Thursday, June 11, 2015

‹‹ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ይሆናል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት፡፡››፡- በቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስፍራው ወዴየት ይሆን?!››በዲ/ን ኒቆዲሞስ
ባለፈው ሳምንት ‹‹በቤተ ክርስቲያናችን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስፍራው ወዴየት ይሆን?!›› በሚል ባቀረብኩት ሐተታ ላይ ተመርኩዞ አንድ ስለ  ቤተ ክርስቲያኔ ያገባኛል የሚል ግለሰብ በኢሜይል አድራሻዬ ስድብ ቀረሽ አስተያየቱንና ዘለፋውን አደረሰኝ፡፡ እንደዚህ ዓይነቶቹ በሃይማኖት ስም ወደለየለት ጽንፈኝነትና አክራሪነት ውስጥ የገቡና ከእኛ በላይ ሃይማኖተኛ ማን ነው ባዮች፣ ከቃላት ውርጅብኝ በላይም ዘገር ነቅንቀው፣ ጦር ሰብቀውና ሰይፋቸውን መዘው ዘራፍ ለማለት ወደኋላ የሚሉ አይደሉም፡፡
በአንድ ወቅት በዕውቀቱ ሥዩም በጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ ላይ ተመርኩዞ በባህላችን ዙርያ ባሰነበበው ሞጋች መጣጥፉ ምክንያት የደረሰበትን የስድብ ውርጅብኝና ዱላ ያስታውሷል፡፡ በወቅቱ ቤተ ክርስቲያናችንን ደፍሯል፣ ቅዱሳን አባቶቻችንም አቃሏል በሚል ብርቱ ቅናትና ቁጣ ተነሳስተው የደበደቡትን ጎረምሶች ለመፋረድ ፍርድ ቤት የቀረበው በዕውቀቱም ለክቡር ፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ፡-
‹‹የቀደመው ትውልድ የአሳብ ልዩነትን በሰይፍ፣ በጠመንጃ ነበር የሚፈታው ዛሬው የእኔ ትውልድ ደግሞ በጥቂቱም ቢሆን ተለውጦና ዕድገት አሳይቶ የአሳብ ልዩነትን በቡጢና በዱላ ለመቋቋም መነሣቱ አንድ መሻሻል ነው፡፡›› ሲል ነበር የቆምንበትን የጥላቻና የጽንፈኝነት ጥግ ሊያሣየን የሞከረው፡፡
መቼም ይህ ዓይነቱ አካሔድ የተለመደና ብዙዎቻችን የአዋቂነት፣ የመንፈሳዊ ጀግንነነት/አርበኝነት መለኪያ/መታወቂያ አድርገን የወሰድነው ነገር ስለሆነ እምብዛም አያስገርምም፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስም የተቋቋሙና የቁጥራቸው ማነስ እንዳለ ሆኖ አሉ የሚባሉትም ከጥቂቶቹ በቀር እነዚሁ ድረ-ገጾችና የመጦመሪያ መድረኮች በመንፈሳዊነት ስም ጀብደኝነትን፣ ስድብን፣ ማዋረድን፣ ጥላቻን፣ መለያየትን… ወዘተ የሚያራግቡ ጽሑፎችን፣ መረጃዎችን፣ አስተያየቶችን ለማስተናገድ እንግዳ አይደሉም፡፡
እነዚህን ድረ-ገጾችና የመጦመሪያ መድረኮች የሚከታተሉ በርካታ አንባብያንም በሚሰጧቸው አስተያየቶችና ምላሾችም ይኸውን የጀብደኝነት፣ የጥላቻ፣ የስድብና የውርጅብኝ መንገድ የሚከተሉ ናቸው፡፡ አሳብን በአሳብ ከመሞገት፣ በትሕትናና በፍቅር ከማስተማርና ከመገሠጽ ይልቅ የግለሰቦችን ስምና ሰብእና ማዋረድ፣ ማጥላላት፣ ማናናቅ፣ መፈረጅ… ወዘተ ማስተማር፣ ማሳወቅ፣ ድል ማድረግ የሚመስለንና ስሜታዊነት የሚነዳን ጸሐፍትና አስተያየት ሰጪዎች ቁጥራችን በርካታ ነው፡፡
ከእኛ በላይ ኦርቶዶክሳዊ፣ ለተዋሕዶ ተቆርቋሪስ ማን ነው የምንል ‹‹ለአሚነ ሥላሴ›› የምትበቃ ጥቂት እውቀትን ይዘን፣ ከፍቅርና ከትሕትና ይልቅ ትዕቢትንና መታጀርን ጌጥ አድርገን (አባ ሕርያቆስ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ቅዳሴው፡- ‹‹እንግዲህ ሞትን የምታለብስና ወደ ሲኦል የምታወርድ ትእቢትንና መታጀርን ጌጥ አናድርግ፡፡ … እንግዲህ እንደ ማርያም ትዕግሥትንና አርምሞን ጌጥ እናድርግ ማርያምስ የማይቀምዋትን በጎ እድል መረጠች ብሎ ጌታችን አመስግኑዋታልና፡፡›› እንዲል) በሌሎች ላይ ስድብን፣ ንቅትንና፣ ፍርድን የምናስተላለፍ ሰዎች በእውነት በእጅጉ እናሳዝናለን፡፡

ይህ የግብዝነት፣ የፈሪሳዊነት የክፋት አካሔድ ደግሞ ከግለሰብ እስከ ማኅበርና ተቋም ድረስም የዘለቀና ሥር የሰደደ ነው፡፡ እናም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስም የተቧደኑ ሰዎች በግልና በማኅበር ሆነው አንዱ ሌላውን በማውገዝና በማጥላላት በድረ-ገጾች፣ በመጦመሪያ መድረኮች፣ በሕትመትና በሶሻል ሚዲያው የሚጽፏቸው ጽሑፎች፣ የሚሰጧቸው አስተያየቶች ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ምናልባት በዚህ አንገብጋቢ ርእሰ ጉዳይ ላይ በሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበት ይሆናል፡፡
ለዛሬ ግን ይህችን ትዝብቴን ቋጭቼ ባለፈው ሳምንት ወደ ጀመርኩት ጽሑፌ ከማምራቴ በፊት ግን እኛ ክርስቲያኖችና ሚዲያዎቻችን/መገናኛ ብዙኃኖቻችን የገባነበትንና ያለንበትን ዝቅጠትና የሞራል ውድቀት የሚያሳይ ከአንድ በቅርቡ ከቀረበ ጥናታዊ ጽሑፍ ጥቂት መስመሮችን ብቻ ልጥቀስ፡፡
የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አዘጋጅቶት በነበረውና ‹‹የክርስቲያናዊ ሚዲያ አገልግሎት›› በተሰኘው ሲምፖዚየም ላይ ‹‹የመረጃ/የመገናኛ አውታርና ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር›› በሚል ርእስ በመንበረ ፓትርያርክ የቤተ መዝክርና የቤተ መጻሕፍት ዋና ሓላፊና በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተመራማሪ የሆኑት መ/ር ዳንኤል ሰይፍ ሚካኤል ባቀረቡት በጥናታዊው ወረቀታቸው ላይ ከሥነ ምግባር አንጻር የክርስቲያን ሚዲያው (አጥኚው በዚህ ጥናታቸው የሌሎችንም እምነት ድርጅቶችንም ማካተታቸውን ልብ ይሏል)  ያለበትን ጉድለትና አደገኛ አካሄዱን እንዲህ ሲሉ ነበር የገለጹት፡-
‹‹የእኛ የክርስቲያኖች ሚዲያ (በዋናነት የሕትመት ሚዲያውንና እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ስም የተቋቋሙ  ብሎጎችንና ሶሻል ሚዲያውንም ጨምሮ መሆኑን ልብ ይሏል) በዓለማውያን ዘንድ ብዙም የማይታየውን፣ ከማያምኑ ሰዎች እንኳን የማይጠበቀውን ሥራ በማስተናገድ፣ የስድብ፣ የድብድብ፣ የጠብ፣ የጥላቻ፣ የነገር፣ የሥጋትና የትርምስ፣ የሐሰት፣ ኃላፊነት የጎደለው፣ የስንፍናና የደካማነት መገለጫ በመሆን እንኳን የምናመለክውን አምላክ ክብርና የቤተ ክርስቲያን ዓላማ ሊገልጽ ይቅርና አንድ በሰለጠነ ዓለም የሚኖር የ፳፩ኛው ክ/ዘመን አዋቂ ሰውን ገጽታ የሚያስገምቱ ሆነው ይገኛሉ፡፡››
‹‹ምንም እንኳን በድረ ገጾች፣ በብሎጎችና በሶሻል ሚዲያው ላይ ብዙ በጎ ነገር እየተጻፈ ቢሆንም፤ በአሁኑ ጊዜ በመንፈሳዊነት ስም የሚጻፉ አንዳንድ ጽሑፎችና የሚሰጡ አስተያየቶችና ምላሾች አጠቃላይ መልክ ስናጤን በምእመናን መካከል ጠብ የሚጭሩ፣ የራስን እምነት በትሕትና ከማስረዳት ይልቅ በሌሎች አስተምህሮና ሥርዓት ላይ ሥልቅና ትችት የሚያበዙ፣ የስሜት ትኩሳት በእጅጉ የሚያይልባቸው … ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሕሊና እውነታ በላይ የቡድን ታማኝነት የሚሸንፋቸው፣ ከብርሃን ይልቅ ሙቀትን/ስሜታዊነትን የሚጨምሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡››
ንግባዕኬ ኀበ ጥንተ ነገር እንዲል ባለፈው ሳምንት ጽሑፌ ዓላማው በክርስቶስ ደም የተዋጀችውን ንጽሕትና ቅድስት የሆነችውን ሐዋርያዊት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ዶግማዋንና ቀኖነዋን፣ ሥርዓትዋንና ትውፊቷን የማጣጣል፣ የማራከስ ጉዳይ አይደለም፡፡ በጽሑፌ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከቤተ ክርስቲያናችን የአዋልድ መጻሕፍት ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በቤተ ክርስቲያናችን ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ማይጠራበት፣ ማይመሰገንበት፣ የማይወደስበት አገልግሎት የለም፡፡
እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንቶች አስተምህሮም፣ ‹‹እግዚአብሔር ስንል አብን፣ ወልድን እና መንፈስ ቅዱስን›› ማለታችን መሆኑንም አልሳትኩም፡፡ ግና በአንደበታችን አብዝተን የምንጠራው መንፈስ ቅዱስ በተግባር ግን ከእኛ የራቀ ስለመሆኑ የእለተ እለት ሕይወታችን ምስክር መሆኑን በቤተ መቅደሱ በነገሠው ዘረኝነት፣ መለያየት፣ ሙስና፣ ዝርፊያ፣ በልባችን ውስጥ በተንሰራፋው ዓመፃ፣ በደልና ኃጢአት የተነሣ መንፈስ ቅዱስ ከመካከላችን የተሰደደ መሆኑን ግብ ያደረገ/የሚያጠይቅ መጣጥፍ ነው፡፡
ይህን የመወያያ አሳብ ፍሬ አሳብ በልቦናችን ይዘን በመንፈስ የተወለድንባት ቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ እኛ ራሳችን ከየት እንደወደቅን እያሰብን፣ ከየት ሥፍራ እንዳለን እየመረመርን በፍቅር፣ በቅን ሕሊና፣ በየዋህነት መንፈስ አብረን እንዝለቅ፣ አብረን እንቆይ፡፡ በዛሬው ቆይታችንም ከመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ይልቅ የሥጋ ፍሬና እርኩሰት እጅጉን ጎልቶና አይሎ በሚታይባት ቤተ ክርስቲያናችን መንፈስ ቅዱስ ከመቅደሱ/ከመካከላችን ስለመሰደዱ የሚጠቁሙ አንዳንድ ማሳያዎችን ልጥቀስ፡፡
1.   የመንግሥትና የፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነትና ውሣኔ ማዕበል እያናወጣት ያለች የኖኅ መርከብ
