Tuesday, May 12, 2015

ለእኛ ግን የበቀል ሰይፋችን ፍቅር ነው!፡- ኢትዮጵያዊነት ፍቅርና ይቅር ባይነት የገነነበት ማንነት ነው!!

Read in PDF

በዲ/ን ኒቆዲሞስ  nikodimos.wise7@gmail.com

‹‹ሰይፍህን አንሣ፣ ክተት ሠራዊት፣
ዝመት ለፍቅር፣ ሰልጥን ለምሕረት፡፡››  (ዘሪቱ ከበደ)
                                  
ከሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ በቆንጨራ ለተጨፈጨፉ፣ በሚያሰቅቅና በሚዘገንን ኹናቴ እሳት በቁማቸው ለተለቀቀባቸው፣ ሀብት ንብረታቸው ለተዘረፈባቸውና ለጋየባቸው፣ የጦርነትና የእልቂት አውድማ በሆነችው በአገረ የመን ለሞቱና በጭንቅ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖቻችንና በተለይም ደግሞ በሊቢያ በአይ ኤስ የአክራሪና ጽንፈኛ ቡድን የተሠዉትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን አስመልክቶ በጥቂቱም ቢሆን የጥበብ ባለ ሙያዎቻችን በሥራዎቻቸው ሕመማችንን እየታመሙ፣ ጭንቀታችንን እየተጨነቁ፣ ብሶታችንን፣ ሰቆቃችንንና ዋይታችንን አብረውን እየጮኹ፣ እየተካፈሉ ነው፡፡
በእርግጥስ የጥበብ ባለ ሙያዎቻችን በሥራቸው የተገኙበትን የሕዝባቸውን ወይም የሀገራቸውን ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ትውፊት፣ ማንነት እያስተዋወቁ ነውን?!፤ በሀገራችን ያሉ የጥበብ ባለሙያዎችስ ላለንበትና ለሚያጋጥሙን ማኀበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶቻችንና ፈተናዎች መፍትሔ በማመላከት፣ ስለ ፍቅር፣ ሰላም፣ ነፃነትና ፍትሕ በመጮኽ፣ ለሕዝባቸው አንደበት፣ ዓይንና ጆሮ በመሆን ሙያዊ ግዴታቸውን እየተወጡ ነው ወይ?! ልክ እንደ ሰሞኑንም እንዲህ አገር የኀዘን ማቅ ስትከናነብ፣ በለቅሶና በዋይታ ስትናጥ፣ ሕዝብ ይዘው ይጨብጠው ሲጠፋ የጥበብ ሰዎቻችን አድራሻቸው ወዴት ነው?!፣ ስለ ምድራችን ግፉአንና ምስኪኖችስ ድምፃቸው ከፍ ብሎ ይሰማል ወይ?! ወዘተ … የሚሉ ጥያቄዎችን ብናነሣ ምላሹ ብዙም የሚያረካ እንዳልሆነ እርግጠኛ ነኝ፡፡

