Wednesday, April 22, 2015

“ጌታ ሆይ፥ በISIS ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው”


 Read in PDF
ምንጭ፡-የዲያቆን አቤንኤዘር ተክሉ ገጽ
በድጋሚ በግፈኛው ISIS ለተሰው ክርስቲያን ኤርትራውያን ፣ ኢራቃውያን ቤተሰቦች ጌታ መንፈስ ቅዱስ መጽናናትን እንዲያድላቸው ብርቱ ጸሎታችን ነው!!!
    የአንዲት ሕያው ቤተ ክርስቲያን ልዩና የሁል ጊዜ መገለጫ፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ለሁሉ በማዳረስ ማስፋትዋና የደቀ መዛሙርትን ቁጥርና እጅግ የሚታዘዙትንም ማብዛቷ ነው፡፡” (ሐዋ.6፥7) የባለበት ሂድ ወይም የእየቀጨጩ ዕድገት ጤናማነቱ ተፈጥሮዐዊም ፤ መንፈሳዊም አይደለም፡፡ በብዛትም በጥራትም ማደግ የጤናማ ተፈጥሮዐዊና መንፈሳዊ ዕድገት መገለጫ ነው፡፡ ወንጌሉ ሕያው ነውና ተበትኖ ፤ ተሰብኮ እንደዋዛ አይቀርም ፤ ሕያው ፍሬንም ያፈራል እንጂ፡፡

     ክርስትና ገና ጉዞውን በጀመረበት ቀደምት ጊዜያት፥ በአንድ የስብከት ርዕስና በአንድ ብርቱ ተአምራት ስምንት ሺህ የሚጠጉ አማኞች ወደአንድ መቶ ሐያው የጌታ ቤተሰብ ተጨመሩ፡፡ ሥራውን ሠሪው መንፈስ ቅዱስ ስለሆነ የቁጥሩ አጨማመር ከመደመርም ከብዜትም ይልቃል፡፡ እኛ የቀደምንበት አገልግሎት ጠላትን አለጊዜው ያጎለምሳል ፤ ጌታ የቀደመበት አገልግሎት ግን ጠላት ተኩላ እያለ ሥራውን ያሠራል፡፡(ማቴ.10፥16)

     ክርስትና ገና ከኢየሩሳሌም ሳይወጣ ፤ ያመኑት የመጀመርያው ወደስምንት ሺህ የሚጠጉ ክርስቲያኖች በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ እስጢፋኖስ በስምንት ሺህ አማኞች ላይ አሳላፊ ሆኖ እያገለገለ ባለበት ወራት፥ “የነፃ ወጪዎች ከተባለችው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያም ሰዎች ከኪልቅያና ከእስያም ከነበሩት አንዳንዶቹ ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር፤” (ሐዋ.6፥9)
      ጌታን በአድመኝነት አሳልፈው የሰጡት እኒያው ሰዎችና መሪዎች ዛሬም በእስጢፋኖስ ላይ ተነሳሱበት፡፡ ተኩላው ይጮኻል ፤ ያደባል ፤ በጎቹም ተኩላዎቹ ባሉበት ዓለም ይሠማራሉ፡፡ ለጌታ ያልራሩ ገዳዮች እንዲሁ ለእስጢፋኖስ ስስ አንጀት የላቸውም፡፡ “እስጢፋኖስም ጸጋንና ኃይልን ተሞልቶ በሕዝቡ መካከል ድንቅንና ታላቅ ምልክትን ያደርግ ነበር። … ይናገርበት የነበረውንም ጥበብና መንፈስ ይቃወሙ ዘንድ አልቻሉም።” (ሐዋ.6፥8 ፤ 10) 

