Saturday, August 15, 2015

ውግዘትና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት - ክፍል ሦስት

Read in PDF
በዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ


3.  ክህነት ያለው ሁሉ አያወግዝም!
     አውግዞ መለየት ከእግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠ ሥልጣን ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ የሚበልጠውና ለቤተ ክርስቲያን የተሰጠው የአደራና የዘላለም ተልዕኮ ማስተማርና ለፍጥረት ሁሉ ወንጌልን ማድረስ ነው፡፡ (ማቴ.28፥19) የቤተ ክርስቲያን ትልቁ የሥራ ድርሻዋ ይህ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አጽንታ ወንጌልን የምታስተምር ከሆነ ደግሞ የፊተኞቹ ቢጽ ሐሳውያን(ሐሰተኛ ወንድሞች) የኋለኞቹ መናፍቃን መነሳታቸው   የማይቀር ነው፡፡ ማውገዝ ፣ መለየት ፣ ከምዕመናን አንድነት ማሰናበት የዚህ ጊዜ መምጣቱ ግድ ነው፡፡
    ይህ ሲሆን ግን ሁሉም ወደማውገዝ ሊመጣ አልተፈቀደላትም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አላት፤ የቤተ ክርስቲያን ወገን ነኝ የሚል አካል ደግሞ ሥርዓቷን ሊያከብር ግድ ይገባዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት ከኤጲስ ቆጶስ በቀር ቄስና መነኩሴ የማውገዝ ሥልጣን የለውም፡፡ (ፍትሃ ነገስት አን.5 ቁጥር.117-124) ከዚህ በተጨማሪ አንድን ሰው መናፍቅና ከሀዲ ብሎ ለመለየት ደግሞ ከኤጲስ ቆጶስ ባሻገር ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ሠርቶ ማውገዝ ይህ የቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና ነው፡፡

