Thursday, March 5, 2015

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የመሪነት ኀላፊነታቸውን በተገቢ እየተወጡ አለመሆኑን አስታወቁ፡፡

 •  Read in PDF 
 •   ምንጭ ተሐድሶ ዘኦርቶዶክስ ተዋህዶ
 •  
 • ቤተ ክርስቲያን ሰውም እግዚአብሔርም በሚወድደው መንገድ ልትመራ ይገባል፡፡  
 • ·        የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ሁለተኛ ዓመት በዓለ ሢመት ተከበረ፡፡
 • ·        የቤተ ክርስቲያን የመሪነት አቅም አጠያያቀቂ መሆኑ በፓትርያርኩ ተገልጧል፡፡
 • ·        ብፁዕ አቡነ ማርቆስ የስሕተት ትምህርቶችን፣ ሙስናንና በዓለም አቀፍ ደረጃ በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያ የተመለከቱ ቅኔዎችን በበዓሉ ላይ አቅርበዋል፡፡፡
የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ/ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓጥርያርክ ሆነው የተሾሙ መሆኑን አንባብያን ያስታውሳሉ ብለን እናስባለን፤ የካቲት 24 ቀን 2007 ዓ/ም ደግሞ የፓትርያርኩ በዓለ ሢመት ሁለተኛ ዓመት በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተከብሯል፡፡ በዓሉ የአንድ ፓትርያርክ በዓለ ሢመት ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን በዓል እንደመሆኑ መጠን ቤተ ክርስቲያን በአግባቡ በማስተባበርና በማደራጀት ብትጠቀምበት ትልቅ የትምህርት መድረክ ሆኖ ሊያገለግል ስሚችል እንደቀላል እድል ታይቶ ምእመናን የማይሳተፉበትና ካህናትም በግዴታ ትቀጣላችሁ ተብለው ለእንጀራ ብቻ የሚያከብሩት የፖለቲካ በዓል አይነት ሆኗል፡፡ በበዓሉ ላይ ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ መስቀልና ጽና ይዘው የመጡ አንዳንድ ካህናት ካልመጣችሁ ትቀጣላችሁ፣ ከሥራ ትባረራላችሁ እየተባሉ ስለመጡ ሲያማርሩ ሰምተናቸዋል፡፡ አንዳንዶችም በዓሉ በጸሎት ከተከፈተ በኋላ ልብሰ ተክህኖአቸውን በፌስታልና በቦርሳ እየከተቱ ወጥተው ሲሄዱ አይተናል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የበዓሉን ጠቃሚነት ለካህናትና ለምእመናን ከማስረዳት ይልቅ በፓርቲ አካሄድ አይነት ሰውን ባላመነበት በዓል ላይ በግድ እንዲሳተፍ ማድረግ ተገቢ ስላይደለ ካህናት ደስተኛ ስላልሆነ ነው፡፡
የበዓሉ ሥርዐተ-ጸሎት መዝ.109 ቁጥር 4 ላይ “መሐለ እግዚአብሔር ወኢይኔስሕ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከጼዴቅ እግዚአብሔር በየማንከ” በአማርኛ “እግዚአብሔር ማለ፤ አይጸጸትም፤ እንደመልከጼዴቅ ባለሹመት አንተ የዓለም ካህን ነህ፤ እግዚአብሔር በቀኝህ ነው” የሚለው መዝሙር በዲያቆን ከተዘመረ በኋላ ከዮሐንስ ወንጌል ምዕ. ቁጥር 15-24 ያለው ተነብቧል፤ ነገር ግን የወንጌሉም ሆነ የመዝሙረ ዳዊት መልእክት አልተሰበከም ወይም መልእክቱ ተብራርቶ አልቀረበም፡፡