     እስጢፋኖስ በተቃዋሚዎቹና በገዳዮቹ ፊት ምስክርነቱን የሰጠው በግልጥ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ምስክርነት በእግዚአብሔር ፊት ለዘወትር ቃሉን በማጥናት ፤ በጸሎትም በመትጋት የሚመጣ ነው፡፡ እስጢፋኖስ የመሰከረው ምስክርነት አይሁድን መልስ ያሳጣና ድንቅ ምስክርነት ነው፡፡ ምስክርነቱን መቃወም ስላልተቻላቸው የሐሰትን ክስ በሚገባ አቀናበሩበት፡፡ (ሐዋ.6፥13-14)
      ሊቀ ካህናቱም ፊት በቀረበ ጊዜ ሳያፍር ፣ ሳይፈራ ለሕዝቡ የተነገረውን የመሲሁን ይመጣልን ከሥሩ ጀምሮ ተረከላቸዋል ፤ ባልተቀበሉትና በገደሉት መሲህ ፊት ለፊት አምጥቶ ገተራቸው፡፡ ፊት ተሟግተው ባላሸነፉት ጊዜ ከተበሳጩት መበሳጨት ይልቅ፥ የአሁኑን ምስክርነት “በሰሙ ጊዜ በልባቸው በጣም ተቈጡ ጥርሳቸውንም አፋጩበት።” (ሐዋ.7፥54) ጠላት በተሸነፊ ጊዜ “የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራል” እንጂ ምንም አቅም የለውም፡፡ በሌላም ሥፍራ ጌታችን “ሥጋንም የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል እንደማይቻላቸው” ተናግሯልና በነፍሳችን ላይ ምንም ሥልጣን የላቸውም፡፡ (ማቴ.10፥28 ፤ 1ጴጥ.5፥9) ግና ጠላት ነፍሳችንን ያገኘ እየመሰለው ሥጋችንን አብዝቶ ያሰቃየዋል፡፡
    እስጢፋኖስ ስለመሲሁ እውነተኛ ምስክርነትን ከሰጠ በኋላ ሹመት ፤ ሽልማት አልገጠመውም፡፡ በቃሉ ተናግሮ የመሰከረውን የመሲሁን መሞትና በክብር ትንሳኤ ተነስቶ በአባቱ ቀኝ በሕያውነት መቆም በሰሙ ጊዜ “በታላቅ ድምፅም እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፈኑ፥ በአንድ ልብ ሆነውም ወደ እርሱ ሮጡ” ፤ (ሐዋ.7፥57-58) ዓለም የአብ አንድያ ልጁን “ከወይኑ አትክልት ውጪ አውጥታ እንደገደለችውና” (ማቴ.21፥39) “ኢየሱስ ደግሞ በገዛ ደሙ ሕዝቡን እንዲቀድስ ከበር ውጭ መከራን ተቀበለ።” ተብሎ እንደተነገረለት እንዲሁ እስጢፋኖስንም “ከከተማም ወደ ውጭ አውጥተው ወገሩት።” (ሐዋ.7፥58)
   እስጢፋኖስ ሲወገር አንድ ጎበዝ የገዳዮችን ልብስ ይጠብቅ ነበር፡፡ ሟቹ እንዲገደል ትዕዛዝ እየሰጠ የገዳዮችን ልብስ ይጠብቃል ፤ እየጠበቀም መወገሩን ያያል፡፡ እስጢፋኖስ በመጨረሻይቱ ሰዓት እንደመሰከረለት መሲህ ኢየሱስ፥ ስለሚወድሩት ጠላቶቹ “ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው” የሚል ቃል ከአንደበቱ ወጣ፡፡  የሚረግምን መባረክ ፣ የሚጠላን መውደድ ፣ ክፉ ለዋለ መልካም ብድራት መመለስ (ማቴ.5፥43 ፤ ሮሜ.12፥20-21) በደሙ ከዳነ አማኝ የሚገኝ የቅድስና ፍሬ ነው፡፡ ክርስቲያን ተብለን ስለተጠራን ብቻ ይህ ፍሬ አይኖረንም ፤ በጸጋው ከዳንን ፍሬውንም ልናፈራ ይገባናል፡፡ የየዋህነትና የብልኀነት መንገድ (ማቴ.10፥16) አሁን ነው መጀመር ያለበት፡፡ ለመመስከር ቀድሞ በልብ ማመን ይገባናልና ከሞትን አይቀር ለጠላት ምህረትን አድርገን እንሙት፡፡
