Wednesday, August 5, 2015

“መድሎተ ጽድቅ” በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን(ክፍል 2)

ምንጭ፡- http://www.chorra.net/
READ IN PDF

ካለፈው የቀጠለ -
“ሦስቱ የተሐድሶ ስልቶች” በ“መድሎተ ጽድቅ”
ጸሓፊው በመቅድሙ ላይ የሚያነሣቸውና ምላሽ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሌሎቹ ፍሬ ነገሮች፥ ሦስቱ የተሐድሶ ስልቶች የተባሉት ናቸው። በቅድሚያ ተሐድሶ በሚለው ቃል ላይ በእርሱ በኩል የተሳሳቱ ምልከታዎች መኖራቸውንና የተዛቡ አስተያየቶች መሰጠታቸውን መግለጥ ያስፈልጋል። ተሐድሶ በዚህ ምድር ላይ ላለችው ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ የንስሓ ዕድል እንጂ ዐዲስ ሃይማኖት አይደለም፤ ወይም እርሱ እንደሚለው ኦርቶዶክስን ፕሮቴስታንት የሚያደርግ እንቅስቃሴ አይደለም። ተሐድሶ፥ እግዚአብሔር በገዛ ደሙ የዋጃት ቤተ ክርስቲያኑ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ እንድትገኝለት የሚያደርግበት የተቀደሰ አሠራሩ ነው (ሐ.ሥ. 20፥28፤ ኤፌ. 5፥25-27)። ይኹን እንጂ እርሱ ተሐድሶን እኛ ለመፍጠር እየሞከርነው ያለ ዐዲስ ሃይማኖት አድርጎ ያቀርባል (2007፣ ገጽ 33)። በተጨማሪም ራሳችንን ተሐድሶ ብለን እንደምንጠራና ቃሉ (ተሐድሶ) መጠሪያ ስማችን እንደ ኾነ አድርጎ ጽፏል (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 12)።
ተሐድሶ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚታወቅና ሲሠራበት የቈየ የተለመደ ቃል ነው። ይልቁንም የራሷን ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ መሾሟን ተከትሎ ያ ክሥተት “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መታደስ” ተብሎ ተጠርቷል። ከዚያ ወዲህ ባሉ ዓመታትም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ በርካታ ተሐድሶኣዊ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፤ ውጤቶችም ታይተዋል። በየልሳኖቿም ተሐድሶን የተመለከቱ ጽሑፎች ይወጡ ነበር። በተለይ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ከኾኑ ወዲህ በርካታ ተሐድሶኣዊ እንቅስቃሴዎች እንደ ነበሩና በርካታ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ ፊት የሚያራምዱ ተግባራት እንደ ተከናወኑ ይታወቃል። ይህን በሚመለከት በጮራ ቊጥር 41 ላይ ከቀረበው ጽሑፍ ውስጥ የሚከተለውን መጥቀስ ለዚህ ጽሑፍ አንባብያን ይረዳል ብለን እናምናለን። 
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ፓትርያርክ ኾነው ሲሾሙ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ የተደረገው፥ በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ እየታየ የነበረው ተሐድሶ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ዘንድ እውን እንደሚኾን ነበር። ፓትርያርክ ኾነው በተሾሙ ጊዜ የዛሬዪቱ ኢትዮጵያ የተሰኘው አንጋፋ ጋዜጣ እንዲህ ብሎ ነበር፤ ‘የሌሎች አገሮች አብያተ ክርስቲያኖች እንደ ታደሱ ኹሉ የእኛም እንደ ዘመኑ መራመድ ይኖርባታል። የዐሥራ ዐምስተኛው ክፍለ ዘመን ሰዎች አስተሳሰብና የኻያኛው ክፍለ ዘመን ፍልስፍና በጣም የተራራቀና የተለያየ ስለ ኾነ፥ ሊያሳምን በሚችል በዐዲስ ዘዴ መቅረቡ የተሻለ ውጤት ያስገኛል። ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ይህን ኹሉ በማመዛዘን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ፣ በአሠራር፣ በአስተሳሰብና በአፈጻጸም የታደሰችና የዘመኑን ሥርዐት የተከተለች እንደሚያደርጓት ከፍተኛ ኀላፊነት ይጠብቃቸዋል’ (1963፣ ገጽ 2)።

ካለፉት ስድስት ዐሥርት ዓመታት በላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን ኾኖ የሚያገለግለው ዜና ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ፥ ከ1960ዎቹ መጨረሻ አንሥቶ እስከ መስከረም 1982 ዓ.ም. ድረስ የተሐድሶ ዐምድ ነበረው። የዐምዱ ስያሜ በመጀመሪያ ‘ለተሐድሶ ዓምድ ለውይይት’ የሚል ነበር። በኋላ ‘ተሐድሶ ዐምድ ለውይይት’ ኾኗል። በዚህ ስያሜ እስከ ነሐሴ 1979 ዓ.ም. ድረስ ቀጥሏል። ከዚያ እስከ መስከረም 30/1982 ዓ.ም. ድረስ ‘የተሐድሶ ዐምድ ለውይይትና ለትምህርት’ ተብሎ ቀጥሎ የነበረ ሲኾን፥ ከዚያ ወዲህ ግን ዐምዱ ቀርቷል። የቀረበት ምክንያት የቤተ ክርስቲያቱ ተሐድሶ ተጠናቆ ነው በማለት ይኹን፥ ወይም ወቅቱ ከአስተዳደራዊ ተሐድሶ በላይ፥ ወሳኙ መንፈሳዊ ተሐድሶ እየመጣ የነበረበት ወቅት ስለ ኾነ፥ ያን በመፍራት ይኹን የታወቀ ነገር የለም። ከዚያ ወዲህ ግን ቀድሞ በበጎ ይታይና ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስፈላጊነቱ ታምኖበት ይሞካሽ የነበረው ተሐድሶ፥ ፀረ ተሐድሶ ዐቋም ባላቸው ወገኖች፥ መጥፎ ገጽታን እንዲላበስና እንዲጠላ ተደርጎ ብዙ ስለ ተነገረበትና በሌሎችም ምክንያቶች አንዳንዶች ዛሬም ተሐድሶ የሚለውን ስም በበጎ ጎኑ አይመለከቱትም።

በዐምዱ ላይ የሚቀርቡትን ጽሑፎች በተመለከተ ዐምዱ፥ ‘የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር የሚሻሻልበትን፣ የገቢ ምንጭዋ የሚስፋፋበትን፣ መሪዎችዋ የሚመረጡበትንና በተሐድሶ ጐዳና የምትመራበትን መንገድ በማብራራትና በማስረዳት በግለ ሰቦች የሚቀርቡ አስተያየቶች ናቸው’ ይላል። ጋዜጣው በዘመኑ የነበረውን የቤተ ክርስቲያኒቱን ተጨባጭ ኹኔታ መሠረት ያደረገ ተሐድሶኣዊ መልእክት ያስተላለፈባቸው ርእሰ አንቀጾችም አሉት። ለምሳሌ፡- የጥር 20/1971 ዓ.ም. እና የመስከረም 5/1972 ዓ.ም. ርእሰ አንቀጾች፥ [በቅደም ተከተል] ‘ተግባራዊ ተሐድሶ’ እና ‘ተሐድሶ በተግባር’ በሚሉ አርእስት ተሐድሶኣዊ መልእክቶችን አስተላልፈዋል። በተለይ የመስከረም 5/1971 ዓ.ም. ርእሰ አንቀጽ ‘የኢትዮጵያ አብዮት ከፈነዳ ወዲህ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ብዙ ጊዜ በቃህ[ል] ሲነገር ይሰማል፤ ይኹን እንጂ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ አንዳንድ የተሐድሶ ምልክቶች ሊታዩ አልቻሉም ብለን መናገር ባንደፍርም፥ ብዙ በቃል የሚነገረውን ያኽል በተግባር ተተርጕሟል ብሎ መናገር ደግሞ አዳጋች ይኾናል’ በማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ ከሚነገረው በላይ ተሐድሶን በተግባር እንድታሳይ መልእክቱን አስተላልፏል።

