Tuesday, June 16, 2015

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚታየው የለውጥ እርምጃና የማኅበረ ቅዱሳን አደናቃፊነትበአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሥራ አስኪያጅ ለውጥ ከተደረገ ወዲህ በርካታ የለውጥ እርምጃዎች እየተወሰዱና ለውጥም እየታየ መሆኑን ከለውጡ ተጠቃሚ የሆኑት በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ካህናት የሚመሰክሩት ሐቅ ነው፡፡ ነገር ግን በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል እንደሚባለው በመጣው ለውጥ ኪሳራ የደረሰባቸው ማኅበረ ቅዱሳንና ተለጣፊዎቹ ግን በዚህ ደስተኞች ስላልሆኑ ለውጡን ወደኋላ ለመመለስና ቤተክርስቲያን የሁሉም ወገን ስብስብ ሳትሆን የአንድ አካባቢ ሰዎች ብቻ የሚመሯት ናት በማለት የቀደመውን ሙስናዊ አስተዳደር እንደገና ለማስፈን ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋት እየሠራ መሆኑ እየታየ ነው፡፡ እንደዚህ የምንለው በከንቱ ወይም ስም ለማጥፋት በሚል አይደለም፡፡ እየታየ ያለው ያ ስለሆነ ነው፡፡
እውነቱን እንነጋር ካልን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመጋቤ ሐዲስ ይልማ፣ በአባ እስጢፋ እና በቀሲስ በላይ ጊዜ የባከነውና የተዘረፈው የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረት፣ እንዲሁም በካህናቱ ላይ የደረሰው ግፍና በደል በታሪክ የሚረሳ አይደለም፣  የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም እንዲሉ አበው፡፡ በጊዜው ዝርፊያውና ሙስናው ግፉና በደሉ ራሱ አፍ አውጥቶ እየጮኸ እያለ፣ ካህናቱም እርዱን ድረሱልን ተናገሩልን ብለው ወደ ማኅበሩ ሰዎች ሚዲያዎች ቢጮኹ፣ ማቅ ስለ እውነት ለመመስከር ጥፋትን በጥፋትነቱ ለመቃወምና ያጠፋውን ለመገሰጽ አልታደለምና፣ በጊዜው በሥልጣን ላይ የነበሩት ሰዎች የእርሱ አባላትና ተለጣፊዎች የወንዝ ልጆችም ስለሆኑ ብቻ ይዝረፉ ይጠቀሙ አገራቸው ነው ወንዛቸው ነው ብሎ ድምጽ ሳያሰማ ቆይቷል፡፡ ይልቁንም በተገላቢጦሹ በጥፋታቸው ይቀጥሉ ጥሩ አደረጉ እንኳን አጠፉ በጥፋታቸውም ሊጠየቁ አይገባም በማለት እነ ሐራ አብዝተው ጮኸዋል፡፡ ይባስ ብለውም የነሊቀ አእላፍ በላይን ግፍና በደል በቅዱስ ፓትርያርኩ ሲደፈድፉና እርሳቸውን ሲኮንኑ ታይተዋል፡፡ ታዲያ ከእነዚህ የጨለማ ልጆች የእፉኝት ባሕሪ ተጋሪዎች በክርስቶስ ያምናሉ ኃጢአትን ይቃወማሉ ጽድቅን ይወዳሉ ብሎ ህብረት መፍጠርና የክርስቶስን ስም መጥራት ስሙን ማሰደብ አይሆንምን? 
 እነዚህ ማህበረ እኩያን ቤተ ክርስቲያንን ወደየት ሊወስዷት እንደሚችሉ ምን ዓይነት ፍሬ እንደሚያፈሩ ከማንም ስውር አይደለም፣ የሚያፈሩት እንክርዳድና አሜከላ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት “በሊህ እገሪሆሙ ለክዒወ ደም” እንዳለው የሰውን ደም በከንቱ ለማፍሰስ እግራቸው የፈጠነ ናቸው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎም በመጨረሻ ዘመን ይነሣሉ በማለት የዘረዘራቸው የክፉ ሥራዎችና ጠባያት ባለቤቶች ናቸው፡፡ ይኸውም ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብን የሚወዱ ትምክሕተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ ቅድስና የሌላቸው፣ ፍቅር የሌላቸው ዕርቅን የማይሰሙ ሐሜተኞች ራሳቸውን የማይገዙ ጨካኞች መልካም የሆነውን የማይወዱ ናቸው፡፡ ሁል ጊዜም እየተማሩ እውነትን ወደማወቅ ከቶ መድረስ የማይችሉ የተባሉትስ እነዚህ አይደሉምን? እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ከሰማይ ይገለጣልና፣ 2ጢሞቴዎስ 3፥1-5፣ ሮሜ 1፥18፡፡
እንደተባለውም መልካምን የማይወዱ በመሆናቸው ነው እንጂ በእውነት ለቤተ ክርስቲያን የቆሙ ሰዎች ቢሆኑ ኖሮ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቀደሙት ሥራ አስኪጆች ያልታየውን ነገር ሁሉ አሁን እያሳዩን ያሉትን  ለውጥን በወሬ ሳይሆን በተግባር እያሳዩን ያሉትን፣ ዘር ሳይቆጥሩና ሰሜን ደቡብ ሳይሉ በጥሩ መንፈስ እየሠሩ ያሉትን የልጅ ዐዋቂዎች ሥራ አስኪያጆች በርቱ ከዚህ የበለጠ ለውጥ አምጡ ማለት ይገባቸው ነበር፡፡ ይህ የቲፎዞነት ጉዳይ እንዳይመስል እየሆነ ስላለው ለውጥ በየአድባራቱ ያሉና በለውጡ ተጠቃሚ የሆኑ አገልጋይና ሠራተኞችን መስማትና ማድመጥ ይቻላል፡፡ እንደዚህ ስንል እዚህም እዚያም ጉድለት የለም እያልን አይደለም፡፡ ለምሳሌ በመንበረ ፓትርያክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም እየተሠራ ያለውና ሰሞኑን የተደረገው ነገር በአግባቡ ያልታየና በጥንቃቄ ያልተወሰነ ጉዳይ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ከፍተኛ የሀብት ብክነት የደረሰበት ሆኖ እያለ ፓትርያርኩም ሳይቀሩ ይመርመር ብለው የሰጡት ትእዛዝ ሳይከበር ቁጥጥሩን የበለጠ እንዲያጠፋ በእድገት መዛወሩና ወደሌላ ደብር ማለትም ወደ ቃሊቲ ገብርኤል መላኩ ተገቢ አልነበረም፡፡ የቅዱስ ፓትርያኩ ትእዛዝም ተፈጻሚ አልሆነም፡፡ በእርግጥ ይህ ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ላይሆን ይችላል፡፡ በሀገረ ስብከት ያሉ አንዳንዶች በሰጡት የተሳሳተ ምስክርነት ሊሆን ይችላል እንጂ እነ ሊቀማእምራን የማነ እና መጋቤ ብሉይ አእመረ እንዲህ ያለ ስህተት ይሠራሉ ብለን አናምንም፡፡
በመንበረ ፓትርያክ ከቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ከአለቃ እስ ጸሐፊ እውቀትም ሆነ ሞያ የሌላቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር ሥራ አስኪያጆቹ ያልታያቸው ጉድለት የለም እያልን አይደለም፡፡ በእውነት እንነጋገር ካልን ግን ለቤተ ክርስቲያኗ ክብር እጅግ ብዙ ረጅም ርቀት ተጉዘዋል፡፡ ለክፉዎችና ለዘረኞች ባይታያቸው የተጣመመውን በማስተካከል እንጀራውን የተቀማውን በመመለስ፣ የሚያለቅሰውን እንባ በማበስ በእግዚአብሔርና በሊቃውንቱ ግን ታሪካዊና የተወደደ መሥዋዕት ሆኖ መመዝገቡ ውለታን በማይዘነጋው ጌታ ዘንድ ከቶ አይረሳም፡፡
