Sunday, August 30, 2015

ያሬድ አደመና የማያባራ ሸፍጡ

ለእውነት የቆሙ ወንድሞች ከሓዋሳ

ቤተክርሰቲያን በብዙ ነገርየተሞላች ነች። ከበጎ ህሊና ተነስተው በጎውንአምላክ በእውነት የሚያመልኩናየሚገዙለት ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ከአእምሮዋቸው ጥልቅ ዋሻ ውስጥ ተዘርቶ የበቀለውን ክፋት እያንቆለጳጰሱ ለጠላት ዲያቢሎስ ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተው ነገሮቻቸውን ሁሉ በተንኮል የመሰረቱ ብዙዎች አሉ። የእግዚአብሔር ወንጌል ሳይገባቸው ገባን እያሉ ኪዳኑን ሳይቀበሉ “ባለኪዳን” ሆነው በወንጌል ስም የሚያጭበርብሩ እንዲሁ አሉ።
በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ለታመነው ወንጌል የቆሙና ጌታን የሚያገለግሉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ በየዋሁ ህዝብና በሚያድነው ቃል እየዘበቱ ለግል ጥቅማቸው የሚሯሯጡም አሉ።  እነዚህ ሰዎች እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ አድርገው ለምድራዊ ጥቅም የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ የተጠሩበትን እውነት ትተው ያልተጠሩበትን ገንዘብ የሚያገለግሉ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግስት ሥራ እያስነቀፉ ይገኛሉ።

እውነተኛና የዋሃን የሆኑ አገልጋዮች ቢሳሳቱ ልባቸው ለመመለስ ቅርብ የሆነ ማንንም ለመጉዳት የማይሞክሩና ተስፋቸውን በጌታቸው ላይ የጣሉ ናቸው።ክፉዎቹ ደግሞ ሰላም የማይስማማቸው፣ እውነት የሚጎረብጣቸው፣ ተንኮል ካልሰሩበት ቀኑ የማይመሽላቸውናጌታን ከማገልገል ይልቅ ወሬ በማማታት ጊዜ የሚያጠፉ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ለምን እንደተፈጠሩ፣ በማን እንደተለዩና ማንን እንደሚያገለግሉ ማሰብ አይፈልጉም፡፡ ይልቁንም በዙሪያቸው ያለውን ሰው ሁሉ ካልነኩና ካላነካኩ ሠላም የማይሰማቸው ናቸው። ይህን መሰል ሰዎች ማኅበረ ቅዱሳን ሲያገኙ ያለምንም ማቅማማት ማቅ የሚሆኑ ጴንጤ ሲያገኙ ዋና ባለጉዳይ ሆነው የሚገኙ ከተራማጅ ኃይሎች ጋር ራሳቸውን ለማመሳሰል ስንፍና የማይገኝባቸው ናቸው። ይህ የእስስት ባህሪያቸው የማንም ወዳጅ እንዳይሆኑ ማንንም ከልብ እንዳይቀርቡ አድርጓቸዋል። የሚያምኑበት እምነት እና የተመሰረቱበት እውቀት የላቸውም፡፡ ለሚያደርጉት ነገር ሁሉ መሰረት አድርገው የሚነሱት ጥቅምን ነው። ጥቅም እስካገኙበጠዋት ተነስተው ያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ሌላ አልሰብክም ይላሉ። ከሰአት ደግሞ ከማርያም ውጭ ለማንም አልዘምርም ለማለት አይሰንፉም።
በሁሉም ነገር መሰረታቸው ጥቅም ነው። ለማያውቃቸው ሰው ስለ እነርሱ ብዙ ለማለት ድፍረት አይሰጡም። ከሁሉም ጋር ይመሳሰላሉ። በዚህ መመሳሰል ውስጥ ግን ልባቸው ከሚያገኙት ጥቅም ጋር እንጂ ከማንም ጋር የለም። ያምናሉ እንዳንል የእምነት ሕይወትና የአማኝ ልብ የላቸውም። አያምኑም እንዳንል አማኞች ካሉበት ሥፍራ እና መድረክ አይጠፉም።
በዚህ ባህሪ ከተያዙ ሰዎች መካከል የአንዱን ማንነት፣ ባህሪና ካደረጋቸው ክፋቶች አንዳንዶቹን ጠቅሰን ለመጻፍ ተገደናል።ይህን የምናደርገው ስም ለማጥፋት ብለን ሳይሆን የወንጌሉን አገልግሎት ከጥፋት መልእክተኞች ለመጠበቅ ባለብን ሃላፊነት ነው፡፡ አባ ሰላማ ብሎግም ይህን ከግምት አስገብታ ጽሁፉን እንደምታወጣልን እናምናለን።ይህ ግለሰብ ለቤተክርስቲያኒቱ በጎ ለውጥ ከሚታገሉ ወንድሞች መካከል ተወሽቆ ብዙ ነገሮችን እየፈጠረና እያበላሸ ይገኛል። ለምክር የማይመችና የሚፈልገውን ጥቅም እስኪያገኝ ድረስ ወደ ኋላ የማይል ሰው ነው። ስለ ሰውየው ማንነት አንባቢ የራሱ ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ ይህን ጽሁፍ ጽፈናል። ይህ ሰው ያሬድ አደመ ይባላል።

Thursday, August 27, 2015

ውግዘትና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት - ክፍል አራት

በዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
1.    ትምህርተ ሥላሴን መካድ

የነገረ መለኮት ተማሪዎች፣ “ትምህርተ ሥላሴ በመናፍቃንና በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የቆመ የመለያ ሰንደቅ ነው፡፡” ይላሉ፡፡ ትምህርት ሥላሴ ለመኖራችንም ፤ ለመዳናችንም መሠረትና የፍጥረትን ዕድል ፈንታ፤ ጽዋ ተርታ ወሳኝ ትምህርት ነው፡፡ መናፍቃን ይህን ትምህርት በአንድም በሌላም መንገድ ይቃወማሉ፤ ይክዳሉ፡፡ ለምሳሌ፦
1.1. የሦስትነት አካላቱን ይክዳሉ