‘ተሐድሶ’ የሚለው ቃል ለቤተ ክርስቲያኒቱም ኾነ ለኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት እንግዳ ባለ መኾኑ፥ መጽሐፍ ቅዱሳዊነቱን ተገንዝበው ከጥንት ጀምሮ ሲጠቀሙበትና ሲሠሩበት እንደ ነበረ ይታወቃል። ቃሉን በግልጥ ከተጠቀሙ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አንዱ ናቸው። እኒህ ትጉሕና የለውጥ ሐዋርያ የነበሩት አባት፥ ለ፩ኛ ዓመት የፓትርያርክነት በዓለ ሢመት ያቋቋሟትን መጽሔት ስም ‘ሐዲስ ሕይወት’ ብለው ሰይመዋታል። ከሽፋኑ እግርጌው ላይም ‘ንሕነኒ ናንሶሱ ውስተ ሐዳስ ሕይወት’ የሚል ቃል በግእዝ ተጽፏል፤ ‘እኛ ግን በሐዲስ ሕይወት እንመላለሳለን’ ማለት ነው።
የመጽሔቱ መክፈቻ የኾነውና ‘ሐዲስ ሕይወት’ የሚለው የቅዱስነታቸው መልእክት፥ ‘የሰው ልጅ ዳግም ልደት ያገኘበት መንፈሱ፣ ኅሊናው፣ ኹለንተናው የታደሰበት፥ ኹል ጊዜ በየቀኑ የሚታደስበት የዘለዓለም ፍሥሓ መገኛ የሚኾን የእግዚአብሔር ጸጋ ከእናንተ ጋር ይኹን’ በሚል ሰላምታ ይጀምራል። ሐተታውን በመቀጠልም፥ ‘ዐዲስ፣ አሮጌ፥ ዘመናዊ፣ ጥንታዊ የሚል የተለያየ ሐሳብ በየዘመኑ የነበረ ያለም ነው። ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ሕይወት ዐዲስነት ከዚህ ጋር ግንኙነት የለውም። የማያረጅ፣ የማይለወጥ ኹል ጊዜ ዘላቂ፣ ጠባዩን እንደ ያዘ የሚኖር፥ መታደስን ለሚመኙና ለሚያስፈልጋቸው ኹሁሉ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚያዩበት መለኮታዊ መርሕ ያለበት ትምህርት ነው” ይላል።
ቅዱስነታቸው፥ ተሐድሶ ሰው ሠራሽ ፍልስፍና ሳይኾን መለኮታዊ ሐሳብ ያለበት ቃል መኾኑን ለማስገንዘብ፥ ቃሉ የተነገረባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ዋቢ አድርገው በመጥቀስ የሚከተለውን ሐሳብ አስፍረዋል። ‘ሐዲስነት ያለ ማቋረጥ ኹል ጊዜ በክርስቶስ መታደስ (ወእንተ ውስጥነሰ ይትሐደስ ኵሎ አሚረ - ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤ 2ቆሮ. 4፥16 እንደሚለው) መኾኑን ለማስገንዘብ ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመናት መካከል ያለ ማቋረጥ የሚያስተጋባ ብርቱ ድምፅ ደጋግሞ አሰምቶአል።
‘ወይእዜሰ በክርስቶስ ተሐደሰ ኵሉ ዘኮነ ወኀለፈ ዘትካት - ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢኾን ዐዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር ዐልፎአል፤ እነሆ፥ ኹሉም ዐዲስ ኾኖአል።’ (2ቆሮ. 5፥17)፤
‘ሐደሰ ለነ ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት ግብተ በመንጦላዕተ ሥጋሁ - በሥጋው መጋረጃ በኩል የሕይወትንና የጽድቅን መንገድ ፈጽሞ ዐድሶልናል’ (ዕብ. 10፥20/ የ2000 ዓ.ም. ዕትም)፤
‘እስመ ኀለፈ ዘቀዳሚ ሥርዐት ወናሁ ተሐደሱ ኵሎሙ - እነሆ፥ ኹሉን ዐዲስ አደርጋለሁ’ (ራእ. 21፥5)፤
‘ንሕነኒ ናንሶሱ ውስተ ሐዳስ ሕይወት - እንዲሁ እኛም በዐዲስ ሕይወት እንድንመላለስ …’ (ሮሜ 6፥4)፤
‘ሐድሱ መንፈሰ ልብክሙ ወልበስዎ ለሐዲስ ብእሲ ዘሐደሶ እግዚአብሔር በጽድቅ ወበርትዕ በንጽሕ - በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፥ ለእውነትም በሚኾኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን ዐዲሱን ሰው ልበሱ’ (ኤፌ. 4፥24)። በዚህ ትምህርተ ተሐድሶ፥ ጽድቅ፣ ርትዕ፣ ንጽሕ ለሰው ኹሉ የመንፈሳዊ ሕይወት ጕዞ (አቅጣጫ) መሪዎች ናቸው” (ሐዲስ ሕይወት 1964፣ 7)።
ቅዱስነታቸው ቤተ ክርስቲያንን ከልማድ ቊራኛነት በማላቀቅ፥ በትክክለኛው የወንጌል ጐዳና እንድትጓዝ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ አንዳንድ ሙከራዎችን ጀምረው ነበር። የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዋና ሥርዐተ አምልኮ መፈጸሚያ የኾነውን መጽሐፈ ቅዳሴን ከግእዝ ወደ ዐማርኛ በመተርጐምና በአገልግሎት ላይ በማዋል ሕዝቡ በሚሰማው ቋንቋ እግዚአብሔርን እንዲያመልክ ዕድል ፈጥረዋል፤ ከውጭ ቆሞ የሚያስቀድሰው ሕዝብም የአምልኮው ተካፋይ እንዲኾን ሥርዐተ ቅዳሴውን በድምፅ ማጕያ እንዲካሄድ አድርገዋል (ተኮናኙ ኮናኝ 2000፣ 35)። ‘ቀዳሾች ዐምስት ካልሞሉ ቅዳሴ ሊከናወን አይችልም’ የሚለውን ልማድም፥ ብዙ አገልጋይ በሌለበት ቦታ ምእመናን እንዳይጕላሉ ከ3 ባላነሱ አገልጋዮች  እንዲቀደስ ማሻሻያ አድርገዋል (ዝክረ ቴዎፍሎስ ሰማዕት 1989፣ 35)።  
በአጽዋማትና በበዓላት ላይም ማሻሻያ እንዲደረግ በቅዱስ ሲኖዶስ ተጠንቶ ሕዝቡ አስተያየት እንዲሰጥበት ተወስኖ የነበረ ሲኾን፥ ሲኖዶሱ የሚከበሩትን ዓመታውያን በዓላት ዝርዝር አቅርቧል። ‘ሕዝቡ ግን እንደ ልማድ አድርጎ ዛሬ በየወሩ የሚያከብራቸው በዓላት በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የተሠሩ ናቸው እንጂ፥ ሲኖዶስ ዐውቋቸው የምእመናን ግዴታ ኾነው የሚከበሩ አይደሉም’ በማለት፥ ሕዝቡ የተዘረዘሩትን በዓላት ብቻ እንዲያከብርና በሌሎቹ ግን እንዲሠራ የሚል የማሻሻያ ሐሳብ በማቅረብ ሕዝብ አስተያየቱን እንዲሰጥበት ውሳኔ አስተላልፎ ነበር (ሐዲስ ሕይወት 1967፣ 32-33)።
አጽዋማትን በተመለከተም ሰባቱ አጽዋማት ተብለው ከሚታወቁት መካከል ጌታ የጾመው ፵ ጾም፣ ረቡዕና አርብ፣ የልደት ገሃድ፣ የጥምቀት ገሃድ፣ ጾመ ነነዌ፣ ጾመ ፍልሰታ የተለመዱ መኾናቸውን ጠቅሶ፥ ሕሙማን፣ ወታደሮች፣ መንገደኞች፣ የፋብሪካ ሠራተኞች፣ ከፍተኛ ጥናት ባለው በትምህርት ላይ የሚገኙና ከባድ ሥራ የሚሠሩ ከጥሉላት (የፍስክ ምግቦች) በቀር ቊርስ እንዲበሉ ተፈቅዷል። ጾመ ነቢያት (የገና ጾም) እና ጾመ ሐዋርያት (የሠኔ ጾም) ግን ‘እንደ ዐበይት አጽዋማት ስለማይቈጠሩ የጾሙ መታሰቢያነት እንዳይረሳ ያኽል የነቢያትና የሐዋርያት ጾም ለሕዝቡ ሲባል፥ ካልጾሙ ፋሲካ ካላዘኑ ደስታ አይገኝምና ከየአጽዋማቱ መጨረሻ ዐምስት፥ ዐምስት ቀናት በመጾም የክርስቶስ ልደትና የሐዋርያት ዓመት በዓል እንዲከበር’ ሐሳብ ቀርቧል (ዝኒ ከማሁ ገጽ 33)።  ይህንኑ ተዳፍኖ የቈየውን የማሻሻያ ሐሳብ በ2000 ዓመተ ምሕረት በጠቅላይ ቤተ ክህነት የታተመውና “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም.” የተሰኘው መጽሐፍ ቈስቊሶታል (ገጽ 37፡52)።        
ቅዱስነታቸው ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎቹንም ተሐድሶ ያወጁባቸውን ልማዶችና ወጎች በሥራ ላይ እንዳያውሉ ‘መሻሻልንና ለውጥን ከማይፈልጉ ወግ አጥባቂዎች’ እና ከሌሎችም ፀረ-ቴዎፍሎስ ቡድኖች የነበረባቸው ተግዳሮት ቀላል አልነበረም (ዝክረ ቴዎፍሎስ ሰማዕት 1989፣ 35)። የእርሳቸውን ራእይ የሚደግፉ ወገኖች የቅዱስነታቸው ራእይ ቢፈጸም ኖሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ወደ ተሻለ መንፈሳዊ ደረጃ ትደርስ ነበረ ሲሉ፥ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ኾነው ድምፃቸውን እያሰሙ ነው።
በጎፋ መካነ ሕያዋን ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ‘ራእየ ቴዎፍሎስ’ በሚል ስያሜ በተዘጋጀው መጽሔት ላይ፥ ‘በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ’ በሚል ርእስ የቀረበው ጽሑፍ፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ በሕይወት ቢቈዩ ኖሮ ሊመጣ የሚችለውን ለውጥ ዘርዝሯል። ከሚጠቀሱትም መካከል፥ ‘ፓትርያርክ ቴዎፍሎስ እስከ ዛሬ ድረስ ቢኖሩ ኖሮ፥ … እምነትን ከማይጠቅም ባህል፣ ልማድና ተረት በመለየት በነበራቸው ጥበብና ድፍረት፥ የቤተ ክርስቲያቱን አንድ ወጥ የእምነት ሥርዐት እንዲዳብር ያደርጉ ነበር’ የሚለው ይገኝበታል (ራእየ ቴዎፍሎስ 2002፣ 16)። (ጮራ ቍጥር 41 የዘመን ምስክር ዐምድን ይመለከቷል)።
“ተሐድሶ” የሚለው ቃል ዛሬ እንደ ዲ/ን ያረጋል ባሉ ግለ ሰቦችና ቡድኖች ሌላ ትርጉም እንዲሰጠው ከመደረጉ በፊት፥ ቤተ ክርስቲያን ስትጠቀምበት እንደ ነበረ ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ዘመን ከቤተ ክርስቲያኒቱ የወጡ ጽሑፎች ይመሰክራሉ። አንዳንድ ጽሑፎችን አጠናቅሮ ካቀረበው (tehadeso.com) ብሎግ ላይ ከወጣው ጽሑፍ የሚከተለውን እንጠቅሳለን።
ዜና ቤተ ክርስቲያን በየካቲት 16 ቀን 1972 ዓ.ም. ዕትሙ፥ በተሐድሶ ዐምድ ሥር ‘መታደስ በመንፈስ ቅዱስ’ በሚል ርእስ የቀረበውን የቄስ ዘውዴ ደስታን ጽሑፍ አስነብቦናል። ጽሑፉም፥ ‘በመንፈስ ቅዱስ ለመታደስና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመሞላት የክርስቶስን፥ መድኀኒትነት ለመግለጽና የአማኞች ሰውነት ከልዩ ልዩ የጣዖት አምልኮት ተላቆ ፍጹም የክርስቶስ ማኅደር ኾነው በእምነታቸው ጸንተው የዲያብሎስን ሽንገላ ለመቃወም እንዲችሉ ለማድረግ በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉና የተቃኙ እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስን ሥልጣን የተቀበሉ ጳጳሳት ወይም ቀሳውስትና ዲያቆናት እንዲኖሩን ያስፈልጋል።’ የሚል ለሕይወት መታደስ የመንፈስ ቅዱስን አስፈላጊነት በአጽንዖት የሚገልጥ ነበር።
ማዕዶት የተሰኘው የቤተ ክርስቲያኒቱ መጽሔት ስያሜውን ያገኘበትን ምክንያት ሲገልጽ፥ ‘ይህ መጽሔት በዚህ ታዳጊ ዓለምና የሽግግር ወቅት ውስጥ በተሐድሶ ላይ የምትገኘውን ጥንታዊቷንና ታሪካዊቷን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዐት ታሪክና ዜና ጠቅላላ ህልውናዋንና ወቅታዊ እንቅስቃሴዋን ሁሉ የሚገልጽ ስለ ኾነ ማዕዶት ተብሎ ተሠየመ’ በማለት ነበር። (ማዕዶት ቍጥር 1 ጥር 1972)።
በ1971 ዓ.ም.  ቅዱስ ሲኖዶስ ባጸደቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ደንብ ስለ ስብከተ ወንጌል በሚናገረው በክፍል ኹለት በተራ ቍጥር 1 ላይ፥ ‘በቤተ ክህነት በኩል ያለው አስተዳደር በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመራና ተሐድሶ የሚታይበት እንዲኾን ያስፈልጋል’ ተብሎ መደንባቱን ትንሣኤ መጽሔት በቍጥር 20 የካቲት 1971 ዓ.ም. ዕትሙ በገጽ 14 ላይ አስነብቧል።
ታላቁ ሊቅ አለቃ ነቢየ ልዑል ዮሐንስ፥ ‘የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ተሐድሶ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ’ በሚል ርእስ ትንሣኤ መጽሔት ላይ ካቀረቡት ጽሑፍ የሚከተለውን እንመልከት። “እስካሁን ድረስ ቤተ ክርስቲያኗ መሻሻልና መለወጥ እምነትን የሚነካ እየመሰላት እንደ ኲሬ ውሃ በአንድ ቦታ ቆማ በአብርሃና አጽብሐ ዘመነ መንግሥትና በአቡነ ሰላማ መጀመሪያ በተመሠረተው አመራር ከመሄድ በቀር በውስጧ የሚተዳደሩት ሊቃውንትና ምእመናን እነርሱ ተሻሽለው ሌላውም እንዲሻሻል ሳታደርግ ባለህበት እርገጥ በሚለው ባልኾነ ፈሊጥ እየተመራች እስካለንበት ቈይታለች። ስለዚህ ሃይማኖትን ከሚመለከቱ ነገሮች በቀር ጊዜውን ተከትሎ መሻሻልና ለውጥ እንደሚያስፈልግ ተሐድሶንም ከኦሬንታል አብያተ ክርስቲያናት መረዳት ያስፈልጋል። … እንግዲህ ብዙ ታሪኮችን አይተናል፤ ያለፈው ዐልፏል፤ ማሰብ ወደ ፊት ለሚመጣው ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሐድሶ አመራር እንቅስቃሴ ለዚህ ዐይነት አሠራር መነሻ ምክንያት እንደሚኾን የብዙዎቻችን እምነት ነው  (ትንሣኤ የመስከረምና ጥቅምት ወራት 1984 ዓ.ም. ቍጥር 150፤ ገጽ 10-11)።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዐምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ኾነው በተመረጡ ጊዜም የቤተ ክርስቲያኒቱ ተስፋ፥ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የተጣለውን የተሐድሶ መሠረት እንደ ገና ለመጣል መኾኑን እንዲህ ሲል መስክሯል፤ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሠኔ 28 ቀን 1984 ዓ.ም. ባደረገችው ፓትርያርካዊ ምርጫ ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ 5ኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ኾነው በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በካህናትና በምእመናን ከፍተኛ ድምፅ ተመርጠዋል። ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጳውሎስ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የተሐድሶ መሠረት በጣሉበት ወቅት የመጀመሪያው ተመራጭ አባትና የተሐድሶውን መሠረት የመጣሉን ተግባር ከቅዱስነታቸው ጋር ዐብረው ያከናወኑ ሐዋርያ ስለ ነበሩ፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ የተሐድሶ ተግባርን በብፁዕነታቸው ዘመነ ሢመት እንደሚቀጥል ስለ ተገመተ የምርጫው ዜና በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን ያስተጋባውን ልባዊ የደስታ ስሜት ለመግለጽ ተመራጭ ቃል አይገኝም። …
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የተሐድሶ መሠረት እንደ ገና ለመጣል ‘ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር’ በተባለው መሠረት ዘወትር ለጸሎት የተዘረጉት የመላ ኢትዮጵያውያን የክርስትና እጆች አላፈሩም። ልዑል እግዚአብሔር ቀድሞ በትሩፋታቸው የሚያውቃቸውንና በተጋድሎአቸውም ወቅት ለአንድ አፍታም ያልተለያቸውን ዶ/ር ብፁዕ አቡነ ጳውሎስን ከስደት ጠርቷል። …
ስለዚህ ‘ፀሓይ ሳለ እሩጥ አባት ሳለ አጊጥ’ እንዲሉ … ራስን በንስሓ አስተካክሎ ለትምህርተ ወንጌል ታጥቆ መነሣትና ለቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ መዘጋጀት የብፁዓን አባቶች የመላው ካህናትና ምእመናን ወቅታዊ ግዴታ ነው (፭ኛው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ልዩ ዕትም 1984 ገጽ 3-4)።
ስድስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለ2005 ዓ.ም. የትንሣኤ በዓል ባሰሙት ቃለ ምዕዳን በክርስቶስ የአድኅኖት ሥራ የተመሠረተና በሕይወት መታደስ ላይ ያተኰረ ግልጥ መልእክት አስተላልፈው ነበር። እንዲህ በማለት ‘ያረጀው  ነገር  ሁሉ በክርስቶስ ደም ተቀድሶና ነጽቶ ሐዲስ ኾኗል፤ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሠርቶ የሚያሠራ የመልካም ነገር ኹሉ አርኣያና መሪ እንደ መኾኑ መጠን ዐዲሱን መንገድ ከፍቶ እንድንጓዝ ሲያደርግ እኛም በሐዲስ ሕይወት ልንመላለስበት እንጂ እንደ ገና የሚያሠራ የመልካም ነገር ኹሉ አርኣያና መሪ እንደ መኾኑ መጠን፥ ዐዲሱን መንገድ ከፍቶ እንድንጓዝ ሲያደርግ እኛም በሐዲስ መንፈስ በሐዲስ ሕይወት ልንመላለስበት እንጂ እንደ ገና ወደ አረጀውና ወደ አፈጀው ሕይወት ተመልሰን ልንዘፈቅ አይደለም። ዐዲስ ሕይወት ማለት እግዚአብሔር ለሰው ዘር ኹሉ መድኀኒት እንዲኾን በላከው በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዘለዓለም ድኅነትን ማግኘት ነው፤ ምንም ዐይነት አማራጭ የማይገኝለትን ይህን የእግዚአብሔር የማዳን ጸጋ የሰው ዘር ኹሉ ተቀዳሚ ሥራው አድርጎ ሊቀበለው ይገባል፤ በዚህ በኩል ካልኾነ ሌላ የምንድንበት መንገድ የምናመልጥበት ዐውድ ፈጽሞ የለምና። …’ (eotcssd.org)
እነዚህ በቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳኖች ከተገለጡ የአበው ምስክርነቶች አንጻር፥ ተሐድሶ ዐዲስ ሃይማኖት ሳይኾን ቤተ ክርስቲያን ከምትገኝበት የተሳሳተ ትምህርት፥ ሥርዐትና አካሄድ ተመልሳ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ወደ ተመሠረተውና እግዚአብሔር ወዳየላት ግብ የምትጓዝበት መንገድ ነው። እኛ ተሐድሶ ስንል እንዲህ ማለታችን ነው እንጂ፥ እርሱ እንደሚለው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ወደ ፕሮቴስታንት የሚቀይር ዐዲስ ሃይማኖት ወይም ስልት አይደለም። ይህን እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ ጥቅም ያስነሣውን እንቅስቃሴ ሌላ መልክ ሰጥቶ ማቅረብም ኾነ ቤተ ክርስቲያን በዚህ አቅጣጫ ተሐድሶ አያስፈልጋትም ማለት ትልቅ ስሕተት ነው፤ የእግዚአብሔርንም ሐሳብ መቃወም ይኾናል።
በ “መድሎተ ጽድቅ” እኛ ራሳችንን ተሐድሶ ብለን እንደምንጠራ ተደርጎ የተጻፈውም ስሕተት ነው። ከላይ ደጋግመን ለመግለጥ እንደ ሞከርነው ተሐድሶ እግዚአብሔር ያስነሣው እንቅስቃሴ እንጂ ዐዲስ ሃይማኖት ባለ መኾኑ ስሙ በድርጊቱ ላይ የሚያርፍ ነው። ይኹን እንጂ ብዙዎች በእንቅስቃሴው ውስጥ ያሉትን ሰዎች እንዲወክል በማድረግ የእነርሱም መጠሪያ ኾኖ እንዲያገለግል እየተጠቀሙበት ይገኛል። ከዚህ የተነሣ እገሌ ተሐድሶ ነው መባል እየተለመደ መጥቷል። በእንቅስቃሴው ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎችም ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው ወደ መጥራት ተሸጋግረዋል። ይህም ተሐድሶ ከእንቅስቃሴነቱ ውጪ ዐዲስ ሃይማኖት ኾኖ እንዲታይ የረዳ ይመስላል። ስለዚህ ጸሓፊው ተሐድሶን በእንቅስቃሴነቱ ሳይኾን በዐዲስ ሃይማኖትነት እንዲታይ ነውና የሚፈልገው፥ በእንቅስቃሴው ውስጥ ያሉትን ሰዎችም ተሐድሶዎች እያለ ነው የሚጠራው፤ እውነታው ግን ይህ አይደለም። 
በአጠቃላይ ተሐድሶን በዚህ መልኩ ሳይኾን እርሱ በሚፈልገው በሌላ መንገድ የተረዳውና ለማስረዳትም የሚሞክረው ጸሓፊው የተሐድሶ ዋና ዋና ስልቶች ሦስት ናቸው በማለት የሚከተሉትን ጠቅሷል። ስልቶች ብሎ ለጠቀሳቸው ለእያንዳንዱ ምላሽ እንሰጣለን።  
“1) አንደኛው ስልት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና አስተምህሮ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊውና ከቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ትምህርት የተለየና የራቀ አስመስሎ ለማሳየት መሞከር ነው። ይህም የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን አስተምህሮንና እምነቷን፥ ምስጢራቷንና ሥርዐቷን፥ ይትበሃሏንና ትውፊቷን በአጠቃላይ ኹለንተናዊ ሕይወቷን በሙሉ ከጥንቱ ከጌታችንና ከሐዋርያት እንዲሁም ከሊቃውንት ትምህርት የራቀና የሚቃረን አስመስሎ ማሳየት ነው። ይህም ለቤተ ክርስቲያኒቱ መልኳ ያልኾነውን ሌላ መልክ በመስጠት ሰዎች ከልቡናቸው ውስጥ እንዲያወጧትና እንዲጠሏት ለማድረግ ይረዳናል በሚል ነው። ለዚህ ዐላማቸውም ቤተ ክርስቲያኒቷ የምታምነውን እንደማታምን፥ የማታምነውን ደግሞ እንደምታምን፥ የምትለውን እንደማትል፥ የማትለውን ደግሞ እንደምትል እያስመሰሉ ያለ ይሉኝታና ያለ ኀፍረት ጽፈዋል።” (2007፣ ገጽ 12)።
የተሐድሶ ስልት ተብሎ በመጀመሪያ የተጠቀሰው ይህ ነጥብ በራስ መንገድ የተቃኘ እንጂ የእኛ አመለካከትና አሠራር እንዳልኾነ በቅድሚያ መግለጥ እንወዳለን። እኛ፥ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና አስተምህሮ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊውና ከቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ትምህርት የተለየና የራቀ” አስመስለን አላቀረብንም። ቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙ ምእት ዓመታትን ያሳለፈች እንደ መኾኗ፥ ስትመሠረት የነበራትና አኹን የሚታየው አስተምህሮዋ፥ እምነቷ፥ ምስጢራቷ፥ ሥርዐቷና የመሳሰሉት ኹሉ በተለያዩ ምክንያቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተንሸራተዋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ገጽታዋ የደበዘዘና ሌላ ገጽታን የተላበሰ ኾኖ ይታያል። በሊቃውንቱ ዘንድ የሚገለጠውና በሕዝቡ ዘንድ የሚታመነውም ለየቅል ነው። ቤተ ክርስቲያን በዚህ ኹኔታ ስትገኝ ተሐድሶ ልታደርግ፥ ወደ ቀደመው እውነተኛ መሠረቷ ልትመለስና የተመሠረተችበትን እውነት ጠብቃ ልትጓዝ ይገባታል ነው የምንለው።
እንዲህ ማለት እውነታውን መግለጥ ነው እንጂ የሌላትን መልክ ለቤተ ክርስቲያን መስጠት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በዚህ መንገድ ኹኔታውን መግለጥም ዐላማው ቤተ ክርስቲያኒቱ እንድትጠላ ማድረግ ሳይኾን፥ ተሐድሶ ማድረግ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስፈላጊ መኾኑን መጠቈም ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከጌታ ፈቃድና ሐሳብ ውጪ በመመላለስ በልዩ ልዩ የትምህርትም የሕይወትም ስሕተትና ችግር ውስጥ የተገኙትን አብያተ ክርስቲያናት፥ ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፋቸው መልእክታት ስሕተታቸውን አሳይቷቸዋል፤ ንስሓ እንዲገቡም አሳስቧቸዋል፤ በዚህ ረገድ የቆሮንቶስን፥ የገላትያን እንዲሁም የዕብራውያንን መልእክታት መጥቀስ ይቻላል። ጌታ በእስያ ለሚገኙት ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያን የላከው መልእክትም ተመሳሳይ ይዘት ያለው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም ኾነ ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ መልእክቱን ያስተላለፉት አብያተ ክርስቲያናቱ በንስሓ እንዲታደሱና ወደ መጽሐፍ ቅዱሳዊው መሠረት እንዲመለሱ እንጂ፥ አብያተ ክርስቲያናቱን ከሰዎች ልብ ለማስወጣትና ለማስጠላት አይደለም። እኛም ከዚህ የተለየ አላደረግንም።
በመጨረሻ ላይ የተባለውና፥ “ለዚህ ዐላማቸውም ቤተ ክርስቲያኒቷ የምታምነውን እንደማታምን፥ የማታምነውን ደግሞ እንደምታምን፥ የምትለውን እንደማትል፥ የማትለውን ደግሞ እንደምትል እያስመሰሉ ያለ ይሉኝታና ያለ ኀፍረት ጽፈዋል።” የሚለው ግን ለአንባቢ ፍርድ ቢተው የተሻለ ነው። ጽሑፎቻችን የሚታየውን እውነታ በግልጥ የሚያሳዩና በማስረጃ የተደገፉ ስለ ኾኑ ጕዳዩን ካለው ተጨባጭ ኹኔታ ጋር ማገናዘብና የኅሊና ፍርድ መስጠት እንጂ፥ ገልብጦ ማውራት እውነተኛ አያሰኝም። እኛ ቤተ ክርስቲያን የምትለውን እውነት ገልጠን እንደምንመሰክር፥ ጕድለቷ የኾነውን ጕዳይም በማሳየት ተሐድሶ ታደርግ ዘንድ እንደምናሳስብ ጽሑፎቻችን ይመሰክራሉ፤ ከዚህ ውጪ እርሱ እንደሚለው አላደረግንም። ለመኾኑ ቤተ ክርስቲያን የማታምነውን ታምናለች፥ የምታምነውን አታምንም፤ የምትለውን አትልም፥ የማትለውን ደግሞ ትላለች እንዴት ይባላል? ለምንስ ይባላል? እንዲህ የሚባለውስ ከቶ ምን ለማትረፍ ይኾን? በዚህ መንገድ እግዚአብሔርን ማገልገልስ እንዴት ይቻላል? በእውነቱ ይህ በያረጋል ልብ ውስጥ እንጂ በእኛ ዘንድ የሌለ ሐሳብ ነው። ለኹሉም ለዚህ አመለካከቱ ያረጋል ከጽሑፎቻችን ጠቅሶ ያቀረበውን ትችት ከስፍራው ስንደርስ እንመለከተዋለን።     
“2) በመቀጠልም እንዲህ ባለ ኹኔታ ለቅድስትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ሌላ መልክና ስም ለመፍጠር ከሞከሩ በኋላ ራሳቸውን የእውነተኛው የሐዋርያትና የሊቃውንት ትምህርት አማኞችና ጠበቆች አድርገው ለማቅረብ ሞክረዋል። ፕሮቴስታንቲዝምን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ከአውሮፓ ከመጡት ሚስዮናውያን እግር ሥር ቁጭ ብሎ ፕሮቴስታንታዊነትን የቀጸለው መሠረት ስብሐት ለአብ የተባለው ግለ ሰብ በ1951 ዓ.ም. ‘ስምዐ ጽድቅ ብሔራዊ’ ብሎ በጻፈው መጽሐፉ ላይ ይህን ስልትና ዐላማውንም በፈሊጥ ለዘብ አድርጎ ለማሳየት ሞክሯል። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ፕሮቴስታንት ለማድረግ በስልት ይሠሩ የነበሩት ሚስዮናውያን የእነ ዳቪድ ስቶክስ ደቀ መዝሙር የነበረው መሠረት በጻፈው መጽሐፉ ላይ እንዲህ ብሏል፡-
ሊብራሩ ሲገባቸው በዘመን ብዛትና በአገር ላይ በሚኾን ተለዋዋጭ ኹናቴ፥ በመንፈሳዊ ዕውቀት ማነስ፥ በመናፍቃን ስሕተቶች ምክንያት የተቀበሩና የተሸፈኑ ጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን መምህራን ዋና ዐላማ አድርገው ሲሠሩባቸውና ሲያስተምሩባቸው የኖሩ ብዙ ነገሮች እንዳሉ የአኹኖቹ ደጋጎች መምህራን ኹሉ የሚያውቁት ነው። (2007፣ ገጽ 12-13)።
ጸሓፊውን ጨምሮ ኹሉም ራሱን የእውነተኛው የሐዋርያትና የሊቃውንት ትምህርት አማኝና ጠበቃ አድርጎ ያቀርባል። መኾን አለ መኾኑ የሚታወቀው ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝኖ ነው እንጂ በሌላ አይደለም። አለቃ መሠረት የወንጌልን እውነት የተረዱት ከዳዊት እስቶክስ ጋር ከመገናኘታቸው አስቀድሞ ከኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ጋር ባሳለፉባቸው ጊዜያት በተፈጠሩላቸው አጋጣሚዎች መኾኑን ራሳቸው የሰጡት ምስክርነት ያስረዳል (ጮራ ቍጥር 14፣ ገጽ 8-9)። በዚህ አቅጣጫ በሕይወታቸው ለተገኘው ተሐድሶ አስተዋፅኦ ካበረከቱት ሊቃውንት መካከል፥ የመርሐ ቤቴ ተወላጅ የነበሩት አለቃ በየነ ዳምጤ የመጀመሪያው ናቸው። በ1935 ዓ.ም. ወደ አክሱም ሄደው በዚያ ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ የቈዩት አለቃ በየነ፥ በቅዱሳት መጻሕፍት ዕውቀት የበረቱና “በዚያን ጊዜ ከንባቡ በስተቀር ቃሉ በሕይወት ተተርጕሞ የማያውቅ ወንጌልን በግልጽ ይሰብኩ” የነበሩ ሊቅ ናቸው። ቅኔና ዜማም ዐዋቂ ነበሩ።
በተጨማሪ አለቃ መሠረት ደብረ መንኰል በተባለ ስፍራ የቅኔ ትምህርታቸውን ለማስፋፋት እዚያ ከታላቁና ስመ ጥር ከኾኑት የቅኔ መምህር ከየኔታ ዐወቀ ዘወቄጣ ዘንድ ሲማሩ፥ ከእርሳቸው በሰሟቸው የቅዱሳት መጻሕፍት ምስጢራት ምርቱን ከግርዱ፥ ፍሬውን ከገለባው መለየት መቻላቸውን እንዲህ ሲሉ ነበር የገለጡት፥ “ከአለቃ በየነ የሰማሁትንና እየተገነባሁበት የመጣውን ምርምሬን የሚያጐለብት ኾነልኝ። በእውነቱ የኔታ ዐወቀ በቅኔው የሚደነቁበትን ዕውቀት ያኽል ቅዱሳት መጻሕፍትን የመመርመርና የመረዳት ችሎታቸው ፍጹም ሳይኾን እንዳልቀረ ዐወቅሁና ታዝቤ ዐለፍሁ።” (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 9)።
የክርስቶስን የማዳን ሥራ የተረዱትና ሕይወታቸው የተለወጠበት አጋጣሚ የተፈጠረውም፥ በዚያው በቅኔ ቤት ሳሉ ይጠይቋቸው ለነበሩ ተማሪዎች እውነቱን ገልጠው በሚያስረዱበት ጊዜ ነው። ይኸውም ገላትያ ምዕራፍ 2 ከቍጥር 1-21 ያለውን በማንበብ እያስረዷቸው ሳለ፥ ለተማሪዎች ማስረዳታቸውን ረስተው ቍጥር 21 ላይ የተጻፈውን፥ “ጽድቅስ በኦሪት ከኾነ እንኪያስ ክርስቶስ በከንቱ ሞተ” የሚለውን ንባብ ለራሳቸው ደጋግመው በማንበብ፥ “ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ነው ከኀጢአቴ ያዳነኝ፤ ጌታ ኢየሱስ ያላዳነኝ ኖሮ ቢኾን ሞቱ ከንቱ ነው በተባለ ነበር” እያሉ በተመስጦ በማሰላሰል ላይ ሳሉ ነው። ከዚያ፥ “በውስጤ የሚፈስ ቀዝቃዛ ነገር ይሰማኝ ነበር፤ ዐዲስ ደስታ፥ ሰላም ዕረፍትና ርካታንም ይሞላብኝ ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በጌታዬ ሞትና ትንሣኤ የተገኘውን መዳን፥ መጽደቅ፥ የእግዚአብሔር ልጅነት፥ የዘላለም ሕይወት ባለ መብትነት የሚያረጋግጡት፥ ቀደም ሲል በውስጤ የነበሩት ጥቅሶች ኹሉ ተከታትለው መጡ። እግዚአብሔር በቃሉና በመንፈሱ ሕይወቴን የቀመመበት ለራሱም ለሰውም ጣዕምና ቃና ያለውን ኑሮ እንድጀምር ያደረገበት ልዩ ወቅት ይህ ነበር።” ሲሉ የሕይወት ተሐድሶ ያገኙበትን ኹኔታ መስክረዋል (ዝኒ ከማሁ፣ ገጽ 10)።
አለቃ መሠረት በጊዜው ሌሎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች እንደ ተማሩት ኹሉ ከዳዊት እስቶክስ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወንጌልን ለመስበክ የሚረዱትን ተጨማሪ ኮርሶችን ወሰዱ እንጂ፥ ያረጋል እንደሚለው ፕሮቴስታንቲዝምን አልቀጸሉም። መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መሠረት መረዳትና ወንጌልን መስበክ ፕሮቴስታንቲዝም ነው ከተባለ ግን እርሱ ሌላ ጕዳይ ነው። እርሳቸው ፕሮቴስታንቲዝምን እንዳልተከተሉና እንዳላቀነቀኑ ግን ከማንም በላይ ምስክሮቻቸው ከፍ ብለን የጠቃቀስናቸው የጽሑፍ ሥራዎቻቸውና ከሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ሴሚነሪ ካስወጧቸው በኋላ፥ በመካነ ኢየሱስ ሴሚናሪየም ባሳለፉአቸው ዓመታት ያስተምሩ የነበረው ትምህርት ምንነት ነው። ስለዚህ አለቃ መሠረት ኦርቶዶክሳዊውን ትምህርትና ሥርዐት በመጽሐፍ ቅዱስ መነጽር በመመልከት መጽሐፍ ቅዱሳዊነቱ እንዲታወቅና እንዲጠበቅ፥ ፍሬው ከገለባው እንዲለይ ነው ያደረጉት እንጂ ፕሮቴስታንቲዝምን አላቀነቀኑም።
ይቀጥላል