ፖለቲካና ፖለቲከኞች፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት፣ መለያየትና መከፋፈል እየናጣትና እያናወጣት በምትገኘው የኖኅ መርከብ/ቤተ ክርስቲያናችን ሕጋዊ ሲኖዶስ፣ የአገር ቤቱ ሲኖዶስ፣ ገለልተኛ… ወዘተ በሚል አባቶቻችን ተለያይተውና ተነጣጥለው ባሉባት ቤተ-መቅደስ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አላዘነም፣ አልተሰደደም የሚል እርሱ አልሰማም፣ አላይም ብሎ አውቆ የተኛ ዳተኛ/ሰነፍ መሆን አለበት፡፡ እስቲ ያነሣሁትን ርእሰ ጉዳይ ለማጠናከር ቤተ ክርስቲያን የምትገኝበትን እውነታ ከትናንትና የዳጎሰ ታሪኳና አሁን ካለችበት/ከምትገኝበት አጠቃላይ ኹኔታዋ በመነሣት በጥቂቱ ለመፈተሽ እንሞክር፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በስፋት ያጠኑት፣ በሞት የተለዩን የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ምሁርና ‹‹Church and State›› በሚለው ድንቅ መጽሐፋቸው የሚታወቁት ዕውቁ የታሪክ ሊቅ ፕ/ር ታደሰ ታምራት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከረጅም ጊዜያት በኋላ ራሷን ለማስተዳደር በጀመረችው ጉዞ ያገጠማትን እንቅፋቶችና ቀውሶች ሲገልጹ፡-
‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ራሷን ቻለች በተባለችባቸው ኀምሳ ዓመታት ከግብፅ ጥገኝነት ብትላቀቅም በተቃራኒው ግን በመንግሥት ላይ ሙሉ በሙሉ ጥገኛ ወደ መሆን መሸጋገሯን፡፡›› በመግለጽ የቤተ ክርስቲያኒቱን የኀምሳ ዓመታት ራሷን የማስተዳደር ጉዞዋ፣ ‹‹ፍፁማዊው ከነበረው የውጭ ጥገኝነት፣ ፍፁማዊው ወደሆነው የውስጥ/የመንግሥት ጥገኝነት የተሸጋገረበት ነው፡፡›› በማለት በአጭር ቃል ፖለቲካው በቤተ ክህነቱ ያሳደረውን ትልቅ የሆነ ተጽዕኖ ገልጸውታል፡፡
በቤተ ክህነቱና በቤተ መንግሥቱ መካከል ስለነበረው ግንኙነት የዳጎሰ ታሪክና ይህም በተለያዩ ዘመናት ስላስከተለው ቀውስ ወደኋላ ሔዶ ለመተንተን ጊዜውም ሆነ ገጹ የሚፈቅድልኝ አይመስለኝም፡፡ ግና ለማሳያ እንዲሆን መንግሥትና ቤተ ክህነቱ በአዋጅ ከተለያዩበት የቅርብ ዘመን ታሪክ ልጀምር፡፡
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ምዕራፍ ከ፲፱፻፷፮ቱ አብዮት ፍንዳታ በኋላ በይፋ መንግሥትና ቤተ ክህነት ተለያይቷል ተብሎ ቢታወጅም ወታደራዊው መንግሥት ደርግ በዚህ ዐዋጅ ማግሥት በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ ረጅም የሆነ እጁን አስገብቶ የቤተ ክርስቲያኒቱን ፓትርያርክ የሆኑትን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን በማጋዝ በመጨረሻም በአሰቃቂ ኹናቴ በገመድ ታንቀው እንዲገደሉ በማድረግ ዐዋጁን በመሻር ኢሰብአዊነቱን፣ ወደር የለሽ ጭካኔውንና ግፉን በተግባር አሳይቷል፡፡
በፓትርያርኩ ላይ ለተላለፈው የግድያ ዕርምጃ ዕውን መሆን ለደርጉ የልብ ልብ የሰጠው በወቅቱ የነበሩት የቤተ ክህነት ሰዎች እንደነበሩ ዛሬም ድረስ በቁጭት የሚናገሩ አባቶች አሉ፡፡ በቤተ ክህነቱ የነበሩ አባቶችና አገልጋዮች ለዚህ የጭካኔ ዕርምጃ በፊርማቸው ጭምር ሣይቀር ፈቃደኝነታቸውን መግለጻቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አቶ አበራ ጀንበሬ ‹‹የእስር ቤቱ አበሳ›› በሚል በጻፉት ድንቅ መጽሐፋቸው እንደገለጹት ቤተ ክህነቱ ለፓትርያርኩ ፊቱን አዙሮባቸው እንደነበር ነው የሚተርኩት፡፡
በወታደራዊ ደርግ ዘመን መንፈሳዊ መሪዋን ያጣቸውና በብዙ መከራና ጭንቅ ውስጥ ያለፈችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የደርግ መንግሥት በወደቀ ማግሥት ደግሞ ሌላ ወደረኛ፣ ብርቱ ጉልበተኛ የሆነ ኃይል ነበር ያጋጠማት፡፡ የኢሕአዴግ ሠራዊት ደርግን በጣለ ማግሥትም በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ደማቅ አሻራ ያላትን የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን እንዲሁ ብቻዋን ሊተዋት አልፈቀደም፡፡ ከበረሃ ጀምሮ ማርክሲስት ነኝ ሲል የነበረው ኢሕአዴግ ከሚከተለው ርእዮተ ዓለም ተቃራኒ በሆነ መልኩ መንፈሳዊ ካባውን ደርቦ ወደ ቤተ ክህነቱ ጎራ በማለት በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ውስጥ ሆኖ ማያውቅ ሌላ ክፉ የታሪክ ጠባሳን ተወ፡፡