እኛ እንደተረዳነው ከመዝሙረ ዳዊት የተሰበከው ቃል ለክርቶስ የተነገረ ትንቢትና በክረስቶስ የተፈጸመ የክርስቶስን የዘለዓለም ካህንነት የሚገልጥ ቃል ነው፤ የዕለቱ ተረኛ የሆነው የሰአሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካህናት ይህን መዝሙር የመረጡት ክርስቶስን ለመስበክ ፈልገው ከሆነ ተገቢ ነው እንላለን፤ የአባ ማትያስ ክህነት እንደመልከጼዴቅ ባለ ሹመት የዘለዓለም ነው ብለው ከሆነ ግን አባ ማትያስ እንደማንኛውም ሰው ሟች ስለሆኑ ሞት በሚከለክለው ሕይወት የተሾሙ እንጂ እንደ ክርስቶስ የዘለዓለም ክህነት የላቸውምና አስተካክሉ ብለን በክርስትና ፍቅር እንመክራቸዋለን፡፡
ወንጌሉ ግን በትክክል የፓትርያርኩን ኀላፊነት የሚመለከት ነው፤ ነገር ግን እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ የዛሬ ፓትርያርክና አባቶች ጳጳሳት፣ ካህናትና ሰባክያን ትወድዱኛላችሁን? ተብለን ብንጠየቅ አዎን ብለን ለመመለስ ድፍረት አለን ብለን አናስብም፤ ስለዚህ የወንጌሉን መልእክት በትክክል ተገንዝበን ለኀላፊነታችን ራሳችንን በእግዚአብሔር ቃልና በመንፈስ ቅዱስ ኀይል እናዘጋጅ ከማለት በቀር ሌላ የምንለው ነገር የለም፡፡
በዕለቱ የቀረቡ መዝሙራት መልእክት መሆን የነበረበት እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ነጻ ስላወጣትና የራሷን ልጆች ለራሷ መሪዎች አድርጎ ስለሰጣት ማመስገንና እርሱን እግዚአብሔርን ማክበርን እንዲሁም በዓሉ የዋለበት ወቅት የጌታ ሥራዎች በሰፊው የሚሰቡበትና የሚሰበኩበት የዐቢይ ጾም (የጾመ  ኢየሱስ) ወቅት ስለሆነ ወቅቱን የተመለከተ መልእክትን የያዙ መሆን ነበረባቸው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ግን እግዚአብሔርን ሳይሆን ሰውን (ፓትርያርኩን)፣ ወይም በዕለቱ መታሰቢያ የሌላቸውን ቅዱሳን የሚያመሰግንና የሚያከብር መዝሙርን ብቻ አቅርበው ለእግዚአብሔር ግን በበዓሉ ላይ ምስጋናና ክብር ከልክለውት ውለዋል፡፡ ይህ የሚሀነው ደግሞ ለእግዚአብሔር (ለክርስቶስ) የቀረቡ መዝሙሮችን በመቀየር ሰውን እንዲያመሰግኑ በማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ፡- “አንተ ውእቱ ዘላዕለ ኵሉ ሢመት ዘቤተ ክርስቲያን ወኵሉ ስም ዘይሰመይ” ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ማትያስ፡- ትርጉም፡- የሊቃነ ጳጳሳት አለቃ አባ ማትያስ ሆይ! “አንተ ከቤተ ክርስቲያን ሢመት ሁሉ በላይ ነህ፤ ከሚጠራ ስም ሁሉ በላይ ነህ”  የሚለው አንዱ ነው፡፡ አባ ማትያስ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አባት መሆናቸው ምንም ክርክር የለውም፤ የቤተ ክርስቲያን ሁሉ ራስ ግን ክርስቶስ ነው፤ ይህ መዝሙርም በመጽሐፍ ቅዱስ የተነገረው ለክርስቶስ ነው፤ ቅዱስ ያሬድም የዘመረው የቅዱስ ጳውሎስን ቃል ሳይለውጥ ለክርስቶስ ሰጥቶ ነው፤ ዛሬ ለአባ ማትያስ ተሰጥቶ ተዘመረ፤ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ስለሆነ በክርስቶስ ቦታ አባ ማትያስ ሳይገባ (ሳይተካ) ለክርስቶስ ተሰጥቶ በዕለቱ ቢዘመር ክርስቶስም ይከብራል፤ ቃሉም አይለወጥም፡፡
