Friday, April 24, 2015

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አስተዳደር የሥራ አስኪያጅ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ለውጥ ከተደረገ በኋላ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እየታዩ ነው


በሙስና የተዘፈቀውና በርካታ አገልጋዮችን በግፍ ሲጨቁንና ሲበዘብዝ የነበረው አማሳኙ የነቀሲስ በላይ አስተዳደር ከተሻረና ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ እና መጋቤ ብሉይ አአመረ አሸብር ከተሾሙ ወዲህ ጥሩ ጅምሮች እየታዩ መሆኑን እያስተዋልን ነው፡፡ ኃላፊዎቹ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በመልካም ጀማሮ የጀመሩት መሆኑ በርካታ ግፉዓንን አስደስቷል፡፡ የሥራቸው መጀመሪያ ያደረጉትም የተበላሸውን የማስተካከል እና ፍትሕ ያጣውንና የተበደለውን በተገቢው መንገድ መካስ መሆኑ ቀደም ብሎ የነበረውን ልቅሶና ጩኸት በተወሰነ መልኩ ወደ ደስታ ለውጦታል፡፡ በቀሲስ በላይ ሥራአስኪያጅነት ዘመን 80 የሚደርሱ የታገዱ፣ ሕገወጥ ዝውውር የተካሄደባቸውጉዳያቸው በእንጥልጥል ላይ የነበረ ነበሩ፡፡ ከእነዚህ መካከል አብዛኛው ጉዳያቸው መፍትሔ አግኝቷል፡፡ ይህን በጎ ጅምርና ሥራ አስኪያና ምክትላቸው እየወሰዱት ያለውን አዎንታዊ እርምጃ የተገፉ ብዙዎች በአድናቆት እየተመለከቱት መሆኑን መናገር እንችላለን፡፡ በአንጻሩ ለማድነቅ መቸኮል አያስፈልግም ጊዜው ገና ነውና ፍጻሜያቸውን አይቶ ነው ማመስገን የሚሉም አልጠፉም፡፡ ይሁን እንጂሰዎች መልካም ሲሰሩ ማመስገን ሲያጠፉ ደግሞ መውቀስና እንዲስተካከሉ ማድረግ ነው እንጂ፣ ምስጋናውንም ሆነ ወቀሳውን በጊዜ መገደብ ተገቢ አለመሆኑን ለአዳዲሶቹ ኃላፊዎች አድናቆት እየቸርን ያለን እናምንበታለን፡፡
በእነዚያ ወገኖች መከራከሪያ መሠረት አድናቆታችንም ሆነ ወቀሳችን በምክንያት ላይ የተደገፈ ካልሆነ ግን የክፉዎች ስብስብ ከሆነው ከማኅበረ ቅዱሳን የአድናቆትና የወቀሳ መንገድ አልወጣንም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ማኅበረ ቅዱሳን ዘርና ጐሣ እየመረጠ የሚያደንቅና ዘር እየለየ ስም የሚያጠፋ ነውና፡፡ ለምሳሌ ያህል አባ ወልደ ገብርኤል የተባሉ የትግራይ ተወላጅ መነኩሴ በ1998 ዓ.ም. ቆባቸውን ጣሉ፤ ትግራይ አባ ወ/ገብርኤልን ብቻ የወለደች ይመስል በየጋዜጣውና በአራት ኪሎ በሚገኙት ምግብ ቤቶች በሙሉ ፖስተር ሲለጥፍ፣ በየጋዜጣው ሲፅፍና ሲሳደብ መኖሩ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ የሚኖሩት ጳጳስ አባ ኤዎስጣቴዎስ ግን ጳጳስ ሆነው በዓለም የሚኖር ሰው እንኳን የማያደርገውን ከሁለት እህትማማች ጋር ግንኙነት እንደነበራቸውና በአሁኑ ጊዜ ቆባቸውን ጥለው ትዳር መስርተው የሚገኙ ሰው መሆናቸውን በተመለከተ አንድም ቀን ትንፍሽ አለማለቱ ከፈጸማቸው ታሪካዊ ስህተቶች አንድ ትልቅ ትዝብትና ማሳያ ሆኗል፡፡ ስለዚህ እኛን ከዚህ እኩይ ማህበር የሚለየን አንዱ ነጥብ ሰው መመስገን ያለበት በመልካም ሥራው ነው፤ መወቀስ ያለበትም በክፉ ሥራው ነው እንጂ በሌላ መስፈርት ሊሆን አይገባም ማለታችን ነው፡፡ አበው እንደሚሉት መልካሙን መልካም ማለት ትክክለኛ አስተሳሰብ ነው፤ ክፉውን መልካም ማለት ደግሞ አጋንንታዊ ነው፡፡ ስለሆነም ገና ያለጉቦ በተገቢው መንገድ ለድኾችና ለግፉዓን በተሰጠው ፍትሕ ከጅምሩ ስለተሠራው መልካም ነገር አድናቆታችንን መግለጽና በርቱ ከጎናችሁ ነን ማለት እንወዳለን፡፡

ምን ተሠርቶ ነው ለአድናቆት የተቸኮለው ሊባል ይችላል ብለን እንገምታለን፡፡ ከተሠሩ ሥራዎች መካከል አንዱ አይሞከርም የተባለውን በጥቂቶች እንደልብ በመገልበጥና በመዘረፍ የሚታወቀውን ሙዳየ ምጽዋትን በተመለከተ አቆጣጠሩ ዘመናዊ መንገድን የተከተለ እንዲሆን በማድረግ ባንክ ቤተክርስቲያን ተገኝቶ እንዲቆጥርና እንዲረከብ መደረጉ ነው፡፡ ይህ ገና በጥዋቱ ቆራጥነትና ልዩ ማስተዋልና ጥበብ የተሞላበት አሠራር የጥቂቶች ሲሳይና የሊቃውንቱ ማሳደጃ ለሆነው፣ በሕገ ወጥ መንገድም ይዘረፍ ለነበረው የሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ ትልቅ መፍትሔ ይዞ የመጣ አሠራር ነው፡፡ የሙከራ ቆጠራውም መጋቢት 28/2007 ዓ.ም. በቦሌ መድኀኔ ዓለም በባንክ እንዲቆጠርና በግልጽ እንዲገባ ሲደረግ ቀድሞ የነመምህር ሰሎሞን በቀለ የግል ርስት የነበረው የሙዳየ ምጽዋት ገንዘብ፣ እርሱንና ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቆጠራውን ለመታዘብ የተላኩ ሰዎችን ሳይቀር ደም እንባ ያስለቀሰ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ብልጽግናና ሕዳሴዋን ለሚመኙ ሐሴትና የምሥራች ሆኖ ያለፈ አጋጣሚ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ጅምር ለአንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ለዘለቄታው ተግባራዊ መደረግ አለበት፡፡ በአንድ ደብር ብቻ ሳይሆን በሁሉም አድባራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግበት ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ በዚህ ውስጥ ገንዘቡ ሲቆጠር ከደብሩ ካህናት መካከል ቆጠራውን በንቃት እንዲከታተሉ ኮሚቴዎች መሰየም አለባቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር ሙዳየ ምጽዋቱ ለግልበጣና ለዝርፊያ በማያመችና ዘመናዊ በሆነና ወጥ በሆነ መንገድ እንዲሠራ ማድረግ ቢቻልም ጥበቃውን ለማጠናከር ይረዳል፡፡
