Tuesday, April 28, 2015

ቤተ ክርስቲያን በአደጋ ክበብ ውስጥ (ክፍል አምስት)

Read in PDF

የመጨረሻ ክፍል
                                          ከዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
በአለፉት አራት ተከታታይ ጽሁፎች ቤተክርሰቲያንን አስመልከቶ የታዩኝን ችግሮች ከነመፍትሔዎቻቸው የሚጠቁም ጽሁፍ አቅርቤያለሁ። ይህ የመጨረሻው ክፍል ነው። መልካም ንባብ ይሁንላችሁ። ጊዜው ሳይመሽ እና ዕድል ሳያመልጠን ቤተክርሰቲያናችንን ከከበቧት አደጋዎች እንታደግ።
1.9.      ትላንት በግልጽ ዛሬ ደግሞ “በመንፈስ የግብጻውያን” ተጽዕኖ አለመቅረቱ

     ከአንድ ሺህ አምስት መቶ አመት በላይ ከአንድ መቶ አስራ አንድ አባቶች የማያንሱ ጳጳሳት የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከግብጽ እልፍ አዕላፍ ወርቅ ፣ ዕንቁ ፣ የዝሆን ጥርስ ፣ አልማዝ ፣ የከበረ ድንጋይ ፣ ብር ፣ የተለያዩ ውድ አልባሳትና ሌሎች ብዙ እጅ መንሻዎችንና ገጸ በረከቶችን በማቅረብ (ልዋጭ በመስጠት) ታስመጣ ነበር፡፡ የማስመጣቷ ምክንያት ደግሞ እስከዛሬ ከፍትሐ ነገስታችን ላይ ጉብ ብሎ እስካልተነሳው ስርዋጽ አንቀጽ የተነሳ ነው፤
                     “የኢትዮጲያ ሰዎች ከዐዋቂዎቻቸው ወገን በራሳቸውም ፈቃድ ሊቀ ጳጳሳትን
                        ለራሳቸው አይሹሙ፡፡ ጳጳሳቸው ከእስክንድርያው በዓለ መንበር ሥልጣን በታች
                   ነውና፡፡” ፍትሐ ነገስት.አን.፬ ቁ.፶ (ገጽ.30)
      ይህ አንቀጽ ለምን ይሆን ዛሬስ ከፍትሐ ነገሥቱ ላይ ያልተነሳውና ወደሙዝየም ያልገባው? ነው ወይስ ለዳግመኛ ባርነት ሌላ የሚጠብቀው ትውልድ አለ? በጣም የሚያሳዝነው ሌላው ታሪክ ደግሞ በአንድ ወቅት ኢትዮጲያውያን ጳጳስ ይሾምልን ብለው ግብጻዊውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤልን እነአጼ ሐርቤ ስለጠየቁ “ንጉሡ ኢትዮጲያውያን ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ በመጠየቁ እግዚአብሔር ተቆጥቶ በአገሩ በኢትዮጲያ ላይ መቅሰፍት አወረደ” ይላል በሚያዝያ ፲ ቀን የሚነበበው “ስንክሳራችን”፡፡ እንዴት በገዛ እጃችን በራሳችን ላይ ተሳልቀናል?! እንዴት ባለ ትብታብና ድንዛዜ ነው የተያዝነው?  
    ከግብጽ ከሚመጡት ጳጳሳት ከእጅግ በጣም በጣም ጥቂቶቹ በቀር አብዛኛዎቹ  እንደ“አቡነ” ዳንኤል ያሉት ገንዘብ አፍቃሪዎች ፣ እንደ“አቡነ” ሳዊሮስ ያሉት መስጊድ የሚያሠሩ የሙስሊም ኢማሞች … ሌሎቹ ደግሞ አመንዝሮችና ቅጥ ያጡ ጥቅመኞች ነበሩ፡፡ ሌሎቹ  እንደአቡነ ሚካኤል ያሉት ደግሞ ከእርጅና የተነሳ ምንም መሥራት የማይቻላቸው ነበሩ፡፡ (የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፤ አባ ጎርጎርዮስ (M.A) ፤ 1991 3ኛ ዕትም ፤ አዲስ አበባ ፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ.34-35)
   የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ትላንት “ከጠቀመችን ጥቅም” ይልቅ በጉዳት ያጠቃችን ጥቃት እጅግ ይበልጣል፡፡ በታሪካችንና በአምልኮአችን ውስጥ ረጅም እጇን ሰድዳ ወደአሻት አቅጣጫ ስትመራን ኖራለች ማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን በግብጽ ቤተ ክርስቲያን የደረሰባትን በደል አባ ጎርጎርዮስ ሲያስረዱ፦
       
“ … በነዚህ አያሌ አመታት ውስጥ ውስጥ ለመላው ኢትዮጲያ ሚላከው አንድ ጳጳስ ብቻ ነበር ፤ እሱውም የሕዝቡን ቋንቋ ስለማያውቅ ለማስተማርም ሆነ ለማስተዳደር በስማ በለው ነበር፡፡ የሚቀመጠውም ንጉሡ ባለበት ቦታ በከተማ ብቻ ስለነበር ፤ በገጠሩ የሚኖረው ሕዝብ ቤተ  ክርስቲያኑ እንዳይዘጋበት ሕጻናቱን በጀርባው አዝሎ በትከሻው ተሸክሞ ጳጳሱ ወዳለበት የወር የሁለት ወር ጐዳና ተጉዞ ይመጣል፡፡ ከዚያም ገንዘቡን ከፍሎ ካኑልኝ ሲል ጳጳሱ ገንዘቡን ተቀብሎ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ዕድሜው ለክህነት ሳይደርስ ፤ ለክህነት የሚያበቃ ሙያ ሳይኖረው እየካነ ይልከዋል፡፡ ልጁም ተክኖ በቂ ትምህርት ሳያገኝ በቤተ ክርስቲያን በድምጫ የሰማውን ብቻ ይዞ … ያገልግላል፡፡” (ገጽ.75)

