Sunday, March 29, 2015

ቤተ ክርስቲያን በአደጋ ክበብ ውስጥ (ክፍል አራት)                                         ከዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
…….ካለፈው የቀጠለ
1.7.      እንደወንጌሉ ታላቅ መርሖ አለመኖር

1.7.1    መርሖ አንድ፦ “ሂዱ”

     ከወንጌል ትውፊትና ዋና መርሖ አንዱ ሂዱ የሚለው ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን የዕድሜ ልክ ታላቁ ተልዕኮዋም “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ …” (ማቴ.28፥19) የሚለው ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ተዘልላ ተቀምጣ የሚመጡትን ብቻ መጠበቅ የለባትም፡፡ ውኃ በአንድ ቦታ ሲቀመጥ ይሸታል ፤ አማኞችም አንድ ቦታ ሰፍረው እንዲቀመጡ አልተባለላቸውም፡፡ እንደዘር እንዲበተኑና እየዞሩ ወንጌሉን እንዲሰብኩ እንጂ፡፡  (ሉቃ.10፥1 ፤ ሐዋ.8፥4 ፤ 13፥1-4)
   ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት በትምህርታቸው የገለጡትን የክርስቶስን የማዳን እውነትና የገለጡትን አዲስ ኪዳን መሠረት አድርጋ በዓለም ሁሉ በመሔድ ወንጌልን መናገር ይገባታል፡፡ በእርግጥም የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአፍሪካ ወንድሞችና እህቶቿ ከተወቀሰችው አንዱ ነገር፥ ይህን የታላቁን ጌታ ታላቅ ተልዕኮ ይዛ ጎረቤቷ ያሉትን አፍሪካዊ ወንድሞችና እህቶቿን እንኳ እንደታዘዘችው ሄዳ ማገልግል ሳትችል ቀርታ ምዕራባውያን ከሩቅ አህጉር መጥተው ሰብከው እንደወሰዷቸው በቁጭት ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ ( እንዴት ልብ የሚነካ ቁጭት ነው!!!) እንኳን በሩቅ ላሉት በቅርባችን ላሉት መድረስ አለመቻላችን እንዴት ያለ ከባድ ድንዛዜ ያዘን የሚያስብል የቁጭት ጥያቄ ያጭራል፡፡ (በእርግጥ ዛሬም አልመሸም፡፡ ለአፍሪካ ስደት ፣ ዘረኝነት ፣ ጦርነት ፣ እርስ በእርስ አለመተያየት ፣ ሙስና  … መፍትሔ ለማምጣትና ለማሳየትና እንዲጠቀሙበት እንደጌታ በጸሎት ማሰብና ፍሬውን ማየት … አዎን! አልመሸም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሆይ! ተነሺና ሂጂ!!!)
   ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ያዘዘው ለእርሱ ደቀ መዛሙርትን እንድታፈራ ነው፡፡ ይህም ማለት ቤተ ክርስቲያን የአባላትን ቁጥር በማብዛት ላይ ብዙ መሥራት አለባት ሳይሆን የዚህን ዓለም ክፉ ኃጢአትና ርኩሰት ተጠይፈው የተለዩ ፥ ከበጎ ነገር ጋር የሚተባበሩትን (ሮሜ.12፥9) ፤ “የጨለማውን ሥራ አውጥተው የብርሃንን ጋሻ ጦር የለበሱትን” (ሮሜ.13፥12) ፤ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ የማይጠመዱትን” (2ቆሮ.6፥14) ፤ “በክርስቶስ ፍርሃት የሚገዙትን” (ኤፌ.5፥21) ፤ “ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር የሚርቁትን” (1ተሰ.5፥22) ፤ “በእውነት ቃሉ የሚኖሩትን” (ዮሐ.8፥31) ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ይገባታል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ማስፈጸሚያው ዋናው መርሖ ደግሞ ሂጂ ተብላለችና ፈጽሞ መቀመጥ አይገባትም፡፡

1.7.2   መርሖ ሁለት፦ “ወንድማማች ነን”

   ለመመካከርም ፤ ለመወቃቀስም ፤ ለመገሳሰጽም ፤ ለመቆጣጣትም … ድፍረት የሚሆነን ወንድማማችነት ነው፡፡ በክርስቶስ መንግስት “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው” እንጂ መለያየት ፤ መበላለጥ፥ አንዱ ሎሌ ሌላው ጌታ ፣ አንዱ ምንዝር ሌላው አለቃ ፣ አንዱ ትንሽ ሌላው ትልቅ ፣ አንዱ ታዛዥ ሌላው በበላይነት አዛዥ የሚሆንበት የሥልጣንና የሹመት ተዋረድ ሳይሆን የተጠራነው በወንድማማችነት እንድንዋደድ (ሮሜ.12፥9) ፤ በወንድማማችነት እንድናገለግል (ማቴ.23፥8) ፤ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ሆኖ እንደተመላለሰው ጌታ (ሮሜ.8፥29) በትሁት መንፈስ እኛም ልንመላለስ ይገባናል፡፡
   ዛሬ ታላላቅ እንደሆኑ የሚያስቡትን ወይም የሚመስሉትን (ገላ.2፥6 ፤ 9) ባጠፉና በስህተት በተያዙ ጊዜ እንደጳውሎስ በግልጥ መቃወም ያልተቻለን (ገላ.2፥11) በእርግጥም የአለቅነትና የአዛዥነት ሠንሠለት በመካከላችን ተዘርግቶ የወንድማማችነት መንፈስ ከመካከላችን ፈጽሞ ስለጠፋ ነው፡፡ ስለዚህም “ … ለእውነት እየታዘዝን ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችንን አንጽተን እርስ በርሳችን ከልባችን አጥብቀን ልንዋደድ ይገባናል።” (1ጴጥ.1፥22)

1.7.3   መርሖ ሦስት፦ “ወንጌሉ መሸቃቀጥ አይሻም”
                      
                  “የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ
                  ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር
                   እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን
                     እንናገራለን።” (2ቆሮ.2፥17)

“የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት
  ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት
   አስታወቅናችሁ።” (2ጴጥ.1፥16)