‹‹በሕመም ምክንያት ነው›› በሚል ሰበብ መንግሥት የቤተ ክርስቲያኒቱ ፓትርያርክ የነበሩትን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን ከሥልጣናቸው አስወግዶ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ተካ፡፡ ምንም እንኳን መንግሥት በሕመም ምክንያት ነው ቢልም ይህ ዕርምጃው የለየለት፣ ግልጽ የሆነ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት መሆኑ ግን ሳይውል ሳያድር ለሁሉ ታወቀ፡፡
በአሜሪካ አገር በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑ ዶ/ር ዋለ እንግዳአየሁ ከጥቂት ዓመታት በፊት The Ethiopian Orthodox in the Diaspora: Expansion in the Midst of Politics, Religion, and Schism በሚል ርእስ ባስነበቡት ፴ ገጽ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ምስጢራዊ ሰነዶችን እየበረበረ ይፋ የሚያደርገውን የዊክሊክስ መረጃ ዋቢ በማድረግ እንደጻፉት፣ ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ በመንግሥት ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነትና ግፊት ከሥልጣናቸው እንደተወገዱ ጽፈዋል፡፡
ዶ/ር ዋለ እንግዳየሁ በዚሁ ጥናታዊ ጽሑፋቸው የወቅቱን እውነታ እንዲህ ይጠቅሱታል፡-
Wikileaks began publishing the Global Intelligence Files in February 2012, encompassing over five million e-mails. One of the e-mails, containing data from U.S. State Department diplomatic cables classified as confidential and covering the period between July 2004 and late December 2011, revealed that the former Prime Minister of the TPLF-led government had in fact dethroned the Patriarch with his order Tamerat Layne, (1991-1995).
ዶ/ር ዋለ እንደሚሉት ጠቅላይ ሚ/ር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ይሄን ጉዳይ በወቅቱ የአሜሪካ አምባሳደር ከሆኑት ዶናልድ ያማማቶ ጋር በተነጋገሩበት ጊዜ እርሳቸውና መንግሥታቸው በፓትርያርክ አቡነ መርቆሪዮስ ላይ ስለወሰደው ፖለቲካዊ የግፍ ዕርምጃ መጸጸታቸውን እንዲህ ገልጸውላቸዋል፡-
When the ex-Prime Minister met Donald Yamamoto, who served as U.S. Ambassador to Ethiopia from 2006 to 2009, he confided to the Ambassador that he regretted the action he took in regards to the Ethiopian Orthodox Church “…because he signed the order that removed the original patriarch and bifurcated the church.”
ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስን አውርዶ በፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ የመተካቱ ሂደት በመንግሥት በኩል በሚገባ የተጠናና ትልቅ ፖለቲካዊ ስሌት/ፋይዳ የነበረው ጉዳይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በየዘመኑ የሚመጡ መንግሥታት ሁሉ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ እንዲህ እንዳሻቸው የወደዱትን ለማድረግ የቤተ ክህነቱ ተለማማጭና ከመንግሥት ጥገኝነት ለመላቀቅ ፈቃደኛ አለመሆኑም ሊሰመርበት የሚገባው ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ የመንግሥትና የፖለቲከኞች ጣልቃ ገብነትና እኩይ ዓላማ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ፈታኝና አስቸጋሪ የሚባል ጊዜን ነው ያሳለፈችው፡፡
መራሩ እውነታ ግን አሁንም ድረስ ቤተ-ክህነቱ ፖለቲከኞች እንዳሻቸው የሚዘውሩት፣ የሚያሽከረክሩት ተቋም ከመሆን መላቀቅ አልተቻለም፣ እንዲላቀቅም የሚፈለግ አይመስልም፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ባሉ መንፈሳዊ መሪዎችና አባቶችም ትልቅ ቦታ ተሰጥቶት የሚሰማውና የሚፈራው መንፈስ ቅዱስ ሣይሆን መንግሥትና መንግሥት ብቻ እየሆነ መጥቷል፡፡ ያለፉት ሃያ ዓመታት ያሳየን እውነታ ቢኖርም ቤተ ክህነቱ በመንግሥት ሳምባ የሚተነፍስ ተቋም መሆኑን ነው፡፡