   ይህንን ተንተን አድርገን ብናየው፦
1.     ለድፍን ኢትዮጲያ አንድ ጳጳስ ብቻ ነው ያለው፡፡
2.    ጳጳሱ የሕዝቡን ቋንቋ አያውቅም ፤ ስለዚህም ማስተማርም ሆነ ማስተዳደር አይችልም፡፡
3.    የሚቀመጠው ንጉሡ ባለበት በዋናው ከተማ እንጂ ወደሕዝቡ አይወርድም፡፡
4.    የገጠሩ ሕዝብ ማንም ፤ ምንም አስታዋሽ የለውም፡፡ ስለዚህ ጳጳሱን ለማግኘት ወደከተማ በብዙ ድካም ይመጣል፡፡
5.    ክህነት ለመቀበል ለጳጳሱ የሚሰጥ ክፍያ አለው፡፡ ጳጳሱም በመቀበል ክህነትን ይሰጣል፡፡
6.    የተካነውም ዲያቆንም ሆነ ቄስ ትምህርት ሳይማር ክህነት ይሰጠዋል፡፡ ከዚያም በስማ በለው ሲያገለግል ይኖራል፡፡
    ይህ በግብጻውያን ጳጳሳት ዘመን የነበረውን “ትንሽ” ችግር ይዘን ወደዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ብንመለስ፥ ያው ችግር አድጎ ፤ ሰፍቶ ፤ ሥር ሰዶ ተንዠርግጎ በእጅ አዙር ይታያል፡፡
·        የሰው ኃይል ሳያጥር ሁለት ሀገረ ስብከት ዛሬም በአንድ ሊቀ ጳጳስ ሲመራ ከማየታችን ባሻገር አመዳደቡ እንኳ ፍጹም የሚያሳዝን ነው፡፡ የማይገናኙ ሀገረ ስብከቶችን ለአንድ ሊቀ ጳጳስ ሲሰጡ እናያለን፡፡ ለምሳሌ ፦ ጠቅላይ ቤተ ክህነትንና ከንባታና ዳውሮን ፣ ምስራቅ ሸዋና ምዕራብ አርሲን ፣ አዲስ አበባና ጅማን ፣ ምሥራቅ ሐረርጌና ምዕራብ ጎጃም ፣ ምዕራብ ሐረርጌና ድሬደዋን  አንድ ሊቀ ጳጳስ ሲመራ እናያለን፡፡
·        ሁሉም ማለት ይቻላል ሊቃነ ጳጳሳቶቻችን የሚችሉት መደበኛ ቋንቋ አማርኛ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ትግርኛ፡፡ ከሰማንያ በላይ ቋንቋ በሚነገርባት ኢትዮጲያችን ውስጥ በሌሎች ሕዝቦች ቋንቋ የሚናገሩ ጳጳሳት ማየት እጅግ ብርቃችን ነው፡፡ በቅርቡ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች ጳጳሳት ያየን ቢሆንም ግና አሁንም ያልተነካ ነው፡፡ ይህን ስለብሔርተኝነት አንልም ፤ ቅዱሳን ሐዋርያት በሁሉም አለም የሚነገረው ቋንቋ ለወንጌል አገልግሎት ከመንፈስ ቅዱስ የተነሳ ተገልጦላቸዋል፡፡ (ሐዋ.2፥6) ዛሬ ለአንድ ጳጳስ ወይም የወንጌል ሰባኪ በአለም ላይ ያለው ቋንቋ ይገለጥ አንልም ፤ ወይም ብለን አንጸልይም፡፡ ምክንያቱም በሁሉም አለም ባሉ አገራትና ብሔራት ቋንቋ ተናጋሪ አማኝ ክርስቲያኖች አሉና፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ሆና በውስጧ ግን ብዙ ብልቶች አላትና ጸጋ ተጠቅልሎ ለአንድ ሰው የሚሰጥበት ሁኔታ የለም፡፡
     መንፈስ ቅዱስ ለአንድ ሐዋርያ ከሰባ ቋንቋ በላይ የገለጠበት ምክንያቱ ክርስትና ገና ያልተሰበከና የአስተምህሮ መሠረቱ ያልተጣለበት ዘመን ስለነበር ፥ ሐዋርያት መሠረቱን ሊያንጹ (ኤፌ.2፥20) ወደሁሉም አገሮች በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት ሄደዋል፡፡ ዛሬ የኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን በአለም ላይ ካሉ አብዛኛዎቹ ቋንቋዎችን ተናጋሪ አማኞች አላት ፤ በቋንቋቸውና በባህላቸው የሚያስተምራቸው ፣ የሚያጠምቃቸውና ደቀ መዝሙር የሚያደርጋቸው አገልጋይና አባት ግድ ያስፈልጋቸዋልና ቤተ ክርስቲያን አብዝታ ልታስብለት ትችላለች፡፡  
·        ጳጳሳቱ ዛሬም የሚኖሩት በ“ሀገረ ገዢው” ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ከእነርሱ ያዩ ሰባኪዎችና ዘማሪዎቹም ጉባኤ በደመቀበት ከተማ እንጂ ወደገጠር መሄድና ማገልገል አይመቻቸውም፡፡ ከማን ይሆን የተማሩት? “እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ … ”(ሐዋ.10፥38) ከተባለው ከኢየሱስ ነውን? … ወይስ ስለወንጌል “ … ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ … በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።” (2ቆሮ.11፥25-27) ካለው የተወደደ ሐዋርያ ነውን? ከማን ይሆን የተማሩት?
   ታዲያ የገጠሩ ሕዝብ በጥንቈላና በሌላ ነገር ቢያዝ ምን ይደንቃል? እኛ ያልራራንለት ሕዝብ ጠላት ሰይጣን ቢጨክንበት ምን ይደንቃል? አዎ! ተበትኖ ሳለ ላልራራንለት ፤ ግራና ቀኙን ያልለየውን ሕዝብ ነፍስ ደም፥ እግዚአብሔር ከእኛ ይፈልጋል፡፡
·        እንዲሁ አገልግሎት ከገጠር ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጦ የሚመጣ ሕዝብ ዛሬም ቁጥሩ ትንሽ አይደለም፡፡ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ አጥተው መዘጋት ከጀመሩ ቆይተዋል ፤ ስለዚህም በገጠሩ ያሉት ሕዝቦች ወይ ወደእስልምና ወይ ደግሞ ኃይማኖት የለሽ ከመሆን የሚተርፉት ጨክነው አገልግሎት ወዳለበት ከተማ መምጣት ከቻሉ ብቻ ነው፡፡
·        አይኖቻችን አይተው አብዝተው ከተጠየፉት ነገር አንዱ ክህነትና የቤ ክህነት የሥራ ዝውውር በገንዘብ መሆኑ ነው፡፡ ይኸው ከእነዚያ ባዕዳን ግብጻውያን በምን ነው የምንለየው? እነርሱም ይዘርፉ ነበር ፤ እኛም ይኸው ከመዝረፍ ማን ከልክሎን? የክፋትን ውርስ ወራሽ ከእኛ በቀር ማን አለ?
·        ወንጌልን በወንጌል ዓውድና በወንጌላዊ ባህርይ ሳይሆን ፥ በስማ በለው የሚሰብከው ቁጥሩ ስንት ይሆን? እውነቱን ብናወራ ወንጌል ዛሬ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚሸቀጠውንና በስማ በለው የሚሰበከውን ያህል በሌላ ጊዜ አልሆነም ብል ግነት ያለበት አይመስለኝም፡፡
     እንኪያስ፥  እኛ ከእነዚያ በምን ይሆን የምንለየው? ቤተ ክርስቲያን ከባዕዳን አስተዳደር ተገላገለች እንጂ ከግፈኞች ፣ ለሕዝብ ምንም ከማይገዳቸው ፣ ከሙሰኞች ፣ ከአመንዝሮችና በአለማዊነት ከሚቀማጠሉት መሪዎች ገና መች ተላቀቀች? አምልኮው ሲጠነዛ ፤ አስተዳደሩ እንደመርገም ጨርቅ ክብሩን ሲያጣ ፤ በሥነ ምግባር ብልሹነት ከልጅ እስከ አዛውንቱ እኩል ሲወድቁ ፤ አገልግሎት ንግድ ፣ መዝሙርና ስብከት ችርቻሮ ሲሆን ምን አሉ ይሆን “የእኛ ተወላጅ” ሊቃነ ጳጳሳትና ጳጳሳት? ኤጲስ ቆጶሳትና ቆሞሳትስ ቢሆኑ የት ያሉት? የነገረ መለኮት ተማሪዎችም ብንሆን ትልቅ ሥራ ከእናንተ ብዙ ይጠበቅ ነበር … እናንተስ የት ነው ያላችሁት? ዲያቆናቱስ የት ነው ያለነው? በእውኑ ይህ ሕዝብ እንዲህ እንደጎበጠ ፤ ቀና ሳይል ይኖር ዘንድ መልካም ነውን?