ሌላው በለውጡ የታየው አንድ ነገር ሁለቱም ሥራ አስኪያጆች የሚወስኑት ውሳኔ ተግባራዊ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በዋና ሥራ አስኪያጅ ብቻ ውሳኔ ሲከናወን የነበረው ሥራ በአሁኑ ጊዜ በምክትሉም ጭምር እየተከናወነ ነው፡፡ ስለዚህ ባለጉዳይ የግድ ዋና ሥራአስኪያጁን መጠበቅ አይኖርበትም፡፡ ይህም በእነዚህ ሥራ አስኪያጆች የታየ ትልቅ ለወጥ ነው፡፡ ለሥራውም ቅልጥፍና ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ በጉቦ መሥራት ቀርቶ ማስታወቂያ እየወጣ በውድድር ሰራተኞች የሚቀጠሩበት አሰራር ተዘርግቷል፣ ተግባራዊም እየሆነ ነው፡፡
ሌላው ሳይጠቀስ የማይታለፈው ጉዳይ በሊቀ አእላፍ በላይ ጊዜ ለካህናቱ ይሰጥ የነበረው ክብር እጅግ አሳዛኝና አስከፊ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ ከሥራ ታግደው በአየር ላይ ተንሳፈው ተባረው የመጡ ሊቃውንቱና ካህናቱ ወገባቸው እስኪነቀጠቀጥ በመቆም ብዙዎቹ እግራቸው አብጦ እንደ ሰው ሳይቆጠሩ በረንዳ ላይ ውለው ይመለሱ ነበር፡፡ አሁን ግን እነሊቀ ማእምራን የማነ የካህናቱ ድካምና እንግልት ስለገባቸው የአባቶቻቸውም ክብር መዋረድ ስላስቆጣቸው ለአቤቱታ የመጣ ሁሉ ሊስተናገድበት የሚችልና የሚያርፍበት ወንበር አዘጋጅተው የሊቃውንቱንና የካህናቱን ክብር አስመስለዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ዋስትና አገኘሁ መፍትሄ አገኘሁ ብሎ የማይደሰት ሰራተኛ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ እንደዚህ እያደረጉ ያሉትን የወጣት አዋቂዎች ሥራ አስኪያጆችን አደጉልን ተመንደጉልን በማለት ፈንታ ማኅበረ ቅዱሳን የተባለ የጥፋትና የጎጥ ስብስብ የእኛ ወገን ያልሆነ መልካም ቢሰራም እውቅና አንሰጥም በማለት ቤተ ክርስቲያኗን ወደ ኋላ ለመመለስ ላይ ታች እያለ ይገኛል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት መልካም ጅምሮች መሬት ላይ መኖራው እየታወቀ፣ የቤተ ክስቲያኗን አስተዳደርና አሰራር መቆጣጠሪያ ሲስተም ከተዘረጋ ተጠያቂነትና ግልጽነት ያለው አሰራር ከሰፈነ ማቆች ለምን ከፋቸው? ለምስን አመማቸው? በየቤተ ክርስቲያኑ እየዞሩ ለጅማ ቤተ ክርስቲያን እያሉ በምክንያት ሲዘርፉ የነበሩት አባ እስጢፋን፣ ያለመማለጃ (ጉቦ) ሥራ የማይቀጥሩትንና የማያዛውሩትን አባ እስጢፋን ከጎንዎ ነን እናግዞታለን ሲሉ የነበሩ ማቆች አሁን ያለ ምንም አድልዎ ያለምንም መማለጃ የቤተ ክርስያኗን ችግር ለማስተካከል ላይ ታች ከሚሉት ከሊቀ ማእምራን የማነና ከመጋቤ ብሉይ አእመረ ጎን መሰለፍ ለምን ተሳናቸው? ለምስን ይህን ለማድረግ አቅም አጡ? ብለን ብንጠይቅ የሚከተሉትን ሐቀኛ ምላሾች እናገኛለን
1.  ማቆች ለገንዘብ ለስልጣንና ለዝና ትርፍ እንጂ ለሃይማኖት (ለእውነት) የቆሙ ስላልሆኑ ይህን ለማድረግ ሞራሉና ብቃቱ የሌላቸው በመሆኑ
2. የወንዞቻቸው ልጆች ስላልሆኑ የእነርሱ ስም በመልካም ሲነሳ ስለሚያንገበግባቸው
3. የእነርሱ ወኪሎችና ተለጣፊዎች ያልሰሩትን ሥራ የአሁኖቹ ሥራ አስኪያጆች በድፍረትና በሐቅ ስለጀመሩት፣ በዚህ መልካም ጅምር ብርሃንነት የእነርሱ (የማቆቹ) ክፉ ሥራ ስለሚገለጥ ፍጻሜ እንዳያገኝ ለማጨናገፍ፣
4.  ዋና ሥራ አስኪያጁ ተረጋግቶ ስራውን እንዳይሰራ ጠዋት ማታ እየተነኮሱ ለማማረርና  ተበሳጭቶ እንዲለቅና ቦታውን እነርሱ እንዲረከቡት ለማድረግ፣
5. እነሊቀ ማእምራን የማነ ከተሾሙ ወዲህ እረፍት ያጣው ማቅ ብስሉን ከጥሬው ወጣቶችን ከአዋቂ ጋር እየመለመለ በመላክና በማወክ መንግስትም ህዝብም ሀገረ ስብከቱ በሰው መጨናነቁን አይተው ችግር እንዳለ እንዲቆጥሩና እንዲፈርዱ፣ በዚህም እስካሁን የተሠራውን መልካም ሥራ ሁሉ ጥላሸት በመቀባት ዋጋ ለማሳጣት ነው፡፡
የሚገርመውና የሚደንቀው ማህበረ ቅዱሳን የአመፀኞችና የወንበዴዎች ዋሻ እንደመሆኑ ትናንትና ሲዘርፉና ሲደልሉ የነበሩትን እነ ኃይሉ ጉተታን በአሁኑ ወቅት አቅፎ ከዚያ ሆነው ያስተኩሳሉ፡፡  ኃይሉ ጉተታ ማነው?