    አካል ፥ “ፍጹም ምሉዕና ቀዋሚ እኔ ባይ” ማለት ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የአካልን ትርጉም “ፍጹም ገጽ፣ፍጹም መልክ ያለው፣ ራሱን የቻለ በራሱ የበቃ፣ እኔ የሚል ህላዌ፣ ነባቢ፣ ቁመት ቁመና፣ የባህርይ የግብር ስም ባለቤት እገሌ የሚባል፡፡ እኔ ማለትም የሚገባ ዕውቀት ላላቸው ለማይሞቱና ለማይጠፉ ለሦስቱ ብቻ ነው፡፡ ለአምላክ፣ ለመልአክ፣ ለነፍስ፡፡” በማለት በስፋት ያብራሩታል፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/፤መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡(1948 ዓ.ም)፤አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡ ገጽ. 229)
    ሦስቱን ፍጹማን አካላት ሥላሴ ስንል የአንዱን እግዚአብሔር በአካላት ሦስት መሆን ወይም ሦስቱን አካላት አብ ፣ ወልድ ፣ መንፈስ ቅዱስን መጥራታችን ነው፡፡ “እውነተኛና ሕያው የሆነ አንድ አምላክ ብቻ አለ፡፡ ይህ አንዱ አምላክ በሦስት አካላት ስለሚኖር ሥላሴ የሚለው ቃል የአንዱን አምላክ የአካል፥ የስምና የግብር ሦስትነት ያመለክታል፡፡ (የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር(2002)፡፡የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9ኛ እትም፣አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡ ገጽ 64)
     አካል ከዓለመ ግዘፍ ጋራ መያያዝ የለበትም፡፡ ብዙ ጊዜ አካልን ከቁሳዊ ነገር ጋር ስለምናያይዝ ያለመረዳት ችግር ወይም ረቂቁ አካል የለውም ወደሚል እሳቤ እንሳባለን፡፡ ነገር ግን አካል የመያዝና የመጨበጥ ጉዳይ ሳይሆን ፈቃድ፣ ስሜትና ዕውቀት ያለው መሆኑንና ራሱን መግለጡ ከመቻሉ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ይህንን ስንል ግዙፉ አካል በግዙፍነቱ ረቂቁን መረዳት አይችልም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ጴጥሮስ ዘምስር እንዲህ ይላል፦
“ረቂቅ ነገርን መረዳት ወይም ማግኘት የሚቻለው በረቂቅ፤ ግዙፍ ነገርንመረዳት ወይም ማወቅ የሚቻለው በግዙፍ ነገር ነው፡፡”

     አካላት ስማቸው የሚቀያየርም አይደለም፡፡ ይህም ማለት አብ፥ አብ እንጂ ወልድ ወይም መንፈስ ቅዱስ፤ ወልድ፥ ወልድ እንጂ አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ፤ መንፈስ ቅዱስ፥ መንፈስ ቅዱስ እንጂ አብ ወይም ወልድ ተብሎ አይጠራም፡፡ ይህ በሌላ አገላለጥ አብ የሚባለው አካል ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ይለያል፤ ወልድም የሚባለው አካልም ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ይለያል፤ መንፈስ ቅዱስ የሚባለውም አካል ከአብና ከወልድ ይለያል፡፡

“የሥላሴ ገጻት በየአካላቸው ልዩ ሲሆኑ በመለኮት አንድነት ጸንተው ይኖራሉ፡፡  አንድ ሲሆኑ ሦስቱ አካላት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ስለመገለጣቸው ሦስትናቸውና፡፡”
(ሃይማኖተ አበው ዘዲዮናስዮስ ምዕ.10 ክ.1 ቁ.11)

     አካሉ የሚጠራው ሦስት  በመሆን ብቻ ነው፡፡ አስማተ አካላት ሦስት ናቸው ስንል በአካል ስሞች ብቻ ነው፡፡ በስመ ዋህድ ግን ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚሁ ጋር እነዚህ ሦስት ፍጹማን አካላት በአንድ ባህርና በእሪና (በዕኩልነት) ስለሚኖሩ ሦስት አማልክት አንልም፡፡
 “አብ አምላክ ነው፤ ወልድ አምላክ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው፡፡ ግን ሦስት አማልክት አይባሉም፤ አንድ አምላክ እንጂ፡፡”
 (ሃይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ ምዕ.25 ክ.1 ቁ.4)

Tuesday, August 25, 2015

“የሚሰማኝ ግን በእርጋታ ይቀመጣል፥ ከመከራም ሥጋት ያርፋል።” (ምሳ. 1፥33)በምድር ላይ ከሚታዩና ከሚከሰቱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮችና አደጋዎች በስተጀርባ ምንድነው ያለው? ለችግሮቹ መከሰት ምክንያቱ ወይም ተጠያቂው ማነው? ቢባል የእኛ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ መሆኑን የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል፡፡ አሁን ለተከሰተው የዝናብ እጥረትና ድርቅ ምክንያቱም ይኸው ነው፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘዳግምን በማንበብ እግዚአብሔር የሚለንን እንስማ፣ ሰምተንም ራሳችንን እንመርምር፣ ራሳችንን መርምረንም ንስሐ እንግባ እግዚአብሔርም ፊቱን ወደእኛ ይመልሳል፡፡

ኦሪት ዘዳግም 28
1 እንዲህም ይሆናል፤ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ፥ ዛሬም ያዘዝሁህን ትእዛዙን ሁሉ ብታደርግ ብትጠብቅም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ከምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል።
2 የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ብትሰማ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይመጡልሃል ያገኙህማል
3 አንተ በከተማ ቡሩክ ትሆናለህ፥ በእርሻም ቡሩክ ትሆናለህ።
4 የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ቡሩክ ይሆናል።
5 እንቅብህና ቡሃቃህ ቡሩክ ይሆናል።

Thursday, August 20, 2015

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህር ቸሬ አበበን ከሥራ አሰናበተ


ከመምህር ቸሬ አድራጎት የምንረዳው አብዛኞቹ የዋሃን አባላቱ ሳይሆኑ አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን ትክክለኛ ዓላማ የገባቸውና ዓላማውን ለማስፈጸም የሚሰሩ አባላቱ ተሰግስገው ባሉበት መንግስታዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ተቋም ውስጥ ተመሳሳይ ድርጊቶችን እንደሚፈጽሙ ነው፡፡ በቸሬ የስንብት ደብዳቤ ላይ የተዘረዘሩት ጥፋቶች እነዚሁ የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች ዕለት ተዕለት የሚፈጽሟቸው ጥፋቶች መሆናቸው ከማንም ስውር አይደለም፡፡ የመጀመሪያው አሉባልታ ነው፡፡ ቸሬ በፓትርያርኩና በአቡነ ጢሞቴዎስ መካከል ጠብን ለመዝራት የሄደበት መንገድ ከዚህ ቀደም የማኅበሩን ዕድሜ ለማራዘም ማኅበሩ ከተጠቀመባቸው ስልቶች መካከል እውነታዎችን ገልብጦ ማውራት በኃላፊዎች መካከል ልዩነትን መፍጠርና ከተቻለ ማጣላት አንዱ ስልት ነው፡፡ ይህን በዌብ ሳይት ጭምር የሚጠቀሙበት ስልት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ሐራ የተባለው የማኅበሩ  እንደሆነ የሚታመነው ብሎግ አንድን ክስተት ገልብጦና የተደረገውን አዛብቶ በማቅረብ ይታወቃል፡፡ በቅርቡ እንኳን ስለ ሊቀ ሥዩማን የማነ የጻፈው ሥራ አስኪያጁን ከፓትርያርኩና ከመንግሥት ለማጋጨት ያለመ ቢሆንም “ልቦለዱን” ያቀረበበት መንገድ ግን ማንንም የማያሳምን ሆኖ ነው የተገኘው፡፡

