Tuesday, March 10, 2015

ቤተ ክርስቲያን በአደጋ ክበብ ውስጥ (ክፍል ሦስት)      Read in PDF                                    
ከዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
(ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጽሁፎቼ ቤተክርስቲያን በአደጋ ክበብ ውስጥ ነች የሚያሰኙዋትን ምክንያቶች እየዘረዘርኩ ነበር። ዛሬም ካቆምኩበት የሚቀጥለውን ክፍል ለአንባቢያን በትህትና አቀርባለሁ። መልካም ንባብ)
1.4  አይን ያወጣ ጉበኝነት

·        ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል፡፡
·        ሹም ሲቆጣ ማር ይዞ እደጁ፥ ደስ ሲለው ማር ይዞ እደጁ፡፡
    በምሳሌነት ይህን ተረት አነሳን እንጂ ከዚህ ተመሳሳይነት ያላቸው ተረቶችና ምሳሌያዊ ንግግሮች በተወሰነ መልኩ በባህላችን ውስጥ ተሰንቅረው ለጉበኝነትና ለመታያ የሚሰጡት ድጋፍ አለ፡፡  
     የእግዚአብሔር ቃል በግልጥ “ፍርድን አታጣምም ፊት አይተህም አታድላ ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና ጉቦ አትቀበል።” (ዘዳግ.16፥19) ይናገራል፡፡ አንድ ሹም ጉቦ ወይም መማለጃን የሚቀበለው እውነቱን ሐሰት ፤ ሐሰቱን እውነት ለማለት ወይም ለማድረግ ነው፡፡ እውነቱን ሐሰት ስንል ጻድቁን ወይም እውነተኛውን እንበድላለን ፤ ሐሰቱን ደግሞ እውነት ነው ስልን ኅጢአተኛውን በጻድቁ ላይ እናሰለጥናለን፡፡
    በእስራኤል ፊት ያለነውር በሞገስና በመወደድ ፤ ያለምንም መማለጃ ይመላለስ የነበረው (1ሳሙ.12፥3) ታላቁ ነቢይ ሳሙኤል ልጆቹ እንደእርሱ የተባረኩ አልነበሩም፡፡ ስለልጆቹ ታላቁ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ልጆቹም በመንገዱ አልሄዱም፥ ነገር ግን ረብ ለማግኘት ፈቀቅ አሉ፥ ጉቦም እየተቀበሉ ፍርድን ያጣምሙ ነበር።” (1ሳሙ.8፥3) ይላል፡፡ ይህ ማለት በሳሙኤል እጅ ትፈረድ የነበረችው የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ መማለጃን በቀኝ እጃቸው በተመሉ (መዝ.26፥10) በልጆቹ ጠማማ ፍርድ በሌላ መንገድ ትፈርስ ነበር ማለት ነው፡፡
   ያለምንም ማባበያ ቃል ዛሬ ቤተ ክርስቲያን በጉበኞችና መማለጃን በሚወድዱ፥ ንብ የማር ቀፎን እንዲከብብ ተከብባለች፡፡ አምስትና ሐምሳ ሺህ ለመጠየቅ አምስቱን አዕማድ ፣ ሰባት ሺህ ለመጠየቅ ሰባቱን ምስጢራት ፣ አስር ሺህ ለመጠየቅ አስሩን ሕግጋት በኰድ የሚጠቀሙ ፌዘኛና አታላዮች ቤተ ክርስቲያናችን ከተከበበች ውላ አድራለች፡፡ ዛሬ የተመረጡ አድባራት ላይ ከድቁና እስከ ቁምስና  ለመመደብ ጉቦው ራሱ በልዩ ጨረታና በእሽቅድምድም ነው የሚሰጠው፡፡ ከተመደቡ በኋላ ደግሞ ለመቆየትና ላለመነሳት ምጽዋተ ሙዳይ እየሰበሩና ካላቸውና ከወዛቸው እየቆረሱ መማለጃ የሚሠጡትን ስንሰማ ጆሮ ጭው ሊያደርግ ይችላል፡፡
    ከብሔርተኝነት በማይተናነስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምናየው አስጨናቂ ነውር ጉበኝነትና መማለጃን መውደድ ነው፡፡ ነገር ግን ጉቦን በመቀበል የችጋረኛውን ፍርድ የሚያጣምሙትን እግዚአብሔር ኃጢአታቸው የጸና እንደሆነ ይናገራል፡፡ (አሞ.5፥12)
   “መማለጃን ከመጨበጥ እጁን የሚያራግፍ …  እርሱ ከፍ ባለ ስፍራ ይቀመጣል ጠንካራ አምባ መጠጊያው ይሆናል እንጀራም ይሰጠዋል፥ ውኃውም የታመነች ትሆናለች።” (ኢሳ.33፥15-16)
    ፍትሐ ነገሥቱም “ሳይገባው ገንዘብ ተቀብሎ የሚሾም ኤጲስቆጶስ ቢኖር ይለይ፡፡ …” (አን.5 ቁ.177)
ምን እናድርግ?
1.4.1    በልክ መኖር