          ወንጌል በብልጣ ብልጥ አቀራረብ ፈጽሞ አይገለግልም፤ ወይም ሀብትን ፣ ተቀባይነትንና ስኬትን፣ መወደድን ፣ ዝናንና ክብርን ፣ የዕለት እንጀራቸውን ለማግኘት ሲሉ ወንጌል መስበክ የሚጠይቀውን ዋጋ (መስዋዕትነት) ችላ በማለት ለማገልገል የወንጌልን ክብር የሚቀንሱትን ሐዋርያው በቁርጥ ቃል ሲናገራቸው እናያለን፡፡ ወንጌልን በመሸቃቀጥ የሚያገለግሉ ሰዎች ሰዎችን የመግባባት “ችሎታ” (ብልጣ ብልጥነት) ያላቸውና በራሳቸው የሚመኩ ሰዎች ናቸው፡፡ ትልቁ ትኩረታቸው የወንጌል ምስክርነት ሳይሆን በወንጌል ካባነት ሀብትን ማጋበስ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ይሰብክ የነበረው ከማንም ቀለብ ሳይሰፈርለት በራሱ ወዝ ጥሪት ሲያገለግል (ሐዋ.18፥3 ፤ 1ቆሮ.9፥12 ፤ 2ቆሮ.11፥7) እንዲያውም ስለሌሎች መዳን “ያላቸውን ሳይሆን … ገንዘቡንም ፥ ራሱንም በመክፈል ያገለገለ ነው፡፡ (2ቆሮ.12፥14)፡፡ ወንጌሉን በመሸቃቀጥ የሚያገለግሉቱ ግን አንዳንዶች “መጥፎውን ረብ በመመኘት” (1ጴጥ.5፥2) ሌሎች ደግሞ “ለወገናቸው ወይም ለግል ምኞታቸው [ጥቅም] ከቅንነት ጎድለው” ወንጌልን ይሰብካሉ፡፡(ፊሊ.1፥17)
    በዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ወንጌሉ የሚሸቃቀጠውና ሥፍራውን ያጣው ስለሆድ መብል ነው፤ በተለይ እንጀራቸውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የመሰረቱት (ከእጅግ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ በቀር) “ወንጌሉን በወንጌሉ ክብር” ሳይሆን ጳጳስ ፣ የደብር (የገዳም) አለቃ (አበምኔት) ለማስደሰት ብቻ አስበው እንጂ ስለእግዚአብሔር ክብር ፍጹም ተጨንቀው አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ በየስብከቱ መሐል ዘወር እያሉ ከኋላ ላለው አለቃና ጳጳስ እየሰገዱና እጅ እየነሱ አበላቸውንና ደመወዛቸውን  ያበስላሉ እንጂ የበላዩንና የተጠሩለትን ትልቁን ጌታ ትዝ ብሏቸው ሲያገለግሉ ብዙም አይስተዋልም፡፡
   የስብከት ማዕከል የሆነውን የክርስቶስን ነገረ ድህነት ዘንግተው እልፍ ዕላፍ ቦታ ዘባርቀው ከመድረክ የሚወርዱ ለቁጥር የሚታክቱ ናቸው፡፡ በእርግጥም ወንጌል የጨከነና የማይደራደር አገልጋይ እንጂ በየመሐሉ ገንዘብና ዝና አሳዳጅን አትሻም፡፡ ክርስቶስን በእውነተኛ ግርማው እንደሐዋርያው ጴጥሮስ  ያየው ሰው በዚህ ዓለም ያለው ነገር ያንስበታል እንጂ ከክርስቶስ ወንጌል ይልቅ ተረታ ተረትን አያስቀድምም፡፡
    በእርግጥም ክርስቶስን በግርማው ያላዩ ሰዎች ብልሃታዊ ተረትን ፈጥረው ሕዝብን ከወንጌል ለይተው ቢያስቱት የሚደንቅ ነገር አይደለም!   


1.8   ግብረ ሰዶማዊነት

“ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ …” (ሮሜ.1፥26-27)

“ … ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ … የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”   (1ቆሮ.6፥9-10)