Tuesday, August 18, 2015

በደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ማቅ የጎርጎርዮስ ቅርንጫፍ ሊያደርገው ያሰበው ት/ቤት ታገደበትየደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ችግሮችን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በመረጃዎች የተደገፉ ዘገባዎችን ማውጣታችን ይታወሳል፡፡ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ችግሩ ስለሌለ ሳይሆን የማቅ ጥቅም ስላልተነካ ሐራ በጉዳዩ ላይ ዝምታን መርጣ ነው የከረመችው፡፡ አለቃው አባ ገብረ ሚካኤል በሙስናና በስነምግባር ብልሹነት ውስጥ የተዘፈቁ ቢሆንም አሁንም በደብሩ ውስጥ ሰልጥነናል ያሉ ዕድሜያቸው ከሰንበት ት/ቤት የዕድሜ ጣራ የዘለለ አባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ተስማምተው የግል ጥቅማቸውን ሲያሳድዱና ለማቅም ምቹ ሁኔታዎችን ስላመቻቹ ሐራ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝምታን መርጣ ቆይታለች፡፡ ሲያልቅ አያምርምና አለቃውና የማቅ ቡድን የሆኑ በሰበካ ጉባኤ፣ በሰንበት ት/ቤትና በህንጻ አሰሪ ኮሚቴ ውስጥ የነበሩ አባላት ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ ጉዳቸውን መዘካዘክ ያዙ፡፡ አለቃውም መታገድ አለባቸው ያሉትን አገዱ፡፡ ለሀገረ ስብከቱም አሳወቁ፡፡ ይህን ተከትሎ አማሳኙ የማቅ ቡድን ከአለቃው ጋር እርቅ ቢጤ በማውረድ ከእርቅ መልስ ጮማ ወደሚቆርጡበት መጠጥ ወደሚጠጡበት ቦታ ተያይዘው ሄዱ፡፡ አለቃውም ለታገደው በተለይ ለሰበካ ጉባኤው ምክትል ሊቀመንበር እግዱን አነሳልሃለሁ ብለው ተስፋ የሰጡ ቢሆንም ጉዳዩ በሀገረ ስብከቱ የተያዘ ከመሆኑ አንጻር በቀላሉ የሚነሳ አልሆነም፡፡
በዚህ መካከል ያረጀ ቢሆንም አባቷ ደጀሰላም ድረገጽ የሚጠቀምበትን ስልት እርሷም መጠቀሙን ተያይዛዋለች፡፡ ከዚህ ቀደም ማቅ ከካዝናው እየዛቀ በሚያፈሰው ገንዘብ የተቆጣጠራቸውን የግል ፕሬሶች ውጤቶችን በመጠቀም ዘገባዎች እነርሱ ላይ እንዲወጡ ካደረገ በኋላ ደጀሰላም እነርሱን ምንጭ አድርጎ ይጠቀም ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜም የፕሬስ ውጤቶቹ ከደጀሰላም ዘገባዎችን በመውሰድ እየተናበቡ የማኅበረ ቅዱሳንን ትግል ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ ሐራም ይህን “የተበላ” ስልት መጠቀሟን ቀጥላለች፡፡ አዲስ አድማስን፣ ኢትዮ ምኅዳርንና ሰንደቅን በዚህ በኩል እየተጠቀመችባቸው ነው፡፡ በቅርቡ ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ከፍለው ዘገባ ያሰሩትና የእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያንን በየቤተሰብ ተደራጅተው እየቦጠቦጡ ያሉት የማቅ ቡድን አባላትና ደጋፊዎች እውነቱን ለማድበስበስ ሲጥሩ ታይቷል፡፡ እጅግ በሚዘገንን የእምነትና የሥነምግባር ችግሮች ውስጥ የሚገኙትንና አንዳንድ በሰበካ ጉባኤ በሰንበት ት/ቤትና በሕንጻ አሰሪ ኮሚቴ ውስጥ ያሉትን አባላት ጻድቃን አድርጎ ሲያቀርባቸው በበላበት መጮኹን አስመስክሯል፡፡ ሐራ ጋዜጣውን ጠቅሳ በሙዳየ ምጽዋት የሚሰበሰበውን ገንዘብ በአግባቡ በመጠቀም እና የራሳቸውን አስተዋፅኦ በማከል ሥራው አኹን ለሚገኝበት ደረጃ ያበቁት የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴው አባላት ትጋት እና ታማኝነት በአጥቢያው ምእመናን የሚጠቀስ ነው፡፡” ብላለች፡፡ (የአይጥ ምስክር ድንቢጥ አሉ!) ሕዝቡ እያለ ያለው የሕንጻው ሥራ ከሚፈለገው በላይ ዘገየ፡፡ እጅግ በርካታ ሚሊየን ብር ተበልቶበታል ነው፡፡