     ኑሮዬ ይበቃኛል አለማለትና ባለጠግነትን አብዝቶ መሻት “በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም እንደሚጥል” (1ጢሞ.6፥9) የእግዚአብር ቃል በግልጥ ያስቀምጣል፡፡ ይልቁን የእግዚአብሔር አገልጋዮች “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል።” (ምሳ.30፥8 ፤ 1ጢሞ.6፥8) ሊሉ ይገባቸዋል እንጂ ወይም ፍትሐ ነገሥቱ እንደሚለው “ኤጲስቆጶስ ከምግብና ከልብስ የሚበቃውን ያህል የሚወስድ ይሁን ለሚያገለግል ዋጋው ይገባዋልና ፡፡ ልብሱን አያሳምር ሥጋውን ለመሸፈን የሚበቃውን ያህል ይውሰድ እንጂ፡፡ ሌላ ጌጥ የሚያስፈልግ አይደለም፡፡” (ፍትሐ ነገሥት አን.5 ቁ.127) እንደሚለው ራሳቸውን ልከኞች አድርገው ሊኖሩ ይገባቸዋል፡፡
   መጥምቁ መለኮት የጌታን መንገድ ለመጥረግ ይመላለስ  በነበረበት ዘመኑ ልብሱ የግመል ጠጉር ፤ ወገቡ ጠፍር የታጠቀ ፣ ምግቡ አንበጣና የበረሃ ማር ፣ ቤቱ ምድር በዳ መሆኑ ምን ይሆን የሚያስተምረን? እንደዛሬው አገልጋዮች ሽቶ የተገቡና ውድ የሆኑ ቀሚሶችንና የእጅ ፣ የአንገት መስቀልን መልበስና መያዝ ይሆንን? ወይስ በሁለትና በሦስት ከተማ ያማሩ ቤቶችን መገንባት? ወይስ ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን ቤት ትተው የራሳቸውን በከተማው መካከል ቪላ መገንባት ነውን? ወይስ ጰጵሶ ብዙ ሚሊየን ብር በባንክ አስቀምጦ ወለዱን ቁጭ ብሎ መብላት ነውን? ወይስ መንኩሶ ሳይሰሩ ቁጭ ብሎ ፍትፍት እያማረጡ መብላት ነውን?
     በእውኑ “ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” (ሉቃ.9፥58) ያለው ጌታ ምንን ይሆን የሚያተምረን? ሁሉን እያለው ድሃ የሆነው ጌታ ሕይወቱ አይዘልፈንንምን?
   አዎ! “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነውና” በኑሯችን ልከኞች እንሁንና በኑሯችን ጌታችንን እናክብረው ፤ ከጉበኝነትም እንራቅ፡፡

1.4.2   ከክፉ መጎምጀት መራቅ

             “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም
                           ሁሉ ተጠበቁ” (ሉቃ.12፥15)
             “ … አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን
              ወጉ። አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ … ” (1ጢሞ.6፥10-11)

 በልክ ለመኖር መሠረቱ ልብን ከሚከፍለው ክፉ መጎምጀትና ራስን በክፉ ከሚወጋ ምኞት መጠበቅ ፤ መጠበቅና መሸሽ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ ላይ በምንኩስናና በተለያየ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘርፍ መሳተፍ ለቅዱስ አገልግሎት ከመሠማራት ይልቅ ምድራዊ ሀብትን ማግኛ አጭር መንገድ ሆኗል ብንል ምንም ግነት የለበትም፡፡ ክፉ መጎምጀት ወይም ስግብግብነት  ወደዘላለም ጥፋት የሚመራ ኃጢአት ነው፡፡
   በአንድ ወቅት በእስራኤል ልጆች የበረሃ ጉዞ ታሪክ “በመካከላቸውም የነበሩ ልዩ ልዩ ሕዝብ እጅግ ጐመጁ … ” (ዘኁል.11፥4) ይለናል ታላቁ መጽሐፍ፡፡ የእነዚህ ሕዝቦች ፍጻሜ ግን “የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት እጅግ መታ። የጐመጁ ሕዝብ በዚያ ተቀብረዋልና የዚያ ስፍራ ስም የምኞት መቃብር ተብሎ ተጠራ።” (ቁ.33-34) በማለት በአጭሩ ያስቀምጥልናል፡፡ እንኪያስ የዛሬዎቹም አገልጋዮች ለጉበኝነትና የሌላውን ቤት የሚያሳያቸው አንዱ ነገር ክፉ መጎምጀት ወይም ስግብግብነት ወይም ራስ ወዳድነት ነውና ከዚህ መራቅ ይገባል፡፡1.4.3   የሰዎችን ችግር በመካከላቸው ተገኝቶ ማየት