በነጋ ጠባ ጥበብና የጥበብ ሰዎቻችን ወዴት አቅጣጫ እየሔዱ ነው?!፣ የሕዝብ አንደበትና ጆሮ የመሆን ሙያዊ ግዴታቸውስ ወዴት ነው?! የሚል ሮሮ በገነነበትና የቁጭት ደመና ባጠላበት ሁኔታ፣ በአገራችን የጥበብ እንዱስትሪ ውስጥ እንደ መስቀል ወፍ ብቅ በማለት በአገራችን ሙዚቃ (ይህን ስል ከባህላችን፣ ከታሪካችን፣ ከወጋችን ያልወጡና የሞራል ሕግን ያልጣሱ የሙዚቃ ስራዎችን ማለቴን እነደሆነ ልብ ይሏል፡፡) ታሪክ እንደ አጥቢያ ኮከብ ደምቀው ያበሩና እያበሩ ያሉ፣ ለሕዝብ የተፈጠሩ፣ ለሕዝብ እየኖሩ ያሉ ባለሙያዎችን ግን ፈጣሪ አላሳጣንምና ተመስገን ነው፡፡
መቼም ሥነ ጥበብ በአንድ አገር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስና ማንነት እንዲሁም በፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችና በሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ማኅበራዊ ግንኙነቶች ላይ ያለው ጉልህ አስተዋፅኦና ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ/የምጣኔ ሀብት ምሁር፣ ሐያሲና የሥነ ጽሑፍ ሰው ጋሽ አስፋው ዳምጤ ‹‹ፎረም ፎር ሶሻል ስቴዲስ›› ለሁለት ዓመታት በተከታታይ ባደረገው ‹‹ልማትና ባህል በኢትዮጵያ›› በሚለው የውይይት መድረክ ላይ ‹‹ሥነ ጥበብና ልማት›› በሚል ባቀረቡት የጥናት ጽሑፋቸው የጥበብን ሁለተናዊ ፋይዳ አስመልክተው እንዲህ ብለው ነበር፡-
‹‹ ሰው በተፈጥሮው ከአራዊት ወይም ከእንሰሳት የሚዛመድባቸውን ባሕርያት መሞረድ፣ ማለዘብ፣ እና የሰብአዊነት ባሕርያቱን ማጎልበት፣ ብሎም የማኅበራዊ ሕይወት ንቃቱን ከፍ በማድረግ፣ በጎና ሁለተናዊ ለሆኑ የልማት የጋራ ግቦች ለመነሳሳት ምቹ የሚያደርገው የአስተሳሰብ ዝንባሌ እና አመለካከት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የጥበብ ዘርፎች ሁሉ ዓላማና ግብ ነው፡፡›› በማለት ሥነ ጥበብ በሰው ልጆች ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ያለውን ሁለተናዊ ፋይዳ አብራርተዋል፡፡
በሥነ ጥበብ ዘርፍ ውስጥ ከሚካተቱትና ከፍጥረት ወይም ከሰው ልጆች ታሪክ ጅማሬ ዘመን ጋር አቻ ሊባል በሚችል በጥንታዊነቱ ወይም በዕድሜ ጠገብነቱ የሚነሳው አንጋፋው ሙዚቃ፣ በሰው ልጆች ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወትና መስተጋብር ውስጥ ትልቅ ድርሻና ግዙፍ አሻራ እንዳለው ብዙዎች የዘርፉ ምሁራን ይስማሙበታል፡፡