Sunday, August 16, 2015

“መድሎተ ጽድቅ” በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን - ክፍል ሦስትካለፈው የቀጠለ -
ዳዊት እስቶክስና የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር
ብንደግፈውም ብንቃወመውም፥ ቢስማማንም ባይስማማንም አንድን የተፈጸመንና የራሱን አሻራ ትቶ ያለፈን እውነተኛ ታሪክ መለወጥ አንችልም። ታሪኩን ለመለወጥና ሌላ መልክ ሰጥተን ለመግለጥ ብንሞክር ግን በታሪክ ተወቃሽ ከመኾን አናመልጥም። እንዲህ ሲባል ግን ታሪክን አዛብቶ ማቅረብና ያን የተዛባ ታሪክ ሰዎች እውነተኛ ታሪክ መስሏቸው ለጊዜውም ቢኾን እንዲቀበሉት ማድረግ አይቻልም ማለት አይደለም። ለምሳሌ፦ ሞትን ድል አድርጎ የተነሣውን የጌታችንን የትንሣኤ የምሥራች፥ ከሞት መነሣቱ ኪሳራ የሚያደርስባቸው መኾኑን የተረዱ የካህናት አለቆችና ሽማግሌዎች በሌላ የፈጠራ ታሪክ እንደ ተኩትና፥ ‘ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰረቁት እንጂ፥ ኢየሱስ ከሙታን ተለይቶ አልተነሣም’ የሚለው የፈጠራ ታሪክ እውነት መስሎ ወንጌላዊው ማቴዎስ ወንጌሉን እስከ ጻፈበት ጊዜ ድረስ እንኳ በአይሁድ ዘንድ ሲወራ እንደሚኖር ጽፏል (ማቴ. 28፥11-15)። ስለ ዴቪድ እስቶክስ ከዚህ ቀደም በማኅበረ ቅዱሳን፥ አኹን ደግሞ በ“መድሎተ ጽድቅ” እየተተረከ ያለው የተዛባ ታሪክ ከዚህ የተለየ አይደለም።
ታላቁ ሰው ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ስለ ታሪክ አጻጻፍ ያስቀመጡት መርሕ እዚህ ላይ ቢወሳ መልካም ነው። እንዲህ ነበር ያሉት፥
ታሪክን መማር ለኹሉ ሰው ይበጃል፤ … የታሪክ ትምህርት ግን የሚጠቅም የውነተኛ ታሪክ ትምህርት ሲኾን ነው። እውነተኛንም ታሪክ ለመጻፍ ቀላል ነገር አይደለም። የሚከተሉትን ሦስት የእግዚአብሔር ስጥወታዎች ያስፈልጋልና። መጀመሪያ ተመልካች ልቦና፥ የተደረገውን ለማስተዋል፤ ኹለተኛ የማያደላ አእምሮ፥ በተደረገው ለመፍረድ፤ ሦስተኛ የጠራ የቋንቋ አገባብ፥ የተመለከቱትንና የፈረዱትን ለማስታወቅ። ያገራችን የታሪክ ጻፎች ግን በነዚህ ነገሮች ላይ ኀጢአት ይሠራሉ። በትልቁ ፈንታ ትንሹን ይመለከታሉ። ለእውነት መፍረድንም ትተው በአድልዎ ልባቸውን ያጠባሉ። አጻጻፋቸውም ድብልቅልቅ እየኾነ ላንባቢው አይገባም (2002፣ገጽ 1)።
በ“መድሎተ ጽድቅ” ስለ ዳዊት እስቶክስ የተጻፈው በአብዛኛው ይህን መስፈርት ያላሟላ ከመኾኑም በላይ፥ ታሪክን ያላገናዘበ፥ በእውነታው ላይ ያልተመሠረተና ምንጭ የሌለው፥ በጭፍን ጥላቻ ላይ የተመሠረተ ተራ ስም ማጥፋት ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ማኅበረ ቅዱሳን ከዚህ ቀደም “የገሃነም ደጆች” በሚል ርእስ በስምዐ ጽድቅ ልዩ ዕትም ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ባወጣው ጽሑፍ፥ በተለይ በመጋቢት 1995 ዓ.ም. ዕትሙ የብዙዎችን ስም አክፍቶ በጻፈ ጊዜ፥ እንዲሁም “የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ” በሚል ርእስ በ2003 ዓ.ም. ባሳተመው አነስተኛ መጽሐፍ ላይ፥ የዳዊት እስቶክስን ታሪክ ያቀረበው በዚሁ መንገድ ነው። ዳዊት እስቶክስና ማኅበራቸውን “የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር”ን አገልግሎት በተሳሳተ መንገድ ነው ያቀረቡት። ይህም የሚያሳየው ለዐላማቸው መሳካት ሲሉ የነበረውን ታሪክ ለውጠው በማቅረብ እውነተኛውን ታሪክ እያጠፉና ራሳቸው የፈጠሩትን ዐዲስ ታሪክ አሥርገው እያስገቡ መኾናቸውን ነው።
ዳዊት እስቶክስና “የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር” በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያከናወኑት ተግባርና ያበረከቱት አስተዋፅኦ ብዙ ቢኾንም፥ በዚህ ጽሑፍ ግን ለአብነት ያኽል እጅግ ጥቂቱን ለመጠቃቀስ እንሞክራለን። (ለዚህ ምንጫችን በዋናነት፥ “The Most Valuable Thing: The Word at Work in Ethiopia” በተሰኘ መጽሐፋቸው ከሚሲዮናውያቱ አንዷ የነበሩት ዶሪስ ቤንሶን የጻፉት የማኅበሩ የአገልግሎት ታሪክ ነው። በተጨማሪ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በትምህርቶቻቸው ከተሳተፉትና በሕይወት ካሉት፥ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥና በሌላም ስፍራ በልዩ ልዩ የሥራ መስክ ላይ ከሚገኙት ከአንዳንዶቹ ያገኘነውን መረጃም በምንጭነት ተጠቅመናል።)

“Bible Church Men’s Society” (BCMS) በእንግሊዝ አገር በሎንደን የተቋቋመ ማኅበር ሲኾን፥ አባላቱ በአብዛኛው ከአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ናቸው። በኢትዮጵያ ተቋቁሞ ይሠራ የነበረው የዚህ ማኅበር ቅርንጫፍ፥ “የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር” በመባል ይታወቅ ነበር። ማኅበሩ በኢትዮጵያ የ”BCMS” ቅርንጫፍ ኾኖ ይሠራ የነበረው በመንግሥት ፈቃድና ድጋፍ ሲኾን፥ በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር በቅርብ በመተባበር ነበር። ይልቁንም በጎንደር ከሰሜንና በጌምድር ሀገረ ስብከት፥ በአሥመራ ከኤርትራ ሀገረ ስብከት፥ በመቀሌ ከትግራይ ሀገረ ስብከትና በሸዋ ለመዘዋወር ከሀገረ ስብከቱ ፈቃድና ስምምነት እያገኘ ሲኾን፥ በአዲስ አበባ ከመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጋር ወዳጅና አጋር በመኾን ከፍተኛ የወንጌል አገልግሎት አበርክቷል።

የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር ዐላማ ምን ነበር?
የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበርን ያቋቋሙት ሚስዮናውያን ዐላማቸው “መድሎተ ጽድቅ” እንደሚለው በስልት ተጠቅመው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ፕሮቴስታንታዊ ማድረግ ፈጽሞ አልነበረም። ማንነቷ እንደ ተጠበቀ መጽሐፍ ቅዱስን በማሠራጨት አገልጋዮቿ ቀሳውስትና ዲያቆናት ስብከተ ወንጌልን እንዲያፋጥኑና ለሕዝባቸው ወንጌልን እንዲያደርሱ ለማድረግ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ የተከናወነውን የቤዛነት ሥራ በመግለጥ፥ የወንጌሉን የምሥራች ለሕዝባቸው ማድረስ እንዲችሉ ከስብከተ ወንጌል ጋር የተገናኘና መሰል ትምህርቶችንና ሥልጠናዎችን በመስጠት ቤተ ክርስቲያኗን መርዳትና መደገፍ ላይ ያተኰረ ነበር። ቀጥሎ የቀረቡትና በጽሑፍ ያሰፈሯቸው የዐላማቸው ነጥቦችና የሠሯቸው ሥራዎች ይህን ይመሰክራሉ። የሚከተሉት “ዘጠኝ ነጥቦች” የማኅበሩ ዐላማዎች ሲኾኑ፥ እነ አልፍሬድ ባክስተን በኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎታቸውን በይፋ ከመጀመራቸው በፊት ያስታወቋቸው ናቸው።
1.      ኹሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት መኾን አለባቸው ብለን እንመኛን።
2.     ስለ ኾነም የእኛ እውነተኛ ምኞት ይህቺኑ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መርዳት፥ ከክርስቶስ ትእዛዝ ጋር በተገናኘም የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ወደሚቻለው የምድሪቱ የጠረፍ አካባቢዎች እንድትሰብክ ማድረግ ነው።
3.     በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሕዝቡ በሚታወቀው ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን የማሠራጨትና የማስተማር ተግባር መጽሐፍ ቅዱስን በማቅረብ እርሷን መርዳት ፍላጎታችን ነው።
4.     በያንዳንዱ መንደር [ሕንጻ] ቤተ ክርስቲያን ይገነባ ዘንድ ፍላጎት አለን።
5.     በዚህ መንገድ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በከፍተኛ ኹኔታ ማደግ ስላለባት፥ እኛ ሕዝቡን በስብከተ ወንጌል እንዲያግዝ እናስተምረዋለን፤ ይህን የምናደርገውም ከጥንቷ ቤተ ክርስቲያንና ከታሪኳ ጋር በተስማማ ኹኔታ ነው።
6.    የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለመዳን የሚያስፈልጉ ነገሮች ኹሉ በብሉይና በሐዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ መኖራቸውን እንደምታምን ኹሉ፥ የእኛም እምነት ይኸው ነው።           
7.     የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኒቅያ የእምነት መግለጫ ዋናው የእምነት አጠቃላይ መግለጫ መኾኑን ታምናለች፤ እኛም እናምናለን።
8.     ክርስቶስ ኹለቱን ምስጢራት ማለትም ጥምቀትንና ቍርባንን እንድንፈጽም አዞናልና አማኞች ኹሉ እነርሱን መፈጸም አለባቸው። ስለዚህ የእኛ ሐሳብ በስብከተ ወንጌል ምክንያት ወደ ቤተ ክርስቲያን ለሚመለሱት፥ ወይም ለሚጨመሩት ክርስቲያኖች ኹሉ እነዚህን ምስጢራት መፈጸም ያለበት የኦርቶዶክስ ቄስ ሊኾን ይገባል የሚል ነው።
9.    ግእዝ ወንጌልን ለሚሰብኩ ጠቃሚ መርጃ መሣሪያ መኾኑን በመገንዘብ፥ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ግእዝ ላለው ጠቀሜታ ዕውቅና እንሰጣለን። ስለዚህ ኹሉም ሰባክያን ግእዝን እንዲያጠኑ ማበረታታት አለብን።
በኋላ ላይ 4ኛውንና 9ኛውን ነጥቦች በአፈጻጸም ረገድ ሊያስቸግሩ ይችላሉ በሚል ሰርዘዋቸዋል (ቤንሶን፣ ገጽ 18፡19)።  
እነዚህ ዐርማዎች “The Most Valuable Thing: The Word at Work in Ethiopia” ከተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 63 ላይ የተወሰዱ ናቸው

የሠራዊተ ክርስቶስ ማኅበር የመጀመሪያውም ኾነ በኋላ የተሻሻለው ዐርማ የማኅበሩን ዐላማ ገላጭ እንደ ነበር መመልከት ይቻላል። ዐርማውን ብቻ እንኳ በማየት፥ የእነ ዳዊት እስቶክስ ዐላማ ኦርቶዶክስን ፕሮቴስታንት ማድረግ ሳይኾን፥ ኦርቶዶክስን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት አገልግሎቷን እንድታፋጥንና ወንጌልን ለኢትዮጵያውያን ኹሉ እንድታደርስ መርዳት እንደ ነበር መገንዘብ ይቻላል።
ዳዊት እስቶክስ ከወረራው በኋላ ከአልፍሬድ ባክስተን አመራሩን ተረክበው በማገልገል ላይ ሳሉ፥ የምስጢር አገልግሎት ክፍል ዋና ኀላፊ የኾነ አንድ ጣሊያናዊ፥ የተልእኮአቸውን እንቅስቃሴ ለመመርመር በቀረበና በጠየቃቸው ጊዜ ዳዊት እስቶክስ እንዲህ ነበር ያሉት፤ “እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል ነው እንጂ፥ ዐዲስ ቤተ ክርስቲያን ለመጀመር ዐላማ የለንም።” በዚህ ጊዜ ጣሊያናዊው ዐላማቸውን በመደገፍ ዐይነት ተደንቆ ነበር፤ በመጨረሻም ሰባኪዎቻቸውን እንደሚያምናቸውና ከዚህ በኋላ ጣልቃ እንደማይገባባቸው ለዳዊት እስቶክስ ዋስትና ሰጥቶ ነበር (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 34፡35)።

