Saturday, July 25, 2015

ውግዘትና - የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት -ክፍል ሁለትበዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
ስለውግዘት ያለን የተሳሳተ ትርጉም
1.    ማውገዝ “መናፍቅ”ን ብቻ ነውን?

     ብዙ ጊዜ የውግዘት ነገር ሲነሳ ከሁሉም ሰው ህሊና የሚደቀኑት መናፍቃን ናቸው ብንል የተጋነነ አይደለም፡፡ እውነት ነው፤ መናፍቃንን በምንም አይነት መልኩ መታገስ አይገባም፡፡
      የአህዛብ ሐዋርያ ሊሆን የተጠራውና በብዙ ምስክርነት የክርስቶስ ኢየሱስን መንግስት ያገለገለው ቅዱስ ጳውሎስና አቡቀለምሲሱ ቅዱስ ዮሐንስ መናፍቅነት ብቻ ሳይሆን “ሌሎችም” ኃጢአቶች ከእግዚአብሔር መንግስት ውጪ እንደሚያደርጉ ሳያወላዱ ፤ ያለአንዳች ማወላወል በግልጥ ተናግረዋል፡፡ መናፍቅነት ብቻ ያስወግዛል ማለት የኃጢአትን ባህርይ በትክክል አለመረዳትና፤ አርካሽነቱንም አለማስተዋል ነው፡፡
ኃጢአት ምንድር ነው?
       “ኃጢአት” በቁሙ ሲፈታ በደል፣ ዐመጥ፣ ግፍ፣ ህገ ወጥ ሥራ፣ በኀልዮና በነቢብ፣ በገቢር የሚሠራ” በማለት ከገለጡ በኋላ በሌላ የትርጉም አንቀጽ “ኀጥአት” ማለት ደግሞ ማጣት መታጣት፣ ዕጦት፣ ችግር፣ ሽሽት፣ ኩብለላ በማለት ይተረጉሙታል፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ (አለቃ)መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡(1948 ዓ.ም)፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡ ገጽ.474) የኋለኛውን ትርጉም በመያዝ ይመስላል፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን “ኃጢአት” የሚለውን ትርጉም ጸጋ እግዚአብሔርን፣ ረደረኤተ እግዚአብሔርን ማጣት፤ ንጽሐ ኅሊናን ማጣት፤ አብርሆተ መንፈስ ቅዱስን ማጣት … ብለው የሚተረጉሙት፡፡ ምናልባትም ኃጢአትን የሚሠራ ሰብአዊ ማንነት ከሚገጥመው ወይም ከሚያገኘው ነገር በመነሳት የሚሰጡት ትርጉም ነው፡፡
   በእርግጥም ኃጢአት በተግባር በተከናወነ ጊዜ ሰዎች ሁሉ የገጠማቸውን ከታላቁ መጽሐፍ ስናስተውል የምናየው እውነት ትርጉሙን ይበልጥ የሚያጎላ ነው፡፡
v መሸሽና የጌታን ድምጽ መፍራት በአዳም (ዘፍ.3፥11)
v መቅበዝበዝና ኰብላይነት በቃየልና በቃየል (ዘፍ.4፥14)
v ስብራት በዖዛ(2ሳሙ.6፥7)
v ሰብዓዊ ክብርን ማጣት በናቡከደነጾር(ዳን.4፥25)
v የንጉሥ ብልጣሶር መሞት (ዳን.5፥30)
v በትል ተበልቶ መሞት በሄሮድስ(ሐዋ.12፥23)
v ይህንን ዓለምና በውስጡ ያለውን መውደድ በዴማስ(2ጢሞ.4፥10)
v እና ሌሎችንም በመያዝ የተረጎሙት፡፡
      ኃጢአት” ማለት ስህተት፣ ክፋት፣ ህግን መተላለፍ፣ ዓመፃ በጎ ነገርን አውቆ አለመሥራት፣ በእምነት መሠረት አለመኖር፣ ወደ እግዚአብሔር ክብር አለመብቃት፡፡” (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፡፡ የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፡፡ ገጽ.133)
     “ኃጢአት ማለት ለእግዚአብሔር ለፈቃዱም አለመገዛትና አለመታዘዝ፥ በሃሳብም፥ በንግግርም በሥራም መግለጥ ነው፡፡” (መልከ ጼዴቅ(አባ)፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ሁለተኛ ዕትም፡፡(1996)፡፡አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡ ገጽ.129)

    ኃጢአት ራሳችንን ከእግዚአብሔር ባራቅንና(ኤፌ.4፥18) ምኞታችንን ለክፉው አሳልፈን በሰጠን ጊዜ የሚያገኘን ርኩሰት ነው፡፡ የኃጢአት መነሻ ነገሩ ክፉ ምኞት ሲሆን(ምሳ.18፥1 ፤ 1ጢሞ.6፥10 ፤ ያዕ.1፥14) ፤ ምኞታችንን ለእግዚአብሔር አሳልፈን ባልሰጠን መጠን ደግሞ የገዛ ምኞታችን ለማንወደውና ለባህርያችን ለማይስማማው ኃጠአት አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ (ያዕ.1፥15 ፤ ሮሜ.1፥20-32) ፍጻሜው ሁለተኛ ሞትና የዘላለም ገሃነም ነው፡፡(ሮሜ.6፥23 ፤ ራዕ.20፥14 ፤ 21፥8) እግዚአብሔር ለቅድስና በሚስማማ ባህርይ እንጂ ለኃጢአት ባህርይ ሊስማማ በሚችል መልኩ አልፈጠረንም፡፡ ከጥንት የእግዚአብሔር ሃሳቡ እኛ በህይወትና በቅድስና እንኖር ዘንድ ነውና፡፡  (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(አለቃ) ገጽ.25) እንሆን ዘንድም የተጠራነው እርሱን እንመስል ዘንድ ነውና(ዘሌ.19፥2 ፤ ማቴ.5፥48 ፤ ሉቃ.6፥36፤ …. )
     ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ፈቃዱ እኛ ከኃጢአት እንርቅ ዘንድ የወደደ ቢሆንም በመውደዱ ብቻ ግን የተወን  ብቻ አይደለም፡፡ ይህን የምንችልበትም ጉልበትና ብርታት ሰጥቶናል፡፡  ይህን ባናደርግ ግን እግዚአብሔር ፈጽሞ ከመንግስቱ ይሰደናል፤ ራቁም ይለናል፡፡ እርሱ የሚያሳድደን አይደለም፡፡ የገዛ ነውራችን ከእርሱ ያርቀናል እንጂ፡፡ ለዚህ ጥቂቱን ብንጠቅስ፦
             
“ … ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ ታታልሉማላችሁ፥ ያውም ወንድሞቻችሁን። ወይስ  ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ ፤ ሴሰኞች  ቢሆን ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም  ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”(1ቆሮ.6፥9-11)

“የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ ፥ ምዋርት ፥ ጥል ፥  ክርክር ፥  ቅንዓት ፥  ቁጣ ፥  አድመኛነት ፥ መለያየት ፥  መናፍቅነት ፥  ምቀኝነት ፥ መግደል፥ ስካር ፥  ዘፋኝነት ፥  ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”(ገላ.5፥19-22)
“ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን  የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም።”(ኤፌ.5፥5)
              ቅዱስ ዮሐንስም በራዕዩ፦
“ለበጉም በሆነው በሕይወት መጽሐፍ ከተጻፉት በቀር፥ ጸያፍ ነገር ሁሉ ርኵሰትና ውሸትም የሚያደርግ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።”(ራዕ.21፥27)
               “ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰ ገዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።”(ራዕ.22፥15)
     እነዚህንና ሌሎችንም ኃጢአቶች የሚያደርጉ ሁሉ ከእግዚአብሔር መንግስት በውጪ ያሉ ናቸው፡፡ ይህ ማለት በዚህች በምድር ባለችው ቤተ ክርስቲያን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለመኑና በመንፈስ ቅዱስ ፍጹም ልጅነትን በማግኘት ከአጥቢያዋ ቤተ ክርስቲያን ህብረትም ውጪ ናቸው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህችው ቤተ ክርስቲያን ናትና ቅድስት፤ ያለነውርና ፊት መጨማደድ ፍጽምት ሆና እያደገች(ኤፌ.2፥21፤5፥27፤1ጴጥ.2፥5) በላይ በሰማይም ጸንታ በጉ ብቻ በመካከል ነግሶ የሚኖርባትና ለዘላለም የሚመለክባት፡፡(ራዕ.22፥3)