ዋቢ ጽሑፎች
ሃይማኖተ አበው (1986) ዐዲስ አበባ፣ ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት።
መሠረት ስብሐት ለአብ (1951) ስምዓ ጽድቅ ብሔራዊ። ዐዲስ አበባ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት።
                 (1988) ሥላሴ በተዋሕዶ። ዐዲስ አበባ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት።
ማኅበረ ቅዱሳን (2003) የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ፡፡ አዲስ አበባ፣ ማተሚያ ቤቱ ያተገለጸ፡፡
ማንሰል፣ ኮ. (2003) ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ። ዐዲስ አበባ፣ ንግድ ማተሚያ ድርጅት።
ምስክረ ብርሃን (ነሐሴ) 1964። 
                 (ጥቅምት) 1964።
ስምዐ ጽድቅ (መጋቢት) 1995 ዓ.ም.።
ቃሉ ይናገር (ቍጥር 1፣ 2፣ 3፣ 4) (1999) ወሩ እና ቀኑ ያልተጠቀሰ።
በመስቀሉ ገነትን ከፈተ (2003) መስከረም 16።
ተግሣጽ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ። (1987) ዐዲስ አበባ፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ማተሚያ ቤት። ትንሣኤ (ሐምሌ) 1972።
ክርስቶስ ዘሀሎ ወይሄሉ (1999) ሚያዝያ (ቀኑ ያልተጠቀሰ)።
ዜና ቤተ ክርስቲያን (1996) መጋቢትና ሚያዝያ (ቀኑ ያልተጠቀሰ)።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም.። (2000)፣ አዲስ አበባ፣ ሜጋ ማተሚያ ኀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር።
ያሬድ ካሳ (ሊቀ ሊቃውንት) (1993) ሕያው ስም። (ማተሚያ ቤቱና ቦታው ያልተጠቀሰ)።
ያሬድ ፈንታ (አለቃ)(2005) ባሕረ ሐሳብ፥ የቀመርና የሥነ ፈለክ ምስጢር። ዐዲስ አበባ፣ ፋር ኢስት ትሬዲንግ ኃላ. የተ. የግ. ማኅበር። 
ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ (ነጋድራስ) (2002) ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ሥራዎች። ዐዲስ አበባ፣ አአዩ ማተሚያ ቤት።
ጌታቸው ኀይሌ (ጌታቸው ኀይሌ)፥ “ባሕረ ሐሳብ፥ የዘመን ቈጠራ ቅርሳችን ከታሪክ ማስታወሻ ጋራ”
ግርማዊ ቀዳማዊ ዐፄ ኀይለ ሥላሴና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን (1993) ጥቅምት፡፡
ጮራ (አልቦ ወርኅ ወዓመተ ምሕረት)።
ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር) (1991) የሥነ ቃል መምሪያ። ዐዲስ አበባ፣ ቦሌ ማተሚያ ድርጅት።
Benson, Doris. The Most Valuable Thing: The Word at work in Ethiopia. n.d.
www.abaselama.org. 18 September 2012. Article. 14 May 2015.
www. eotcssd.org. 7 May 2013. Massage. 12 May 2015.