     ታች በድህነት ያለው ሕዝብ በምነ አይነት ድህነት ውስጥ እንደሚኖር ብናስተውልና ያሉበት ድረስ በመሄድ ችግሮቻቸው ምን እንደሚመስል ብናስተውል እጅግ መልካም ነው፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የአገር መሪዎች በገጠር የሚኖረውን እረኛ “ምን ብሏል ዛሬ” ይሉ እንደነበር እንሰማለን፡፡ ምክንያቱም እረኛው አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ በሥነ ቃል አዋዝቶ ያስቀምጠዋልና ነው፡፡ በእርግጥም ሕዝብ ያለውን እየሰሙ እንጂ ሕዝብ ባለው እየተመሩ አገርን መምራት ማስተዋልን ይሻል፡፡
    ይሁንና ራስን ባዶ አድርጎ (ፊሊ.2፥7) የታችኛውን ሕዝብ ማየት ራስን ለቅምጥለትና ለስግብግብነት አይጋብዝም፡፡ ማንም ባለአዕምሮ የሆነ ሰው በረሃብ የታጠፈ አንጀት አይቶ ምግብ ስለማማረጥ አያስብም ፣ የትኛውም የሚያስብ ህሊና ያለው ሰው በአልጋው ላይ እንደትኋን የተጣበቀ ሰውን አይቶ ገንዘብ ስለማከማቸት አያምረውም ፣ ከንፈሩና እግሮቹ ተሰንጥቀው ፤ ልጆቹን እቤት አስርቦ ከሚመጣ ገበሬ ላይ ውድ ጫማ መግዣና ያማረ የእጅ መስቀል ወይም መስቀል መግዣ የሚጠይቅ ይኖራል ብሎ መገመት እጅግ የሚዘገንን ነው፡፡ ግን ሕዝቡ ያለበትን አለማየታችን  እንዲህ ያለውን ነገር ሳናፍር እያደረግን ነው ያለነውና ፥ መለስ ብለን ያለንበትንና የምኖርበትን ማህበረሰብ ብናይ ከጭካኔያችን ምናልባት እንራራ ይሆናል፡፡ (ማን ያውቃል?)

1.5      በፍርድ ቤት መክሰስና መካሰስ

     በታሪክ እስከአሁን ያልተሰማ እንግዳ ሆኖ እየሰማን ካለው ነገር አንዱ የቤተ ክርስቲያን የገዛ ልጆቿን ዓለማዊ ፍርድ ቤት አቁማ ፤ ጠበቃ ቀጥራ የመክሰሷ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ነገር በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ተከስቶ እንደነበር “ … ወንድም ወንድሙን ይከሳል፥ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን? እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው።” (1ቆሮ.6፥6-7) በማለት ሐዋርያው አስቀምጧል፡፡
   በእኛ መካከል ያለው ግን በሐዋርያው ዘመን እንዳሉት በአማኞች መካከል ያለ መካሰስና መወነጃጀል ያይደለ በእኛ ዘመን ያለው በተደራጀ መዋቅር ውስጥ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ናት  ጠበቃ አቁማ የገዛ ልጆቿን የምትከሰው ፤ ያውም የክሱ ምንጭ ብዙ አገልግለው ስለማገዷ ምክንያት የሠሩበትን ደመወዝ መከልከሏ ሳያበቃ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ በአንድ ሀገረ ስብከት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ላይ በደመወዝ ክልከላ በተያያዘ የቀረቡ አስራ አንድ ክሶችን የማየት ዕድል ገጥሞታል፡፡ የሚያሳዝነው በሁሉም ክሶች ላይ ቤተ ክርስቲያን እንድትከፍል መወሰኑን ስናይ ደግሞ ምን ያህል ህግ “የማናከብር” መሆናችንን ያሳብቅብናል፡፡
   ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ “ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ ታታልሉማላችሁ፥ ያውም ወንድሞቻችሁን።” (1ቆሮ.6፥7-8) ያለው ፍጹም መንፈሳዊ ምክር እኛንም ከእንዲህ ያለ ውርደት ብዙ በጠበቀን ነበር፡፡ ምናልባት የዚህን መፍትሔ አሳንሰው አስተዳደራዊ መፍትሔ ነው ብለው “መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶችን እናቋቅም” የሚሉ ወገኖችን እሰማለሁ ፤ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን ትልቁ ድርሻ በጎችን ሁሉ በአንድ መጠበቅና የታላቁ ጌታዋን ቃል ለአለም ሁሉ መናኘት እንጂ ተመርቆ የተከፈተውን አዲሱንና ሕያው የጽድቅን መንገድ ዘግታ ፤ አዲስ ችሎት ሰይማ እንድታስሟግት አይደለም፡፡
  
