Tuesday, April 7, 2015

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማማት የምናስበው ለምንድነው?

Read in PDF

ይህ ሳምንት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት የሚታሰብበት ሳምንት ነው፡፡ ከሰሙነ ሕማማት ጋር በተያያዘ እስኪ የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንጠይቅ፤ ሕማማቱን የምናስበው ለምንድነው? የቀደሙ አባቶች ይህን ሥርዓት ሲሠሩ ዋና ዓላማቸው ምን ይሆን? ያ ዓላማቸው ዛሬ ላይ ሲታይ ግቡን መቷል ወይስ ዒላማውን ስቷል? ታዲያ በዚህ የሕማማት ሳምንት ምን እናድርግ?
ለእነዚህ ጥያቄዎች ሁሉም ሰው የየራሱን ምላሽ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ወይም ምላሹን መስጠት ይከብደው ይሆናል፡፡ ሆኖም ጥያቄዎቹ በዚህ ሰሙነ ሕማማት ጌታችን ስለእኛ የሆነውንና ያደረገውን እንድንረዳ ዕድሉን ይሰጡናልና ጥያቄዎቹን በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ለመመለስ እንሞክር፡፡
ሕማማቱን የምናስበው ለምንድነው? ወይም ለምን መሆን አለበት? በዚህ ወቅት የጌታን ሕማማት የምናስበው ጌታ ስለእኛ ኀጢአት የተቀበለውን መከራ በማሰብ ለፍቅሩ ተመጣጣኝ ምላሽ ባይገኝም በተቻለ መጠን በምስጋናና በአምልኮት ምላሽ ለመስጠት፣ በጌታ ድንቅ ፍቅር ይበልጥ ልብን ለማቀጣጠል፣ በዚህም በጸጋ ባገኘነው መዳን እየተደነቅን መዳን እንደተደረገለት ሰው ለመኖርና መዳናችንን ለመፈጸም ብርታትና ኀይል ለማግኘት፣ በጌታ ፍቅር ታስረን እስከመጨረሻው ጌታን ለመከተል የጀመርነው ጉዞ የቆመበትን ጽኑ መሠረት ማለትም የጌታን ሞትና ትንሣኤ በመንፈስና በዐይነ ኅሊና ለማስተዋል እንዲረዳን ነው፤ መሆንም አለበት፡፡
የቀደሙ አባቶች አንድ ጊዜ የተከናወነውንና ለዘወትር እምነው የሚቀርቡትን የሚያድነውን የክርስቶስን ሕማማትና የቤዛነት ሥራውን በሰሙነ ሕማማት በየዓመቱ እንዲታሰብ ያደረጉት ከላይ የተዘረዘሩት መልካም ነገሮችን በመፈጸም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ኅብረት እንድናጠናክርበት ለማድረግ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም የክርስቶስ ሕማማት የፈውሳችን ምክንያት ነው፤ የመዳናችን መሠረት ነው እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቁስል እኛ ተፈወስን” እና “በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ” (ኢሳ. 53፥5፤ 1ጴጥ. 2፥25) እንዲሉ መጻሕፍት፡፡ ጌታ የተቀበለው መከራ ስለመተላለፋችንና ስለበደላችን የተከፈለ ካሳ ነው፤ እርሱ የእኛ ምትክ ሆኖ በሥጋ የመጣ አምላክ እንደመሆኑ በእርሱ መከራ መቀበል ካልሆነ በቀር ሌላ ምንም የመዳን ተስፋ አልነበረንም፤ የለንምም፡፡ ስለዚህ በሕይወታችን ውስጥ ከዚህ የበለጠ የምናስበው ነገር ሊኖር አይችልም፤ አይገባምም፡፡ ለዚህ ነው ቀደምት አበው የክርስቶስን መከራ መስቀል እናስብበት ዘንድ ሰሙነ ሕማማትን የሠሩልን፡፡ ሰው የክርስቶስን ሕማማት በዚህ መንገድ ሲያስብ ከላይ የተዘረዘሩትን ነገሮች በማስታወስ በክርስቶስ ፍቅር የበረታ ይሆናልና፡፡ 

