Monday, April 20, 2015

አዝነናል

Read in PDF

አይሲስ የተባለ የሰይጣን ደቀ መዝሙር ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ክርስቲያን መሆናቸውን ብቻ እንደ ትልቅ ወንጀል ቆጥሮ ዘግናኝ በሆነ መልኩ ገድሏል። እንኳን  በወገን ላይ እንኳን በወንድም ላይ በእንስሳ ላይ እንኳን ሲፈጸም ማየቱ የሚዘገንንን ደርጊት በወንድሞቻችን ላይ ፈጽሟል። ይህ የክፉ መንፈስ አንጋሽና የሀሰተኛው ክርስቶስ እንደራሴ የሆነው ጽንፈኛ ድርጅት ለልባችን ስብራትን ትቶ አልፏል። የማኅበራዊ ሚዲያዎች በዚህ ጉዳይ በሰፊው ዘግበዋል። በርካታ ኢትዮጵያዊያንም የልባቸውን ስብራት በተለያየ መንገድ ገልጸዋል። ነገሩ ልብ የሚያደማ እንቅልፍም የሚነሳ ነው። ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ ሳያባራ የዚህኛው መከሰት ሀዘኑን ከባድ አድርጎታል።

 ለኢትዮጵያውያን ሳምንቱ ጥቁር ሳምንት ነው። ሀዘኑ ጥልቅ ቢሆንም በአይሲስ ታጣቂዎች እጅ ሰማዕት የሆኑት ወገኖቻችን እምነታቸውን አንክድም ብለው መሞታቸውን ማወቅ ደግሞ ደስ ያሰኛል። በዚህም ዘመን ለእውነት አንገት መስጠት መቻል መታደል ነው። በኢየሱስ ስም የምንቀበለው መከራ ለክብር ነው። ሞታችንም የድል አክሊል ነው። 

ምንም እንኳ አርፍዶ በዛሬው ዕለት የ3 ቀን ብሔራዊ ሐዘን ቢያውጅም በትናንትናው ዕለት የሀገራችን መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ያወጣው መግለጫ ብዙ ወገኖችን አሳዝኗል። ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው ምንም ማረጋጫ የለኝም ብሎ መግለጫስ ይሰጣል ወይ? መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ምን ቸገረው? ምን ጊዜ ወሰደበት? አሳማኝ ምክንያት ካለስ ለምን እስኪያረጋግጥ አልቆየም? የሚሉት ጥያቄዎች ለብዙዎች በቀላሉ መመለስ ያልተቻሉ እንቆቅልሾች ሆነዋል።  
ወንድሞቻችን ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቅስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ። ማቴ10:28 የሚለው ቃል እምነት ሆኖላቸው ሥጋን የሚገድሉትን ሳይፈሩ ለነፍሳቸው ጌታ ታምነዋል። መሞታቸው ቢያሳዝነንን ለሚበልጠው ተስፋ ታምነው በመገኘታቸው ደግሞ ደስ እንሰኛለን። ጌታን አለመካድ በሞት ውስጥ እንኳን ቢሆን ታላቅ ክብርን ያስገኛልና።