1.6     ዝሙት

    መጽሐፍ ቅዱስ የዝሙትን መዘዝ በግልጥ ያስቀምጣል፡፡ በሥጋ ከሚያመጣው ደዌና በሽታ ባሻገር በግልጥ ቃል “ … አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም … አመንዝሮች  … የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (1ቆሮ.6፥9-10) በማለትም ይናገራል፡፡ ማምለጫውም አንድ መንገድ ብቻ ፥ እርሱም መሸሽ ብቻ እንደሆነ ታላቁ መጽሐፍ ያስቀምጣል፡፡ (ዘፍ.39፥12 ፤ 1ቆሮ.6፥18)
  አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መዲናይቱ አዲስ አበባ ላይ ባሉት ማሳጅ ቤቶች ላይ ፥ አቶ በላይነህ ዘለለውና አቶ ዮሴፍ አህመድ ከማክቤዝ ሚዲያ ኮሚኒኬሽንና ከአዲስ አበባ አስተዳደርና ኤች አይ ቪ መቆጣጠርያና መከላከያ ማስተባበርያ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ባቀረቡት አንድ ጥናት በአገራችን ያለው የዝሙት መንፈስ እጅግ አስፈሪ ከመሆኑም ባሻገር ለፍርድ እየሰባን መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በተለይ የሴት እንተኛ መሸታ ቤቶች ወደግለሰብ ቪላ ቤቶችና ወደማሳጅ ቤቶች መቀየራቸውን ላስተዋለው ድርጊቱ በሕገ ወጥ መንገድ በንግዱ ዓለም ከተሳተፉ ግለሰቦች ያለፈና ሌሎችም እየተቻኮሉ የገቡበት መሆኑን ያሳያል፡፡
  በሌላ አንድ ጥናት ደግሞ “ኢትዮጲያ የወሲብ ቱሪዝም ስበት (ማግኔታዊ መስህብ) ያላት አገር እየሆነች ነው” የሚል ዘገባም ቀርቧል፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ እጅግ አጸያፊ የዝሙት ነውር በመካከላችን አለ፡፡ የዚህ ነውር ተካፋዮች ደግሞ በውጪ ያሉት አለማውያንና አህዛብ ብቻ ሳይሆኑ “ከትንሽ እስከትልቅ የኃይማኖት መሪዎች ፣ ሰባኪዎች ፣ ዘማሪዎች ፣ ዲያቆናት ፣ ቀሳውስት ፣ መነኮሳት ፣ መነኮሳይያት ፣ ቆሞሳት ፣ ጳጳሳት ፣ ፓስቶች ፣ መጋቢዎች ፣ የሃገር መሪዎችና ባዕለሥልጣናት … ጭምር” ናቸው፡፡
    ከዚህ ባሻገር በየጊዜው በፍርድ ቤቶች እየበዛ ያለው የጋብቻ ፍቺ አስፈሪ ቁጥር፥ ነገ ትዳር ሊመሰርት በዝግጅት ላይ ላለው ወጣት ያለው አሉታዊ መልዕክትም ቀላል አይደለም፡፡ ውበት መመለክ ከተጀመረ ፣ ዘፋኝ ከበረከተ ፣ ሽንጥና ዳሌ እንደበሬ ሥጋ ረክሶ ለሽያጭ ከተገመተ … በእርግጥ አገር ለመቀጣቷ ፤ የመቅሰፍትን ፍርድ በራሷ መጥራቷ ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዋቢ መጥቀስ ይቻላል፡፡ (ዘፍ.6፥2 ፤ 13 ፤ 2ሳሙ.11፥2 ፤ 12፥10 ፤ ምሳ.6፥26 ፤ 32 ፤ ኤር.5፥7-9) በሌላ መልኩ ፦
              “ከወደዱም አይቀር መውደድ ነው አቡን
               መስቀል እየሳመ የሚስመውን”

              “መታማት ካልቀረ ባንተማ ልታማ
               ከግብጽ የመጣኸው አቡነ ሰላማ”
               “እንጦንስና መቃርስ ምንኛ ተጐዱ
                የልጆቻቸውን ሰርግ ሳያዩ የሔዱ”
የሚሉትና ሌሎች ህዝባዊ ሥነ ቃሎች እንዲሁ እንደዋዛ አስፈግገው የሚያልፉ ፤ የሚታለፉ አይደሉም፡፡ መነሾ ነገራቸው ምን እንደሆነ ያለትርጓሜ ያሳብቃልና፡፡ ይህንንም ዝሙት ግን  ከግብጻውያን አቡኖች (እንደ አምልኮው ሥርዓት) ተዋርሶን ነው ለማለት ካላፈርን በቀር (ኢትዮጲያ ዛሬም ቅድስትና ምንም ነውር የለባትም የሚሉ ጥቂት አይደሉምና) መጠሪያችን ሊሆን አንድ ሐሙስ የቀረው ነው፡፡   እንደመፍትሔ፦

