Sunday, May 3, 2015

“ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል፡፡” (ምሳ. 28፥13)

Read in PDF


ሰው ትእዛዘ እግዚአብሔርን አፍርሶ በኀጢአት ከወደቀ በኋላ ደካማ ስለሆነ ከበደልና ከስሕተት ፈጽሞ ነጻ ሊሆን አይችልም፡፡ አንዳንዱ ሰው በመርሕ ደረጃ በዚህ የሚስማማ ቢመስልም በተግባር ግን ይህን እውነታ ለመቀበል ብዙ ጊዜ ሲቸገር ይታያል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እንደ ምሳሌና መሪ አድርጎ የሚያያቸውን ሰዎች ምንም እንከን የማይገኝባቸውና ፈጽሞ የማይሳሳቱ አድርጎ ስለሚመለከታቸው ነው፡፡ ሲሳሳቱና ስሕተታቸው ሲገለጥ እንኳ መሳሳታቸውን ወይም መውደቃቸውን ከመቀበል ይልቅ አልተሳሳቱም፣ ሌሎች ስማቸውን በሐሰት እያጠፉ ነው ብሎ ቢያስተባብል ይቀለዋል፡፡ በሌሎች እንደምሳሌና መሪ የሚታዩት አንዳንዶችም ለክብራቸው ስለሚጨነቁ ራሳቸውን ፍጹምና የማይሳሳት አድርገው ነውና የሚመለከቱት አንዳንድ ጊዜ ስሕተት ሲፈጽሙ፣ ስሕተታቸውን ከመቀበል ይልቅ ኅሊናቸውን ሸጠው ስሕተታቸውን ለመሸፈንና የማይሳሳቱ አድርገው በቆጠሯቸው ሰዎች ዘንድ ራሳቸውን እንከን የለሽ አድርገው ለማቅረብ ሲተጉ ነው የምናስተውለው፡፡ ይህ ግን በእውነት ደካማነት ነው፡፡ ሰው ማለት የማይሳሳት ሳይሆን መሳሳቱ በታወቀው ወይም በተነገረው ጊዜ “ተሳስቻለሁ” የሚልና ስሕተቱን ለማረም ዝግጁ የሚሆን ነው፡፡
ከሳምንታት በፊት የፕሮቴስታንቶች ዘማሪ የሆነው ተከሥተ በኀጢአት መውደቁን የሰሙ ብዙዎች አዝነውና አፍረው ነበር፡፡ በርግጥም ነገሩ ለሰሚው የሚያሳዝንና በተለይም ፕሮቴስታንቶቹን አንገት ያስደፋ ክሥተት ነበር፡፡ በአባ ሰላማ ብሎግም ይህን በአንዳንድ ሚዲያ ይፋ የተደረገውን የውድቀት ወሬ ግለሰቡ ንስሓ እንዲገባበትና ሌሎችም እንዲማሩበት በማሰብ ወጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁንና የውድቀቱን ያህል ባይወራለትም ተከሥተ ኀጢአቱን አምኖ ንስሓ መግባቱና የበደላቸውን ሁሉ ይቅርታ መጠየቁ ተሰምቷል፡፡ ይህም አስቀድሞ ተፈጥሮ የነበረውን ያን መጥፎ ስሜት ሊለውጥ የሚችል ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ ጉዳዩን የሰማና የታዘበ ሁሉ ሊያስብ የሚችለው በኀጢአት ስለወደቀው ተከሥተ ሳይሆን በንስሓ ስለተነሣው ተከሥተ ነው፤ መሆን ያለበትም ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ፣ “ኀጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል፡፡” ሲል ኀጢአቱን በመሰወር ፈንታ በኀጢአቱ የተናዘዘና ያን ኀጢአቱን የተወ ሰው ምሕረትን ከእግዚአብሔር እንደሚቀበል ይመሰክራልና፤ ክርስቲያንም በንስሓ የተመለሰውን ሰው እግዚአብሔር በሚያየው በዚህ መንገድ መመልከት ይገባዋል እንጂ ያለፈውን እያሰበ ወደኋላ መመለስ የለበትም፡፡

እግዚአብሔር “እንደ ልቤ የሆነ ሰው” ብሎ የመሰከረለት ዳዊት በአንድ ወቅት የኦርዮን ሚስት ቤርሳቤሕን ወስዶ አብሯት ከተኛ በኋላ ስታረግዝበት ይህን ኀጢአቱን ለመሸፈን ሲል ወደጦርነት ወጥቶ የነበረውን ባሏን ኦርዮን አስጠርቶ ወደሚስቱ ገብቶ እንዲተኛና የተረገዘው ፅንስ የእርሱ ሆኖ እንዲቆጠር ለማድረግ የራሱን “ኀጢአትን የመሸፈን ጥበብ” ተጠቅሞ ነበር፡፡ ኦርዮ ግን ነገሩን ዐውቆ ሳይሆን በቅንነትና ከኅሊናው አንጻር የእስራኤል ሰራዊት በጦርነት ላይ እዱር እያደረ እኔ ወደ ሚስቴ አልገባም ብሎ ድርቅ አለ፡፡ በሚቀጥለው ቀን እንዲበላና እንዲጠጣ ፈቃደ ሥጋውም እንዲነሣሣ ለማድረግ ተሞከረ፤ አሁንም ኦርዮ በአቋሙ ጸና፡፡  ዳዊት በዚህ መንገድ ኀጢአቱን ለመሸፈን የተጠቀመው የእርሱ ጥበብ እንዳልሠራ ባየ ጊዜ፣ የመጨረሻ ያለውን ጥበብ ኦርዮንን ማስገደልን እንደ መፍትሔ ወሰደ፡፡ ምንም ያልበደለው ኦርዮ የተፋፋመ ጦርነት ባለበት ግንባር ላይ እንዲሰለፍና ሕይወቱ እንዲያልፍ የሚያዘውንና የሚገደልበትን ንጉሣዊ ደብዳቤ ይዞ እንዲሄድ አደረገና በዚህ መንገድ ተገደለ፡፡ በጣም የሚያሳዝን ታሪክ ነው፡፡ ሰው ስሕተቱን ከማመን ይልቅ ለመሸፈንና ክብሩን ለመጠበቅ ሲል ምን ያህል ሊጓዝና ከአንዱ ኀጢአት ወደሌላው ኀጢአት ሊሸጋገር እንደሚችል ይህ የዳዊት መጥፎ ታሪክ ያሳየናል፡፡
ዳዊት ለምን እንዲህ አደረገ? ቢባል ኀጢአቱን ለመሸፈንና በኀጢአት የተዋረደ “ክብሩን” ለመጠበቅ ነው፡፡ ኀጢአቱን ለመሸፈን የሞከረው ግን ጽድቅን በመሥራት ሳይሆን ሌላ ኀጢአት በማድረግ ነው፡፡ ከንስሓ ውጪ ኀጢአት  በተሳሳተ መንገድ ሊሸፈን የሚችለው ሌላ ኀጢአትን በመሥራት ብቻ ነውና፡፡ ዳዊትም ያደረገው ይህንኑ ነው፤ ኦርዮን አስጠርቶ ወደ ሚስቱ እንዲገባ ገፋፋው፤ አልሆን ቢለው እንዲገደል አደረገ፡፡ ዳዊት ኀጢአቱን ለመሸፈን የሞከረው “አትግደል” የሚለውን ሕገ አምላክ ጥሶ የመግደል ኀጢአትን በመሥራት ነው፡፡ ዳዊት ኀጢአቱ እስከሚገለጽ ድረስ ጻድቅ መስሎ ነበር የተቀመጠው፡፡ ነቢዩ ናታን መጥቶ በጥበብ ቃል ሀብታሙ በድኻው ላይ የፈጸመውን አሳዛኝ ድርጊት ሲነግረው፣ ዳዊት “በዚህ ጉዳይ ላይ ፍርድ ለመስጠት ሞራል የለኝም” ከማለት ይልቅ ፈራጅ ሆኖ ስለ አንዲቱ ፈንታ አራት ዕጥፍ ይክፈል ሲል በየነ (2ሳሙ. 12፥1-6)፡፡ ሰው ኀጢአት ሠርቶ ኀጢአቱ ካልተገለጠበት ስለ ኀጢአቱ ንስሓ ከመግባት ይልቅ፣ ጻድቅ መስሎ በሌላው ላይ ፈራጅ አድርጎ ራሱን ሊሠይም ይችላል፡፡ ወይም ምንም እንዳልተፈጠረ ቆጥሮ የቀድሞ አገልግሎቱን ሊቀጥል ይችላል፡፡
ይሁን እንጂ ዳዊት ፍርዱን ከሰጠ በኋላ ነቢዩ ናታን፥ ያ ሰው አንተ ነህ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፥ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፤ የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር።አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ?አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፥ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል። ስለዚህም አቃልለኸኛልና፥ የኬጢያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘላለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም።እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ከቤትህ ክፉ ነገር አስነሣብሃለሁ ሚስቶችህንም በዓይንህ ፊት እወስዳለሁ፥ ለዘመድህም እሰጣቸዋለሁ፥ በዚህችም ፀሐይ ዓይን ፊት ከሚስቶችህ ጋር ይተኛል።አንተ ይህን በስውር አድርገኸዋል እኔ ግን ይህን በእስራኤል ሁሉ ፊትና በፀሐይ ፊት አደርገዋለሁ።” (2ሳሙ. 12፥7-11) አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ዳዊት የሰወረውን ኀጢአት እግዚአብሔር እንደገለጠው ዐውቆ ሌላ ምክንያት ከመስጠትና ከመከራከር ይልቅ ኀጢአቱን አምኖ “እግዚአብሔርን በድያለሁ አለው። ናታንም ዳዊትን፦ እግዚአብሔር ደግሞ ኃጢአትህን አርቆልሃል አትሞትም።” (ቊጥር 13)፡፡ ዳዊት የሠራው ኀጢአት ትልቅ ቢሆንም ኀጢአት ሠርተሃል ሲባል አልሠራሁም ብሎ በመከራከር ራሱን ጻድቅ አድርጎ ለማቅረብም ሆነ ለመከራከር፣ ወይም ሌላ ኀጢአቱን ለመሸፈን የሚረዳውን ጥበብ ለመጠቀም፣ ወይም ከውድቀቱ እንዲነሣ ሊረዳው የመጣውን ነቢዩ ናታንን “ስሜን አጠፋ” በሚል እርሱ ላይ ሊያላክክ አልሞከረም፤ ከዚህ በላይ ርቆ መሄድ ብዙ ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ከባድ መዘዝ አለውና “እግዚአብሔርን በድያለሁ” ሲል ኀጢአተኛነቱን በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ሆኖ አመነ፣ ተናዘዘም፡፡ ዳዊትን እግዚአብሔር እንደ ልቤ የሆነ ሰው ያለበት አንዱ ምክንያት ይህ አስቀድሞ አይቶ ሊሆን ይችላል፡፡ በእውነትም ሰው ማለት የማይሳሳት ሳይሆን መሳሳቱ በታወቀው ወይም በተነገረው ጊዜ “ተሳስቻለሁ” የሚልና ስሕተቱን ለማረም ዝግጁ የሆነው ነው፡፡
ዳዊት በዚህ ክፍል በዐጭሩ “እግዚአብሔርን በድያለሁ” ብሎ ኀጢአተኛነቱን አምኖ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ኀጢአቱ ጋር በተያያዘ ንስሓ መግባቱን የእግዚአብሔርን ምሕረት መለመኑንና ንስሓ ለመግባቱ የሚያሳየውን ፍሬ የገለጸበትን መዝሙር በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ እንዲካተት አድርጓል፡፡ መዝሙር 50/51 የሚናገረው ስለዚህ ጉዳይ ነው፡፡ ለመዝሙሩ የተሰጠው ርእስም “ለመዘምራን አለቃ ወደ ቤርሳቤሕ ከገባ በኋላ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ የዳዊት መዝሙር” የሚል ነው፡፡ ከቁጥር 1-9 ድረስ ባለው ክፍል ውስጥ ዳዊት የእግዚአብሔርን ምሕረትና ቸርነት ሲለምን፣  በሠራው ኀጢአት የበደለው እግዚአብሔርን መሆኑን፣ ለሠራው ኀጢአት መነሻው ሰው በመሆኑ በኀጢአት የተበከለ ማንነትን ወርሶ የተወለደ መሆኑን ሲገልጽ፣ እግዚአብሔር ከኀጢአቱ እንዲያጥበውና እንዲያነጻው፣ እግዚአብሔር ይህን ካደረገለትም እንደሚነጻና ሐዘኑ ወደ ደስታ እንደሚለወጥ፣ ወዘተ. ይናገራል፡፡