ሌላው ማሳያ በእነ ሊቀ አእላፍ በላይ መኮንን ፍትህ ያጡ እና ለተበደሉ ካህናትና ልዩ ልዩ ሠራኞች በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ ሥራ ሠርተዋል፡፡ ምክንያቱም አምላካችን ፍትህ እና ርትእ የባሕርዩ ስለሆነ ለስም አጣራሩ ውዳሴ ይሁንና ልጆቹ ፍትህ ሲያገኙ ይደሰታል፡፡ ቀድሞ እነ ቀሲስ በላይን እንጀራ ስጡን ያሉ አንዳንድ መነኮሳት ከሃያ እስከ ሰላሳ ሺህ ብር ድረስ ባለመስጠታቸውና የሚበሉት ስለሌላቸው ሲጉላሉ መቆየታው ይታወቃል፡፡ መጋቢት 28/2ዐዐ7 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት የነበረው ሁኔታ እንባ ያራጨ ነበር፡፡ ይኸውም መነኮሳቱ ተራብን ተቸገርን ብለው ሲያለቅሱና ቆባችንን ጥለን እንሄዳለን ሲሉ ለተመለከተ ሁኔታው እጅግ አሳዛኝ ነበር፡፡ ሲፈጸም የነበረው ግፍና በደልም ሰዎችን የት ድረስ እንደገፋቸው ትልቅ ማሳያም ሆኗል፡፡ እነ ሊቀ ማእምራን የማነ ግን እንባን አይተው ከንፈር መምጠጥ ሳይሆን የመረጡት ያለ ምክንያት ዘር ሳይቆጥሩ፣ ጉቦ ሳይቀበሉና ይዋል ይደር ሳይሉ በወሰዱት ማስተዋል የተሞላበት እርምጃ በቀቢጸ ተስፋ ውስጥ የነበሩት መነኮሳትና ሠራተኞች እንጀራ ሊያገኙ ችለዋል፡፡ ይህ በአምላካችን ፊት የተወደደ መስዋዕት እንደሚሆን ጥርጥር የለንም፡፡ ይበል ይቀጥል ብለናል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች በተለይም ሐራ ምንም አለማለቱ ከማስገረሙም በላይ፣  ይህን ጊዜ እነዚህ መነኮሳትና ሠራተኞች በጠቀሱት ምክንያት ቆባቸውን ጥለው ወደሌላው ቢሄዱ ኖሮ እገሌ የተባለ መነኩሴ ወይም ሠራተኛ መናፍቅ ሆነ ለማለት ማንም አይቀድመውም ነበር፡፡
እውነተኛ ርዳታ ሰጪ የሆነ ድርጅት ርዳታ ሲሰጥ ለተራበ ሰው ዳቦ ይሰጣል እንጂ አገሩን ወንዙን አይጠይቅም፡፡ እነ ቀሲስ በላይ ግን ድሃ ነኝ፣ ምንም የለኝ፣ አወዳድሩና ቅጠሩኝ፣ ተራብኩ፣ ለሚላቸው ጉቦ አምጣ፣ አገርህና ወንዝህ የት ነው? ቋንቋህ ምንድነው? በሚል ያለፉትን ጊዜያት እዚህ ግባ የሚባል ቁምነገር ሳይሰሩበት በማለያየት፣ ጐሰኝነትን በማስፈንና የግል ሀብታቸውን በማካበት ታሪካዊ ስህተት በመሥራት አሳልፈዋል፡፡ ማቆችም እነዚያን ክፉ ሥራዎች የተፈጸሙባቸውን ጊዜያቶች እያዩና እየሰሙ በዝምታ ነው ያሳለፉት፡፡ አሁንም እየተደረገ ያለውን መልካም ጅምር ሳይሰሙ ቀርተው ሳይሆን እያዩና እየሰሙ በብሎጎቻቸውም ሆነ በሌሎች ሚዲያዎቻቸው ምንም አልተነፈሱም፡፡ እነሱ ክስና መርዶን እንዲሁም ለእኛ ይጠቅመናል የሚሉትን ጉዳይ ብቻ እንጂ የምሥራችን እና መልካሙን ነገር ለማውራት አልታደሉምና፡፡ አሁን እኛ እንዲህ እያልን ያለነው ሥራ አስኪያጁንም ሆነ ምክትላቸውን በውዳሴ ከንቱ ለመጥለፍ ፈልገን ሳይሆን መልካም ሲሰሩ መልካም ግድፈት ሲኖር ልክ አይደለም ይህ ይስተካል ማለት መለመድ ያለበትና ለመለወጥ ወሳኝ ነገር ስለሆነ ነው፡፡ አሁን የተጀመረውም ለውጥ ዝም ብሎ የመጣ አይደለም፡፡ ዱሮስ የመማር ጥቅሙ ለውጥ ለማምጣት አይደለምን? ትምህርት ከባለቤትነት ስሜት ጋር ሲገናኝ ደግሞ መልካም ይሆናል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙ አንዳንድ ሠራተኞች ግን በዚህ አንዳንድ ለውጥ እያየን ባለንበት ወቅት ገንቢዎች መስለው አፍራሾች ስለሆኑና ምክራቸውም ምክረ አኪጦፌል ወይም ምክረ ሰይጣን ስለሆነ ወግዱ ሊባሉ ይገባል፡፡ ምክንያቱም