1.6.1    ጳጳስ ሚስት ቢኖረው ወይም በምሳሌነት ሚስት ያላቸውም ቢሾሙ

     መጽሐፍ ቅዱስ ከኤጲስ ቆጶስ ዋና ዋና ባህርያት አድርጎ ካስቀመጣቸው መስፈርቶች በተደጋጋሚ የጠቀሰው “የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሚሆን” የሚለውን ነው፡፡ (1ጢሞ.3፥2 ፤ ቲቶ.1፥6 ፤ ፍትሐ ነገሥት.አን.5 ቁጥር 83 ፤ 89) ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስም የስድስተኛውን ጉባኤ ቀኖና አንቀጽ 12 በመጥቀስ “ኤጲስቆጶሳት ለመሆን መብት ያላቸው ግን በድንግልና የመነኮሱ የቅስናና የቁምስና ማዕረግ ያላቸው ናቸው፡፡” በማለት አስፍረዋል፡፡ ( ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ፤ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ፤ 1993 ፤አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ማህበረ ቅዱሳን ፤ ገጽ 57)  
     መጽሐፍ ቅዱስና የቤተ ክርስቲያናችን ፍትሐ ነገሥት አንዲት ሚስት ያለው ቢልም ይህ መሥፈርት ሆን ተብሎ ሲዘለል ያየንበት ጊዜም ደግሞ አለ፡፡ (ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ፤ 1993 ፤ አዲስ አበባ ፤ አሳታሚ ማህበረ ቅዱሳን ፤ ገጽ 113 ፤ እና ሐመር ፤ ፲፫ዓመት ቁጥር ፭ ፤ መስከረም/ ጥቅምት ፲፱፻፺፰ ዓ.ም ፤ ገጽ ፳፮)
    መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ኤጲስ ቆጶስ “የአንዲት ሚስት ባል የሚሆን” ካለ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መታዘዝ አጅግ የሚበልጥና መንፈሳዊ ብልኅነት ነው፡፡ ጥቂት ያይደሉ ጳጳሳት የመነቀፋቸውና በነውር የመያዛቸው ምክንያት ለዚሁ ቃል ካለመታዘዝ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ መጽሐፍ እንደሚል “ … ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት።” (1ቆሮ.7፥2) የሚለው ቃል መላውን አማኝ ክርስቲያን የሚመለከት ነው፡፡
    ቤተ ክርስቲያን መነኮሳትን ብቻ በመሾም ሳይሆን የአንዲት ሚስት ባል የሚሆኑት ፤ ቤተ ሰቦቻቸውንም በአግባቡ የሚያስተዳድሩትን ቅዱሳን ቀሳውስትም በመሾም “የአገልግሎቱን ቅድስና” ልትጠብቅ ይገባታል፡፡
   
1.6.2   ምንኩስና ከቅዱስ ጋብቻ በምንም እንደማይበልጥ ትምህርት ቢሰጥ

     ያለምንም ማስተባበያ በአብዛኛው ሰው ህሊና “በትዳር ተሳስረው በዚህ ዓለም ከሚኖሩት ሰዎች ይልቅ በብህትውና ወይም በምናኔ ወይም በምንኩስና ተወስነው የሚኖሩ ሰዎች ወደእግዚአብሔር የመቅረብ ወይም ቅዱሳን መሆን እንደሚቻላቸው“ ያምናሉ፡፡  እውነት ነው ከአገልግሎት አንጻር ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው “ … ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና … ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል ፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፥ ልቡም ተከፍሎአል።” (1ቆሮ.7፥7 ፤ 26 ፤ 32-33) እንዳለው እግዚአብሔርን የዘመናቸው ጌታ አድርገው ዕድሜያቸውን ሳይከፍሉ ለጌታ ብቻ መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቡ ከባዕለ ትዳሮች ይልቅ የተሸለ የአገልግሎት በር አላቸው፡፡
   ይህን ብቻ ይዞ ግን መንኩሶ ፣ መንኖ ፣ በህትዎ … መኖርን ከቅዱስ ጋብቻ አብልጦ ማቅረብ  የተሳሳተ መንገድ ነው፡፡ ለሰው ሁሉ የተሰጠው የብርታትና የመተባበር መንገድ ቅዱስ ጋብቻ ነው (ዘፍ.2፥18 ፤ መክ.4፥12 ፤ ማቴ.19፥5 ፤ 1ቆሮ.7፥2) ፤ ያለጋብቻም ሆነ በጋብቻ ጸንቶ መኖርን “ … ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም ፥ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል ፤ ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና ፥ መልካም አደረገ ። እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ።” በማለት አስቀምጦታል፡፡ (1ቆሮ.7፥37-38) ስለዚህም በድንግልና መኖር ከጋብቻ በምንም የሚበልጥ ነገር የለውም፡፡ ይህንን ማበላለጣችን ጵጵስናን ከድንግልና መኖር ጋር ብቻ አያይዘነው ጋብቻን አሳንሰነዋል፡፡ ይህ ግን በፍጹም ሊሆን አይገባውም ነበር፡፡

