Friday, May 29, 2015

ስደተኛው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፡- በዓመት አንድ ቀን ብቻ የሚዘከረው መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያናችን ስፍራው ወዴየት ይሆን?! ክፍል -፩በዲ/ን ኒቆዲሞስ
የዛሬ ወር ገደማ በብትሕውና ሕይወት እየኖሩ ያሉ አንድ አባት ቤታቸው ብቅ ብዬ ጠበል እንድቀመስ ስልክ ደወሉልኝ፡፡ ለወትሮው በቤታቸው የሥላሴን፣ የመድኃኔ ዓለምንና የእመቤታችንን ዝክር በመዘከር ድሆችን ጠርተው እንደሚያበሉ ስለማውቅ የእዚህ ቀን የጠበል ቅመስ ጥሪያቸው ከእነዚህ በውል ከማውቃቸው ቀናቶች የተለየ ቀን በመሆኑ በጥቂቱ ግራ አጋባኝ፡፡ እናም አባ ዛሬ ዕለቱ ዐሥራ አንድ ነው፣ ቅዱስ ያሬድን ወይም ቅድስት ሐናን መዘከር ጀመሩ እንዴ ስል ጠየኳቸው፡፡
እኚህ መናኝ አባትም በምላሻቸው አይ ቅዱስ ያሬድን ወይም ቅድስት ሐናን ለመዘከር አይደለም፡፡ እንግዲያውስ አባ ምንን አስመልክተው ነው አልኳቸው፤ እርሳቸውም ወር በገባ በ፲፩ ዕለቱን ለመዘከር የወሰኑበትን ምክንያታቸውን እንዲህ ሲሉ በመንፈሳዊ ቅናት እየተቃጠሉ አብራሩልኝ፡፡
አየህ ወንድሜ በቤተ ክርስቲያናችን ለእግዚአብሔር አብ፣ ለእግዚአብሔር ወልድ፣ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም፣ ለቅዱሳን መላእክት፣ ለጻድቃንና ለሰማዕታት ለእነዚህ ኹሉ ወርኻዊና ዓመታዊ የመታሰቢያ በዓል አላቸው፡፡ የሚገርመው ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ግን በዓመት አንድ ጊዜ በዓለ ፕራቅሊጦስ/በዓለ ኀምሳ በሚል ከምናከብረው ውጪ ወርኻዊ የመታሰቢያ በዓል የለውም፡፡

ስለሆነም እኔ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ወር በገባ ኹሌም በየወሩ በ፲፩ ለማክበር የዛሬውን ዕለት ለመንፈስ ቅዱስ የመታሰቢያ ዕለት እንዲሆን በማሰብ በዓሉን ለማክበር ዛሬን አሐዱ ብዬ ጀምሬያለኹ፡፡ እናም በዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ወርኻዊ የመታሰቢያ በዓል ዝክር ላይ እንድገኝና ሌሎች መንፈሳዊ ጓደኞቼንም ጭምር እንድጋብዝ አደራ አሉኝ፡፡ አስከትለውም ከቀናቶች መካከል ፲፩ን ለመንፈስ ቅዱስ ወርኻዊ መታሰቢያ በዓል እንዲሆን የመረጡበትንና የወሰኑበትን ምክንያታቸውንም ከወንጌል ቃል በማጣቀስ እንዲህ ሲሉ አብራሩልኝ፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ግብር በሥጋ መወለዱን ኦርቶዶክሳውያን ኹሉ እናምናለን፡፡ ልደቱንም በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በደስታና በሐሴት እናከብራለን፡፡ ከልደቱ በኋላም ጌታችን የነቢያትን ትንቢት ለመፈጸም፣ አንድም ለእኛ አርዓያ/ምሳሌ ሊሆነን ተጠምቋል፤ በሌላም በኩል ለድነታችን የጥምቀትን ሥርዓት ሠርቶልናል፡፡ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የሰኞ ዕለት ውዳሴው፡-
‹‹በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ኹሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለ ሰው ፍቅር ወደዚህ ዓለም የመጣህ ፍጥረት ኹሉ በመምጣትህ ደስ አለው፡፡ አዳምን ከስሕተት አድነኸዋልና ሔዋንንም ከሞት ፃዕረኝነት ነፃ አድርገኻታልና የምንወልድበትን መንፈስ ረቂቁን ልደት ሰጠኸን…፡፡›› ብሎ እንዳመሰገነ፡፡