በንስሓ የመመለሱ ፍሬም በታደሰ ሕይወት መገኘትና ሰዎች እንደርሱ ያለ ኀጢአት እንዳይሠሩ “ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፤ ኀጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ” ሲል መስክሯል (ቊጥር 13)፡፡ አክሎም እግዚአብሔር ከደም እንዲያድነው ይማጸናል፡፡ በመጨረሻም ስለ ሰጠው ምሕረትና ስላደረገለት ቸርነት ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕትን ያቀርባል፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ ዳዊት እውነተኛ ንስሓ እንደገባ በግልጽ ማየት እንችላለን፡፡ እውነተኛ ንስሓ፣ ንስሓ ገብቻለሁ ብሎ በመናገርና ሌሎችም ይህን እንዲያስወሩልን በማድረግ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ እውነተኛ ንስሓ የሚታይ ፍሬ አለው፡፡ ይህም ፍሬ በታደሰ ሕይወት መመላለስና ያን ኀጢአት ደግሞ አለመሥራትን፣ በዚያ መንገድ ለሚገኙ ኀጢአተኞችም የእውነትን መንገድ በማሳየት ኀላፊነትን መወጣትን ያጠቃልላል፡፡ ዳዊት ይህን እንዳደረገ ግልጽ ነው፡፡           
መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “በምድር ላይ መልካምን የሚሠራ ኀጢአትንም የማያደርግ ጻድቅ አይገኝምና።” ይላል (መክ. 7፥20)፡፡ እንዲሁም፥ “የማይበድል ሰው የለምና” ይላል (2ዜና. 6፥36)፡፡ በሐዲስ ኪዳንም፥ “ጻድቅ የለም አንድ ስንኳ … ሁሉ ኀጢአትን ሥርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋልና” ተብሎ ተጽፏል (ሮሜ 3፥11፡23)፡፡ እነዚህ ጥቅሶች ስለ ሰው የሚነግሩን እውነት፣ ሰው ኀጢአተኛ በመሆኑ ፍጹም ሊሆን እንደማይችልና ከስሕተት ነጻ እንዳልሆነ ነው፡፡ እዚህ ላይ ቁም ነገሩ ክርስቲያን ይልቁንም አገልጋይ፣ ሰው ስለሆነ ኀጢአት እንደሚሠራ ሊካድ የማይቻል እውነት መሆኑ ነው፡፡ አገልጋይ ስለሆንኩ ሰዎች ይህን ቢሰሙ ይሰናከሉብኛል፣ ከዚህ በኋላ ዓይንህ ላፈር ይሉኛል ብሎ ማሰብ በራሱ ትልቅ ወጥመድ ነው፡፡ ይህ ለራስ ክብርና ሰዎችን ደስ ለማሰኘት የሚደረግ ኀጢአትን የመሸፋፈን ሥጋዊ ጥበብ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ኀጢአታችን እስኪገለጥ ድረስ ተሸፋፍነን ልንቀጥል እንችላለን፡፡ ጽዋው ሞልቶ ኀጢአታችን ሲገለጥም ይህንኑ ጥበብ ለመጠቀም መሞከር ግን እጅግ አደገኛ ነው፡፡ እግዚአብሔር የገለጠውን ከቶ በምን መሸፈን ይቻላል? በምንም! ስለዚህ እግዚአብሔር የሚሰጠንን የንስሓ ዕድል ለመጠቀም መጨከንና ሕይወትን ማስተካከል ይገባል፡፡      
ከላይ ለመግለጽ እንደ ተሞከረው ኀጢአት በንስሓ ካልተወገደ ሊሸፈን የሚችለው ኀጢአትን በመሥራት ብቻ ነው፡፡ ኀጢአቱን ለማመንና ንስሓ ለመግባት ያልፈለገ ሰው ኀጢአቱን ለመሸፈን የሚያደርገው አንዱ ነገር መዋሸት ነው፡፡ “የተባለውን ኀጢአት እኔ አላደረግሁትም” ይላል፡፡ ይህም መሸፈኛ አልበቃ ሲለው፣ “ይህን ኀጢአት እኔ አላደረግሁም፣ ሌሎች ስሜን ሲያጠፉት ነው እንዲህ እያሉ የሚያስወሩት” በማለት በሌሎች ላይ የሐሰት ምስክርነት ይሰጣል፡፡ ካልሆነ ደግሞ በኀጢአቱ ምክንያት እየከፈለ ያለውን ዋጋ በክርስቶስ ወንጌል ምክንያት እንደሚቀበለው መከራ ተደርጎ እንዲታይለት ነገሩን መንፈሳዊ ጭንብል