Friday, June 12, 2015

የደብረ ሲና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ችግር እየተባባሰ ነው፡፡አዲሱ ገበያ የሚገኘው የደብረ ሲና ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ ችግር እየተባባሰ መጥቷል፡፡ በአማሳኞቹ እከክልኝ ልከክልህ እርስ በርስ ተሸፍነው የቆዩት ብዙ ምስጢሮች እየወጡ ሲሆን የደብሩ አስተዳደርም እጅግ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮችን ለሀገረ ስብከቱ አሳውቋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ፦
ለቤተ ክርስቲያኑ በውርስ ባለ አንድ ፎቅ ቤት ከአንድ ግለሰብ ተሰጥቶ የነበረ ሲሆን የቤቱን ካርታ የተቀበለው በድብቅ ሽያጩን ያከናወነው እስጢፋኖስ ኃይሉ መሆኑ ታውቋል፡፡ ስንት ተሸጠ? ለማን ተሸጠ? የተሸጠው ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ነወይ? የሚሉት ወሳኝ ጥያቄዎችም መነሳታቸው ግድ ብሏል፡፡ ምክንያቱም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ የቤተ ክርስቲያንንን ንብረት አስተዳደሩ ሳያውቅ የሰበካ ጉባኤው ሊቀመንበርና እስጢፋኖስ ሲሸጡ በሀገረ ስብከቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይሆን እንዳልቀረ እየተነገረ ነው፡፡ ጉዳዩ ለሀገረ ስብከቱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ሙስና የተጋለጠው ሌሎች ችግሮችን ተከትሎ በወጣው ምስጢር ነው፡፡
ሌላው ውሳኔ ሥዕል በማሳል ሊያገኙ የነበረውን የሙስና ገንዘብ የደብሩ አስተዳደር በወሰደው ፈጣን እርምጃ ታግዶ ለሀገረ ስብከቱ ማሳወቁ ነው፡፡ ይህም ደብሩ ሳያውቀውና ለጨረታ ሳይቀርብ ሊከናወን የነበረ ድርጊት ነው፡፡ የቤተክርስቲያኗን ትውፊት ጠብቀው ሊስሉ የሚችሉ የማቅ ሰዓሊያን ናቸው በሚል ምክንያት በከፍተኛ ገንዘብ ሥራውን ሊሰጡ አቅደው የነበረ ቢሆንም ደብሩ በማገዱ ውጥናቸው ከሽፏል፡፡
የደብሩ አስተዳደር ለ13 ዓመት አንድም ቀን ኦዲት ተደርጎ የማያውቀውን የሕንጻ አሠሪውን ኮሚቴ ኦዲት እንዲደረግ በቅርቡ ለሀገረ ስብከቱ በጻፈው ደብዳቤ መሠረት በማሳወቁ ይህም በቅርቡ ተፈጸሚ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ እያስጨነቀው ያለው የአማሳኙ ቡድን ባለፈው እሁድ ዕለት በተደረገው የሰንበት ት/ቤት ስብሰባ ላይ አቶ ይድነቃቸው መኮንን  በ60 ዓመቱ የሰንበት ት/ቤት አባል ነኝ ብሎ ገብቶ ከአጀንዳው ውጪ በመዘባረቅ አምልጦት ሕንጻው እስካሁን 16 ሚሊዮን ብር እንዳወጣ የገለጸ ሲሆን ይህን ጉዳይ ያለቦታው ለምን አነሳው ቢባል “ምን ያለበት ምን አይችልም” እንደሚባለው ሊመጣበት ያለውን ችግር ከወዲሁ ስለተገነዘበ እንደሆነ ብዙዎች ግንዛቤ ወስደዋል፡፡

