Thursday, July 30, 2015

“መድሎተ ጽድቅ” በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን (ክፍል አንድ)

 READ IN PDF

ምንጭ፡- ጮራ http://www.chorra.netመንደርደሪያ
ታላቁ ሊቅ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ “ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ” በተባለውና መሠረታውያን የኾኑ የክርስትና ትምህርቶችን በእግዚአብሔር ቃል መሠረትና የጥንት አበውን ምስክርነት በመጥቀስ ባዘጋጁት መጽሐፋቸው መቅድም ላይ፥ መጽሐፉ የተጻፈበትን ምክንያት ካተቱ በኋላ እንዲህ ብለው ነበር፤
… ይህን ሁሉ ማተታችን መምህራኑ የማያውቁት ኾነው እነርሱን ለማስተማር አይደለም። ነገር ግን የዚህን ሐሳብና ምስጢር ቃለ መጻሕፍትን መመገብ የሚያዘወትሩ ሊቃውንት እያወቁት ሳለ፥ ብዛት ያላቸው መሃይምናን አያውቁትም። አያውቁምና መምህራን ለማነጽ ጠቃሚ መኾኑን ተረድተው የሚደግፉትን፥ ‘ለሕዝበ ክርስቲያንም ይረባል’ ሲሉ የሚያቅዱትን ጥልቅ አስተያየት፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያልጸና የመሃይምናኑ አእምሮ እንደማይደርስበት የታወቀ ቢኾንም (፩ቆሮ. ፪፲፩)፥ መሃይምናኑ ራሳቸው ስለ ሃይማኖት ያላቸው ዕውቀት ዝቅተኛ መኾኑን መዝነው ስፍራውን ይለቅቁላቸው ዘንድ ተገቢ በሚኾንበት ፈንታ፥ ሊቃውንቱን በመናፍቃን ስም ቀብተው ‘አብዝኆ መጻሕፍት ያዘነግዕ ልበ።’  የሚል የአረማዊውን የፊስጦስን ቃል እየጠቀሱ (የሐዋ ፳፮፥፳፬) ወዲያውኑ እንደ ተለመደው በሠለስቱ ምእት ሊቃውንት ወንበር ላይ ተቀምጠው ሊፈርዱባቸው እንዳይቸኵሉና በዚሁ አስገራሚ አኳኋን የቤተ ክርስቲያንዋ መሻሻል ዕድል እንዳይሰበር አሥጊ መኾኑን ብቻ ለማሳሰብ ነው። (መሠረት 1951፣ ገጽ 15 አጽንዖት የግል)
በርግጥም አለቃ ያሉት የደረሰ ይመስላል። ዛሬ ትልቁ ችግር መሃይምናኑ የሊቃውንቱን ስፍራ መንጠቃቸውና በእነርሱ ወንበር ላይ ተቀምጠው ሊቃውንቱን “መናፍቅ” የሚል ስም ቀብተው ለመፍረድ መቸኰላቸው ነው። ይህም እርሳቸው እንዳሉት የቤተ ክርስቲያንን መሻሻል ወደ ኋላ የሚጐትት እንዳይኾን ያሠጋል። በዚህ አጋጣሚ ሌላውን ቀድሞ መናፍቅ ማለት አማኝ ለመኾን ማረጋገጫ እንዳልኾነ፥ በዚህ መንገድ መናፍቅ በመባልም መናፍቅ መኾን እንደሌለ መግለጥ እንወዳለን።  

ለዚህ ጽሑፍ መነሻው ያረጋል አበጋዝ የተባለ ዲያቆን “መድሎተ ጽድቅ” በሚል ርእስ የጻፈውና አሳትሞ መጋቢት 2007 ዓ.ም. ለገበያ ያቀረበው መጽሐፍ ነው። መጽሐፉ ተሐድሶኣዊ አገልግሎት ላይ ያተኰሩትን፦ “ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ”ን፥ “ጮራ መንፈሳዊ መጽሔት”ን፥ የተቀበረ መክሊት”ን፥ “የለውጥ ያለህ!!!”ን እና ሌሎችንም የሥነ ጽሑፍ ውጤቶች በመተቸት የተዘጋጀ ነው። ጸሓፊው በእነዚህ ሥራዎች ላይ ትችት ለማቅረብ ሲነሣ፥ ዝም ብሎ እንዳልተነሣና እነዚህ ሥራዎች በሕዝቡ ውስጥ ያሳደሩት ተጽዕኖ ቀላል አለ መኾኑን ስለ ተገነዘበ እንደ ኾነ እንረዳለን። እርሱ ግን፥ የተቻቸው መጽሔትና መጻሕፍት ውጤት እንዳልተገኘባቸው አስመስሎ ቢጽፍም፥ እውነታው እንደዚያ እንዳልኾነና እርሱንም ይህን መጽሐፍ እንዲጽፍ ግድ እንዳለው መካድ አይቻልም። ጽሑፎቻችንን ተችቶ ሲጽፍ፥ በአንድ በኩል እኛ ተሐድሶ ያስፈልጋቸዋል ብለን የገለጥናቸውን ትምህርቶች በመደገፍ፥ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረትም ኾነ በማኅበሩ ውስጥ ለመናገር የማይደፍራቸውን እውነቶች፥ እነዚህን የጽሑፍ ሥራዎች ተተግኖና ‘ቤተ ክርስቲያን የማትለውን ትላለች ይላሉ’ የሚል ምክንያት በመስጠት በነጻነት ለመግለጥ ሰፊ ዕድል እንዳገኘ ተገንዝበናል።

Tuesday, July 28, 2015

“መለከት ድራማ”ና የመጽሐፍ ቅዱስ ይትበሐልን አጠቃቀሙ

“ምነው የ“ጥበብ” መንገድን ከፈጣሪ ቃል ጋር ካልተዘባበታችሁ በ“ጥበብነቷ” ብቻ ማሳየት አይቻላችሁምን? ስለምንስ የማሰናከያን ድንጋይ በትውልድ መንገድ  ላይ  ታስቀምጣላችሁ?”