እነርሱን የሚያሳስባቸው የቤተክርስቲያን ጉዳይ ሳይሆን ከየአድባራቱ የሚያገኙት የተዘረፈው ብር ጉዳይ ነው፡፡ እነቀሲስ በላይ አስፋፍተውት የሄዱት ዘረኛነት የተባለ መጥፎ በሽታ ጉዳይም ሊረሳ አይገባውም፡፡ ሌላው የአንዳንድ አድባራትና ገዳማት አለቆችና ጸሐፊዎች ለመዝረፍ እንዲመቻቸው በሕዝብ የተመረጡ የሰበካ ጉባኤ አባላትን “የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ናቸው” በሚል ውሸት ለስርቆት እንዲመቻቸው የሚነዙት ወሬ በጥንቃቄና በአጽንኦት ሊታይና ሊፈተሽ ይገባል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሙሰኞች ወዳጅና ለቤተክርስቲያን አሳቢ መስለው ነገር ግን ለዝርፊያ እንዲመቻቸውና የተጀመረውን መልካም ጅምር ለማደናቀፍ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ላይ እንዳሉ እየሰማን ነውና፡፡ በእርግጥ በዚህ ውስጥ የተሰማሩና ማኅበረ ቅዱሳንን ተገን ያደረጉ ሙሰኞች መኖራቸው ባይካድም እነዚህ ሰዎች ግን ስተው እንዳያስቱ በአንድ ወገን መረጃ ብቻ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ሁለቱንም ወገኖች አነጋግሮና በመረጃ አረጋግጦ ውሳኔ መስጠቱ እጅግ ጠቃሚ ነው እንላለን፡፡
እንዲህ የምንለው በከንቱ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በደብረ ከዋክብት አቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን የተፈጠረው ክስተት አግባብነት ባለው ሁኔታ ታይቶና ተጣርቶ ዳኝነት ይሰጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ምክንያቱም በአቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን የነበረው ሁኔታ ከአሁን በፊት የሚከፈል ገንዘብ ጠፍቶ በሰራተኛው ላይ የመበተን አደጋ አንዣቦበት የነበረ ቤተክርስቲያን ሲሆን አሁን ያለው ሰበካ ጉባኤ ከተመረጠ ወዲህ ግን በታሪኩ ከፍተኛ የሆነ ገቢ በጥቅምት 14/2007 ዓ.ም. ብር 720,000.00 /ሰባት መቶ ሃያ ሺህ ብር ማስገባት የቻለ ሰበካ ጉባኤ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ጠንካራ ሰበካ ጉባኤ ያለአግባብ መበልጸግ የለመዱ አለቃና ጸሐፊ እንደፈለጉ መሆን ስላልቻሉ ሰበካ ጉባኤውን በሐሰትና በክፋት በመወንጀል የማኅበሩ አባላት ናቸው፤ ደመወዝ አልፈርምም በማለት አላሰራ አሉን በሚል ምክትል ሊቀመንበሩ ያላለውንና ያላደረገውን ፈጥረው በመወንጀል እንዲነሳ አድርገዋል፡፡ እውነታው ግን ይህ ሳይሆን አለቃውና ጸሐፊው ከደመወዝ ውጪ በገዛ ፈቃዳቸው ሌላ ወጪ በመጨመር ሕገወጥ ደመወዝ ለቢሮ ሰራተኞች ብቻ በመጨመራቸው ምክትል ሊቀመንበሩ ደመወዝ ብቻ ነው መፈረም ያለብን እንጂ ለጭማሪው አልፈርምም በማለቱ ነው አላሠራ አለን ተብሎ እንዲነሣ የተደረገው፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ በድጋሚ በጥንቃቄ ቢታይ፣ ለወደፊቱም ሁለቱንም ወገን አነጋግሮ ውሳኔ መስጠት መልካም ነው የሚል አስተያየት አለን፡፡ በእርግጥ ይህን ጽሑፍ በዚህ ሁኔታ ካዘጋጀን በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት እየተደረገ መሆኑን እየሰማን ስለሆነ ፍትሕን ለማስፈን እየተደረገ ያለው ሁለቱንም ወገኖች አቅርቦ የማነጋገሩ ሂደት መልካም ነውና ተጠናክሮ ቢቀጥል መልካም ነው እንላለን፡፡
ከዚህ ቀደም ሊቀ ማእምራን የማነ በቤተ ክህነት ስብሰባ ላይ “በማኅበረ ቅዱሳን ስብስብ ውስጥ መልካምና ቅን ሰዎች የሉም አላልኩም፣ በቅንነትና በሐቅ ቤተክርስቲያንን የሚያገለግሉ ግለ ሰዎች የሉም አላልኩም” ሲሉ እንደተናገሩት እኛም የምንለው ይህንኑ ነው፡፡ ምክንያቱም የዚህ ማኅበር ችግር ከላይ ከአስኳሉ ላይ እንደመሆኑ ሊቃውንቱን የመክሰስ በዘር የመከፋፈል አቋሙን ያስተካክል፣ የአመለካከት ለውጥ ያምጣ፣ ዘመኑን ይዋጅ ነው እያልን ያለነው እንጂ ይጥፋ ይሰረዝ አላልንም፤ ምእመናን አነሱ እያልን እነርሱ ይቀነሱ የሚል አቋም የለንም፡፡ እንዲህ ሲባል ግን ከአስኳሉ በተጨማሪ የማኅበሩ አባላት ሆነው በጥፋት ላይ የተሰማሩ በርካቶችም መኖራቸው ሳይዘነጋ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በወጣው ዘገባ ላይ የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከአለቃው ጋር በመመሳጠር ዝርፊያውን እያጧጧፉት ያሉት የማኅበረ ቅዱሳን አባላት መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡
ሌላው እስካሁን ብንጮህም ሰሚ ያልተገኘለት የጎፋ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ችግር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኑን ሀብትና ንብረት ያለአግባብ ለአለቃውና ለቢሮ ሰራተኞች ጥቅም የዋለ በመሆኑ እነርሱ በከተማችን ውስጥ የሚገኙ ከበርቴዎች መካከል የሚቆጠሩ ሆነዋል፡፡ ለዝርፊያቸው እንዲመቻቸው የነደፉት ዋናው ስልትም ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር መስማማት ነው፡፡ ለዚህም ለማኅበረ ቅዱሳን 5 ኪሎ ካለው በተጨማሪ 2ኛውን የማእከል ሕንጻ እንዲገነባ ቦታ በመፍቀድ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ባቋቋሙት ካቴድራል የእርሳቸውን ስም በመልካም ማንሣት ለማይሆንለትና “ተሐድሶ መናፍቅ” ናቸው እያለ ለሚያስወራባቸው ማኅበር ቦታ መስጠት እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ሌላ አለቃው አባ ገ/ሥላሴ የቃሊቲ መድኃኔ ዓለም አለቃ ሳሉ ከአንድ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የማይጠበቅ ድርጊት ፈጽመው ማለትም በአቶ መለስ ዜናዊ ሞት ደስታቸውን ሲገልጹ ብዙ ምእመናንን አዝነውባቸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ምክንያቱም ቤተክርስቲያን ቢያጠፋም ቢያለማም እንኳን የአገር መሪን ቀርቶ አንድ አባሏን ከሞተ ነፍስ ይማር ትላለች እንጂ፣ እንኳን ደስ አላችሁ አትልም፡፡ አባ ገብረ ሥላሴ ከእርሳቸው በማይጠበቅ ሁኔታ ግን እንዲህ በማለታቸው ፖሊስ ጣቢያ ተስረው በድጋሚ እንዲህ ያለ መልእክት እንዳያስተላልፉ በከባድ ማስጠንቀቂያ ተፈተዋል፡፡
