Sunday, July 19, 2015

ውግዘትና - የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት -ክፍል አንድ በዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
ዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ ከዚህ በፊት ሰፋ ያለ ተከታታይ ትምህርት እንደላከልን ይታወቃል። አሁንም አዲስ ተከታታይ ትምህርት ልኮልናል። ይህ ትምህርት በዘፈቀደ ማንም እየተነሳ የሚያካሂደውን ውግዘት የተመለከተ ነው። በትምህርቱ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው በውግዘት ውስጥ ቤተክርስቲያን ሊኖራት የሚገባው ኃላፊነት ነው። ይህ ጽሁፍ  በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት ብዙዎችን ያስተምራል ብለን እናምናለን፡፡ መልካም ንባብ ይሁንላችሁ።

መግቢያ
“ሳትሞት ሞተች ብለው ምንም ቢቀብሯት
አትሞትም፤አትሞትም፤አትሞትም እውነት፤
እውነት የእግዜር ገንዘብ እንደእግዜር ባህርይ
ዘላለም ሕያው ናት በምድር በሰማይ፡፡”
(ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(አለቃ)፡፡ ሃይማኖተ አበው ቀደምት
ወፍልጠተ ውሉድ ደኃርት(ያልታተመ)፡፡
    እውነት አትሞትም ማለት አትቀበርም ማለት አይደለም፡፡ ህያው ነገር ይቀበራል፡፡ የሚያሳዝኑት የማይሞተውንና ፤ማዳን የሚቻለውን ህያው ነገር የሚቀብሩ ወይም ለመቅበር የሚሞክሩ ናቸው፡፡ እውነት ባህርይዋ የእግዚአብሔር ነው፡፡ ልትቀበር እንጂ በፍጹም፤በፍጹም ልንገድላት፤ ልትሞትም አትችልም፡፡ አይሁድ እውነቱንና እውነተኛውን ጌታ (ዮሐ.14፥6፤17፥17፤18፥37) “በመግደላቸው” የተደሰቱ ይመስላል፤ እንዳይነሳ ማድረግ ግን አይችሉም፡፡
    እግዚአብሔርን መካድ ይቻላል፡፡ እርሱን ብንክደው “ባናምነው፥ እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን ሊክድ አይችልምና።” (2ጢሞ.2፥13) ፤ “የእኛ አለማመንም የእግዚአብሔርን ታማኝነት ማስቀረት አይችልም፡፡” (ሮሜ.3፥3)፡፡ ስለዚህ እኛ ስለእርሱ ልንመሰክር ተጠርተናል፡፡ ዳሩ ባንመሰክረው ፤ ለትውልድም ባንናገረው በአዕምሮዐችን ተቀብሮ ይኖራል፡፡ ነገር ግን እርሱ ብንቀብረውም  እርሱ ራሱን ጠብቆ ይኖራል፡፡ በቆሻሻ ላይ ወጥታ እንደማታድፍ ፀሐይ እርሱ በንጹሐ ባህርይ ገንዘቡ ፥ ቢቀበርም ሙስና መቃብር የማያገኘው ህያው ነው፡፡
   ለዘመናት መናፍቃንና ኃጥአን እግዚአብሔርንና የእውነትነት ባህርይውን ሲክዱና ሲቃወሙ ኖረዋል፡፡ ብዙ ጊዜም ሊቀብሩ፤ ሊያጠፉ፤ ቀብረው ሊያስቀሩም ጥረዋል፡፡ ነገር ግን ራሱን የማይክድ ጌታ ህያው ሆኖ ሲኖር አይተናል፡፡ እርሱ ራሱን አይክድምና፡፡ ለእውነት የጠራን የታመነ፤ ያለውንም የሚያደርግ፤ ከክፉም የሚጠብቀን  ነውና ፍቱም ልንታመንበት ይገባናል፡፡(1ተሰ.5፥24፤2ተሰ.3፥2)
ውግዘት
    ውጉዝ” የሚለውን ቃል በቁሙ የተወገዘ ፣ የተለየ ፣ ርጉም ፤ ህርም የተባለ ፣ የተከለከለ ፣ ህግ የነቀፈው ያፀየፈው ሥራ ማናቸውም ሁሉ” በማለት ይተረጉመዋል፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡ (1948 ዓ.ም) ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡ገጽ.377)
   በሌላ ትርጉም “ግዝት ፥ ውግዘት ፤ ከምዕመናን አንድነት መለየት፡፡” በማለት ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይፈታዋል፡፡ (የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር (2002)፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9ኛ እትም ፣ አዲስ አበባ፡፡ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡ገጽ.248)
    “ግዝት ማለት አንድ ምእመን ከሃይማኖት ወጥቶ ከበጐ ምግባር አድጦ ሲገኝ ከሕዝበ ክርስቲያን እንዲለይ በሥልጣነ ክህነት የሚፈጸም መንፈሳዊ ቅጣት ነው፡፡” ይላሉ፡፡ (ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ (ሊቀ መዘምራን) መርሐ - ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት (1989 ዓ.ም)፤ አዲስ አበባ፡፡ አሳታሚ ገ/ሥላሴ ብርሃኑ፡፡ ገጽ 148) 
    ከዚህ በመነሳት የውግዘትን ጽንሰ ሐሳቦችን ብንመለከት እንዲህ ማለት ይቻለናል፡፡
1.    መለየት (ከአንድነት ማግለል) ፡-  በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን አስነዋሪ የዝሙት ኃጢአት በተሰራ ጊዜ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ አለ … “ … ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ። … ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ … ”(1ቆሮ.5፥2-4)
    ጌታ ስለይቅርታ ባስተማረበት አንቀጹም አንድ ሰው በበደለና ባጠፋ ጊዜ፤ በተደጋጋሚ ሳትታክት ቤተ ክርስቲያን ከመከረች በኋላ አልመለስ ቢል ልታደርግ የተሰጣት ሥልጣን አንዱ እንዲህ የሚል ነው፡፡
  “ … በሁለት ወይም በሦስት ምስክር አፍ ነገር ሁሉ እንዲጸና፥ ዳግመኛ አንድ ወይም ሁለት ከአንተ ጋር ውሰድ፤እነርሱንም ባይሰማ፥ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተ ክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።” (ማቴ.18፥16-17)