       መጽሐፍ ቅዱስ “የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው” (ገላ.5፥19) ይለናል፡፡ ይህም ማለት የሥጋ ሥራ የሚባለው በኃጢአትና በርኩሰት የረከሰው ማንነት በማንም ወይም ከማንም ዘንድ የተሰወረ አይደለም፤ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው ማለት ነው፡፡ የሥጋ ሥራ ተብለው ከተጠቀሱት ከእነዚህ መካከል አንዱን አዘውትሮ የሚፈጽም ሰው በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመራ አይደለም፤ ዘሩ የሥጋ ነውና ፍሬውም የሥጋ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር የተወለዱ ለዘወትር ኃጢአትን በመፈጸም አይኖሩም፡፡ ቅድስና እንጂ ኃጢአት ከማይስማማው፤ ከማይጠፋው ዘር(1ጴጥ.1፥23) የተወለደ አማኝ ፍጹም የሆነ ህብረት ከክርስቶስ ጋር አለውና ኃጢአትን ከጸጋው ብርታት የተነሳ ላያደርግ ይቻለዋል፡፡ ቃሉም
              “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ኃጢአትን አያደርግም፥ ዘሩ በእርሱ
              ይኖራልና፤ ከእግዚአብሔርም ተወልዶአልና ኃጢአትን ሊያደርግ
              አይችልም።” (1ዮሐ.3፥9)  
       በተጨማሪም፦
                             “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ
                              እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት
                              ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ
                              የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።” (1ዮሐ.2፥16)
  ይላልና፡፡
         የእግዚአብሔር ጻድቃን “ህጉን በቀንና በሌሊት ግራም ቀኝም ሳይሉ ያስባሉ”(መዝ.1፥2፤ኢያ.1፥7)፤ ምክሩንም በመፈለግ መንገዳቸውን ንጹህ ያደርጋሉ፤ ያለአዚምም የተሰቀለውን ክርስቶሰን በልባቸው ስለው ሩጫውን በትዕግስት ይሮጣሉና … “ዓመፅንም አያደርጉም፥ በመንገዶቹም ይሄዳሉ።” (መዝ.119፥3፤ገላ.3፥1፤ዕብ.12፥2)
       እልኸኝነት እስራኤልን በምድረ በዳ በሞት ያረገፈ ኃጢአት ነው፡፡(ዕብ.3፥8፤15፤4፥7) አማኝ ኃጢአትን በመፈጸም በእልኸኝነት ልብ ጸንቶ፤ የመንፈስ ቅዱስን ሃሳብ በግልጥ በመቃወም የተገለጠለትን ህይወትና ብርሃን ገድሎና አጨልሞ፤ ወደህይወት የመመለስ ዕድሉን ዘግቶ መንፈሳዊ ሞትን በገዛ ነጻ ምርጫው መሞት ይችላል፡፡ ማንም ቢሆን “እንደ ሥጋ ሥራ የሚኖር ቢሆን ይሞታልና”፡፡(ሮሜ.8፥13) በርኩሰት መጽናት የዲያብሎስ ልጅ ያሰኛል፡፡ “ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።”(1ዮሐ.3፥8) ኃጢአት በምንም መልኩ ከእግዚአብሔር ጋር ህብረት አያደርግም፤ የለውም፡፡ የእግዚአብሔር ባህርይው ቅድስና ነውና እኛም በቅድስና እንኖር ዘንድ ይፈልጋል፡፡ (ዘሌ.19፥2፤1ጴጥ.1፥16 ) እግዚአብሔር ልጁን ወደዚህ ምድር የላከበት ዋናው ምክንያት መልኩን የሰጠው የሰው ልጅ መልኩን ስላበላሸ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ መልኩ ይመልሰው ዘንድ ነው፡፡
    ኃጢአትን የሚያደርግ የተሳለበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መልክና አርአያ(ዘፍ.1፥26) ያበላሻል፡፡ በተንኰለኛና በክፉ ልብ (ኤር.17፥9)፤ ከሥጋ ዘርና ሐሳብ የተነሳ በአለመታዘዝ ይፈጸማልና (ዮሐ.3፥6፤ ሮሜ.8፥7)፤ የሚያደርጉትም ከዲያብሎስ ፈቃድ የተነሳ ነውና (ዮሐ.8፥44) ፤ አድራጊዎቹም ፈጽመው የማይታዘዙና አመጸኞች ስለሆኑ(ይሁ. 15)፤ ልብሳቸውን በበጉ ደምም አላጠቡምና(ራዕ.7፥14)፤ ከእውነተኛው ጌታም ይልቅ ለተገዙለት ለዚያ ጌታ ባርያ ሆነዋልና (1ጴጥ.2፥19)፤ ወደበጉ ሠርግ መግባት አይቻላቸውም፡፡(ማቴ.22፥12፤ራዕ.22፥15) ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም እንዲህ ይላል፦