   የእስጢፋኖስ የምልጃ ልመና የገዳይን ልብ ለንስሐ ጠርቷል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ምርጡን ሐዋርያ ጳውሎስን ያገኘችው በእስጢፋኖስ ጸሎት ነው፡፡ ገዳዮችን መሳደብ ፣ መዝለፍ ፣ በከንቱ መራገም አይገባንም ፤ ይልቁን ካራና ስለት ለጨበጠ እጅና ልባቸው ጸሎትና ምልጃ ያሻል፡፡ ምክንያቱም እኛም በክርስቶስ ደም ከሞተ ሥራ ህሊና (ዕብ.9፥14) ዳንን ፣ ከቁጣ ልጅነት ወደጸጋ ልጅነት ተመለስን እንጂ፥ (ኤፌ.2፥3) እኛም የዲያብሎስ ሠራተኞች ነበርንና፡፡(ዮሐ.8፥44) እንኪያስ ላልተገባን ሰዎች ክርስቶስን በማመናችን እንደ“የተገባን” ከተቆጠርን ፤ ላልተገባቸው እኛም ምህረትን ልንለምን ፤ ልንማልድላቸው ይገባል፡፡
    ቤተ ክርስቲያን ለሞቱት ብቻ ሳይሆን ለገዳዮችም እጅግ እጅግ አብዝታ ልትጸልይ ይገባታል፡፡ አምላካችን አመጸኞችን ሲምር ለመታየቱ እኛም ከታላቁ መጽሐፍ ቀጥሎ ሕያው ምስክሮች ነን፡፡ ጳውሎስ የእስጢፋኖስን ቤተሰብ አጥምቋል፡፡(1ቆሮ.1፥16) የእስጢፋኖስ ቤተሰብ እንዴት ያለ ድንቅ ቤተሰብ ነው?! በልጃቸው ገዳይ እጅ አጎንብሰው የተጠመቁት?! ኦ! ክርስትና እንዴት ያለ ድንቅ የምህረት መንገድ ነው!? ኦ! ኢየሱስ ፍቅርህ እንደምን ከህሊና መረዳት በላይ ይሰፋል?!
     ISIS ይህን ድርጊት የሚያደርጉት የሞተላቸውን ጌታ ባለማወቅና ባለማስተዋል ነው፡፡ ክርስቶስን ያላወቀ ሳውል ክርስትናን ይገፋ ፤ ክርስቶስን ያሳድድ የነበረው ልክ አምላኩን እንደሚያገለግል ሰው በመቅናት ነው፡፡ ISISም ይህን የሚያደርጉት አምላካቸውን የሚያገለግሉ እየመሰላቸው ነው፡፡ እንኪያስ! ከእኛ መካከል የመታረዱና የመገደሉ ጽዋ ለማን እንደሚደርስ አዋቂው ጌታ ብቻ ነው! መቼም ይሁን መች ግን እስጢፋኖሳውያን ሆነን ብዙ ሳውሎች ከገዳዮች መካከል እንዲመለሱ የምንጸልይ ስንቶች እንሆን? የጸለዩትስ ስንቶች ይሆኑ?
      አዎን! እንጸልያለን፦ “ጌታ ሆይ፥ በISIS ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ፤ ይቅርም በላቸው”፡፡ ቅዱስ አውግስጢኖስ ይህን እውነት “በእስጢፋኖስ ጸሎት ቤተ ክርስቲያን የጠፋውን ጳውሎስን አገኘች፡፡” በማለት አስቀምጦታል፡፡ አሜን ጌታ ሆይ ይቅር በላቸው ፤ ደግሞም ተመልሰው የስምህ ምስክር እንዲሆኑ እርዳቸው ፤ የጳውሎስ ዕጣ ለእነርሱም ትውጣላቸው፡፡ አሜን፡፡