    ዛሬ ዛሬ ብዙ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች “ተወግዘውና” ከቤተ ክርስቲያን አንድነት ተለይተው፤ ሙሉ የአምልኮ ነጻነታቸውን አጥተው፤ ብዙ ምዕመናንና ምዕመናትም ከቤተ ክርስቲያን ገረገራ ርቀው የቆሙትና ብሎም ወደዓለም ፊታቸውን ዘወር ያደረጉት አንዳንድ “አላዋቂ” መነኮሳትና ቀሳውስት የግል ጥቅማቸውንና ክብራቸውን ለማስጠበቅ “ይህን ካላደረጋችሁ አወግዛለሁ ፤ ይህን ካላመጣችሁ አስራለሁ ፤ ይህን ብላችሁ ካልተናገራችሁ “አበ ነፍስ” አልሆንም … በሚሉ ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎች እንጂ በእርግጥ ለቤተ ክርስቲያን ዶግማና ቀኖና ተጨንቀውና ገዷቸው አይደለም፡፡ ቢሆንማ ኖሮ ነገሩን አጥርተው ፥ ለአንዲቱ የክርስቶስ የደም ዋጋ በግ ተጠንቅቀው ፣ ከሥጋዊና ከቅንዓት፤ ከቁጣም መንፈስ ጸድተው … የሚናገሩት ኑፋቄ ቢሆን ሥልጣን ላለው አካል ባስረከቡና ባሳወቁ ነበር፡፡
    የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ በዚህ ዙርያ አሳዛኝ ገጠመኝ አለው፡፡ ከ1980ዎቹ አጋማሽ እስከ 1990ዎቹ መጀመርያ ድረስ በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን “ከፍተኛ የሆነ “የለውጥና የተሃድሶ” እንቅስቃሴ ይደረግ” በሚሉ ወገኖች ከአገር ዳር እስከዳር ተነስተው ነበር፡፡ በዚያን ወቅት በአንድ አገር ላይ ይደረግ የነበረውን እንቅስቃሴ በልጅነት አዕምሮዬ በደንብ ዘግቤዋለሁ፡፡ በነበርኩበት ደብር በሰንበት ትምህርት ቤቱና በሠበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ውስጥ ሁለት ቡድኖች ነበሩ፡፡ አንዱ አሳዳጅ ሌላው ተሳዳጅ፡፡ በኋላ ላይ “ሊቀ ጳጳሱ አውግዘዋል” ተብሎ ከሰማንያ በላይ የሚሆኑ “አማኞች” ስም ዝርዝር በደብሩ የስብከተ ወንጌል ኃላፊ ከቅዳሴ በኋላ ተነበበ፡፡ ይህ ንባብ በተነበበ በዚያ ማታ በዚያው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስማቸው ከተጠሩ መካከል ተደብድበው የተፈነከቱ ፣ ተገርፈው የተራቆቱ ፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ዛሬም ድረስ አስታውሳቸዋለሁ፡፡
    በአንድ ሌላ ገጠመኝ ደግሞ “የተለየ አስተምህሮ ተከትለዋል” ተብለው ወደሃያ ስምንት የሚጠጉ ዲያቆናትና ሰንበት ተማሪዎች በአንድ ሰበካ ጉባኤ ፊት ቀርበው ሳለ … ገና ነገሩ መታየት ሳይጀመር ከመካከል አንድ ወንድም … “ይህ ነገር የተረጋገጠ መረጃ ካለው እኛ መዳኘት አንችልም፤ ለምን ለሚመለከተው ክፍል መረጃውን አስረግጠን አንልክም?” ቢል አንድ “አባት” ብድግ ብለው “ … እኛ እነዚህን ለማውገዝ እናንሳለን? እንዲያውም እኛ እዚህ የተቀመጥነው እንዲህ ያሉትን ልናወግዝ ነው …” ብለው እነዚያ ልጆች ከቤተ ክርስቲያን “አንድነት” መለየታቸውን አስታውሳለሁ፡፡
    በእንደነዚህ አይነት ግድየለሽና ኃላፊነት የጎደላቸው ቀሳውስትና መነኮሳት ቤተ ክርስቲያን ጥቂት የማይባሉ በሚሊየን የሚቆጠሩ ልጆቿን ለሌሎች ገብራለች፡፡ እንኳን ቄስና መነኩሴ “ … በየጊዜው ሁሉን እስከማሰርና እስከማውገዝ ድረስ የሚቆጣ ኤጲስ ቆጶስ ቢኖር ይህን ባይተው … ከሹመቱ ይሻር፡፡” ይላል ቀኖናው፡፡(ፍትሐ ነገስት አን.5 ቁ፣182) በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ግን ፍልሰታቸው “ሥልጣናቸውን አላግባብ በተጠቀሙ” ቀሳውስትና መነኮሳት ነው፡፡
    በቤተ ክርስቲያናችን መናፍቃንንና ከሃዲያንን የማውገዝ፤ “እገሌ እንዲህ ነው” የማለት ብቸኛ ሥልጣን ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ብቻ ነው፡፡

4.  የሃይማኖት እንጂ የምግባር ህጸጽ ያለባቸው ሊወገዙ አይገባም!

      ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ምግባረ ብልሹነትን ለማስፋፋትና አብሮ ለማበር እንዲመች ውግዘት እንዳይነካው ከሚፈለጉ ሃሳቦች አንዱ ይህ ሃሳብ ነው፡፡ እንዲያውም ብዙ ጊዜ “አንድ ሰው ለቅዱሳን ፣ ለጻድቃን ፣ ለሰማዕታት ፣ ለመላዕክት ፣ ለማርያም ፣ ለመድኃኒዓለም ፣ ለሥላሴ … ይዘክር ፣ ያብላ ያጠጣ ፣ ይመጽውት ያልብስ እንጂ  የተገለጠ ኃጢአትን ቢሠራም አይኮነንም” በማለት በድፍረት የነበላኤ ሰብዕን ፣ የነክርስቶስ ሰምራን ፍጡራንን ከሲዖል የማጋዝ ታሪክ በዋቢነት ጠቅሰው የሚያስተምሩ ብዙ “መምህራን”(መምህራን ከተባሉ) አሉ፡፡ 
     እንዲያውም ፥ ማስወገዝ የነበረበት ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ ጽሁፎችንና ታሪኮችን ቤተ ክርስቲያንን እንደሚወክሉ አድርጎ ማቅረቡ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን መናፍቃንን ብቻ ሳይሆን የታወቀ ነውር ውስጥ ሆነው ንስሐ ባለመግባት ለብዙዎች መሰናከያ የሚሆኑትንም ልታወግዛቸው እንደሚገባ ዶግማዋም ቀኖናዋም ያዛል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ፦

እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ … ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ … በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም። (ሮሜ.8፥5-9)

በማለት ከተናገረን እኛም በምንም አይነት መንገድ የሥጋ ሥራ ከእግዚአብሔር አይለየንም ብለን መሞገትና አዲስ “የሥጋ ሥራን የሚያጸድቅ ትምህርት” ማምጣት አንችልም፡፡ ስለዚህ ፥ የሃይማኖትም የምግባርም ህጸጽ በብዙ ተመክሮ ፣ ተዘክሮ ፣ ንስሐ እንዲገባ ዕድል ተሰጥቶ አልመለስ ፤ አልቀለስ ቢል “ከሥጋ ሥራ ጋር የመንፈስ ፍሬ ሕብረት ስለሌለው ሊወገዝ ፤ ሊለይ ግድ ነው፡፡ እኛ እንኳ ባንለየው እርሱ ራሱን ሊለይ ግድ ነውና ፤ እኛ  “የሥጋ ሥራ ሆይ! ስለምን ከእኛ ጋር አልኖርክም?” ብለን ልንሞግት አይገባንም፡፡ 

5.  ተሐድሷዊ አመለካከት ያላቸውን ወገኖች ማውገዝና ማስወገዝ

     ከጥንት በተለይም በአጼ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመን ከእስጢፋኖሳውያን መነሳት ጀምሮ ተሐድሷዊ ሕይወት ፣ ትምህርት ፣ አመለካከት ፣ ቀኖናዎች ፣ ሰዎቹም ጭምር  ሲወገዙ ፣ ሲጠሉ ፣ አብዝተው ሲነቀፉ ልባችን እየደማም ቢሆን አይተናል፡፡  በእርግጥም ዛሬ ዛሬ፥ በቤተ ክርስቲያናችን ቦታ የሳቱ ወይም ከተነገረላቸው ዓላማ ውጪ በአብዛኛው ከሚተረጎሙ ብዙ ቃላት መካከል አንዱ ተሐድሶ የሚለው ቃል ነው፡፡ ነገር ግን በብዙ ሰዎች ሕሊና የማይጨበጥና አውሬያዊ መልክ እንዳለው ተደርጎ እንደተሳለውና እንደተወገዘው ያለ ነገር ሳይሆን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረትነት ያለው እውነት ነው፡፡
      ስለዚህ ነገር ጥቂት ነገር ብንናገር ፦ ተሐድሶ “ሐደሰ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙ “አዲስ አደረገ” የሚለውን ትርጉም ታሳቢ ያደርጋል፡፡ በተገብሮ “ተሐድሰ” ከሚለው ቃል ደግሞ “ተሐድሶ” የሚለው የወጣ ሲሆን ትርጉሙ “አዲስ ሆነ” ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ስያሜው እንኳ ድርጊትን እንጂ ተቋሟዊነትን ወይም አደረጃጀትን ፈጽሞ  አያመለክትም፡፡
   ተሐድሶ ድርጊትን ይመለከታል፥ ካልን ድርጊቱ የሚመሠረተው ባለ ነገር ላይ ወይም ያለን ነገር ታሳቢ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ይህንንም በሁለት መልኩ ማየት እንችላለን፡፡
1.     የሚጠበቅ ፤ የሚፈለግ ነገር አለ፤
2.    የማይጠበቅ ፤ የማይፈለግ ነገር አለ፡፡
     ተሐድሷዊ ድርጊት እኒህን ሁለቱን ድርጊቶች ታሳቢ በማድረግ ወደትግበራ ለማምጣት በገቢር ሲተረጎም ፦
       የሚፈለግንና የእግዚአብሔር የሆነውን መጠበቅ ፣ መንከባከብ ፣ ከጠላት መከላከል ፣ እንዳይጎዳ ተገቢውን ቅጥር መቅጠር ሲሆን ፤
       እግዚአብሔር የማይፈልገውን ነገር ደግሞ እንዲወገድ ፤ እንዲቆረጥ ፣ እንዲገረዝ ማድረግንም ያመለክታል፡፡