ያጠልቅለታል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን መከራ ሁሉ የሚመጣብን በጽድቅ ምክንያት ብቻ ሳይሆን በኀጢአትም ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይናገራል፡፡ “ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።” (1ጴጥ. 4፥15-16)፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን በመሆናችን ምክንያት የምንቀበለውን መከራ በኀጢአታችን ምክንያት ከምንቀበለው መከራ ጋር ማምታታትና ጻዽቅ መስሎ ለመታየት መሞከር አሁንም ሌላ ኀጢአት ነው፡፡
አንዳንድ እንደ ምሳሌ መምህርና መሪ ተደርገው የሚታዩና በብዙዎች ልብ ስፍራ ያገኙ ሰዎች በዚህ ብሎግና በሌሎችም ሚዲያዎች ኀጢአታቸው በመረጃ ተገልጦ ንስሐ እንዲገቡ ጥሪ ሲደረግላቸው አንብበናል፡፡ ስለነዚህ ሰዎች በተገለጠ ችግራቸው በስውር በጓዳቸው ንስሐ እንዲገቡ እግዚአብሔር በልዩ ልዩ መንገድ ቢናገራቸውም መመለስን ስላልወደዱ ግለሰቦችን ሲጎዱና “የንስሐ ግቡ” ጥሪ ያቀረቡላቸውን ሰዎች ስም በማጥፋትና በማሳደድ ዳዊት በኦርዮ ላይ እንዳደረገው የማስገደል ያህል እርምጃ ሲወስዱ ሰንብተው በጓዳቸው ንስሐ እንዲገቡ እንዲታረሙ የተሰጣቸውን እድል ባለመጠቀማቸው ኀጢአታቸው ወደ አደባባይ ሲወጣና ለሁሉ ግልጥ ሲሆን፣ ንስሓ ከመግባትና ከኀጢአታቸው ከመመለስ ይልቅ በሰው ፊት “ክብራቸውን” ለመጠበቅ በእግዚአብሔር ፊት ከፍተኛ ቅጣት ወደሚያመጣና ክብራቸውን ወደሚያጎድል ኀጢአት ሲፋጠኑ ይታያል፡፡ እንዲያውም ጻድቃን መስለው በሰዎች ፊት በተለይ ክርስቶስን ሳይሆን እነርሱን በሚሰሟቸውና በሚከተሏቸው ሰዎች ፊት ንጹሕ ነኝ ብለው ለመታየት በሚያደርጉት ጥረት ስለወንጌል ስለክርስትናና ስለክርስቶስ መከራ የሚቀበሉ በማስመሰል “መታገሥ ነው” “ስለስሙ መከራ ልንቀበልም ተጠርተናል” “እግዚአብሔር ስማችንን በከንቱ የሚያጠፉትን እንዲምራቸው መጸለይ ነው” ወዘተ በማለት መድረኮቻቸውን በማስመሰል ሥራ አጨናንቀውታል፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ግን ስለእነዚህ ሰዎች “ኀጢአት አድርጋችሁ ስትጎሰሙ ብትታገሱ ምን ክብር አለበት? ነገር ግን መልካም አድርጋችሁ መከራን ስትቀበሉ ብትታገሱ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ዘንድ ምስጋና ይገባዋል፡፡” (1ጴጥ. 2፥20) ይላቸዋል፡፡ በኀጢአታቸው ምክንያት የተሰጣቸውን ተመለሱ የሚል የንስሓ ጥሪን ስለጽድቅ ስማቸው እየጠፋ እንደሆነ ለማስመለስ የሚያደርጉት የማታለልና የብልጣ ብልጥነት ሥራ ለጊዜው እንጂ ለዘለቄታው የማያዋጣ መሆኑን ከንጉሥ ዳዊት የውድቀት ታሪክ ተምረናል፡፡