ሌላው ደግሞ በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች የቅድስት ድንግል ማርያም ወዳጆች ለመምሰል “ጽርሕ ንጽሕት ማኅደረ መለኮት እሞሙ ለሰማእት ሰአሊ ለነ ማርያም ቅድስት” ትርጉም፡- “ንጽሕት አዳራሽ፣ የመለኮት ማደሪያ፣ ሰማእታት እናታቸው፣ ቅድስት ማርያም ሆይ! ለምኝልን” የሚል መዝሙር ቀርቧል፡፡ የዚህ መዝሙር ችግሩ ክርስቶስ ፈጣሪያችን በአግባቡ ባልከበረበት ቦታ ለፍጡር ብዙ ቦታ መሰጠቱና በዕለቱ ለድንግል ማርያም ውዳሴን ለማቅረብ ምክንያት የሚሆን የበዓሉ ምክንያት ስለሌለ እንዲሁም በዓሉ እግዚአብሔር የሚመለክበትና የሚከበርበት ሆኖ ሳለ ለፍጡር ውዳሴ ማቅረቡ ኢክርስቲያናዊ ሥራ በመሆኑ ነው፡፡
የበዓሉን ታዳሚ ትኩረት የሳበውና የዕለቱ ልዩ ክስተት ሆኖ ያለፈው ነገር ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ያቀረቡት ቅኔ ነው፤ የቅኔው ይዘት በዓሉ፣ በጥምቀት መጽሔት ሊቀ ትጉሃነን ኀይለ ጊየርጊስ ዳኘ ያስተላለፉት የስሕተት ትምህርት፣ በቤተ ክርስቲያን እየተስፋፋና የቤተክርስቲያንን ህልውና እየተፈታተነ የመጣው ሙስና እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ቦታዎች በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለው መከራ ናቸው፡፡
ይለ ጊዮርጊስ ዳኘ የስብከተ ወንጌል መምሪያ ምክትል ኀላፊ ሆኖ እየሠራ ያለ መሆኑ ይታወቃል፤ ቀደም ሲል በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት ሳለ በዘራፊነቱ ከሚታወቀው ከያሬድ ጋር ሆኖ አንድ የማተሚያ ማሽን 25000 ብር ሸጦ ስለበላ ይህ በቤተክህነት የአስተዳድር ጉባኤ ተረጋግጦ እንዲከፍልና ከአሁን በኋላ በኃላፊነጽ ቦታ ላይ እንዳይሠራ ተብሎ የተወሰነ ቢሆንም “ ቀላይ ለቀላይ” እየሄዱ በሀገር ልጅነትና ለማህበር ደጋፊነት ተዛምዶ አቡነ ማቴዎስ ውሳኔውን መተግበር አልፈለጉም፡፡ በዚህ የቤተ ክህነት ሠራተኛ እያዘነ ሳለ “ክርስቶስ ንጹሐ ባሕርይ የሆነው ከምንጩ ከእናቱ ድንግል ማርያም ንጽሐ ባሕርይ የተነሣ ነው” ኢኦርቶዶክሳዊ ትምህርት በቤተ ክርስቲያኒቱ መጽሔት ላይ ጻፈ፡፡ የሚገርመው ነገር ደግሞ በኮሚቴ ታይቶ ይህ ትምህርት ኢ-ኦርቶዶክሳዊ ስለሆነ ይስተካከል ተብሎ የነበረ ቢሆንም ጸሓፊው በእምነቱ የቀና ስላልሆነ ሰእንቢ በማለት አዘጋጁን መጋቤ ምስጢር ወልደሩፋኤልን በማታለል አሳተመው፡፡ መጽሔቱን ያነበቡ ምእመናንና ካህናት በዚህ ጽሑፍ የስሕተት ትምህርት በጣም በማዘን ለሊቃውንት ጉባኤና ለቅዱስ ሲኖዶስ አቤት ቢሉም ማኅበርተኞቹ እየተከላከሉለት እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ማስተካከያ አልሰጠም፤ ሰአንዳንድ ሊቃውንት እንደሚሉት “አርዮስ ክርስቶስን ከአብ አሳነሰው፤ ኀይለ ጊዮርጊስ ደግሞ ከፍጡር አሳነሰው”፡፡ ምክንያቱም እርሱ ንጽሐ ባሕርይን ያገኘው ከምንጩ ከእናቱ እንጂ በራሱ ንጹሐ ባሕርይ አይደለም ብሏልና፡፡ ብፁዕ አቡነ ማርቆስም ይህን የክህደት ትምህርት የሚቃወም ቅኔ በበዓሉ ላይ እንዲህ ብለው አቅርበዋል፡፡
·        ለምንት አርመምኪ ኒቅያ ወኢተናገርኪ ምንተ፤
·        እንዘ እምድንግል ይትሌቃሕ ፈጣሪ ንጽሐ ባሕርይ መክሊተ፡፡