በዛሬው አጭር መጣጥፌ የቀድሞዋ ዘፋኝ አሁን ግን ወደ ሃይማኖት ፈቷን በማዞር ወደ ዝማሬ ያዘነበለችው አርቲስት ዘሪቱ ከበደ በሊቢያ በአይ ኤስ ጽንፈኛ ቡድን ሰማዕት ለኾኑ ወገኖቿ ‹ሰይፍህን አንሳ!›› በሚል ርእስ ከሰሞኑን አንድ ነጠላ መዝሙር አስደምጣናለች፡፡ የዚህ ዝማሬ መልእክቱ እጅግ ጥልቅ የኾነ ፍቅርን፣ ምሕረትንና ይቅርታን የሚሰብክና ከመንፈሳዊነቱ ባሻገርም ኢትዮጵያዊነት ከፈጣሪ የተቸረ በፍቅርና በውበት ጥበብ ተሸምኖ የደመቀ፣ ፍቅርና ይቅር ባይነት የተሞላ ማንነት መሆኑን የገለጸችበትን ዝማሬዋን ከማኅበራዊ ድረ ገጾች አደመጥኩኝ፡፡ እናም አርቲስቷ በዚህ በሰማዕትነት ለተሠዉ ወገኖቻችን በሠራችው ሙዚቃዋ ዙርያ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ወደድኹ፡፡
በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በሊቢያ በግፍ ለታረዱ ልጆቿ የሰማዕትነትን ማዕረግና ክብር መስጠቷ ይታወቃል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንትም ለሰባት ቀን ያህል ቤተ ክርስቲያኒቱ እነዚህ ሰማዕታት የኾኑ ልጆቿን በጸሎተ ፍታትና በምሕላም ስታስባቸው ሰንብታለች፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ መሪና የመንጋው እረኛ የሆኑት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስም እነዚህ ወገኖቻችንን በግፍ የሠዉትን የጽንፈኛው ቡድንን ከፈጣሪ ዘንድ ምሕረትንና ይቅርታን ያገኙ ዘንድ የንስሓ ጥሪ መልእክታቸውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ማስተላለፋቸውንም ተከታትለናል፣ አድምጠናል፡፡
ይህ ፓትርያርኩ ያስተላለፉት መልእክት ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላት ብቸኛው የበቀል ሰይፏ ፍቅር፣ ምሕረትና ይቅርታ መኾኑን ያረጋገጠና ያስረገጠ ነው፡፡ ይህ ታላቅ የሆነ መልእክትም በክርስትና ሃይማኖት ታሪክ፣ በዘመነ ሰማዕታት ለክፉ አውሬ ለአንበሳና ለነብር እየተሰጡ፣ በሰም የተነከረ ሸማ ለብሰው በእሳት እየተቃጠሉና እየጋዩ፣ በሰይፍ እየታረዱና እንደ ጎመን እየተቀረደዱ፣ በስለት እንደ ሸንኩርት እየተከተፉ፣ በድንጋይ እየተወገሩ ያለፉ የወንጌልና የኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው ምስክሮቹ የሆነ ሰማዕታት ሞትን ላወጁባቸው ኹሉ ምሕረትንና ይቅርታን ከፈጣሪያቸው ዘንድ ያገኙ ዘንድ ነው ሲማጸኑ የነበሩት፡፡
ይህ ከወዳጅ አልፎ ለጠላቶችም የሚተርፍና የሚተረፈረፍ ፍቅር፣ ምሕረትና ይቅርታ የክርስትና ሃይማኖት መሠረትና ጉልላት፣ ዋልታና ማገር ነው፡፡ የክርስትናው ዓለም ወርቃማ ሕግም፡- ‹‹ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ፤ ጠላትህንም ደግሞ ውደድ፡፡›› የሚል ነው፡፡ ከዚህ የክርስትናው ዓለም እውነታና አስተምህሮ ጋር አያይዤም አርቲስት ዘሪቱ ከበደ ‹‹ሰይፍህን አንሣ›› በሚል በሰማዕትነት ለተሠዉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን መታሰቢያነት ባቀረበችው ዝማሬዋ ውስጥ ያነሣቻቸውን ልብ የሚነኩና ጥልቅ የኾነ መንፈሳዊ መልእክቶቿን በጥቂቱ ለመፈተሽ እሞክራለኹ፡፡
አርቲስት ዘሪቱ ይህን ከልቧ የፈለቀውን ዝማሬዋን የጀመረችው ወገኗን እንደ እግር እሳት እየለበለበ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣውና ከምድሩ ያሳደደው ድኅነት፣ ችግር፣ ሰቆቃና መከራው፣ ተስፋን፣ ሕይወትንና የተሻለን ነገ አልሞና  ፈልጎ በተሰደደበት፣ በዚያ እዋዩ እንደ ሰደድ እሳት በሚንቀለቀልበትና የአሸዋው ግለት እንደ ወላፈን በሚጋረፍበት የሊቢያ በረኻ በወገኖቿ አንገት ላይ በጨካኞቹና በሞት አበጋዞቹ በአይ ኤስ ቡድን የተጋደመባቸውን ሰይፍ እያሰበችና በዓይነ ሕሊናዋ እየሣለች፡-
‹‹አመመሕ፣ ተቃጠልክ፣ ተቆጨኽ …››  በማለት ነው የወገኖቿን የዘመናት ብሶትና ምሬታቸውን፣ ሰቆቃና ዋይታቸውን በመካፈል ነው ልብን በሚሰረስር ዜማ ዝማሬዋን የምትጀምረው፡፡ ዘሪቱ በሙዚቃው ዓለም በነበረችበት ጊዜ እጅጉን በምትታወቅበትና ተወዳጅነትን ባተረፈችበት በተለየ ቅላጼዋና በሚስረቀረቅ ድምፅዋ፣ ፍቅርን፣ ምሕረትንና ይቅርታ በሰበከችበት የሙዚቃ ሥራዋ እንዲህ ስትልም ኢትዮጵያውያን ወገኖቿንና የሰው ልጆችን ኹሉ በፍቅርና በምሕረት ከፍ ባለ ድምፅ ትጣራለች፡-
‹‹ሰይፍህን አንሣ፣ ክተት ሠራዊት፣
ዝመት ለፍቅር፣ ሰልጥን ለምሕረት፡፡››

ዘሪቱ የሰው ልጆች ኹሉ እንዲያነሡት እያወጀችው ያለው ሰይፍ ስውር፣ ባለ ድልና ኹሉን የሚረታ ሕይወትን፣ ፍቅርን፣ ሰላምን የሚያውጅ መኾኑን እንዲህ ታበስረናለች፡፡ ይህን ሰይፍ አንስቶ፣ ይህ ሰይፍ ታጥቆ የሚተመው፣ የሚከተው ሠራዊትም ሰማያዊ፣ መለያውና በሩቅ ደምቆ የሚታየው ሰንደቀ ዓላማውም ፍቅር እንደሆነ እየነገረችን፣ እያወጀችልን ነው፡፡ አርቲስቷ በዚህ ጥልቅ መልእክትን ባዘለው ዝማሬዋ ይህ ሰይፍ የጨካኞችን ልብ በፍቅር የሚማርክ፣ ሞትን ሣይቀር የሚያሸንፍ፣ የሚረታና ይህ የበቀል ሰይፍ በሕይወትና በፍቅር ላይ የሚነግሥ ባለ ታላቅ ድል መኾኑንም እንዲህ ትነግረናለች፡-
‹‹ሰይፍህን አንሣ ተጋደልበት፣
ቀላል አይደለም ይኼ ጦርነት፡፡
ሰይፍህን አንሣ ማን ይችለዋል፣
ሞትን ራሱን ያሸንፈዋል!!››
የዘሪቱ የዝማሬዋ ጥልቅ መልእክትም ሌላም እውነታን ይነግረናል፡፡ የዝማሬዋ ስንኞች መልእክታቸው ከመንፈሳዊነታቸው ባሻገርም የአገራችንና የሕዝባችንን ግዙፍ ታሪክና ገናና ሥልጣኔ የሚዳስስና የሚተርክ ነው፡፡ በአርእስቴ ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ዘሪቱ በዚህ ዝማሬዋ ፍቅርና ይቅር ባይነት የሰለጠነበትንና የገነነበትን ያን ታላቅ የሆነ፣ በዘመን ተፈትኖ ያለፈ ክቡር የሆነ የኢትዮጵያዊነትን ረቂቅ መንፈስ ወይም ታላቅ ማንነትን እያነሳች፣ እያስታወሰችን ጭምር ነው፡፡
እንደሚታወቀው አገራችን ኢትዮጵያ በረጅም ዘመን ታሪኳና በገናና ሥልጣኔዋ በርካቶችና ጠላቶቿም ጭምር ሣይቀር እንደመሰከሩላት የሰው ልጆች ኹሉ የፍቅር እጇን ዘርግታ የተቀበለች፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ግዞት፣ ስደትና ሞት የታወጃበቸውን የሰው ፍጥረትን ኹሉ የምትታደግ ለፍቅር፣ ለእውነትና ለፍትሕ የቆመች አገር መኾኗንም እንድናስታውስ የሚያተጋን፣ የሚቀሰቅሰን ነው፡፡
ለአብነትም የነቢዩ መሐመድ ተከታዮች በዐረቢያ ምድር ሞት በታወጀባቸው ጊዜ ነቢዩ ፍትሕና ፍቅር ወደነገሠባት የሐበሾች ምድር ይሰደዱ ዘንድ ነበር ለተከታዮቻቸው ያስታወቋቸው፡፡ በእውነትም ክርስቲያኖቹ አክሱማውያን እነዚህ ሰዎች በክብር ተቀብለውና አስተናግደው ነበር በሰላም ወደ አገራቸው የሸኟቸው፡፡ በሰውነታቸው አልቃና አክብራ፣ በሃይማኖት አስተምህሮዋ እግራቸውን አጥባና ፍቅርን አስተምራ ያስተናገደች፣ ሰላምና ፍቅርም የኢትዮጵያዊነት መለያና ሰንደቅ ዓላማ ነበር፣ ነውም!!
በሌላ የታሪካችን ገጽም ድንበር ጥሶና ውል አፍርሶ፣ የኢትዮጵያን ሕዝብን ንቆና ተገዳድሮ ማን ወንድ ነው ከፊቴ የሚቆመው በሚል ትእቢት ከሮማ ምድር ወደ ሐበሻ መሬት ገሥግሦ የመጣውን የቀኝ ገዢውን የኢጣሊያን ኃይል አባቶቻችን ውርደትና ሽንፈትን ካከናነቡት በኋላ ለአውሮፓ አገራት ነገሥታትና የሃይማኖት መሪዎች በጻፉት ደብዳቤያቸው ፍቅርንና ይቅርታን ነበር ያወጁት፡፡
ዐፄ ምኒልክ ከድሉ በኋላ ለፈረንሳይና ለሩሲያ ነገሥታትና ለሮማው ፖፕ በጻፉት ደብዳቤያቸውና ባስተላለፉት መልእክታቸውም፡- ‹‹በድንቁርናቸው ብዛት የእነዛ ሁሉ ክርስቲያኖች ደም በከንቱ በመፍሰሱን እያየኹ ድል አደርኩ ብዬ ደስ አይለኝም፡፡›› ነበር ያሉት፡፡ ንጉሡ እንደውም ኢጣሊያውያኑ ምርኮኞችንም በበቤተ መንግሥታቸው አቅራቢያ አስፍረው ራሳቸውና ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ ነበር ሲንከባከቧቸው የነበረው፡፡ እንደእነ በርክሌይ ያሉት አውሮፓውያን ጸሐፊዎችና የታሪክ ተመራማሪዎች ሣይቀሩ ይህን በምሕረት የሰለጠነ የኢትዮጵያ ሠራዊት በልዩ ክብር አድንቀው ነው የጻፉለት፡፡
ይህ ታሪክ በወርቀ ቀለም የከተበው የኢትዮጵያዊነት እውነተኛ ማንነት ከፈጣሪው ዘንድ ቃል ኪዳን የተቸረው፣ ከቂም በል የጸዳ፣ ለእውነትና ለፍትሕ የሚቆምና የሚከራከር፣ ፍቅርና ይቅር ባይነት የገነነበት ማንነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነትም ከፈጣሪ የተቸረ ነጻነት ያበበበት የቃል ኪዳን ምድር ነው፡፡ ይህ ነጻነትም በአባቶቻችን አኩሪ ተጋድሎ በደም የጸና ግዙፍ ታሪክም ነጻነታቸውን የሚያፈቅሩ፣ ሰብአዊነትን የተላበሱ፣ የመንፈስ ልእልና ላይ የደረሱ የሰው ልጆች ሁሉ የሚጋሩት፣ የሚኮሩበት ከአድማስ አድማስ የናኘ የነጻነት ክቡር መንፈስ እንደሆነ ከግሪክ ጠቢባንና ፈላስፎች እስከ ጥንቶቹ ታላላቅ የታሪክ ጸሐፍትና ምሁራን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ እስከ ቅዱስ ቁርአን በአንድነት የመሰከሩለት ነው፡፡
ኹላችንም ልንኖርባት በተሰጠን በዚህች ምድር ላይ በልባችን ውስጥ ባለ በመለኮታዊው ብርሃን ጨለማውን እያሸነፍን፣ ጽልመትን የምንገፍ የብርሃን ልጆች፣ የክፋትን ኃያላትንና ክፉዎችን በመለኮታዊ ፍቅር ድል የምንነሳ፣ መንፈሳዊ አርበኞች የመኾን ክብር ከፈጣሪ ዘንድ ተችሮናል፡፡ ተጋድሎው፣ መንፈሳዊ አርበኝነቱ፣ ትዕግሥቱና ጽናቱ ትናንትና የተጀመረ አይደለም፡፡ በክርስትና ታሪክ እልፍ አእላፋት የወንጌልና የኢየሱስ ምስክሮች በዚህ መንገድ አልፈው ሕያው የሆነ ኹሉን በፍቅር የሚማርክ የፍቅርን ሐውልት ለዘላለም አቁመው በክብር አልፈዋል፡፡ የእነዚህ አባቶቻችንና እናቶቻችን የፈሰሰ ደማቸው ለፍቅር፣ ለእውነት፣ ለፍትሕ የቆሙ፣ የተከራከሩ እልፎችን ብዙዎችን አብቅሏል፣ አፍርቷል፡፡
ምንም እንኳን በወገኖቻችን ላይ በደረሰውን አሰቃቂ የኾነ ግፍ ኀዘናችን ጥልቅና መሪር ቢሆንም እምነታችን በተግባር የሚፈተን፣ ፍቅራችን በሥራ የሚገለጽ፣ መጽናናታችን የበዛ፣ ተስፋችንም ሰማያዊና የጸና ነው፡፡ በዚህ ኹሉ ግን ትናንትና፣ ዛሬም ወደፊትም የበቀል ሰይፋችን ግን ፍቅርና ፍቅር ብቻ ነው!! የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በዚህ የአምላኳ አስተምህሮ መሠረት ለነፍሰ ገዳዮቹ የአይ ኤስ ቡድን በትሕትና የፍቅርንና የንስሓ ጥሪን በእንባ አስተላልፋለች፡፡
እኛም ክርስቲያኖች በደማቸው ፍቅርን ሠርተውና ኑረው ሕያዋን ምስክር ሆነው እንዳለፉት የሃይማኖት አርበኞችና ሰማዕታት፣ በዘመናችንም ለትውልድ ምስክር እንደሆኑት እንደእነ ማንዴላ፣ ማርቲን ሉተርና ማኅተመ ጋንዲ ሁሉ የጠላቶቻችን ልብ የሚያቀልጠውን፣ የሚያርደውንና ከፊቱ ችለው መቆም የማይቻላቸውን የፍቅርን የበቀል ሰይፍን እናነሳለን ዛሬም፣ ነገም፣ ሁሌም!!
‹‹ሰይፍህን አንሣ የአባቶችህን፣
እግዚአብሔር ይመስገን ባይ ሕዝብ ያደረገኽን፡፡
ሰይፍህን አንሣ፣ በል ጊዜ የለም፣
በክፋት ካራ እንዳትቀደም፡፡
የዘላለም ትጥቅ የዛሬው መከታ፣
የፍቅር ካራ ነው እርሱን ይዘህ ውጣ፡፡
ሰይፍህን አንሣ ክተት ሠራዊት፣
ዝመት ለፍቅር ሰልጥን ለምሕረት፡፡›› (ዘሪቱ ከበደ)

ሰላም!

3 comments:

 1. please do not write....your way of writing is very nasty and crazy.....find out another job pls......I will give you as more amount of money as possible....

  ReplyDelete
 2. መናጢ ደሃ መሆንህን አላወቅኽም እንዴ? ከየት ዘርፈህ ነው ገንዘብ የምትሰጠው?

  ReplyDelete
 3. እኔ እኮ ዲያቆን መስለከኝ ነበር::ዝም ብለህ ትቀላቅላለህ እንዴ? አንዴ ፓትርያርክ እንደዚህ አሉ አንዴ የማንንም መናፍቅ ሙዚቃ ትንታኔ....እረ ባክህ ና እና ካህናትን አግዝ...በቅዳሴው ተሳተፍ.
  ሙዚቃ ከመተርጎም ወደ መጽሐፍትን መተርጎም ተሸጋገር::
  ሙዚቃ ከመተንተን ወደ አንድምታው ወደ መጽሐፍ ቤቱ ወደ ጉባኤው ና::
  ሙዚቃ ከማዳመጥ መዝሙር አዳምጥ::
  ዓለማዊ ሙዚቃ ከዚህ ገጽ ላይ ከማስነበብ መንፈሳዊ መዝሙር እና ስብከት አሳየን::እንደዚያ ካልሆነ የነ ዲያቆን ቀዳሜ ሰማእት እስጢፋኖስን ማዕረግ ለቀቅ!

  ReplyDelete