የታሪክ ተመራማሪው ፕ/ር ታደሰ በጥናታቸው እንደገለጹት ባለፉት ሃያ ዓመታት ነፍሰ ኄር ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ‹‹ከመንግሥት ጋር የነበራቸው የሚባለው የጠበቀ ግንኙነት፣ መንግሥትም በበኩሉ ለይስሙላ ያህል ጣልቃ እንደማይገባ ለማሳየት በሚል የቤተ ክርስቲያኒቱን ውስጣዊ ጉዳዮች በሙሉ ለራሷ ትቻለሁ በሚል ድብቅ አጀንዳ አስተዳዳራዊ ድክመት ወደ አስተዳዳራዊ ቀውስ እንዲሸጋገር መንገዱን አመቻችቷል፡፡›› በማለት ቤተ ክህነቱ የገባበትን ቀውስ፣ ድቀትና መንፈሰ እግዚአብሔር የተለየውን ሥጋዊ አካሔዱን በጥናታቸው በስፋት ገልጸውታል፡፡
መንፈስ እግዚአብሔር የራቀውን የተቋማዊ አሠራሩ ድክመት ባልተቀረፈበት በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ለረጅም ዓመታት በመንበሩ ላይ ቆዩት ፓትሪያሪክ አቡነ ጳውሎስ ከትምህርታቸውና ከውጭ ዓለም ልምዳቸው በመነሳት ስር ነቀል የሆነ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው ቢታሰቡም የተጠበቀውን ያህል የቤተ ክህነቱን መንፈሰ እግዚአብሔር የተለየውን ተቋማዊ አሠራርና አሥተዳደር ከመሠረቱ ለመለወጥ ሳይችሉ ቀርተዋል ሲሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምሁራንና የቅርብ ታዛቢዎች ይተቻሉ፡፡
በእርግጥ የፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር መምጣት በዘመናቸው በአዎንታዊነት ሊጠቀሱ የሚችሉ በርካታ ታላላቅ ሥራዎችን መሥራታቸውና ቤተ ክርስቲያኒቱን በዓለም መድረክ በማስተዋወቅ ረገድ የተጫወቱት ከፍተኛ ሚና እንዳለ ቢሆንም መንግሥት እጁን ያስገባበት የፕትርክና ዘመናቸው በቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ ሁለት ሲኖዶሶች እንዲኖሩ በርን ከፍቷል፡፡ ዛሬም ድረስ እነዚህ ተለያይተው ያሉ አባቶቻችን አንዱ አንዱን ስም ላይጠራ ተማምለው ይኸው ተለያይተውና ተወጋግዘው ሁለት ዐሥርተ ዓመታትን ደፍነው ወደ ሦስተኛ ዐሥርተ ዓመት እየተጓዙ ነው፡፡
ከፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እረፍት በኋላ አንዳንች የሰላምና የዕርቅ ተስፋ ይኖራል ተብሎ የታሰበ ቢሆንም ብዙዎች የተመኙት የእርቀ ሰላም ጉዳይ እንደ ግንቦት ደመና በኖ ቀርቷል፡፡ በወቅቱ በአገር ቤትና በውጭ ያሉ አባቶችን ለማስማማት ተሰይሞ የነበረውን አስታራቂ ሽማግሌዎች ቡድንንም አንድ አንጋፋ የሕወሐት ታጋይ፣ ‹‹እነዚህ እናስታርቃለን የሚሉ ቄሶች ሊሰቀሉ ይገባል፡፡›› እስከ ማለት የደረሱበትን ቃለ መጠይቃቸውን እየመረረንና እየጎመዘዝንም ቢሆን ለማንበብ ተገደናል፡፡ ይህም አስተያየት የኢሕአዴግ መንግሥት በቤተ ክህነቱ ላይ ያለውን የመረረና የከረረ ፖለቲካዊ አቋም የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ዕርቅ የሚባለውን ነገር በጭራሽ ለመስማት የማይፈልገው፣ የማይፈቅደው መንግሥታችንም የተለያዩትን አባቶች አንድ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ገና በእንጭጩ ሣለ እንዲመክንና ፍሬ አልባ እንዲሆን ትልቁን ሚና ተጫውቷል፡፡ በዚህ መካከልም ከፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እረፍት በኋላ ወደ መንበሩ የመጡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስም የመጀመሪያ ሥራዬ በቤተ ክርስቲያኒቱ አባቶቻችን መካከል ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ መሥራት ነው ቢሉም፣ የዕርቀ ሰላሙ ጉዳይ ‹‹የውሾን ነገር ያነሳ …›› እንደሚባለው ሆኖ ቀርቷል፡፡ ለወደፊትም የሚነሳ አይመስልም፡፡
እናም ዛሬም በኢትዮጵያ ሲኖዶስ፣ በአሜሪካው ሲኖዶስ፣ በገለልተኛ፣ በቦርድ … ወዘተ የትግሬ፣ የጎንደሬ፣ የኦሮሞ … ወዘተ የሚባሉ አብያተ ክርስቲያናት በውጩ ዓለም እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ በአገር ቤትም ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪና አባት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስም ከመንግሥትና ከዘመኑ ፖለቲከኞች ሴራ ለማምለጥ የተቻላቸው አይመስሉም፡፡ ለአብነትም በቅርቡ በሊቢያ በሰይፍ ታርደው የተሠዉትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ልጆች በተመለከተ በቤተ ክህነቱ ዘንድ የታየው ዳተኝነትና የኋላ ኋላም በመንግሥት ይሁንታ አርፍዶ የተሰጠው መግለጫም ቢሆን ከአንድ ሐዋርያዊትና ጥንታዊት ከሆነች የሃይማኖት ተቋም ሣይሆን፣ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት በመጦመሪያ መድረኩ እንደገለጸው፡-
‹‹… የቤተ ክርስቲያኒቱን ክብር፣ ሥርዓቷን፣ ትውፊቷንና ባህሏን ከግምት ውስጥ ያላስገባ መንፈሳዊ ሽታ የሌለው፣ ደረቅና ሕይወት አልባ የሚመስል፣ በእጅጉ የመንግሥትና የፖለቲከኞች ፕሮፓጋንዳ የተጫነው የሚመስል የኀዘን መግለጫና የማጽናኛ መልእክት መሆኑን ነበር፡፡›› በኀዘኔታ ሆኖ የገለጸው፡፡
የዘመኑ የብሔር ፖለቲካ እያናወጣት ባለችው ቤ/ን ከአስተዳደራዊ ቀውሱ ባሻገርም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ የዓመፀኞች፣ የጠንቋዮች፣ የአማሳኞች፣ የሴረኞችና የጎጠኞች ምሽግ ወደመሆን እየተሸጋገረች ነው፡፡ በሂደትም ሙስና፣ ዝርፊያ፣ ጎሰኝነት፣ ሥርዓተ አልበኝነት፣ የሞራል ውድቀትና ዝቅጠት፣ የመንፈሳዊ ሕይወት መደብዘዝና መጥፋት… የቤተ ክርስቲያኒቱ ዋና መለያና መታወቂያ ሆኗል፡፡ መንፈሰ እግዚአብሔር ሣይሆን የሰው/የሥጋ ጥበብና እውቀት በቤተ ክርስቲያኒቱ እጅጉን ተንሰራፍቷል፣ አይሏል፡፡
‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡›› ‹‹በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ›› የሚለው የወንጌል ቃልና ትእዛዝ በዚህ ዘመንም ተዘንግቷል፡፡ በአንጻሩ መለያየትና መከፋፈል፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት ነው ቤተ ክርስቲያኒቱን ክፉኛ እያናወጣትና እየነጣት ያለው፡፡ ይህን ክፋትና ዓመፃ ሊያስወግዱ የተገባቸው ሃይማኖት መሪዎችና መንፈሳዊ አባቶችም ለእግዚአብሔር ቤት ከመቅናት ይልቅ ዝምታ ውጧቸዋል፤ አሊያም ራሳቸው የችግሩ መንሥኤና ሰለባ ሆነዋል፡፡
በመሠረቱ የቤተ ክህነቱን ተቋም የሚመሩ አባቶች፣ ሥጋቸውን የበደሉ፤ ለነፍሳቸው ያደሩ ናቸው ተብሎ ነው በብዙዎቻችን ምእመናን ዘንድ የሚታመነው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች/አባቶች ለጽድቅ ማለት ለእውነት እንዲሁም ለፍትሕና ለእኩልነት የቆሙ ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡ ለሀብትና  ለሥልጣን ግድ ስለሌላቸው ከዚህ ዓለም ጣጣ ውጭ ናቸውም ተብለው ነው የሚቆጠሩት፡፡
የሃይማኖት መሪዎች ለፍትሕ፣ ለስው ልጆች ነፃነትና እኩልነትም ድምፃቸውን የሚያሰሙ የእውነት ጠበቃዎች ናቸው፡፡ ልዩ ክብር በሚያሰጣቸው በመንፈሳዊ ሰብእናቸውና ሥልጣናቸው የተነሣም በእውነትና በፍትሕ ተቃራኒ የሚቆሙ መንግሥታትን፣ መሪዎችንና ክፉዎችን ሁሉ የመገሠጽና ፊት ለፊት የመቃወም መለኮታዊ ሥልጣን ከላይ ከአርያም የተቸራቸው እንደሆኑ ነው በአብዛኛው ምእመናን ዘንድ የሚታሰበው፣ የሚታመነውም፡፡ በተግባር እየታየ ያለው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡
እንደ እኔ እምነት ቤተ ክህነቱ አርአያ የሚሆን መንፈሳዊ መሪና አባት አጥቶ፣ በአብዛኛው መንፈስ ቅዱስን ያሳዘኑና የገፉ፣ የሞራልን ዋጋ የናዱ ሰዎች የሚፈነጩበት ተቋም ወደ መሆን ተሸጋግሯል፡፡ ይሄን በቤተ መቅደሱ የነገሠውን ዓመፃና ክፋት እያዩ ሌትና ቀን እንደ ሎጥ ጻድቅ ነፍሳቸውን አስጨንቀው ያሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ እውነተኛ መንፈሳዊ አባቶችና አገልጋዮችም በጾምና በጸሎት፣ በእንባ አምላካቸውን አቤቱ እባክህ ለቤትህ ራራ፣ ጅራፍህን አንሣ እያሉ በተማጽኖ ላይ ናቸው፡፡
እኛም ቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆችና አገልጋዮች ከእውነት፣ ከጽድቅ፣ ከፍትሕ ጋር በጽናት ከቆሙት ከእነዚህ አባቶቻችን ጎን ለመቆም ልንደፍር የሚገባን ጌዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁንና አሁን ይመስለኛል፡፡ መቼም በዚህ ሁሉ ቤተ መቅደሱን እያናወጠና ክፉኛ እየነጣ ባለው ዓመፃና ክፋታችን የተነሣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አላዘንም፣ አልተሰደደም ማለት ይቻለን ይሆን …?! በፍጹም አይመስለኝም!! እንደው የሰሞኑስ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና ምእመናን ሰልፍ፣ ሮሮና አቤቱታ፣ በአባቶችና በልጆች መካከል የተፈጠረው ልዩነትና መረጋገምስ ምንድን ነው የሚነግረን?!
