Friday, May 29, 2015

ስደተኛው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፡- በዓመት አንድ ቀን ብቻ የሚዘከረው መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያናችን ስፍራው ወዴየት ይሆን?! ክፍል -፩በዲ/ን ኒቆዲሞስ
የዛሬ ወር ገደማ በብትሕውና ሕይወት እየኖሩ ያሉ አንድ አባት ቤታቸው ብቅ ብዬ ጠበል እንድቀመስ ስልክ ደወሉልኝ፡፡ ለወትሮው በቤታቸው የሥላሴን፣ የመድኃኔ ዓለምንና የእመቤታችንን ዝክር በመዘከር ድሆችን ጠርተው እንደሚያበሉ ስለማውቅ የእዚህ ቀን የጠበል ቅመስ ጥሪያቸው ከእነዚህ በውል ከማውቃቸው ቀናቶች የተለየ ቀን በመሆኑ በጥቂቱ ግራ አጋባኝ፡፡ እናም አባ ዛሬ ዕለቱ ዐሥራ አንድ ነው፣ ቅዱስ ያሬድን ወይም ቅድስት ሐናን መዘከር ጀመሩ እንዴ ስል ጠየኳቸው፡፡
እኚህ መናኝ አባትም በምላሻቸው አይ ቅዱስ ያሬድን ወይም ቅድስት ሐናን ለመዘከር አይደለም፡፡ እንግዲያውስ አባ ምንን አስመልክተው ነው አልኳቸው፤ እርሳቸውም ወር በገባ በ፲፩ ዕለቱን ለመዘከር የወሰኑበትን ምክንያታቸውን እንዲህ ሲሉ በመንፈሳዊ ቅናት እየተቃጠሉ አብራሩልኝ፡፡
አየህ ወንድሜ በቤተ ክርስቲያናችን ለእግዚአብሔር አብ፣ ለእግዚአብሔር ወልድ፣ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም፣ ለቅዱሳን መላእክት፣ ለጻድቃንና ለሰማዕታት ለእነዚህ ኹሉ ወርኻዊና ዓመታዊ የመታሰቢያ በዓል አላቸው፡፡ የሚገርመው ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ግን በዓመት አንድ ጊዜ በዓለ ፕራቅሊጦስ/በዓለ ኀምሳ በሚል ከምናከብረው ውጪ ወርኻዊ የመታሰቢያ በዓል የለውም፡፡

ስለሆነም እኔ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ወር በገባ ኹሌም በየወሩ በ፲፩ ለማክበር የዛሬውን ዕለት ለመንፈስ ቅዱስ የመታሰቢያ ዕለት እንዲሆን በማሰብ በዓሉን ለማክበር ዛሬን አሐዱ ብዬ ጀምሬያለኹ፡፡ እናም በዚህ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ወርኻዊ የመታሰቢያ በዓል ዝክር ላይ እንድገኝና ሌሎች መንፈሳዊ ጓደኞቼንም ጭምር እንድጋብዝ አደራ አሉኝ፡፡ አስከትለውም ከቀናቶች መካከል ፲፩ን ለመንፈስ ቅዱስ ወርኻዊ መታሰቢያ በዓል እንዲሆን የመረጡበትንና የወሰኑበትን ምክንያታቸውንም ከወንጌል ቃል በማጣቀስ እንዲህ ሲሉ አብራሩልኝ፡፡
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ግብር በሥጋ መወለዱን ኦርቶዶክሳውያን ኹሉ እናምናለን፡፡ ልደቱንም በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በደስታና በሐሴት እናከብራለን፡፡ ከልደቱ በኋላም ጌታችን የነቢያትን ትንቢት ለመፈጸም፣ አንድም ለእኛ አርዓያ/ምሳሌ ሊሆነን ተጠምቋል፤ በሌላም በኩል ለድነታችን የጥምቀትን ሥርዓት ሠርቶልናል፡፡ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የሰኞ ዕለት ውዳሴው፡-
‹‹በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ኹሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለ ሰው ፍቅር ወደዚህ ዓለም የመጣህ ፍጥረት ኹሉ በመምጣትህ ደስ አለው፡፡ አዳምን ከስሕተት አድነኸዋልና ሔዋንንም ከሞት ፃዕረኝነት ነፃ አድርገኻታልና የምንወልድበትን መንፈስ ረቂቁን ልደት ሰጠኸን…፡፡›› ብሎ እንዳመሰገነ፡፡