Saturday, August 15, 2015

ውግዘትና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት - ክፍል ሦስት

Read in PDF
በዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ


3.  ክህነት ያለው ሁሉ አያወግዝም!
     አውግዞ መለየት ከእግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ሥልጣን ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ የሚበልጠውና ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠው የአደራና የዘላለም ተልዕኮ ማስተማርና ለፍጥረት ሁሉ ወንጌልን ማድረስ ነው፡፡ (ማቴ.28፥19) የቤተ ክርስቲያን ትልቁ የሥራ ድርሻዋ ይህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አጽንታ ወንጌልን የምታስተምር ከሆነ ደግሞ የፊተኞቹ ቢጽ ሐሳውያን(ሐሰተኛ ወንድሞች) የኋለኞቹ መናፍቃን መነሳታቸው   የማይቀር ነው፡፡ ማውገዝ ፣ መለየት ፣ ከምዕመናን አንድነት ማሰናበት የዚህ ጊዜ መምጣቱ ግድ ነው፡፡
    ይህ ሲሆን ግን ሁሉም ወደማውገዝ ሊመጣ አልተፈቀደላትም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አላት፤ የቤተ ክርስቲያን ወገን ነኝ የሚል አካል ደግሞ ሥርዓቷን ሊያከብር ግድ ይገባዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት ከኤጲስ ቆጶስ በቀር ቄስና መነኩሴ የማውገዝ ሥልጣን የለውም፡፡ (ፍትሃ ነገስት አን.5 ቁጥር.117-124) ከዚህ በተጨማሪ አንድን ሰው መናፍቅና ከሀዲ ብሎ ለመለየት ደግሞ ከኤጲስ ቆጶስ ባሻገር ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሠርቶ ማውገዝ ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ነው፡፡

Thursday, August 13, 2015

እስመ ናሁ ኃጥኣን ወሰቁ ቀስቶሙ ...“እስመ ናሁ ኃጥኣን ወሰቁ ቀስቶሙ ወአስተዳለዉ አሕፃቲሆሙ ውስተ ምጕንጳቲሆሙ ከመ ይንድፍዎሙ ለርቱዓነ ልብ” “ኃጢአተኞች እነሆ ቀስታቸውን ገትረዋል፣ ፍላፃቸውንም በአውታር አዘጋጅተዋልና ልበ ቅኖችን በስውር ይነድፉ ዘንድ፡፡” (መዝ. 10፥2)
ባለፈው ጊዜ አባ ሰላማዎች በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በተደረገው ለውጥና እየተገኘ ባለው አዎንታዊ ውጤት ዙሪያ በሰፊው ዘግባችሁ ሊበረታቱ ስለሚገቡ ነገሮች በስፋት አስነብባችሁን ነበር፡፡ እውነትም የማይካዱ ተጨባጭ ለውጦች ጠላትም ሆነ ወዳጅ ሊክዳቸው የማይችሉ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ ለምሳሌ ከዘር ከሙስና ከአድልዎ በጸዳ መልኩ የተሰሩ በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ አባ ሰላማ ድረገጽ ጥሩና ሚዛናዊ ሚዲያ እንደመሆኑ መጠን ወደፊት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችንም ስለነሊቀ ማእምራን የማነ አንዳንድ ስጋቶችን ተንብዮ ነበር፡፡ በመሆኑም ከሰሞኑ ደስ የማያሰኝ ለቅዱስ ፓትርያርኩም ትልቅ ሐዘን የሚሆን ወሬ እየተወራ ነው፡፡ ወሬውን የሚያስወራውም ቅኖችን በስውር እንደ እባብ የሚናደፈው ባለሦስት ባህርይ የሆነው የብሔረ ጽጌው አለቃ አባ ነአኩቶ ነው፡፡ ሦስት ባህርይ የተባለው ውሸታም አመንዝራና ሌባ በመሆኑ ነው፡፡
ይህ ተኩላ በአባ እስጢፋኖስ ጊዜ በመልአከ መንክራት እና በሊቀ ትጉሃን መካከል ለነበረው አለመግባባት የተጫወተው አፍራሽ ሚና ቀላል አልነበረም፡፡ በዚህ እንደ ፈለኩ ለመሆን “የሕይወት ኢንሹራንስ” 80 ሺህ ብር ለጅማ ከፍያለሁ እያለ ሲያላግጥ ነበር፡፡ ሲቀጥል ደግሞ ወደብሄረ ጽጌ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ካዘወሩኝ አንድ ውለታ እውልሎታለሁ ይኸውም መልአከ መንክራት ሃሌ እና ሊቀ ትጉሃን ዘካርያስ በሚወጡበትና በሚገቡበት ቦታ እንዲከታተሉሎት አደርጋለሁ፤ ነገር ግን በየቀኑ ለላዳ ታክሲ እንዲከፍሉ ይሁን ብዬ የከፈልኳቸውን ብር በተዘዋዋሪ ተቀብያቸዋለሁ፡፡ በብልጠትም ብሄረ ጽጌ ገባሁ ብሎ በየመሸታ ቤቱ ይፎክርበታል፡፡ ነአኩቶ ማለት አቡሃ ለኃጢአት ማለት ነው፡፡ 

Tuesday, August 11, 2015

ታላቁ መጽሐፍ

በዲ/ን ኒቆዲሞስ
‹‹የቅዱሳት መጻሕፍት ሊቃውንት እንደተረጎሙት በአማርኛ የተገኘ እንደሆነ ቢታተምልኝ ዓይነቱን ዐይቼ በብዙ እንድትልኩልኝ ምላሽ እልክልችኋለሁ፡፡ ቀደም ሲል እንደላካችሁልኝ ያሉትን መጻሕፍት ሕዝባችን ይወዳቸዋል፤ ይልቁንም ከአማርኛና ከግዕዝ ጋር ሆነው የታተሙትን ስላለካችሁልኝም በረከት የልቤን ምስጋና ለማመልከት ሁለት የዝሆን ጥርስ ለጉባኤው ሥራ ጥቃሞት ልኬያለሁ፡፡ በመንፈሳዊ ሥራችሁ ስላሰባችሁኝ እግዚአብሔር ያኑራቸሁ፡፡›› ጳጉሜ ፪ ቀን ፲፰፻፹፬ ዓ.ም. ዐፄ ምኒልክ ለዓለም መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ከአንኮበር ከተማቸው የላኩት የምስጋና ደብዳቤ፡፡
በሰው ልጆች ታሪክ ላይ ይህን ነው ተብሎ ሊገለጽ በማይችል ትልቅ ተጽዕኖንና አሻራን ያሳረፈ፣ የዓለማችንን ፖለቲካ/ሥነ-መንግሥት ሒደት ላይ ጉልህ ድርሻ ያለው፣ በሕግና በፍልስፍና፣ በሕዋ ሳይንስና በሕክምና፣ በኪነ ጥበብና በኪነ ሕንጻ፣ በሥነ ጽሑፍና በጥበብ ሥራዎች ላይ ተጽዕኖው እጅግ የገነነ፣ የተደነቀና የተወደደ ዘመናት ያስረጀ አንድ ታላቅ መጽሐፍ አለ፡፡ ለዚህ መጽሐፍም ሲሉ በርካታዎች ከአገር ወደ አገር ተሰደዋል፣ ተግዘዋል፣ ተንከራተዋል፤ ክቡር ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገው አቅርበዋል፣ በእሳት ተቃጥለውና ተሠቃይተው ለአሠቃቂ መከራና ሞትም ተዳርገዋል፡፡