1.     ኃይሉ ጉተታ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በስብከተ ወንጌል ተመድቦ ሲሰራ ያልተማረና ውዳሴ ማርያምን እንኳ የማያውቅ፣ ክህነት የሌለው ነገር ግን በድፍረት ቤተ መቅደስ የሚገባ ሰው ነው፡፡
2.    በየመድረኩ ገንዘብ ሲሰርቅ እጅ ከፍንጅ እየተያዘ ብዙ ጊዜ የተዋረደ አጭበርባሪ ነው
3.    ከሐሰተኛነቱ የተነሳ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠርተውኝ፣ ፕሬዝዳንቱ አስተምረኝ ብለው እኔ ነኝ የማስተምራቸው እያለ “የሚቀደድ”፣ ዱርዬ አመንዝራ ሙሰኛ ነው፡፡ ለማጣራት በየተላከበት ደብር ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ ክፈሉኝ እኔ አስጨርስላችኋለሁ እያለ ከባድ ጥፋት ሲያሰራ የነበረ ሃይማኖት የለሽ ሰው ነው፡፡ ግለሰቡ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት እንደገባ ስድስት ወር ሳይሞላው መኪና የገዛ ሲሆን ደብዳቤ ለማስመራት እንኳን ብር ሳይከፈለው የማይንቀሳቀስ ነው፡፡ ትናንትና እኔ የደኅንነት አባል ነኝ የማህበሩን አላማ አውቃለሁ ድብቅ አላማ ስላለው መፍረስ ነው ያለበት እንዳላለ አሁን ይህ አሳፋሪ ሥራው ሲጋለጥ ቄደር ወስዶና እንደ አዲስ ተጠምቆ የማህበሩ አስተኳሽ ሆኖ እያስተኮሰ ይታያል፡፡
ሌላው ገና ከጅምሩ በማጭበርበር ሥራውን የጀመረው ታዴዎስ የተባለው፣ ትክክለኛ ስሙ ግን አበበ ሽፈራው የሆነውና የተማረ መስሎ የህግ ክፍል ሆኖ ሲሰራ የነበረው፣ ያልተማረውን ህግ ስሙን ቀይሮና የወንድሙን የታዴዎስን መረጃ የራሱ አድርጎ ባልተማረው የህግ ትምህርት ስም ህግን ሲጥስና ፍትህን ሲያዛባ የቆየ ሰው ነው፡፡ በተጨማሪም ወሊሶ ስብከተ ወንጌል ተመድቦ በሄደ ጊዜ ሴት አስገድዶ መድፈሩ ሲታወቅ ጉዳዩ በሽምግልና ተሸፋፍኖለት ቀርቷል፡፡
ሌላው የሙሰኞች አለቃ የሆነው መ/ሰ ዳዊት ያሬድ ከዚህ ቀደም በአባ ሰላማ ብሎግ እንደተገለጸው በተለይ በጎንደር ተወላጆች ላይ የተለየ ጥቃት በማድረሱ አባት እንደ ሌላቸው ልጆች እየኮረኮመንና እያሳደደን ነው ሲሉ ብሶታቸውን በቅኔ ገልጸው ነበር፡፡ የአራዳ ክፍለ ከተማ ስራ አስኪያጅ በነበረበት ጊዜ በህዝቡና በካህናቱ በኩል ጩኸት ስለበዛ ከሥራ አስኪያጅነቱ ሊነሳ ችሏል፡፡ አምስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም ያካበተው ሃብት 30 ወይም 40 ዓመት ሰርተው ሌሎች ያላገኙት ሲሆን፣ እርሱ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቃሊቲ ላይ ትልቅ ቪላ ቤት፣ ጀሞ ላይ አንድ ኮንደሚኒየም፣ አሁን የሚኖርበት ቤት በሰሚት ኮንዶሚኒየም ያለው ሲሆን የ5L ሚኒባስ ባለቤትም ነው፡፡ እነዚህ ሊደበቁ የማይችሉ የሚዳሰሱና የሚታዩ ሀብቶቹ ናቸው፡፡
የማቅ ብሎጎች ግን ከላይ የተጠቀሱትን ግለሰቦች ምንም እንዳላጠፉ በመቁጠርና ከነወንጀላቸውና ከነነውራቸው በመደገፍ ያለመከሰስና ያለመጠየቅ መብት ሰጥተዋቸዋል፡፡ ግመል ውጠው ትንኝ ማጥራት ሥራቸው በመሆኑም እነዚህን ዓመፀኞች ዝም ብለው በዚህ የማይታሙትንና በተግባርም የተፈተኑትን  ሐቀኛ ሰዎች የእነርሱ ደጋፊ ስላልሆኑ ብቻ ስማቸውን እያከፉና እያጠፉ ይገኛሉ፡፡ ለሃይማኖቱ ቀናኢና ሐቀኛ  መሆኑ የተመሰከረለትን ሊቀ ትጉሃን ገብረ መስቀል እና ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ማቅን ስለማይደግፉ ብቻ የስም ማጥፋታቸው ሰለባ ሆነዋል፣ እነዚህ የቤተክርስታየን ልጆች ሥራቸው በታሪክ የማይረሳ ስለሆነ ግን የማቅ ስም ማጥፋት ቢያስተዛዝብ እንጂ ውሃ የሚያነሳ አይሆንም፡፡
ሊቀ ትጉሃን ገብረ መስቀል የሀገረ ስብከቱ ቁጥጥር ሆኖ የሚሰራ ሲሆን ከዚህ ቀደም በኡራኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጥሮ የነበረውን ከባድ የሙስና ችግር ለማጣራት ተልኮ በነበረው የማጣራት ተግባር ሌሎች ሲንሸራተቱና በሙስና ሲጠለፉ፣ እርሱ ግን ማንንም ሳይፈራና ሳያፍር፣ በዘር በጓደኝነት ሳይታለል ብቻውን እንደ ወርቅ ተፈትኖ ያለፈ የቤተ ክርስቲያኒቱ ምርጥና የቁርጥ ቀን ልጅ ሆኖ በመገኘት ታላቅ ታሪክ ሠርቷል፡፡ ባደረገው መልካም ነገር መሸለም ይገባው ነበር፡፡ ማቆች ግን ይባስ ብሎ ቅዱሱን ርኩስ ማለት ልማዳቸው ስለሆነ በሐራ ብሎጋቸው ላይ እርሱ የሰራውን መልካም ስራ ለማጠልሸት ከ30 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በቤተ ክህነትም በሀገረ ስብከቱም የሠራው ሰው እንደመሆኑ አንዲት ትንሽዬ መኪና ገዛ ተብሎ አገር ይያዝ ሲሉ ተሰምቷል፡፡
በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በዘመናዊ ትምህርት ሰይፍ ዘክልኤ አፉሁ የተባለው ሊቀ ጠበብት ኤልያስም የማቅ ወገን ስላልሆነ ብቻ በነኃይሉ ጉተታ አቀናባሪነት ከትምህርት ይዞታው እስከ ሙሰኝነት ሲተች ከርሟል፡፡ ታላቁ አባት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስን አንድ ቄስ እርሳቸውን ተሳድቦ “ዳህጸ ልሳን ነው” ሲላቸው ታዲያ ቢያዳልጥህ ወደ ላይ እንዴት ያዳልጥሃል? ብለው እንደ ነበር ይነገራል፡፡ የድጓው ሊቅ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ በነኃይሉ ጉተታ መሰደብም ሆነ መመዘን አለበት ወይ? ኃይሉ ጉተታም አልታወቀውም እንጂ ያዳለጠው ወደላይ እኮ ነው፡፡ ነገር ግን በሞራልም ቢሆን ሊቀ ጠበብት ኤልያስ በማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ላይ ተፈጥሮ በነበረ የሙስና ችግር እርሱም እንደ ጓደኛው በመቶ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ቢቀርብለትም እምቢ እምነቴን አለውጥም “ወቅብዐ ኃጥአንሰ ኢይትቀባዕ ርእስየ” ብሎ በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ ትልቅ ታሪክ ሠርቷል፡፡
በአንጻሩ የነሃይሉ ጉተታ አማሳኝ ቡድን እንኳንስ በመቶ ሺህ ቀርቶ በመቶ ብርም በየሄደበት ቦታ ፍትህን ሲያጣምሙ ለገንዘብ ብለው ስንት የቤተ ክርስቲያን ሀብት እንዲባክን ሲያደርጉ እንደነበር አገር ያውቀዋል፡፡ እንዲህ ስንል እውነቱን ለመመስከር ያህል እንጂ ሊቀ ትጉሃን ገብረ መስቀልም ሆነ ሊቀጠበብት ኤልያስ ምንም እንከን የሌለባቸው የመላእክት ወገን አድርገን እየሳልናቸውና ለጵጵስና ምርጫ እያጨናቸው አይደለም፡፡ እንደ ሰው ሊሳሳቱ ይችላሉ፣ የሠሩትን መልካም ታሪክ ጥላሸት ሲቀቡትና ሲቀብሩት ስላየን ግን እውነቱን ለመመስከር ያህል ነው፡፡ ምናልባት እነዚህ ሁለት ሰዎች የማቅ ወዳጆች ቢሆኑ ኖሮ እኮ ይህን ጊዜ ባለ ክንፍ ጻድቃን ተብለው ይሞካሹ ነበር፡፡
በመጨረሻም ለሊቀ ማእምራን የማነ እና ለመጋቤ ብሉይ አእመረ ጥቆማ ሳንሰጥ አናልፍም፡፡ ይኸውም ባለፈው መጋቢት ወር ላይ የተላለፈው የሙዳየ መጻት ቆጠራ ጉዳይ ደብዳቤ ጽፎ ብቻ ዝም ማለት ሳይሆን ክትትልና ቁጥጥር ቢደረግ፣ እስከ ፍጻሜው ድረስ ክትትል ተደርጎም ውጤቱ ቢመዘን፣ ለዝውውርም ሆነ ለማሰራት አስቸጋሪ እየሆነ ያለው በዚህ ረገድ አብያተ ክርስቲያናቱ የተዘጋና የተከፈተ እየተባለ ስም እየወጣላቸው ስለሆነ አድባራቱን በሙሉ አንድ ገዢ የሆነ ሥርዓት በአስቸኳይ ቢዘረጋ መልካም ነው እንላለን፡፡ ሌላው በአንዳንድ አድባራት እየተፈጸሙ ያሉትን የሕግ ጥሰቶች ከደብር ደብር በማዛወር ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ተመጣጣኝ የሆነ እርምትና አስተማሪ የሆነ ቅጣት ቢደረግ ጥሩ ይሆናል እንላለን፡፡ ለምሳሌ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ከአለቃ እስከ ጸሐፊ  ከሞያቸው ጀምሮ እስከሚፈጽሙት በደል ጉዳያቸው በሚገባ ቢታይ፣ በቦሌ ቡልቡላ መድኃኔ ዓለም እየተፈጸመ ያለው ዘረፋ በአስቸኳይ እንዲቆም ቢደረግና ችግሩ ቢፈታ ጥሩ ነው የሚል እምነት አለን፡፡
 
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የምንገኝ ካህናት

1 comment:

  1. ቤተ ክርስቲያን ለራሷ ጥሩ ቤት እንድትሠራ ክፉ ጐረቤት ማቅን ጥሎባታል።
    እሷም የልቧን ታገኛለች ማቅም የምኞቱን ይከፈላል። እግዜር እጀ ሰፊ ነውና፤

    ReplyDelete