ጌታችንና አምላካችን በሠራልን በምሥጢረ ጥምቀት ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊ ልደትን አግኝተናል፡፡ ራሱ አምላካችን፣ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስም ለኒቆዲሞስ፡-‹‹ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይቻለውም፡፡›› እንዳለው፡፡ በዚህም ሰማያዊና ልዩ ረቂቅ የጥምቀት ምስጢር የተገፈፍነው የልጅነት ጸጋ ተመልሶልናል፡፡
ጌታችን ኢየሱስም፡-‹‹እንግዲህስ ጽድቅን ኹሉ ልንፈጽም ይገባናል፡፡›› ባለው አምላካዊ ቃሉ መሠረትም በአገልጋዩና በባህታዊው በቅዱስ ዮሐንስ እጅ በተጠመቀበት ጥር፲ ለ፲፩ ሌሊት መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይም እንደተቀመጠበት ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል፡፡ በጌታችን ጥምቀትም የባህርይ አባቱ እግዚአብሔር አብ በሰማይ ኾኖ፡- ‹‹በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው፣ የምወልደው ልጄ እርሱ ነውና እርሱን ስሙት፡፡›› የሚል ታላቅ ድምፅን/ምስክርነትን አሰምቷል፡፡
እንዲሁም በዚህ ዕለትም ምስጢረ ሥላሴ በጉልህና በተረዳ እንደተገለጸ ቤተ ክርስቲያናችን ታስተምራለች፡፡ ከልደትም በኋላ የሚመጣውን ዘመንም ‹‹ዘመነ አስተርእዮ/የመገለጥ ዘመን›› በሚል ምስጢረ ሥላሴ በጉልህ፣ በተረዳ መገለጡንና ከሦስቱ አካላት አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ ከእመቤታችን ሰው መሆኑን፣ በዚህም የእግዚአብሔር ፍቅር ለኹሉ መገለጡን ታስተምራለች፡፡
ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አባቶቻችንም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ፣ በተለየ አካሉ፣ በእርሱ፣ በሰማያዊ አባቱ በአብ፣ በባሕርይ ሕይወቱ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሰው ልጆችን ኹሉ ለማዳን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ የተገለጸበትን ሰማያዊ ምሥጢር፡-
ወአስተርአየ ገሃደ፣
በለቢሰ ሥጋ ኮነነ ዘመደነ፡፡
በማለት በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን የቅድስት ሥላሴ ምሥጢር በገሃድ መገለጹንና፣ የእግዚአብሔር ልጅነትን ጸጋ መጎናጸፋችንን፣ የእግዚአብሔር ወገኖች፣ ዘመዶች ተብለን መጠራታችንን በመንፈስ ቅዱስ እንዲህ አመስጥረው ተቀኝተዋል፣ ዘምረዋል፡፡
 ‹‹ፍቅሩ ለእግዚእ›› በመባል የሚጠራው ሐዋርያውና ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም በመልእክቱ፡- ‹‹በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ…፡፡›› ብሎ እንደተናገረ፡፡ እንዲሁም በወንጌሉ፡- ‹‹መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለው አንድ ልጁ እርሱ ተረከው፡፡›› እንዲል በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን እግዚአብሔርን ዐየነው፣ ዳሰስነው፣ ምስጢረ ሥላሴም ተገለጠ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምም በሐሙስ ውዳሴ ማርያም ድርሳኑ፡- ‹‹የማይታወቅ ተገለጠ፣ የማይታይ ታየ፣ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ በርግጥ ሰው ኾነ፡፡›› ብሎ በመንፈስ ቅዱስ እንዳመሰገነ፡፡