  ይኸው ተሐድሷዊ ድርጊት በተገብሮ ሲተረጎምም እኒህን ሁለት ነገሮችን ገንዘብ ያደርጋል ፦
       የእግዚአብሔር ሆኖ የሚፈለገውን ነገር ማጥበቅ ፣ እንዲንከባከቡ ፣ ከጠላት እንዲከላከሉ ማድረግን ሲያመለክት ፤
       እግዚአብሔር የማይፈለገውን ነገር ፈጽሞ መወገዱን ፣ መቆረጡን ፣ መገረዙንም የሚያሳይ ነው፡፡
      ይህን እውነት ከተረዳን የጉዟችንን አቅጣጫ ያስተካክልልናል፡፡ ተሐድሶ ድርጊት ከሆነ ከድርጊቱ በፊት ድርጊቱን ፈጻሚ አካል ማለትም የሰው ልጅ፥ በአዳሹ እግዚአብሔር መታደስ ፤ መቀደስ ፤ ለሥራው መለየት ፤ ከዓለምና ከዚህ ጠማማ ትውልድ በድንቅ ጥሪው መጠራት  ይኖርበታል፡፡ እኛ በእግዚአብሔር ድርሻ ውስጥ የምንገባውና አብረነው የምንሠራው ታዳሽ  መሆናችንን አምነን ስንቀርብና ራሳችንን ስናዘጋጅ ነው፡፡
   ሌላው ትልቁ ነጥብ የማይፈለገውንና የእግዚአብሔር ያልሆነውን ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ይወገድ ስንል ፥ ቀድሞ ነገር የሚፈለገው እንዳይጠፋ በብርቱ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡ ለምሳሌ፦ ተሐድሶ መጽሐፍ ቅዱስን ይጠብቃል እንጂ አያድስም፡፡ እንዲሁ በእኛ ልብ ከክርስቶስ ውጪ የነገሠና የከበረ ካለ ያንን ልብ በማስተማርና ዙፋኑን ለክርስቶስ በማስለቀቅ ማደስ (ባዕዱን አካል ማስወገድ) ይገባል ማለት ነው፡፡
    ይህን እውነት በማስተዋል አይተን ፥ የቀደሙት የቤተ ክርስቲያን አባቶቻችንን ትምህርት ያየን እንደሆን ይህን እውነት ይበልጥ ያስረግጡልናል፡፡ ለምስክርነትም ፦
       ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ መንፈሳዊ ተሐድሶ በምድር ላይ ባለ ሕይወት ላይ የሚተገበር እንደሆነ በማተኮር አዳምን ከመምሰል ባለፈ እግዚአብሔርን ወደመምሰል የምናድግበት ሂደት እንደሆነ ይመሰክራል፡፡
       ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያ ደግሞ መንፈሳዊ ተሐድሶ የሚከናወነው በመንፈስ ቅዱስ አሠራር በሰብዓዊ ፍጥረት ልብ ውስጥ እንደሆነ አትቶ ጽፏል፡፡
       ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያም መንፈሳዊ ተሐድሶ ግላዊ ልምምድ መሆኑ ላይ በማተኮር መንፈስ ቅዱስና ሰው በመተባበር ሰው እግዚአብሔርን ወደመምሰል የሚያድግበትና የሚደርስበት ሂደት ነው፡፡ ይህም የሚከናወነው መንፈስ ቅዱስ ከአማኙ ጋር አብሮ በመተባበር እንደሆነ ጽፏል፡፡
      እውነታው ይህ ሆኖ ሳለና “የውስጥ ነቃፊ ጠጋኝ ፥ የውጪ ነቃፊ አፍራሽ መሆኑ ሊታወቅ ሲገባው” (ጌታቸው ኃይሌ (ፕ/ር) ፤ ደቂቀ እስጢፋኖስ ፤ 2002 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ፕሬስ ፤ ገጽ.44) ለረጅም ዘመናት ቤተ ክርስቲያን ጠቃሚና ጠቃኝ ተሐድሷዊ ምልከታ ያላቸውን ብዙ ቅዱሳን ልጆቿን ስታሳድድ ፣ ስትገድል ፣ ስትበድል ፣ በጠላት ላይ የማይፈጸመውን የከፋ ረሃብና እርዛትን ስትፈርድ ታሪክም እኛም ታዝበናል፡፡ 