ይሁን እንጂ በአራት ዓመት ውስጥ በተቀያየሩ 3 አለቆች አማካይነት እንኳን 14 ሚሊዮን ብር የወጣ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የዘጠኝ ዓመቱስ ወጪ ስንት ይሆን? የሚለው ምላሽ የሚፈልግ ወሳኝ ጥያቄ ሆኗል፡፡ ይድነቃቸውን ከወይራ ሰፈር አዲሱ ገበያ የሚያመጣው የታቦቱ ፍቅር ነው? ወይስ የጥቅም ጉዳይ የሚለውም በእጅጉ አነጋጋሪ ነው፡፡ በእርግጥ ግለሰቡ ኮሜርስ አስተምራ ያስመረቀችውን አልባሹና አጉራሹ የሆነችውን የሴት ጓደኛውን ትቶ በምንም የማይገናኛትን የአሁን ሚስቱን ያገባው ከቤተሰቦቿ ያገኘቸውን ውርስ ተመልክቶ እንደሆነ አገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ ይህም የሚያሳየው ግለሰቡ ምን ያህል የጥቅም ሰው እንደ ሆነ ነው፡፡ የህንጻውን ገንዘብ ለመዝረፍ ያጋለጠውም ይኸው ጸባዩ እንደሆነ ይነገራል፡፡
እሑድ በተደረገው የአመራር ምርጫ ላይ አማሳኙ ቡድን በዘንድሮ የፋሲካ በዓል ከሕዝቡ ሰብስቦ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እሰጣለሁ ያለውን 75 ሺ ብር ሆስፒታሉ በተጠየቀው መሰረት ምንም ሳንቲም እንዳልደረሰው፣ ሰንበት ት/ቤቱም ተጠይቆ እስካሁን መልስ መስጠት እንዳልቻለ በይፋ ተነግሯል፡፡ እነሱም ይህን ጉዳይ አቅጣጫ ለማስቀየር ዘወትር የለመዱትን መከረኛ “ተሐድሶ አስቸገረን” ማለታቸውን ቀጥለዋል፡፡ የሆነው ሆኖ የደብሩ አስተዳደር ደብሩን ለመታደግ እየተጻጻፈ ያለው ደብዳቤ ውጤት እያመጣለት ነው፡፡ ሙስናውና ዝርፊያው በዚህ መንገድ መቀጠል እንደሌለባቸው አምኖ መንቀሳቀሱ ካህናቱም ለዚህ ጉዳይ መተባባራቸው እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ መስመር ግቡ ሲባሉ አምቢ ያሉ ደጋፊዎቻቸው እሑድ ለቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ለግለሰቦች ቆመው መታየታቸው ብዙዎችን አስተዛዝባል፡፡ ለምሳሌ ሰንበት ት/ቤቱን ወክላ የሰበካ ጉባኤ አባል የተደረገችው የ57 ዓመቷ የሰንበት ተማሪ ወ/ሮ ንግሥት ሙሉዓም ከዘራፊዎቹ ጋር ወግና መቆሟ በእጅጉ አስገርሟል፡፡
ነገ ደግሞ ከዚህ የበለጡ ምስጢሮች ይወጡ ይሆናል፡፡ ደብሩ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡ በእነርሱ በኩል ችግሮችን ሁሉ በሃይማኖት ማሳበብና “ተሐድሶ” የሚለውን አቅጣጫ ማስለወጫ ስልትን መጠቀም ጊዜው ያለፈበት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን እንደዚህ ያሉ ችግሮቹንና የማሳኝ አማሳኝ አባላቱንና ደጋፊዎቹን ገበና ለመደበቅ የሚሞክረው “ተሐድሶ መናፍቃን” እያለ እንደ ሆነም በዚህ ደብር ውስጥ በሚገባ ታይቷል፡፡ እሑድ ዕለት ለእነዚህ አማሳኞች ወግነው ሲናገሩ የነበሩት አንዳንድ ዲያቆናት አማሳኞቹን ደግፈው መናገራቸውና ወደ አደባባይ መውጣታቸው ጥሩ ነው፡፡ ድጋፋቸው ከምን የመነጨ እንደ ሆነ ግን በቀጣይ የምናየው ይሆናል፡፡ ምናለበት እንዲህ ላለው ጥፋት ሳይሆን ለወንጌሉ አገልግሎት ቢፋጠኑ?