6 comments:

 1. Amen (I agree with you .)

  ReplyDelete
 2. ለተከበረው ወንድማችን! ክፉ የሚያደርጉ ሁሉ አያውቁምና እግዚአብሔር ይቅር ይበላቸው! እግዚአብሔር ደግሞ እኛ ሁላችን በጥምቀት ወደ እርሱ የተለየን ሁሉ ከዚህ ዓለም አስተሳሰብ የራቅን ስለሆነ በእውነት መንገድ በኢየሱስ ክርስቶስ ቃል የሚመሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ወታደሮች ስለሆኑ ሁልጊዜም ይጠላሉ። መስዋእትነትም ግዴታ ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት በቁጭታ አትመጣም።በዚህም ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አባቱ ከመመለሱ በፊት ለወገኖቹ ለደቀ መዛሙርቶቹ መልካም እንዲሆንላቸው ወደ አባቱ በሚጸልይበት ወቅት "14 እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው።" (ዩሐ. ም17) ይላል። ልብ እናድርግ መጀመሪያ የምናመልከውን አምላክ ካወቅነው እርሱም ያስተማረውን ከተረዳን ሁሉም ነገር እንደ ቅዱሱ እስጢፋኖስ ታሪክ ዓለም የጠላናል። ቅዱስ እስጢፋኖስ ያንን ሁሉ ተጋድሎና መስዋዕት ያደረገው ከእርሱ ጋር ያለው የተቀደሰ መንፈስ ወይም የክርስቶስ ልቦና ስላለው ነው። በዚህም የክብር አክሊልን ወደፊት የእረኞች አለቃ በሚገለጥበት ወቅት አክሊሉን ያገኛል። ምክንያቱም አንድ ወታደር ለሐገሩ እንደሚሞት ሁሉ እርሱም የክርስቶስ ወታደር ስለነበረ የተላቶቹን ስንፍና ያውቅ ነበርና ለጠላቶቹ መልክምን ነገር ተምኝቷል። እንዲሁም በወታደርነቱ ጊዜ ለእርሱ የሚያስፈልገውን ትጥቅና መሳሪያ ነበረው። እኛ ዛሬ ይህ ቅዱስ እስጢፋኖስ የነበረው መሳሪያና ትጥቅ አለን? አዎ ይህ ዛሬ ዓለማችን ላይ የምናየው አስከፊ ነገር ሁሉ ድንገት የመጣ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል ከተረዳነው እንደሚመጣም ይህም ደግሞ የምጥ መጀመሪያ እንደሆነ ያስተምረናል። ስለዚህ ቅዱስ እስጢፋኖስ ያ ሁሉ እንግልት በሚደርስበት ጊዜ በጀግንነት የቆመው በእርሱ ውስጥ የተቀደሰው መንፈስ የሆነ የአምልኩ ቃል በልቦናው ስላለ ምንም አልፈራም። በተመሳሳይ መልኩ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለሚጠብቁ ሁሉ መከራና ሥቃይ የአሕዛብ ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ግዴታ ይኖራል። ለምሳሌ ያህል እግዚአብሔር ለልጁ ለእየሱስ ክርስቶስ ኢየሱስ ክርስቶስም የእርሱን የተቀደሰ መላዕክ ልኮ ለቅዱስ ዩሐንስ ቶሎ ይሆን የሚገባውን ነገር በነገረው መሠረት ወደፊት በኋለኛው ዘመን ይሚሆነውን እንዲህ ብሎ ነግሮታል፡"7 ቅዱሳንንም ይዋጋ ዘንድ ድልም ያደርጋቸው ዘንድ ተሰጠው፥ በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው።8 ከዓለምም ፍጥረት ጀምሮ በታረደው በግ ሕይወት መጽሐፍ ስሞቻቸው ያልተጻፉ በምድር የሚኖሩ ሁሉ ይሰግዱለታል።9 ጆሮ ያለው ቢኖር ይስማ።10 ይማረክ ዘንድ ያለው ማንም ቢኖር ወደ ምርኮነት ይሄዳል፤ በሰይፍ የሚገድል ማንም ቢኖር ራሱ በሰይፍ እንዲገደል ይገባዋል። የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት በዚህ ነው።" (ዩሐ. ራዕይ ም13) ይላል። ስለዚህ ዛሬ ከዚህ የምንማረው እራሳችንን ከዚህ አስከፊ ነገር እንድንወጣ ወደ እግዚአብሔር ዕቅፍ መግባት ያስፈልገናል። በስመ ክርስትና የእግዚአብሔር መንግሥት ስለማይገኝ የግዴታ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅና መኖር ያስፈልገናል። ይህ የምናየው ነገር ሁሉ በእግዚአብሔር ዓይን የተሰወረ አይደለም። እግዚአብሔርም እሥራኤልን ያዕቆብን ቤት ሲገጽስ እንድተናገረው፡
  " 5፤6፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፤ በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ አስታጠቅሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔም ሌላ ማንም የለም።7፤ ብርሃንን ሠራሁ፥ ጨለማውንም ፈጠርሁ፤ ደኅንነትን እሠራለሁ፥ ክፋትንም እፈጥራለሁ፤ እነነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።" (ኢሳ. ም45) ይላል። በዚህም ዛሬም ዋናው ቁም ነገር ይህ ሁሉ ለእኛ ትምህርት ሲሆን በግፍ በክፉዎች ለተገደሉትም ወንድሞቻችን እግዚአብሔር ነፍስ ይማር! ለቤተሰቦቻቸውና ለወገናቸው ለሐገራቸውም መጽናናት ይሁንላቸው! አሜን!
  ወስብሃት ለእግዚአብሔር!