“ሊወገዙ የሚገባቸው” መናፍቃን

      አንድ ቃል ከአንድ በላይ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ትርጉሙንም የሚወስነው ቃሉ የገባበት አውድ ነው፡፡ የአውዱን ጠቅላላ ሐሳብ በመረዳት የቃሉን ትርጉም በሚገባ መረዳት ይቻላል፡፡ “መናፍቅ” የሚለው ቃል “ነፊቅ” ከሚለው ግስ ወጥቶ ሲረባ “ነፈቀ ፣ ይነፍቅ ፣ ይንፈቅ ፣ መንፈቅ ፣ መሰንጠቅ ፣ አስተካክሎ መክፈል ፣ ወይም መለየት የሚለውን ይሰጠናል፡፡ መናፍቅ ማለት ደግሞ በቁሙ ናፋቂ ፣ አናፋቂ ፣ የሚያጠራጥር ፣ ጠርጣሪ ፣ አጠራጣሪ ፣ ሃይማኖቱ ህፁፅ የሆነ ምሉዕ ያልሆነ ፣ መንፈቁን አምኖ መንፈቁን የካደ ማለት ነው፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡(1948 ዓ.ም)፤አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡)
    በሌላ ትርጉም “ኑፋቄ” የሚለውን በቁሙ ሲፈታው “  ነፈቀ … ከኃይማኖት የወጣ ፣ እምነተ ሰንካላ ፣ ተጠራጠረ ፣ መናፈቅን ፣ ከሀዲን ኾነ ነፈቀ፡፡” ብሎ ይፈታዋል፡፡ (ከሳቴ ብርሃን ተሠማ ፤ የዐማርኛ መዝገበ ቃላት ፤ 1962 ፤ አዲስ አበባ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 662)
    በአዲስ ኪዳኑ ግሪክ “መናፍቅ” የሚለውን የቃል ትርጉም “ክፍፍል፤ ልዩነት” (ሐዋ.24፥14 ፤ ገላ.5፥19-20) ብሎ ሲተረጉመው የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ ይህን ቃል የተጠቀመችው “መሠረታዊውን የክርስትና እምነትን እንደሚክድ ግለሰብ (ቡድን) ትጠቀምበትና እንዲህ ያለውን አካል ከህብረቷ መለየት እንደሚያስፈልግ ታስተምር” ነበር፡፡ (ሐዋ.24፥14)
      “መናፍቅ፤ በአንድ ሃይማኖት ውስጥ የተለየ ትምህርትን ተከታትሎ በመጠራጠር መለያየትን የሚፈጥርና የሚወግን (2ጴጥ.2፥1 ፤ ቲቶ.3፥10 ፤ 1ቆሮ.11፥19)” በማለት ደግሞ መዝገበ ቃላቱ ይፈታዋል፡፡ (የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር(2002)፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9ኛ እትም፣ አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡)
     በጥቅሉ መናፍቅ ማለት፦
·        የሚያጠራጥር አጠራጣሪ፣
·        ጠርጣሪ፣ ሃይሞኖቱ ህፁፅ፣ መንፈቁን አምኖ መንፈቁን የሚክድ፣
·        ከሃይማኖት የወጣ፣
·        ከሀዲ፣
·        መሠረታዊውን የክርስትና እምነት የሚክድ፣
·        የተለየ ትምህርትን የሚከተልና የሚፈጥር ነው ማለት እንችላለን፡፡