ከአለቃው በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ እነ ሊቀ ማእምራን የማነ ከዚህ ቀደም በስብሰባ ላይ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን የተናገሩትን ትክክለኛ አቋም መነሻ በማድረግና የማኅበረ ቅዱሳን ጠላት አድርጎ በማቅረብ እርሱም ማኅበረ ቅዱሳንን የሚጠላ መስሎ እየቀረበ ያለው ጸሐፊው ዲ/ን አበበ በተግባር ግን፣ ሙሰኛው አለቃ አባ ገብረ ሥላሴ በገንዘብ ስለጠለፉት ለማኅበረ ቅዱሳን እየሰራ መሆኑ ሲታወቅ ቀደም ሲል በተጠቀሰው ስብሰባ ላይ ማኅበረ ቅዱሳንን ተቃውሞ በመናገሩ በነሊቀ ማእምራን የማነ ዘንድ ግን ማኅበረ ቅዱሳንን የሚቃወም መስሎ መቅረቡን እንደቀጠለ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉትን አፋቸው ሌላ ልባቸው ደግሞ ሌላ የሆኑትን አድርባዮችና ጥቅመኞች በንቃት መከታተል አስፈላጊ ነው እንላለን፡፡ ምክንያቱም አበበ በአሁኑ ጊዜ ጥቅም ተጋሪ ስለሆነ በሙስና የተዘፈቁትን አለቃ እየደገፈና ካህናቱን ደግሞ እያስፈራራ ነው፡፡ ማስፈራሪያ አድርጎ የሚያቀርበው ደግሞ ከሊቀ ማእምራን የማነ ጋር ያለውን  ትውውቅ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ አበበ የደብሩ ጸሐፊ ሆኖ እንደመጣ ትውውቅ ሲደረግ ለመጀመሪያ ጊዜ በቆመበት በዚያ መድረክ ላይ “በደብሩ ውስጥ ኢቦላዎች ካላችሁ አስወግዳችኋለሁ” በማለት በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ሊነገር የማይገባ “የዱርዬ አነጋገር” በመናገር ብዙዎችን አሳዝኗል፡፡ ይህ ሰው ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስም ፎርጂድ ማኅተም አስቀርጾ ሲያጭበረብርና ሰው ቀጥሮ በመገኘቱ 3 ወር ታስሮ  የተፈታው ነው፡፡ በዚህ ስነምግባሩና በሌላውም ሁሉ ለካቴድራሉ የማይመጥን ሰው ሲሆን አሁን እያሳየ ያለው አስመሳይነት ደግሞ ሥራ አስኪያጁንና ምክትላቸውን እንዳያሳስት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል እንላለን፡፡
እነዚህን ችግሮች ከመፍታትና የሙስናውን በር ከመዝጋት ጎን ለጎን በሂደትም ቢሆን ከዚህ ቀደም ጉቦ እየተበላባቸው ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ከሰሜን ወደደቡብ በሕገወጥ መንገድ የተዛወሩትንና ለአላስፈላጊ የትራንስፖርት ወጪ የተዳረጉትን፣ በኑሯቸውና በቤተሰባቸው ላይ ምስቅልቅል የተፈጠረባቸውን ሠራተኞች ያለአድልዎና ያለመማለጃ በአካባቢያቸውና በአቅራቢያቸው እንዲሠሩ እንደሚደረግ፣ ዝውውርና እድገትም ሙያና ችሎታ የአገልግሎት ዘመንም ታይቶ እንደሚከናነው ሙሉ ተስፋና እምነት አለን፡፡