     ቤተ ክርስቲያን ከተሰጣት ሥልጣን አንዱ አሳፋሪ ተግባር የፈፀመውን ማናቸውንም ሰው ከምዕመናን አንድነት፤ ከቤተ ክርስቲያን አካልነት ማስወገድ ነው፡፡
   ተወጋዡን ለሰይጣን አሳልፈን የምንሰጠው ወይም እንደአረመኔና እንደቀራጭ መቁጠርንና  ከህብረቷ መለየትን፤ የበዳዩንም ሥጋ እንዲያጎሳቁል ለሰይጣን ፈቃድ አሳልፎ መስጠትን ያሳያል፡፡ መለየቱ ቁርጥ ቤተ ክርስቲያን ከእውነት ጋር ያላትን ጭከናንም ያመለክታል፡፡   
     በቤተ ክርስቲያን ታሪክም አብነት ሊሆኑ መንፈሳዊና ህጋዊ ውግዘቶችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
2.    መረገም ፦ ውግዘት በሌላ ትርጉም መረገምን ያመለክታል፡፡ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይለ ቃላትን ብናነሳ፦
     
ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወድ ቢኖር የተረገመ ይሁን። ” (1ቆሮ.16፥22)

 ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።አስቀድመን እንዳልን  እንዲሁ አሁን ሁለተኛ እላለሁ፥ ከተቀበላችሁት የተለየውን ማንም ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን።”(ገላ.1፥8)
   ጌታ ኢየሱስን አለመውደድ አለማመንን ያመለክታል፡፡ ስለዚህም “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።”(ዮሐ.3፥36) የሚለው ቃል ተፈጽሞበታልና ርጉም ነው፡፡ ይህ መርገም በእግዚአብሔር ምስክርነት ላይ የተመሰረተ ነውና ጌታን በማይወዱና በማይታዘዙ ሁሉ ላይ ተፈጻሚ ነው፡፡ ሐዋርያው ለእግዚአብሔር እጅግ የታመነ ነውና በእርግማኑ ራሱንና ሐዋርያትን “እኛ” ብሎ ጨምሮ በማካተት ጨክኖ ይናገራል፡፡ የሰማይ መላዕክትም፣ ሐዋርያትም፣ ሌሎች ማናቸውም ቢሆኑ የተሰበከላቸውን ወንጌል ለውጠውና አሻሽለው ለመስበክ ምንም መብትና ሥልጣን የላቸውም፡፡
    ከዳግም ምጽአት አስፈሪ ቃላት መካከል “በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ።” የሚለው ነው፡፡(ማቴ.25፥41)  ይህ ከእኔ ሂዱ የሚለው እርግማን ግን  የዚያን ጊዜ የሚሰማና የሚቀርብ እርግማን አይደለም፡፡ ጌታ ኢየሱስን የማይወዱና በእርሱም ያላመኑ፤ እንዲሁም ለእርሱ ባለመታዘዝ የሚኖሩትን ጌታ የማያውቃቸውና አላውቃችሁም የሚላቸው ያኔ በዳግም ምጽአት አይደለም፤ ቃሉ እንዲህ ይላልና፦