እስካሁን ድረስ በደብሩ አስተዳደር እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች በጥሩ ጎኑ የሚወሰዱ ናቸው፡፡ ይበልጥ ግን ለሌላውም ትምህርት እንዲሆን አማሳኞቹ በዝምታ መታለፍ የለባቸውም፡፡ ጉዳያቸው ተጣርቶ ፍትህ መገኘት አለበት የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ እነ እስጢፋኖስ ኃይሉ የሸጡትን ቤት በተመለከተ፣ የቤተ ክርስቲያኑ ወለል ንጣፍ ከዋንዛ ፈርኒቸር መቼና እንዴት ባለ መንገድ እንደ ተገዛ መጣራት አለበት፡፡ ለጥቁር አንበሳ ተሰጠ ተብሎ ቀልጦ የቀረው የ75 ሺህ ብሩ ጉዳይ አመራሮቹን ከስልጣን በማውረድ ብቻ ሳይሆን በሕግ መጠየቅም አለባቸው፡፡ በመንግሥት በጀት የሚተዳደርን ሆስፒታል እደግፋለሁ ማለት ለሙስና በር ለመክፈት እንጂ ምንም መነሻ የለውም፡፡ በቅርቡ የሚሰየመው የህንጻው ኦዲት ኮሚቴ  ይህን አጣርቶ ካሳወቀ በኋላ አማሳኞቹ በሕግ መጠየቅ እንዳለባቸው የብዙዎች ተስፋ ነው፡፡  
ደብሩ እየወሰደ ያለውን ይህን እርምጃ ተከትሎ ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳትና በማስፈራራት አቅጣጫ ለማስለወጥ የሞከሩትን የእነዚህን አማሳኞች ቡድን ደብሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በጻፈው 3 ገጽ ደብዳቤ ፖሊስ ሥነ ሥርዓት እንዲያስይዝለት ጠይቋል፡፡ በዚሁ ደብዳቤ ላይ ዮናስ መኮንን “አቶ” የተባለ ሲሆን፣ ይህም ዲያቆን ሆኖ ሳለ ጋብቻውን ስላፈረሰ እንደሆነ መገመት ቀላል ነው፡፡ ብዙዎቹም ያለአጥቢያቸው ለጥቅም የተሰባሰቡ መሆናቸውን ደብዳቤው የጠቆመ ሲሆን የማህበረ ቅዱሳን አባል እንደሆነ የሚታወቀው ዶ/ር ኃይሉ በዛ ዓለሙ ግን መኖሪያ አድራሻው እንኳ የማይታወቅ እንደ ሆነ ተጠቁሟል፡፡ የደብሩ አስተዳደር ይህን እያወቀ እስካሁን ዝም ማለቱ አጠያያቂ ሲሆን ደብሩን በእጅጉ እንደጎዳውም መገመት አያስቸግርም፡፡ 
ቦታው ላይ እየተፈጠረ ያለው እያንዳንዱ ችግር ከጥቅም  ጋር የተያያዘ ሲሆን ከጀርባ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ማኅበሩ በአንድ ደብር እንዲህ ካደረገ በሌሎች ደብሮች ምን ያህል ጥፋት እያደረሰ ይሆን? ከሰሞኑ እንኳን በሰሚት መድኃኔ ዓለም ሰንበት ት/ቤት እያደረሰ ያለውን ጥፋት ተከትሎ ደብሩ በወሰደው እርምጃ ያልተደሰተው ማኅበረ ቅዱሳን ለአድማ ያዘጋጃቸውን ወጣቶች አሰልፎ የሀገረ ስብከቱን ጽህፈት ቤት ለማወክ ሞክሯል፡፡ ከቀድሞው በተሻለ መንገድ እየሠራና ውጤትም እያሳየ ያለውን ሀገረ ስብከቱን በማበረታታት ፋንታ ሥራ ለማስፈታት ጥረት አድርጓል፡፡ ሀገረ ስብከቱ እኮ ቢያንስ በጉቦ ይፈጸም የነበረውን ቅጥር ሙሉ በሙሉ አስቀርቶ በችሎታና በውድድር እንዲሆን እያደረገና ውጤትም እየታየ ነው፡፡ ይህን ለውጥ የማይወደውና ድብቅ አጀንዳውን ለማስፈጸም ማንኛውን የሙስና መንገድ እየሄደበት ያለው ማቅ ግን የሥራ አስኪያጆቹን ቀና የሥራና ለለውጥ ቁርጠኛ ሆኖ የተነሳሳ መንፈስ ለመረበሽ በሚመሰል መልኩ ለአመፅ ቀን ያደራጃቸውን ወጣቶች አሰልፎ ሁከት ለመፍጠር መሞከሩ ለቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ለግል ጥቅሙ እንደቆመ ራሱን ያጋለጠበት ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ 

No comments:

Post a Comment