ይህ የዓለምን ታሪክና የሰው ልጆችን ሕይወት በብዙ መንገዶች የለወጠና ብዙዎችም ራሳቸውን መሥዋዕት አድርገው እስከመስጠት ድረስ በፍቅር የወደቁለት የትኛው ትንግርተኛ መጽሐፍ ይሆንን ብለን ለአፍታ ቆም ብለን ራሳችንን መጠየቃችን አይቀርም፡፡  ይህ በሰው ልጆች ታሪክ ላይ ደማቅና ጉልሕ የሆነ አሻራውን የተወው ድንቅና ተወዳጅ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡

Sunday, August 9, 2015

ሙስና የተፈጸመበት “የመሬትና የሕንጻ ኪራይ ጥናታዊ ሪፖርት” ጥያቄዎች እየተነሱበት ነውከማንኛውም ተቋም ይልቅ ሙስና የተንሰራፋው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ በሚገኙ አብዛኞቹ አድባራትና ገዳማት ውስጥ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ሆነው ከተሾሙ ወዲህ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር፡፡ በተለይም በሊቀ አእላፍ በላይ አስተዳደር ጊዜ እጅግ የነቀዘውንና አስጊ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረውን ሙስናዊ አስተዳደር ለመለወጥ የተደረገውን ጥረት በዘረኛነት ፍላጻ ክፉኛ የተነደፉት እነአባ ማቴዎስ እንዳልሰሙና ምንም እንዳልተፈጠረ ቆጥረው በቸልታ አልፈውት ነበር፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን ብሎግ ሐራም በጉዳዩ ላይ አንድም ትንፍሽ ሳትል ነው የቆየችው፡፡ የኋላ ኋላ እውነተኛ ጩኸት ሲበዛ ግን ፈቃዳቻው ባይሆንም እነሊቀ አእላፍ በላይ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጓል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ባለፉት ስምንት ወራት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስር ባሉ አድባራትና ገዳማት ያለውን ሙስናዊ ተግባር የሚያጣራ ኮሚቴ ተሰይሞ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ የማጣራት ሥራው ተሰርቷል ከተባለ በኋላ የቀረበውን ሪፖርት መሠረት በማድረግ ረጅም እጁን በየቦታው የሚዶለው ማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊዎቹ ያልሆኑትን ሙሰኞች ብቻ በመጥቀስ ትልልቅ የሙስና ወንጀል እየተፈጸመባቸው ያሉትንና የሚታወቁትን አድባራት በዝምታ እንዲታለፉ ማድረጉ ሪፖርቱ ላይ አመኔታን የሚያሳጣ ጥላ አጥልቷል፡፡

Thursday, August 6, 2015

ጸልዩ በእንተ ዝናም


 READ IN PDF
ኢትዮጵያ አገራችንን የዝናም እጥረትና ድርቅ ቢያንስ በየዐሥር ዓመቱ የሚጐበኟት አገር ከሆነች ውሎ አድሯል፡፡ በ1967 የወሎ ረኃብን፣ የ1977ቱን ድርቅ እያለ እነሆ ዘንድሮ በ2007 ደግሞ በዘንድሮው የክረምት ወራት በአብዛኛው የአገራችን ክፍል ዝናም እየዘነበ አይደለም፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ገበሬዎች ከአንድም ሁለት ጊዜ እየገለበጡ እየዘሩ ቢሆንም ዝናብ ግን የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ እንዲህ የሚሆነው ለምን ይሆን? ይህን ጥያቄ በትክክል መመለስ የሚችል አንድዬ ብቻ ነው፡፡ ሆኖም የአንድዬን ቃል ያነበበና ያስተዋለ ሰውም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው ተነሥቶና የምንገኝበትን ተጨባጭ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ መስተዋትነት ተመልክቶ ያመነበትን ምላሽ ሊሰጥ ይችላል፡፡
ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ገንብቶ ከጨረሰ በኋላ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ቆሞ ካቀረባቸው ልመናዎች አንዱ፥ አንተን ስለ በደሉ ሰማይ በተዘጋ ጊዜ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢያከብሩ፥ ባስጨነቅሃቸውም ጊዜ ከኃጢአታቸው ቢመለሱ፥ አንተ በሰማይ ስማ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ በማሳየት የባሪያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብ ስጥ።” (1ነገ. 8፥35) ከዚህ ልመናው የምንገነዘበው ዝናብ ከሚጠፋባቸው ምክንያቶች አንዱ እግዚአብሔርን መበደል እንደኾነ ነው፡፡ እንዲህ ሲባል ዝናም የሚዘንበው ሰው መልካም ስለሆነ ነው ማለት ግን አይደለም፡፡ በቃሉ ውስጥ እንደተጻፈው ጌታ ቸር ስለሆነ በክፉዎችና በበጎዎች መካከል ልዩነት ሳያደርግ ለሁሉ ፀሐይ ያወጣል ዝናብም ያዘንባል (ማቴ. 5፥44-45)፡፡ ሆኖም በበደል ምክንያት ሰማይ ዝናብ እንዳይሰጥ ሊከለከል ይችላል፡፡ 
እንደኛ ሰው የነበረው ነቢዩ ኤልያስ በአምልኮተ ጣኦት ምክንያት ለለእግዚአብሔር ስለቀና ጸልዮ ዝናብ እንዳይዘንብ አድርጎ ነበር፡፡ በኋላም ጸልዮ ዝናብ ዘንቧል፡፡ ይህም በኃጢአት ምክንያት ዝናብ እንደሚጠፋ ሌላው ማስረጃ ነው፡፡ ሰዎች ተጸጽተው የእግዚአብሔርን ስም ቢያከብሩና ከኃጢአታቸው ቢመለሱ እግዚአብሔር እንዲሰማቸው ሰሎሞን ይማጸናል፡፡ እግዚአብሔርም “በፊቴ የጸለይኸውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቻለሁ” (1ነገ. 9፥3) ሲል ምላሽ ሰጥቶታልና በበደል ምክንያት ዝናብ በተከለከለ ጊዜ በንስሐ ወደ ፈጣሪ ብንጮህ ልመናችንን ሰምቶ ዝናብን ሊሰጠን የታመነ ነው፡፡ በዚህ ወቅት እንደተጻፈው ራሳችንን አዋርደን ብንጸልይ እግዚአብሔር እንደሚሰማንና ዝናመ ምሕረቱን እንደሚያወርድልን እሙን ነው፡፡