          
    ኀጢአትን አዘውትረው ለሚሰሩ ሰዎች ሁሉ (ክርስቲያኖችን ጭምር) መንፈሳዊ ሞት የሚያገኛቸው መሆኑን ታላቁ መጽሐፍ ደጋግሞ ተናግሯል፡፡ (ሮሜ.6፥16 ፤ 8፥13 ፤ ገላ.5፥21 ፤ ኤፌ.5፥5-6 ፤ 1ዮሐ.2፥4 ፤ 3፥9 ፤ ያዕ.1፥15) ኀጢአትን በተመለከተ ምንም መታለል አይገባም ፤ ብዙ ሰዎች በክርስቶስ ሞት ያገኙትን ነጻነት ለራሳቸው የኃጢአት ሥራ በነጻነት ለመፈጸም እንዲያመቻቸው ሲጠቀሙበት እናያለን፡፡ ይህንንም በተመለከተ ታላቁ መጽሐፍ ፦ “ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ … ” (ገላ.5፥13) እንዲሁም “አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ።” (1ጴጥ.2፥16) በማለት በግልጥ ያለምንም ማወላወል አርነታችንን ኀጢአትን ለመፈጸም እንደመሸፈኛ ማቅረብ እንደማንችል ያስቀምጣል፡፡
   ግብረ ሰዶማዊነት አስነዋሪ ምኞት በመሆኑ (ሮሜ.1፥26) ፍጹም ኀጢአት ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ኀጢአት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ፈጽሞ ልትተባበር አይገባትም፡፡ ነገር ግን ዛሬ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ይህን ለመቃወም አቅም እያጣች የመጣች ይመስለኛል ፤ የምዕራቡ አለም አብያተ ክርስቲያናት ዛሬ ላይ በግልጽ ተቀብለው በየአብያተ ክርስቲያናቱ እንደመብት ቆጥረውት እየፈጸሙት ነውና የዚያ ተጽዕኖ አሻራና በዋናነት የእኛም ኀጢአተኝነት ታክሎበት በአስፈሪ ፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን እያየን ነው፡፡
   ቤተ ክርስቲያን ከመቃወም ዝምታን መምረጧ ብቻ ሳይሆን በዚህ ጉዳይ የሚሳተፉና የተሳተፉትን አገልጋዮችና አባላቶቿን ዝም ብላ በጉያዋ ሸሽጋ ማስቀመጧ የቅድስና ቀሚሷን በፈቃዷ ለማውለቅና ለእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣ ራስዋን እያዘጋጀች ይመስላል፡፡ በአንድ ወቅት አንድ አገልጋይ በዚህ ነውር በግልጽ ተይዞ በንስሐ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ከአንዲት “የቤተ ክርስቲያን ሴት አዛውንት” አንደበት የተሰማው መልስ ምት እጅግ አስደንጋጭ ነው፡፡ “እናንተ በእርሱ እንትን … (በስም ነው የጠሩት)  እናንተ ምን አገባችሁ? … እርሱ የፈለገውን ቢያደርግበትስ?” እንዲህ በቤተ እግዚአብሔር ተቀምጠው ኀጢአተኞችን የሚያበረታቱ “ቀላል አዛውንቶች” ቤተ ክርስቲያን አክብራ ፤ አንከብክባ መያዟ እጅግ ለልብ የማይሽር ቁስል ሕመም ነው፡፡
 ------ይቀጥላል

4 comments:

 1. the dogs will shout and the camels will go ,the character of a dog is to shout at others when we are talking about other it is the measure of our personality,degmomem begziabher bet beykerta enji beygebagnal anemelalesem debek agendachuh tetachu kalue becha sebeku besew tsga atekenu egziabher sew selalhone betsga setotaw aystetsetem

  ReplyDelete
 2. ምን? ግብረ ሰዶም የቤተክርስቲያን ችግር ነው? የናንተው ነው እንጂ። አቶ አሸናፊ መኮንን የተባለው በ2003 የተወገዙው መናፍቅ እኮ የናንተው ነው እንጂ የኛ አይደለም። ግብረ ሰዶማዊ ነቱን ጸሀይ ሞቀው እኮ ብትደብቁትም መስማታችን አልቀረም። ስለዚህ ችግራችሁን እራሳችሁ ጋር አቆዩት እኛን አትጠጉን

  ReplyDelete
 3. ወዬ ጉድ ነው ዘንድሮ !!! በአቢይ ጾም ውስጥ እንኳን ሊቃነ ጳጳሳቱ ዱላ ይማዘዙ ጀምሩ። በጾም ወቅትም አንድም ለእግዚአብሔር የምታዘዝ ሊቀ ጳጳስ እንጣ። አለመታደል ነው። ክፉ ዘመን። ለጌታችን ሞት ተጠያቅዎቹ ሊቀ ካህናት ነበሩ። ለፓትራርኩም ሰላም ነሽዎች እነዚሁ ሊቃ ጳጳሳት ናቸው። እርሾው አልጠፋ ብሎ አስቸገረን ። የማቅ ነዋይ እንደዚህ ያስክራል ያሳብዳል። ጉድ ጉድ ነው። እነዚህ አባቶች የዓቢይ ጾመኞች ልባሉ ይችሉ ይሆን? ሰዉ ሰላም ያዉጃል አባቶቻች ቦክስ ያዉጃሉ ። ማቅን ለማስደሰት እግዚአብሔር ተርስቶ...............

  ReplyDelete
 4. "ወንጌል በብልጣ ብልጥ አቀራረብ ፈጽሞ አይገለግልም፤ ወይም ሀብትን ፣ ተቀባይነትንና ስኬትን፣ መወደድን ፣ ዝናንና ክብርን ፣ የዕለት እንጀራቸውን ለማግኘት ሲሉ ወንጌል መስበክ የሚጠይቀውን ዋጋ (መስዋዕትነት) ችላ በማለት ለማገልገል የወንጌልን ክብር የሚቀንሱትን ሐዋርያው በቁርጥ ቃል ሲናገራቸው እናያለን፡፡ ወንጌልን በመሸቃቀጥ የሚያገለግሉ ሰዎች ሰዎችን የመግባባት “ችሎታ” (ብልጣ ብልጥነት) ያላቸውና በራሳቸው የሚመኩ ሰዎች ናቸው፡፡ ትልቁ ትኩረታቸው የወንጌል ምስክርነት ሳይሆን በወንጌል ካባነት ሀብትን ማጋበስ ነው፡፡" (ከዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ)። ይህ ብቻ አይደለም መጀመሪያውኑ የሚመሰከርለትን ክርስቶስ ኢየሱስን በመጽሀፉ ውስጥ የተመዘገበውን እርሱን ይረዱታል? አዎ ባለመረዳታቸው ምክንያት ሁሉም በራሱ ጥበብ እያስተማረ ሰዎችን ከእግዚአብሔር መንገድ የሚለዩና በመካከላችን መከፋፈልልን መለያየትን የሚያደርጉ በቤተ ክርስትያናቻን በብዛት አሉ። በዚህም እግዚአብሔር አስቀድሞ እንደተናገረው
  " 9፤ ተደነቁ ደንግጡም፤ ተጨፈኑም ዕውሮችም ሁኑ፤ በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ሰከሩ፤ በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገደገዱ።10፤ እግዚአብሔር የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋል ዓይኖቻችሁን ነቢያትንም ጨፍኖባችኋል ራሶቻችሁን ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል።11፤ ራእዩም ሁሉ እንደ ታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ። ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ። ታትሞአልና አልችልም ይላቸዋል፤12፤ ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ። ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ። ማንበብ አላውቅም ይላቸዋል።13፤ ጌታም። ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፥ በከንፈርቹም ያከብረኛልና፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፥ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛልና" (ኢሳ. ም29) ብሎ የተናገረው ቃል በተግባር የምናይበት ዘመን ነው። ቤተ ክርስትያናችን በጠቢባን በሊቀ- በሐዋርያት በተለያዩ ቅጥል ስም ወይም ማዕረግ የሚጠሩ ሰዎች የሞላባት ቤት ናት። ነገር ግን ራእዩም ሁሉ እንደ ታተመ መጽሐፍ ቃል ሆኖባችዋል፤ ማንበብንም ለሚያውቅ። ይህን አንብብ ብለው በሰጡአቸው ጊዜ ጊዜ እርሱ ታትሞአልና አልችልም ይላሉ። ደግሞም መጽሐፉን ማንበብን ለማያውቅ። ይህን አንብብ ብለው በሰጡት ጊዜ እርሱ። ማንበብ አላውቅም ይላሉ።
  ስለዚህ በዚህ ምክንያት ቅዱሳን አባቶቻችን በእውነት የመሰከሩለትን ኢየሱስ ክርስቶስን በመጽሀፉ ውስጥ ተረድተው የሚያውቁት በጣም አናሳ ናቸው። ነገር ግን የገበያ ዘመን ስለሆነ ሁሉንም ነገር ለሥጋ ሥራ ቃሉንም በመዝሙር ሆነ ያስተማሩትን የሚቸበችብበት ታላቅ ጥሬ ዕቃ ሆኗል። ለዚህም ነው የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኛ በመራቁ ዛሬ ለጠላታችን ስይጣን ተጋልጠን ሁሉም የራሱን ቤተ ክርስትያን በየቦታው የሚገነባው። እንዲሁም በዚህ ምክንያት ሕይወት የሚሰጠው የእግዚአብሔር ሕያው ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በልቦናችን ባለመኖሩ ሕይወትን አጥተን በመንፈሳችን በሙታን ጉባኤ የምንገኘው። የእግዚአብሔር ቃል ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው። ይህም መንፈስ ደግሞ የተቀደሰ ነው። ስለዚህ ማነው ዛሬ እንደ ሐዋርያት ተንስቼ እውነተኛውን ቃል ልመስክር ብሎ የሚነሳ? ምክንያቱም ለመመስከር የግዴታ የምናመልከውን አምላክ ማን እንደሆነ ማወቅ አለብን። አባቶቻችን ያወቁት የተረዱት የእግዚአብሔር መንፈስ በእነርሱ ላይ የሆነው መምህራቸው ኢየሱስ ክርስቶስ በሕጉ በነቢያቱ በምዝሙሩ ያለውን ቃል ስላስተማራቸው ነው። እነርሱም ይህንኑን ቃል ዛሬ በወንጌል ላይ ጽፈው እኛም ከእነርሱ ጋር ህብረት እንዲኖረንና እነርሱ የተመገቡትን መንፈሳዊ ምግብ ተመግበን እውቅትን ጥበብና ማስተዋልን አግኝተን እንድንኖር ይመክሩናል። ነገር ግን ይህች ዓለም አሸናፊ በሆነችበት ዘመን ዘመናዊው ሐዋርያት ይህ ሁሉ ለእነርሱ ባዳ ነው። አባቶቻችንም እንዲህ ብለው መስክረዋል።
  "4 ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው።5 ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው?6 በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም።7 መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው።8 የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ።9 የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና።10 በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።11 እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው።12 ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።" (1ኛ ዩሐ. ም5) ብለው መስክረዋል። ይህ በውኃና (በጥምቀት) በደም (በመስቀሉ) መመንፈስም (በቃል)የተመሰከረለት "ኢየሱስ " ተብሎም ሲጠራ ይህ የእርሱ ስም አይደለም የባዳ ስም ነው ብለው የሚያወግዙም ብዙ ናቸው። ስለዚህ ልጁ ያለው ሕይወት አለው ስላለ ሁላችንም በቃሉ ልጁን በመመገብ ሕይወት አግኝተን የእግዚአብሔርን መንግስት ለመውረስ መዘጋጀት አለብን። ሰውን ተከትለን መሮጥ የለብንም። በሰዎች ጽድቅ መመራት የለብንም። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ጽድቅ ከመጽሀፉ በመረዳት በቃሉ ወይም በመንፈሱ መመላለስ ይገባናል። ምክንያቱም ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች እንዳስተማራቸው እንደመከራቸው፡
  "5 እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ።6 ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።7 ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤8 በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።9 እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም።10 ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው።11 ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል።" (ሮሜ ም8) ብሎ የእግዚአብሔርን መንፈስ በመመገብ ሕይወት እንድናግኝ ይመክረናል። ነገር ግን አሁን እኛ የምንጨነቀው ስለስንበት ድግስ ብቻ ነው። ይህ ሁሉ ከንቱ ነው። እባካችሁ መጽህፉን አንብቡና ተረዱት ዝም ብለን በልምድ ትምህርት እራሳችንና ወንድማችንን አንበድለው። ሁላችንም የምናመልከውን አምላክ ለማወቅ መማር ያስፈልጋል።
  ወስብሃት ለእግዚአብሔር

  ReplyDelete