       እኒህ መናፍቃን በአብዛኛው ዘመናቸው ራሳቸውን የሚጠሩት በሌላ ስም ሳይሆን (ማለትም በእስልምና ፣ በሒንዱ ፣ በሻንቶ፣ በቡሂድ … ) “እኛ ነን” ብለው ስለሚጠሩ ይህን ሥያሜ ሊያገኙ ችለዋል፡፡ ሁሉም መናፍቃን ከክርስትና አካል የነበሩና በኋላ ግን በእንግዳ ትምህርት (ኤፌ.4፥14 ፤ ዕብ.13፥9) ተጠላልፈው የወደቁ ፤ የተለዩ ናቸው፡፡
      መናፍቃን የሚታወቁበት ልዩ ባህርያቸው መሠረታዊውን የክርስትና መሠረተ እምነት በግምሽ(መንፈቁን)  በመካድ ወይም ሙሉ ለሙሉ ባለመቀበል ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ጉባኤ ሠርታ የማውገዟና የመለየቷ ምክንያትም መሠረተ እምነትን በመናዳቸውና ባለመቀበላቸውም ጭምር ነው፡፡
      መናፍቃን በጌታ አጠራር “ጸራዊ”፤ በሐዋርያት አነጋገር “ቢጽ ሐሳውያን (የሐሰት ወንድሞች)” ሲባሉ በሊቃውንት ግን “መናፍቃን” ተብለዋል ቢባልም በሐዋርያትም ዘመን ግን መናፍቃን ይባሉ እንደነበር ማሳያዎች አሉ፡፡(ገላ.5፥19)
     የመጀመርያዎቹ የቤተ ክርስቲያን መናፍቃን በመባል የሚታወቁት ግኖስቲካውያን(ግኖሲሳውያን) ናቸው፡፡ “ግኖሲስ” ማለት በግሪኩ “ዕውቀት” ማለት ሲሆን የእምነቱ ተከታዮች ስያሜ የሆነው “ግኖስቲዝም” ማለት ደግሞ ትርጉሙ “አዕምሮዐዊ ፤ ዕውቀታዊ ፤ መዳን በዕውቀት ፤ ዕውቀታውያን” የሚል ሃሳብን የያዘ ነው፡፡
     ግኖስቲካውያን በክህደታቸው የመጀመርያይቱ ቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ፈተናዎች ብቻ ሳይሆኑ ቤተ ክርስቲያን ካሳለፈችበት ከየትኛውም ጊዜ ፈተናዎቿ በእነዚህ መናፍቃን የደረሰባት ጥቃትና ጥፋት የሰፋና መልኩን እየቀያየረ ዛሬም ድረስ የዘለቀና ብዙዎችን ጠላልፎ የጣለ አደገኛ ትምህርት ነው፡፡
     ስለነዚህ መናፍቃን ሁሉም ሐዋርያትና ደቀ መዛሙርት ክህደታቸውን ጠቅሰው እንደቃሉ መልስን በመስጠት አሳፍረዋል ፤ ሃይማኖትን ጠብቀዋል፡፡ የቅዱሳን ሐዋርያት የአዲስ ኪዳን መልዕክታትን ለመጻፍ ሲነሱ በሁሉም ህሊና የመጀመርያዎቹ የቤተ ክርስቲያን መናፍቃን ግኖስቲካውያን በቤተ ክርስቲያን የሚያደርሱትን ጥፋትና የበጎችን ስርቆት በመቃወም በወንጌል እውነት ላይ በመቆም የተጻፉ መልዕክታት ናቸው፡፡
     ሐዋርያት መናፍቃንን በጽሁፎቻቸውና በትምህርታቸው በግልጥ ተቃውመዋል፡፡ የሐሰት ትምህርቶቻቸውን ገልጠው ከመንፈስ ቅዱስ በተሠጠ ስለታማ የወንጌል ቃል ቆራርጠውታል፡፡ ለምሳሌ፦
1.     ክርስቶስ እርሱ አምላክ አይደለም፤ የአብ ሙላት ነው እንጂ ለሚሉ ግኖስቲካውያን መናፍቃን ቅዱስ ጳውሎስ የክርስቶስ ሙላት ማለት ኀይሉን ባህርይውንና የእግዚአብሔርን ሁለንተና የሚገልጥና እንዲሁም የአብ የባህርይ ልጁ ክርስቶስና ኢየሱስ ሁሉን የፈጠረና ከሁሉ በላይ መሆኑን በግልጥ ተናገረ፡፡ (ቆላ.1፥15-21፤2፥9፤21)
