Sunday, June 28, 2015

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያዘጋጀው ሥልጠና መልካምነትና የማቅ ሴራየአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች በቅርቡ የሰጡት ስልጠና እጅግ ግሩምና የተሳካ ሲሆን የአሰልጣኞች አቅምና ችሎታ በግልጽ የተለካበት ነበር ብሎ ማመንና መቀበል ይቻላል፡፡ ሁለገብ ዕውቀት ያላቸው ስራ አስኪያጆች ለቦታው እጅግ የሚመጥኑ ሆነው በመገኘታቸው በተሰብሳቢዎች ደስታም አግራሞትም ሐዘንም የተንጸባረቀበት ጊዜ ነበር፡፡ ደስታው በቤተክርስቲያኒቱ እንደዚህ ዓይነት በዕውቀት የተገነቡና ዘመኑን የዋጁ ልጆችን ቅዱስ ፓትርያርኩ ሲሾሙ ምን ያህል አርቀው እንዳሰቡ በማስተዋላቸው ነው፡፡ ሐዘኑ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከዚህ ቀደም ለቦታው የማይመጥኑና ስንዴን ከገለባ የማይለዩ ዕውቀት የሌላቸውንና ለሀገረ ስብከቱ የማይመጥኑ ለሊቃውንቱም ክብርን የማይሰጡ ይልቁንም ስደትና መከራ ሲያበዙ በነበሩ ሹመኞች የደረሰው ግፍና በደል ሲታሰብ እጅግ ያንገበግባል፡፡ 

እርግጥ ነው ጥቂት ሥራ አስኪያጆች አንድ ሁለት ሊባሉ የሚችሉ እንደ ወርቅ ተፈትነው ያለፉ አልነበሩም እያልን አይደለም፣ ነበሩ፡፡ እያልን ያለነው የአሁኖቹ ሥራ አስኪያጆች በአመራርና በብስለት በእውነት ተዝቆ በማያልቅ እውቀታቸው ያለፈውን ክፍተትና ቁጭት እየሞሉ ነው፣ ለወደፊቱም ይህን መንገድ በማይከተሉት ዘንድ ፈተናው ከባድ እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ ምክንያቱም ሊቀ ማእምራን የማነና መጋቤ ብሉይ አእመረ አሁን ቢመደቡም ለወደፊቱ ነዋሪዎች አይደሉምና ከእነርሱ በኋላ ለሚሾሙ ኀላፊዎች ፈተናው ቀላል አይሆንም፡፡ ይህን የተጀመረውን መልካመ ጅምር የሚያስቀጥሉ ካልሆኑና ወደቀደመው ነገር የሚመለሱ ከሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱ ትልቅ ቀውስ ውስጥ መግባቷ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም አሁን እየታየ ያለውን የፍትሐዊ አሰራር ፍሬ የቀመሱ ሁሉ በኋላ በጄ አይሉምና፡፡ 

በሁለቱ ቀን ሥልጠና የነበረው መግባባትና መነቃቃት በጣም የሚገርም ነበረ፡፡ ወደኋላ መለስ ብለን በአባ እስጢፋኖስ ጊዜ የተሰጠውን ስልጠና ስናስታውስ ዶ/ር ወረታው ተራ አሉባልተኛ አቶ ታደሰ እንደ እባብ ተናዳፊ ነበር፡፡ ስልጠናው ካህናቱን ሆን ተብሎ ለማዋረድና ለመሳደብ የተጠራ ነበር የሚመስለው፡፡ ለምሳሌ አቶ ታደሰ የተባለው የማህበሩ ጽንፈኛ ሰው በጓጉንቸርና በእንቁራሪት እየመሰለ ሲሳደብ ትናትና በቆሎ ትምህርት ቤት በረሃብ የተሰቃዩትን ሊቃውንት “የከተማውን ቤተ ክርስቲያን ለእኛ ለቃችሁ ወደጋምቤላና ወደአፋር እኛ የምንሰፍርላችሁን መቁነን እየበላችሁ ትኖራላችሁ” ነበር ያለው፡፡ ሊቃውንቱ ትናንት ከውሻ ንክሻና ረሃብ ወጥተው ንጹሕ መብልና መጠጥ መብላት ስለጀመሩ ማቆች ዓይናቸው ደም ለብሶ በአባ እስጢፋኖስ አጋፋሪነት ተቀነባብሮ የነበረው ቤተ ክርስቲያንን የመውረስ ዓላማ በጥቂት የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ተጋድሎ ከተጋረጠባት ከጨዋ አስተዳደርና ከዜማ አልባ የአራት ኪሎ አማሳኝ ቡድን ልትድን ችላለች፡፡ በወቅቱ እንደ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫኔ የመሰሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች አባ እስጢፋኖስን “ኧረ አባታችን ይህ ነገር ይጠና ጉዳዩ ወዲህ ነው” ብለው ቢናገሩም ማስተዋልና ጥበብ የጎደለው ለአንድ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ የማይገባ ከልጆቻቸው ከማቆች የተጫኑትን ዘለፋና ዛቻ አስተላልፈዋል፡፡ በተረፈ ዶ/ር ወረታውና አቶ ታደሰ ሆን ተብሎ ሊቃውንቱን ለማዋረድና ለመሳደብ የተጠሩ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ አንድ የማህበሩ አባል የሆነና ስለሂሳብ አያያዝ ሊያስረዳ የመጣ ሰው ትሁት የሆነ ቃል በመናገር ለአባቶች በጥሩ ለዛ መልእክቱን ማስተላለፉ አይዘነጋም፡፡