እንግዲህ ይህ ጌታችን የተጠመቀበትን ወርኀ ጥር ፲፩ን እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት በታላቅና በደማቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት እናከብራለን፡፡ ይህ ዕለትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል የተገለጠበት፣ የወረደበት ዕለት ነው፡፡ ወርኻ ጥርም እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ‹‹ዘመነ አስተርእዮ›› በሚል ይታወሳል፣ ይከበራል፡፡
በዚኹ በወርኻ ጥር ፳፩ ቀንም የሚከበረው እመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም በዓልም ከዚሁ ከእግዚአብሔር/ከቅድስት ሥላሴ መገለጥ፣ በገሃድ መታየት ጋር የተያያዘ ታሪክ አለው፡፡ ስለዚህም አሉኝ እኚህ አባት ይህን የወንጌል ታሪክና ቅዱስ ቃል መሠረት በማድረግ ወር በገባ በ፲፩ መንፈስ ቅዱስን አከብራለኹ፡፡ እንደምታውቀው በዓለ ፕራቅሊጦስ ቀኑ ስለሚቀያየርና በዓመት አንድ ጊዜም ብቻ ስለሚመጣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ለማሰብ፣ ለመዘከር ይህ ቀን የተገባ መስሎ ታየኝ፡፡ ስለሆነም ወር በገባ ኹሌም በ፲፩ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን እዘክራለኹ፡፡ ወዳጄ ይህን አንተም ለሌላ መንፈሳዊ ጓደኞችህና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም አሳውቅልኝ አሉኝ፡፡
ቅዱስ መጽሐፍም፡- ‹‹ቀንን የሚያከብር ለእግዚአብሔር ብሎ ያከብራል፡፡›› እንዲል እኚህ አባት ወር በገባ ፲፩ን ለመንፈስ ቅዱስ ወርኻዊ የመታሰቢያ በዓል እንዲሆን በግላቸው ያደረጉት ውሳኔና መንፈሳዊ የልባቸው ቅናት እጅጉን አስገረመኝ፣ አስደመመኝም፡፡ ከእኚህ አባት ጋር ከዚሁ ከመንፈስ ቅዱስ ወርኻዊ በዓል ጋር በተያያዘ አንዳንድ መንፈሳዊ ጉዳዮችን አንሥተንም በሰፊው ተጨዋወትን፡፡
ከእኚህ መናኝ አባት በጨዋታችን መካከልም፡- በቤተ ክርስቲያናችን ለመንፈስ ቅዱስ ለምን ተገቢው ስፍራ ሊነፈጋቸው ቻለ?!  ስደተኛው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለምን ይኾን በወር አንድ ቀን ተነፈጎት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እንድናክብረው የኾነበት ምክንያቱስ ምንድን ነው?! ለምንስ በቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ተዘነጋ፣ ተተወ?! በማለት ከዚሁ ጋር አያይዘው በአንድ ወቅት ያጋጠማቸውን ያስገረማቸውንና ያሳዘናቸውን ገጠመኛቸውን እንዲህ አጫወቱኝ፡፡
በአንድ ወቅት በዚሁ በመዲናችን በአዲስ አበባ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ጠበል ስፍራ የተገኙት እኚህ አባት አንዲት እናት ጠበል እንዲቀዱላቸው ይጠይቋቸዋል፡፡ እኔም አሉኝ እኚህ አባት እኔም ጀሪካናቸውን ተቀበልኩና ምንም ወረፋ የሌለበትን የእግዚአብሔር አብ ጠበልን ልቀዳላቸው ስሔድ እኚህ እናት ‹‹አይ… አይ… አባቴ እኔ የገብርኤልን ጠበል ነው ነው የምፈልገው አሉኝ፡፡›› ፈጠን ባለ ድምፅ፡፡
በወቅቱ ይህን ያደረኩት አሉኝ እኚህ አባት የእመቤታችንን፣ የገብርኤል፣ የሚካኤል ጠበል ላይ በርከት ያሉ ጀሪካኖች ተደርድረው ስለነበር እሳቸውን ላለማቆየት አስቤ ነበር ጀሪካናቸውን አንድም ሰው ወረፋ ወዳላስቀመጠበት የእግዚአብሔር አብን ጠበል ልቀዳላቸው የሔድኩት፡፡ እርሳቸው ግን አብዛኛው ሕዝብ በወረፋ የሚቀዳውን የገብርኤልን ጠበል እንጂ የእግዚአብሔር አብ ጠበልን እንደማይፈልጉ ነገሩኝ፡፡ እኔም ኀዘንና ግርምትን ተሞልቼ እንደው ፈቃዳቸውን ለመሙላት ብቻ ስል የቅዱስ ገብርኤልን ጠበል ቀዳኹላቸው፡፡ አየኽ ልጄ ይሄ ፍጡርን ከፈጣሪ ቀላቅሎ ያለ መንፈሳዊ እውቀት በጨለማ እየተመላለሰ ላለው ሕዝባችን ጥሩ ማሳያ የሚሆን ይመስለኛል አሉኝ ፈርጠም ብለው፡፡ 
