ እኛም ብዙ ጊዜ እንዲህ ያለ ከማድረግ የእግዚአብሔር እጅ ከልክላን እንጂ እንዲህ ያለ ደም ለማፍሰስ የታቀዱ ብዙ ዕቅዶች ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር ግን ትልቅ ነው!!!
     እኛ ከእግዚአብሔር በመወለዳችን የዚህ አለም ዘር(ማንነት) አያንጨረጭረንም፡፡ እኛ “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ነንና” በመካከላችን  “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችን በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ነንና፡፡”(ገላ.3፥26 ፤ 29) እንዲህ በክርስቶስ የጸናውን አንድነት በቤተ ክርስቲያን መካከል እንዲያቆጠቁጥ ማድረግ አደገኛ አጋንንታዊ አስተምህሮ ነው፡፡
     ዘረኝነት በመካከላችን አብቦ አፍርቷል፡፡ ሲካድና ሲስተባበል እንዳልነበር አሁን በግልጥ ቃል እንዲህ እስከመባል ተደርሷል ፦ “ … አሁን አሁን ነገራችን እንደዖዝያን ለምጽ ሊሸፈንበት ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ራሱ ችግሩም “አለሁ ፣ አለሁ” ብሏል፡፡ የለህም ብንለውም ራሱን በራሱ ያስመሰክራል፡፡ … የዘመድ አሠራሩ … ወዘተ አግጠው ወጥተዋል፡፡” (ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ፤ ስማችሁም የለም ፤ 2006 ፤ አዲስ አበባ፡፡ ገጽ 15)
     በምዕራቡ ዓለም በአሜሪካና በአውሮፓ ያሉ ጥቂት ያይደሉ “ክርስቲያኖች” በጽዋና በማህበር ሰበብ የሚሰባበሰቡትና የሚያመልኩት “ከዘራቸው” ካልሆነ ሰው ውጪ እንዳልሆነ የጠራራ ሐቅ ሆኗል፡፡ ሁላችን የአዳም ልጆች ሆነን ፥ የአዳምን እጁን ከንባታ ፣ እግሩን አፋር ፣ ጭንቅላቱን ሶማሊያ ፣ አይኑን ሐዲያ ፣ አፍንጫውን ኦሮሞ ፣ ጆሮውን ትግሬ ፣ ጡቱን ሲዳማ ፣ ጥርሱን ሐመር … አድርገን የምንከፋፍል አይንና አይንን ለማበላለጥ የምንሻ የህሊና ድሆች እንዴት ይሁን የምናሳዝነው? … ለብዙዎቻችን እውቀታችን ከዘረኝነት ሀሁ አለማለፉ እንዴት ያሳዝናል? ሐገርንና ወገንን መውደድ ከዘረኝነት መርገም ጋር ለውሰን ሌላውን ለመስበክ የምንጥር ከንቱዎችም በጌታና በባዕለ ህሊናዎች ፊት ሥራችሁ የጠራ መሆኑን አምናችሁ ንስሐ ብትገቡ እጅግ መልካም ነው፡፡   
    በተለይ ቤተ ክርስቲያን በአንዳንድ “መጻህፍቶቿ” ውስጥ “እገሌ የሚባለው ዘር ወይም ከእገሌ ዘር ጋር መጋባትና በሩካቤ መገናኘት መንግሥተ ሰማያት አይገባም ፤ አብሮ የፈጸመውም አይገባም” (መጽሐፉን መጥቀስ አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም) የሚል ጽሁፍ በግልጥ ተቀምጧል፡፡ እነዚህ መጻህፍት አንዳንዶቹን ማተሚያ ቤቶቹ በሌላ ሲቀይሩት ቢታይም አሁንም በገበያ ላይ አሉ፡፡ ስለነዚህ መጻህፍት ቤተ ክርስቲያን ዝምን እንጂ ሌላ ነገር የመረጠች አይመስልም፡፡ ነገር ግን እነዚህ መጻህፍት ለብዙ ምዕመናን መሰናክል ምክንያት እንደሆኑ መካድና ማስተባበል ሳያሻ ቤተ ክርስቲያን ያለአንዳች ማቅማማት ይቅርታ በመጠየቅ እኒህን የዘረኝነት መርገም ያለባቸውን መጻህፍት ከመካከልዋ ልታስወድግ ይገባታል፡፡
ምን እናድርግ?
1.2.1.   እውነተኛው ወንጌል ይሰበክ