1.10የዘፋኞችንና የአለማውያንን ዝናና ዕውቅና “መቀላወጥ”

      ቤተ ክርስቲያን ከአስተማሪዋ መንፈስ ቅዱስ የተማረችው አንድ ትልቅ እውነት “ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞትን በመካድ … ራስዋን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን መኖርን” ነው፡፡ (ቲቶ.2፥12-14) “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ እንጂ፥ በእኛ መልካም ሥነ ምግባር አለመዳናችንንም አውቀን” (ቲቶ.3፥5) መዳናችንን በመልካም ሥራ መገለጽ እንዳለበት ጸጋን አደላዳዩ መንፈስ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ ምክንያቱም ትክክለኛ የሆነ ሥነ ምግባር ምንጩ ትክክለኛ ትምህርት ነውና፡፡  
    ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር መንግሥት መገለጫና የመንግሥቱ ሥራ ብቻ የሚታወጅባት አውድ ከሆነች በውስጧ ሊያገለግሉ የሚገባቸውም አገልጋዮች እንደቤተ ክርስቲያን ራስ፥ ክርስቶስ ኢየሱስ “በመንፈስ ድሆች የሆኑ (ማቴ.5፥3 ፤ ፊልጵ.2፥8) ፣ የሚያዝኑ (ማቴ.5፥4 ፤ 9፥37) ፣ የዋሆች (ማቴ.5፥5 ፤ 11፥29) ፣ ጽድቅን የሚራቡ (ማቴ.5፥6 ፤ 21፥18 ፤ ዮሐ.19፥29) ፣ የሚምሩ (ማቴ.6፥7 ፤ ሉቃ.6፥36 ፤ ኤፌ.2፥4 ) ፣ ልበ ንጹሕ (ማቴ.5፥8 ፤ 23፥4 ፤ ዕብ.7፥26) ፣ የሚያስተራርቁ (ማቴ.5፥9 ፤ 2ቆሮ.5፥18) ፣ ስለጽድቅ የሚሰደዱ (ማቴ.5፥10 ፤ ሮሜ.8፥35-36) ፣ በስሙ የሚነቀፉና የሚሰደዱ ክፉው ሁሉ በውሸት የሚነገርባቸው (ማቴ.5፥11 ፤ ዕብ.13፥12 ፤ 1ጴጥ.2፥23) ሊሆኑ ይገባቸዋል እንጂ ስለዘፈናቸውና በአደባባይ የበደሉትን ሕዝብ ገና ይቅርታ ያልጠየቁና ንስሐ ያልገቡ ሊሆኑ አይገባቸውም፡፡
    እግዚአብሔር እርሱን የሚያገለግሉትን አገልጋዮች ሰው እንደሚያይ አይቶ አይመርጥም፡፡ (1ሳሙ.16፥7) እግዚአብሔር እንደልቡ የሚሆንለትንና የሚመላለስለትን ፤ ፈቃዱንም ሁሉ የሚያደርግለትን እንጂ (ሐዋ.13፥22) በሁለት ሃሳብ የሚያነክሱ ዘፋኞችን አይፈልግም፡፡ (1ነገ.18፥21 ፤ ማቴ.6፥24) ቤተ ክርስቲያን አለም ያከበረቻቸውንና በዘፈን ኀጢአት የመሰከረችላቸውን ለምን ሄዳ ደጅ እንደምትጠናቸው ወይም እናገልግል ሲሉ ለምን ተንገብግባ፤ አሰፍስፋ እንደምትቀበላቸው ግልጽ አይደለም፡፡
    ከአገልግሎት በፊት መጠራት ፤ ከመጠራት በኋላ ደግሞ የሕይወትና የምግባር ምስክርነት እንደሚስፈልግ የዘነጋች ወይም ቃየላዊ መሥዋዕትን የወደደች ይመስላል፡፡ በተደጋጋሚ ዘፋኞችና ሌሎች  የዘፋኝነትና የታወቀ ነውራቸውን በክርስቶስ ደም አጥርተው ፤በንስሐ የበደሉትን ሕዝብ ክሰው ሳይመለሱ  “የወንጌሉን አውደ ምህረት” ረግጠው “ለህንጻ ማሠርያ አገልግለው” ወደቀደመ ሥፍራቸው ተመልሰዋል፡፡ በዘፈን ትውልድ እያጠመዱ ለዝሙት እያጩ ዘላለማዊውን የሥላሴ ህንጻ ያፈርሳሉ ፤ ነገር ግን ነገ ለሚፈርሰው ህንጻ ደግሞ “በድምጻቸው” ብር ይሰበስባሉ፡፡ አይ ቤተ ክርስቲያን! የዘላለሙን እየከሰረች ለጊዜያዊው ትደክማለች! ምናለ ሕንጻው ቀርቶ አንድ የሥላሴ ህንጻ ክርስቶስ የሞተለትን ማዳን መቻሉ፥ ከአንድ ህንጻ እንደሚበልጥ ብናስተውል!?
   ያለድርድር ይህም ክፉ ምሳሌነታችን የንስሐ ልቅሶና ኑዛዜ ያስፈልገዋል!!!   መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት እንዲል … ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ፡፡
    ሌሎችን ብዙ ችግሮችን  ማንሳት ቢቻልም እኒህን ለማሳያነት ማንሳቱ በቂ ነው፡፡ እኒህ ሁሉ ግን የችግሩ ዋና ምንጮች አይደሉም፤ አሁን ላለችው ቤተ ክርስቲያን ዋናውና አንኳሩ የችግሮች አውራው ደግሜ እላለሁ፦
1.    እግዚአብሔር ብቻ አለመመለኩ ነው

   ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን ብቻ ያላመለከችበት ወይም የሚያመልኩትን ፊት የነሳችበት ዘመን ብዙ ነው፡፡ ለምሳሌ የቅርቡን ብናነሳ ፦
      “ … ለገበሬው ማርክሲዝም ሌኒኒዝም በስፋት ተሰበከ፡፡ በሶሻሊስት ቲዮሪ ታንፆ ገበሬው ማርክሲስት ሆነ፡፡ መጣቱ ማቴሪያሊስት ሆኖ እግዚአብሔርን ትቶ በቁስ አካል ማመን ደረጃ ላይ ደረሰ፡፡ አንዳንድ ማርክሲስት የሆኑ ቄሶች ሁሉ ነበሩ፡፡ ከሐሙሲት (ቆላ ሐሙሲት) የአንድ ቀን መንገድ ርቃ በምትገኘው ፀባሪያ በምትባል መንደር ላይ ይኖሩ የነበሩ አንድ ሽማግሌ በያመቱ የሚዘክሩትን የሀምሳት በዓል (ከፋሲካ በኋላ) ደግሰው ሲያበሉ ለታዳሚው ድግሴን ለመጨረሻ ጊዜ ብሉ ከእንግዲህ አላዘክርም ብለው ተናግረዋል፡፡ ቲዮሪው እስከዚህ ዘልቆ ነበር፡፡”  (ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ ፤ ደራሲው ያልተጠቀሰ ፤ ቅጽ አምስት ፤ 1993 ፤ አዲስ አበባ ፤ሜጋ አሳታሚ ድርጅት፡፡ ገጽ21)


   ምንም ልንክደው የማንችለው እውነት በደርግ ዘመን ቤተ ክርስቲያን “እግዚአብሔር የለም” የሚሉ ካህናትን፣ ሰባክያንንና ሌሎችንም በጉያዋ ይዛ ነበር ፤ ይህ ብቻ ያይደለ “የፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ መገደልን በተመለከተ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኒቱም ሲኖዶስ እጅ አለበት” የሚለው ከባድ ጥርጣሬ መነሾው ተራ ነገር አይደለም፡፡ ያኔ “እግዚአብሔር የለም” ዛሬ ደግሞ “እግዚአብሔር ወይም እውነት አንጻራዊ ነው” የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ቤተ ክርስቲያን ምንም ማለት በሚያስደፍር መልኩ ተቃውሞ አለማሰማቷና በመቃረን ጨክና አለማስተማሯ ነው፡፡
   የዚያኔ አውነተኛውን ወንጌል አለማስተማሯ ብቻ ሳይሆን ፥  አሁንም እንኳ ያንን ያስተማረችውንና የኖረችውን ሕይወት በመቃወም ማስተማርና ንስሐ መግባት ሲገባት፥ “በአልተሳሳትኩም ፤ አልሳሳትምም” እልኸኝነት መንፈስ ስትመላለስ እናያታለን፡፡ ቤተ እስራኤል በጠላት ተላልፈው የመሰጠታቸውና የመሸነፋቸው ምክንያት እንዲሁም እግዚአብሔርን እየተከተሉ የማዘናቸውን ነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል ሲነግራቸው “እግዚአብሔርን ብቻ አለማምለካቸው” እንደሆነ በነገራቸው ጊዜ በፍጹም መመለስ ነበር ንስሐ የገቡት፡፡ ለዛሬዋም ቤተ ክርስቲያን በቤቱ ስደተኛ ያደረገችውን ጌታ አምላክዋን ይቅርታ በመለመን ንስሐ ስትገባ ብቻ እርቅን ታገኛለች እንጂ የአሁኑ መንገዷ ፈጽሞ የትም አያደርስም፡፡
         
2.   የሐዋርያትን ትምህርትና ትውፊት አለመከተላችንም ነው፡፡ (ሐዋ.2፥42)