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም በጉዳዩ ላይ ሀዘንዋንም እና አቋምዋን የሚገልጥ መግለጫ አውጥታለች። ጥሩ ነው። ሀዘኑ የሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድነት የደረሰብንን በደል ተቃውሞዋል። አባ ሰላማም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የደረሰበው ሀዘንን ትጋራለች። በወንድሞቻችን ላይ የተፈጸመ ወንጀል በጣም አሳዝኖኗል። 
የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫበስመ አብ ወወልድ መወንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡ አሜን፡፡
ሚያዝያ 11 ቀን 2007 .. በሊቢያ ሀገር በንጹሐን ወገኖች ላይ ስለተፈጸመው አሠቃቂ ግድያ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
ሚያዝያ 11 ቀን 2007 .. ከእኩለ ቀን ጀምሮ በመላው ዓለም ያሉ የዜና ማሰራጫዎች በሰሜን አፍሪካ በሊቢያ የሜድትራኒያን ባሕር ዳርቻ አካባቢ አይ ኤስ በተባለ አሸባሪ ቡድን በንጹሐን ወገኖች ላይ አሠቃቂ ግድያ እንደተፈጸባቸው ዘግበዋል፡፡
በዘገባው፣ ከምኑም ከምኑ የሌሉበት ንጹሐን ክርስቲያን ወጣቶች በታጠቁና ፍጹም ሰብአዊነት በሌላቸው አሸባሪዎች ሲገደሉ የሚያሳየው ምስልም በመላው ዓለም እየታየ ይገኛል፡፡
አሠቃቂው ግድያ ስለተፈጸመባቸው ንጹሐን ወጣቶች ዜግነት እና ማንነት ግልጽ እና አስተማማኝ የኾነ መረጃ ለማግኘት ጥረት እየተደረገ ቢኾንም እስከ አኹን ድረስ በበርካታ የዓለም የዜና ማሰራጫዎች ሲነገር እንደሚሰማው፣ የዚኽ የግፍ ወንጀል ሰለባዎች ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች መኾናቸውን የዜና ማሰራጫዎቹ አክለው እየገለጹ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፈጣሪ የተሰጠች የማንኛውም የሰው ልጅ ሕይወት ሓላፊነት በማይሰማቸው እና በእነርሱ ላይ ሊደረግ በማይፈቅዱ ምንም ዓይነት ሰብአዊ ርኅራኄ በሌላቸው እንድትቀጠፍ ስለማትፈቅድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህን አሠቃቂ ድርጊት በጽኑ ትቃወማለች፤ አጥብቃም ታወግዘዋለች፡፡
ስለዚኽ፣ የዚኽ ግፍ ሰለባ የኾኑት ወገኖቻችን ማንነት ተረድተን፡-
  • በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሃይማኖታዊ እና ቀኖናዊ ትውፊት መሠረት አስፈላጊውን ኹሉ የምናደርግ መኾኑን ሕዝበ ክርስቲያኑ መላው ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ተገንዝበው ኹኔታውን በትዕግሥት እንዲጠብቁ፤
  • እንደዚኹም የተፈጸመው የጭካኔ ተግባር የማንኛውም ሃይማኖት ተቋምና እምነት የማይወክል የአሸባሪዎች ተግባር መኾኑን ተገንዝበው ኢትዮጵያውያን የኾኑ ኹሉ እንደ ቀድሞው በአንድነት በማውገዝ የዚኽ ድርጊት ፈጻሚዎች ኪሳራ እንጂ ምንም ዓይነት ትርፍ የማያገኙ መኾናቸውን በተግባር እንዲያሳዩዋቸው እናሳስባለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም

ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

አዲስ አበባከፌስ ቡክ ካገኘናቸው አንዱን እናካፍላችሁ

ይድረስ isis
መቼም የወንድሞቼ ገዳይ ሆነህ "ሰላም ላንተ ይሁን" ብዬ መጀመሬ እንደማይገርምህ እርግጠኛ ነኝ።ምክንያቱም አንተ የገዳዩ የአባትህ ልጅ እንደሆንክ ሁሉ እኔና ሰማዕታቱ ወንድሞቼም ለፍቅር ነፍሱን የሰጠን መግደል ሳይሆን ለፍቅር መሞትን ያስተማረን የመሀሪው የኢየሱስ ልጆች መሆናችንን ጠንቅቀህ ታውቃለህና። ለዚህም ደግሞ አንተ ሰይፍ እንኳን ደቅነህባቸው በድፍረትና ሙሉ በሆነ ሰላም ለስሙ ሞትን በደስታ የተጎነጯት ሰላማውያን ወንድሞቼ ምስክር ናቸው። አታውቅም እንጂ ብታውቅ እኮ እነዚህ የምትገድላቸው ክርስቲያኖች የሄዱበት መንገድ አስቀድሞ ኢየሱስ በደም የመረቀው ነው። ስለዚህ ከመከራው ይልቅ የምናየው ሄደን በፍቅር የሚቀበለንን በላይ ያለውን ናፍቆታችን ክርስቶስን ነውና በአንተ አረመኔነት እያዘንን በወንድሞቻችን ሞት ግን አሰይ! እልል!እንኳን አፀናልን!ስንል ሞኞች ሆነን ሳይሆን አድራሻቸው ሙሽራው ክርስቶስ መሆኑን አውቀን ነው።

ስለዚህ እኛ ሰማዕታት ስለሆኑ አምላካቸውን ስላልካዱ፤የሄዱት ወደ ታላቁ ደስታ ነውና በፅናታቸው ደስ ብሎናልና ደስ አይበልህ!!!!!!!!!!
ዘማሪት ፍቅርተ

2 comments:

  1. amen amen amen.we proud of our brothers who gave their life for truth christian faith. Anybody, anyone will die, anywhere,anytime. Buy those brothers died for Lord cross. We proud of them.................

    ReplyDelete
  2. ዘማሪት ፍቅርተ እኔም ይህንን የአንቺን ሐሳብ እጋራሻለሁ፡፡ በጣም ጥሩ መልዕክት ነው የገለፅሽው፡፡ እግዚአብሔር የአገልግሎት ዘመንሽን ይባርክልሽ፡፡

    የሺእመቤት

    ReplyDelete