Tuesday, May 26, 2015

ስብከተ ወንጌልና ተግዳሮቶቹ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

በምድር ላይ ላለችው ተዋጊዋ ቤተክርሰቲያን ስብከተ ወንጌል ዋና ተልእኮዋ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የምትሰብከው ወንጌልን ነው፡፡ ወንጌልን የምትሰብከውም ሰዎች በሃይማኖት ውስጥ ሲኖሩ በታሪክ የሚያውቁትን ነገር ግን በሕይወታቸው የራሳቸው ያላደረጉትን የክርስቶስን አዳኝነት ገንዘብ እንዲያደርጉትና በበጎ ምግባር ጸንተው መዳናቸውን እየፈጸሙ እንዲኖሩና የዘላለማዊ ሕይወት ባለቤቶች እንዲሆኑ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን እንደ ቤተክርስቲያን መቀጠል የምትችለውም ወንጌል ሲሰበክባትና ሰዎች በክርስቶስ አዳኝነት አምነው የዘለላለም ሕይወት ባለቤቶች ሲሆኑ ነው፡፡
ስብከተ ወንጌል ዋና ስለመሆኑ ከፓትርያርኩ አንስቶ ብዙዎች ይናገራሉ፤ ይጽፋሉ፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ሆነው ከተመረጡ በኋላ ከዜና ቤተ ክርስቲያን መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ አንዱ የተነሣው የስብከተ ወንጌል ጉዳይ ነው፡፡
ዜና ቤተክርስቲያን “ከቤተክርስቲያናችን ቁልፍ ሥራዎች አንዱ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴው የሚፈለገውን ያህል አይደለም፡፡ ይህን የቤተክርስቲያንዋ ቀዳሚ  ሥራ የሆነውን ተልእኮ ለማጠናከር ቤተ ክርስታየኒቱ ምን ማድረግ አለባት?” ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ ፓትርያርኩ ሲመልሱ እንዲህ ብለዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርክ፡-“እንደኔ እምነት ቤተክርስቲያን ትልቁን በጀት መመደብ ያለባት ለስብከተ ወንጌል ሥራ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ቤተ ክርስቲያናችን ከሁሉ አኀት አብያተ ክርስቲያናት የበለጠ ተከታይ ምእመን አሏት፡፡ በቅድሚያ ያሉንን ምእመናን በእምነታቸው፣ በዕውቀታቸው እንዲጠነክሩ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ያላመኑትን ለማስተማር፣ ወጣቱን ትውልድ  በሚገባ ለመያዝ የተጠናከረ የስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ወደ ተግባር ለመለወጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ በአጠቃላይ መምሪያው በሠለጠነ የሰው ኃይልና በበጀት ሊጠናከር ይገበዋል፡፡”(ዜና ቤተክርስቲያን መጽሔት ሚያዝያ 2005 ገጽ 9)፡፡

Thursday, May 21, 2015

ኢትዮጵያ ውስጥ የተዳፈነ አክራሪነት አለ!ምንጭ፡- ደጀ ብርሃን
ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያ ውስጥ በእምነት ተከባብሮ የመኖር የቆየውን ልምድ በተቃራኒው የሚፈታና የሚመለከት የፍጅት፤ የእልቂት፤ የሁከትና ኢስላማዊ መንግሥት የማቋቋም የተዳፈነ አክራሪ ኃይል አለ። ይህንን ጉዳይ ጠበቅ አድርገን መናገራችን እርስ በእርስ አለመተማመንን እንዲኖር ሳይሆን በመሬት ያለውን እውነታ ደብቀን «የኢስላሚክ ስቴት ሽብርተኛ ቡድን እኛን አይወክለንም» የሚለው ወቅታዊ መፈክር የችግሩን አደገኛነት ስለማይለገልጽ ላይ ላዩን ማውራቱ ለአብሪነት በቂ መልስ መሆን ስለማይችል ብቻ ነው። በተለይ መንግሥት ከቀበሌ አንስቶ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሕዝቡን እያወያየ ያለውን የአክራሪ ኃይል በተለይም ወጣቱን በማሳተፍ ስር ነቀል መፍትሄ ካልሰጠበት ውሎ አድሮ አደጋውን መቀልበስ ከማይቻልበት መድረሱ አይቀርም። ይህንን ሐቅ ከሚያረጋግጡልን ማስረጃዎች አንዱ «ጀማል ሀሰን አሊ ይመር» የተባለ ከሙስሊም ቤተሰብ የተገኘ ኦርቶዶክሳዊ፤ በሙስሊም ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ መካከል ያለውን ችግር ከተወለደበት መንደር ባሻገር እየተከሰተ ያለውን የአክራሪነት አደጋ በዓይን ምስክርነት እንዲህ ያወጋናል።

 
ሦስት መልዕክቶች አሉኝ!
መልዕክቶቹም ክርስቲያኑንና ሙስሊሙን ኅብረተሰብ እና መንግሥትን ይመለከታሉ፡፡
መልዕክት አንድ-ለሙስሊም ወገኖቻችን፡-በፎቶው ላይ በቀኝ በኩል ያለው የሥጋ ወንድሜ "አህመድ ሀሰን" ሲሆን በግራ በኩል ያለሁት ደግሞ እኔ ጀማል ሀሰን ነኝ፡፡ ነገር ግን ስመ ጥምቀቴ ገብረ ሥላሴ ነው፡፡ ሁለቱ ሴቶች ደግሞ ወላጅ እናቴና አኅቴ ሲሆኑ ከእኔ ጋር በልጅነት የተነሳው ነው፡፡ ሙስሊም የሆነው የሥጋ ወንድሜ አህመድ ከደቡብ ወሎ ወደ አዲስ አበባ እኔን ክርስቲያን ወንድሙን ሊጠይቀኝ መጥቶ 3 ሳምንት እኔ ጋር ከርሞ ከሄደ ዛሬ ገና 8 ቀኑ ነው፡፡
ጁምዓ ጁምዓ አህመድን አንዋር መስጊጂድ አድርሼው እኔ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን እገባ ነበር፡፡ የሙስሊም ሥጋ ቤት ሄደን ገዝተን እቤት ሄደን እኔው ራሴ ሠርቼ አህመድ ሲመገብ ነው የቆየው፡፡ እኔ ደግሞ አባቴን ሀሰን ዓሊንና ሌላውንም ሙስሊም ቤተሰቤን ልጠይቅ ወሎ ስሄድ ለብቻዬ በግ ያርዱልኛል፡፡ በአጠቃላይ ከእኔም ቤተሰብ አልፎ ወሎ ስሄድ የማየው የክርስቲያኑና የሙስሊሙ ፍቅርና ተቻችሎ መኖር እንዴት ያስቀናል መሰላችሁ!!! ቤተ ክርስቲያን ሲሠራ ሙስሊሞቹ በገንዘብም በጉልበትም ሲረዱ በዓይኔ ተመልክቻለሁ፡፡ መስጂድም ሲሠራ ሕዝበ ክርስቲያኑ አብሮ ከሙስሊሞች ጋር ሠርቷል፡፡