     የሐዋርያት ትምህርት መጀመርያው የክርስቶስ ነገረ ድኅነት ፍጻሜውም በክርስቶስ ኢየሱስ የተገኘውን የዘላለም ሕይወት ለአለሙ ሁሉ የምሥራች ብሎ መስበክ ነው፡፡ (ዮሐ.20፥31) ከእርሱ ወንጌል በቀር ምንም ዕዳ ፤ አንዳች ሸክም እንደሌለባቸው አበክረው ተናግረዋል፡፡ ይህንን አገልግሎትና ሥራ እንዲተው ብዙ ማስጠንቀቂያ ፣ ማስፈራራት ፣ ዛቻ ፣ ድብደባና ፣ ግድያ ቢደርስባቸውም አብዝተው ከማገልገል ሊያግዳቸው ከቶውንም አልቻለም፡፡ (ሐዋ.4፥2 ፤ 18 ፤ 5፥40 ፤ 7፥58 ፤ 12፥1-3 ፤ 13፥50 ፤ 14፥2 ፤ 19 ፤ 16፥22-24 ፤ 17፥5 ፤ 32 ፤ 19፥9 ፤ 28 ፤ 21፥35 ፤ 22፥22 ፤ 24፥5 27 ፤ ሮሜ.1፥26 ፤ 1ቆሮ.1፥23 ፤ ገላ.5፥11)
      ስለጌታ ኢየሱስ ማስተማርን በተቃወሟቸውም ጊዜ ጸሎታቸው “ … አሁንም፥ ጌታ ሆይ፥ ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ፥ ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው።” የሚል ነበር፡፡ (ሐዋ.4፥29-30) ቅዱስ ጳውሎስ በቁም እስሩ ሳለ ያደርግ የነበረውም “ … የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር።” (ሐዋ.28፥31) ስለዚህም የሐዋርያት ትምህርት ስንል ለመጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ መሆናቸውንና ያንኑ ብቻ በማስተማር መጽናታቸውን ማንሳታችን ነው ፤ ደቀ መዛሙርቱ የጌታን ትምህርት ያካተተውንና  እጅግ ታማኝ የነበሩበት ትምህርታቸው “የሐዋርያት ትምህርት ወይም መሠረት” ተብሎ ተጠርቷል፡፡ (ሐዋ.2፥42 ፤ ኤፌ.2፥19-20)
     የቅዱስ ጳውሎስ ትልቁ ምጥና ጭንቀት በአማኞች ልብ ክርስቶስ እስኪሳል መትጋትና ስለአማኞች ማሰብ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ (2ቆሮ.11፥28 ፤ ገላ.4፥19) እንኪያስ ትልቁ የጌታችን ሐዋርያት ፤ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነትና ተልዕኮ የጌታን መንግሥት ወንጌል እስከኣለም ፍጻሜ መስበክና መናኘት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሌላ ሥራ ፤ ሌላ ኃላፊነት ፈጽሞ አይኖርም፡፡ (ማቴ.28፥19)
    ስለዚህም ሐዋርያት በትውፊታቸው፦
       ነገርን ሁሉ በጸሎት የመጀመርና የመፈጸም ወግ ፤ እንዲሁም በጸሎት የመትጋት ልማድ ነበራቸው፡፡ ጸሎትም “ከሁሉ በፊት እንዲደረግ” በመልዕክቶቻቸው ያሳስቡ ነበር፡፡ (ሐዋ.1፥25-26 ፤ 2፥42 ፤ 46 ፤ 3፥1 ፤ 4፥24-31 ፤  6፥4 ፤ 6 ፤ 9፥40 ፤ 12፥5 ፤ 13፥2 ፤ 14፥23 ፤ 1ተሰ.5፥25 ፤ 1ጢሞ.2፥1-2 ፤ ዕብ.13፥18)
       መንፈሳዊ ትምህርቶችን መስማት ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እያወጡ ያነቡ ነበር ፤ ስብከትም ይሰብኩ ነበር፡፡
       በዜማና በመዝሙርም ይሰብኩ ነበር፡፡
       ዘወትርም የጌታን እራት በመቁረስ ይተጉም ነበር፡፡ (ሐዋ.2፥42 ፤46 ፤ 20፥7)
       በአንድነትም በመመገብ ፤ ለሌላቸው የማካፈል ፤ገንዘባቸውንም በአንድነት የማኖርና ፤ በህብረት የመኖር ልማድም ነበራቸው፡፡ ( ሐዋ.4፥32-36 ፤ ፊልጵ.4፥14-17)
       ያመኑትን በውኃ ያጠምቁ ነበር፡፡ (ሐዋ.2፥41 ፤ 8፥12 ፤ 38 ፤ 10፥48 ፤ 1ቆሮ.1፥18)
       በየሰንበቱም በአይሁድ ምኩራብ (በጸሎት ሥፍራ) ይገኙ ፤ ይሰብኩም ነበር፡፡ (ሐዋ.13፥5 ፤ 14 ፤ 44 ፤ 14፥1 ፤ 16፥13 ፤ 17፥2 ፤ 19፥8 ፤ 21፥26-29)
       ክርስቲናዊውን ኑሮ የመሩበት ሥርዓት ማለትም ወግ ነበራቸው፡፡ (ሐዋ.16፥4 ፤ 1ተሰ.3፥6)
       የራሳቸው የማስተማሪያ መንገድ ነበራቸው፡፡ (1ቆሮ.14፥27-33) ከዚሁ ጋር በተያያዘ  ሴቶች ዝግ ብለው እንዲማሩ እንጂ እንዲያስተምሩ የሚፈቅድ ትውፊት አልነበራቸውም፡፡ (1ቆሮ.14፥34-36 ፤ 1ጢሞ.2፥11-13)
       በጸሎት ሰዓት ሊሆን የሚገባ የአለባበስ ልዩ ወግም ነበራቸው፡፡ (1ቆሮ.11፥13-16)
       በትውፊታቸው ሁሉም አማኞች የተማሩት ከማን እንደሆነ አውቀው በተማሩት ትምህርት እንዲጸኑ ፤ ለተማሩትም ትምህርት እንዲጠነቀቁ የማስተማር ልማድ ነበራቸው፡፡ (1ጢሞ.2፥1-2 ፤ 3፥14-16)
       ስለአገልግሎታቸው የሰውን እጅ የማይጠብቁና በራሳቸው ገቢና የእጅ ሥራ ሙያ ይተዳደሩ የነበሩም ናቸው፡፡ (ሐዋ.18፥3 ፤ 2ተሰ.3፥7)
ስለዚህም እኛም፦
o   የመጽሐፍ ቅዱስን ሉዓላዊነት(የበላይነት) ፍጹም ልናምን ይገባናል፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ቅድመ ኬልቄዶን እንደነበሩት አበው “ኦርቶዶክስ” የሚለውን ስያሜ ከሐዋርያት ትክክለኛ አስተምህሮ ጋርና ከኒቂያ ጉባኤ ውሳኔ ጋር በማገናዘብ (በማዛመድ) ለትምህርቱ ትክክለኛነት ሰጥተው ተርጉመውታል፡፡ የዚህ እውነታው ደግሞ እንደሐዋርያት ትውፊት ለመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ለሙሉ ታማኝ መሆንን ያገናዝባል፡፡
o   ከላይ ያየናቸው ሐዋርያውያን ትውፊቶች በመካከላችን በእውነት ቢኖሩ ዛሬ የምናየው ምስቅልቅሉ የወጣው መንፈሳዊነት መስመር ይዞ ውበትና መልክ ይኖረው ነበር፡፡

ፍጻሜ ቃል
     ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ በቤተ  ክርስቲያን ድካም ላይ ማተኮራችን ቤተ ክርስቲያን ራስዋን በመመልከት ለንስሐና በሙሽራዋ ፊት ለመናዘዝ እንድትቸኩል ለማለት እንጂ “ምንም ምን ጠንካራ ነገር የላትም” የሚል አቋም የለኝም፡፡ የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን እንኳ በክርስቶስ ፊት ጠንካራ የመሆኗን ያህል የጸሎቷን መልስ ለመቀበል የተጠራጠረችበትም ጊዜ ነበርና (ሐዋ.12፥12-17) በዚህ ምድር ያለች ቤተ ክርስቲያን ሙሽራዋ መጥቶ እስኪጠቀልላት ድረስ በድካም መያዟ ብዙም ግር አያሰኝም፡፡ ነገር ግን ለንስሐ በመዘግየት ከወዴት እንደወደቀች አስባ አለመመለሷ ከሁሉ የበረታ ቅጣትን ማምጣቱ አይቀርም፡፡ (ራዕ.2፥16)
     ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦  “ዓለም እውነቱን ለመቃወም ከተነሳች አትናቴዎስ ደግሞ አለምን ለመቃወም ይነሳል፡፡” በማለት፡፡ እንኪያስ! ይህን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚቃወመውን ማንኛውንም ኃይልና መንፈስ በክርስቶስ ኢየሱስ ስምና ሥልጣን አጽንተን እንቃወማለን፤ እናወግዛለንንም፡፡ ትልቁ መሻታችን ቤተ ክርስቲያን በቅድስናና በንጽዕና ለምልማ ፤ በመንፈሳዊ ፍሬ ጎምርታ ማየት እንጂ ድካምን በማውራት ብቻ ዘመንን መቁጠር አይደለም፡፡ ይህ እንዲሆን የዘወትር መቃተታችንና ጸሎታችን እንዲሆን ፥ በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ የምታምኑ አማኞችን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን ትንሳኤ በጸሎት እንድትተጉ በመስቀሉ ርኅራሄ እለምናችኋለሁ፡፡
   ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን። (ኤፌ.6፥24)
     ተፈጸመ፡፡