አሁን ትልቁ ጥያቄ አበው የሠሩት ያ ዓላማቸው ዛሬ ላይ ሲታይ ግቡን መቷል ወይስ ዒላማውን ስቷል? የሚለውን መመለስ በመቻሉ ላይ ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው የሰሙነ ሕማማት መሠረታዊ ዓላማና መልእክት ዛሬም ሙሉ በሙሉ አልጠፋም ማለት ይቻላል፣ በዚህ ወቅት በተለይ የቅዱሳት መጻሕፍት ክፍሎች ይነበባሉ፤ በሰሙነ ሕማማት በቀጥታ ሊታሰብ የሚገባው ጌታ በዜማ ይመሰገናል፤ ውለታው በቅዱሳት መጻሕፍት ንባብና በያሬዳዊ ዝማሬዎች ይዘከራል፡፡ አምልኮትና ስግደት ሳይከፋፈልና ሌሎች እንዲጋሩት ሳይደረግ “ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ለዓለመ ዓለም” (ምስጋና ክብርና ኀይል ለአንተ ነው)፣ ለአምላክ ይደሉ (ይገባል)፣ ለሥሉስ ይደሉ (ለሥላሴ ይገባል)፣ ለማሕየዊ ይደሉ (ለአዳኙ ይገባል) ለኢየሱስ ይደሉ ለክርስቶስ ይደሉ … እየተባለ ስግደት ለአምላክ ብቻ እንደሚገባ ይታወጃል፤ በተግባርም ስግደት ለአምላክ ብቻ ይቀርባል፡፡ ይህም የሚያሳየው ሰሙነ ሕማማት ዛሬም የክርስቶስ ሕማምና ሞት የሚዘከርበት ወቅት መሆኑን ነው፡፡
እንዲህ ሲባል ግን እንደ ተአምረ ማርያም ያሉ የዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ልቦለድ ድርሰቶች እየተነበቡ ንጹሑን አምልኮት እየበረዙት፤ ምእመኑን ከክርስቶስ ፍቅር እያናጠቡትና እየለዩት፣ አምልኮቱንም እየቀየጡበት አይደለም ማለት አይቻልም፡፡ ከእዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ነገሮችን ለማስታወስ በትእምርትነት የተሰጡና ከተለያዩ የተለመዱ ድርጊቶች የመታቀብ ሥነ ሥርዓቶች ዋናውን የክርስቶስን ሕማማተ መስቀል ከማመልከት ይልቅ ራሳቸውን በዚህ እውነት ስፍራ እየተኩትና ምእመናንን ግራ እያጋቧቸው ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በዚህ በሰሙነ ሕማማት ትከሻ ለትከሻ መሳሳም ክልክል ነው የሚል ሥርዓት አለ፡፡ ይህ ሥርዓት ለምን ተሠራ? ብለን ብንጠይቅ ይሁዳ መድኃኒታችን ኢየሱስን አሳልፎ የሰጠው በመሳም ስለሆነ ያንን ለማስታወስ ነው የሚል ምላሽ ሥርዓቱን ከሚሰብኩና ለመጠበቅ ከሚጠነቀቁ ወገኖች ይነገረናል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች በዚህ ውስጥ የክርስቶስን መከራ መስቀል ምን ያህል አስበውት ይሆን? ብለን ብንጠይቅ መልሱ ሥርዓቱን ለመጠንቀቅ ከመሞከር ያለፈ ሆኖ አናገኘውም፡፡ ይህንና ይህን የመሳሰሉ በርካታ፣ በዚህ በሰሙነ ሕማማት የክርስቶስን መከራ መስቀል ያመለክታሉ የተባሉና በመታቀብና በመፈጸም የሚከናወኑ ሥርዓታት የክርስቶስን መከራ መስቀል ከመግለጥ ይልቅ እየሸፈኑት መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡
በሌላም በኩል አብዛኛው ሰው ይህን ሰሙነ ሕማማትን የሚያስበው ዓመታዊ ኃጢአቱን በስግደት ብዛት ለማራገፍ እንደሆነ በግልጽ ይስተዋላል፡፡ በተለይም የስቅለት ዕለት ይህ ጎልቶ የሚታይ ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማት ኃጢአታችንን በስግደት ብዛት የምናወራርድበት ወቅት ሳይሆን ኃጢአታችን በክርስቶስ ሞት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወራረዱን እያስታወስን በክርስቶስ ፍቅር ዳግም ራሳችንን የምናበረታበት ነው ሊሆን የሚገባው፡፡ ስለኃጢአታችንም አምነን ንስሐ ብንገባ፣ በሰሙነ ሕማማት ብቻ ሳይሆን ዘወትርም በዚያው ኢየሱስ ራሱን የተወደደ አድርጎ አንድ ጊዜ ባቀረበው መሥዋዕት አማካይነት ስርየትን እናገኛለን፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍትም የሚመሰክሩት ይህንኑ ነው፡፡
“እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” (ዕብ. 7፥27)
ሊቀ ካህናትም በየዓመቱ የሌላውን ደም ይዞ ወደ ቅድስት እንደሚገባ፥ ራሱን ብዙ ጊዜ ሊያቀርብ አልገባም፤ እንዲህ ቢሆንስ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ብዙ ጊዜ መከራ ሊቀበል ባስፈለገው ነበር፤ አሁን ግን በዓለም ፍጻሜ ራሱን በመሠዋት ኃጢአትን ሊሽር አንድ ጊዜ ተገልጦአል።” (ዕብ. 9፥25-26)
“በዚህም ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አንድ ጊዜ ፈጽሞ በማቅረብ ተቀድሰናል። ሊቀ ካህናትም ሁሉ ዕለት ዕለት እያገለገለ ኃጢአትን ሊያስወግዱ ከቶ የማይችሉትን እነዚያን መሥዋዕቶች ብዙ ጊዜ እያቀረበ ቆሞአል፤ እርሱ ግን ስለ ኃጢአት አንድን መሥዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀመጠ፥ … አንድ ጊዜ በማቅረብ የሚቀደሱትን የዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋልና።” (ዕብ. 10፥10-12፡14)
ስለዚህ ቃሉ ከሚለው ውጭ እየተደረጉ ካሉት ሥርዓታት አንጻር ሰሙነ ሕማማት በተወሰነ መልኩም ቢሆን አበው በሰሙነ ሕማማት የሠሩት አንዳንዱ ሥርዓት ዒላማውን እየሳተና ግቡን እየመታ አለመሆኑ በግለጽ ይታያል፡፡ ይህን ያደረገውም ጠላት ሰይጣን መሆኑ አይካድም፡፡ በቅዱስ ቃሉ ወንጌላችን የተከደነ ቢሆን እንኳ የተከደነባቸው ለሚጠፉ ነው። ለእነርሱም የእግዚአብሔር ምሳሌ የሆነ የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፥ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ።” እንደተባለው (2ቆሮ. 4፥3፡4) ሰዎች የክርስቶስን መከራ መስቀልና ዐላማውን መገንዘብ የተሳናቸውና ዋናውን ጉዳይ ሳይሆን ዋናውን ጉዳይ እንዲያሳዩ በትእምርትነት በተሰጡ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ ያደረጋቸው በዋናነት ሰይጣን መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ስለዚህ አንተ ሰይጣን ወግድ ልንለው ይገባል፡፡
ታዲያ ወደ ትክክለኛው የሰሙነ ሕማማት ዐላማ ለመመለስ ምን ላድርግ? የሚል ጠያቂ ካለ በቅድሚያ ይህ ወቅት የሚያሳስበው ክርስቶስ ስለእርሱ ኀጢአት መከራ መቀበሉንና የኀጢአት ዕዳውን መከፈሉን ነውና፣ ይህን ያላመነ ሰው ካለ ክርስቶስ ዕዳውን ለመክፈል እንደተንገላታለትና ዕዳውን እንደከፈለለት በማመን የዘላለም ሕይወት ባለቤት መሆኑን ሊያረጋግጥ ይገባል፡፡ በዚህ ሰሙነ ሕማማትም ይህን እያስተዋሰ በክርስቶስ ፍቅር ሕይወተሩን ሊያበረታ ይገባዋል፡፡ የተሠሩ ሥርዓታት ሁሉ ወደዚህ እውነት ሊያደርሱት ይገባል፤ ካላደረሱት ግን ዓላማቸውን ስተዋልና የእነርሱ ተገዢ በመሆን ከክርስቶስ ፍቅር ሊለይ አይገባውም፡፡ ለሁሉም በዚህ ሰሙነ ሕመማት ጌታ ያደረገልንን እያሰብን ልባችንን በክርስቶስ ፍቅር እናበርታ፡፡