      የታረደው በግ  “ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ከዋጀ” (ራዕ.5፥9) ቤተ ክርስቲያን ከልዩነት ይልቅ አንድነት ላይ ትልቅ ሥራ ልትሠራ ይገባታል፡፡ የዘረኝነት መንፈስ ማጥፋት የሚቻለው ማንነታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የተወረሰና የእኛ የሆነ ምንም እንደሌለን መረዳት ሲቻለን ነው፡፡ “በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” (ሮሜ.1210) የሚለን ሕያው ቃሉ እንደማይለያይ ወይም መለያየት እንደማይችል ቤተሠብ አንድ መሆናችንን ያገናዝባል፡፡
    የሥጋ ወንድማማችነትን መካድ አይቻልም ፤ ብንክደው እንኳ እኛ ውሸታሞች እንሆናለን እንጂ ወንድምነትን መካድ አንችልም፡፡ እንዲሁ አንድ የሆንበትንና የተወለድንበትን ዘር መካድ ፈጽሞ አንችልም፡፡  “ትልቅ ዘር” እንዳለን የምናስብ ሰዎች መርጠን አላገኘነውም ፤ እንዲሁ “ትንሽ ዘር” የምላቸውም ሰዎች መርጠው አልተወለዱበትም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ከዚህ ነውር ነጽታ በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የፈረሰውን የዘር ልዩነትን መልሳ ከመገንባት እጇን ልትሰበስብ ፤ ይህን የሚያድርጉትን ልትምክር ፣ ልትገስጽ ፣ በመቆጣትም ልትመልስ ይገባታል፡፡
1.2.2.  ቤተ ክርስቲያን ይቅርታ ትጠይቅ!
   ቤተ ክርስቲያን “በመጻህፍቶቿ” ያሰፈረቻቸው የሌላውን ዘርና ብሔር የሚያንቋሽሽ ጽሁፎችን በግልጥ አስቀምጣለች፡፡ በዚህ ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱን ጥለው የሄዱ ምዕመናንና ምዕመናት ቀላል ቁጥር የላቸውም፡፡ ስለዚህም ያለምንም ማወላለወል ቤተ ክርስቲያን ይቅርታ መጠየቅ ይገባታል፡፡ ያለይቅርታና ያለንስሐ የትኛውም ቁጣ አይበርድም ፤ አይሰክንምምና፡፡
    የሮማው ፖፕ የነበሩት ዳግማዊ ጆን ፖል ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዘመናት የመራችውንና ለብዙዎች ማለቅ ምክንያት የሆነውን የመስቀል ጦርነት ዳግም ቤተ ክርስቲያኒቱ እንዳትወቀስ ያደረጉት በዓለም ሁሉ ፊት በግልጥ ስለድርጊቱ ይቅርታ በመጠየቃቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር “እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት ፥ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ … ይቅር ባይ፥ ቸርና መሐሪ አምላክ፥ ለቍጣም የሚዘገይ፥ ምሕረትንም የሚያበዛ ነው ፥ … ምሕረቱንም ለሚጠሩት ሁሉ የበዛ” ነው፡፡ (ዘጸአ.34፥7-8 ፤ ነህ.9፥17 ፤ መዝ.85፥5)
   ይቅርታን ለሚሹ በእውነት እግዚአብሔር ይቅር ባይ ነው፡፡ በኃጢአታችን ጸንተን እልኸኞች ብንሆን ግን “በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው” (ዘጸአ.34፥7) አብ በልጁ ክርስቶስ ኢየሱስ በሞቱ የሰጠንን የይቅርታ ዘመን ልንጠቀምበት ይገባናል፡፡ አልያ ግን እግዚአብሔር ፈራጅም ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በዘረኝነት ዘርያ ስለተጻፉ ጽሁፎች ብዙዎችን ስለማዳንና መንገዷን ስለማጥራት ይቅርታ ልትጠይቅ ይገባታል፡፡
1.2.3.  ዘረኝነትን የሚደግፉ መጻህፍት ይወገዱ!