                                   ዋቢ መጻህፍት

v የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር(1962)መጽሐፍ ቅዱስ፡፡አዲስ አበባ፣ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፡፡
v ሃይማኖተ አበው፡፡ ፤1982 ፤ አዲስ አበባ ፤ ተስፋ ማተሚያ ቤት፡፡
v ፍትሐ ነገሥት ሥጋዊ ወመንፈሳዊ የሕግ ምንጭ በግዕዝና በአማርኛ፡፡ 1992 ፤ አዲስ አበባ ፤ ተስፋ ማተሚያ ድርጅት፡፡  
v ኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር(2002)፡፡የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9ኛ እትም፣አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡
v ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ፤ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ፤ 1993 ፤አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ማህበረ ቅዱሳን፡፡
v አባ ጎርጎርዮስ (M.A) ፤ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ  1991 3ኛ ዕትም ፤ አዲስ አበባ ፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፡፡
v ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ፤ 1993 ፤ አዲስ አበባ ፤ አሳታሚ ማህበረ ቅዱሳን ፡፡
v ዲበኩሉ ዘውዴ(ዶ/ር)፤ ፍትሐ ነገሥት ፡ ብሔረ ህግ ወቀኖና ፤ 1986፤ አዲስ አበባ፡፡
v አማርኛ መዝገበ ቃላት ፤ የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ማርምር ማዕከል ፤ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ፤ የካቲት 1993 ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት፡፡
v የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት፤ አዲስ አበባ ፤ 1978 ፤ ኩራዝ ማተሚያ ድርጅት፡፡
v ደራሲው ያልተጠቀሰ ፤ ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ ፤ ቅጽ አምስት ፤ 1993 ፤ አዲስ አበባ ፤ሜጋ አሳታሚ ድርጅት፡፡
v የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ፤ ሰኔ 16 2004 ዓ.ም. ፤ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ባዘጋጀው “የአብያተ ክርስቲያናት ትብብር ለሰላምና ለልማት” ሲል ያዘጋጀው መጽሔት፡፡
v ዲ.ን ዳንኤል ክብረት ፤ ስማችሁ የለም ፤ ነሐሴ 2006 ፤ አግዮስ ኅትመትና ጠቅላላ ንግድ ሥራ ሐላ.የተ.የግል ማኅበር፡፡
v ሐመረ ተዋህዶ ዘዕሥራ ምእት፤ ማህበረ ቅዱሳን ፤ ሐምሌ 2000፤ አዲስ አበባ፡፡
v ሐመር ፤ ፲፫ዓመት ቁጥር ፭ ፤ መስከረም/ ጥቅምት ፲፱፻፺፰ ዓ.ም ፤ ገጽ ፳፮፡፡
v ጥር 30 1999 በአሜሪካ ሬድዮ የአማርኛው ፕሮግራም ላይ የቀረበ ዜናና መግለጫ፡፡
v ጥር 25 1999 ዓ.ም ከምሽት ዜና በኋላ በኢትዮጲያ ሬድዮ አገልግሎት የቀረበ ዜናና መግለጫ፡፡


9 comments:

 1. The level of ignorance and ineptitude deeply ingrained inside the current members of "The old Church" is beyond imagination. The Church since long has curtailed Christ behind the shadow of "gedils" and "te-amirs." Such articles shade a bright light to penetrate the artificial shadow and see a glimpse of the True Light- Jesus Christ.

  ReplyDelete
  Replies
  1. hey Mr anonymous, first and foremost you should clean your toxin infested divilish eyes before you open your rotten mouth, before you cast your woefully ignorant ideology. have you ever noticed what is going on your Protestant "church"? I will never say Protestantism is Christianity as it is not. who teaches that fake biblical- like "gospel"? did you open your blind eye and see what is happening in the "gospel" prospered Western society? why is that in the west where "gospel" was ingrained into the daily lives the people for the last 400 years or so, why is that very society becoming more and more moral less and atheism in exponential growth? is that the goal of your so called "gospel" preaching? I know for sure the goal of evil Protestantism is dragging souls to hell for eternity! we know what the world of protestantism is! this shameful evil organization which desguises itself in the name of Christianinty is being ridiculed for its nonsense, shameful, and dirty tricks it performs everyday in its ugly stage.

   Protestantism is Satanism.

   Delete
  2. Hey Mr Maru, what does your little silique have to do with the Anonymous’ comment? A person doesn't need to be a protestant to challenge the church's some wrong gedels. I wonder if the Ethiopian church will ever translate teamire mariam and other unbiblical gedels to English for all our oriental brothers to see & find out what the church has been carrying for the last few centuries. I tell you in Lord's name, that will be the day they strip "orthodoxy" from our name!

   Delete
  3. hey Mr anonymous, have you ever went to , say , the Coptic church and investigated what that holy church is doing in its everyday spiritual practice? of course not. you don't know how the Coptic church or other sister churches teach their their followers. you uttered this words because a Protestant pastor said so and you believed so. you blindly tried to distance but in vain the Ethiopian Holy church from other sister churches.

   Delete
  4. Actually Mr. Maru, for your information, yes I have attended and still attend regularly Coptic church here in the state. They follow the early church's teachings and tradition and don't accept any book as "inspired" unless it has its root from the early church or/and doesn't blatantly contradict the bible. Reading the lives of the saints should inspires a person to strive to be like them and brings him/her to Christ. But when we read some wrong gedels in the Ethiopian church, you have no choice but to denounce it. I strongly urge you to follow the early church's teachings and not some made up stuff over the years.