          “ከብዙ ኃጢአታችን ኋላ ቆመን በእልኸኝነት ከፀናን በፍርድ ቀን
           ከሚመጣው ቁጣ የሚያድን ያለ እንዳይመስላችሁ፤ አመጻችን
           የእሳቱን ነበልባል ይጨምርብናል እንጂ፡፡”

      እንኪያስ! እንዲህ ያለ ኃጢአት የሚያደርጉ ሁሉ የተገለጠ ነውራቸው ቤተ ክርስቲያን በማየት ዝም ልትል አይገባትም፡፡ በክፉ ሥራው አለመተባበሯን በህብረቷ ላለመቀበል፤ ሰላምም ባለማለት(2ዮሐ.10)፤ ያለሥርአት የሚሄዱትን በግልጥ መገሰጽ(1ተሰ.5፥14)፤ የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን እየካዱ፤ እውነትን በአመጻ እየከለከሉ ለማይረባም አዕምሮ ተላልፈው የተሰጡ ናቸውና ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን በመምሰል እንደዚህ ካሉት ልትርቅ እንደሚገባት ቃሉ በግልጥ ይናገራል፡፡(ሮሜ.1፥18፤28፤ 1ጢሞ.4፥2፤8) ምክንያቱም እንደነዚህ ያሉ ሰዎች “ … በኋላም የካዱትን እንደገና ለንስሐ እነርሱን ማደስ የማይቻል ነው፤ ለራሳቸው የእግዚአብሔርን ልጅ ይሰቅሉታልና ያዋርዱትማልና።”(ዕብ.6፥6)
     ነገር ግን ለምን እንደሆነ ግራ እስኪገባኝ ድረስ ቤተ ክርስቲያን “መናፍቃንን” በሙሉ ኃይሏ (አንዳንዴ ጥላቻንም ባንጸባረቀ መልኩ) የምታወግዛቸውንና ሲኖዶስ ሰብስባ የምትቃወመውን ያህል ለምን ሌሎች ደፋር ኃጢአተኞችንና የተገለጡ ነውረኞችን ሲኖዶስ ሰብስባ፤ ልጆቿን መክራ እንደማትመልስ ወይም እንደማትለይ አይገባኝም፡፡ ለምሳሌ፦
                 ሀ. ዝሙት ፦  በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ከተነሱት ነውሮች አንዱ ሮማውያን እንኳ የማይፈጽሙት የዝሙት ተግባር ነበር፡፡ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፦
            “ይህን ሥራ የሠራው ከመካከላችሁ ይወገድ።እኔ ምንም እንኳ በሥጋ ከእናንተ ጋር ባልሆን፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝ፥ ከእናንተም ጋር እንዳለሁ ሆኜ ይህን እንደዚህ በሠራው ላይ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አሁን ፈርጄበታለሁ፤ እናንተና መንፈሴም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ጋር ተሰብስበን፥ መንፈሱ በጌታ በኢየሱስ ቀን ትድን ዘንድ እንደዚህ ያለው ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ፍርዴ ነው።”(1ቆሮ.5፥2-6)
     እውነት ማውገዝና መለየቱ “ለማፍረስ ያይደለ ለማነጽ የተሠጠ ከሆነ ” (2ቆሮ.13፥10) እንዲህ ያለውን ኃጢአት በምንም መልኩ መታገስ አይገባም፡፡
     ግኖስቲካዊ አመለካከት የነበራቸውንና የሚናገረውን የመንግስቱን ወንጌል የተቃወሙትን ሄሜኔዎስ፣ እስክንድሮስንና ፊሊጦስን ይኸው ቅዱስ ሐዋርያ “እንዳይሳደቡ ይማሩ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፎ ሰጥቷቸዋል፤ ቅዱስ ልጁ ጢሞቴዎስንም “ከእነዚህ መናፍቃንና ኃጢአተኞች” እንዲጠበቅም መክሯል፡፡(1ጢሞ.1፥20፤2ጢሞ.2፥12፤4፥15)
    መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ወህኒ ለመውረዱና አንገቱ ለመሰየፉ ምክንያቱ የወንድምህ ሚስት “እርስዋ ለአንተ ትሆን ዘንድ አልተፈቀደም” (ማቴ.14፥4) ማለቱና መቃወሙ ነበር፡፡ ሴሰኝነትን የተቃወመው ዮሐንስ በዘፈንና በሴሰኝነት መዘዝ አንገቱ ተሰየፈ፡፡ ምንም መሸፋፈን ሳያስፈልግ ይህ ቅዱ ዮሐንስ አንገቱ የተሠየፈበት ነውርና ኃጢአት የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ተጨማልቃበታለች፡፡ ጥቂት የማይባሉ የሠበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አባላት፣ የስብከተ ወንጌል አባላትና አመራር፤ “መምህራን”፣ ዘማርያን፣ መነኮሳት  … በታወቀ የሴሰኝነትና የዝሙት ነውር ተይዘው “አንድም ዘመን” ግን ሲወገዙ ወይም ካልተመለሳችሁና ንስሐ ካልገባችሁ ብሎ ያወገዘ አባትም፤ ሲኖዶስም አላየንም፡፡
    እንዲያውም የተቃወሙና ያወገዙ ብዙ ቅዱሳንና መነኮሳት የሚያሰቅቅና ዘግናኝ መከራዎች ደርሶባቸዋል፡፡ ከሚያሳፍረውና የቤተ ክርስቲያንን ሥም ከሚያጎድፈው የታሪክ ተግባር አንዱ የቤተ ክርስቲያን “ታላላቅ መሪዎችና መምህራን” ሁለት ሚስትና ከዚያ በላይ ያላቸውን ነገስታትና መኳንንት ከመሾም ከመቀባት ባሻገር ሥርዓተ ተክሊል ይፈጽሙ እንደነበር የኖረ፤ የነበረ፤ ያየነውም የታሪክ ሐቅ ነው፡፡ ምሳሌ፦
1.     “አፄ ዓምደ ጽዮን የአባቱን ሚስት የእንጀራ እናቱን ዕቅብት አድርጎ ይዞ ስለነበር አቡነ ፊሊጶስ ረድአቸው አኖሬዎስ ዘጸጋጃን አስከትለው ወደቤተ መንግስቱ ገብተው ያባትህን ሚስት ልትይዝ አይገባህም ብለው ገሰጹት፡፡ ዮሐንስ ሔሮድስን የወንድምህን ሚስት ልትወርስ አይገባህም ብሎ እንደገሠጸው፥ ንጉሡም ተናዶ ከነረድአቸው ገረፋቸው፡፡ በዚያም ሌሊት የነዚህ ቅዱሳን ደም የፈሰሰባት ከተማ በእሳት እንደወደመች እና እጨጌ ፊሊጶስም ወደሰሜን ኢትዮጲያ መሰደዳቸውን በሰፊው ተተርኳል፡፡” (አባ ጎርጎርዮስ (ሊቀጳጳስ)፡፡ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ 2ኛ ዕትም ፣ (1986) ገጽ.47 ) ዕጨጌ ፊሊጶስና አባ አኖሬዎስ በመቃወማቸው ሌሎች የሚበዙቱ ግን ዝምታን በመምረጣቸው ወይም በመደገፋቸው የከፋን መከራ ተቀብለዋል፡፡
2.    “ … ዐፄ ፋሲለደስ በንግስና ዘመኑ የፈጸማቸው የጥፋት ተግባራትም ነበሩ፡፡ የዐፄ ፋሲለደስ የጥፋት መንገድ ከዝሙት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ፋሲለደስ እጅግ በርካታ ዕቁባቶች በጎንደር ከተማና በየቦታው ከማስቀመጡ አልፎ አብረውት ያደሩትን ሴቶች እየገደለ በቤተ መንግስቱ አጠገብ ባስቆፈረው ጥልቅ አዘቅት ውስጥ ይጥላቸው እንደነበር በሰፊው ይነገራል፡፡ … ይህ ሁሉ ሲሆን አሁንም ፋሲለደስ የችግሩ መነሻ ራሱ መሆኑን አልተገነዘበም ነበር፡፡ በአጠገቡ ከነበሩት የሃይማኖት አባቶች መካከልም አንዱም ቢሆን ማመንዘሩን እንዲተው የነገረው አልነበረም፡፡ … በዚህን ጊዜ ከጎንድ ተክለ ሃይማኖት ተወክሎ የመጣው መነኩሴ ዐፄ ፋሲለደስን በይፋና በአደባባይ አወገዘው፡፡ በሁኔታው የተናደደው ፋሲለደስ መነኩሴው እብድ ስለሆነ አንገቱ ተቀልቶ ይሙት ሲል አዘዘ፡፡ በትእዛዙ መሠረትም በከተማው ዋና አደባባ አንገቱ ተቀልቶ እንዲሞት ተደረገ፡፡”(ካህሳይ ገ/እግዚአብሔር፡፡ ምንኩስና በኢትዮጲያ ዛሬና ትናንትና፤ 2000፤ አሳታሚ አልተጠቀሰም፤ ገጽ.81-84) እውነትም! እንዲህ ለእውነት የሚጨክን እብድ እንጂ ምን ሊባል ይችላል?
3.    አፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ አንዲት ሚስትና ከሁለት ዕቁባት በላይ እንደነበራቸው ነገር ግን ምንም አይነት ተቃውሞና ውግዘት ወይም የተመለስ ተግሳጽ እንደገጠማቸው ምንም አልተመዘገበልንም፡፡
4.    ልጅ ኢያሱ አንዲት ሚስትና  ብዙ ቁባቶች እንደነበሩት እጅግ የሚያሳፍረው በአደባባይ ሳይቀር ከቤተ ክርስቲያኒቱ አማኞች ውጪም ቁባቶች እንደነበሩት የቅርብ ጊዜ ያልተሰወረ እሙን ነበር፡፡ በሐሜትና በጥላቻ ከማግለል በቀር ግን በግልጥ ያወገዘ አልሰማንም፡፡ ነገር ግን የአባቶቻችን ትምህርት በግልጥ እንዲህ ልነበር፡፡
        
       “ … እኒህን ሰዎች መላ ዘመናቸውን ከቤተ ክርስቲያን እንዳይገቡ