      ከይቅርታና ከንስሐ ቀጥሎ ደግሞ ተግባራዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ይኸውም ዘረኝነትን የሚያጸናባርቁና የሚያቀነቅኑ መጻህፍት ከአገልግሎት መድረክ ወርደው (ተወግደው) ወደሙዚየም ሊገቡ ይገባል፡፡
1.3.    መለያየት

   መለያየት ከሥጋ ሥራዎች አንዱ ነው፡፡ (ገላ.5፥21) ቅዱስ ጳውሎስ በልመና ቃል “ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።” በማለት ይናገራል፡፡ (1ቆሮ.1፥10) መለያየት መነሻው የገዛ ምኞትን ከመከተል እንደሆነ ሲገልጥ ጠቢቡ “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፥ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።”
    ላለመተያየት የጥላቻ ግንብ ገንብተናል፡፡ መናፍቃንና ከሐዲያንን ለማውገዝ የምንጠቀምበትን ሰማያዊ ሥልጣን ባልንጀራችንና ወንድማችንን ለማውገዝ በድፍረትና በትዕቢት ተጠቅመንበታል፡፡ አለም እስኪታዘበን ድረስ በአደባባይ መጠላላታችንንና መለያየታችንን በአዋጅ አሳውጀናል፡፡ ጥር 25 1999 ዓ.ም ከምሽት ዜና በኋላ ኢትዮጲያ ውስጥ ያለው ሲኖዶስ በአሜሪካ የሚገኘውን ሲኖዶስ በመረረ ውግዘት ማውገዙን ሰምተናል ፤
§  “ሊቃነ ጳጳሳት ፣
§  ጳጳሳት ፣
§  ኤጲስ ቆጶሳት ፣
§  ቆሞሳት ፣
§  ቀሳውስት ፣
§  ዲያቆናትና መዘምራን ፣
§  ምዕመናንና ምዕመናት በሙሉ … የተሰበሰቡትን የዘመናችን የጸረ ማርያምን የተሐድሶ መናፍቃን ስብስቦች ቃላቸውን እንዳታምጡ ፣ ትምህርታቸውንም እንዳትቀበሉ ፣ ኢ-ቀኖናዊ ሥርዓታቸውን እንዳትከተሉ ፣ ሥልጣነ ክህነትም ከእነርሱ እንዳትቀበሉ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ከእነሱ ጋር እንዳትሳተፉ ፣ የእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አውግዟል፡፡” በማለት አባቶቻችን በአንድ በረት እንዳለ ሁለት ወይፈን መቻቻል ተስኗቸው ሲወጋገዙ ታዝበናል፡፡
    በዚህ ሳያበቃ የአሜሪካውም ሲኖዶስ “ክፉን በክፉ በመመለስ” ጥር 30 1999 በአሜሪካ ሬድዮ የአማርኛው ፕሮግራም “ … በሕጋዊው ሲኖዶስ የተወገዙትን … ቃል እንዳትሰሙ ፣ ትምህርታቸውን እንዳትቀበሉ ፣ በምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከእነርሱ ጋር ኅብረት እንዳይኖራችሁ ፤ … በስደት አገር የሚገኘው ሕጋዊው … ሲኖዶስ አውግዞአል፡፡ … ” በማለት አስነብቦናል፡፡
   እንኪያስ፦ በቃለ እግዚአብሔር ዳኝነት ማን ይሆን ትክክል? “የውግዘትን ኃይል” የምንጠቀመው ለምንድር ነበር?  ተወጋግዞ ጉዞ ለመሆኑ የት ያደርሰናል? ብዙዎች በዚህ ውግዘት መካከል ከማቀራረብ ይልቅ ውዳሴና መወደድን ለማግኘት ብለው በእሳቱ ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉ ሃፍረት እንኳ አልተሰማቸውምም? ይህ ውግዘት ሳይፈታ ዛሬም ሁለቱም አካላት ጸሎትን ለአምላካችን ነው ይላሉ፡፡ ግና ባልንጀራን ላለመቀበልና ወንድምን በሚጠላ ነፍሰ ገዳይነት ውስጥ ሆነን (1ዮሐ.4፥20) ፤ የሰማይ ደጅን በገዛ እጃችን ቆልፈን ቅዳሴና ምህላ እንዴት ያለ ምስኪንነት ነው!!!? ብናውቅስ እግዚአብሔር አይዘበትበትም!
   የተወጋገዙት ጳጳሳት አብዛኛዎቹ ዛሬም በሕይወት አሉ፡፡ ግና አሁንም ለይቅርታ ሊሸነፉና ከእግዚአብሔር የለያያቸውን ቂመኝነትና አልታዘዝ ባይነት በንስሐ ለመሸፈን ያሰቡም አይመስሉም፡፡ ግና በገዛ እጃችን የገነባነውን የመለያየት ግንብ በንሥሐና በይቅርታ ካላፈረስን ለእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣ “እየሰባን” ለመሆናችን ምንም አይጠረጠርም፡፡
ምን ይደረግ?
1.3.1.   ንስሐ መግባት