1.6.3   ወጣቶችን የሚመለከት ሥራ በሠፊው ቤተ ክርስቲያን ብትሠራ

   የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ሰኔ 16 2004 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ባዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ “የአብያተ ክርስቲያናት ትብብር ለሰላምና ለልማት” ሲል ባዘጋጀው አንድ መጽሔት በገጽ 53 ላይ የግሎባላይዜሽንን አሉታዊ ተጽዕኖዎች ሲያስቀምጥ፦
“ሀ. ዓላማዊነትን (securalism) ያስፋፋል ፤
ለ. በመጽሐፍ ቅዱስ ኅጢአት ለመሆናቸው የተረጋገጡ ተግባራትን እንደመብት ሊሰብክ ይችላል፡፡” ወዘተርፈ በማለት ያስቀምጣል፡፡
   እ.ኤ.አ. በ2007 የተደረገው የሕዝብ ቆጠራ እንደሚያሳየው በኢትዮጲያ ውስጥ 63.2 ከመቶውን የሚሸፍኑት ከ24 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶችና ሕጻናት እንደሆኑ ያሳያል፡፡ ይህ ማለት በአገሪቱ በአብዛኛው “በሸመገለ ጊዜ ከእርሷ ፈቀቅ እንዳይል፥ በሚሄድበት መንገድ የሚመራው አባትና መሪ” (ምሳ.22፥6) አብዝቶ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም “በኃያል እጅ እንዳሉ ፍላጾች፥ የጐልማስነት ልጆች እንዲሁ ናቸው …  ና” (መዝ.127፥3) በአግባቡ ሊገሩ ፤ ሊመሩ ይገባቸዋል፡፡ በኃያል እጅ ያሉ ፍላጾች ኢላማ የማይስቱት ገታሪው በአገባቡ ስለሚገትረው ነው፡፡ ልጆችም ኢላማቸውን እንዳይስቱ ቤተ ክርስቲያን በምክርና በተግሳጽ ትውልድን የመንከባከብ  አደራ ተረክባለችና (ኤፌ.6፥4) የአንበሳውን ድርሻ ከማህበረሰቡ በሚበዛ መልኩ በመያዝ ይህን ልታደርገው ይገባታል፡፡ 
    ከዚህ አንጻር ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች ላይ እየሠራች ያለው፥ እየደረሰ ካለው ጥፋት ጋር ሲመዛዘን ተካካይ ነው ብሎ አፍ መልቶ ለመናገር አያስደፍርም፡፡  በየአጥቢያውና አድባራቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም የተሰጣቸው ትኩረት እምብዛም ነው ፤ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በአመራርነት በአብዛኛው የያዩዙት ሞገደኞችና ስሜታውያን ከመሆናቸውም ባሻገር የቤተ ክርስቲያኒቱ “ሙሉ ዕውቀት” የሌላቸው ናቸው፡፡ እጅግ የሚያስፈራውና የሚጨንቀው ነገር ደግሞ በአንድ ሰንበት ትምህርት ቤት ላይ ለዘመናት የአመራር ሥልጣንን ተቆናጠው፥ አዲስ ተማሪዎች ሲመጡ የራሳቸውን ዶግማና ቀኖና የሚያስጠኑ ደፋሮችም መኖራቸውን ስናስብ በእርግጥም ቤተ ክርስቲያን  ወጣቶችን አብዝታ ችላ ማለቷን እናስተውላለን፡፡ በተጨማሪም “ዘመናዊነትንና መንፈሳዊነትን”  ከማደባለቅ አልፎ “እንደኅጢአት ሲቆጠሩ በግልጽ ያየናቸው ተግባሮች (ለምሳሌ፦ ዝሙት ፣ ዘፈን ፣ መዳራት ፣ ርኩሰት ፣ የዝሙት ፊልሞችን ማየት ፣ አድመኝነት …) በአንዳንድ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ወጣቶች ዘንድ መታየቱን ልብ ይሏል!!!
    የእግዚአብሔር ቃል በሚሰበክበት ጉባኤ ላይ ተቀምጦ ቃሉን እየሰማ ፣ ቅዳሴ ቆሞ እያስቀደሰ ፤ ፎስ ቡክ ፣ ጐጉል የሚጐለጉል ወጣት እየበዛ ፤ ሥርዓተ አምልኮ መስመሩን ሲስት እያየን ነው፡፡ ቴክኖሎጂንና መንፈሳዊነትን አለማስታረቅ ፤ ለዚህም የሚጠቅማቸውን ትምህርትና ከዝሙት እንዴት መሸሽ እንዳለባቸው ያለውን የሥነ ጾታ ትምህርት መንፈሳዊ ለዛውን ጠብቆ በግልጥ የሚሰጥበትን መንገድ ማደላደል እጅግ ሊታሰብበት የሚገባ ነገር ነው፡፡  ይህ ግን አለመሥራቱ ብቻ ሳይሆን አለመታሰቡ ለምን? የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡


1.6.4   ሕገወጥ ደላሎችንና ነጋዴዎችን ቤተ ክርስቲያን በግልጥ መቃወም

   ትላንት ቤትና መኪና ለመሸጥ በድለላ ሥራ የተሰማሩ አብዛኛዎቹ ሰዎችና እጅግ በጣም አዳዲስ ደላሎች፥ ዛሬ የተሰማሩት በትምህርት ገበታ ላይ የተሰማሩትንና በየቤቱ ያሉትን ጨቅላ ወጣቶችንና ሕጻናትን ህሊና ለሌላቸው ባዕለጠጎችና ባዕለ ሥልጣናት የሚደልሉ መሆናቸውን ፤ ይህም ድርጊት ከዕለት ዕለት እየጨመረ እንጂ ምንም አለመቀነሱን እያስተዋልን ነው፡፡
   ቤተ ክርስቲያን የማህበረሰቡ አንዱ ገጽታ ናት ፤ ማህበረሰቡ በሚጎዳበት በአንዱ ይሁን በብዙ ነገር እርሷም የችግሩ ተጎጂ ፤ ተጋሪም ናትና ይህን ከባድ አደጋ ከማስወገድ አንጻር የእርሷም ድርሻ ጉልህ ነው፡፡ በሞቴላቸውና በሆቴላቸው ሕጻናትንና ወጣቶችን ለዝሙትና ለግብረ ሰዶም የሚያከማቹ ፤ ሃብትን የሚያጋብሱ ነጋዴዎችና ደላሎች፥ በአንድም ይሁን በሌላም መንገድ ከቤተ ክርስቲያን ጋር የመገናኘት ዕድላቸው ሰፊ ነው ፤ ቤተ ክርስቲያን ግን እነዚህን ሰዎች በጉያዋ ባለመምከር ፤ ባለመገሰጽ ፣ ባለመቆጣት ዝም ብላ ተሸክማ የምትኖርበት አቅምም ሆነ ትዕግስት ፈጽሞ ሊኖራት አይገባም፡፡
    እኒህ ሰዎች የሚያበላሹትና የሚመርዙት ግለሰቦችን ሳይሆን ትውልድን ነው፡፡ የትላንቱ “የውቤ በረሃ ትውልድ” ይነስም ይብዛም አሁን ባለው ትውልድ ላይ ያስቀመጠው የዝሙትና የስድነት ሕይወት እንዲሁ በቀላል የሚታለፍ አይደለም፡፡ የዚያ አሻራ ሳያገግም ሌላ ረመጥና እሳት በትውልዱ ላይ የሚጨምሩትን ግን በዝምታ ማለፍ ለቤተ ክርስቲያን “በእንቅርት ላይ … ” እንደሚባለው ጉዞዋን ጨለማና ከድጥ ወደማጥ ያደርግባታል፡፡
                      ይቀጥላል