  ReplyDelete
 3. For Anonymous 9:49 so how is Jesus the son of God to be equal with God when in the verse you quoted Isiah 45 clearly says there is no other God. I am trying to understand the word of God. Was Jesus with the Father one God when he create everything. Can anybody explain this for me please.
  GOD BLESS YOU ALL. No religion explanation just explain the word. I mean I believe in one God and what is written in the Bible so please try to answer me by the scripture word.

  ReplyDelete
 4. "For Anonymous 9:49 so how is Jesus the son of God to be equal with God when in the verse you quoted Isiah 45 clearly says there is no other God. I am trying to understand the word of God. Was Jesus with the Father one God when he create everything. Can anybody explain this for me please.
  GOD BLESS YOU ALL. No religion explanation just explain the word. I mean I believe in one God and what is written in the Bible so please try to answer me by the scripture word."
  ለተከበረው ወንድማችን! ጥያቄህ በጣም ጥሩ ጥያቄና ሁላችንም ልንረዳው የሚገባ መብራራት የሚገባው ነው። ጥያቂህን እንደተረዳሁት እግዚአብሔር በቃሉ ለእስራኤል በሚናገርበት ወቅት " 5፤6፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፤" (ኢሳ. ም45) ብሎ ተናግሯል። ይህም ቃል የራሱ ቃል ነው ቃሉም አይለወጥም ወይም ሰዎች እንደፈለጉ ሊተርጉሙት አይችሉም። ነገር ግን ነገሮችን ለመረዳት እንዲቻልህ ከሕጉና ከምስክሩ ጥቂት ከዚህ ጥቂት ከዚያ ሥርዓት በሥርዓት ትእዛዝ በትእዛዝ አድርገን መረዳት ያስፈልገናል። በዚህም መሠረት
  በዚህም መሠረት ከመሰረቱ ስንሄድ በቤተ ክርስትያናችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ የመሰረተ እምነት አስተምህሮ ውስጥ አምስት አእማደ ምስጢርያዊ ትምህርት አለ። ከነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው ምሥጢረ ስላሴ ይባላል። በዚህም ትምህርት መሠረት " በኩነቱ አብን በልብ መሆን ልባዊነት ወልድን በቃል መሆን በነባቢነት መንፈስ ቅዱስን በሕይወት መሆን ሕያውነት መረዳት ማለት ነው ብሎ ያስተምረናል፡፡" በዚህም እግዚአብሔር አስቀድሞ