በአንጻሩ ሰሞኑን የነበረው ስልጠና ወይም ምክክር ቢባል የተሻለ ነው የተሳካ ነበር፡፡ ምክክር የተባለበት ምክንያት ለካህናቱ የቀረበው ሥልጠና በራሳቸው ቋንቋና ልጆች ስለነበር በተለይ በሥራ አስኪያጆች የቀረበው መልእክት ምክርና ስልጠና በጨው የተቀመመና የማይሰለች፣ እጅግ መደማመጥ የነበረበት ጊዜ በመሆኑ ከአንዳንድ ሊቃውንት ቁጭትና እልኽ የተቀላቀለበት ንግግርና አስተያየት ይሰጥ ነበር፡፡ እንደነዚህ ያሉ ብርቅና ብልህ ልጆች እያሉ እስካሁን ተሸሽገውና ተደብቀው የተማሩትን ያህል ለውጥ ለማምጣት ዐቅም እያላቸው ለምን ተደበቁ የሚሉ ብዙ አለቆች ነበሩ፡፡ በአዳራሹ የነበረው ሰልጣኝ በአንድ ዓይነት መግባባትናና ደስታ ውስጥ ነበር፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ በማቅ በኩል ግን ሁልጊዜ ከሚዛን በታች በሆነው ሚዲያቸው በሐራ ሊቀ ማእምራን የማነና ሊቀ ጠበብት ኤልያስ አስፈራርተውና አስገድደው ስልጠና ሰጡ እያሉ ማውራታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ለነገሩ ከሐራ ከዚህ የበለጠ አይጠበቅም፤ ለዚህም ነው ሊቃውንቱ ሐራን “አዋልድ” እያሉ የሚጠሩት፡፡ አዋልድ ሴቶች ልጆች ማለት ሲሆን፣ ልጆች ደግሞ በሀገሪቱ ሕግም ሆነ በመንፈሳዊው ሕግ ለምስክርነት እንደማይበቁ ሁሉ ሐራም ዘወትር ውሸት የሚያወራና ወገንተኛ ሆኖ የሚዘገብ በመሆኑ “አዋልድ” ተብሏል፡፡ በማስፈራራት ሥራ የሚሠራ ቢሆን ኖሮ በአባ እስጢፋና በማቅ በኩል አስፈራርተውና አስገድደው ነበር ግን አልሰራላቸውም፡፡ አሁን እየሆነ ያው እነርሱ እንዳሉት ሳይሆን የሰከነና ጥሩ መግባባት የታየበት ስልጠና ነው፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ለምን መዋሸት እንዳስፈለገና ነገሩን በዚህ መንገድ እንዳቀረበው፣ ከዚህ የሚያገኘው ትርፍ ምን እንደሆነ ከሐራ በቀር የሚያውቅ የለም፡፡ በዚህ ግን ከኪሳራ በቀር እውነታውን የሚለውጠው አንዳች ነገር አይኖርም፡፡  