     “መለከት” ድራማ በተከታታይነት በኢትዮጲያ ብሮድ ካስት ቴሌቪዥን በእሁድ መዝናኛ ፕሮግራም ይቀርባል፡፡  እንደመታደል ጊዜ ሰጥቶ ብዙም ድራማን የመከታተል ልማድ የለኝም ፤ ድንገት ግን እግረ መንገድ ከመጣ አያለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስንና ጌታዬ ክርስቶስን “የሚዳስስ”ና በዚህም ዙርያ በአሉታዊም ሆነ በአዎንታዊ መልኩ የሚንጸባረቅ ከሆነ ትኩረቴን አሳርፍበታለሁ፡፡ እናም “መለከት”ን እንደዋዛ አየሁት ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ይትበሐልን በአንዱ ተዋናይ አማካይነት ሲጠቀም አየሁትና በማስተዋል አጤንኩት ፥ ከዚያም ሁለት ነገርን ከውስጡ እንዲህ አስተውዬዋለሁ፡፡


      መጽሐፍ ቅዱስ እንደሌሎች መጻሕፍት ያይደለ ራሱን ለትችት በማጋለጡ ምንም የማይፈራ ቅዱስ መጽሐፍ ነው፡፡ ለዘመናት መጽሐፍ ቅዱስ “በቃን ፤ ነቃን ፤ ሰለጠን ፤ አወቅን” ባሉት “ልሂቃንና ምሁራን” እልፍ አዕላፍ ጊዜ በአሉታዊነቱ ቢተችም ፤ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ የነበሩት የፍልስፍናው ዓለም ነቢያትም “መጽሐፍ ቅዱስ ከእንግዲህ የመነበቢያው ጊዜ አልፏል” ቢሉም ፥ እነርሱ “ትንቢቱ”ን በተናገሩ ማግስት  “Guinness book of world record” 1988 እ.አ.አ እትም ዘገባው ከ1815-1975 እ.አ.አ ባሉት ዓመታት ውስጥ 2‚500‚000‚000 (ሁለት ቢሊየን አምስት መቶ ሚሊየን) የእንግሊዝኛ ኮፒዎችን በመባዛትና ለዓለም ሕዝብ በመሰራጨት ተወዳዳሪ ያልተገኘለት መሆኑን አስፍሮታል፡፡ ታዲያ! እኒያ “ነቢያት” እንኳንም ትንቢት ተናገሩ አያሰኝም!?

Saturday, July 25, 2015

ውግዘትና - የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት -ክፍል ሁለትበዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
ስለውግዘት ያለን የተሳሳተ ትርጉም
1.    ማውገዝ “መናፍቅ”ን ብቻ ነውን?

     ብዙ ጊዜ የውግዘት ነገር ሲነሳ ከሁሉም ሰው ህሊና የሚደቀኑት መናፍቃን ናቸው ብንል የተጋነነ አይደለም፡፡ እውነት ነው፤ መናፍቃንን በምንም አይነት መልኩ መታገስ አይገባም፡፡
      የአህዛብ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራውና በብዙ ምስክርነት የክርስቶስ ኢየሱስን መንግስት ያገለገለው ቅዱስ ጳውሎስና አቡቀለምሲሱ ቅዱስ ዮሐንስ መናፍቅነት ብቻ ሳይሆን “ሌሎችም” ኃጢአቶች ከእግዚአብሔር መንግስት ውጪ እንደሚያደርጉ ሳያወላዱ ፤ ያለአንዳች ማወላወል በግልጥ ተናግረዋል፡፡ መናፍቅነት ብቻ ያስወግዛል ማለት የኃጢአትን ባህርይ በትክክል አለመረዳትና፤ አርካሽነቱንም አለማስተዋል ነው፡፡
ኃጢአት ምንድር ነው?
       “ኃጢአት” በቁሙ ሲፈታ በደል፣ ዐመጥ፣ ግፍ፣ ህገ ወጥ ሥራ፣ በኀልዮና በነቢብ፣ በገቢር የሚሠራ” በማለት ከገለጡ በኋላ በሌላ የትርጉም አንቀጽ “ኀጥአት” ማለት ደግሞ ማጣት መታጣት፣ ዕጦት፣ ችግር፣ ሽሽት፣ ኩብለላ በማለት ይተረጉሙታል፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (አለቃ)መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡(1948 ዓ.ም)፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡ ገጽ.474) የኋለኛውን ትርጉም በመያዝ ይመስላል፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን “ኃጢአት” የሚለውን ትርጉም ጸጋ እግዚአብሔርን፣ ረደረኤተ እግዚአብሔርን ማጣት፤ ንጽሐ ኅሊናን ማጣት፤ አብርሆተ መንፈስ ቅዱስን ማጣት … ብለው የሚተረጉሙት፡፡ ምናልባትም ኃጢአትን የሚሠራ ሰብአዊ ማንነት ከሚገጥመው ወይም ከሚያገኘው ነገር በመነሳት የሚሰጡት ትርጉም ነው፡፡
   በእርግጥም ኃጢአት በተግባር በተከናወነ ጊዜ ሰዎች ሁሉ የገጠማቸውን ከታላቁ መጽሐፍ ስናስተውል የምናየው እውነት ትርጉሙን ይበልጥ የሚያጎላ ነው፡፡
v መሸሽና የጌታን ድምጽ መፍራት በአዳም (ዘፍ.3፥11)
v መቅበዝበዝና ኰብላይነት በቃየልና በቃየል (ዘፍ.4፥14)
v ስብራት በዖዛ(2ሳሙ.6፥7)
v ሰብዓዊ ክብርን ማጣት በናቡከደነጾር(ዳን.4፥25)
v የንጉሥ ብልጣሶር መሞት (ዳን.5፥30)
v በትል ተበልቶ መሞት በሄሮድስ(ሐዋ.12፥23)
v ይህንን ዓለምና በውስጡ ያለውን መውደድ በዴማስ(2ጢሞ.4፥10)
v እና ሌሎችንም በመያዝ የተረጎሙት፡፡
      ኃጢአት” ማለት ስህተት፣ ክፋት፣ ህግን መተላለፍ፣ ዓመፃ በጎ ነገርን አውቆ አለመሥራት፣ በእምነት መሠረት አለመኖር፣ ወደ እግዚአብሔር ክብር አለመብቃት፡፡” (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፡፡ የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፡፡ ገጽ.133)
     “ኃጢአት ማለት ለእግዚአብሔር ለፈቃዱም አለመገዛትና አለመታዘዝ፥ በሃሳብም፥ በንግግርም በሥራም መግለጥ ነው፡፡” (መልከ ጼዴቅ(አባ)፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ሁለተኛ ዕትም፡፡(1996)፡፡አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡ ገጽ.129)

Thursday, July 23, 2015

በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የማኅበረ ቅዱሳን አለኝታ የነበረው መ/ር ቸሬ አበበ ተባረረበቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሬጂስትራር የነበረው መ/ር ቸሬ አበበ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ለሆኑ ግለሰቦች ሳይማሩና የሚጠበቅባቸውን ሳያሟሉ ዲግሪና ዲፕሎማ እንዲሁ ሲሰጥ በመገኘቱ ከሥራ መባረሩን ምንጮች ገለጹ፡፡ በቀንም በማታም ለሚማሩ የማቅ አባላት እንዳሻው ዲግሪና ዲፕሎማ በማደል የሚታወቀው መ/ር ቸሬ አበበ፣ ወደ ቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ከመግባቱ በፊት የማቅ የጥናትና ምርምር ክፍል ሆኖ መስራቱ ሲታወቅ ወደ ኮሌጁ በዓላማና የማቅን ተልእኮ ለመፈጸም እንደገባ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ይህን በተመለከተ ብዙዎች ኮሌጁ ከማቅ ተጽእኖ ነጻ እንዲወጣ የቸሬን ጉዳይ ቢጠቁሙም ሰሚ ሳያገኙ እስካሁን ድረስ ብዙ ጥፋት ደርሷል፡፡

መ/ር ቸሬ አበበ በኮሌጁ ማኅበረሰብ ዘንድ የሚታወቀው ወሬ በማመላለስና ሠራተኛን ከሠራተኛ በማጋጨት ጠብ ዘሪ ጠባይ ሲሆን፣ በእርሱ ዘመን እርሱ ያላጣላውና ያልተጣላ አይገኝም፡፡ በዚህ ጠባዩ የአቡነ ጢሞቴዎስ ቀራቢ በመምሰል በኮሌጁ የሚያጋጥሙ አንዳንድ ችግሮችን በማባባስና መረጃዎችን ለማቅ የወሬ ፍጆታ እንዲውል በማድረግ በኮሌጁ ውስጥ የማቅ ጆሮ ሆኖ ሲሰራ ነው የኖረው፡፡ የያረጋል አበጋዝ አድናቂ የሆነው መ/ር ቸሬ አበበ ኮሌጁ በሃይማኖት እንዲጠረጠርና በማቆች ግቢው እንዲደፈር ለያረጋል መረጃ በመስጠት ትልቁን ድርሻ መወጣቱን ምንጮቻችን ያስረዳሉ፡፡ በግቢው እንደፈለገች ትፋንን ከነበረችው ከወ/ሮ ዘውዴ ጋር ልክ እንደ መ/ር ደጉ የተለየ ቀረቤታ እንደነበረው የሚነገረው መ/ር ቸሬ አበበ ቀረቤታው በአገር ልጅነት ይሁን በሌላ ያልተመለሰ የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ እስካሁን አለ፡፡

Wednesday, July 22, 2015

“ወሐሰት ርዕሰ ዓመፃ” “ሐሰትም የዓመፃ አበጋዝ ናት” (መዝ. 26፥12)“የሐሰት ምስክሮች” ክርስቶስን እሩቅ ብዕሲ ነው፣ ራሱን የአይሁድ ንጉሥ ብሏል ብለው የሐሰት ምስክሮችን በማደራጀት ክርስቶስ ያላለውን ብሏል፣ ያላደረገውን አድርጓል በሚል የሐሰት ክስ ለሞት የሚያበቃ ምንም ምክንያት ያልተገኘበት ሆኖ እያለ፣ ይልቁንም ለታሠሩት ነፃነትን ለተበደሉት ፍትህንና ሰላምን ይዞ መጥቶ እያለ፣ በመልካምነቱ ያልተደሰቱት አይሁድ፣ ለሁሉም ሰው እኩልነትን ስላወጀና ፈሪሳውያን በህዝቡ ላይ ያደርሱት የነበረውን ኢፍትሃዊነትና በደል ስላጋለጠባቸው ነቃብን፣ በሕዝቡ ዘንድ የነበን ክብር ይቀንሳል በሚል ሥጋት የክብር ጌታ በውሸት በጥላቻ ተነሳስተው ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት፡፡ እግዚአብሔር የሐሰትን አደገኛነት ይህን አስቀድሞ በመንፈሰ ትንቢት የገለጸለት ንጉስ ቅዱስ ዳዊት ሐሰት መናገርና መመስከር አደገኛ መሆኑን ስለተረዳ፣ ሐሰት የኃጢአት ሁሉ አውራ አበጋዝ ናት አለ፡፡ ሐሰት ታሪክን ስለሚያበላሽና እውነተኞችንና ንፁሃን ስለሚያስገድል “ወሐሰት ርዕሰ ዓመፃ የሐሰት ምስክርነት የኃጢአት ሁሉ ራስ ነው አለ፡፡
        የአገራችን ታሪክ ስንመረምር የተከናወኑ በጎ ነገሮች የመኖራቸውን ያህል ትልልቅ ስህተቶች ተፈፅመዋል፡፡ በአገራችን የገባው ስህተት እውነትን አስለቅቆ የእውነት ቦታ ነጥቆ ይኖራል፡፡ በሌላው ዓለም ስህተቶች ሲገቡ ተነቅሰው ይወጣሉ፣ በአገራችን ግን ተተክለው ይቀራሉ፡፡ እንዲጸኑና እውነት መስለውና የእውነትን ቦታ ነጥቀው እንዲቀመጡ ይደረጋል፡፡  ለምሣሌ ያህል ብንጠቅስ ዘርዓ ያዕቆብ በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፈጃቸውን ሰማዕታት ማለትም ደቂቀ እስጢፋኖስ የተባሉት ሰማእታት ለእምነታቸው ሰማዕታት ሆነው እያ ነፍሰ ገዳዩ ዘርዓ ያዕቆብ ፃድቅ ስለ ሃይማኖታቸው የሞቱትን ሰማእታት ደግሞ መናፍቃን ብለው ታሪክ አጣመው ፃፉ ደብተሮች ምክንያት እስከ አሁን ድረስ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን ትልቅ ጠባሳ ሆኖ ንስሃ ትገባበት ሲገባ፣ ጭራሽ በየትኛውም ሃይማኖት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሰ ገዳዩን ፃድቅ እያለች ትገኛለች፡፡ 