             ከምዕመናን እንዳይገናኙ ሊከለክሏቸው ይገባል”   
             (ተግሳጽ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አን.4 ገጽ.43)
 ለ. ጥንቈላ፦ ጥንቈላ እግዚአብሔር ባልፈቀደው መንገድ መንፈሳዊ ኃይልን መፈለግ ነው፡፡(የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት) በጠቅላላ ትርጉም መተተኛ፣ አስማተኛ፣ ድግምተኛ፣ ቃላተኛ፣ አንዳንዴም ሞራ በመግለጥ፣ ጠጠር በመጣል፣ መናፍስትን በመጥራት ዕድል ነጋሪዎችንም  … የሚለውንም በውስጡ የሚያካትት ነው፡፡
    ጠንቋዮች ከጥንት የነገስታት ልዩ አማካሪ በመሆንና እግዚአብሔርን በመገዳደር የሚታወቁ ናቸው፡፡ ፈርዖን እንደሙሴና አሮን ተዓምራትን የሚያደርጉና የሚያማክሩት ጠቢባንና መተተኞች፤ የግብጽ ጠንቋዮችና አስማተኞች ነበረው፡፡(ዘፀ.7፥11፤2ጢሞ.3፥8) ናቡከደነጾርም ህልም ተርጓሚዎችን ጭምር ነበረው፡፡(ዳን.2፥2)
      ጠንቋዮች የእግዚአብሔርን ፈቃድና ምሪት ባለመቀበል፤ በራሳቸው ጥበብና ማስተዋል በመደገፍ፣ ርኩስ መንፈስንና የሙታንን መናፍስት በመጠየቅ፣ ምስጢራውያን አስማትን በመድገም፣ልዩ ልዩ መሥዋዕትን በማቅረብ፣ የእንሰሳት ሆድ ዕቃና ሌሎች ነገሮችንም በመመልከት የሚመጣውን የሚናገሩ፤ ጠላቶቻቸውን የሚጎዱ ወዳጅ የሆኗቸውን ደግሞ የሚጠብቁ ናቸው፡፡
    ስለዚህ ጠንቋዮችና መናፍስት ጠሪዎች በምድሪቱ እንዳይኖሩ እግዚአብሔር ተናገረ፡፡(ዘፀአ.22፥18) ለእግዚአብሔር ያደሉና እውነተኛ ነገስታት “የሕጉን ቃል ያጸኑ ዘንድ፥ መናፍስት ጠሪዎቹንና ጠንቋዮቹን ተራፊምንና ጣዖታትንም በይሁዳ አገርና በኢየሩሳሌም የተገኘውን ርኵሰት ሁሉ …  አስወገዱ።”(2ነገ.23፥24) ሳኦል ምንም እንኳ በመጀመርያ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር ያጠፋ ቢሆንም በኋላ ግን የእግዚአብሔርን ቃል ባለመጠበቅ መናፍስት ጠሪን በመጠየቁ መንግስቱ እንደሳሙኤል ቀሚስ ተቀደደች፡፡(1ዜና.10፥13፤1ሳሙ.15፥27)
     በሐገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ነገስታትና መሪዎች ልዩ የጥንቈላ ምሪት ተቀባይ እንደነበሩ የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡ በቤተ ክህነት ቅብዐ መንግስት ተሸመው የጠንቋይ ቃል ደጅ የሚጠኑ ነገስታት የቅርብ ትዝታ ናቸው፡፡ እስከእግር እጣቢ ያጠጡትን ጠንቋዮችና አስማተኖችን “አለም የተቃወመችውን ያህል” ቤተ ክርስቲያን ዝምታን መምረጧ፤ በተለያየ ምክንያት ክህነታቸው የተሸረ ደብተራዎችና፤ ክህነት ያላቸው ጥቂት የማይባሉ ቄሶችና መሪጌቶች በዚህ ርኩሰት ተይዘው ከመታማት አልፈው እጅ ከፍንጅ ሲያዙ እንኳ ከሥራ ዝውውር ውጪ ዝም መባሉ በአንድ ጉያ ስንት ነገር ነው ታቅፈን የምንኖረው ያስብላል?
    አዎ! እግዚአብሔር የጠንቋዮችን መንፈስ ባዶ፤ ምክራቸውንም ወና ያደርጋል(ኢሳ.19፥3) ጠንቋዮች የሚገለገሉበት ቁስ እጅግ የከበረ ዋጋ የሚያወጣ ሆኖ ቢገኝ እንኳ ሊቃጠልና ሊወድም እንጂ በምንም መልኩ ለእግዚአብሔር ወንጌል አገልግሎት ሊውል አይገባውም፡፡ “ ከአስማተኞችም ብዙዎቹ መጽሐፋቸውን ሰብስበው በሰው ሁሉ ፊት አቃጠሉት፤ ዋጋውም ቢታሰብ አምሳ ሺህ ብር ሆኖ ተገኘ።”(ሐዋ.19፥19)፡፡ በእነዚህ ሰዎች የሚመጣ የትኛውም ምስክርነት፤ እውነት ቢሆን እንኳ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፡፡(ሐዋ.16፥17)
     በመጨረሻም ጥንቁልና የሥጋ ሥራና ከመንግስተ ሰማያት በውጪ የሚያኖር ኃጢአት ነውና(ገላ.5፥20፤ራዕ.22፥15) ሊወገዝ ፣ ሊለይ የዚህ ድርጊት ተባባሪዎችም ያለምንም ማመቻመች ንስሐ ገብተው ካልተመለሱ ሊጎነደሉ ፍጹም የተገባ ነው፡፡ እነዚህን ዝም ማለት ግን ከየት መጣ?