ሁል ጊዜ ከውሸትና ከብጥብጥ ትርፍ የሚጠብቁ ማቆች እንደሚያገሳ አንበሳ እየዞሩ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳለው አንድ ክርስቲያን ከክፋትና ከተንኮል ሥራ ወጥቶ መልካም ነገር መሥራት ሲጀምር ጠላት ዲያብሎስ የተጀመረውን መልካም ሥራ ለማበላሸት እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራል 1ጴጥ.5፥8፡፡ ክርስቶስ በአንበሳ ተመስሏል፤ ይኸውም በግርማ ሞገሱ በመዋኢነቱ /በአሸናፊነቱ/ ነው፡፡ ዲያብሎስም ከአንበሳ ጋር ተነጻጽሯል፤ አንበሳ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚዞርና እንደሚያገሳ ሁሉ ዲያብሎስም ሰውን ከእግዚአብሔር መንገድ ለማስወጣት ስለሚዞርና ስለሚያስፈራራ፣ ክፉ ጨካኝና ምህረት አልባም በመሆኑ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አንበሳ በባህርይው በረትን ሰብሮ አይገባም፤ ከውጭ ሆኖ ሲያገሳ ግን ከብቶቹ በድንጋጤ ደካማ በረት ከሆነ እየተፈተለኩ ስፍራቸውን እየለቀቁ በድንጋጤ ወደሱ ይሄዳሉ በቀላሉም ይበላቸዋል፡፡ የዚህ ክፉ አውሬ ምሳሌ የሆነ ማህበርም/ማቅ/ እያዞረ ይጮሃል፤ የተጀመረውን መልካም ጅምር ወደ ኋላ ለመመለስ ሥራ አስኪያጆቹንም ከስፍራቸው ለማስለቀቅ የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ እየጣረ ይገኛል፡፡

በመሠረቱ ይህ ማኅበር ፀረ ሊቃውንትና ፀረ ክርስቶስ መሆኑ ገና ከአበቃቀሉ እየታወቀ የክርስትና ሥራ ይሰራል ብሎ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ ምክንያቱም ማቅ የተወለደው በደርግ ጉያ ብላቴን ሲሆን “አብያተ ክርስቲያናት ይትአፀዋ” ብሎ ቤተ ክርስቲያናችንን ካዘጋ፣ ባለራእዩን ቅ/ፓትርያርክ ብፅዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን ከገደለ ቡድን ምን መልካም ነገር መጠበቅ ይቻላል? ለዚህም ነው በአገሪቱና በቤተ ክርስቲያኒቱ መረጋጋትና ሰላም እንዳይሰፍን አብዝተው እየሰሩ የሚገኙት፣ ለምሳሌ ያህል በቅርቡ ማቅ ያደራጃቸውና ከአንድ ደብር ተሰልፈውና ተፈራረመው ከመጡ ሰዎች መካከል 47ቱ ሙስሊሞች ነበሩ፡፡ ታዲያ ይሄ ወዴት ነው የሚወስደው? ለቤተ ክርስቲያን መቆርቆር ወይስ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት? የእነሱ ጉድ ከደርግ እስከ አሁን በቤተክርስቲያን ውስጥ ያፈሰሱት ደም በደልና ስርየቱ እንዲሁ የሚነፃ አይደለምና ይቆየን፡፡

ሌላው ማህበሩ ከመጀመሪያው ውሸታምና ዘረኛ መሆኑ እየተረጋገጠ የመጣው፣ አባላቱና የወንዙ ሰዎች በሙስና የተጨማለቁ ሆነው እያለ በውሸት ምስክርነት ሌባውን ንፁህ ለማድረግ በሚነዛው የሐሰት ወሬ ነው፡፡ በሐራ ብሎግ በቦሌ ቡልቡላ መድሃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን የተፈፀመውን ሙስና በዋናነት የፈጸመው ዋናውና መሪው አለቃው ቄስ ገ/ሚካኤል ሆኖ እያለ የነሱ ሰው ስለሆነ ብቻ ስሙን ጠርተው ይሰርቃል ለማለት ዓቅም ስላጡ ቢያንስ ዝም ማለት ሲገባቸው ይባስ ብለው አለቃው የለበትም አልሰረቀም ብለው ዘግበዋል፡፡ ምናለ እውነቱን መመስከር ባይሆንላቸው ዝም ቢሉ? 