6 comments:

 1. Medihanialem keseferebh seytan yalakh. Egziabhier lib ystachihu

  ReplyDelete
  Replies
  1. ergetegnanegn satanebew new yehenen yetsafekew AnonymousMarch 11, 2015 at 7:19 AM keegziabhier yehonene lib magegnte melekame new leantem yenureke

   Delete
 2. Yedigil lij welde amlak, eyesus kirostos yaderebihin saitan yigesitsilih..... Be medhanite Eyesus kirstos sim zore bel saitan!!!!

  ReplyDelete
 3. ይቀጥላል
  የእውነትና የቤተክርስቲያን ጠላቶች የተሰማሩበትን የጥፋት ተልኮ ለማራመድ የሚጉሱሙት ነጋሪት የእውር ድንብር ነጋሪት ነው። የሚናገሩትንና የሚጽፉትን የማያውቁ የእነሱን የሰይጣን ማንፌስቶ እውነትና ቤተክርስቲያን ትክክል አይደላችሁም ስላለቻቸው ብቻ በጥላቻ ብቻ የሚተቹና የሚያጥላሉ ግብዝ ናቸው። የይቀጥላል ተብየ ጽሑፍ ጸሐፊ እየተናገረ ያለው ለዚህ ማሳያ ነው። ጽሑፍ ተብየው አስተያየት ይሁን ማሳሰቢያ፤ እርዕሰ አንቀጽ ይሁን መልክት፤ ወንጌል ይሁን የጥናት ጽሑፍ እዚህ አዛ የሚቀባዠር ምን ተብዬ ጽሑፍ እንደሆን የማይታወቅ ልቦለዳዊ አሉባልታ ነው። ይህ ጸሐፊ ለቤተክርስቲያን ካለው ጥላቻ የተነሳ በአደጋ ክብ እያለ የሚወነጅላትና ጠልቶ ለማስጠለታ ከሚዳክርባቸው አንዱ የግለሰቦችን የምግባር ክንዋኔዎችን ነው። ይህ ግለሰብ አለም የሚተገብረውን የምግባር ብሉሹነትን ሁሉ የአንዲቷ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን ተግባርና መገለጫ ለማድረግ ምንም አልቀረው። የጥፋት ተልኮውንና ቤተክርስቲያንን የመንቀፍና የማስጠላት አላማው እውነተኛ ለማስመሰል የእግዚአብሔርን ቃል ይጠቀማል። አንዳንድ ይዛመድልና ለመሰሪው ተልሿችን መከላከያ ይናሉ የሚሏቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እየተጠቀሙ ቤተክርስቲያንን ይፈታትናሉ ልጆቿንም ለማዋከብና ግራ ለማጋባት ይጥራሉ። የመጽሐፍን ቃል ትክክለኛ አገልግሎት በተሳሳተ መንገድ በመተርጎምና በማደናገር የጥፋት ተልሿቸውን አባታቸው ሰይጣን ጌታ ክርስቶስን ጥቅስ እየጠቀሰ እንደፈተነው እውነትንና ቤተክርስቲያንን ይፈትናሉ። የሚገርመው ይቅጥላል ባዩ ፀሐፊ ከቤተክርስቲያን ያልሆነ ሆኖ ሳለ ቤተክርስቲያኗ ውስጥ አለሁ ብሎ ነው የጥላቻና የሞት መርዙን እየረጨ ያለው። በንግግራቸውና በሚጽፉት ጽሑፍ ሁሉ እራሳቸውን ፍፁምና ንፁሕ እንከን የለሽ ሥጋ ያለበሱ አድርገው ነው የሚገልፁት። እስቲ አሁን ክርስቶስ ለኛ ቤዛ ሊሆን በመጣ ጊዜ እየነገራቸው ያልሰሙ በጥፋት ስራዎቻቸው የቀጠሉ፤ አብሮት እየዋለ እያደረ እንጀራውን ሁሉ በልቶ የካደው ይሁዳ ና የመሳሰሉት ነበሩና የክርስቶስ ችግር ነው ሊባል ነውን? ይህ ፀሐፊም ግለሰቦች ያድርጉም አያድርጉ ነገሮችን ሁሉ ቤተክርስቲያን ላይ ነው እየደፈደፈ ያለው። ለምን ግን በአንዲቷ ቤበክርስቲያን ላይ ይሁሉ የሰይጣን ዘመቻ?ለምን ይሁሉ የቤተክርስቲያኗ አካል ሳይሆኑ ማስመሰል?ለምን ስለሌሎች የእምነት ድርጂቶች አይናገሩም? ለምን የቤተክርስቲያን እምነቷ ለኛ አይሆንም ካሉና የራሳችን የእምነት አስተሳሰብ አለን ካሉ የቤተክርስቲያን ለራሷ ትተው በግልጽ ራሳቸውን ችለው ያመኑበትን አያራምዱም? መልሱ አንድና አንድ ነው። ቤተክርስቲያን የክርስቶስ ስለሆነች። እውነት ስላላት። የጽድቅ ቤት ስለሆነች ነው። ጠላት ደግሞ የክርስቶስ የሆነውን ሁሉ መተቸት፣ መክሰስ፣ ተመሳስሎ ገብቶ ማተራመስ እና ብዙ የጥፋት በትሮችን መሰንዘር ነው። ይህ ይቀጥላልም ይኸው የሰይጣንን ተግባር ነው አይምሮውን ሳይቆጠቁጠው እንደመጣለት ያንንም ይህንም የሚተቸውና ቤተክርስያንን የሚወቅሰው። ቀጥሎት ቀጥሎት በምን እንደሚሰፍውና ቅጥሉ እስከመቸ ፀንቶ እንደሚቆም ባይታወቅም ነገም የይቀጥላል ሀሜትና ማጥላላት እራሱን ደግሞ ሊቅና ፍፁም የማድረግ ትረካው ያው ይቀጥላል ነውና ይቀጥል። ቤተክርስቲያንም በአለቱ ተተክላለችና የተቀጠለው አሉባልታና ከንቱ ትችት ይበጠሳ እሷ ግን ፀንታ ትቆማለች።

  ReplyDelete
  Replies
  1. ውይ ዳሞት ምን ይሻልሃል? ሰው እንዳንተም ሆኖ ይፈጠራል? አይንህን ጨፍነህ እኮ ነው የቆምከው። አንተ ላይ የሚሰራውን መንፈስ ጌታ ይገስጸው

   Delete
  2. ለanonymous narch 14, 2015 at 9:59pm
   ለእኔማ እውነትና ክርስቶስ ይሻሉኛል። ለእኔማ በእግዚአብሔር ደጂ በቤተክርስቲያን መጣል ይሻለኛል። ለእኔማ እውነትን መፈለግ እውነትን በአገኘሁበትም ፀንቶ መቆም ይሻለኛል። ለእኔማ ሳያምኑና የቤተክርስቲያኗ ወገን ሳይሆኑ መስሎና ተመሳስሎ ጭብል አጥልቆ የእውከት መንፈስን ፈፃሚ ከመሆን እኔ ለእምነቴ ብቻ በግልፅ ሆኘ መገኘትና መመስከር ይሻለኛል። ሌላው " ሰው እንዳንተም ሆኑ ይፈጠራል ?" ነው ያልከኝ። ወዳጄ፦ አንተኮ ሰው ከመሆን የወጣህ ከበልዓም አህያ አንስህ የተገኘህ ከእምነትና እውነትን ከመፈለግ የወጣህ በአሉባልታና በሰይጣን መንፈስ የሐሰት ክስና ስም አጥፊነት ነጋሪት የምትደልቅ የቤተክርስቲያን ጠላት የክፋ ሰራዊት ነህ። ሰው ማለት በማስተዋልና በበጎ ህሊና የሚመላለስ ከአሉባልታና በሐሜት፣ ከሐሰትና ሐሜት በአጠቃላይ በክፋት ፍሬዎች የተለየ ነው።" አይንህ ጨፍነህ እኮ ነው የቆምከው" የሚል አባባል ይሁን ተረት
   ተናግረሀል። አይንህ ጨፍነህ ማለትስ ምን ማለት ይሆን? መቆም ላልከው ግን በአመንኩት እምነትና ቦታ ፀንቸ እቆማለሁ። እንዳንተ በእንክርዳድ ብዛት ግራ ተጋብተህ መቆምም አቅቶህ እንደምትወዛወዘው መሆን አያስፈልግምና ነው። በመጨረሻ ስለመገሰጽ ተናግረሀል። ለመሆኑ ለመገሰጽ አንተ ማን ነህ? ደሞስ ጌታ የምትለው በአንተ ላይ ይሰራ ዘንድ ፤በክፋትና በተንኮል እንዲሁም በክህደትና በአለማዊ አስተሳሰብ እንዲሁም እውነትንና ህይወትን ትክድና ትቃወም ዘንድ እንዲሞላህ የፈቀድክመት የዚህ አለም ገዥ የቅዱሳን ከሳሽ በኔ ላይ ስልጣን የለውምና አትድከም። ገባህም አልገባህ እንዲህ ነኝ እኔ። ደህና ሁን ወዳጄ።

   Delete