እንደእነዚህ ያሉ ሰዎች በማስመሰል ብቻ ሳይቆጠቡ ኀጢአታቸውን የሚያውቁባቸውን ሰዎች ሲያገኙ ንስሓ እንደገቡ ለመናገር ይሞክራሉ፡፡ እንደምናውቀው ንስሓ አፋዊ አይደለም፣ ወይም ንስሓ ገብቻለሁ በሚል ንግግር ብቻ የሚገለጥ አይደለም፣ የራሱ የሆነ ፍሬ አለው፡፡ ፍሬ የሌለውን ንስሓ ገብተናል የሚሉ አንዳንዶች በሌላ አቅጣጫ እውነተኛ ንስሓ እንዲገቡ የተናገሯቸውን ሰዎች ለመበቀል ቀንና ሌሊት ይደክማሉ፡፡ የሚበቀሉበትን መንገድ ተግተው ይፈልጋሉ፣ ሰዎችን በገንዘብ ጭምር ገዝተው የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ሁሉ ይሞክራሉ፡፡ ይህ ሁሉ በመንፈሳዊ ካባ ውስጥ ተደብቀው ስለሚያደርጉት የአንዳንዶች ኀጢአት እጅግ የከፋና በእግዚአብሔር ቃል የተወገዘ ቢሆንም እንኳን የሚያታልሏቸውንና የሚያስከትሏቸውን ሰዎች ዛሬም አላጡም፡፡ 
ለእንደዚህ ዓይነት ኀጢአተኝነታቸው በግልጽ ለታወቀባቸውና ንስሓ እንዲገቡ ጥሪ ለተደረገላቸውና እንቢ ላሉ አገልጋዮች ያለን መልእክት ዛሬም አልመሸባችሁም፣ ፈጥናችሁ ወደሚምራችሁ አምላክ ተመለሱና ከኀጢአት እስራት የተፈታችሁ ንጹሓን ሁኑ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚል “እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” ካልሆነ ግን ነገ መከላከል እንኳን በማትችሉበት ሁኔታ የእግዚአብሔር ፍርድ ይመጣል፣ ለብዙዎችም ድንጋጤና ለጌታም ስም የበለጠ መሰደብ ምክንያት ትሆናላችሁ የሚል ሲሆን፣ እነዚህን በኀጢአትና በዐመፃ የተጨማለቁና የተሰጣቸውን የንስሓ እድል ላቃለሉ ሰዎች አለኝታ እሆናለሁ ብላችሁ ከኀጢአተኞች ጋር ወግናችሁ ዐመፃቸውን እንዲገፉበት የምትተጉ ወደልባችሁ ተመለሱ፣ ዐይናችህንም ከሰው ላይ አንሡ፣ ምንም እንከን የሌለበትን ክርስቶስን ተመልከቱ፣ እርሱን የተከተሉቱ ለዘላለም አያፍሩምና እልከኛ አትሁኑ፣ የምትከተሉት ሰው “የተያዘበትን የኀጢአት ሥራ ሲፈጽም ባየው እንኳን ከእርሱ አልለይም” እያላችሁ በከንቱ ከእግዚአብሔር ጋር አትጣሉ፣ ክርስቶስ ይሻላችኋል እንላለን፡፡

4 comments:

 1. gena erer telalachehu enante mekegnoch. yewengel enkefatochena seyetanoch nachehu.

  ReplyDelete
  Replies
  1. ስማ ማንን ነው የሰደብከው? እንደ እኔ ግምት ራስህን ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም የእውነተኛ ንስሀን መልእክት ከሚቃወም በቀር የወንጌል እንቅፋትና ሰይጣን ያለ አልመሰለኝም ስለዚህ ለማስተዋል ብትሞክር ጥሩ ነው፡፡ ስድብ ከሰይጣን ነው፡፡

   Delete
  2. የመጀመሪያዉ Anonymous ሆይ ቆይ=ቆይ= ለመሆኑ አሹ ለምን ይህንን አላደረግሁም ይህንን ያለኝን አቅርቡልኝና እናንተ ባላችሁበት እንነጋገር ብሎ ራሱንም ወዳጆቹንም ለምን ነፃ አያወጣም ብለህ አስበህ ታዉቃለህ ወይ፡ እኔ ከእናቴ ልጅ በላይ የምወደዉ ሰዉ ነበርኩ፡ በእርሱ ዝምታ በሚያዉቁኝ ሰዎች ዘንደ ሁሉ ዋጋ እየከፈልኩ ነዉና እባክህን የሚሰማህ ከሆነ ስድቡን ትተህ ወደ አደባባይ ዉጣና ዉሸታችሁን ነዉ ብለህ አስተንፍሰን በለዉ፡፡ እኛም እኮ እንደሱ መደበቅ ባለመቻላችን የሰዉ ሁሉ መቀለጃ ሆነናል፡፡ ይህ በስጋ ነዉ በነፍስም ቢሆን መጠራጠራችን በራሱ ምን ያህል አስጨናቂ ነዉ፡እስቲ እንደሰዉ ማሰብ ብትችል ደስ ይለኛል፡፡ አሹ፡ ተጫወትክብን ሌላ ምን እላለሁ፡፡

   Delete
 2. እንደ እግዚአብሔር ቃል መኖር ለሚፈልግ ይህ ትልቅ እውነት ነው። ጌታ ይባርካችሁ

  ReplyDelete