በእርግጥም አብዛኛው የቤተ ክርስቲያናችን መእምናን ለእመቤታችን፣ ከመላእክትም ለቅዱስ ገብርኤልና ለቅዱስ ሚካኤል የተለየ ስፍራን ይሰጣል፡፡ ከዚህ የተነሣም እንኳን ዓመታዊው አይደለም ወርኻዊው ቅዱስ ገብርኤል መታሰቢያ በዓል እጅጉን የደመቀና በርካታ ሕዝብ የሚገኝበት ነው፡፡ የዚህ የእግዚአብሔር መላእክ መታሰቢያ ቀን የሆነው ፲፱ በብዙዎች ልብ ውስጥ የታተመ ዕለት ነው፡፡ ከመኖሪያ ቤት እስከ ቡቲኮች፣ መሸታ ቤቶችና መዝናኛ ስፍራዎች በሳር ጉዝጓዝ የሚደምቁበትም ዕለት ነው፡፡
እስቲ እውነት እንነጋገር ከተባለ ለእግዚአብሔር አብ መታሰቢያ በዓል እንዲሆን የተወሰነውን ፲፫ን፣ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ኢየሱስ የሚለውልበትን ፮ን የሚያውቀውና በልቡ የሚያስበው ስንቱ የቤተ ክርስቲያናችን መእምናን ነው ቢባል ምላሹ አሳፋሪ ነው የሚኾነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግሞ ወር በገባ በስድስት አርመናዊቷ የቅድስት አርሴማ በዓል በመደረቡ ከኢየሱስ ስምና በዓል ይልቅ ደምቆና ጎልቶ የወጣው የቅድስት አርሴማ ስምና በዓል እየሆነ እንደመጣ እየታዘብን ነው፡፡
ይህን እውነታ ለመታዘብ የፈለገ ሰው ወር በገባ በስድስት በአዲስ አበባ ከተማዎች ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ ዞር ዞር ቢል በኔ ቢጤዎች አንደበት ጎልቶ የሚሰማው የማን ስም እንደሆነ ማረጋገጥ ይችላል፡፡ በአንድ ወቅትም እኚህ አባት እንዲህ ብለውኝ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አብ በቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ዘንድ እንደነገሩ ይነሣል፣ እግዚአብሔር ወልድ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ደግሞ በፍርሃት፣ በጭንቅ ይጠራል፣ መንፈስ ቅዱስ ግን ጨርሶ የተዘነጋ፣ የተተወ ነው የሚመሰለው፡፡
የእኚህ አባት ትዝብት አንድ የሚነግረን ትልቅ እውነታ አለ፡፡ በቀጣይ ጽሑፌ ከመቅደሱ ስለተሰደደው፣ በቤተ ክርስቲያናችን መሪዎች፣ አገልጋዮችና ምእመናን ዘንድ ስለተተወውና ስለተዘነጋው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስና በዚህም የተነሣ በተቀደሰው ተራራው ስለነገሰው ክፋትና ዓመፃ ጉዳይ ጥቂት የመወያያ አሳቦችን በማንሣት ለመመለስ ከወዲሁ ቃል እገባለሁ፡፡ እስከዛው ግን እንኳን ለበዓለ ፕራቅሊጦስ ኹላችንን በፍቅር፣ በሰላም አደረሰን ለማለት እወዳለኹ፡፡
በዓለ ፕራቅሊጦስ፡- መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ላይ የወረደበት፣ አማንያን በሐዋርያት ስብከትና በምሥጢረ ጥምቀት ከክርስቶስ ጋር ተዋሕደው የአዲስ ኪዳን አዲስ ሕይወት የጀመሩበት፣ በመንፈስ ቅዱስ የምትመራው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን እለት ‹‹የቤተ ክርስቲያን ልደት›› ቀን ሲል እንደጠራው በይፋ የተቆረቆረችበት ቀን ነው፡፡
አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፣ እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያስተምራችኋል፡፡ ዮሐ. ፲፬

12 comments:

 1. በጣም ግብዝ ነህ፤መንፈስ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ የወረደበት ይከበራል እንጂ,ሥላሴ አብርሃም ቤት የገቡበትና የሰናዖር ግንብ የናዱበት በዓል ይከበራል እንጂ፤ለሥላሴ የመንፈስ ቅዱስ በዓል ብሎ ማክበር ከመጀመሪያው ትክክል አይደለም,ሁሉም ቀኖች የሥላሴ በዓላት፣የመንፈስ ቅዱስ ዘመን ነውና።ካንተስ ምእመናን ይሻላሉ;ዲያቆን መባልም አይገባህም

  ReplyDelete
 2. ለዲያቆን ኒቆዲሞስ
  ክስ እንጂ ሌላ ስትናገርም ይሁን ስትፅፍ አላየሁህም:: ስትፈርድ እንጅ እኔ ምናምንቴ ነኝ ስትል አልሰማሁኝም:: ስታስመስል እንጅ ሆነህ አላየሁህም:: ስለ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ እምነት በሐሰት ስታወራ እንጅ ስለ አንተ ቤት እምነት ስታወራ አልሰማሁም:: ብቻ ሌሎችን ትከሳለህ ፈራጅም ሆነህ ፍርድን ታራምዳለህ:: ለመሆኑ ሃይማኖትህ ምንድን ነው? ቤተ እምነት ካለህ የቤተ እምነትህ መተሬያህ ማን ይባላል? ብቻ በሁለቱም ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እንዳንትልና ዲያብሎስን እንዳታስደምመው::
  ወንድም ከሳሽ ኒቆዲሞስ; ምንም እንኩዋን ይህን ክስህን ስትፅፍ የቤተክርስቲያን ሰው መስለህ ቢሆንም የሰነዘርሃቸው የክስ ሃሳቦችህ ግን ጠላቷ መሆንህን ነው የሚያሳዩት:: ምክንያቱም በቅዱሳኑ በዓላት ወቅት የሚገኘው ሕዝብ ለእግዚአብሔር አብ ከሚገኘው ሕዝብ ይበልጣል ትልና ይህም የሆነው በሕዝቡ ልብ ውስጥ እግዚአብሔር አብ ስለሌለ ነው የሚል ክስና ፍርድን አድርገሃል:: እውነታው ግን አንተ ያልከው አይደለም:: እውነታው ግን እውነትኞቹ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዩች አምላካቸውን ከቅዱሳኑ ጋር እንዳለና እግዚአብሔርም እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል ያለውን ስለሚያውቁ ወደ ቅዱሳኑ ክብረ በዓል ይጎርፋሉ:: ሁለተኛው ሞዕመናን ወደ ቅዱሳኑ በዓል የምጎርፉበት ምክንያት በቅዱሳኑ የሚጠራው ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር ቤት ስለሆነና በመቅደሱ የምመለቀው እግዚአብሔር መሆኑን ስለሚያውቁ ነው:: የጠበሉም ተመሳሳይ ነው:: በጠበሉ የምረበው የእግዚአብሔር መንፈስ መንፈስ ቅዱስ ነውና የሚፈውሰውም እሱ ነው:: መንፈስቅዱስ ደግሞ በቤተ ክርስቲያንና በቅዱሳኑ ሆኖ ይሠራልና ወደዚያ ይጎርፋሉ:: ብዙ ምክንያቶችን መጥስቀስ ቢቻልም አንድ ልጨምርና ወደሌላ እሻገራለሁኝ:: ሶስተኛው ደግሞ በረከት በፃድቅ እራስ ላይ እንደሆነ ስለተማሩና ስለሚያውቁ ወደ ቅዱሳን በዓላትን ለማክበርና በረከትን ለማግኘት ይጎርፋሉ:: በቅዱሳኑ እራስ ያለው በረከት የአምላካችን የእግዚአብሔር በረከት ነው:: ምን አይነት በረከት? የፅድቅ; የፈውስ; የሀብት; የልጅ; የሕይወትና የብዙ መልካም ፍሬዎች በረከት::
  ሌላኛው አሳፋሪው ትረካህ ከአንድ አባት ያገኘሁት ብለህ የተወንህው ተውኔትህ አንዲት እናት ጠበል ሊወስዱ ጀሪካን ይዘው መጡ እኔም ብዙ ከሚቆሙ ብዩ ወረፋ ከሌለበት ወደ እግዚአብሔር አብ ጠበል ወሰድኩት እኒያ እናትም እኔ የገብርእኤል ነው የምፈለገው አሏቸው ያልከው ነው:: ብለው ቢሆን እንኩዋን ካላቸው ፍቅርና በገብራኤል በኩል እግዚአብሔር ካደረገላቸው የተነሳ ሊሆን ይችላል:: ባይሆንም እንኩውንና ነገሩኝ ብለህ የገለፅሃቸው አባት ባለጠበሏ ተሳስተዋል ካሉ ማስተማር እንጂ ይህን ያክል እንደ ክህደትና ሌላ ታምር የሚነገር አይደለም:: በተጨማሪም እኒህ ነገሩኝ የምትላቸው የሰይጣንን ተግባር ነው የሰሩት:: ይህውም በተንኮል ባለጠበሏን ተፈታትነዋታልና ነው::
  በመጨረሻ እግዚአብሔር መንፈስቅዱስ የት ተሰደደ በሚል ሌላ ክስ እንደምትመለስ ከሰይጣን ጋር ቃልኪዳን አድርገሃል:: የት እንደምታሰድደው የማየው ቢሆንም መንፈስ ቅዱስ የትም አልተሰደደም አይሰደድምም:: መንፈስ ቅዱስ በቤተክርስቲያን በቤተ መቅደስ; በስብከቱ; በዝማሬው; በቅዳሴው; በጠበሉ; በቅዱሳን በዓላቱና በአጠቃላይ በቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎቶችና በክርስቲያኖች ሕይወትና ኑሮ ውስጥ አለ ይሰራልም::
  እኔ አንተን ጥያቄ ልጠይቅህና ላገባድ:: ለመሆኑ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ተጠቅሷል? ምን መንፈስ ቅዱስ ብቻ አብ ስንት ጊዜ ተጠቅሷል? እግዚአብሔር አብ; እግዚአብሔር ወልድ; እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እኩል በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቁጥር ተጠቅሰዋልን? ይህን እንድትመልስልኝ:: ነገ ደግሞ መፅሐፍ ቅዱስንና የፃፉትን ትከስ ይሆን? መቸም አሳባቸው የታወረባቸው ይህን አይሉም ብሎ ማሰብ ከባድ ነው::

  ReplyDelete
 3. ውዳሴ ማርያምን በስህተት የተሞላ መጽሓፍ ነው እያላችሁ እየነቀፋችሁ እንዴት እንደ መረጃ(ሪፈረንስ) ትጠቀሙበታላችሁ?

  ReplyDelete
 4. በብትሕውና ሕይወት እየኖሩ......እኚህ መናኝ አባትም..............አንተ ዲያቆን ነህ ግን "አየህ ወንድሜ" እያሉህ ነው ስለዚህ ልጅነትህ ወዴት ነው?
  መናኙን አባት ደግሞ ወደ መዲና አወጣሃቸውና "በመዲናችን በአዲስ አበባ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ጠበል ስፍራ የተገኙት እኚህ አባት አንዲት እናት ጠበል እንዲቀዱላቸው..." በማለት ትወናውን ቀጠልህ!
  አሪፍ ድርሰት ነው ግን ትዘላብዳለህ::
  በራስህ character እየፈለግህ ተዋንያንን እንደፈለግህ ከበረሃ ወደ መዲና እያመጣህ አንዴ አንተ አንዴ አንቱ እያልህ ስትፈልግ በብትህውና ስትፈልግ ጀሪካን አስይዘህ በአዲስ አበባ እየሳልህ ........ብቻ ጥሩ ድርሰት ነው::
  የቅድስት ድንግል ማርያም በዓል ሲከበር የሚመሰገነው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው ወዳጄ!
  እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቅዱሳንን ቅዱስ እንዲባሉ ያደረገ መሆኑ መቸም ለአንተ 'ለመናኙ አባትህ' ወንድም አይጠፋህም::

  ReplyDelete
 5. Emabetachen Kidist Mariam melekotawi hayil yelatim. Besiga yemedhanitachen ye Kirstos enat nat. Eyasus Kristos ye Mariam fetarina getawa new, Esu kealem befit nebere, ye yetewoledechew yezare 2035 amet gedema new. Adagnina Feraj esu becha new. Ersuwam "Ersun becha simut" bilalech. Wedase Mariam ye ena Zaria-Yakob yefetara sirana tiraka new. Praying to saints and Mary has no biblical basis. Read the BIBLE, not Semen Ethiopian's LEGEND!!!

  ReplyDelete
 6. ‘’አፍ ሲከፈት የውስጥ ባዶነት ይታያል፡፡’’ ይሉሀል ይሄ ነው፡፡
  ዛሬ ደግሞ የማታምንበትን ውዳሴ ማርያም ደጋፊ አድርገህ መጥቀስህ….ውሸታም ብቻ ሳትሆን እራስህም ውሸት መሆንህን እራስህ መሰከርክ፡፡

  ReplyDelete
 7. አንተን ያደቆኑ ‘’አባ’’ ከዚህ በላይ ቢያውቁ ይገርመኛል፡፡ ሁኔታህ ያዝናናኛል፡፡

  ReplyDelete
 8. በጣም የሚገርም ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ በዓላት ሁሉ የእግዚአብሄር ናቸው፡፡ ከመታሰብያነት ያለፈ ክብር ለማንም አይሰጥም አንስጥምም፡፡ ስለዚህ አትሞኝ ሰውን ከማስተማሪህ በፊት ለራስህ ተማር እሽ……….