      መለያየት ከሥጋ ሥራዎች አንዱ ነው፡፡ (ገላ.5፥21) “የክርስቶስ ኢየሱስም የሆንን ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቅለናልና” (ገላ.5፥24) “ሁላችን አንድ ንግግር እንድንናገር በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበርን እንድንሆን እንጂ መለያየት በመካከላችን እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በፍቅር ልመና ተለምነናል” (1ቆሮ.1፥10) በቤቱ ያለን ወንዶችና ሴቶች የክርስቶስን መንግሥት በመውረስ አንበላለጥም ፤ ክርስቶስ ኢየሱስ በዳግመኛ ምጽአቱ ሲመጣ “እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።” (ማቴ.25፥34) የሚላቸው ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን ነው፡፡
   አለም እንኳ መለያየት እንዳላዋጣት አስተውላ ወደአንድነት መምጣት ከጀመረች መሰነባበቷን የበርሊን ግንብ ተንዶ ጀርመን አንድ መሆኗን ትልቅ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የክፉዎች አጋንንትም መለያየት መንግሥታቸውን እንደማያጸና ጌታ “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ሁላ ትጠፋለች፥ እርስ በርሱ የሚለያይ ከተማም ሁሉ ወይም ቤት አይቆምም። ሰይጣንም ሰይጣንን የሚያወጣ ከሆነ፥ እርስ በርሱ ተለያየ፥ እንግዲህ መንግሥቱ እንዴት ትቆማለች?” (ማቴ.12፥24-25) በማለት አጽንቶ ተናግሯል፡፡ ክፉ እንኳ ለክፋቱ መተባበር እንዳለበት ካመነ ቤተ ክርስቲያን “ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያየች አብልጣ ማድረግ ያለባትን መሰባሰብንና እርስ በርስ መመካከርን” (ዕብ.10፥25) ስለምን ይሆን የተወችው?   
   ዛሬ ላይ ክርስትናን “ሊያጠፉ” (አይቻላቸውም እንጂ) የተነሱ አካላት በሙሉ ኃይላቸው በአንድነት ሲነሱ ቤተ ክርስቲያን የገዛ ልጆቿን አንድ የሚያደርግ የአንድነትን መንፈስ ማጣቷ እጅጉን ልብ የሚነካ ነገር ነው፡፡ ከመሥዋዕት በፊት መታዘዝ ፣ ከመጰጰስና ከመመንኮስ በፊት ለባልንጀራ ይቅርታ ማድረግ ፣ ቁርባን ከመፈፈትና ከመቀደስ በፊት ምህረት ማድረግን ትተን ከቂም ጋር መቁረብን ፣ ከጥላቻ ጋር ወንጌል መስበክን ፣  ከመለያየት ጋር መዘመርን ፣ ካለመስማማት ጋር ቀድሶ ማስቀድስን ከየትኛው ወንጌል ይሆን ያገኘነው?
  የሥልጣን እርከናችንና ትዕቢታችንን ለማጽናት ወንጌልን ወደጎን በመግፋት ለትውልድ የመለያየትን ነውር ማቆየታችን በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ ቅጣት እንደምናገኝበት ግን ምንም ልንጠራጠር አይገባንም፡፡ እግዚአብሔር “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” (ማቴ.18፥20) አለ እንጂ በተለያዩና በማይስማሙ ሚሊዮኖች መካከል እገኛለሁ አላለምና ምክንያታችንን ወደጎን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ንስሐ እንግባ፡፡

1.3.2.  ይቅርታን መስጠትና መቀበል

    አባቶቻችን እውነተኛ አባቶች ከሆኑ የሚኖሩትን ኑሮ በእውነት ሊያሳዩን ይገባል፡፡ የጠብ ግድግዳቸውን በይቅርታ አፍርሰው “ … በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ፤ … እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ።” (ፊሊጵ.2፥2-4) የሚለውን ቃል ፈጽመው ማየትን እንወዳለን፡፡ ሌሎችን ከማስታረቃቸው በፊት እነርሱ ታርቀው ፣ ልዩነታቸውን ሽረው ፣ ጠባቸውን በፍቅር አጥበው … በወንድማማች መንፈስ አንድ ሆነው አብረው በአንድነት ቅዳሴ ገብተው ፣ የጌታ እራትን ላይ ተካፍለው ሲያካፍሉ ማየትን ነፍሳችን አብዝታ ትናፍቃለች!!! መቼ ይሆን?!
ይቀጥላል

1 comment:

  1. this is what we need. tebarek bro

    ReplyDelete