5 comments:

 1. ለተከበራችሁ አባ ሰላማ!
  ጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማማት የምናስበው በትክክለኛው ጊዜ ነው? የመጽሀፉን ቃል ተከትለን ይህንን የመታሰቢያ በዓል እናከብራለን? ይህንንም ልትመልሱ ይገባል። እንግዲህ ዋናው የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማትና መሰቀሉ ለእኛ ሲል ደሙን ማፍሰሱ ዋናው ምክንያት ምነድን ነው? እግዚአብሔር አስቀድሞ ፍጥረታት ሳይኖሩ በፊት አዳም ወደ ሞት ይገባ ዘንድ ያውቅ ነበርና እግዚአብሔር ይህንን ባለመታዘዘ ምክንያት የሚሞተውን አዳም ሕይወት ለመስጠት የእርሱን ጸጋ ፍጥረታት ሳይኖሩ በፊት አዘጋጅቶት ነበር። በዚህም ይህንን የእግዚአብሔር ጸጋ ሕይወት የሚሰጠውን መንፈሱን ወይም ቃሉን ልጁን ከሙታን በማስነሳት ለእኛ ሁሉ እንዲበዛልን በብዛት አፈሰሰልን። ለዚህም ነው አስቀድሞ እኛን ነጻ ለማውጣት ሕይወት የሚሰተውን የእግዚአብሔርን መንፈስ ይዞ እንደሚመጣ የተናገረው። በዚህም መሠረት
  "1፤ የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፥ ለተማረኩትም ነጻነትን ለታሰሩትም መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል።" (ኢሳ. ም61) ብሎ በዮርዳኖስ የእግዚአብሔርን መንፈስ በመሞላት ለእና ሁሉ ሕይወት የሚሰተውን መንፈሱን ወይም ቃሉን አፍሶልናል።
  " 20-21 ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ፥ ነገር ግን እምነታችሁና ተስፋችሁ በእግዚአብሔር ይሆን ዘንድ፥ ከሙታን ባስነሣው ክብርንም በሰጠው በእግዚአብሔር በእርሱ ስለምታምኑ ስለ እናንተ በዘመኑ መጨረሻ ተገለጠ።" (1ኛ ጴጥ. ም1) ብሎ ያስተምረናል። ስለዚህ ይህንን ሕይወት የሚሰጠውን መንፈሱን የእግዚአብሔር ጸጋ የሰው ልጆች ሕይወት እንዲያገኙ በእምነት የሚሆን ስጦታ አደረገው። በዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች እንዳስተማራቸው
  " 25 እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥26 ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው።" (ሮሜ ም3) ብሎ ያስተምረናል። በዚህም መሠረት ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ጸጋ ለሰው ልጆች ይሰጥ ዘንድ ደሙን ያፈሰሰው በእውነቱ በአርብ ቀን ነው? የተነሳውስ እሑድ ቀን ነው? የሚለውን ጥያቄ ሁላችንም በመጽሀፉ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት መመለስ ግዴታ አለብን። ይህንንም ለመረዳት እንድንችል የግዴታ መጽሀፉን መመርመር ይገባናል። በዚህም መሠረት አሁን እኛ ይዘን ያለነው ሥርዓት የተገኘ ከየት ነው? ከታች በእንግሊዘኛ ቁንቋ ተመዝግቦ እንደሚገኘ እሁድ የፋሲካ ወይም የትንሳኤ በዓልና አርብ የስቅለት ቀን እንዲሆን የተደረገው በኒቅያ ጉባኤ እንደሆነ ታሪክ ያስተምረናል። በዚህም