ከዚህ በመቀጠል ደግሞ በሥራ አስኪያጆቹ በኩል ሊስተካከል ይገባል የምንለውን ጉዳይ እንጠቁማለን፡፡
በመጀመሪያ በሀገረ ስብከቱ ያሉ ርዝራዢዎች አሁንም የሰላም ጠንቅ በመሆናቸው ያልተደረገውንና ያልተባለውን በውሸት እየቀመሙ “እገሌ ተቀይረሃል ታግደሃል” እያሉ ሰራተኛው ተረጋግቶ እንዳይሰራ በየአድባራቱ ያሉ ሰራተኞች በነዚሁ ሽብር ምክንያት በየቀኑ ስራ ፈተው በሀገረ ስብከቱ ተኮልኩለው ይውላሉና በሀገረ ስብከቱ ያሉ አንዳንድ ሰራተኞች አሁንም ቢጠኑና እንዲህ ካለ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ቢደረግ፣ ሰራተኛውም በሆነ ባልሆነ እንዳይሸበር ዋስትና የሚያገኝበት አሠራር ቢዘረጋ፡፡

        ሌላው የሀገረ ስብከቱን ስም እያስጠፋና ፍትህ ጠፍቶ ጉዳዩ አፍ አውጥቶ አብዝቶ እየተናገረ ስለሆነ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውዝግብ ሊታሰብበትና መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ፍትህ መስጠት የባህርይ ስለሆነ ለድሆች ፍትህ ሲሰጥ እግዚአብሔር ይደሰታል፡፡ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተክርስቲያን እየተነፈገ ያለውን የፍትህ ጉዳይ እስቲ በእውነት እንነጋገር፡፡ ለእኛ እነሊቀ ማዕምራን የማነ ብዙ መልካም ነገር ሰርተው ፍትህም ሰጥተው ከነሱ በፊት የተሰራውን በደል ክሰው ለብዙዎች መፍትሄ ሲሰጡ ባየንበት በዚህ ጊዜ፣ በእነርሱ ዘመን ከላይ በተጠቀሰው ቤተ ክርስቲያን እየተፈፀመ ያለውን ግፍ እንዴት ማየት አልቻሉም? ለዝምታቸው ምክንያቱስ ምን ይሆን? አለቃው ፀሃፊው በተለይ ሒሳብ ሹሙ ምንም እውቀት የሌላቸው መሃይሞች ሆነው እያለ የሰበካ ጉባኤ አባል የሆኑት ከህናት ያለጥፋት፣ የድጓው መምህር ሊቅ የሆነው መ/ር ነብየ ልዑል በእነዚህ አላዋቂዎችና ከስራና ደመወዝ ታግዷል ቤተክርስቲያን እንዳይገባ ተከልክሏል፡፡ በተለይ የገዳሙ ሒሳብ ሹም በሽጉጥ እያስፈራራ ከአሁን በፊት የዘረፈው ገንዘብ አልበቃ ብሎት “ሰበካ ጉባኤው እንዲፈርስ ኑ ፈርሙ አለበለዚያ እንደ መ/ር ነቢየ ልዑል ትባረራላችሁ” እያለ እያስፈራራ ይገኛል፡፡ አቶ ክብሮም ሦስት መነኮሳት በፈፀሙት ነውር እያስፈራሩ በዝሙት ቅሌት በሲዲ ዶክሜንት ስላለን እየዞራችሁ ሰበከ ጉባኤውን ይውረድ እያላችሁ አሳምኑ በማለት እየዞሩ እንደ እብድ ውሻ ይጮሃሉ፡፡ በእውነት ያስቆጫል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ በቶሎ እልባት ሊሰጠው ይገባል አሊያ ጥሩውን ጅምር ጥላሸት የሚቀባ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ፍትሕን እንጠብቃለን፡፡

      በመጨረሻም ተራ ወጥቶ ባለጉዳይ በየክፍለ ከተማው እንዲስተናገድ ከተደረገ የወጣው ተራ አንዳንዶችን የማይገዛቸው ለምንድነው? እንደነ አባ ነአኩቶ የጎፋ ገብርኤሉ ጸሐፊ ዲ/ን አበበን የመሳሰሉ በሕግ አይገዙም፡፡ ክቡር ሊቀ ማእምራን የማነ ስለህግ ጉዳይ ለእርስዎ አናስተምርም ጥቆማችን ግን ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው የሚለው መርሕ ቢከበር መልካም ነው የሚል ነው፡፡ እንደእዚህ ያሉ ጥቃቅን የሚመስሉ ግን ውጤታቸው ግን ትልቅ ሊሆን የሚችል ግድፈቶች ሊታረሙ ይገባል እንላለን፡፡  


በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የምንገኝ ካህናት

2 comments:

 1. ፍቅረማርያም አበራJune 30, 2015 at 12:25 AM

  የቡልቡላው አለቃ ስማቸው መልአከሰላም ወርቃለማሁ ነው፡፡ከምንም ተነስተው የተሾሙትም የዛሬ ሁለት አመት በአቡነ ቀውስጦስ ምልጃና ተማጽኖ ነው፡፡ወንድማቸውም እንዲሁ አስተዳዳሪ ናቸው እድሜ ለአቡነ ቀውስጦስ፡፡ለሐራ የሚታያት ግን የየማነና የዘመንፈስ ዝምድና ብቻ ነው፡፡ነፍሳቸውን ይማርና ዐይነስውሩ ሊቀጠበብት ያሬድ በማደጎ ያሳደጓቸው ደላላው በቀለ በመካኒሳ አቦ አለቅነት ሲሾምላቸው በተመሳሳይ ሲመራቸው የኖረውን ዳዊትን ከተመደበበት ክፍለሀገር ቀርቶ በሙዳየምጽዋት ገንዘብ ዛሬ ባለብዙ ቤቶችና መኪኖች የልጅ ሀብታም አድርገውታል፡፡የነሊቀሊቃውንት ኃይለመስቀል ውቤ (ወይ ሊቀሊቃውንትነት!ሥም አይከብድ!)ሚሊኒየርነት ለእነ ሐራ አይታያቸውም፡፡የቦሌ ሚካኤሉን ባለዶልፊን አስተዳደሪም የምናውቃቸው አይመስላቸውም፡፡ሁሉን እናውቃለን፡፡እነሆ እነዚህ ሁሉ ማሰኑ!ግን ሀገራቸው የሐራ(‹‹አራ›› ቢባል ይሻላል!) ልጆች ከበቀሉበት ነውና ኃጢኣታቸው ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረላቸው፡፡ታዲያ እንዲህ ሲባል ሐራ የምታነሳው ሙስና ሁሉ ሀሰት ነው ማለት አይደለም፡፡ከሁሉም ብሔር በችግሩ የተዘፈቁ ግለሰቦች ሳሉ የተወሰኑትን(በብዛት ትግሬዎችን) ብቻ ለይታ ማሳደዷ በተለይ ለሸዋ ሲሆን ዐይን ያወጣ ጥብቅና ጭምር ስትቆም ይሉኝታ ማጣቷ ስህተት መሆኑን ለማመልከት ብቻ ነው፡፡


  እንደ እውነቱ በአሁኑ ሰዓት ሐራ እያደረገችው ያለችው ቅስቀሳ በማኅበረቅዱሳንነትና እና በሰንበት ትምህርት ቤት ስም የተሸፋፈነ ግልጽ ዘረኝነት ነባሩን ችግር ከማባባስና እኔን ጨምሮ ብዙዎቻችን የቤተክርስቲያን ልጆች ሳንወድ በግድ በተሐድሶዎች እንደሚተዳደር አንዳች የማንጠረጥረውን መናፍቁን አባ ሰላማ ብሎግ ሚዛን ለማስጠበቅ ስንል እንድንቃኝ ያደረገ ነው፡፡በሐራና በመሳሰሉት በማኅበረቅዱሳንና በሰንበት ትምህርት ቤት አድረው አመጻን በሚሰብኩ ባለቤት አልባ ብሎጎች የተነሳ ምዕመኑና አስተዳደሩ ለውዥንብርና ላተፈለገ ዐላማ እየሆነ ነው፡፡የአባ ሰላማ እዳው ገብስ ነው፡፡የመናፍቅ ብሎግ መሆኑን ከምዕመን እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለው የቤተክርስቲያኒቱ አባል ሁሉ ያውቃል፡፡የቤተክርስቲያን ጠላትነቱን መቅደሱን ከነዶግማው ገልብጭ አድሳለሁ በሚል ትእቢቱ ራሱን ገልጹዋል፡፡እንደአመጣጡ እንመክተዋለን፡፡‹‹ጠላትህን አንድጊዜ ተጠንቀቀው፤ወዳጅህን ግን ሺህ ጊዜ›› ይባል የለ ከነተረቱስ፡፡የሐራ ወዳጅ መስሎ የሚካሄድ መሰሪ ከፋፋይነት በውስጡ ዘረኝነትና ፖለቲካ ያለበት እና ለቅንና ርቱእ ኦርቶዶክሳውያን ተደራሽ በመሆኑ እንዲሁም እስከ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት የተዘረጋ ሕዋስ ስላለው አካሄዱ በተያያዘው መንገድ ያለ ይሉኘታ ከቀጠለ ምናልባት ከግብስብሱ አባሰላማ ብሎግም በላይ አደገኛ ነው፡፡