በቀጣይ ጽሑፌ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስላሳዘንበትና ቅዱሱን የእግዚአብሔር ቤት እያረከሰ ስላላው በቤተ ክህነቱና በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች መከካል እንደ ሰደድ እሳት እየተስፋፋና እየተዛመተ ስላለው ሙስና፣ ዘረኝነት፣ ጎጠኝነት፣ ሴሰኝነት፣ ዝሙትና በግብረ ሰዶማዊነት ዙርያ ጥቂት ነገሮችን በማንሣት ለመመለስ እሞክራለሁ፡፡

7 comments:

 1. ኒቆዲሞ ዲ/ን ከሚባል ስምህ ፓስተር ለምን አትልም እራስህን እውነት እኮ ክርስቶስ ነው አቤት ብር እንደዚህ በሀሰት ያዘላብዳል አይደል ያልሆኑትን ያስመስላል ነው ሴጣን ጠፍጥፎ የሰራህ ቅናታም ነህ ለቤተክርስቲያን የምትቆረቆር መስለህ ብዙ መፃፍ ለምን እንደው በትክክለኛ ማንነትህ እውነተኛ የኦርቶዶክስ ልጆች እንደሚፅፉት ለምን አትፅፍም ሲልህ አባ ሕርያቆስ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ቅዳሴው ትላለህ ለማጭበርበር ሲልህ ፓስተር እከሌ በጥናታቸው ብለህ ስለቤተክርቲያን ትንሽ እንን የማያገባቸውን ትገለጻለህ እንደአንተአይነቱ ምን እንደሚባሉ ታውቃለህ ግራጴ ማለትም ግራ የገባው ጴንጤ ወይም ሆዳጴ ሆዳም ጴንጤ ነው የምንላቸው ከናንተ ምንም አይጠበቅም ለምን ፓስተር ተብዬህ በእመነቱ ውስጥ ስላሉት የሰው ሚስት ስለሚቀሙት የቤተክርስቲያን አገልጋዮች በዝሙት እንዴት ቤተክርስቲያቸው እንደቆሸሸች አያወሩም አንተንም ጨምሮ እነ ፓስተር ዳዊት፣ ዘማሪ ተከስተ፣ ፓስተር ወዳጄነህ መችም ትልልቹ አስተማሪዎቻችው ናቸው አይደል ስለነሱ አይወራም ዛሬም አፋችሁን ሞልታችሁ ታወራላችሁ የኛ ቤተክርስቲያ ግዴለም ተዋት እውነተኛ ስለሆነች ፈተናው ብዛ ነው እንደ ቤተክርስቲያን ግዴለም አንድ ቀን ይስተካከላል የራስህ ቤት ይጭነቅህ ያው ሴጣን ዘመቻ ቢከፍትም ነዚህ ነው እንዴ ወንጌለ አታስተምሩም ወንጌልን ማስተማር ከማቅ ብሎግ ተማሩ ሥራ ፈት ወሬ ለቃቃሚ ጴንጤ ለማጥፋት ቢጥርም ግን ማንም አያጠፋትም ፖለቲካውን ብቻ ፃፍከው እሳ የናንተ የተሐድሶ ዘመቻስ በፖለቲካ ስም ገብታችሁ የነ አባ ሰረቀ፣ የነኤልያስ ያው እኮ መንግሥትን ጠጋ ብላችሁ አይደል ጫፍ ይዛችሁ ደሞ እዩ ቤተክህነቱን ትላላችሁ ስታሳዝኑ ህሊና ያጣችሁ ለናንተ አዝነናል ግድ ነው እቺ በሁላችሁም ልትፈተን እርሶ ግን አጠፋም እናንተ እንጅ ክርስቶስ በደሙ ያዋጃት ነች

  ReplyDelete
  Replies
  1. በጣም የተመቸኝ ቃል ግራጴና ሆዳጴ አረ አነተስ ግራ የገባህ አይደለም ሆዳም ጴንጤ ነህ

   Delete
 2. ግብረ ሰዶማዊነት እኮ በተሐድሶ ብሶል ወንድም አሸናፊ መኮንን ተረሳ፣ የውጩ የኘሮቴስታን ቄሶች እርስ በርስ ያጋባችው አንግሎ ቸርች ከአሜሪካንማ እንምሰማው ብዙ ነው ተው አያውቁመ ብለህ ብዙ እንዳትዘላብድ መቼም ያው ያንተም እምነት የመጣው ከወደዛው ነው ብዬ ነው ሎተራውያን መሆንህ አይደል ከናንተ የሚብስ የላትም በእውነት ዛሬማ ጉድ እየሰማን ነው እኮ ፓስተሮቻችሁን ለመሆኑ ከላይ የገለጽከው ፓስተር ሰላም ነው በእርግጥ እሱስ የሰራው ነገር የለም አንተም ይሄኔ ከጠቀስቃቸው በአንዱ የተጨማለክ ነው በል እሱ የፍታህ

  ReplyDelete
 3. አያያያያያያያያገባህም ጴንጤ ስማ ያንተ ቢጤ አስመሳይ ጴንጤዎችና ሃይማኖት የሌላቸው ፖለቲከሄች እኮ ናቸው የሚሰርቁት የሚመዘብሩት ዘማዊዎች እንጂ የቤተክርስቲያን ልጆች እኮ እንዳልሆኑ ታውቀዋለህ እኮ ግብረሶዶማውያlም ይሀው እነማን እንደሆኑ በናንተው ብሎግ እየሰማን ነው ነእንደሱ ሲኖዶስ ማውገዝ አለበት ስማ እስቲ የቤተክርስቲያን ልጁ የሆኑት መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ አባባል ልንገርህ

  "....ሰው ራሱን መለወጥ ሲያቅተው ስረአት ለመለወጥ ይታገላል ራሱን ማደስ ሲያቅተው ሃይማኖትን ለማደስ ይታገላል።..የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ተሰርታ ያለቀች ናት ተሰርቶ ባለቀ ቤት ገብቶ መኖር እንጂ ይቀየር የማለት መብት የለህም በዝቷል ይቀነስ ረዝሟል ይጠር ተጣሟል ላቃና የሚባል ነገር የለም።ቤተ ክርስትያን ሰውን ታድሳለች እንጂ ሰው ሊያድሳት አይችልም።......" እወቅ እንዲህ ይነግርሃል ቁርጥ ያለውን አይንዘባዘብም እንዳንተ አይወሻክትም ግልጽና ቀጥተኛ ንግግር ገባህ