ትርጉም፡- “ኒቅያ ሆይ! ፈጣሪ የባህርይ ንጽሕና መክሊትን ከድንግል ሲበደር ለምን ዝም አልሽ? ለምንስ ምንም አልተናገርሽም?” የሚል ነው፡፡ መልእክቱ ክርስቶስ ንጽሐ ባሕርይ አለው የምንለው ከእናቱ ከደንግል ማርያም ንጽሐ ባሕርይ የተነሣ ነው ብሎ ክርስቶስ በባሕርዩ ንጹሕ መሆኑን ክዶ ሀይለጊዮርጊስ የጻፈውን የኒቅያ ጉባኤን የምታምን ቤተ ክርስቲያን ለምን ዝም ብላ አየችው? ብሎ ተቃውሞን የሚያሰማ ቅኔ ነው፡፡
ኀዳፌ ሐመር ማትያስ አመ ትገብር በዓለ፤ አዝኅን ማእበለ ሙስና ዘኮነ ሀያለ፡፡ ትርጉም፡- የመርከብ መሪ አባ ማትያስ ሆይ! በዓለን በምታደርግበት ጊዜ እያየለ የመጣውን የሙስና ማእበል አስታግስልን (ጸጥ አድርግ)” የሚለው ሁለተኛው ቅኔ ሙስናን አባ ማትያስ እንደተናገሩት እንዲከላከሉ ወይም እንዲያስታገሡ የሚያሳስብ ነው፡፡
የሁሉንም የበዓል ተሳታፊ አእምሮ የያዘው ሌላው የቅኔ መልእክት ደግሞ በእስክንድርያ፣ በሶርያና በሌሎችም የዓለማችን ክፍል በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለውን መከራ ያሰቡበት ቅኔ ነው፡፡ ዓለም ዛሬ “በሀዘነ ልብ ተረግዘት ወዘእንበለ አቅም ሀዘነት ንግሥተ ሰላም ኢትዮጵያ፤ እስመ ዘኢይትመወት ሞተ ሞተት እስክንድርያ፤ ወበሕማማ ለግብፅ ውሉደ ሶርያ ተእኅዙ እስመ እኅተ ግብፅ ሶርያ፡፡ ትርጉም፡- የሰላም ንግሥት ኢትዮጵያ በልብ ሀዘን ተወጋች፤ ያለመጠንም አዘነች፤ እስክንድርያ የማይሞት ሞትን ሙታለችና፤ በግብፅ ሕማምም የሶርያ ልጆች ተያዘች፤ ምክንያቱም ሶርያ የግብፅ እኅት ናትና” የሚል ነው፡፡ የቅኔው መልእክት አይ ኤስ የተባለው አክራሪ ቡድን በግብፅና በሶርያ ክርስቲያኖች ላይ እያደረሰ ያለው መከራ እኅት ቤተ ክርስቲያን ለሆነችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀዘን መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡
·        በመጨረሻም በዋና ሥራ አስኪጁ አቡነ ማቴዎስና በፓትርያርኩ ማጠቃለያ ንግሮች የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፤ የበዓሉ ጠንካራ ጎኖች እንደተጠበቁ ሁኖ ሊታረሙ ይገባቸዋል ያልናቸውን ነገሮች በመጠቆም ዘገባችንን እናጠቃልል፡፡
·        በዓሉ የቤተ ክርስቲያን በዓል መሆኑ ለካህናትና ለምእመናን የማስተማር ሥራ ቢሠራና ምእመናንና ካህናት በፍቅርና በአንድነት የሚያከብሩት እንጂ ካህናት ብቻ ያውም በግድ እየታዘዙ ሊያከብሩት አይገባም፡፡
·        በበዓሉ የቤተ ክርስቲያን አምላክ ክርስቶስ እንጂ ሰው ሊከብርበትና ሊመሰገንበት አይገባም፤ አቡነ ጳውሎስን ይነቅፉ የነበሩት አቡነ ማትያስም መመስገኑ እየጣማቸው የመጣ ስለሚመስል ይህ ከንቱ ውዳሴ የእግዚአብሔርን ክብር የሚነካ የቤተ ክርስቲያንን ዓላማ የሚያስት ስለሆነ በጊዜ ሊታረምና እግዚአብሔር ሊከብር ይገባል፡፡
·        በበዓሉ ቤተ ከርስቲያን ለ1600 ዓመታት በግብፅ ቤተ ክርስቲያን ሥር ሳለች ያገኘችው ጥሩ ነገርና ያጣቻቸው ጥቅሞች ካሉ በባለሙያዎች እየተጠኑ ለበዓሉ ተሳታፊዎች ቢቀርቡ፤
·        ተመሳሳይ መዝሙሮችን ከማቅረብና በማይጠቅሙ መርሐ ግብሮች ሰአቱን ከማጥፋት ይልቅ ትምህርተ ወንጌል እንዲሰጥና የመርሐ ግብር ይዘቱም መዝሙር ብቻ ሳይሆን ልዩ ልዩ ነገሮች ቢቀርቡ ጥሩ ነው በማለት ጥቆማችን በማቅረብ ጽሑፋችንን እናጠናቅቃለን፡፡
 እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ያስፋ! በቃሉ ታድሳ ለተጠራችበት ዓላማ  የበቃች ያድርግልን!

11 comments:

 1. Abaselama,

  Are you reporting that Abune Mathias is legitimate Patriarch? Are you saying that Abune Mathias is performing his duties? Or he is perfo2rming Abay Tsehaye's /weyane's duties? Aba marks? Do you really know what did in Minnesota and in many other places? It looks like Gebre Kidanemihret Desta's message is influencing this site?

  ReplyDelete
  Replies
  1. THIS IS CHURCH AFFAIR. WE ARE CHRIST'S CHILDREN.

   Delete
 2. great may God bless Ethiopia.

  ReplyDelete
 3. እባካችሁ ሰዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ በደመነፍስ ነው እየተመራች ያለችው እግዚአብሔር ምሕረቱን ያውርድላት: በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ሀገራችንም!

  ReplyDelete
 4. you are Anti Mary and Anti Christianity

  ReplyDelete
 5. በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!!!!

  በጣም ሊታረሙ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው። በማይገባና በማይጠቅም ሙገሳና ውዳሴ ከንቱ ጠፍሮ ስልጣኑን በፈቃደኝነት በማካፈል በሚታወቀውና ቸር ከሆነው አምላክ ጋር ማራራቅ አያስፈልግም። ከብር ማለት እግዚአብሄርን አክብሮና አስከብሮ መገኘት ብቻ ነው።

  ReplyDelete
 6. ለanonymous march 10,2015 at 4:32am
  ወዳጄ፦ መቸም ሲጠሩ ወይም የሆነ ሰው ሲል ሰምተህ ይሆናል እንጂ በአውነቴና በእምነት መንፈስ ተረድተህ አውቀሃቸው አይመስለኝም የእግዚአብሔርን የሶስትነቱን መጠሪያ በመግቢያህ ያስቀመጥኸው። ለሁሉም ወርደህ ስተት መናገር ብትጀምርም የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስን ስም መጥቀስህ መልካም ጅምር ብየልሀለሁ። ማን ያውቃል ወርደህ በተሳሳተ መንገድ የተቸኸውን ነገ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በእግዚአብሔር መንፈስ ስትረዳ ተሳስቸ ነበር ልትል ትችላለህ። ወዳጄ ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ታነብ ይሆናል። ግን በውስጡ ያሉትን የህይወት መልክቶችና ትምህርቶች የገቡህ አይመስለኝም። የጻፍከው አስተያየት እንሿን ቃላት ከቃላት ይጋጫሉ። አንዴ "ስልጣኑን በፈቃደኝነት በማካፈል ትልና መጨረሻ ላይ ክብር ማለት እግዚአብሔርን አክብሮና አስከብሮ መገኘት ብቻ ነው" ትላለህ። የጻፍከውን መለስ ብለህ ብትመለከተው የሚገባህም አይመስለኝም። እስቲ መልስልኝ የትኛውን ክብሩን ነው በፈደኝነት የአካፈለው? ደሞስ አንድ ክርስቲያን ከእምነቱ የተነሳ ክብርም ይሁን ውርደትን ያገኛል እንጂ ሌሎችን እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ ካላደረገ አይከብርም ተብሏልን? ታዲያ ሐዋሪያው ጳውሎስ በብዙ ነገር ልንከብድባችሁ ሲገባን እኛ ግን ከእናንተ ምንም አልወሰድንም ያለው ምን ለማለት ይሆን? ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ ማለትስ ምን ይሆን? ለምድር ነገስታትም እንሿን ቢሆን ታዘዙ የተበላውስ ምን ማለት ነው? አንድን ሰውስ ካላከበርከው እንዴት ልትታዘዘውና ትእዛዙን ትፈጽማለህ? ወዳጄ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ልብ ወለድ አይደለም እንዲሁ ማንብ ስለተቻለ ብቻ የሚነበብ። መማርና ማመን አለብህ። ካመንህ ቀኋላ ያወቅኸውን ለመጻፍ ሞክር እንጂ አንብቢያለሁ ብለህ በትቢት ስህተት አትጻፍ። በእንዲህ አይነት የትእቢት ትችት ክርስቶስ አይታለልም ፤ ህይወትም አያሰጥህም። ደህና ሁን!

  ReplyDelete
 7. ለዳሞት

  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን!!!!

  በጣም ሊታረሙ የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው። በማይገባና በማይጠቅም ሙገሳና ውዳሴ ከንቱ ጠፍሮ ስልጣኑን በፈቃደኝነት በማካፈል በሚታወቀውና ቸር ከሆነው አምላክ ጋር ማራራቅ አያስፈልግም። ከብር ማለት እግዚአብሄርን አክብሮና አስከብሮ መገኘት ብቻ ነው።

  ReplyDelete
 8. ለእንደዚህ ዓይነቱ ቱልቱላና ቱሪናፋ ስው ትህትና አይገባውም "ጃ ሞት"!!!

  ReplyDelete