             “ የዚያን ጊዜም፦ ከቶ አላወቅኋችሁም ፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ
               እመሰክርባቸዋለሁ።” (ማቴ.7፥23)
     እርግማኑ ከቀድሞ መሆኑን ቃሉ ከቶ አላውቃችሁም ሳይሆን አላወቅኋችሁም በማለት ያጸናዋል፡፡ በእርግጥ ይህ ቃል ዛሬ ደብዝዘው ብለው ከሚነገሩት ቃላት መካከል አንዱ ቢሆንም፡፡ አዎ! ኢየሱስ ክርስቶስን የማይወዱ ሁሉ ይህ አስፈሪ ድምጽ ይጠብቃቸዋል፡፡ ከሁሉ ይልቅ ደግሞ መርገማችን የተወገደበትን፣ ነጻነታችን የታወጀበትን፣ ልጅነታችን የጸደቀበትን፣ በጸጋ የዳንበትን፣ ወደእግዚአብሔር የቀረብንበትን፣ የኃጢአት ማሥተስርያ ሆኖ ዛሬም የቆመልንን “የኪዳኑን ደም እንደርኩስ ነገር የምንቆጥር፤ የጸጋውንም መንፈስ የምናክፋፋ የእግዚአብሔርን ልጅ ካለመውደድም በላይ ረግጠነዋልና፡፡” የሚብስ እርግማንና ቅጣት ያገኛናልና፡፡(ዕብ.10፥28-31)
     መዳንና የኃጢአት ሥርየት በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ደም ማመን ብቻ ሆኖ ሳለ፤ (ሉቃ.24፥47፤ዮሐ.1፥7፤ሐዋ.4፥12) መዳንና የኃጢአት ሥርየት በራስ ሥራና በሌላ መንገድ ለማግኘት ማሰብና መጓዝ የእግዚአብሔርን ልጅ መርገጥ፤ የኪዳኑንም ደም ማክፋፋት ነውና ይህን የሚያደርጉ ሁሉ ከኪዳኑ የተለዩ በእርግማንም የተያዙ ናቸው፡፡ እግዚአብሔር ከሁሉ ይልቅ ልጁንና ሞቱን የሚያክፋፉትን በእርግማን ብቻ ሳይሆን በዘላለም ሞትና በገሃነመ እሳት፤ በዲንም ይቀጣቸዋል፡፡  
   በሌላ በኩል ቅዱሰ ጳውሎስ “ልዩውን ወንጌል በመያዝ የሚያናውጡትንና ሊያጣምሙ የሚወዱትን አንዳንዶች አሉ እንጂ፡፡” ብሎ በአጽንዖት ይህን ተናገረ፦
“እርሱ ግን ሌላ ወንጌል አይደለም፤ የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን።”(ገላ.1፥7-8)

ቃሉን ለተነገረለት ዓላማ ሳይሆን ለራስ ሃሳብ በመጠምዘዝ መተርጎምና የክርስቶስን ወንጌል ማጣመም ከተወገዙ ርጉማን ያስመድባል፡፡ ለሁለት ሺህ አመታት የክርስቶስን ወንጌል ብዙዎች ሲያጣምሙ ታይተዋል፡፡ ነገር ግን ቀድመው በእርግማን ተለይተዋልና በቃሉ ላይ አንዳች መጨመርም ሆነ መቀነስ፤ ማጥፋትም አልተቻላቸውም፡፡
     እንዲህ ያሉትን ቤተ ክርስቲያን ያለመማንታት ከቃሉ ጋር ተባብራ ልታወግዛቸው፤ ልትጎምዳቸው፤ ልትቆርጣቸው ይገባል፡፡ እርግማን ከመባረክና ከጸጋው መጉደል ከህይወት ግንድ፤ ከቅርንጫፉም መወገድ ነውና፡፡
3.   ህግ የነቀፈው፤ ያጸየፈው ማናቸውም ሥራ

    ህግ በአድርግ ያዘዘው መልካም፤ በአታድርግ የነቀፈውና የተጸየፈው ደግሞ የተወገዘ ነው፡፡ ህግ የነቀፈውን ማክበር፤ የተጸየፈውን ደግሞ መውደድ ኃጢአት ነው፡፡ የእኛ ለህግ አለመታዘዝ ህግ የኃጢአት ምንጭ እንዲሆን አደረገው እንጂ፤ ህጉ ፍጹም ኃጢአተኝነትን በማሳወቅ ወደጌታ የሚመራ ሞግዚት ነበር፡፡(ሉቃ.24፥44፤ሮሜ.3፥20፤24፤5፥20)
   በብሉይ ኪዳን ህጉ የነቀፈውን ወይም የተጠየፈውን ማናቸውንም ሥራ ማድረግ ማስወገዝ ብቻ ሳይሆን ቅጣቱም ከባድ ነው፡፡(ዘዳ.17፥2) ከማውገዙና ከመለየቱ፤ ህጉ የነቀፈውንና የተጠየፈውን ነገር ፈጽመዋልና ብሎ ለቅጣቱ ከመቸኰል ተቆጥቦ ነገሩን መመርመር፤ ምስክር ማድመጥ እጅጉን ማስተዋል ይገባል፡፡(ዕብ.10፥28)
  በአዲስ ኪዳን ብቃት ያለው አዳኝ ሆኖ ክርስቶስ መጥቶልናልና በህግ ብንነቀፍ፤ አጸያፊና ቤተ ክርስቲያን የሚያረክስ ነገር ብንሰራና ብንገኝ ያለርህራሄ ከአንድነቱ  ልንለይ ግድ ነው፡፡ ይህ ህግ በዘፈቀደ ሳይሆን በብርቱ ጥንቃቄ ሊሆን ይገባዋል፡፡
የውግዘት አላማው ምንድር ነው?
1-   እምነትን ስለመጠበቅ
     ይህ በሥነ መለኮት ትምህርት “ዓቃቤ እምነት(Apologistics)” በመባል የሚታወቅ ሲሆን ይህን ሥራ የሚሠሩ አገልጋዮች ደግሞ የቤተ ክርስቲያን “ጠበቆች” በመባል በብዛት ይታወቃሉ፡፡ የቃሉ ትርጉም በቁሙ ሲፈታ “አቀበ የሚለው ጠበቀ፣ ከለከለ፣ አስጠነቀቀ፣ ከለለ” ሲሆን ከእምነት ጋር ሲተረጎም ደግሞ “እምነትን መጠበቅ፣ መከላከል፣ መጋረድ”  የሚለውን ፍቺ ይሰጠናል፡፡
    እርግጥ ነው እምነታችንን ሁል ጊዜ በውግዘት እንጠብቃለን ማለት አይቻልም፡፡ የመጠበቂያውና የመከለያው አንዱ አካል እንጂ፡፡ ምክንያቱም መናፍቃን ልዩ ወንጌል፣ ልዩ መንፈስ፣ ልዩ ኢየሱስ፣ ልዩ ትምህርትና ልዩ ልዩ የመዳን መንገዶች ያላቸው ስለሆነ ትምህርቶቻቸውንና ሃሳቦቻቸውን በትኩረት በማጤን ልናየው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ልንፈትሽና ልንመዝነው እንደቃሉም ሆኖ ሳይገን ሲቀር ልንለየው፤ ልንጎምደው፣ ልንቆርጠው ግድ ያስፈልገናል፡፡
    ስለዚህ ከማውገዝ በፊት ኑፋቄ ምንጩ ብዙ ነውና በዚህ ሥራ ላይ የተሰማራ አገልጋይ ከብርቱ ትጋት ጋር ዕወቀቱ መድብላዊ፣ ሰፊና ጥልቅ፣ ሁሉን አቀፍም ትምህርት ሊኖረው ሥራቸውና ትምህርታቸው የሐሰት መሆኑን ገልጦ ሊናገር ይገባዋል፡፡ ይህንን በተመለከተ የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን በጣም ከባድ ችግር ውስጥ ያለች ይመስላል፡፡ “መናፍቃንን” በጥላቻና በንቀት፤ በስድብባ በማቅለል ከመጮህ በዘለለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ላይ በመቆም የጥንት እውነተኛ አባቶችን አስተምህሮ በመከተል መናፍቃንን የመቃወምና የማሳፈር ብሎም እምነትን የመጠበቅ ሥራ የተሰራባቸውን ጨዋ መጻህፍትና ሥራዎችን ማግኘት በባህር ውስጥ የወደቀችን የዕንቁ ቅንጣት የመፈለግ ያህል ይከብዳል፡፡
    ከጥንታዊ ጸሐፍት ቅዱሳን አባቶች በቀር ዛሬ ላይ ያሉቱ “ሊቃውንትና አበው” የወረራ ያህል የተንሰራፉና ሥውር በሆነ አሰራር ክርስትናንና መጽሐፍ ቅዱስን ፣ ክርስቶስ ኢየሱስንና ሥላሴን፣ ዳግም መምጣቱንና ዘላለማዊ ህይወትን … ስለሚክዱ፣ ስለሚንዱ፣ ስለሚጎምዱ … መናፍቃን ዝምታን መርጠው መቀመጣቸው ልብ ይሰብራል፡፡ ጽፈናል የሚሉቱ ደግሞ ከእጅግ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ በቀር ሐቲት አልባ ጽሁፎችን ስናይ ደግሞ “የእሳት ልጅ አመድ ወለደ እንዴ?”ያሰኛል፡፡
    እምነትን የሚጠብቅ አካል ወይም አገልጋይ ‹‹ ማንም ልዩ ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ሆኖ ቢያገኘው”(1ጢሞ.6፥3-5) ይህ ሰው  “ለእግዚአብሔር መጋቢነት አይጠቅምምና” (1ጢሞ-1፤4) ከእንደነዚህ አይነት ሰዎች ልንርቅ (1ጢሞ.6፥20) ይገባናል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች “የክርስቶስ ተቋዋሚ” (1ዮሐ.2፥18) ፣ ሐሰተኞች (1ዮሐ.2፥22)፣ ዲያብሎስ ልጆች (1ዮሐ.3፥10)፣ አሳች (1ዮሐ.2፥26) ስለሆኑና “ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር መራቅ” ስላለብን ነው፡፡(1ተሰ.5፥22)
     መራቁ እንዳለ ሆኖ ግን ቤተ ክርስቲያን የእነዚህን አካላት የትምህርት ምንጭ በማጥናትና መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ ትምህርት አዘጋጅታ በመመለስ እነርሱም እንዲመለሱ ሰፋ ያለ፤ የማያስነቅፍ ዕድልና የንስሐ ጊዜ ሰጥታ፥ ባይመለሱ ልታወግዝ ከምዕመናን አንድነት ልትለይ ይገባል፡፡
2.   ቤተ ክርስቲያን  “ቅድስት” እንድትሆን

    ቅድስና የብሉይ ኪዳንም የሐዲስ ኪዳንም ዋና የእግዚአብሔር ሐሳብና የጠራቸው ህዝቡ ሁሉ  ለእርሱ ፍፁም የተለዩ ይሆኑ ዘንድ በመውደድ ፦
“እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ሰውነታችሁን ቀድሱ፥ ቅዱሳንም ሁኑ፥ እኔ ቅዱስ ነኝና …” (ዘሌ.11፣44)         
    
“እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ በላቸው፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ።”(ዘሌ. 19፥1 -3)
  “እንደሚታዘዙ ልጆች ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት አትከተሉ።ዳሩ ግን። እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ ተብሎ ስለ ተጻፈ የጠራችሁ ቅዱስ እንደ ሆነ እናንተ ደግሞ በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።(1ጴጥ.1፥14-17)
በማለት ተመሳሳይ መንፈሳዊ ጥሪ አስተላልፎልናል፡፡ በብሉይ ለእስራኤል ዘሥጋ በሐዲስ ደግሞ ለእግዚአብሔር እስራኤል የቀረበው ጥሪ ይህ ድንቅና ውብ ጥሪ ነው፡፡
  ቅድስና በቤተ ክርስቲያን ህይወት ሁሉ መታየት አለበት፡፡ የእግዚአብሔር ህዝብ ከእግዚአብሔር ማንነትና ካደረገለት በጎነት የተነሳ ራሱን ሙሉ ለሙሉ በሁሉ ነገር አሳልፎ ለሰጠው ለእግዚአብሔር መስጠት አለበት፡፡ እኒያን ህዝቦች ከግብጽ ምድር፤ከባርነት ቤት፣ በጸናች እጅ፤ በተዘረጋች ክንድ፣በድንቅ ባርኮት፤ በውብ መግቦት ወደተስፋይቱ ምድር መርቶ አውርሷቸዋል፡፡ እኛን ደግሞ እንዲሁ በሆነ ፍቅር በልጁ ሞት ከኃጢአት ቤት፤ከአጋንንት እስራት ነጻ አውትቶ ዘላለማዊት የሆነች መንግስቱንና ህይወቱን አውርሶናል፡፡
     ሞታችንን ሞቶ ከኃጢአት ነጻ ያወጣን ጌታ ከእኛ የሚፈልገው በጽድቅ የተመላለሰበትን የቅድስና ህይወት እኛም እንመላለስ፤ በኑሮዐችንም ቅዱስ እንሆን ዘንድ ይፈልጋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንደሙሽራዋ ነጽታ ሙሽሪት ሆና በመገኘት የህይወት ምስክርነት እንድትሰጥ ፍቅሩ ይለምናታልና ዘንበል ብላ በሙሉ ፈቃድዋ ልትታዘዝለት ይገባል፡፡
    ቤተ ክርስቲያንን በዕድፈት ከምትያዝበት ነገር አንዱ መናፍቅነት ነው፡፡ መናፍቅነት የሥጋ ፍሬ ነው፡፡(ገላ.5፥21) የሥጋ ፍሬ ደግሞ ኃጢአተኝነትን ያስፋፋል፤ ይህም ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር ያላትን ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ ያለቅድስና በማድረግ ከጌታዋ ያቆራርጣታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ትልቁን ጌታዋን ላለማጣትና ከአምላኳና ሙሽራዋ ጋር ያላትን ፍጹም  ዝምድና ኃጢአተኝነትንና መናፍቅነትን በማውገዝ ወይም በመለየት ቅድስናዋን ልትጠብቅ ይገባታል፡፡ የተጠራነው ለዚህ ነውና፦
    “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤ ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ … ”(ቲቶ.2፥11) ፍጹም ለክርስቶስ ኢየሱስ ፍቅር በመገዛት ልንኖር ነውና፡፡
    ኃጢአተኛነትና መናፍቅነት በግልጥ ተገልጠው ቤተ ክርስቲያንን በርኩሰት እስኪወርሱ መጠበቅ አይገባም፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ በቃሉ መሠረትነት ላይ ቆማ  ኃጠአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ልትክድ፤ ልታወግዝ ይገባታል፡፡ አልያ “ተጠምደው ያልተያዙ ጥቃቅኖቹ ቀበሮዎች ወይም በጊዜ ያልታረሙ የኃጢአት አረሞች ያበበውን ወይንና የወይኑን ቦታ ላያጠፋ”(መኃ.2፥15) ምንም ዋስትና የለምና ቤተ ክርስቲያን ሳትታክት በበጉ ደም ቅድስናዋን ልትጠብቅ ይገባታል፡፡
3.  ክፋቱ ወደሌሎች እንዳይተላለፍ
    በአዲስ ኪዳን ኃጢአት ወይም ክፋት ከተገለጠለት ምሳሌ አንዱ እርሾ ነው፡፡(ማር.8፥15) የፈሪሳውያን ትንሿ ትምህርታቸው ሥር ሰድዳ በብዙዎች ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ስህተትና ክህደት የሆነን ነገር እንደእምነት፤ ርኩሰትና ክፋቱን ደግሞ እንደቅድስና  ይገልጣልና ጌታ መራቅና መጠንቀቅ እንደሚገባ አበክሮ ተናገረ፡፡(ማቴ.16፥6)
   ቤተ ክርስቲያን የኃጢአትን እርሾ ማስወገድ አለበት፡፡ “ ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም።”(1ቆሮ.5፥8) ምክንያቱም ጥቂቱ እርሾ ብዙውን ሊጥ እንዲያቦካ እጅግ በጣም ጥቂቱ ኃጢአት ወደሌሎች ንጹህ ወደሆነው ሊጥ በመተላለፍ ያረክሳልና አዲሱ አማኝ የተቀደሰውን ኑሮ በመኖር የእርሾ ጠባይን ማስወገድ እንዲገባ ቃሉ ያስረዳል፡፡
    በእርግጥም ኃጢአትን የሚያስተውላት ስለሌለ፤ ወግታ የጣለቻቸው ብዙ፤ የገደለቻቸውም እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ በፊቷም ማንም ይቆም ዘንድ አይችልም፡፡(ምሳ.7፥27፤27፥4) ቤተ ክርስቲያን ኃጢአተኝነትንና መናፍቅነትን በመቃወም የምታወግዘው መዘዙና ጥፋቱ ብዙዎችን በማዳረስ፤ እንደወረርሽኝ ሁሉን ወርሶ እንዳይገዛ ነው፡፡ ከጥንት ሲጀመርም “ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ … ”(ሮሜ.5፥21) እንዲል የአንድ አማኝ ኃጢአት ቀላል ነው ተብሎ እንደዋዛ ሊታለፍ የሚገባው ነገር አይደለም፡፡
    በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያን ራሷን መጠበቅ ያለባት ከመናፍቃንና ከከሃድያን ብቻ ሳይሆን ከገዛ ራሷም ድርጊት ነው፡፡ አማኝ ወይም አገልጋይ የሚሠራው ስህተትና ጥፋ በቃሉ መሠረት ፈጥኖ መፍትሄ ካልተበጀለት ሥር የሰደደና የማይነቀል ነውርን የሚተክልበት ጊዜ ጥቂት አይደለም፡፡ “ተረቱም፦ “አንድ ሞኝ የተከለውን አሥር ብልህ አይነቅለው” እንዲል፡፡ ለዚህ ምሳሌ ይጠቀስ ቢባል እንደቀኖናዊ ሥርዓት ታከው ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ብዙ የሚያስጨንቁና ትውልዱን ከወንጌል የለዩ ብዙ ነገሮች ቤተ ክርስቲያን በቃሏም በመጽሐፏም ያልያዘቻቸው ግን እንደዋዛ በአንድ ወቅት የተደረጉ “ግለሰባዊ ሥርዓቶች” ነበሩ፡፡ እኒህን ግን በግልጥ እንደመናፍቅነት ሊወገዙ ይገባቸው ነበር፡፡
4.  ተወጋዡ ከክፋቱ እንዲመለስ
    የውግዘት ዋና አላማው ተወጋዡ ከክፋቱ ራሱን በማየት በንስሐ ተፀፅቶ እንዲመለስ ማድረግ ነው፡፡ ውግዘት ለተወጋዡ ከባድ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው፡፡ ኃጢአቱ ስለታየ፤ ነውሩ ስለተገለጠ፣ የእርሱም ክፋት ሌላውን ጠላልፎ እንዳይጥል ለማድረግ … የተላለፈበት ይህ ሰው በቶሎ እንዲመለስ የተሰጠው የፊተኛው ትንሳኤ ዕድል ነው፡፡
   ውግዘት ለንስሐ ዕድል መስጫ እንጂ ማክተሚያ፤ ማብቂያና የመጨረሻ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የእርሷ አካል የነበረውን ሰው ኃጢአተኛ ወይም መናፍቅ ብላ ስታወግዘው መመለሻውን መንገድም አደላድላ ልታሳየው፤ልትነግረውም ይገባል፡፡ ይህን ባታደርግ ግን ቤተ ክርስቲያን የዚያ ሰው ደም በእጇ አለ፡፡ቃሉ እንዲህ እንዲል፦
“እኔ ኃጢአተኛውን፦ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ አንተም ባታስጠነቅቀው  ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢአተኛው አስጠንቅቀህ  ባትነግረው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአት ይሞታል ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።” (ህዝ.3፥18-19)
  አማኙ ሰው ቤተ ክርስቲያን ስታገለው ለሰይጣን ፍላጻ ተጋላጭ ይሆናል፡፡ ከክርስቶስ አካል ከቤተ ክርስቲያን ጋር አልተባበረምና የቤተ ክርስቲያን እንክብካቤ ይርቀዋል፡፡ የሰይጣን ኃይል አጊኝቶ ሊሰብረው ይችላል፡፡ በዚህም ከወዴት እንደወደቀ አስቦ ይነሳ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ውግዘት ሲደረግ እንዲመለስ ታስቦ ሊሰራ ይገባዋል፡፡
------ይቀጥላል

3 comments:

  1. ዛሬ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውግዘት በሽ ነው የጠሉትን ማስወገጃ መሳሪያም ነው

    ReplyDelete
  2. አንተ ሰው የምትጽፈ ጽሁፍ መልካም ነው

    ReplyDelete