  "26፤ እግዚአብሔርም አለ። ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፥ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።" (ዘፍ. ም1፡ 26) ብሎ ሲፈጥር እኛን በእርሱ መልክ አድርጎ ፈጥሮናል። እንዲሁም በምሳሌ ሲል ደግሞ እነዚህ አብ (ልብ) ወልድ (ቃል) መንፈስ ቅዱስ (እስትንፋስ) የተባሉትን ሰውነት እግዚአብሔር በሶስት ሰውነት ይዞታል። ነገር ግን በምሳሌው የፈጠረው ሰው እንዚህን በአንድ ሰውነት ይዘናቸዋል። በዚህም አብ በአካላዊ አቋሙና በባሕርዩ ፍልሰት ሳይኖርበት በራሱ እኔነት ልብ በመሆኑ ለእርሱ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስም ልብ ነው። እንዲሁም ወልድ በአካላዊ አቋሙና በባሕርዩ ፍልሰት ሳይኖርበት በራሱ እኔነት ቃል በመሆኑ ለራሱም ለአብና ለመንፈስ ቅዱስም ቃል ነው ቃል ሆኖ ይኖራል ይሠራል። መንፈስ ቅዱስ በአካላዊ አቋሙና በባሕርዩ ፍልሰት ሳይኖርበት በራሱ እኔነት ሕይወት በመሆኑ ለራሱም ለአብና ለወልድም ሕይወት ነው። ብላ ቤተ ክርስትያናችን ታስትምረናለች።
  በዚህም መሠረት እግዚአብሔር ብለን ስንጠራ እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማለታችን ነው። በዚህም እግዚአብሔር (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) " ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን " እንፍጠር ብለው ሲነሱ ይህ ሁሉ ነገር ምንጩ ከልብ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ሕይወት ያለው ሰውም ነገሮችን የምናምነጨው ከልባችን ይሆናል። ከዚያም ወደ ቃል ይለውጣል። ከዚያም ያ ቃል በመንፈስ በሰውነታችን በጆሮአችን በመስረጽ በኃይል ስራውን ይሠራል። በዚህም ቃል ያለ ልብ አይኖርም ልብም ካል ቃል አይኖርም መንፈሱም ካለ ቃል አይኖሩም ሁሉም እኩል ድርሻ አላቸው። በዚህም እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰማይና ምድርን በሚፈጥርበት ጊዜ ሁሉንም በቃል ነው የሠራው። በዚህም ይህ ቃል ደግሞ መንፈስም ነው ይላል። በዚህም በመንፈስ ሁሉንም ነገር ሕይወት ሰጠው። ለዚህም ነው " 7፤ እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ። (ዘፍ. ም2) ብሎ የሚያስተምረን።
  በተጨማሪም ለዚህም ነው ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ (ወልድ ቃል) በምድር ላይ በሚመላለስበት ወቅት ለምሳሌ ያህል፡" 8 ፊልጶስ። ጌታ ሆይ፥ አብን አሳየንና ይበቃናል አለው።9 ኢየሱስም አለው። አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ። አብን አሳየን ትላለህ?10 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ አታምንምን? እኔ የምነግራችሁን ቃል ከራሴ አልናገረውም፤ ነገር ግን በእኔ የሚኖረው አብ እርሱ ሥራውን ይሠራል።" (ዩሐ. ም14) ብሎ የተናገረው። በተጨማሪም ይህንኑ ለመረዳት እንድንችል አሁንም እንደዚሁ ለወገኖቹ እንዳስተማራቸው፡" 22 የአስቆሮቱ ያይደለ ይሁዳ። ጌታ ሆይ፥ ለዓለም ሳይሆን ራስህን ለእኛ ልትገልጥ ያለህ እንዴት ነው? አለው።23 ኢየሱስም መለሰ አለውም። የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።24 የማይወደኝ ቃሌን አይጠብቅም፤ የምትሰሙትም ቃል የላከኝ የአብ ነው እንጂ የእኔ አይደለም።25 ከእናንተ ዘንድ ስኖር ይህን ነግሬአችኋለሁ፤26 አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል።" (ዩሐ. ም14) ይላል።..........ይቀጥላል