Wednesday, August 5, 2015

“መድሎተ ጽድቅ” በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን(ክፍል 2)

ምንጭ፡- http://www.chorra.net/
READ IN PDF

ካለፈው የቀጠለ -
“ሦስቱ የተሐድሶ ስልቶች” በ“መድሎተ ጽድቅ”
ጸሓፊው በመቅድሙ ላይ የሚያነሣቸውና ምላሽ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሌሎቹ ፍሬ ነገሮች፥ ሦስቱ የተሐድሶ ስልቶች የተባሉት ናቸው። በቅድሚያ ተሐድሶ በሚለው ቃል ላይ በእርሱ በኩል የተሳሳቱ ምልከታዎች መኖራቸውንና የተዛቡ አስተያየቶች መሰጠታቸውን መግለጥ ያስፈልጋል። ተሐድሶ በዚህ ምድር ላይ ላለችው ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ የንስሓ ዕድል እንጂ ዐዲስ ሃይማኖት አይደለም፤ ወይም እርሱ እንደሚለው ኦርቶዶክስን ፕሮቴስታንት የሚያደርግ እንቅስቃሴ አይደለም። ተሐድሶ፥ እግዚአብሔር በገዛ ደሙ የዋጃት ቤተ ክርስቲያኑ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ እንድትገኝለት የሚያደርግበት የተቀደሰ አሠራሩ ነው (ሐ.ሥ. 20፥28፤ ኤፌ. 5፥25-27)። ይኹን እንጂ እርሱ ተሐድሶን እኛ ለመፍጠር እየሞከርነው ያለ ዐዲስ ሃይማኖት አድርጎ ያቀርባል (2007፣ ገጽ 33)። በተጨማሪም ራሳችንን ተሐድሶ ብለን እንደምንጠራና ቃሉ (ተሐድሶ) መጠሪያ ስማችን እንደ ኾነ አድርጎ ጽፏል (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 12)።
ተሐድሶ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚታወቅና ሲሠራበት የቈየ የተለመደ ቃል ነው። ይልቁንም የራሷን ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ መሾሟን ተከትሎ ያ ክሥተት “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መታደስ” ተብሎ ተጠርቷል። ከዚያ ወዲህ ባሉ ዓመታትም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በርካታ ተሐድሶኣዊ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፤ ውጤቶችም ታይተዋል። በየልሳኖቿም ተሐድሶን የተመለከቱ ጽሑፎች ይወጡ ነበር። በተለይ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ከኾኑ ወዲህ በርካታ ተሐድሶኣዊ እንቅስቃሴዎች እንደ ነበሩና በርካታ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ፊት የሚያራምዱ ተግባራት እንደ ተከናወኑ ይታወቃል። ይህን በሚመለከት በጮራ ቊጥር 41 ላይ ከቀረበው ጽሑፍ ውስጥ የሚከተለውን መጥቀስ ለዚህ ጽሑፍ አንባብያን ይረዳል ብለን እናምናለን። 
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ኾነው ሲሾሙ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ የተደረገው፥ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እየታየ የነበረው ተሐድሶ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ዘንድ እውን እንደሚኾን ነበር። ፓትርያርክ ኾነው በተሾሙ ጊዜ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ የተሰኘው አንጋፋ ጋዜጣ እንዲህ ብሎ ነበር፤ ‘የሌሎች አገሮች አብያተ ክርስቲያኖች እንደ ታደሱ ኹሉ የእኛም እንደ ዘመኑ መራመድ ይኖርባታል። የዐሥራ ዐምስተኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች አስተሳሰብና የኻያኛው ክፍለ ዘመን ፍልስፍና በጣም የተራራቀና የተለያየ ስለ ኾነ፥ ሊያሳምን በሚችል በዐዲስ ዘዴ መቅረቡ የተሻለ ውጤት ያስገኛል። ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ይህን ኹሉ በማመዛዘን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ፣ በአሠራር፣ በአስተሳሰብና በአፈጻጸም የታደሰችና የዘመኑን ሥርዐት የተከተለች እንደሚያደርጓት ከፍተኛ ኀላፊነት ይጠብቃቸዋል’ (1963፣ ገጽ 2)።

Monday, August 3, 2015

የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ በስሙ የሚነግደውን መ/ር ሮዳስ ታደሰን አስጠነቀቀከማኅበረ ቅዱሳን “ሊቃውንት” አንዱ የሆነውና ራሱን መጋቤ ሐዲስ በማለት የሚጠራውን መ/ር ሮዳስ ታደሰን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስጠነቀቀ፡፡ ኮሌጁ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የጻፈው ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተማሪ ባልሆነበት ሁኔታ በየመገናኛ ብዙሃኑ፣ በዓውደ ምሕረትና በሚጽፋቸው መጻሕፍት ላይ ራሱን “የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሐዲስ ኪዳን መምህር” ብሎ በመሰየም በኮሌጁ ስም እየነገደ መሆኑን ስለደረሰበት እንደሆነ ገልጿል፡፡ ኮሌጁ አክሎ እንደገለጸው ግለሰቡ ከድርጊቱ ካልተቆጠበ ጉዳዩን ወደ ሕግ እንደሚወስደው አስጠንቅቋል፡፡

መ/ር ሮዳስ የኮሌጁ መምህር ሆኖ ከዚህ ቀደም ለ2 ወራት የቆየ ሲሆን ሊባረር የቻለው በሚያስተምረው ትምህርት ምንጭ አድርጎ የሚጠቅሰው ሐመርና የማቅ ህትመቶችን መሆኑ ያበሳጫቸው የቀን ተማሪዎች አይመጥነንም ብለው ወደ ክፍል አናስገባም በማለት ስለተቃወሙት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ መ/ር ሮዳስ  ኮሌጁን “የግቢ ጉባኤ” በማስመሰል የማኅበረ ቅዱሳን የኅትመት ውጤቶችን እንደ ማስተማሪያ መጠቀሙ የማኅበሩን “ርእዮተ ዓለም” በኮሌጁ ለማስረጽ ካለው ጉጉትና ከተሰጠው ተልእኮም አንጻር ያደረገው እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