   Delete
 2. ይድረስ ለዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ!
  " የሐዋርያት ትምህርት መጀመርያው የክርስቶስ ነገረ ድኅነት ፍጻሜውም በክርስቶስ ኢየሱስ የተገኘውን የዘላለም ሕይወት ለአለሙ ሁሉ የምሥራች ብሎ መስበክ ነው፡፡" (ዮሐ.20፥31) (ዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ)። ነገር ግን ቅዱስ ዩሐንስ እንደሚመስክረው፡
  " 31 ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።" (ዩሐ. ም20 ፡31) ብሎ ያስተምረናል። ይህ የቤተክርስትያናችን ዋና ዓላም ሆኖ በቤተ ክርስትያናችን ስንደቅ ዓላም ላይ የሚሰቀል ብሩህ የሆነ መለእክት ነው። ለምንድን ነው ወደ ቤተ ክርስትያን የምንሄደው? የምንጾመው? የምንጸልየው? ስጦታ ይዘን የምንሄደው? እኛ በአባታችን አዳም ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙ ምክንያት የመጣብንን ሞት ቀይረን ሕይወት እንድናገኝ ነው። ሕይውትስ ማለት ምን ማለት ነው። ሕይወት ማለት የሞተ ነግርን መልሶ በነበረበት ነፍስን ማንሳት ወይም መኖርን ማድረግ ነው። አስቀድሞ የአዳም ልጆች የእግዚአብሔርን መንፈስ በመገፈፋቸው ምክንያት በሞት ወይም መልካምና ክፉን የሚያሳውቀን መንፈስ ተሞልተን እንኖር ነበር። አሁን ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ፍጥረታት ሳይኖሩ በፊት ሕይወት የሚሰጠውን መንፈሱን አዘጋጅቶት ነበር። በዚህም በኋለኛው ዘመን ይህንን የሰው ልጆች ከሞት ወደ ሕይወት የሚቀይራቸውን መንፈሱን በክርስቶስ ኢየሱስ ከሞት በማስነሳት ለእኛ ሁሉ ገለጠው ብሎ የእግዚአብሔር ቃል ያስተምረናል። በዚህም ቅዱስ ጴጥሮስ እንደሚያስተምረን፡
  " 20-21 ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።" (1ኛ ጴጥ. ም1)። ይላል። ይህም የእግዚአብሔር ጸጋ ይባላል። ይህም ጸጋ ደግሞ በእምነት ይገኛል ይላል። ይህ በእምነት የሚገኘው የእግዚአብሔር ጸጋ (ስጦታው) የሆነው ደግሞ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ነው። ምክንያቱም ሕይወት ከሞትንበት ነገር መነሳት የሚገኘው በመንፈስ ነው ይላል። በዚህም ራሱ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚያስተምረን ፡" 63 ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።" (ዩሐ. ም6) ይላል። ስለዚህ ቤተ ክርስትያናችን ዛሬ ሁላችንም ከሞት ወደ ሕይወት እንድንሻገር እኛን ሁሉ መመገብ ያለባት ይህ ሕይወት የሚሰጠውን ቃል ነው። ይህም ቃል እግዚአብሔር ነው። እንዲሁም በኋላም ከእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ የለበሰው ሕይወትን የሚሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። በዚህም ምክንያት ይህ በሕጉ በነቢያቱ በመዝሙሩና በምሥክሩ የተጻፈው ቃል ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ቃል ነው። ሰዎች ይህንን ቃል ካልተመገቡና ካላወቁ እምነታቸው ሁሉ ከንቱ ነው። ምክንያቱም አሁንም የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያስተምረን፡፡
  " 13 የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።14 እንግዲህ ያላመኑበትን እንዴት አድርገው ይጠሩታል? ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?15 መልካሙን የምሥራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው ተብሎ እንደ ተጻፈ ካልተላኩ እንዴት ይሰብካሉ?16 ነገር ግን ሁሉ ለምሥራቹ ቃል አልታዘዙም። ኢሳይያስ። ጌታ ሆይ፥ ምስክርነታችንን ማን አመነ? ብሎአልና።17 እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።" (ሮሜ ም10)። ይላል። በዚህም ቃል መሠረት እምነት የሚገኘው ከእግዚአብሔር ቃል ነው። የምናምነው ደግሞስ ምንድን ነው? ከላይ በዩሐንስ ወንጌል እኛ ሁሉ የምናመልከውን አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን እንድናውቀው የግዴታ በመጽሀፉ የተጻፈውን ቃሉን መማርና ምሥጡሩን መረዳት ያስፈልገናል ይላል። የምናምነው ደግሞ ምን እንደሆነ ቅዱስ ዩሐንስ እንደሚመስክረው፡
  " 31 ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።" (ዩሐ. ም20 ፡31) ብሎ ያስተምረናል። ስለዚህ እምነታችን ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው። ለዚህም ነው ቅዱስ ዩሀንስ በመልእክቱ ውስጥ እንደመሰክረው እኛ ሁሉ ከእነርሱ ጋር ወይም ከሐዋርያቶቹ ጋር ሕብረት እንዲኖረንና የምናመልከውን አምላክ እንድንረዳው በሚመክሩን ወቅት እንደመስክረው፡ "1 ስለ ሕይወት ቃል ከመጀመሪያው የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውንም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፤2 ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል እንመሰክርማለን፥ ከአብ ዘንድ የነበረውንም ለእኛም የተገለጠውን የዘላለምን ሕይወት እናወራላችኋለን፤3 እናንተ ደግሞ ከእኛ ጋር ኅብረት እንዲኖራችሁ ያየነውንና የሰማነውን ለእናንተ ደግሞ እናወራላችኋለን። ኅብረታችንም ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው።4 ደስታችሁም እንዲፈጸም ይህን እንጽፍላችኋለን።" (1ኛ ዩሐ. ም1)። ይላል። እንዲሁም በመቀጠል ቅዱስ ዩሐንስ እንደሚመስክረው፡
  "1 ክርስቶስ ነው ብሎ በኢየሱስ የሚያምን ሁሉ ከእግዚአብሔር ተወልዶአል፥ ወላጁንም የሚወድ ሁሉ ከእርሱ የተወለደውን ደግሞ ይወዳል።2 እግዚአብሔርን ስንወድ ትእዛዛቱንም ስናደርግ የእግዚአብሔርን ልጆች እንድንወድ በዚህ እናውቃለን።3 ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።4 ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና፤ ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው።5 ኢየሱስም የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ከሚያምን በቀር ዓለምን የሚያሸንፍ ማን ነው? 6 በውኃና በደም የመጣ ይህ ነው እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በውኃውና በደሙ እንጂ በውኃው ብቻ አይደለም7 መንፈስም እውነት ነውና የሚመሰክረው መንፈስ ነው።8 የሚመሰክሩት መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ። 9 የሰውን ምስክር ብንቀበል የእግዚአብሔር ምስክር ከእርሱ ይልቅ ይበልጣል፤ ስለ ልጁ የመሰከረው የእግዚአብሔር ምስክር ይህ ነውና።10 በእግዚአብሔር ልጅ የሚያምን በነፍሱ ምስክር አለው፤ በእግዚአብሔር የማያምን እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረውን ምስክር ስላላመነ ሐሰተኛ አድርጎታል።11 እግዚአብሔርም የዘላለምን ሕይወት እንደ ሰጠን ይህም ሕይወት በልጁ እንዳለ ምስክሩ ይህ ነው።12 ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።13 የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ። (1ኛ ዩሐ. ም5)። ይላል። በዚህ መሠረት ውሃው ሲል በጥምቀቱ ደሙ ሲል በስቅለቱ መንፈስ ሲል በቃሉ እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን መስክረዋል። በዚህም እነዚህ የሚመሰክሩት ማለትም መንፈሱና ውኃው ደሙም ሦስት ናቸውና፤ ሦስቱም በአንድ ይስማማሉ ይላል። የተስማሙት የሆነውን በመመስከራቸው ነው።

  ReplyDelete
 3. በመቀጠልም፡
  ዛሬም እኛም የግዴታ ከአባቶቻችን ጋር ይህንን በእምነት ሆነን ለመመስከርና ሕይወት ለማግኘት ወንጌልን በቤተ ክርስትያናችን ውስጥ መማር ያስፈልገናል እንዲሁም ለሁሉም ማዳረስ ይገባታል። ይህንን ስል ወንጌል አይሰበክም ለማለት አይደለም ነገር ግን ሰዎች ሁልጊዜ የሚናገሩት በራሳቸው እውቀትና መጽሀፍ ስለሆነ ለእኛ ለነፍሳችን የሚያስፈልጋትን ጥሩ ጮማ ጥሩ ውኃ ጥሩ ወይን ጥር ስብ ባለማግኘቱ ምክንያት በረሃብ የወደቁና ጉድጓድ ውስጥ ገብተው የሞቱ ብዙ ናቸው። ስለዚህ መልካም እንዲሆንልን እውቀትን አግኝተን አምላክችንን እንድናገለግለው ጥበብም አግኝተን እግዚአብሔርን እንድንፈራው ማስተዋልም ኖሮን ከኃጢያት እንድንርቅ የግዴታ ፡
  "13፤ ስለዚህ ሄደው ወደ ኋላ እንዲወድቁ እንዲሰበሩም ተጠምደውም እንዲያዙ የእግዚአብሔር ቃል ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ትእዛዝ በትእዛዝ፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ሥርዓት በሥርዓት፥ ጥቂት በዚህ ጥቂት በዚያ ይሆንላቸዋል።" (ኢሳ. ም28)፡ ይላል። በዚህም ቃል መሠረት ይህ ባለመሆኑ ምክንያት ወንጌል ያለውን ይህ ነው ብለን ስትናገር የተለያዩ ስሞችን ይሰጣሉ። ስለዚህ ቤተ ክርስትያንም በአባቶቻችን ሐዋርያት ትምህርት ላይ በክርስቶስ መሠረት የተመሰረትች ስለሆነ የግዴታ እኛንና አባቶቻችንን ህብረት የሚሰጠንን ወንጌል መማርና ማስተማር ግዴታ ነው። ቅዱስ ጳውሎሰም ለኤፌሶን ሰዎች እንደመክራቸው ዛሬም ለሁላችንም እንድሚመክረን በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ ይላል። በዚህም ሐዋርያትና ነቢያት ያስተማሩትን ተከትለን ብንጉዝ እውነተኛውን አምላክችንን እናገኛለን እንዲሁም ከተሳሳተ ትምህርትን እንወጣለን። በዚህም
  " 8 ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤9 ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።10 እኛ ፍጥረቱ ነንና፤ እንመላለስበት ዘንድ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን።11 ስለዚህ እናንተ አስቀድሞ በሥጋ አሕዛብ የነበራችሁ፥ በሥጋ በእጅ የተገረዙ በተባሉት ያልተገረዙ የተባላችሁ፥ ይህን አስቡ፤12 በዚያ ዘመን ከእስራኤል መንግሥት ርቃችሁ ለተስፋውም ቃል ኪዳን እንግዶች ሆናችሁ በዚህም ዓለም ተስፋን አጥታችሁ ከእግዚአብሔርም ተለይታችሁ ያለ ክርስቶስ ነበራችሁ።13 አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል።14-15 እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥16 ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።17 መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁ ለእናንተ ሰላምን፥ ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን የምስራች ብሎ ሰበከ፤18 በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለንና።19 እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባላገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም።20 በሐዋርያትና በነቢያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፥ የማዕዘኑም ራስ ድንጋይ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፤21 በእርሱም ሕንጻ ሁሉ እየተጋጠመ በጌታ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንዲሆን ያድጋል፤22 በእርሱም እናንተ ደግሞ ለእግዚአብሔር መኖሪያ ለመሆን በመንፈስ አብራችሁ ትሠራላችሁ።" (ኢፌ. ም2)። ይላል።  ወንጌልም የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለችና ንስሀ ግቡ ብላ የምታስተምረው። ሰዎች ካለባቸው የሥጋ መንፈስ ተላቀው የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲያገኙና ሕይወት እንዲደርግ ነው የሚመክረው። አሁንም ሕይወት የሚሰጠውን ነገር የሚገኘው ከወንጌል ነው። ወንጌልን ወይም የእግዚአብሔር ቃል በጆሮአችን በሚገባበት ወቅት እኛን ሁሉ አስተሳሰባችንን ይቀይረዋል። በዚህም ከክፉ ሥራ እራስችንን በማላቀቅ ወደ መልካም ሥራ ይመራናል። በዚህም የሞተው ሕሊናችን ሕይወትን አግኝቶ መልካም ፍሬ ያፈራል። በዚህም ሰዎች ቃሉን በመመግባቸው ምክንያት ሰላስም ስድሳም መቶም ፍሬ ያፈራሉ። ለዚህም ነው ሕይወትን የሚሰጥ እኔ የነገርኳችህ ቃል ነው ብሎ የሚአስተምረን። ቃሉንም በትክክል ሳናሳንስ ሳንጨምር በመጽሀፉ ውስጥ የተመዘገበውን መናገርና መስማት ያስፈልገናል። ስለዚህ እግዚአብሔር እኛ ሁሉ ሕይወትን እንድናገኝ፡
  "1፤ እናንተ የተጠማችሁ ሁሉ፥ ወደ ውኃ ኑ፥ ገንዘብም የሌላችሁ ኑና ግዙ ብሉም፤ ኑ ያለ ገንዘብም ያለ ዋጋም የወይን ጠጅና ወተት ግዙ።2፤ ገንዘብን እንጀራ ላይደለ፥ የድካማችሁንም ዋጋ ለማያጠግብ ነገር ለምን ትመዝናላችሁ? አድምጡኝ፥ በረከትንም ብሉ፥ ሰውነታችሁም በጮማ ደስ ይበለው።3፤ ጆሮአችሁን አዘንብሉ ወደ እኔም ቅረቡ፤ ስሙ ሰውነታችሁም በሕይወት ትኖራለች፤ የታመነችይቱን የዳዊትን ምሕረት፥ የዘላለምን ቃል ኪዳን ከእናንተ ጋር አደርጋለሁ።" (ኢሳ. ም55)። ይላል። በዚህም ትክክለኛውን ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነ እናውቃለን። አባቶቻችን ሐዋርያት አማልክቸውን እንዲረዱት ያደረገው በመጽህፉ ነው። በዚህም ቅዱስ ሉቃስ እንደሚመስክረው፡ "44 እርሱም። ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው።45 በዚያን ጊዜም መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው፤" (ሉቃ. ም24)። ይላል። ስለዚህ ወገኖቼ ሁሉ መደረግ የምሚገባው ነገር ቤተ ክርስትያናችንም ትኩረት ማድረግ የሚገባት ነገር ሕይወት የሚሰጠውን ቃል ማቀጣጠል ነው። በሰዎች መጽሀፍ ሳንመራ በእግዚአብሔር መጽሀፍ ተመርተን ሕይወትን እናግኝ። በዚህም ቅዱስ ሰለሞን እንደሚመክረን፡ " 1 ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥2 ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ።3 ረቂቅ እውቀትን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥4 እርስዋንም እንደ ብር ብትፈላልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤5 የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ።6 እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤7 እርሱ ለቅኖች ደኅንነትን ያከማቻል፤ ያለ ነውር ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፤8 የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፤ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናል።9 የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ።10 ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፥ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤11 ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል፥" (ምሳ. ም2)። ይላል።
  ወስብሃት ለእግዚአብሔር!

  ReplyDelete
 4. <<" 31 ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።" (ዩሐ. ም20 ፡31) >> Is this the word of Protestantism or Satanism???? Please check your book! Knowledge is not bad, but helps you understand about your GOD. Is this time of knowledge and read the book do not afraid.

  ReplyDelete
 5. ትናንት በሉተር የተፈበረከን ተራ ተረት ክርስትና ነው ለማለት ትንሽ አይሰቀጥጥም? በክርስትና ስም የሚወራጨው፣ በአለም አቀፍ ደረጃ በሚሰራው፣ በአስፀያፊ ና አስቂኝ ስራው የሚታወቀው ፕሮቴስታንቲዝም የሰይጣን እቅድ አስፈፃሚ ነው፣

  ReplyDelete