  ReplyDelete
 5. በአጭሩ ወልድ አብን አባቴ ይለዋል አብም ወልድን ልጄ ይለዋል። በዚህም አባትና ልጁ እኩል ሥልጣን አላቸው በዚህም ወልድ ለማይታየው እግዚአብሔር አብ ምሳሌ ነው። ሁሉንም ነገር ለልጁ ሰጥቶታል ብሎ መጽሀፉ ያስተምረናል። ለዚህም ነው ። "17 እነሆም፥ ድምፅ ከሰማያት መጥቶ። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ።" (ማቴ. ም3)። እንዲሁም ቅዱስ ጳውሎስ በትምህርት ወቅት እንዳስተማረው፡
  " 6 እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥7 ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥8 በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።9 በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤10 ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥11 መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።" (ፊል. ም2)።
  በዚህም መሠረት በነቢዩ ኢሳያስ ላይ እግዚአብሔር ሲል ሁሉን ለፈጠረው ለክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ክርስቶስ ኢየሱስ ስንል ደግሞ ወልድን ማለታችን ነው። ወልድም የሚያደርገው ሁሉ ከልብ ከሆነው ከአብ ይመነጫል። ወልድም እንዲሁ በመንፈስ ቅዱስ ስራውን ይሠራል። በዚህም ሁሉም ነገር ሕይወት ያለው ይሆናል። በዚህም እግዚአብሔር ይባላል። አባትና ልጅ ተብለው ሲጠሩ አንዱን ከአንዱ ማሳነስ አይደለም ።በዚህም ሶትም አንድም ብለን እናምናለን። ነገር ግን ዛሬ ሁላችን የምናመልከው የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ነው። በዚህም እርሱ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም ይላል። አምላክ ስንል የሚመለክ ማለት ነው። ሲፈጥር ሁላችንንም ፈጥሯል። ነገር ግን የፈጠራቸው ሰዎች ግን በተለያዩ ነግሮች ያመልካሉ። በድንጋይ የሚያመልኩ አሉ በዛፍ የሚያመልኩ አሉ በዚህም እነዚህ በጣኦት የተፈጠርውን የሚያመልኩ ሁሉ ሕይወት የሚሰጠውን ከሞት ወደ ሕይወት የሚያሻግረውን አምላክ አያመልኩም።፡ነገር ግን እኛ ሕያው የሆነውን ሁሉንም ማድረግ የሚችለውን የፈጠረንን ኢየሱስ ክርስቶስን እናመልካለን።፡
  ለዚህም ነው በነቢዩ ኢሳያስ ላይ አድሮ ቃል የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ወይም እግዚአብሔር ወልድ "5፤6፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም ሌላ ማንም የለም፤ ከእኔም በቀር አምላክ የለም፤ በፀሐይ መውጫና በምዕራብ ያሉ ከእኔ በቀር ማንም ሌላ እንደሌለ ያውቁ ዘንድ አስታጠቅሁህ፥ አንተ ግን አላወቅኸኝም፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔም ሌላ ማንም የለም።7፤ ብርሃንን ሠራሁ፥ ጨለማውንም ፈጠርሁ፤ ደኅንነትን እሠራለሁ፥ ክፋትንም እፈጥራለሁ፤ እነነዚህን ሁሉ ያደረግሁ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።" ብሎ የተናገረው።
  ምክንያቱም አህንም የእግዚአብሔር ቃል ወይም መጽሀፍ እንደሚያስተምረን፡" 3-14 እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።15-16 እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው። የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል።17 እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል።18 እርሱም የአካሉ ማለት የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው። እርሱም በሁሉ ፊተኛ ይሆን ዘንድ፥ መጀመሪያ ከሙታንም በኵር ነው። " (ቆላ. ም1) ይላል።
  በዚህም ትንሽ ለማብራራት ሞክርያለሁ በተጨማሪም የእግዚአብሔርን ቃል ሁልጊዜ ብንማረው ብንሰማው ቃሉ ቀስ በቀስ ይገባናል። አምሰግናለሁ!
  ወስብሃት ለእግዚአብሔር!

  ReplyDelete
 6. እግዚአብሔር አምላክ ልብ ይስጣቹ

  ReplyDelete