  ReplyDelete
 2. " The First Council of Nicaea (/naɪˈsiːə/; Greek: Νίκαια [ˈni:kaɪja]) was a council of Christian bishops convened in Nicaea in Bithynia by the Roman Emperor Constantine Iin AD 325." መሆኑን ታሪክ ያስተምረናል። በዚህም መሠረት በክርስትና እምነት ተከትያዮችና በይሁዳውያን እምነት ተከታዮች መካከል ባለባቸው ከፍተኛ አለመግባባት ምክንያት በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔር ፋሲካን (ስቅለት) አክብሩ ብሎ የሰጠውን ቀን ከእነርሱ ጋር አብረን አናከብርም በማለት የራሳችን ቀን አቆጣጠር በመቀመር ይህው አሁን ይህንኑ የተቀየረውን ሥራዓት ይዘን አናከብራለን።
  ነገር ግን የእግዚአብሔር መጽሀፍ እንደሚያስተምረን፡
  " 1 ፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።2፤ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። የተቀደሰ ጉባኤ ብላችሁ የምታውጁአቸው በዓላቶቼ፥ የእግዚአብሔር በዓላት፥ እነዚህ ናቸው።3፤ ስድስት ቀን ሥራ ይሠራል፤ በሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት ነው፤ የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንበታል፤ ምንም ሥራ አትሠሩም፤ በምትኖሩበት ሁሉ ለእግዚአብሔር ሰንበት ነው።4፤ እነዚህ የእግዚአብሔር በዓላት፥ በየዘመናቸው የምታውጁአቸው፥ የተቀደሰ ጉባኤ ናቸው።5፤ በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው።" (ሌዋ. ም23) ብሎ ይህም የእግዚአብሔር ፋሲካ እንዴት እንደሚያከብሩት እግዚአብሔር ለእስራኤል እንደነገራቸው፡ በዚህም መሠረት እንዲሁም
  "14፤ ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፥ ለእግዚአብሔርም በዓል ታደርጉታላችሁ፤ ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ሆኖ ለዘላለም ታደርጉታላችሁ።" (ዘጸ. ም12) ብሎ ነግሯቸዋል። በዚህም ቃል መሠረት
  ኢየሱስ ክርስቶስና የእርሱም ደቀ መዛሙርቶች ይህንኑ በዓል በመጽሀፉ በተጻፈው መሠረት በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ሲመሽ የእግዚአብሔር ፋሲካ አክብረውታል። በዚህም ቅዱስ ማቴዎስ እንደሚመስክረው፡
  "17 በቂጣው በዓል በመጀመሪያ ቀን ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ቀርበው። ፋሲካን ትበላ ዘንድ ወዴት ልናሰናዳልህ ትወዳለህ አሉት።18 እርሱም። ወደ ከተማ ከእገሌ ዘንድ ሄዳችሁ። መምህር። ጊዜዬ ቀርቦአል፤ ከደቀ መዛሙርቴ ጋር ከአንተ ዘንድ ፋሲካን አደርጋለሁ ይላል በሉት አለ።19 ደቀ መዛሙርቱም ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ ፋሲካንም አሰናዱ።20 በመሸም ጊዜ ከአሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርቱ ጋር በማዕድ ተቀመጠ።" (ማቴ. ም26)። ይህም የሆነው ወር በገባ በአሥራ አራተኛው ቅን ምሽት ነው። ከዚያም ሲነጋ ፋሲካ ስለሆነ በዚህም ቀን በአሥራ አምስተኛው ቀን የሆነውን እንዲህ ሲል ቅዱስ ማርቆስ መዝግቦታል።
  " 24 ሰቀሉትም፥ ልብሱንም ማን ማን እንዲወስድ ዕጣ ተጣጥለው ተካፈሉ።25 በሰቀሉትም ጊዜ ሦስት ሰዓት ነበረ።26 የክሱ ጽሕፈትም። የአይሁድ ንጉሥ የሚል ተጽፎ ነበር።27 ከእርሱም ጋር ሁለት ወንበዶች አንዱን በቀኙ አንዱንም በግራው ሰቀሉ።28 መጽሐፍም። ከአመፀኞች ጋር ተቆጠረ ያለው ተፈጸመ።" (ማር. ም15) ብሎ መዝግቦታል። በዚህም ይህ ለሰው ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰተው ጸጋ ወይም በደሙ ነጻነት ያገኘንበት ቀን የፋሲካ ቀን ይባላል። ይህም ቀን የሚውለው ወር በገባ ባሥራ አምስተኛው ቀን በኒሳን ወር ወይም በሐቢብ ወር ነው። ይህም ቀን በተመሳሳይ ቀን እሥራኤል የበግ ደም አፍሳ ከባርነት ነጻ የህነችበት ቀብን ነው። ስለዚህ እኛ ዛረኢ ስቅለት ብለን ይምናከብረው ቀን የእግዚአብሔር ፋሲካ ቀን ነው። ይህም የነጻነት ቀን ነው። የሚውለውም በየዓመቱ ወር በገባ ባሥራ አራተናው ቀን ምሽትና በሚቀጥለው ቀን ነው። ለዚህም ነው ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፡ ወር በገባ በአሥራ አምስተኛው በፋሲካ በዓል ቀን።
  " 34 በዘጠኝ ሰዓትም ኢየሱስ። ኤሎሄ፥ ኤሎሄ፥ ላማ ሰበቅታኒ? ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ፤ ትርጓሜውም አምላኬ፥ አምላኬ፥ ለምን ተውኸኝ? ማለት ነው።35 በዚያም ከቆሙት ሰዎች ሰምተው። እነሆ፥ ኤልያስን ይጠራል አሉ።36 አንዱም ሮጦ ሆምጣጤ በሰፍነግ ሞላ በመቃም አድርጎ። ተዉ፤ ኤልያስ ሊያወርደው ይመጣ እንደ ሆነ እንይ እያለ አጠጣው።37 ኢየሱስም በታላቅ ድምፅ ጮኸ ነፍሱንም ሰጠ።38 የቤተ መቅደስም መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ከሁለት ተቀደደ።" (ማር. ም15)።
  ስለዚህ አሁንም የእግዚአብሔር ቃል የሚያስተምረን እኛ ሁሉ ምን ያህል ከእግዚአብሔር ቃል ርቀን የራሳችንን ፈቃድ ጽድቅ በማድረግ ከእግዚአብሔር እንደራቅን ያስተምረናል። በዚህም ሁላችንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ባለማወቃችን ምክንያት አሁንም በመካከላችን የክርስቶስ ወገን የሚያደርገን የእግዚአብሔር ጸጋ በደሙ ማስተርያ አድርጎ ያቆመው መንፈሱ በእኛ ስለሌለ ሁላችንም በእዳ የተያዝን በክፋትና በመለያየት የምንኖር ነን። ስለዚህ የግዴታ የእግዚኦአብሔርን ቃል አስተውለን በሚለው በታዘዘው መሠረት በዓሉን መታሰቢያውን ብናደርግ እንባረክበታለን።
  ወስብሃት ለእግዚአብሔር!