  ReplyDelete
 9. ዳይ-ቆን ኒቆዲሞስ!!
  ከተቆረቆርክ አይቀር ከዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራዕይ ባለው መጽሐፍ ቅዱስ፡- ኦሪት ዘፍጥረት፣ዘፀአት፣ዘኍልቁ…መጽሐፈ-መሳፍንት፣ሳሙኤል፣ነገሥት፣ሩት፣ኢዮብ…..ትንቢተ-ኢሳይያስ፣ሕዝቅኤል፣ዳንኤል፣ኤርምያስ….ወንጌለ-ማቴዎስ፣ማርቆስ፣ሉቃስ፣ዮሐንስ፣የሐዋርያት ሥራ…የጳውሎስ መልእክት፣የጴጥሮስ፣ዮሐንስ፣ያዕቆብና ይሑዳ መልእክት ብቻ የሚለውን መጽሐፍ ቅዱስ በጌታ መንፈስቅዱስ የሚጠራ የመጽሐፍ ክፍል የለውም ብለህ መውቀስ ነበረብህ፡፡በመሰረቱ ወንጌልም ቢሆን በዋናነት ሥግው ስለሆነው እግዚአብሔር ወልድ ነው በዋናነት የሚተርከው፡፡እንዲያው ወግ ላሳምር ብለህ እንጅ!
  ሥላሴ፣መድኃኔዓለም፣አማኑኤል፣በዓለ-ወልድ በጉልህ የሚጠሩ ጌታ በዓላት መሆናቸውን ስታውቅ እንዳላየ አለፍካቸውሳ፡፡
  በዲቁና ደረጃ በመሆንህ ብዙም አልፈርድብህም፡፡እስኪ ግዴለም መሪጌቶችን ጠይቅ፡- ማንኛውም ቤ/ክ ሲመረቅ ለዛቲ ቤት ሣረራ አብ ቀዲሙ፣ሐነጻ ወልድ ወ ፈጸማ መንፈስቅዱስ የሚል ንባብ ይነግሩሀል፡፡ምስጢራተ-ቤተክርስቲያን በሚፈጸምበት ሁሉ የአብ ወልድ መንፈስቅዱስን ሥም በመጥራት እንደሆነ አትስተውም፡፡እንደነ እንትና በኢሱስ ሥም ብለን በደፈናው መቀላቀል ሳይሆን ጥምቀታችን ዳግም ልደታችን ከምፈስቅዱስ መሆኑን አምነን ነው--አጠምቀከ/ኪ በአብ ወልድ ወ መንፈስቅዱስ የምንለው፡፡በአጠቃላይ ምስጢረ-ጥምቀት፣ክሕነት፣ንስሐ…የመንፈስቅዱስ ስጦታዎች መሆናቸውን እናምናለን፤እናስተምራለን፡፡
  ሆኖም የመንፈስቅዱስ ስጦታን ልሳን ወረደልን፣ቅባት መጣልን፣ሀብተ ትንቢት ተሰጠን፣ዘምር-ዘምር አለን፣በራዕይ ተገለጸልን እያሉ እንደሚያቃልሉ የዘመኑ ሀሳውያን አንቀልድበትም፡፡
  ፍጡር ከፈጣሪ ለመለየት ተሳነን አስመስለህ፤ፍጡርን ከፈጣሪ ያስበለጥን አስመስለህ ልታደነቁረን መሞከርህ ይገርማል፡፡ለነገሩ እንዲህ ካልጻፍክ ብሎጉም መድረክ አይሰጥህም፡፡አይፈረድብህም፡፡ብትችል ግን ምጥ ለእናት ለማስተማር አትሞክር፡፡

  ReplyDelete
 10. ያቃታቸው በቤ/ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን እውነተኛ መፃህፍት ስለመንፈስ ቅዱስ የሚናገሩትን በግልፅ አለመናገራቸው ነው.....

  ReplyDelete
 11. '‹‹ፍቅሩ ለእግዚእ›› በመባል የሚጠራው'፤ዲ/ን ነኝ እያልክ ይኽንን ግእዝ ኮርጆ እንኳን መጻፍ አቃተህ? ለማንኛውም 'ፍቁረ እግዚእ' ነው የሚባል እሺ፡፡አስመሳይ ከሳፋች፣ባልዋልክበት!

  ReplyDelete
 12. 'በብትሕውና ሕይወት እየኖሩ ያሉ አባት' ቤታቸው ብቅ ብዬ ጠበል እንድቀመስ ስልክ ደወሉልኝ፤
  ባለ ስልክ ከሆኑ፣ ሰውን እየደወሉም ኑ ወደኔ ኑ የሚሉ ከሆነ፣ ዝክር ዘክሮ ሰውን ሁሉ የሚያበላ ንብረት ካላቸው፣ ብሕትውናው ምኑ ላይ ነው? ደግሞም አንተ በባሕታውያን የታወቅክ፣ የምትፈለግ ሰው ሆነህ! የራስህን ክብር ከፍ ከፍ ታደርጋለህ!

  ReplyDelete