Tuesday, July 21, 2015

ምናለ ቤተ ክርስቲያንን መሳቂያና መሳለቂያ ባናደርጋት?

የተአምረ ማርያም አንካሳ ሀሳብ

Read in PDF 
በዲያቆን ያለው
ባለፈው ሐምሌ 5/2007 ዓ.ም. በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከቅዳሴ በኋላ ተአምረ ማርያም በድምፅ ማጉሊያ ሲነበብ እጅግ ነው ያፈርኩት፡፡ ያሳፈረኝም የተነበበው ክፍል በመጽሐፍ ቅዱስ የሚታወቅን ታሪክ ተአምረ ማርያም ወደራሱ ወስዶ የኢየሱስን ለማርያም ሰጥቶ በማቅረቡ ነው፡፡ ያን “ተአምር” መርጠው ያነበቡ ቀሳውስት ምናልባት ለበዓሉ ተስማሚ ንባብ መረጥን ብለው ልባቸው ወልቋል፡፡ ለካስ ተአምረ ማርያም ልቦለድ ነው የሚባለውን ብቻ ሳይሆን የወንጌልን እውነት ለመለወጥና የኢየሱስን አዳኝነት በማርያም ለመተካት ታልሞ የተጻፈ ነው ብዬ እንድደመድም አድርጎኛል፡፡ ምናለ ቤተ ክርስቲያንን መሳቂያ መሳለቂያ ባናደርጋት? የሚል ሐሣብም መጣብኝ፡፡  
እንደሚታወቀው ሳውል ክርስቲያኖችን እያሳደደ ወደ ደማስቆ ሲወርድ ድንገት በእርሱ ዙሪያ ከሰማይ ብርሃን ካንጸባረቀበትና ምድር ላይ ከወደቀ በኋላ “ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ?” የሚለውን ድምፅ ነው የሰማው፡፡ ከዚያ ሳውል ጌታ ሆይ አንተ ማነህ? ብሎ ጠየቀ፡፡ የሰማው ድምፅም “እርሱም፦ አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል አለው።” (የሐዋ. 9፥1-5)፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ማርያም ፈጽሞ የለችም፡፡ ተአምረ ማርያም ግን ሌላውን የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ምዕራፍ 12 ክፍል ከዚህ ጋር በማገናኘት ጳውሎስ ስለማርያም እንደተናገረ አድርጎ ጽፏል፡፡
በሐዋርያት ሥራ ላይ የተጻፈው ታሪክ በ2ኛ ቆሮንቶስ ምእራፍ 12 ላይ ከተጻፈው ታሪክ ጋር የሚገናኝ አንዳች ነገር የለውም፡፡ በሐዋርያት ሥራ ላይ እንደተጻፈው ሳውል ከሰማይ ብርሃን ካንጸባረቀበትና የጌታን ድምፅ ከሰማ በኋላ፣ የተናገረውንም ድምፅ ማንነት ከለየ በኋላ ተናጋሪው የሚለውን ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ “ጌታም፦ ተነሥተህ ወደ ከተማ ግባና ታደርገው ዘንድ የሚያስፈልግህን ይነግሩሃል አለው።” በተነሳና አይኖቹን በከፈተ ጊዜ ግን ማየት አልቻለም፡፡ ሰዎችም እየመሩት ወደ ደማስቆ ወሰዱት፡፡ ለሶስት ቀን ሳያይ ሳይበላና ሳይጠጣ ቆየ፡፡
በዚህ መካከል ግን ወደ ሶስተኛው ሰማይ ተነጠቀ የሚል ታሪክም አልተጻፈም፡፡ ያ ከዚያ በኋላ የተፈጸመ ታሪክ ነው፡፡ ሆኖም አንዳንድ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት ሁለቱን አያይዘው ነው የሚተረጉሙት፡፡ ለምሳሌ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ “ነቅዕ ንጹሕ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ እንደ ገለጡት “ቅዱስ ጳውሎስ ይህን [2ኛ ቆሮንቶስ] መልእክት የጻፈው በ፶ (፶፯) ዓ.ም. ነው፡፡ ከ፶ው ዓመት ፲፬ ሲነሣለት ፴፮ ዓመት ይቀራል፡፡ እንግዲህ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ደማስቆ ሲሄድ በመንገድ ላይ ብርሃን በርቶበት ጌታም ተገልጦለት ነበርና በአካለ ሥጋ ወይም በአካለ ነፍስ አላወቀውም እንጂ እስከ ሦስተኛው ሰማይ ወጣሁ በዚያም ሰው ሊናገረው የማይቻል ነገር ሰማሁ ያለበት ዘመኑ ጌታችን በተወለደ በ፴፮ ዓመት መሆኑን ያስረዳናል፡፡” ብለዋል (ገጽ 164)፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት ንባቡ ከእነ ትርጓሜው ግን ጊዜውን ከዚህ ውጪ ነው የሚያደርገው፡፡ 

Sunday, July 19, 2015

ውግዘትና - የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት -ክፍል አንድ በዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
ዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ ከዚህ በፊት ሰፋ ያለ ተከታታይ ትምህርት እንደላከልን ይታወቃል። አሁንም አዲስ ተከታታይ ትምህርት ልኮልናል። ይህ ትምህርት በዘፈቀደ ማንም እየተነሳ የሚያካሂደውን ውግዘት የተመለከተ ነው። በትምህርቱ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው በውግዘት ውስጥ ቤተክርስቲያን ሊኖራት የሚገባው ኃላፊነት ነው። ይህ ጽሁፍ  በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት ብዙዎችን ያስተምራል ብለን እናምናለን፡፡ መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።

መግቢያ
“ሳትሞት ሞተች ብለው ምንም ቢቀብሯት
አትሞትም፤አትሞትም፤አትሞትም እውነት፤
እውነት የእግዜር ገንዘብ እንደእግዜር ባህርይ
ዘላለም ሕያው ናት በምድር በሰማይ፡፡”
(ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(አለቃ)፡፡ ሃይማኖተ አበው ቀደምት
ወፍልጠተ ውሉድ ደኃርት(ያልታተመ)፡፡
    እውነት አትሞትም ማለት አትቀበርም ማለት አይደለም፡፡ ህያው ነገር ይቀበራል፡፡ የሚያሳዝኑት የማይሞተውንና ፤ማዳን የሚቻለውን ህያው ነገር የሚቀብሩ ወይም ለመቅበር የሚሞክሩ ናቸው፡፡ እውነት ባህርይዋ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ልትቀበር እንጂ በፍጹም፤በፍጹም ልንገድላት፤ ልትሞትም አትችልም፡፡ አይሁድ እውነቱንና እውነተኛውን ጌታ (ዮሐ.14፥6፤17፥17፤18፥37) “በመግደላቸው” የተደሰቱ ይመስላል፤ እንዳይነሳ ማድረግ ግን አይችሉም፡፡
    እግዚአብሔርን መካድ ይቻላል፡፡ እርሱን ብንክደው “ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።” (2ጢሞ.2፥13) ፤ “የእኛ አለማመንም የእግዚአብሔርን ታማኝነት ማስቀረት አይችልም፡፡” (ሮሜ.3፥3)፡፡ ስለዚህ እኛ ስለእርሱ ልንመሰክር ተጠርተናል፡፡ ዳሩ ባንመሰክረው ፤ ለትውልድም ባንናገረው በአዕምሮዐችን ተቀብሮ ይኖራል፡፡ ነገር ግን እርሱ ብንቀብረውም  እርሱ ራሱን ጠብቆ ይኖራል፡፡ በቆሻሻ ላይ ወጥታ እንደማታድፍ ፀሐይ እርሱ በንጹሐ ባህርይ ገንዘቡ ፥ ቢቀበርም ሙስና መቃብር የማያገኘው ህያው ነው፡፡
   ለዘመናት መናፍቃንና ኃጥአን እግዚአብሔርንና የእውነትነት ባህርይውን ሲክዱና ሲቃወሙ ኖረዋል፡፡ ብዙ ጊዜም ሊቀብሩ፤ ሊያጠፉ፤ ቀብረው ሊያስቀሩም ጥረዋል፡፡ ነገር ግን ራሱን የማይክድ ጌታ ህያው ሆኖ ሲኖር አይተናል፡፡ እርሱ ራሱን አይክድምና፡፡ ለእውነት የጠራን የታመነ፤ ያለውንም የሚያደርግ፤ ከክፉም የሚጠብቀን  ነውና ፍቱም ልንታመንበት ይገባናል፡፡(1ተሰ.5፥24፤2ተሰ.3፥2)
ውግዘት
    ውጉዝ” የሚለውን ቃል በቁሙ የተወገዘ ፣ የተለየ ፣ ርጉም ፤ ህርም የተባለ ፣ የተከለከለ ፣ ህግ የነቀፈው ያፀየፈው ሥራ ማናቸውም ሁሉ” በማለት ይተረጉመዋል፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡ (1948 ዓ.ም) ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡ገጽ.377)
   በሌላ ትርጉም “ግዝት ፥ ውግዘት ፤ ከምዕመናን አንድነት መለየት፡፡” በማለት ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይፈታዋል፡፡ (የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር (2002)፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9ኛ እትም ፣ አዲስ አበባ፡፡ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡ገጽ.248)
    “ግዝት ማለት አንድ ምእመን ከሃይማኖት ወጥቶ ከበጐ ምግባር አድጦ ሲገኝ ከሕዝበ ክርስቲያን እንዲለይ በሥልጣነ ክህነት የሚፈጸም መንፈሳዊ ቅጣት ነው፡፡” ይላሉ፡፡ (ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ (ሊቀ መዘምራን) መርሐ - ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት (1989 ዓ.ም)፤ አዲስ አበባ፡፡ አሳታሚ ገ/ሥላሴ ብርሃኑ፡፡ ገጽ 148) 
    ከዚህ በመነሳት የውግዘትን ጽንሰ ሐሳቦችን ብንመለከት እንዲህ ማለት ይቻለናል፡፡
1.    መለየት (ከአንድነት ማግለል) ፡-  በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አስነዋሪ የዝሙት ኃጢአት በተሰራ ጊዜ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ አለ … “ … ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። … ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ … ”(1ቆሮ.5፥2-4)
    ጌታ ስለይቅርታ ባስተማረበት አንቀጹም አንድ ሰው በበደለና ባጠፋ ጊዜ፤ በተደጋጋሚ ሳትታክት ቤተ ክርስቲያን ከመከረች በኋላ አልመለስ ቢል ልታደርግ የተሰጣት ሥልጣን አንዱ እንዲህ የሚል ነው፡፡
  “ … በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።” (ማቴ.18፥16-17)

Thursday, July 16, 2015

በሲልጤ ዞን በክርስቲያኖች ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት አሁንም እንደቀጠለ ነው።በሲልጤ ዞን ያሉ ኦርቶዶክሳዊያን ምዕመናን በአካባቢው የእስልምና አክራሪዎች እየደረሰባቸው ያለውን ግፍና ውርደት አስመልክተው የድረሱልን ጥሪ ማቅረባቸው እና የእኛን ብሎግ ጨምሮ የተለያዩ ብሎጎች ዜናውን እንደሰሩት ይታወቃል። ይህን የድረሱልን ጥሪ ማቅረባቸው እንደ ትልቅ ስህተት ተቆጥሮ ወገኖቻችን በዞኑ አክራሪ ባለሥልጣናት ተጨማሪ እንግልት እየደረሰባቸው ይገኛል። እንዲያው የደረሰባቸውን ግፍ እንዲያስተባብሉም ጫና ተደርጎባቸዋል። የማስተባበያ ደብባቤው አጽፈዋቸዋል። ከዛም አልፎ በፍርድ ቤት ተከሰዋል። 


እንዲህ ያለው አካሄድ ተጨማሪ ጫናን የመፍጠር እንጂ መፍትሔ የማፈላለግ ዘመቻ እንዳልሆነ የአካበባቢው ባለሥልጣነት እንዴት እንዳልገባቸው አላወቅንም። መንግስትም በሐይማኖት ጉዳይ የሚፈጠር ቀውስ፤ ቀውሱ የተፈጠረበትን አካባቢ አልፎ ሊሄድ እንደሚችል መገንዘብ ያቅተዋል ተብሎ አይጠበቅም። ቀጣይ ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች መፍትሔም አይሆኑም። ወገኖቻችን ያነሱዋቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ አለባቸው።
በሀገሪቱ ውስጥ እያቆጠቆጠ ያለ አክራሪነት መኖሩ የሚካድ አይደለም። የሲልጤ ዞን ደግሞ ዋናው የሰለፊዎች መፈልፈሊያ ነው።
ይህ ሁኔታ እርግጥ ሆኖ እያለ ጭራሽ ተበደልን ያሉ ወገኖችን ሰብስቦ ፍርድ ቤት ማቅረብ አክራሪው ሀይል የደረሰበትን የእብሪት ደረጃ ያሳያል። መንግስትም ገብቶትም ይሁን ሳይገባው የአክራሪዎቹን ሀሳብ ደግፎ ቆሞ ይታያል። ቤተክህነት እንደተለመደው አንጥፋ ተኝታለች። ለልጆችዎ የድረሱልኝ ጥሪ ምላሹ እስር ሲሆን ምንም ለማለት አልቻለችም። ወይም አልፈለገችም። ወገኖችችን ወደ ፍርድ ቤት የተወሰዱት ቤተክህነት ነገሩን በግዴለሽነት በማየትዋ ነው። አስፈላጊውን ክትትል ብታደርግና ድምጽዋን በተገቢው ሁኔታ ብታሰማ ምላሽ መገኘቱ አይቀርም ነበር።

Saturday, July 11, 2015

የሰበካው (የአጥቢያው) አባል ያልነበረው የሰበካ ጉባኤ ም/ሊቀመንበር ከኃላፊነቱ ተነሣየደብረ ሲና ቅዱስ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ሰበካ አባል ሳይሆን በተጭበረበረ መንገድ የሰበካ ጉባኤው ም/ሊቀመንበር ሆኖ የቆየው ዮናስ ሽፈራው ከም/ሊቀመንበርነትና አባልነት ተሰናበተ፡፡ በማኅበረ ቅዱሳን አባልነትና ደጋፊነት የሚታወቀው ይህ ግለሰብ በተጭበረበረና ከቃለ ኣዋዲው ደንብና መመሪያ ውጪ የተመረጠ በመሆኑና በኃላፊነት በቆየባቸው ዓመታትም የቃለ ዐዋዲውን ደንብና መመሪያ አክብሮና ጠብቆ ባመለገኘቱ ሊሰናበት እንደቻለ የተጻፈበት ደብዳቤ ያስረዳል፡፡ በተደረገው ማጣራትም ግለሰቡ ለደብሩ የሰበካ ጉባኤ አባልነት የሚያበቃ በቂ ማስረጃ እንደሌለው ከባሕር መዝገቡ ተረጋግጧል፡፡ 
በእግድ ደብዳቤው ላይ እንደተጠቀሰው ግለሰቡ በግንቦቱ ሲኖዶስ የመክፈቻ ጸሎት ላይ ከኃላፊነቱ ውጪ የሰንበት ት/ቤቱን ወጣቶች በማስተባበር የጉባኤውን መክፈቻ በማደናቀፍ፣ የሰንበት ት/ቤቱ አመራር የ2007 ዓ.ም. የፋሲካን በዓል ምክንያት በማደረግ ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ህሙማን ድጋፍ በሚል የሰበሰበውንና የት እንደደረሰ ያልታወቀውን ገንዘብና ሌሎችንም ጥፋቶች መሰረት በማድረግ የአመራር ለውጥ ለማድረግ በተጠራው ስብሰባ ላይ ችግር ሲፈጥር በመገኘቱና በሌሎችም ምክንያቶች ከኃላፊነቱ ሊነሳ ችሏል፡፡ ይህ ግለሰብ እስካሁን የተደረሰበት የሰበካው አባል ሳይሆን የሰበካ ጉባኤ ም/ሊቀመንበር የሆነ የመጀመሪያው ሰው ነው፡፡  

Thursday, July 9, 2015

የምናመሰግናችሁ ብቻ ሳይሆን የምንነቅፍባችሁም ነገር አለ“ንብላዕ ወንስተይ ጌሠመ ንመውት ኢያስሕቱክሙ አኀዊነ እስመ ነገር አኩይ ግዕዘ ሠናየ ያማስን”
“ነገ እንሞታለንና እንብላና እንጠጣ። አትሳት ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋልና” 1ቆሮ. 15፡33

ይድረስ ለሊቀ ማዕምራን የማነና ለመጋቤ ብሉይ አእመረ በቅድሚያ ለእናንተ ያለንን አክብሮትና አድናቆት መግለጽ እንወዳለን፡፡ በአንድ ወቅት አዞ እና ጦጣ ጓደኝነት ገጠሙ፡፡ ሁለቱም መኖሪያቸውና ምግባቸው ለየቅል ሲሆን አዞ በውሃ የሚኖርና ሥጋ በል የሆነ እንስሳ ነው፡፡ ጦጣ ደግሞ በዛፍ ላይ ነግሣ የምትኖር ፍራፍሬዎችን ሸምጥጣ የምትበላ ወጥታ ወርዳ ዘላና ቦርቃ ከአንዱ ዛፍ ጫፍ ወደ አንደኛው ዛፍ እየተወረወረች የምትመገብ እንስሳ ነች፡፡ አዞ ውሃ ውስጥ የገባውን ሁሉ ከሰው እስከ አንበሳ አድፍጦ በማጥቃት ምህረት የለሽ በሆነ ባህርዩ ይታወቃል፡፡ አዞ የክፉ ሰዎች ምሳሌ በመሆንም ይታወቃል፡፡ እሱ በሚኖርበት አካባቢ ያለ ምህረት በጭካኔ ስለሚያጠቃ እሱም የብስ ላይ ወጥቶ ለመቀመጥ ለመዝናናት ከ1-2 ደቂቃ በላይ መቀመጥ አይሆንለትም፡፡ ኮሽታ በሰማ ቁጥር ይደነግጣል ዘሎ ውሃ ውስጥ ይገባል፡፡ ባጠቃላይ ሰላም የለውም፡፡ ክፉ ሰዎች ነፍሰ ገዳዮችም ተረጋግተው አይኖሩም፣ ይጨነቃሉ ሰላም የላቸውም፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ለክፉዎች ሰላም የላቸውም እንደ ተባሉ (ኢሳ. 57፥21) ማለት ነው፡፡ 

ወደ አዞና ጦጣ ጉዳይ እንመለስና አዞ ከመኖሪያ ቤቱ እየወጣ ፀሐይ ለመሞቅ ጦጣ ካለችበት ዛፍ ሥር ይተኛል፡፡ መቼም ክፉዎች ለአላማቸው ሲሉ የማይሆኑት ነገር የለምና አዞ ሆዬ ጦጢትን ለመብላት ፈለገ፡፡ ነገር ግን እሷ ያለችው ሰማይ እሱ ያለው መሬት ላይ ሆነና እስዋን የመብላት ህልሙ እውን የማይሆንለት ሆነ፡፡ ከዚያ አንድ ሃሳብ መጣለት ጦጢትን የሚያጠምድበት ዘዴ ዘየደ፡፡
“ጦጢት ሆይ” አለ፡፡
በጥሩ ቃልና ቅላፄ “አቤት” አለች፡፡
“እንደ ምንድነሽ?” አላት ሰላምታ ጀመረና ተግባቡ፡፡ ከዛ “እኔ ምልሽ ለምንድነው እኔ አንቺ ሰፈር እየመጣሁ ስጎበኝ አንቺ ግን የእኔን ሰፈር የማታይልኝ?” አላት፡፡ ይባስ ብሎ የአዞ መኖሪያ ጥሩ እንደሆነ ዛፉ ላይ ተንጠልጥሎ ኑሮ ጥሩ አይደለም ብሎ የእስዋን ኑሮ አንቋሸሸባትና አናናቀባት፡፡ ከአሁን በፊት ጓደኛው እባብ እናታችን ሄዋንን የያዘችውን አናንቆ ክብርዋን እንዳስጣላት ጦጢትም ከነበራት የኑሮ ከፍታ ክብር የሱ መኖሪያ በጣም ጥሩ እንደሆነ ሲገልፅላት ከላይ ታች ጉድጓድ ውስጥ ይሻላል ብላ በሱ ሃሳብ ተጠልፋ ወረደች ተስማማች፡፡
“ነገር ግን እኔ ወዳንተ መኖሪያ መሄድ አልችልም ምክንያቱም እኔ መዋኘት አልችልም” አለችው፡፡
“ለሱ አታስቢ እኔ አዝልሻለሁ” አላት
“ካዘልከኝማ ጥሩ” ብላ የዋሁዋ ጦጢት በክፉው አዞ ተታልላ ታዘለችና ዋና ተጀመረ፡፡ ሰዋኙ ሲዋኙ በከንቱ ውዳሴ እያሞካሸ ስለ ውበቷና ስለ ፀጉርዋ ልስላሴ ሲነግራት “አመሰግናለሁ” አለች፡፡
አሁን ወደ ጥልቁ መግባት ሲጀምሩ ከእጁ ማምለጥ እንደማይቻል ሲያውቅ “አሁን እኔ ካንቺ የምፈልገው ልብሽን ነው” አላት እና ሊበላት እንደሆነ አሁን ገና ገባት፡፡ ብልሃት መቼም ከሞትም ቢሆን ያስመልጣል እና አንድ ሃሳብ መጣላት፣ ወደ ልብዋ ተመለሰች፣ “እንዴ ለምን አልነገርከኝም?” አለችው፡፡
“ምኑን?” አላት፣
“ልቤን እንደምትፈልግ እንዴት ቅድም አልነገርከኝም? ልቤን እኮ እዚያው እዛፉ ላይ አስቀምጨው ነው የመጣሁት!” አለችው፡፡
“ታዲያ ምን ይሻላል?” አላት
“አንድ አፍታ መልሰኝና ላምጣልህ” አለችው፡፡
“እሺ” ብሎ ተሸክሞ ወደ ዳር አወጣት፣
“እዚህ ስፍራ ላይ ጠብቀኝ” ብላ ዛፍ ላይ ከወጣች በኋላ ልብ ሊበላ የጐመጀው አዞ “ልብሽን ይዘሽ ነይ እንጂ ውረጂ” ሲላት፣
ከስህተትዋ ተምራ ወደ ልብዋ በመመለስዋ “አግኝቸዋለሁና ተወው ተመለስ” አለችው፡፡ ታዲያ የአዞና የጦጢት ጓደኝነት እንዴት ወደሌላ አቅጣጫ እንደሄደ እንይ፣ ምንም እንኳን ጦጢት በብልጠትዋና በብልሃትዋ ከሞት ብታመልጥም ሁልጊዜ ወደ ጥልቁና ወደ አደገኛ ቦታ ከሄድን በኋላ ሁልጊዜ እናመልጣለን ማለት አይደለም መቅረትም አለና፣ መስመጥም አለና፡፡

Tuesday, July 7, 2015

ይድረስ ለመምህር ዘመድኩን በቀለ፡- ሰባኪዎቻችንና መምህራኖቻችን ወዴየት እያመሩ ይኾን?!ከዲ/ን ኒቆዲሞስ
በዚህ ርዕሰ ጉዳይ እንድጽፍ ያስገደደኝ ከሰሞኑን መምህር ዘመድኩን የተባለ የኢትዮጵያ ቤ/ን አገልጋይ በፌስ ቡክ ገጹ ያስነበበን ነገር እረፍት ቢነሣኝ ነው፡፡ መምህር ዘመድኩን በሊቢያ በአይ ኤስ አክራሪ ቡድን ሰማዕት የኾኑትን ወንድሞቻችን፣ ቤተሰዎቻቸውን በማጽናናት፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያንን አስተባብሮ ሲያደርገው በነበረው ቀና የኾነ አገልግሎት ስንቶቻችን አስደስቶን ከልባችን መርቀነው እንደነበር የትናንትና ገና ያልበረደ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡
ከሰሞኑን ግን መምህር ዘመድኩን በደቡብ አፍሪካ ባለው መንፈሳዊ አገልግሎት አስታኮ እንዲያ ልባችንን ከነካው አገልግሎቱ፣ ልፋቱና፣ ለወገን ያለው ፍቅርና መቆርቆር በተቃራኒ በሆነ መልኩ አንዳንች ፍቅርና ትሕትና በጎደለው መንፈስ ይሄንንም ያንንም ሲያዋርድ፣ ሲዘልፍና ሲሳደብ ባይ መምህርን ምን ነካው በማለት ይህችን አጭር ጦማር አደርሰው ዘንድ ብዕሬን ለማንሣት ወደድኹ፡፡
አስቀድሜ መምህር ለቤተ ክርስቲያንህ ያለህን ቅናት በግል አደንቃለኹ፡፡ የአባቶቻችን፣ የቅዱሳን አምላክ አገልግሎትህን የቀና እንዲያደርግልህም ጸሎቴ ነው፡፡ ግና በደቡብ አፍሪካ ስላለህ አገልግሎትህ በፌስ ቡክ ገጽህ ባስነበብኸን ጽሑፍ ቅሬታ አድሮብኛል፡፡ እስቲ በጽሑፍህ ቅር ካሰኘኝ መካከል አንዳንዶቹን ላንሣ፡፡ ‹‹… እንዲታወቅልኝ የምፈልገው ነገር ቢኖር አውሮጳም አፍሪካም ለአገልግሎት ስለዞርኩኝ ዩሮና ዶላር አበል ተቀብሎ ነው እንዲህ ደፋር የሚኾነው ብላችሁ የምታስቡ ካላችሁ እርማችሁን አውጡ፡፡ እኔ ዘመድኩን የጋሽ በቀለ ልጅ ሰባራ ሳንቲም ከቤ/ን አበል አልቀበልም፡፡››

Friday, July 3, 2015

ይቺ ናት ተአምረ ሥዕለ ማርያም¡ከላእከ ወንጌል ሃይማኖት ታደሰ
«አስደናቂ ዜና»
“አርብ መርካቶ ሸራ ተራ 8 ሰአት የተነሳው ከፍተኛ ውድመት ያደረሰው የእሳት አደጋ ረዘም ያለ ግዜ ውስዶ ቢያንስ ከፍተኛ ንብረት ማውደሙንና እስከ ለሌቱ, 5 ሰአት ድረስ አለመብረዱን በአቅራቢያ የነበሩ ሰዋች ጠቁመዋል በዚህ አጋጣሚ በጣም ብዙ ንብረት መትረፍ አለመቻሉና ውድመቱ ከፍተኛ መሆኑን ተመልክተናል ከዚህ ውድመት ጋር በተያያዘ ትላንትና ቦታውን ፍርስራሽ ለማንሳት በመፈተሽ ላይ የነበሩ ባለንብረቶች ይቺን የእመቤታችን የወላዲተ አምላክ የድንግል ማሪያም ስዕል አድኖ እሳት ሳያቃጥለው በሚገርም ታዕምር [ተአምር] ተገኝታለች የድንግል በረከት አይለየን ልመናዋ ምልጃዋ ከሁላችንም ይሁን ከዘላለም እሳት ትሰውረን፡፡
አሜን ቅድስት ሆይ ለምኝልን
ይሄን ታምር ሼር በማድረግ ለወዳጅዎ ያካፍሉ! 

እንዲህ ሲል ያስነበበው yehabesha.com ነው፡፡ ወሬው የሰነበተ “ቋንጣ” ቢሆንም ቋንጣም ይበላልና እንደሚሆን አድርጌ በጉዳዩ ላይ ሐሳቤን ለማካፈል ወደድኩ፡፡ ይህን “አስደናቂ ዜና” ብሎ ድረ ገጹ ያቀረበውንና በምን መስፈርት እንደሆነ ሳይታወቅ “ተአምር” ያለውን ክስተት በዝምታ ማለፍ ተገቢ መስሎ አልተሰማኝም፡፡ ወሬው ወር የሆነው በመሆኑ “የጠነዛ” ነው ሊባል ቢችልም በጉዳዩ ላይ የሚነሣው የክርክር ሐሳብ እንደ አዲስ እንድወያይበት ሊያደርግ ይችላልና በሚል እምነት አንዳንድ ሐሣቦችን መሰንዘር ያስፈልጋል፡፡