  ReplyDelete
 3. ዕለተ ሰኑይ /ሰኞ/ በነግህ

  ከሁሉም በፊት የሰዓቱ ተረኛ አገልጋይ ቃጭል እየመታ ሦስት ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑን ይዞራል: የሰባት ቀን ውዳሴ ማርያም፤ አንቀጸ ብርሃን፤ መዝሙረ ዳዊት በሙሉ ይጸለያል፤ በዕለቱ ተረኛ መምህር /መሪጌታ/ የዕለቱ ድጓ ይቃኛል፤ ድጓው ከዐራቱ ወንጌላት ምንባብ ጋር እንዲስማማ ሆኖ ነው የሚቃኘው ድጓውን እየተቀባበሉ እያዜሙ ይሰግዳሉ፡፡ የድጓው መሪ መምህር ሰኞ በቀኝ ከሆነ ማክሰኞ በግራ በኩል ባለው መምህር ይመራል እንዲህ እየተዘዋወረ ይሰነብታል ድጓው ሦስት ጊዜ ተመላልሶ ከተዘለቀ በኋላ፡-


  ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
  አማኑኤል አምላኪየ ለከ ኀይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
  ኦ እግዚእየ ኢየ ሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም፣
  ኀይልየ ወጸወንየ ውእቱ እግዚእየ እስመ ኮንከኒ ረዳእየ እብል በአኮቴት


  እየተባለ በቀኝ በኩል ስድስት፣ በግራ በኩል ስድስት ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል፡፡ በድምሩ 12 ጊዜ ማለት ነው በዚያው ልክ አቡነ ዘበሰማያት በዜማ /በንባብ/ ይደገማል፡፡ ከዚያ በመቀጠል፡-


  ለአምላክ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
  ለሥሉስ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
  ለእዘዙ ይደሉ ክብር ወስብሐተ ወእዘዝ እስከ ለዓለመ ዓለም
  ለመንግሥቱ፣ ለሥልጣኑ፣ ለምኩ ናኑ፣ ለኢየሱስ፣ ለክርስቶስ፣ ለሕማሙ፣ /በዓርብ ለመስቀሉ/ ይደሉ]
  እያሉ በቀኝ በግራ እየተቀባበሉ ይሰግዳሉ በመቀጠል የነግሁ ምንባብ መነበብ የጀምራል፡፡ በመጨረሻ ተአምረ ማርያምና ተአምረ ኢየሱስ ይነበባሉ፡፡ ከዚያ ከዳዊት መዝሙር ምስባክ ተሰብኮ የሰዓቱ ወንጌል ከተነበበ በኋላ ጸልዩ በእንተ ጽንዓ ዛቲ የተባለው ጸሎት በካህኑ ሲነበብ ምእመናንም አቤቱ ይቅር በለን እያሉ በመስገድ ይጸልያሉ፡፡ ከዚያም ሁለተኛው ሥርዓተ ስግደት ይጀመራል፡፡ ዜማው የሚጀመረው አሁንም በቀኝ በግራ በመቀባበል ነው፡፡ አንዱ ይመራል ሌላው ይቀበላል እንዲህ በማለት:-


  ኪርያላይሶን /5 ጊዜ/ በመሪ በኩል
  ኪርያላይሶን /2 ጊዜ/ ዕብኖዲ ናይን በተመሪ በኩል ኪርያላይሶን ታኦስ ናይን
  ኪርያላይሶን ማስያስ ናይን
  ኪርያላይሶን ኢየሱስ ናይን
  ኪርያላይሶን ክርስቶስ ናይን
  ኪርያላይሶን አማኑኤል ናይን
  ኪርያላይሶን ትስቡጣ ናይን