  ReplyDelete
 4. ለአቶ ኒቆዲሞስ
  በአንድ አፍ ሁለት ምላስ
  ምነው ባትደክም! የቤተክርስቲያኗ ልጅ አለመሆንህ በመጀመሪያውም ሆነ በዚህኛው ጽሑፍህ ግልፅ ነው። የእንትና ድንቅ ጥናታዊ ጽሑፍ፣ እንትና በድንቅ መጽሐፋቸው እንደፃፉት፣ ዲያቆን ዳንኤል በመጦመሪያው እንደተናገረው ሌላም ሌላም እያልክ ብዙ በውሸተኛ መሆንህን ለመደበቅና ለቤተክርስቲያን የቀናህ ለመምሰል ዳከርህ። ግን የእምነቷ ተፃራሪ ፤ የስርዓቷ ነቃፊ፤ የመጽሐፍቷና ገድላቷ አንቋሻሽ መሆንህን በመጀመሪያው ጽሑፍህ አረጋግጠሃል።
  በዚህ ጽሑፍ ተብዬህ የሰዎችን ችግርና የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ከዘከርህ ውጭ መንፈስ ቅዱስ የት እንደተሰደደ አልገለጽህም። ይህ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ በቤተ መቅደስ እንደሌለና በሰዎች ልብም አይታወቅም አይጠራም ብለህ የተናገርኸው ውሸትህን እንደሆነና አንተ ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነትና አስተምሮ ጠላት መሆንህን ነው የሚያሳየው።
  ምናልባት ለአንተ በውሸት መንፈስ ሙሌት መጮህ መዘላበድ፤ ማጓራት መንፈራገጥ ሊሆን ይችላል መንፈስ የምትለው። ለቤተክስቲያን ግን የሚያረጋጋ፣ የሚያስተምር፣ ወደ እውነት የሚመራ፣ የሚፈውስ፣ ማስተዋልን የሚሰጥ፣ በእምነት እንድንፀና ሐይልን የሚሰጥ ነው።
  ምናልባት ለአንተ የተናገውን የማያደርግ፤ እጅ ለእጅ ካልተያያዙ የማይፈውስ አጋንትንም የማያስወጣ ውሸተኛ መንፈስ ይሆናል የምትፈልገው። የቤተክርስቲያን መንፈስ መንፈስ ቅዱስ ግን የተናገረውን የሚያደርግ የታመነ እውነተኛ መንፈስ ነው። የቤተክርስቲያን መንፈስ መንፈስ ቅዱስ ሐይል የሌለው እጅ ለእጅ
  ካልተያያችሁ ፣፤ እነደፈለጋችሁ እርስ በርሳችሁ የእተዋወካችሁ ካልተንጫጫችሁ መፈወስም አጋንትንም ማስወጣት አልችልም የሚል መንፈስ አይደለም። ሃልና ማዳኑ በእጁ ነው። ወደደውን ያድናል ከአጋንት እሥረኛነት ነፃ ያደርጋል።
  መንፈስ ቅዱስ ፍጡር አይደለም የሚሰደደው። አንተ ለማሰደድ ሞክረህ ነበር። ግን ለማሰደድ አልቻልክም። መንፈስ ቅዱስ ሙሉ ነው። መንፈስ ቅዱስ በቤቱ በቤተመቅደስ፤ በክርስቲያኖች ውስጥና በቤተክርስቲያን አገልግሎት ሁሉ አለ። መንፈስ ቅዱስ አይሰደድም፤ ነገር ግን ክርስቲያኖች ሲበድሉ ሲረክሱ ያዝናል።
  እናም ወዳጄ ኒቆዲሞስ ያንተ ስላልሆነው ከምታወራ የማታፍርበትና የኔ የምትለው እምነት ካለህ ስለዛ እምነትህ ብትናገር ይሻልሃል። እኛ ግን "መንፈስን ሁሉ አትመኑ" ተብሏንና የአንተን ሐሰተኛ መንፈስ አንቀበልም። እናም ስለ ሌሎች መናገር ህይወትና ፅድቅ አይደለምና እራስህን ሁን።
  የሰዎች የትኛውም የስነምግባር ብሉሹነትና ክፉ ድርጊት የሰዎቹ እንጂ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት አይደለም። ነው ብለህ የምትፈርጅ ከሆ ደግሞ የጌታ ደቀመዝሙር የነበረው ይሁዳ ሌባ የነበረ ጌታውንም ከሌብነቱና ገንዘብን ከመውደዱ የተነሳ ለገንዘብ የሸጠ ነውና የክርስቶስ ኢየሱስ መገለጫ ነው እንደማለት ይሆናል ይቅር ይበልህና። የይሁዳ ድርጊትና ጥማት የራሱ የስጋው ምኞት እንጂ የክርስቶስ አይደለም።
  በመጨረሻ ደግሜ ላሳስብህ፦ ውሸት አያድንም እውነት እንጂ። ስለዚህ መዘላበዱን ተወውና እንደ ጠቀስኸው በውቀቱ ስዮም ቀልድ አሳመርሁ ገቢ ጨመርሁ ብለህ የሚያስፈርድብህን ከመናገር ተቆጥበህ ምንም እንደማያውቅ ጡት እንደሚጠባ ህፃን በትህትና ሆነህ እውነትን ፈልግ ተማርም።

  ReplyDelete
 5. ውሸት አያድንም እውነት እንጂ። ስለዚህ መዘላበዱን ተወውና እንደ ጠቀስኸው በውቀቱ ስዮም ቀልድ አሳመርሁ ገቢ ጨመርሁ ብለህ የሚያስፈርድብህን ከመናገር ተቆጥበህ ምንም እንደማያውቅ ጡት እንደሚጠባ ህፃን በትህትና ሆነህ እውነትን ፈልግ ተማርም YONI

  ReplyDelete
 6. ወዳጄ የምትፈልገው ነው እንዴ የምትጽፈው፤ለመሆኑ በዕውቀቱ በዚያ ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤት መች ቀርቦ ያውቃል፡፡ ነገሩ በፖሊስ ጣቢያ አይደል እንዴ ያለቀው፡፤ ደግሞስ ጎረምሶች ደበደቡት የምትለው፤ አንድ ሰው ብቻ ኮ ነው የተማታውም፣ የተከሰሰውም፡፡ የሌለ ከማምጣት ያው ይበቃህ ነበረ፡፡

  ReplyDelete