  ብሎጉ በመሰረቱ ኦርቶዶክሳዊ መሆኑ ባያጠራጥርም በትምህርተ-ሃይማኖት ረገድ አንድም ቀን የረባ ጽሑፍ ሲያወጣ ታይቶ አያውቅም፡፡ተሐድሶን ለማጋለጥ አልፎ አልፎ ብቅ ድርግም የሚል እንቅስቃሴ ቢያደርግም እሱም ቢሆን ማኅበረቅዱሳን ሲነካ ብቻ በመሆኑ ብዙ የሚወራለት አይደለም፡፡ማኅበረቅዱሳን እስካልተነካ ድረስ ተሐድሶነት ነውር የሌለው ሲሆን ማኅበረቅዱሳን ጋር አለመግባባት የፈጠረ ኦርቶዶክሳዊ ግን ምን በወላዲተአምላክ ቢምል ቢገዘት በእነ ሐራ ከመሳደድ አያመልጥም፡፡ነገሩን ይበልጥ አሳዛኝ የሚያደርገው ተሐድሶዎች እንደአቅሚቲ አስተምሕሮአቸውን ካሉባልታው ቀምረው ምዕመኑን ለማስኮብለል ሲጥሩ ሐራ ግን ባለ በሌለ ኃይሏ የውስጡን ሰው እየገፋች በገፍ በማስወጣት ለነዚሁ ተሐድሶዎች መኖ ለማድረግ ከመድከም በቀር ተሳስታ እንኳ ምዕመኑን የሚያጽናና መንፈሳዊ ትምህርት አትሰጥም፡፡ስራዋ በአሉባልታ ከአጥቢያ እስከ ቅዱስ ሲኖዶስ ወሬ እየዘራች ጳጳሳት ከፓትርያርክ፣አጥቢያ ከሀገረስብከት፣የአጥቢያ አገልጋይ ከአስተዳደር ሰራተኛ፣ምዕመን ከአስተዳዳሪ ማናቆር ብቻ ነው፡፡


  ለኦርተዶክስ ዘብ መቆም(ሐራነት)ለእነሱ ሰውነ በማቅረብ ሳይሆን በማራቅ፣በፍቅርና በይቅር ባይነት ሳይሆን በጥላቻ በቂም፣በመከባበር ሳይሆን በመዘርጠጥ፣በመተባበር ሳይሆን እኛ ብቻ በሚል ስሜት፣በሥርዓት ሳይሆን ሁሉን አፍ እንዳመጣ ተሐድሶ በማለት፣በምክንያታዊነት ሳይሆን በቡድነተኝነት፣በማስተዋል ሳይሆን በስሜት፣በሊቅነት ሳይሆን በአማተርነት፣በማስረጃ ሳይሆን በፍረጃ ማሳዳድ ማሳደድ ማሳደድ የሚገለጽ የስም ኦርቶዶክሳዊነት አይሰለቻቸውም፡፡ካለፈው ጉዟቸውም አይማሩም፡፡ሰው ይታዘበናልም አይሉም፡፡እነሱን መቃወም ማለት ተሐድሶን መደገፍና ኦርቶዶክሳዊነትን መተው እንዳልሆነም አይገባቸውም፡፡ሲጀመር የኦርቶዶክሳዊነትን መለኪያ የኢሚዛናዊ ብሎግ አመለካከት ነው ያለው ማን ነው!ብቻ ይቅር፡፡ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል፡፡ደግነቱ የቤተክርስቲያን አምላክ ቤቱን ከእንደ አባ ሰላማ አይነት በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ለመምታት የሚሞክር ድኩም መናፍቅም ሆነ፤ከእንደ ሐራ አይነት ቡድንተኞች ለመጠበቅ አያንቀላፋም፡፡ግዴለም ሚዛናዊ ሚዲያ እስኪኖረን ድረስ ወደ ላዩ ጌታ እናለቅሳለን፡፡የአማላጂቱ ልጅ ቤቱን ከሁለት ባለ እርኩሳት ዐላማዎች አሉባልታ አንጽቶ እንዲያሳየን እንጸልያለን፡፡

  ReplyDelete
  Replies
  1. ፍቅረ ሰይጣን፣ ክፋት፣ እንዲሁም ከሳሽነት አበራ

   Delete