  እየተባለ በዚሁ መልኩ አንድ ጊዜ ከተዘለቀ በኋላ እንደገና ይደገማል፡፡ በመጨረሻም በግራ በቀኝ በማስተዛዘል አርባ አንድ ጊዜ እየተዜመ ይሰገዳል፡፡


  ከላይ የተጠቀሱት የጌታችን ኀቡዓት ስሞች ናቸው፡፡ ኪርያላይሶን ማለት አቤቱ ይቅር በለን ማለት ነው፡፡ በመቀጠል መልክአ ሕማማት በሊቃውንቱ ይዜማል ከዚያም ካህኑ ፍትሐት ዘወልድ፣ ጸሎተ ቡራኬ፣ ወዕቀቦሙ፣ ኦ ሥሉስ ቅዱስ፣ ኦ ማኅበራኒሁ ለክርስቶስ፣ ነዋ በግዑ የተሰኙ ምንባባትን እያፈራረቁ ያነባሉ፡፡ ካህኑም በጸሎታቸው ፍጻሜ 41 ኪርያላይሶን በሉ ብለው መልእክት ያስተላልፋሉ፡፡ ሕዝቡም መልእክቱን ተቀብሎ ይጸልያል፡፡ ዲያቆኑም ሑሩ በሰላም እግዚአብሔር የሀሉ ምስሌክሙ፤ ንዑ ወተጋብኡ ውስተ ቤተ ክርስቲያን በጊዜ ሠለስቱ ሰዓት ብሎ ያስናብታል፡፡


  አሁን የተመለከትነው ሥርዓት ሰኞ በነግህ /በጥዋት/ የሚከናወነውን ነው፡፡ በ3፣ በ6፣ በ9፣ በ11 ሰዓት የሚከናወነው ሥርዓትም አሁን በተመለከትነው መሠረት ነው፡፡ የሚለያዩት ምንባባቱ ብቻ ናቸው፡፡ የሰሙነ ሕማማት ዜማም ከሰኞ እስከ ረቡዕ ግእዝ፣ ሐሙስ አራራይ፣ ዓርብና ቅዳሜ እዝል ነው፡፡ አሁን በተመለከትነው መሠረት ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ረቡዕ ከምንባባቸው በቀር ከላይ በተመለከትነው አኳኀን ሥርዓታቸው ይፈጸማል፡፡

  ReplyDelete
 4. አሁን ደግሞ የምንመለከተው ሥርዓተ ጸሎተ ሐሙስን ነው፡፡


  ጸሎተ ሐሙስ

  በብሉይ ኪዳን የቂጣ በዓል የሚለውን ትርጉም ከመስጠቱ በተጨማሪ ጌታችን ምስጢረ ቁርባንን ከምስጢረ ጸሎት ጋር አዋሕዶ የገለጠበት ዕለት ስለሆነ ታላቅ የምስጢር ቀን ነው፡፡ በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባባቱ እንደተለመደው ይከናወናሉ ለየት ያለው ሥርዓት መንበሩ /ታቦት/ ጥቁር ልብስ ይለብሳል ጸሎተ ዕጣን ይጸለያል ቤተ ክርስቲያኑ በማዕጠንት ይታጠናል፡፡


  በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኰስኰስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ጸሎተ አኮቴት የተባለ የጸሎት ዐይነት ተጸልዮ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ /በሊቀ ጳጳሱ/ እጅ ተባርኮ የሕጽበተ እግር ሥርዓት ከካህናት እስከ ምእመናን ከወንዶች እስከ ሴቶች በካህኑ አስተናጋጅነት ይከናወናል፡፡ ሥርዓተ ኅጽበቱ የሚከናወነውም በውኃ ብቻ ሳይሆን የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡


  ምስጢሩም የሚከተለውን ይመስላል፡፡

  ወይራ ጸኑዕ ነው ክርስቶስ ጽኑ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ በተጨማሪ እኛም /የሚያጥበውና የሚታጠበው ክርስቲያን/ መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ነው፡፡ የወይኑ ቅጠል በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ ይሆናቸው ዘንድ መስጠቱን ለማዘከር ነው፡፡ ማቴ 26.26 ይህም ሥርዓት ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለምእመናን ለማሳየት ነው ዮሐ. 13፤14፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ሐፀበ እያሉ ይዘምራሉ፡፡


  ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ምእመናን ይቀበላሉ፡፡


  የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ

  ቅዳሴው የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ነው፡፡ ደወሉ የጸናጽል ድምጽ ሲሆን በቀስታ ስለሚጮህ ነው፡፡ የድምጽ ማጉያ አይጠቀሙም፡፡ ምክንያቱም ዲያቆኑና ካህኑ ዜማውን በቀስታ የሚሉት ይሁዳ በምስጢር ጌታችንን ማስያዙን ለመጠቆም ሲሆን በሌላ በኩል የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደነበር ለማስታወስ ነው፡፡ በመቀጠል ክቡር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡


  ዕለተ ዓርብ ነግህ

  ዕለተ ዓርብ የአዳምን ነጻነት ለመመለስ የአዳምን ዕዳ በደል አምላካችን የተሸከመበት ዕለት የኀዘን ዕለት የድኅነት ዕለትም ነው፡፡ በዚሁ ዕለት ሁሉም ነገር እንደተለመደው ይከናወናል:: መሪው እዝል ይመራል ሕዝቡ ይከተላል አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፡፡ በየመሀሉ ወጸቢሖ ተማከሩ ሊቃነ ካህናት፤ ሲነጋም ሊቃነ ከህናት ተማከሩ የሚለው ዜማ በመሪ በተመሪ በሕዝብ ተሰጥዎ ይከናወናል፡፡ ምንባቡም ስግደቱም ድጓውም እንደ አለፈው ይቀጥላል፡፡