በመጨረሻ ማንሳት የምንፈልገው የሀገረ ስብከቱ ዘበኞችን በሚመለከት ነው፡፡ ዘበኞቹ አንዳንድ ባለጉዳይን ለማስገባት የተለያዩ እክሎችን በመፍጠር ገብቶ ለማነጋገር የሚፈልገውን ሠራተኛ ጉቦ እንዲከፍላቸው የሚያደርግ ሁኔታ በመፍጠር ጉቦ ይቀበላሉ፡፡ ስለዚህ እንደ ማንኛውም መሥሪያ ቤት ሀገረ ስብከቱ ለባለጉዳዮች ክፍት የሚሆንበትንና ከዘበኛ ጋር ባለጉዳዮች ድርድር የማያደርጉበትን አሠራር መዘርጋት ቢቻል ጥሩ ነው እንላለን፡፡

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የምንገኝና ለፍትሕ መስፈን የቆምን ካህናት

3 comments:

 1. Friday, May 17, 2013
  Read more »
  at 9:34 PM 2 comments
  Links to this post
  የማቅ ታማኝ አገልጋይ አባ ኅሩይ
  ወንድ ይፍራው ከሥራ
  አስኪያጅነታቸው ታገዱ
  Read in PDF
  የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለ4 ከተከፈለ በኋላ
  የምዕራብ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው
  የተመደቡት አባ ሕሩይ ወንድይፍራው ከስራ
  አስኪያጅነታቸው መታገዳቸውን የሀገረ ስብከቱ
  ጽ/ቤት ለመነኩሴው በጻፈው የእግድ ደብዳቤ
  አስታወቀ፡፡ በደብዳቤው እንደ ተገለጸው ለአባ
  ሕሩይ መታገድ ምክንያቶቹ የተመደበቡበትን
  የሥራ ሃላፊነት በአግባቡ አለመወጣትና ከሊቀ
  ጳጳሱ መመሪያ ሳይቀበሉና ትእዛዝ ሳይሰጥ
  ለሙስናና ለብልሹ አሰራር የተጋለጡ የሰራተኛ
  ቅጥር፣ የደመወዝ ጭማሪና የሰራተኛ ዝውውር
  ማድረግን እንደሚመለከት ለማወቅ ተችሏል፡፡
  እነዚህን ህገወጥና ከፍተኛ ጉቦ የሚበላባቸውን
  ተግባራት ሲፈጽሙ መቆየታቸው ስለተደረሰበት
  ከስህተታቸው እንዲታረሙ በየደረጃው ከቃል
  እስከ ጽሑፍ ምክርና ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም
  አባ ሕሩይ ማስጠንቀቂያውን ከቁብ ሳይቆጥሩ
  በተበላሸ አሰራራቸው በመቀጠላቸው ምክንያት
  የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁእ አቡነ ሕዝቅኤል
  ከሥራ አስኪያጅነት እንዳገዷቸው ደብዳቤው
  ያመለክታል፡፡

  ReplyDelete
 2. ዘገባው በጣም ጥሩ ነው ነገር ግን ቀደም ሲል በምዕራብ ሀገረስብከት ተመድቦ የነበረው በአማሳኝነቱና በዘረኝመቱ የሚታወቀው መሃይሙ አባ ህሩይ የተባለ አጭበርባሪ ተመልሶ በሀገረ ስብከቱ መመደቡ እጅግ ያሳፍራል ቤተ ክርስቲያንዋ ሰው የሌላት ይመስል በዙ አገልጋዮችን ሲበዘብዝና ሲበድል የነበረን ግለሰብ መልሶ መሾሙ የጤና አይመስልም ሙስናና ብልሹ አሰረሰርን ለማስወገድ ከተፈለገ እንደነአባ ህሩይ የመሳሰሉትን ዘረኞችና ሙሰኞች ከሀላፊነት ማስወገድ ያስፈልጋል አለበለዚያ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ይሆናል ነገሩ።

  ReplyDelete