2.    ሥጋን የኃጢአት ምንጭ ስለሚያደርጉ መለኰታዊ ቃል የሰውን ሥጋ የሚመስል እንጂ እውነተኛውን የሰውን ሥጋን አልለበሰም ለሚሉ ዶሴቲክስ ለሚባሉ መናፍቃን  የሰውን ሥጋ የለበሰና የተዋሃደ መሆኑን አስረግጦ ተናገረ፡፡ (1ዮሐ.1፥1፤2፥22፤4፥2) 
3.    ሥጋ ክፉ፤ የኃጢአትም ምንጭ ነውና  ፍጹም ነጻነትን ሊያገኝ አይገባውም፡፡ ሊጐሳቆልና ሊጨቆን፤ ቸልም ሊባል ይገባዋል ይላሉ፡፡ በተለይም ጋብቻን በመከልከል አያስፈልግም ሲሉ፥ ሴትን ልጅን መንካት፤ ሩካቤ ሥጋን መፈጸም የዚህን ዓለም ቁስ መጠቀምም ፍጹም መርከስ ነው ብለው ያስተምራሉ፡፡ ስለዚህ መንካትን፣ መዳሰስን፣ መቅመስን … ፈጽመው ይከለክሉ፤ ይጠየፉም ነበር፡፡ ሥጋን መብላትንና ሌሎችንም ምግቦችን  በመከልከል ሥጋን አብዝቶ መቅጣት እንደሚገባ አስተማሩ፡፡ ጋብቻን የሰይጣን ሥራ ነው ብለው በዚህ ፈንታ ከዚህ ለመራቅ ነፍስና ሥጋን ለመለያየት የሚያበቃ ትኅርምት በቀኖናቸው ያዛሉ፡፡ ምድር ረክሳለች በማለትም ብዙ ጊዜያቸውን በቆጥ ላይ ያሳልፉ፤ ከሰው ጋርም አለመገናኘትን ይመርጡ ነበር፡፡ (በግማሽ ከኤፊቆሮሶች ጋር ሃሳባቸው ይዛመዳል፡፡ ሐዋ.17፥18 ፤ 32) ይህንን ክህደት በግልጽ ቅዱሳን ሐዋርያት ተቃውመውታል፡፡ (ቆላ.2፥21-23 ፤ 1ጢሞ.2፥11-15 ፤ 4፥1-5 ፤ ቲቶ.1፥15-16)        
4.    በመለኰታዊው ባህርይው አምላክ የሆነው ክርስቶስ በጥምቀት ጊዜ ኢየሱስ ከተባለው ሰው ጋር ተዳበለ፤ ኢየሱስ የተባለው ሰው በሞተ ጊዜ ደግሞ ትቶት ሸሸ የሚለው ሴሬንትያን ግኖስቲካውያን ሌሎች የዚሁ አንድ ክፍል ናቸው፡፡ ኢየሱስ በድንግልና ሳይሆን ከዮሴፍ እንደተወለደ ሲናገሩ ፤ ክርስቶስ ደግሞ መታመም የማይሻና ከሰው የማይወለድ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
5.    መዳን ከሥጋዊ አካል ማምለጥ ነው፡፡ ይህም ክርስቶስን በማመንና በደሙ መድኃኒትነት ሳይሆን በዕውቀት ኃይል ነው ይላሉ፡፡ ማለትም በእውቀት ደረጃቸው የሚድኑትን ሲስቀምጡ መዳን የሚገባቸው እነርሱ እንደሆኑና ክርስቲያኖች ነፍሳውያንና የመዳን ዕድል ያላቸው ሲሆኑ ሦስተኛዎቹና መዳን የማይቻላቸው አህዛባውያንና ሥጋውያን ናቸው፡፡
    እነዚህ በጣም ጥቂት የመናፍቅነት ትምህርት ማሳያዎች የእስከዛሬዎቹ መናፍቃን መነሻና መድረሻ ናቸው፡፡ ሁሉም መናፍቃን ከግኖስቲካውያን ዕሳቤና ክህደት ያልሸሹና በዚሁ ክህደታቸው ዙርያ መልካቸውን እየቀያየሩ የሚገለጡና የተገለጡ ናቸው፡፡
     ከግኖስቲካውያን መናፍቃን መካከል የተወሰኑ ግለሰቦች ከሚክዷቸው ዋና ዋናዎቹን መሠረተ እምነቶች ብናነሳ እንዲህ ይጠቀሳሉ፡፡

No comments:

Post a Comment