  በሦስት ሰዓት

  ሥዕለ ስቅለቱ መስቀሉ ወንጌሉ መብራቱ ጽንሐሑ በመቅደሱ በር ላይ ይዘጋጃል ዲያቆኑ በቃለ ማኅዘኒ በሚያሳዝን ቃል ግፍኦሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍኡኒ ይላል፡፡ ካህናቱም ምእመናኑም በዜማ እየተቀበሉ ይሰግዳሉ፡፡ ምስባክ ተሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፡፡ በየመሀሉ የሰዓቱ ድጓ ይቃኛል፡፡


  ስድስት ሰዓት

  የዕለቱ መሪ እዝል ይመራል፡፡ ሦስቱ ካህናት ጽንሐሑን ይዘው ከርቤ እያጠኑ ዲያቆናት መብራት እያበሩ ለመስቀልከ ንስግድ እያሉ ያዜማሉ ምእመናን ዜማውን እየተቀበሉ ይሰግዳሉ፡ ከዚያም ዲያቆኑ ቀነውኒ እደውየ ወእገርየ የሚለውን ምስባክ ሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ በየመሀሉ ድጓው ይዜማል፡፡


  ከዚህ ቀጥሎ ምእመናን ይቀመጣሉ ሦስቱ ካህናት ጥቁር ልብስ ለብሰው በሚያሳዝን ዜማ አምንስቲቲ ሙኪርያ አንቲ ፋሲልያሱ ፤ጌታዬ ሆይ ስለ እኔ ሞትህ ወዮ እኔ ልሙትልህ እያሉ ሦስት ጊዜ ያዜማሉ፡፡ ሕዝቡ ይቀበላል በዚያው አያይዘው ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ እያሉ በዜማ ይጸልያሉ ሕዝቡ ይቆማል ሥርዓተ ስግደቱም ይከናወናል፡፡


  በዘጠኝ ሰዓት

  ሌላው እንደተለመደው ሆኖ ኦ ዘጥዕመ ሞተ በሥጋ ሦስት ጊዜ ካህናቱ በዜማ ይሉታል ምእመናንም ይቀበላሉ፡፡ ምስባክ ተሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ ስግደት እንደተለመደው ነው፡፡ በሦስት ሰዓት፣ በስድስት ሰዓት፣ በዘጠኝ ሰዓት፣ ወንጌላቱ ተነበው እንዳለቁ ለምእመናን ትምህርተ ወንጌል ይሰጣል፡፡ ይህ ግን እንደ ቋሚ ሥርዓት ሳይሆን እንደ ሁኔታው አመቺነት ነው፡፡


  አሥራ አንድ ሰዓት

  ካህናት በአራቱ መዕዘን ቁመው አራት መቶ እግዚኦታ ያደርሳሉ፤ ዕለቱን የሚመለከቱ መዝሙራት ተመርጠው ይነበባሉ፡፡ ንሴብሖ እየተባለ ቤተ መቅደሱን በመዞር በከበሮ በጽናጽል በሕማሙ ያዳነን እግዚአብሔር ይመሰገናል፡፡ ዑደት የሚደረገው ሥነ ስቅለቱን በመያዝ ነው፡፡


  ምእመናን በሰሙነ ሕማማት የሠሩትን ኃጢአት እየተናዘዙ በካህናት አባቶች ንስሐ ይቀበላሉ፤ በወይራ ቅጠልም ቸብ ቸብ ይደረጋሉ የመከራው ተሳታፊዎች መሆናቸውን ለመግለጥ ነው፡፡ ወይራ ጽኑዕ ነው የተቀበልከው መከራም ጽኑዕ ነው እኛም ይህን መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ነው፡፡ በታዘዙት መሠረትም ሰግደታቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡


  ከዚያ በኋላ በካህኑ ኑዛዜ ምእመናን ወደ የቤታቸው ይሰናበታሉ፡፡ መስቀል መሳለም አሁንም የለም የቻለ ከሐሙስ ጀምሮ አሊያም ከዓርብ ማታ ጀምሮ እስከ ዕለተ ትንሣኤው ድረስ ያከፍላል /ይጾማል/ የተጀመረውም በዕለተ ስቅለቱ በሐዋርያትና በእመቤታችን እንደሆነ አበው ያሰተምራሉ፡፡


  ቀዳም ሥዑር

  የማትጾመዋ ቅዳሜ ስለምትጾም ስዑር /የተሻረች/ ተብላለች በዓል መሻርን አይመለከትም፡፡ ቀዳም ሥዑር በጾም ምክንያት የተሻረችው ቀዳሚት ሰንበት ሌሊት ሥርዓቱ የሚጀመረው በመኀልየ ሰሎሞን ምንባብ ነው፡፡ ማኀሌቱም እዝሉ እየተቃኘ፣ እየተመለጠነ፣ እየተዘመመ እየተመረገደ እየተጸፉ ያድራል ጥዋት አቡን መዋሥዕት ውዳሴ ማርያም ዜማ ተደርሶ ወለመልአከ ሕይወትሰ ሰቀልዎ በሚለው ሰላም ይጠናቀቃል፡፡ ገብረ ሰላም በመስቀሉ እየተባለ እየተዘመረ ቀጤማውም ቤተ መቅደሱን ዞሮ በካህኑ ተባርኮ ለምእመናን ይታደላል፡፡


  የቀጤማው አመጣጥና ምስጢርም ከአባታችን ከኖኅ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው ምድር በማየ አይኅ /በጥፋት ውኃ/ በጠፋችበት ወቅት የኖኅ ታማኝ መልእክተኛ ርግብ የውኃውን መጉደል ያበሰረችው ቀጤማ ይዛ በመግባት ነው፡፡ ዛሬም ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች የኃጢአት ውኃ ጐደለ፣ የኃጢአት ውኃ ጠፋ በክርሰቶስ ሞትና ትንሣኤ ነጻነት ተሰበከ ታወጀ በማለት ካህናት ቄጠማ ይዘው ምእመናንን ያበሥሩበታል፡፡ በአጠቃላይ ሥርዓተ ሕማሙን፤ ሰሙነ ሕማማት ብለው የተለየ ሥርዓት አውጥተው አባቶቻችን ተግተው ያቆዩልንን ሥርዓተ መላእክት ልንጠብቀውም ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

  ReplyDelete
 5. ስም ለሌለው በሚያደርገው ለሚያፍረው ፀሐፊ
  ስብከቱን የእንክርዳዱን አንበለበልኸው። የመጽሐፍ ቅዱሱንም ቃል በሚገርም የማጣመምና የማይገናኝ ከደጋን በባሰ በማጣመም ደበላለቅኸው። ማንበብ መቻልህን እንጂ አንድም የሰናፍንጭ ቅንጣት ያክል ስለምታነበው መልእክት ግንዛቤ የሌለህ፤ አፍህ እንጂ ልብህና አይምሮህ አብሮህ የማያነብ የተዘጋ ልብ ያለህ መሆንህን ነው ከዚህ እንክርዳድ የፊደል ጋጋታህ የተገነዘብኩት። አስፍው አሰፍው የስህተት ትምህርቱን እንክርዳድ መርዝ ትፋቱን ልክ ሊሳሳቡ የማይችሉ ማግኔቶችን የማቀራረብ ያክል የቃሉ መልዕክተ ሌላ ሆኖ ሳለ በተሳሳተ መንገድ ቤተክርስቲያን የክርስቶስን ህማም አስመልክታ የምታከናውናቸውንና ልጆቿም የሚፈጽሟቸውን የእምነት ስርዓቶች ለመቃወም ብቻ ሲባል አንዱን ከሌላው ለማገናኘት የተሔደበት መንገድ ስህተቱን አስፍቶ አውጥቶታል። የዚህ ጽሑፍ ፀሐፊና ለጣፊ ከሰው የተለየ መላእክት እንሿን በፊቱ ፍፁማን አይደሉም የሚለውን እንሿን ያለፈ በሰማይ እንሿን የሌለ ፍፁም ሆኖ እራሱን ልዩ ፍጡር ያደረገ ነው። ፀሐፊው ከጽሑፉ ጀምሮ የክርስቶስን ቤተክርስቲያን ለማጥፋትና እውነትንና መልካም የሆነውን የእምነት ስርዓት ለመንቀፍ ጠላት የወሰደው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተቃዋሚና አጥፊ መሆኑ ግልጽ ነው። አባቶቻችን ብሎ አባቶችን የሚያንቋሽሸው ይህ ጠላት ስርዓትን የሰሩልን ይልና የተሰራውን ስርዓት አተገባበሩን እያወቀም ይሁን ሳያውቅ የተለየ መልክና ቅርጽ በመስጠት ለመቃለልና ከወንጌል ውጭ ለማስመሰል በተለይም መስዋትን የተመለከተውን የወንጌል ክፍል በመምዘዝ በህማማት ሰሞን የሚከናወኑትንና ምዕመናን የሚፈፅሟቸውን የእምነት ስርዓቶች ለማጣጣል ተሞክሯል። ይህ አስመሳይ ቆዳ ለስላሳ እባብ የቤተክርስቲያን እምነትና ስርዓት እንዲሁም የልጆቿ ከሳሽና አሳዳጂ የብዩ ኢሳያስን የትንቢት ቃልና የሐዋርያትን ወንጌል በማጣመም ንስሐ መግባት ትክክል እንዳልሆነና በንስሐ እለት እለት በመቅረብ ስለ ሐጢያት መናዘዝን አላስፈላጊ ለማድረግ ብዙ እውነትን ለማጣመም እጂግ ተደክሟል። ሆኖም በዚህ የክርስቶስን ወንጌል የማጣመም የሰይጣን እንቅስቃሴ ምናልባት የክርስትና የመስቀል ጉዞ ያቃታቸው አለም በአሸን ክታቧ የማረከቻቸውን ያገኝ እንደሆን እንጂ እንደ ቀደመው በአዳምና በሔዋን ምክንያት እንደሆነው ሁሉም የሚጠፋ አይደለምና ጠላት መቸም ቢሆን አይሆንልህም። አስመሳይነት የሌባ የክርስቶስ ተቃዋሚ እንጂ በወንጌል ያመኑት አይደለምና ይህ ጽሑፍና ፀሐፊም ለጣፊም አስመሳዮች በራሳቸው መቆም የማይችሉ በሌላው ትክሻ ተንጠልጥለው ተንኮልና እንክርዳድ የሚረጩ የሰይጣን ሰራዊቶች ናቸው።

  ReplyDelete