www.tehadeso.com. 12 January 2012. Article. 14 may 2015.11 comments:

 1. "አለቃ መሠረት በጊዜው ሌሎቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች እንደ ተማሩት ኹሉ ከዳዊት እስቶክስ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወንጌልን ለመስበክ የሚረዱትን ተጨማሪ ኮርሶችን ወሰዱ እንጂ፥ ያረጋል እንደሚለው ፕሮቴስታንቲዝምን አልቀጸሉ"
  አና ዳዊት አስቶክስ ማሪያም ቅዱሳን መላዕክት እና ጻድቃን ያማልዳሉ እያለ ነበር እነ መሰረትን ያስተማረው??ቢያንስ ሰውን ማታለል ስትሞክር ብልጥ ሁን!! የተሻለ መከራከሪያ አቅርብ!!ምን አይነት ጭንቅላት ነው ያለህ በመድሃኔአለም

  ReplyDelete
 2. ውሸታሞች ናችሁ በሂሁ ድረገጻችሁ ስንት ለጆሮ የሚቀፍ ና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ትምህርት ስትጽፉ ቆይታችሁ አሁን ይህ የቤተ ክርስቲያን ጠበቃ የሆነው ዲ/ን ያረጋል ጉዳችሁን ሲያወጣባችሁ እኛ፥ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነትና አስተምህሮ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊውና ከቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ትምህርት የተለየና የራቀ” አስመስለን አላቀረብንም። ትላላችሁ እስቲ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት የምትቀበሉ ከሆነ ስለ እምቤታችን ጾም(ወቅቱ ስለሆነ) አስተምሩ

  ReplyDelete
 3. ዜሮ(ባዶ)
  መካድና ማስካድ፣ መዋሸትና ማስዋሸት፣ ማመጽና ማሳመጽ፣ ሳይሆኑ ነኝ ማለትና ማስመሰል በአጠቃላይ ከመልካም ነገር ይልቅ ክፋትንና ጠማማነትና ማካሔድና ማሰራት ከማያምኑ፣ የክርስቶስን ወንጌል ከሚያጣምሙ፣ የክርስቶስ ቤተክርስቲያንን ከሚቃረኑና ሳይሆኑ ተመሳስለው በጎችን ከሚነጥቁ ተኩላዎች ዘንድ በእምነትነትና በአላማ የተያዙ አጀንዳዎች ናቸው። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ መናፍቅ የሆኑት ናቸው። በአሁኑ ጊዜ ከመናፍቃን አስተሳሰብ የተቀላቀሉት ተሐድሶ ነን ባዮች ናቸው። ከስማቸው መለየት በስተቀር አሥተሳሰባቸው ከቀደሙት መናፍቃን ቢብስ እንጅ የተለየ አይደለም። በዚህ ክፍል ሁለት ባሉት ተረት ተረት ጽሑፋቸው እኛ ተሐድሶ ነን አላልንም አዲስ ሀይማኖትም ይሁን ፕሮቴስታንዚምን ለመመሥረት አልተነሳንም በማለት ዋሽተዋል ። ይህን ያሉበት ምክንያትም ዲያቆን ያረጋል የስሕተት ትምህርታቸውን በመጽሐፍ ቅዱስና በአባቶች አስተምሮ እየመዘነ ስላጋለጠባቸው እንክርዳድ ትምህርታቸውንና አስተሳሰባቸውን ማዳን ሥላልቻሉ በደፈናው አላልንም በሚል ውሸት ተጠምደዋል። እነዚህ ተሐድሶ ነን ባዮች በአባታቸው በዲያቢሎስ አዚም ተደርጎባቸው ለእውነት እንዳይገዙና ለመዳን እንዳይወዱ ሆነዋል። ሥለዚህም ከዜር አንድ ለመሻገር እንሿን የማይሹ ጨምረው የሚክዱና የሚዋሹ ባዶዎች ሆነው ቀጥለዋል።
  ክፍል አንድ በማለትና ምንጭ ጮራ ብለው በገለጡት ጽሑፍ ተብያቸው የዲያቆን ያረጋልን መጽሐፍ በተመለከተ በሚል በዚህ ድህረገፅ ለጥፈው ነበር። በዚያም የዲያቆን ያረጋል መጽሐፍ የሚናገረው ሌላ እነሱ የተረተረቱ ተረት ሌላ ነበር። በዛም አሳዳሪዎቻቸውና የእውነት ወንጌል ያልገባቸውን ነገር ግን ቃላት እየመዘዙ በከንቱ የሚመፃደቁትን ማከም አለመቻላቸውን ያ ክፍል አንዱ ተረታቸው ይናገራል። ለዚህም ይመሥላል ምንጭ ጮራ ማለትን አሥቀርተው በዚህ ክፍል ሁለት የማስመሰል መደለያና የቃላት ጨዋታ ይዘው የለጠፉት። ሆኖም ይህም ውሸትን ከመደረት፣ ከመካድና ቃሉ የተነገረበትን መንፈሳዊ መልእክት ያለመረዳትን ድክመታቸውን ከማንፀባረቃቸው ውጭ ሌላ ትርፍ የላቸውም።
  ተሐድሶ የሚለውን ቃል ለእባባዊ ተግባራቸው መከላከያና መሸፈኛ ለመጠቀም ብዙ ሲዳክሩና ሲዘባርቁ በዚህ ክፍል ሁለት ጽሑፋቸው ይታያሉ። ብዙ ምዕራፍና ቁጥሮችን በመደርደርም ተሐድሶን በመጽሐፍ ቅዱስ ያለ ቃል ነው በማለት የእነሱን እንክዳድ የክህደት ትምህርት ለመከላከልና ለመሸፈን ሞክረዋል። አዲስ ህይወት፣ ታደሱ፣ አድሶናልና የመሳሰሉትን ቃላትን እምነትን ማደስ(አዲስ ሀይማኖት መመሥረት) ማለት ናቸው ለማለት በተዘዋዋሪ ሞክረዋል። ነገር ግን እምነት( ሀይማኖት) ለክርስቲያኖች ፈፅሞ አንዴ የተሰጠች የማትታደስ ፍፅምትና ሁሌም የማታረጅ አዲስ ናት። ቃላቶቹ ግን በአጭሮ ክርስቶስ ከቀደመው አዳማዊ ህይወታችን ሥለኛ እራሱን ለመሥቀል ሞት በመሥጠት ነፃ አውጥቶ በሐጢያት የቆሸሽነውን አዲስ እንዳደረገን የሚገልፅና ሐጢያትን በመተው በንስሃ እንድንታደስ የሚገልፁ ናቸው።
  ሌላው ተሐድሶን ቤተክርስቲያን እንደምትጠቀምበት መናገርንም አብዝተዋል። ለዚህም በቤተክርስቲያኗ ተፃፉ ከሚሉት ጀምሮ ሶስት የቤተክርስቲያን አባቶች ተሐድሶ የሚለውን ቃል ተናግረውታል በማለት በአስረጅነትና በምሳሌነት ጠቃቅሰዋል። በዚህም የእነሱን የተደበቀ ሴራና የውሸት ትምህርታቸውን ለመከላከልና እየተናገርነው ያለው ትክክል ነው ለማለት በድብስብስም ቢሆን ከጅለዋል። ሲጀመር አንድን ቃል ተነገረ በብሎ እኛ ከምንሔድበት ጋር አንድ ናቸው ማለት ጅልነትና ሥተታቸውን ለመሸፋፈን መሞከር አውሬነትና ባዶነት ነው። በጽሑፍም ይሁን በንግግር አንድ ቃል ሲገለጥ የጽሑፉም ሆነ የንግግሩ መነሻ ነጥብን ተመርኩዞ ነው የቃሉ ትርጉም የሚታወቀው። ዝም ብሎ አን ቃል በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ተጠቀሰ ተብሎ እኔ ከማራምደው ጋ አንድ ነው ተብሎ ነጋሪት መጎሰም ያስተዛዝብና ያሳዝን እንደሆን እንጂ ማንንም አይሸነግልም። ቤተክርስቲያን ተሐድሶ የሚለውን ስትጠቀም ሀይማኖትን ከመለወጥና አዲስ አሥተምሮን ከመፍጠር አንፃር ሳይሆን ከንስሃና ከአሥተዳደራዊ ገጉዳዮችና ከልማታዊ እንቅስቃሴዎች አንፃር ነው። በተጨማሪም ተሐድሶ የሚል ቃልን ተጠቅመዋል ብላችሁ በአብዛኛው የጠቀሳችኋቸው በተለይ ጽሑፎቹ የራሳችሁ የመናፍቃኑ ከነ ትንታኒያቸው ውጤቶች ናቸው።
  ሌላው አስገራሚው የቁማር ጨዋታችሁ ደግሞ አፅዋማትን የተመለከተው ነው። ፃምን ለማሥጣል የሔዳችሁበት መንገድና አቀራረባችሁ አሥቂኝ አሳዛኝም ነው። አሥቂኝነቱ ተራ የእብደት ድራማችሁ ሲሆን አሳዛኙ ደግሞ ፃም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑንና በፃም የሚገኘውን የሚፈፀመውንሃይል አለማወቃችሁ ነው። ሲጀመር ቤተክርስቲያን የፃመምን ምንነትና አሥፈላጊነት ታስተምር ትናገራለች እንጂ አስገድዳ አታፆም። ፆም እንዲፆሙና መፆም እንዳለባቸው ትነግራቸዋለች። ክርስቶስ በዚ አለም በነበረበት ዘመን ማንንም አስገድዶ እንዲያምኑትና እንዲከተሉት እንዳላደረገ አካሉ ቤተክርስቲያንም ማንንም አሥገድዳ እምነት ሥርዓቷን እንዲፈፅሙ አታደርግም። በቤተክርስቲያን ሁለተና የሚያምን እምነት ሥርዓቷንና የምትናገረውን በፍቅር ያደርጋል። የማይፈልግ ደግሞ መለየትና ወደ ሚያምንበት( ወደ ሚመሥሉት) መሄድ ነው። ውስጧ ቁጭ ብሎ መበጥበጥና በሥሟ ውሸትና ሞትን መንዛት ግን አይቻልም። ሥለዚህ በማታምኑባት ቤተክርስቲያን እንክርዳድ ተረት ተረታችሁን መንዛት አቁማችሁ የራሳችሁን እምነት በራሳችሁ ሥም በህግ ተመዝግባችሁ አራምዱ። የወተት ዝንብ አትሁኑ!

  ReplyDelete
 4. በክፍል አንድና በዚህ ክፍል ከቀረበው ጽሑፍ የተረዳሁት ነገር፤
  1/ ተሐድሶ ያስፈልጋል የሚባሉት ተሐድሶዎች በእውቀት የበሰሉ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት የተራቀቁ፤ ምስጢራቱን አደላድለው የተረዱ ሰዎች መሆናቸውን ነው። ካላወቁ እውነትና ስህተቱን መለየት እንዳለመቻሉ መጠን በዲያቆን ያረጋልና ተሐድሶ ያስፈልጋል በሚሉት መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ ይታያል።
  2/ በምላሽ ደረጃ የቀረበው ይህ የተሐድሶዎች ጽሁፍ አወራረድና የመረጃ አተናተን ሂደት ምን እየተባለ እንዳለ፤ ምን ሊባል እንደሚገባና መሆን ያለበት ምን እንደሆነ ቃና ባለው ዘይቤ የቀረበ
  ነው። መረጃውና ማስረጃውን ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕድ በማቅረብ ተሐድሶቱን ለሚቃወሙ መልስ ይሰጣል። ይህም ማፈግፈግ እንዳይኖር ያደርጋል።
  3/ ጉዳዩ በዚህ ደረጃ ማለትም መታደስ የእግዚአብሔር አሰራር ነው አይደለም? ወደሚለው የሃሳብ ፍጭት መድረሱ በራሱ የተሸፈነው እውነት የት እንዳለና ማን እንደሸፈነው በቂ እውቀት ለሌለው ጥሩ የመረዳት ጊዜ ስለሚያመጣ እውነቱ ይገለጣል። በዚህም ተሐድሶዎቹ «ሰይፍ ዘክልዔ አፉሁ» በሁለት ወገን ስለት እንዳለው ሰይፍ ሆነው መገኘታቸው እጅግ የሚደንቅ ነው። እነ መምህር መሸ በከንቱ ጉዳዩን ወደፕቶቴስታንትና ሉተር በማላከክ ችግሩን መድፈን ከማይችሉበት ደረጃ ተደርሷል። ይህ እሰይ የሚያሰኝ ቢሆንም ብዙ መሰራት አለበት እላለሁ።

  ReplyDelete
  Replies
  1. ለanonymous August 6,2015 at 11:06 am

   አይ ወንድም! ተሐድሶ ነን ባዮችም ሆኑ አንተ ምንም ብታውቁ እውቀት ብቻውን አይጠቅምም። አላወቃችሁም እንጂ ብታውቁ ኖሮ በቃሉ ባልተሰናከላችሁ ነበር። አላወቃችሁም እንጂ እውነትን ብታውቁ ኖሮ ባመናችሁ ነበር። አላወቃችሁም እንጂ ብታውቁ ኖሮ ትንሽ ትልቁን ከመዝለፍና ሴተኛ አዳሪ አገናኝ ይመሥል እንትና ከእንዲት ሴት ጋ ታየ እያላችሁ የሰውን ስብእና በውሸት ባላንቋሸሻችሁ ነበር። አላወቃችሁም እንጂ ብታውቁ ኖሮ በውሸት ማሊያ ሳይሆን በእውነት ማሊያ የቤተክርስቲያኗ ልጆች ትሆኑ ነበር። አላወቃችሁም እንጂ የክርስቶስ የሆኑትን ቅዱሳኑን ባልተሳደባችሁና ባላአሳደዳችሁ ነበር። በአጠቃላይ አላወቃችሁም እንጂ ከእውነት ጋር ስትቃረኑ ባልተገኛችሁ ባልታያችሁ ነበር።
   ወንድሜ መንፈሳዊ እውቀት ማለት የምድር ፍልስፍና ወይም ሰይጣናዊ እውቀት አይደለም። መንፈሳዊ እውቀት ማለት በሞኝነት የሚገኝ እንጅ በምድራዊ ፍልስፍና የሚገኝ አይደለም። መንፈሳዊ እውቀት በመንፈስ ቅዱስ አሥተማሪነት የሚገኝ እውቀት እንጂ በአለምኛ ኑሮና በሰይጣን መንፈስ የሚገኝ አይደለም። የዲያቆን መጽሐፍ የናንተን ክህደት በመጥቀስ በእግዚአብሔር ቃልና በአባቶች ትምህርት እየመዘነ ስተትነቱ የገለጠ ነው። የናንተ መልስ ካላችሁትደግሞ ማምለጫ አይሉት መጠመጃ ተረት ተረትና የፃፋችሁትን አልፃፍንም የሚል ክህደት ነው። መረጃ የምትለውና የምትሉትም ዲያቆን ስተትነቱን የገለጠባችሁን ልብወለድ መጣጥፋችሁን ኤንጂ ሌላ ነገር የለውም። በዚህም ደግማችሁ ከማፈርና መናፍቃን መሆናችሁን እናንተው ከማረጋገጣችሁ ውጭ ትርፍ አላገኛችሁም።
   ወንድም፦ ሌላው ደካማነትህ የተሐድሶነን ባዮችን ማስረጃ ከቤተክርስቲያን ማእድ የተገኘ ለማለት መሞከርህ ነው። የቤተክርስቲያንን ነገር ከተቀበሉማ መጀመሪያውንም ቤተክርስቲያንን ባልተቃወሙና ባልዘለፉ ነበር። የትኛውን የቤተክርስቲያኗን መረጃ ነው የጠቀሱት(ያቀረቡት)? ይሔ እናንት እየፈበረካችሁ በነቀያፋ መንገድ ያዘጋጃችሁትን ነውን? እሱ ከሆነ የቤተክርስቲያኗ አይደለም። ነው እናዛን በጽሑፍና በንግግር ተጠቀሱ የተባሉትን ቃላት? እነሱ ደግሞ መረጃም አይሆኑምም፤ ቃላቶቹ የሚያስተላልፉት መልእክትና የእናንተ እንቅስቃሴ በምንም አይገናኙም። ቃላቶቹ ደግሞ አይደለም በክርስትና በመንግስታዊ ተቋማት ይነገራሉ ። ታዲያ ቃላት ነው ወይሥ ድርጊት ነው ማሥረጃ የሚሆነው? ምነው ወንድም የቃላት ጨዋታህን አቁመህ መዳን የሚገኝበትን ጥበብ ብትፈልግ።
   ወንድም፦ ሲነገር ሰምተሂልና ለአንተና ለመሰሎችህ አለበስሃቸው። " ሰይፈ ዘክልኤ" አይደል ያልካቸው። እረ ለአንተም ለእነሱም እውነትን የሚቆራርጡ የሚያጠፉበትን ሰይፍ አሳነስከው። ከወንጌል ጀምሮ እስከ ግለሰብ ስንት የክህደት፣ የሥድብ፣ የዘለፋ፣ የውሸት፣ የማስመሰል ወዘተ ሰይፎቸ አሥወነጨፋችሁ። እና ምነው የጥፋት ሰይፋችሁን በሁለት ገደብኸው።
   ተሐድሶ የሚለው ቃል በቁሙ በመጽሐፍ ቅዱስ ባይገለጥም ታደሱ፣ መታደስና የመሳሰሉ ቃላቶች ተገልጠዋል። ቃሉ እራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ ቢኖር እንሿንየሚያስተላልፈው መልእክት እምነትን ሥለመለወጥ ሳይሆን ስለንስሃና በመልካም መንገድ ሥለመሔድ እንጅ እምነትን ሥለመለወጥና ሥርዓትን ሥለማፍረስ አይደለም። ታደሱና መታደስ የሚሉትኔ ቃላቶች ከሙሉ አረፍተነገሩ ጋር ሥናነበው የሚሰጠው መልእክትና ትርጉም ንሥሃንና መልካምን ሥለማድረግ ነው። ተሐድሶ በሚል እየተጠቀሙ ያሉት መናፍቃን ደግሞ እምነትን የመለወጥና ሥርዓትን የማጥፋት እንደሆነ የታወቀና ትምህርቶቻቸውና መሰል ጽሑፎቻቸው ምስክሮች ናቸው። ሥለዚህ ተሐድሶዎች በተሐድሶ ውስጥ የሚረጩትና መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ የያዛቸው መታደስና ታደሱ የመሳሰሉት የሚያስተላልፉት አይገናኙም። መጽሐፍ ቅዱስ ያልያዙ የእምነት ድርጅቶችም ለማመን ሳይሆን ቃሉንና ክርስትናን ለማጥላላት የእግዚአብሔርን ቃል እየጠቀሱ የራሳቸውን ድምዳሜና አመለካከት ያራምዳሉ አይደለም ቃላትን ቀርቶ። ታዲያ እነሱም ለማስረጃነትና ለእውነተኛነት ታጫቸው ይሆን።
   ወንድም፦ የትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ብትደረድሩ ከእውነተኛው የክርስትና ትምህርት የወጣ ከሆነ ፕሮቴስታንዚም ነው። ፕሮቴስት ማለት ደግሞ መቃወም ነው። እውነትን የሚቃወምና የሚቃረንና ቅዱሳንን የሚንቅ የሚሳደብ ደግሞ ፕሮቴስታንትና የፕሮቴስታኒዝም አቀንቃኝ ብቻ ነው።
   ወንድም ቲፎዞነቱ አያድንህምና እራስህን ከትቢት አውጥተህ የመዳንን መንገድ ፈልግ። የተሐድሶ ነን ባዮች ማንነትና መንገዳቸው እንደሆነ ተገልጧል። እሱም ክህደትና ወደ ሞት ነው።

   Delete
  2. AnonymousAugust 6, 2015 at 11:06 AM
   your idea is best
   damot
   lefa belohe egehen tadekemaleke

   Delete
 5. ዜሮ(ባዶ)2
  በዓላትን በተመለከተም ተረት ተረታችሁን ተርካችኋል ።በመጀመሪያ በዓላትን የሚያከብር ለእግዚአብሔር ብሎ ያክብር ተብሎ መጻፉን አትዘንጉ። ሥለተፃፈና ሥለተነገረ መንፈሳዊ በዓላትን መንቀፍና መቃወም የሰይጣን ነው። ምንም እንሿን እግዚአብሔር እራሱ በቀጥታም ይሁን በቅዱሳኑ በኩል ሥራ ያልሰራበት ቀን የሌለ ቢሆንም ቤተክርስቲያን ግን በአብይ በአልነት የደነገገቻቸውን በዋናነት ታከብራለች። በነዚህ በዓላትም ቢሆን ሥራ አትስሩ ብላ ከእለት ተለት እንቅስቃሲያቸው አልአለከለችም። እስቲ አሁን 30(ሰላሳ) ቀናትን ሙሉ በበዓላት ምክንያት ሥራ የማይሰራ የትኛው አባት፣ አገልጋይና ምእመን ነው። ለምን እንዲህ እርቃን የሆነ ውሸት መዋሸት አሥፈለገ? ማንን ለማሳመን? እናንተን መሰሉ ለእውነት እንዳይቆም አዚም የተደገበትና የአዕምሮ ችግር ያለበት ካልሆነ ማንም ይህን ዝሆን የሚያኸል ውሸትና ሐሰተኛ ክስ አይቀበልም። በተራ አሉባልታና ጥላቻ ደግሞ ህይወት ሳይሆን ሞት፤ ፅድቅ ሳይሆን ኩነኔ፤ ክርስቶስን ማገልገል ሳይሆን ማሳዘን፤ ወንጌል ሳይሆን ወንጀል መሆኑ ግልፅና በመጨረሻም የሚያስቀጣ ነው።
  መካድና ውሸት በመጀመሪያ(1) እንደገለጽኩት ዋነኛ መገለጫሁና እምነት አድርጋችሁ የያዛችሁት ነውና በጽሑፍ በንግግር የተናገራችሁትንና እየተናገራችሁት ያላችሁትን አላልንም ቀሚል ከሃዲና ውሸታም መሆናችሁን አረጋግጣችኋል። እኔ በግሌ እንሿን ክርስቶስን የምታመልክን ቤተክርስቲያን አታመልግም እያላችሁ በዚህ ድረገፃችሁ ስትዘላብዱ አንብቢያለሁኝ። ዲያቆን ያረጋል ደግሞ በመጽሐፉ የቤተክርስቲያኗ ያልሆነውን ነው ያላችሁትንና ያላደረጋችውን አድርጋለች ያላችሁትን ጠቅሷል። ለምሳሌ ዘርዐ ያዕቆብን ብዙ ሚቶቹ ላይ ሌላ ሚስት በቤተክርስቲያን ስርዓት አጋብታለች ማለታችሁን። በአሁን ቀደምም በመናፍቅነቱ የተባረረውንና የናንተ አባል የሆነውን አሸናፊ የተባለ ግለሰብ በግብረሰዶማዊነት ሲጋለጥባችሁ የቤተክርስቲያኗ ዲያቆን አሥመስላችሁ ሥታወሩ እንደነበር በሱ ዙሪያ በዚሁ ብሎጋችሁ በፃፋችኋቸው ጽሑፎቻችሁ አንብበናል። በዚህ ክፍል ሁለታችሁም በግልጽ ባትናገሩም በዓላትን በልማድና በዘርዐ ያዕቆብ የገቡ የቤተክርስቲያኗ ሲኖዶስ የማያውቃቸው ናቸው ስትሉ ተናግራችኋል። የቤተክርስቲያን በዓላት ትናንትናም ዛሬም በቤተክርስቲያኗ ሲኖዶስ ታውቀውና ታምነው ይከበራሉ እየተከበሩም ነው። እናንበ ሲኖዶስ የምትሉት የመናፍቃኑን የእናንተን ከሆነ የናንተ ማወቅ አለማወቅ ቤተክርስቲን አይመለከታትም። የፈለጋችሁትን ማመን አለማመን ትችላላችሁ።
  ሟቹን አቶ መሠረትን በተመለከተ በመጀመሪያውም በዚህኛውም እየሰገዳችሁና በሙት አስተሳሰቡ እየካባችሁ ከሞት ይሁን ከእግዚያብሔር ፍርድ ለማዳን ትባዝናላችሁ። በቤተክርስቲያን ነበረ ከሆነ ጌታውን በ30(ሰላሳ) ብር የሸጠው ይሁዳም ሐዋርያት አንዱ ነበር። ዴማስ ከሐዋርያት ደቀመዛሙርት አንዱ ነበር። ግና ሁለቱም ወደ ገዛ ምኞታቸው አዘንብለው ሔዱም በአለምም ወደቁ። ታዲያ ነበርኩና ነበረ ምን ይጠቅማል? ብዙ መናገር ሳያስፈልግ እናንተው እስኪሞት የት ያስተምር እንደነበረ ደግማችሁ ደጋግማችሁ ተናገራችሁት ። ይህም መካነ ኢየሱስ ሴምናሬም እንደነበረ ነው። ታዲያ መካነ ኢየሱስ እነማን ናቸው? መካነ ኢየሱስ እኮ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ እምነት አይደለም። እናንተ በኦርቶዶክ ተዋህዶ እምነት ላይ የከፈታችሁት ሰይጣናዊ ዘመቻ ሁሉ የሚያመለክተው እኮ ከመካነ ኢየሱስና መሰል ድርጅቶች ጋር የተባበራችሁና እምነታቸው እምነታችሁ መሆኑን ነው። ሥለዚህ የማስመሰያ ጭንብላችሁን አውልቃችሁ መካነ ኢየሱስነታችሁን በገሀድ ማጥለቅ ነው። መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁና የመውጊያውን ቀስት ብትቃወሙ የሚብስባችሁ ለናንተው ነውና ቤተክርስቲያን በእኔ እምነት እመኑ ብላ አታስገድድም።
  በአጠቃላይ ክፍል ሁለቱም በእውነት ሚዛን ስመለከተው ሌባነታችሁንና ስትሰርቁ እንዳትታዩ የምታደርጉትን ድብብቆሽ የውር ድንብር ጨዋታችሁን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በተጨማሪም ዲያቆን ያረጋል የፃፈው ሌላ እናንተ የምትተርኩት ተረት ሌላ ነው። ቀለላችሁ እንጂ አላተረፋቼሁም ። ክፍል አንድም ዜሮ ክፍል ሁለትም ዜሮ።
  መናፍቅ ተሐድሶዎች እናንተም በተረት አሉባልታችሁና በእንክርዳዳችሁ ቀጥሉ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል መዶሻ ይዘው ይጠብቋችኋል። በቃሉ መዶሻነትም ተረት እንክርዳዳችሁን እያፈራረሱ እውነትን ይገልጣሉ።

  ReplyDelete
  Replies
  1. አስተያየት መጻፍ ስትጀምር የመጀመሪያህ ነው መሰለኝ። የድረ ገጹን ሰሌዳ ለቅልቀህ ትሞላለህ። ይህን ሁሉ አስተያየት ማን ያነብልሃል? በአስተያየትና በትምህርታዊ ጽሁፍ መካከል ያለውን ልዩነት ስለማታውቅ ከዝባዝንኬህ ሁለትና ሶስት መስመር ካነበብኩ በኋላ ያው ተመሳሳይ ስለሆነ እስክጨርስ አልጠብቅም። መድረክ ላይ ሆነህ ስትለፈልፍ እንቅልፍ ለምታስይዛቸው ዘመዶችህ አዘንኩላቸው። ዳሞት ነህ ዳሞትራ?

   Delete
  2. ለanonymous August 7,2015 at 3:13 am
   አቶ፦ እምነትህ መሰለኝ፣ ይገመታልና እንደሚሆን አይጠረጠርም እንደሆነው ሁሉ ነገርህም መሰለኝ መሆኑ ያለህ መሰለኝና መሰል መሆኑ ግልጽ ነው። ምክንያቱ ከእምነትህ የወረስኸውና እምነትህ መሰለኝ ስለሆነ።
   አሥተያየት እንደ ነገሮች(ጽሑፎች) ሁኔታ ይረዝማል ያጥራል። ሀይማኖትን ለማጥፋት፣ ወንጌልን በእንክርዳድ፣ የእምነት ሥርዓትን በዳንኪራና ህግጋተ እግዚአብሔር በአሉባልታ ለመለወጥና ለማዳፈን ለሚደረግ የእባብ ትፋት በቂ የሆነ አሥተያየትም መልስም የያዘ መፃፍ ተገቢ ነው። ይህን የምለው ለአንተ ሳይሆን ሌሎች ወንድሞቸ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ነው።
   ስለማንበብ አለማንበብህ የሚገደኝ ነገር የለም። ድሮውንም አንተ የምታነበውና የምትከተለው የሞትን ጽሑፍና የሰይጣንን ነገር እንጅ ህይወት የሚገኝበትንና የእግዚአብሔርን ነገር ስላልሆነ አለማንበብህን እውነት ብለሀል። ባያምንም ጠላት ዲያብሎስስ ኢየሱስን አውቀዋለሁ ሲል የኢየሱስን ማንነት የማወቁን አንድ እውነት ተናግሮ አይደለ። አንተም አንድ እውነት ተናግረሀል። እሱም እውነት የሚገለጥባቸውን መልእክቶች አለማንበብህን።
   ሥለመድረክም ነካ አድርገሀል። እኔ በሀይማኖቴ መድረክ የሚባል አጠራር የለም። አምልጦህም ቢሆን ቤትህ አዳራሽ መሆኑን በመድረክ በኩል አሳውቀሃል። መድረክ በአዳራሻችሁ ያለ መደለቂያችሁ ነውና። ሥለመለፍለፍም ተናግረሃል ። እኔ ለፍላፊ አይደለሁም። በተዘዋዋሪም ቢሆን አሥተማሪ ነህ ለማለት የዳዳህ ትመሥላለህና እኔ አሥተማሪም አይደለሁም። ሥለእንቅልፍም ነካ አድርገሃል። አንተ እውነትን እንዳታይ በጥላቻ እንቅልፍና በክህደት አዚም ተኝተህ ሥላለህ ሁሉ እንዳንተ የሚተኛ አይደለም። ለእውነት በንቃት የቆሙ አሉና። ጥግለጥግ ከምትሔድ ግልጽ መሆን ተመኝ።

   Delete
  3. አፈር በበላው ሰንሰለት በባልቴት ተረት የተተበተበ አእምሮ እንዲሁም በተዛባ የምስቅልል ኖሮ ተሣስሮና ተደነጋግሮ ያለ ትውልድ አዲስ ነገር (ተሐድሶ) ብታስተምረው ዓይኑን ያፈጣል ጥርሱን ያገጣል ብትሩን ይመልጣል እንጂ መች እንዲጠቀም ሆኖ ይቀርባል።
   ዕውነታው ግን ከመጀመሪያው ተሓድሶ ነበር ፩ኛ ምድርም ቅጥ የለሽ ነበርች ባለቤቱ ግን
   አስተካከላት አደሳት አበጃት ይላል። ፪ኛ ሔኖክ ሓዲስ ተሐድሶ ማለት ነው ፫ኛ በትንቢተ ሕዝቅኤልም አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ ይላል ፬ኛ ዳዊት በመዝሙሩ አዲስ ምስጋናን ለግዚአብሔር አቅርቡ ይላል። ሐዲስ ኪዳን በሙሉ እስከ ዓለም መጨረሻ አዲስ ነው ዳሩ ግን ልቡ ለክህደትና ለነቀፋ አፉ ለስድብና ለዘለፋ የተዘጋጀ ትውልድ
   ስለዕውነት ብትነግረው ሊቀበል አይችልምና ምንትኑ ጽድቅ ውምንትኑ ተሐድሶ እያለ
   ጊዜህን ያባክናል። ቢሆንም ከዳተኛውን ምከረው አለዚያ መከራ ይምከርው! አስመሳይ በመሆኑ

   Delete
  4. አፈር በበላው ሰንሰለት በባልቴት ተረት የተተበተበ አእምሮ እንዲሁም በተዛባ የምስቅልል ኖሮ ተሣስሮና ተደነጋግሮ ያለ ትውልድ አዲስ ነገር (ተሐድሶ) ብታስተምረው ዓይኑን ያፈጣል ጥርሱን ያገጣል ብትሩን ይመልጣል እንጂ መች እንዲጠቀም ሆኖ ይቀርባል።
   ዕውነታው ግን ከመጀመሪያው ተሓድሶ ነበር ፩ኛ ምድርም ቅጥ የለሽ ነበርች ባለቤቱ ግን
   አስተካከላት አደሳት አበጃት ይላል። ፪ኛ ሔኖክ ሓዲስ ተሐድሶ ማለት ነው ፫ኛ በትንቢተ ሕዝቅኤልም አዲስ ልብ እሰጣችኋለሁ ይላል ፬ኛ ዳዊት በመዝሙሩ አዲስ ምስጋናን ለግዚአብሔር አቅርቡ ይላል። ሐዲስ ኪዳን በሙሉ እስከ ዓለም መጨረሻ አዲስ ነው ዳሩ ግን ልቡ ለክህደትና ለነቀፋ አፉ ለስድብና ለዘለፋ የተዘጋጀ ትውልድ
   ስለዕውነት ብትነግረው ሊቀበል አይችልምና ምንትኑ ጽድቅ ውምንትኑ ተሐድሶ እያለ
   ጊዜህን ያባክናል። ቢሆንም ከዳተኛውን ምከረው አለዚያ መከራ ይምከርው! አስመሳይ በመሆኑ

   Delete