     . የኃጢአተኞችን መባዕ ስለመቀበል ፦ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተንጸባረቁ ካሉትና ከመጡት ነውሮች አንዱ “በአለም የታወቁ” ዘፋኞችና ፖለቲከኞች … ህዝብን ከበደሉበትና ካስነወሩበት ኃጢአታቸው ሳይታጠቡ የመንፈሳዊ ካባ “ለምድ” ለብሰው ሥጦታ፣ ብርና ቁሳቁስ ለአያብተ ክርስቲያናት  እያደሉና እየደለሉበት፤ የህዝቡንና የቤተ ክርስቲያን መንፈስ ሲያረክሱ፤ “እስኪ ንስሐ ይቅደም፤ ቅድሚያ ብዙውን ያሰናከለውን የኃጢአታችሁን ዕድፍ አጥሩ!!!” የሚል አባትና ሲኖዶስ መጥፋቱ ከድጥ ወደማጥ የሚያስብል “መንፈሳዊ” ጉዞ እያየን ነው፡፡
   ቤተ ክርስቲያን ማናቸውንም መባዕና አስራት፤ሥጦታና በኩራት በኃጢአታቸው ከተለዩ ሰዎች ልትቀበል አይገባትም፡፡

       “ልበ ደንዳና ከሆነ ሰው መባዕ አትቀበል፥ ከሚሰርቅም አንጥረኛ ቢሆን ስለትርፍ በሐሰት ከሚምል ነጋዴም ቢሆን ትንሳኤ ሙታንን ከሚክድ ፈርሰው በስብሰው ይቀራሉ ከሚል ሰዱቃዊም ቢሆን የሚሹትን አልሰጣቸው ብሎ አገልጋዮቹ ከሚከሱት ባለጠጋም ቢሆን አትቀበል፡፡ ከሌባም ቢሆን ንስሐ ካልገባ ነፍሰ ገዳይም ቢሆን ግብሩን (ትርፍ መጨመርን) ካልተወ ቀራጭም ቢሆን በሴሰኝነት ካለች ዘማም ቢሆን በሚዛን ከሚሰርቅም ቢሆን እህል እያለው ከማይራራ ከእርሱ ለሚለምን ብድር እንኳን ከማይሰጥ ሰውም ቢሆን ጣዖት ከሚያመልኩም ቢሆን ከሥራየኞችና ከጠንቋዮችም ቢሆን አትቀበል፡፡ ኮከብ ከሚቈጥሩ ጋኔን ከሚጠሩም ቢሆን በሰይጣናዊ ዕውቀት እንዲህ ይሆናል ከሚሉ ዐዋቂዎች ነን ባዮችም ቢሆን ከእነዚህ መባእ አትቀበል፡፡በመብል በመጠጥም ከእነርሱ አትተባበር፡፡  ክፉ ከመሥራት ከማይታገሱ ዐመፀኞች መባእ አትቀበል፡፡ ከወንጀለኞች ከሴሰኞች ከመናፍቃን  የወርቅ የብር የብረት ምስል ቀርፀው አፍስሰው ታዖት ከሚሠሩም ቢሆን ከቀን ወራሪዎች ከሌሊት ሰባሪዎችም ቢሆን አትቀበል፡፡
    ከሰካሮችም ቢሆን ለባህርያቸው የማይገባውን ከሚሠሩም ከሚቀበሉ ቢሆን ከሐሰተኞች  መምህራን በወፍ ከሚያሟርቱም ቢሆን መባእ አትቀበል፡፡ አሁን ከተናገርናቸው ከሌሎች ኃጥአንም ቢሆን መባዕ የሚቀበል ለእግዚአብሔር የሚገባውን መባእ ወደሚያቀርቡበት መሠዊያ የተከለከለውን ዓይኑ የታወረውን እግሩ ያነከሰውን ቃባ የያዘውን በግ ለመሥዋዕት  ያቀርብ እንደነበረው ምሥዋዐ ብርቱን እንደአሳደፈው እንደኦሪቱ ካህን እግዚአብሔርን  በክህነቱ ደስ አያሳሰኘውም፡፡”
     (ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምዕት ምዕ.22 ቁ.6-11 ገጽ.46-47)


“ከደጋጎቹ ምዕመናን ቁርባን በቀር መሥዋዕት አይሠዉ፡፡ የተሳዳቢዎችን የነፍሰ ገዳዮችንየሴሰኞችን የጣዖት አምላኪዎችን የሌቦችን ጣዖት የሚሠሩትን የሰካራሞችን ባልቴቶችንና ድሀ አደጎችን የሚያስቸግሩትን የቀራጮችን የቀማኞችን የዓመጸኞችን መባዕ አይቀበሉ፡፡ ድሆችን የሚያስቸግሩ ጭፍሮች በግድ ሰዎችን ከሚያስሯቸው ባሮቻቸውን በክፉ አገዛዝ  ከሚገዟቸው ክፋትም ከሚያደርጉባቸው በግፍ ከሚበድሉ ሰዎች ወገን መባዕ(መሥዋዕት)አይቀበሉ፡፡ ከወይኑ ውኃ ጨምረው ከሚሸጡ ነጋዴዎች ሕግን ከሚያፈርሱ ሁሉ አይቀበሉ፡፡ ብልሁ ሰሎሞን እንደተናገረ እግዚአብሔር የኃጢአተኞችን መሥዋዕት ይጸየፋልና፡፡(ምሳ.15፥8)
         
                      (ፍትሐ ነገስት አን.13 ቁ.501 ገጽ.138)

     ይህ ግልጽ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና በግልጽ በጠራራ ፀሐይ ሲገረሰስ፤ሲገደፍ ልክ አይደለም ያለ የጭንቅ ያህል አለመገኘቱ “የት ነን?” ያሰኛል፡፡ ይበልጥ የሚያንገበግበው ዘፋኞች ፣ ከሰው ያልተፈጠሩ የሚመስሉ አሸዋ ከስኳር ፣ ቀይ አፈር ከበርበሬ ፣ ሙዝ ከቅቤ … እየቀላቀሉ የሚሸጡ ስግብግብ ነጋዴዎች ፣ሴሰኞች ፣ደም ደም የሚሸቱ ፖለቲከኞች በግልጽም በሥውር እጅም ከኋላ መንፈሳዊውን ዓለም “ሲዘውሩ” ቤተ ክርስቲያን ግን አብራ ከመዘወር ተቆጥባ አንድም ዘመን እኒህን “ንስሐ ግቡ አልያ እጃችሁን ሰብስቡ” ያለችበትን ዘመን ትዝ አይለንም፡፡
    አንድ አገልጋይ ወዳጄ ያጫወተኝን እዚህ ጋ ማንሳት እሻለሁ፡፡ አንድ በቲቪ ድራማ ላይ የምናውቃት “ጨዋ አርቲስት” ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይዛ ወደአንድ ገዳም አስተዳዳሪ ጠጋ ብላ “አስራት በኲራት” እንደሆነ አስገንዝባ ልትሠጥ ስትዳዳ ፤ እኒህ አባት የአስራቱን የት መጣ ለመረዳት ከምን ሥራ አገኘሽው? የሚለውን ሲጠይቋት አላማራትም፡፡ ስለዚህ አኩርፋ ስትወጣ፤ ወዲያው ወደሌላ ገዳም “አበምኔት” ስትደውል ሳያቅማሙ እጅ ዘርግተው ተቀበሏት፡፡ ከጥቂት ጊዜ በፊት ዘፋኞቹ ለአንድ በአሜሪካ ለሚገኝ “ቤተ ክርስቲያን” ማሰሪያ ገንዘብ ሲያሰባስቡ አንድ አባት በመካከል ተገኝተው “የዘፋኞቹን አምኃ መቀበል እንደሚገባ ያስረገጡትንም” ማውሳት እወዳለሁ፡፡ (እግዚአብሔር ግን ከመሥዋዕት፤ ከሚጤስ ስብና ከሚቆጠር ገንዘብና ሳንቲም በፊት ግን ከኃጢአትና ማሰናከያን ከሚያኖር ህይወት ወጥተን እንድንታዘዘው፤እንድንሰማው መሻቱን ማን በነገረን?!) 
    አዎ! መወገዝ ያለበት ሁሉም የሥጋ ሥራ እንጂ መናፍቅነት ብቻውን ተነጥሎ አይደለም፡፡ መወገዝ ያለበት ሁሉም የሥጋ ሥራ እኩል እንጂ፡፡ ሁሌም ግን መዘንጋት የሌለብን ነገር “ብዙዎቻችን እንደዚህ ነበርን፤ አሁን ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በአምላካችንም መንፈስ ታጥበናል፣ተቀድሰናል፣ ፀድቀናል”(1ቆሮ.6፥11) ጋድም ወደኋላ መመለስ አይሆንልንም፡፡ እግዚአብሔር ከዚያ ከነበርንበት ማንነት ዛሬ በልጁ ደምና ኃይል እንጂ ልማድ አድርገን እንድንኖር አልተጠራንም፡፡(ቲቶ.2፥11) የኃጢአት ትንሽና ትልቅ ከሌለው፤ በግልጽ ኃጢአተኞች ከመንግስተ ሰማያትና ከቤተ ክርስቲያን በአፍዓ ከተጣሉ፤ እኛም ኃጢአትን በትልቅና በትንሽ፤ የምግባርና የኃይማኖት ኃጢአት እያልን ከፋፍለን እንናገር ዘንድ አልተፈቀደልንም፡፡
    ቤተ ክርስቲያንን መናፍቅነት ብቻ የሚያረክሳት ሳይሆን የሥጋ ሥራ የተባሉቱም ያረክሷታልና ኃጢአትን በግልጥ የመጠየፍ ፣የመናቅና የመካድን ህይወት “ያለማመቻመች” ልትይዝ ይገባታል፡፡
                   “አንዱስ እንኳ ኃጢአት ለመሥራት የሚሄድ ቢኖር እርሱ
                   የእግዚአብሔርን ፈቃድ ይጠላልና ከዓለማዊ መናፍቅም
                          ጋር ይቆጠራል፡፡ … ”
         (ፍትሐ ነገሥት መንፈሳዊ አንቀጽ 11 ቁጥር 422)
   ስለዚህ፦
      “የእግዚአብሔር አገልጋይ ካህን ሆይ መባእ ስለሚያገቡ ሕዝብ
        መንቃት ይገባሃል፤ ለመብል ብለህ መዓርግህን አታዋርድ፡፡”     
                                   (ሃይማኖተ አበው ዘሠለስቱ ምዕት ምዕ.22 ቁ.5 ገጽ.46)
 ይቀጥላል......

1 comment: