Thursday, August 27, 2015

ውግዘትና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት - ክፍል አራት

በዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
1.    ትምህርተ ሥላሴን መካድ

የነገረ መለኮት ተማሪዎች፣ “ትምህርተ ሥላሴ በመናፍቃንና በክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የቆመ የመለያ ሰንደቅ ነው፡፡” ይላሉ፡፡ ትምህርት ሥላሴ ለመኖራችንም ፤ ለመዳናችንም መሠረትና የፍጥረትን ዕድል ፈንታ፤ ጽዋ ተርታ ወሳኝ ትምህርት ነው፡፡ መናፍቃን ይህን ትምህርት በአንድም በሌላም መንገድ ይቃወማሉ፤ ይክዳሉ፡፡ ለምሳሌ፦
1.1. የሦስትነት አካላቱን ይክዳሉ

    አካል ፥ “ፍጹም ምሉዕና ቀዋሚ እኔ ባይ” ማለት ነው፡፡ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የአካልን ትርጉም “ፍጹም ገጽ፣ፍጹም መልክ ያለው፣ ራሱን የቻለ በራሱ የበቃ፣ እኔ የሚል ህላዌ፣ ነባቢ፣ ቁመት ቁመና፣ የባህርይ የግብር ስም ባለቤት እገሌ የሚባል፡፡ እኔ ማለትም የሚገባ ዕውቀት ላላቸው ለማይሞቱና ለማይጠፉ ለሦስቱ ብቻ ነው፡፡ ለአምላክ፣ ለመልአክ፣ ለነፍስ፡፡” በማለት በስፋት ያብራሩታል፡፡ (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/፤መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡(1948 ዓ.ም)፤አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡ ገጽ. 229)
    ሦስቱን ፍጹማን አካላት ሥላሴ ስንል የአንዱን እግዚአብሔር በአካላት ሦስት መሆን ወይም ሦስቱን አካላት አብ ፣ ወልድ ፣ መንፈስ ቅዱስን መጥራታችን ነው፡፡ “እውነተኛና ሕያው የሆነ አንድ አምላክ ብቻ አለ፡፡ ይህ አንዱ አምላክ በሦስት አካላት ስለሚኖር ሥላሴ የሚለው ቃል የአንዱን አምላክ የአካል፥ የስምና የግብር ሦስትነት ያመለክታል፡፡ (የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር(2002)፡፡የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9ኛ እትም፣አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡ ገጽ 64)
     አካል ከዓለመ ግዘፍ ጋራ መያያዝ የለበትም፡፡ ብዙ ጊዜ አካልን ከቁሳዊ ነገር ጋር ስለምናያይዝ ያለመረዳት ችግር ወይም ረቂቁ አካል የለውም ወደሚል እሳቤ እንሳባለን፡፡ ነገር ግን አካል የመያዝና የመጨበጥ ጉዳይ ሳይሆን ፈቃድ፣ ስሜትና ዕውቀት ያለው መሆኑንና ራሱን መግለጡ ከመቻሉ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ይህንን ስንል ግዙፉ አካል በግዙፍነቱ ረቂቁን መረዳት አይችልም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ጴጥሮስ ዘምስር እንዲህ ይላል፦
“ረቂቅ ነገርን መረዳት ወይም ማግኘት የሚቻለው በረቂቅ፤ ግዙፍ ነገርንመረዳት ወይም ማወቅ የሚቻለው በግዙፍ ነገር ነው፡፡”

     አካላት ስማቸው የሚቀያየርም አይደለም፡፡ ይህም ማለት አብ፥ አብ እንጂ ወልድ ወይም መንፈስ ቅዱስ፤ ወልድ፥ ወልድ እንጂ አብ ወይም መንፈስ ቅዱስ፤ መንፈስ ቅዱስ፥ መንፈስ ቅዱስ እንጂ አብ ወይም ወልድ ተብሎ አይጠራም፡፡ ይህ በሌላ አገላለጥ አብ የሚባለው አካል ከወልድና ከመንፈስ ቅዱስ ይለያል፤ ወልድም የሚባለው አካልም ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ይለያል፤ መንፈስ ቅዱስ የሚባለውም አካል ከአብና ከወልድ ይለያል፡፡

“የሥላሴ ገጻት በየአካላቸው ልዩ ሲሆኑ በመለኮት አንድነት ጸንተው ይኖራሉ፡፡  አንድ ሲሆኑ ሦስቱ አካላት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ስለመገለጣቸው ሦስትናቸውና፡፡”
(ሃይማኖተ አበው ዘዲዮናስዮስ ምዕ.10 ክ.1 ቁ.11)

     አካሉ የሚጠራው ሦስት  በመሆን ብቻ ነው፡፡ አስማተ አካላት ሦስት ናቸው ስንል በአካል ስሞች ብቻ ነው፡፡ በስመ ዋህድ ግን ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚሁ ጋር እነዚህ ሦስት ፍጹማን አካላት በአንድ ባህርና በእሪና (በዕኩልነት) ስለሚኖሩ ሦስት አማልክት አንልም፡፡
 “አብ አምላክ ነው፤ ወልድ አምላክ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው፡፡ ግን ሦስት አማልክት አይባሉም፤ አንድ አምላክ እንጂ፡፡”
 (ሃይማኖተ አበው ዘአትናቴዎስ ምዕ.25 ክ.1 ቁ.4)


   እግዚአብሔር አብ እግዚአብሔር ወልድ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ነው፡፡ ሦስት አካላት አንድ ሥልጣን፤ ሦስት ስሞች አንድ ፈቃድ፤ ሦስት ግብራት አንድ ምስጋና ያለው አምላክ ነው፡፡ ይህም ወላዲነትና አስራጺነት ፍጹማን አካላት ሥራ ማለታችን ነው፡፡
 “ስለሥላሴ የምንናገረው ሰዎች ስለሆን መናገርም ስላለብን ነው እንጂ የሰው ቋንቋ ሙሉ ለሙሉ ሊገልጠው የማይችል የእግዚአብሔር እውነት ነው፡፡”
                                  (ቅዱስ አውግስጢኖስ)

  “በምስጢረ ሥላሴ እግዚአብሔር በስም፣ በግብር፣ በአካል ሦስት፤ በባህርይ፣ በመለኰት፣ በህልውና አንድ መሆኑን እየገለጠ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ መሆኑን እየሰበከ አንድ ገጽ የሚሉ አይሁድንና ሰብዐልዮስን፣እስማኤላውያንን ወልድ ፍጡር የሚል አርዮስን፣ መንፈስ ቅዱስ ህጹጽ የሚል መቅዶንዮስን ሌሎችንም መናፍቃንን ከነወገኖቻቸው ይቃወማል፡፡”
                              (ሃይማኖተ አበው)

  “አብን ያለልጁና ያለመንፈስ ቅዱስ እግዚአብሔር ነው ብንል አላወቅነውም፤መንፈስ ቅዱስንም ያለአብና ያለወልድ እግዚአብሔር ነው ብንል አላወቅነውም፡፡”

                            (መዝገበ ሃይማኖት ምዕ.3 ቁ.20)

 አካላቱን ከሚክዱ መናፍቃን መካከል፦
1.1.1.    ሰብዓልዮስ

       ሰብዓልዮስ (217 ዓ.ም) በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ ከተነሱ መናፍቃን መካከል አንዱና ዋናው ነው፡፡ ይህም መናፍቅ ሦስቱን ፍጹማን የሥላሴን አካላት አንድ ናቸው በማለት ካደ፡፡ ይህን ትምህርቱን ወደሮም ለትምህርት በሄደ ጊዜ እንደተማረው ይነገርለታል፡፡ አንዱ አካል በተለያየ ዘመን ራሱን እየለዋወጠ፤ ቅርጹን እየቀያየረ ታየ ብሎ አስተማረ፡፡(ጎርጎርዮስ (ጳጳስ) ፤የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአለም መድረክ ፤ 1978፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ያልታወቀ፤ ገጽ 72) 
      ሰብዓልዮስ፣ “ኢየሱስ አምላክ ነው” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የንባብ ክፍሎችን ሳይቃወም በመቀበል፤ ነገር ግን “ኢየሱስ አምላክ ነው” ማለት ፥ “አብ አምላክ ነው” ማለት ነው ይላል፡፡ የአካል አንድነትን ለማስቀመጥ የኢየሱስን አምላክነት ሲቀበል ፤ ነገር ግን በሌላ አባባል ማለትም “ኢየሱስ ፍጡር ነው” ከሚለው አርዮሳዊ ትምህርት ጋር በቀጥታ ይጋጫል፡፡ ምክንያቱም “ለክርስቶስ መለኰትነት ከፍተኛ አጽንኦት በመስጠቱ ነው፡፡ የሰብዓልዮስ ትምህርቱ ቅርጻዊ ሞናርኪያኒዝም  “Modalistic Monarchianism” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የዚህ ትምህርት ዋነኛ ባህርይ “ አብም ወልድም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” የሚል ነው፡፡ በዚህም ሦስቱን ፍጹማንና ዘላለማውያን አካላት ፍጹም በመካድ በዋናነት ይታወቃል፡፡   
         ቤተ ክርስቲያን ግን፦
  “ በምስጢረ ሥላሴ እግዚአብሔር በስም፣ በግብር፣  በአካል ሦስት፤ በባህርይ፣ በመለኰት፣ በህልውና አንድ መሆኑን እየገለጠ አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ መሆኑን እየሰበከ አንድ ገጽ የሚሉ አይሁድንና ሰብዓልዮስን፣እስማኤላውያንን ወልድ ፍጡር የሚል አርዮስን፣ መንፈስ ቅዱስ ህጹጽ የሚልመቅዶንዮስን ሌሎችንም መናፍቃንን ከነወገኖቻቸው ይቃወማል፡፡”   (ሃይማኖተ አበው)

በማለት በግልጽ ትቃወማቸዋለች፡፡

1.1.2.   የይሖዋ ምስክሮች (የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማህበር)
(Watchtower Bible and Tract Society)

የእምነቱ መሥራች እንደሆነ የሚታወቀው የአሜሪካዋ ግዛት በሆነችው ፔንሳልቫንያ (Pensaylvznia) ስቴት ውስጥ ፒትስበርግ በሚባለው ከተማ ውስጥ በ1852 እ.ኤ.አ. የተወለደው ቻርልስ ታዝ ራስል(1852-1916) ነው፡፡ ይህ ሰው የግል ሕይወቱ2 ፈጽሞ ሥነ ምግባር የጐደለውና የተበላሸ ሲሆን ለእምነቱ መመስረት ጉልህ ድርሻ ያበረከተ ነው፡፡ በ1879 እ.ኤ.አ በእርሱ ጅማሬነት መታተም የጀመረው “የመጠበቂያ ግንብ” መጽሔት ዛሬ በአለም ሁሉ እየተሰራጨ ያለ የእምነቱ ዋና የትምህርት ማሰራጫ መንገድ ነው፡፡
    የሰብዓልዮስን ሀሳብ ትንሽ ያሻሻሉ በማስመሰል እንደወረደ የሚቀበሉት የይሖዋ ምስክሮች እግዚአብሔር ሦስት አካላት የሌለው አንድ አካል ይሖዋ(ያህዌ) ብቻ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህም “በሥላሴ ትምህርት መሠረት በአንድ አምላክ ሦስት አካሎች አሉ፡፡ በሌላም አነጋገር “አባት፣ ልጅና መንፈስ ቅዱስ የሆነ አንድ አምላክ አለ” ይባላል፡፡ ብዙዎች ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ነገሩ “ምስጢር” ብለው ቢናገሩም ይህንን ሃሳብ ያስተምራሉ፡፡  …. ለመሆኑ ኢየሱስ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ ያውቃልን? በፍጹም አላለም፡፡ … እንደእውነቱ ከሆነ ኢየሱስ ወደምድር ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ በፊት እንደጥንቷ ግብጽና ባቢሎን በመሳሰሉት ሥፍራዎች አማልክት በሦስት በሦሰት እየተደረጉ ወይም በሥላሴዎች መልክ ይመለኩ ነበር፡፡” በማለት ፍጹም የሆኑትን አካላት በግልጥ በመካድ ያስተምራሉ፡፡(በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ፡፡(WATCHTOWER BIBLE AND TRACT SOCIETY OF PENNSYLVANIA)፤ 1991፤ አሳታሚ WATCHTOWER BIBLE AND TRACT SOCIETY OF NEWYORK, INC. Brookly, New York, U.S.A.) ገጽ.39-40)
    ነገር ግን ታላቁ መጽሐፍ የጌታ እግዚአብሔርን ፍጹም የአካል ሦስትነት በማያሻማና በማያዳላ ቃል በግልጥ ያስተምረናል፡፡ ሐዋርያት የሥላሴን ስም፥ ጌታ ባዘዘው በታላቁ ተልዕኰና ደቀ መዛሙርቱ በሰጡት የስንብት ሠላምታ(ቡራኬ) ሦስቱን ፍጹማን ዘላለማውያን አካላት ስም ጠቅሰው ይመርቁና ይባርኩም እንደየርዕስ መክፈቻም ይገለገሉበት ነበር፡፡ (ማቴ.28፥18፤ 2ቆሮ.13፥14፤ ኤፌ.4፥4-7፤ 6፥23፤ 1ጢሞ.2፥3-6)
       አብ ፍጹም ገጽና አካል ያለው ገናና አምላክ ነው፡፡ አብ ፍጹም አምላክ(ኤፌ.1፥3፤ ዮሐ.17፥3)፣ አለምን አፍቃሪ(ዮሐ.3፥16)፣  ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን(1ቆሮ.8፥6)፣ የፈጠረንና የሁላችን አባት(ሚል.2፥10) በቅዱሳን ርስት በብርሃን እንድንካፈል ያበቃን(ቆላ.1፥12) ነውና፡፡ (በተጨማሪም ዘኅል.6፥24-26፤ መዝ.32፥5፤ ኢሳ.6፥3፤ ራዕ.4፥8 ይመልከቱ)
       ወልድ ፍጹም ገጽና አካል ያለው ገናና አምላክ ነው፡፡ ወልድ ሁሉ በእርሱ የሆነ፤ ከሆነውም አንዳች እንኳ ያለእርሱ ያልሆነ፤ ፍጥረት ሁሉ በእርሱ የተፈጠረ(ዮሐ.1፥3)፣ ኃያል አምላክ(ኢሳ.9፥6፤ ዮሐ.1፥1)፣ ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የዋጀ እግዚአብሔር(ሐዋ.20፥28፤ 1ጴጥ.1፥2)፣  የዘላለም አምላክና  ዙፋኑ እስከዘላለም ጸንቶና ነግሶ የሚኖር (መዝ.44፥6፤ ሉቃ.1፥33፤ ዕብ.1፥8)፣ የተባረከ ተስፋችንና አምላካችን(ቲቶ.2፥13)፣ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ህይወት ነው፡፡(1ዮሐ.5፥20)ቤዛነት አምላክነትን የሚጠይቅ ነውና፤ አለም የዳነውና የተቤዠው እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡(ማቴ.16፥26፤ 1ዮሐ.1፥7)
       መንፈስ ቅዱስ ፍጹም ገጽና አካል ያለው አምላክ ነው፡፡ አርነታችን(2ቆሮ.3፥17፤ ገላ.4፥6)፣ የእውነት መንፈስ ነውና መከልከል ሳይኖርበት በውስጣችን ሆኖ መዳናችንንና ልጅነታችንን የሚመሰክርልን(ዮሐ.14፥17፤ ዕብ.10፥15-16)፣ ወደእውነት እንድንመለስ ከሰይጣን ክስ እያስመለጠ የሚወቅሰን(ዮሐ.16፥9)፣ ክርስቶስ ያስተማረንን እውነትና የወንጌል ምስራችን የሚያስተምረንና የሚያስታውሰን(ዮሐ.16፥26) ወደእውነትም ሁሉ የሚመራን ቅን መሪያችን(ዮሐ.16፥13)አምላካችን ነው፡፡
       እርሱ በልዩ አካሉም በዮርዳኖስ በርግብ አምሳል (ማቴ.3፥16) የአዲስ ኪዳንን ቤተ ክርስቲያንን ሊመሠርትና ሊያጸና ደግሞ “እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች” ሆኖ በተለየ አካሉ ተገልጦ በደቀ መዛሙርቱ ላይ አድሮባቸዋል ወይም መልቶባቸዋል፡፡ (ሐዋ.2፥3)
      ስለዚህም አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ፤ አንድ አምላክ የሆኑ ሦስት ፍጹማን አካላት ያላቸው ናቸው፡፡ 
1.2.            “እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፤ አንድ አምላክ ነው” ማለትን ይክዳሉ፡፡

 የአዲሱ እምነት እንቅስቃሴ አማኞች (New age Movement) የክርስቶስን ፍጹም በመካድ “እኛ ራሳችን እግዚአብሔርን የምንመስልና የምንሆን፤ ደግሞም እግዚአብሔራን (ክርስቶሶች) ነን ብለው ያምናሉ፡፡
 የይሖዋ ምስክሮችም የወልድንና የመንፈስ ቅዱስን ፍጹም አምላክነት በመካድና በመቃወም ወልድን የአብ የመጀመርያ ፍጡር፤ መንፈስ ቅዱስን ደግሞ የወልድ ፍጡር እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ያስተምራሉም፡፡
 ሞርሞናውያን (የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ዘመን ቅዱሳን) መስራቹ አሜሪካ፤ ቬርሞንት በተባለ ትንሽ ስቴት ውስጥ በ1805 ዓ.ም የተወለደው ጆሴፍ ስሚዝ በተባለ ሰው፤ በኒውዮርክ ከተማ ውስጥ በ1829 ዓ.ም ነው፡፡ ጆሴፍ በግል ህይወቱ ከጥንቆላ ጋር በተያያዘ የሚታወቅ ፤ ግብረ ገብም የጐደለው ሰው እንደነበር የታሪክ ድርሳኑ ያስረዳል፡፡ ሞርሞናውያን ሥላሴን በተመለከተ ያለው እምነታቸውም በሥላሴ እናምናለን በማለት ሲያብራሩት ግን “አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንደ ሰብዓዊ ሟች ፍጡራን የተለያዩ አካላት ናቸው፡፡ ይህንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረ ይናገራሉ፡፡”
በመቀጠል “ሦሰት አምላኰች እንዳሉና ሥራቸውንም በሕብረት ሆነው እንደሚሠሩ ነው፡፡ እግዚአብሔር አብ እንደሰው ሥጋና ደም እንዲሁም አጥንት ያለው ነው፡፡ ኢየሱስ ደግሞ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት ሥጋን የለበሰ ሲሆን ሥጋና ደም የሌለው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው፡፡ እኒህም ሦስት አካላት ያላቸው ሳይሆኑ ከአንድ አካል በላይ አምላክ አካል የለውም፡፡”  ይህን በሞርሞን የኃይማኖት አንቀጻቸው በገጽ 29-50 ባለው ክፍል ላይ በግልጽ አስቀምጠውታል፡፡
     እኛ ግን ከንጹሑ የሕግና የእውነት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር ቃል እንደተማርን እንዲህ እንላለለን፦ በሦስት አካላት ያለው ቅዱስ እግዚአብሔር እርሱ አንድ አምላክም ነው፡፡ የአካል ሦስትነት እንጂ የባህርይ፣ የመለኮት፣ የሥልጣን … ሦስትነት የለበትም፡፡ ፍጥረትን የፈጠረ እግዚአብሔር፣ ዓለማትን በሠራዒነቱ የሚጠብቀውና በመግቦቱ የሚመግበው፣ የሰውን ልጅ ለማዳን በአባትነት ያፈቀረው አብ፤ መጥቶ ያዳነን ወልድ፤ ማዳኑን ለልባችን ያወጀልንና በልባችን የመሰከረልን መንፈስ ቅዱስም አንድ አምላክ፤ እርሱም መከፈል የሌለበት አንድ እግዚአብሔር ነው፡፡(ዘዳግ6፥4፤ 32፥39፤ 2ሳሙ.22፥32፤ ዮሐ.5፥44፤ ገላ.3፥20)
    መናፍቃን ሦስቱን ፍጹማን አካላት በመለያየት የሚክዱት ፥ ተዋረድ በመስጠት አንዱን ፈጣሪ ሌላውን ፍጡር ለማለት እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የሚደግፋቸው ሆኖ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አንድ፤ አምላካችንም አንድ አምላክ ነው፡፡

1.3.            “ፍጹም አንድ አምላክ አለ” የሚለውን ይክዳሉ፡፡


      እግዚአብሔርን ሦስት አካላት አለው የምንለው እንደአህዛብ አማልክትን የምናመልክ ሆነን አይደለም፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን እርሱ “ከእርሱም ሌላ አምላክ የሌለ”፣ “እኔ ብቻዬን እኔ ነኝ፤ እኔ እኔ ነኝ” (ዘጸ.3፥14፤ ዘዳግ.4፥35፤ 32፥39፤ ኢሳ.43፥11)፣ “እኔ ፊተኛ ነኝ እኔም ኋለኛ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም አምላክ የለም።  እንደ እኔ ያለ ማን ነው? … ” (ኢሳ.44፥6፤ ያዕ.2፥19፤ ራዕ.1፥8)፣ “እውነተኛ ፤ሕያውና የዘላለም ንጉሥ የሆነ አምላክ”(ኤር.10፥10፤ 1ተሰ.1፥9) እኒህና ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባትና ጥቅሶች እርሱ እግዚአብሔር መከፈል የሌለበት ፍጹም አንድ አምላክ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
   መናፍቃን ፍጹም አንድ አምላክ አለ ብለው የሚያምኑ ቢሆኑ እንኳ ይህን ትምህርታቸውን ሲያብራሩ ከተናገሩት በተቃራኒ ወይም ሥላሴነትን በአንድም በሌላም መንገድ በመካድና በመቃወም የሚያስተምሩ ናቸው፡፡
     እኒህ ጥቂት ማሳያዎች መናፍቃን ከትምህርተ ሥላሴ አንዱን ለመካዳቸው ማሳያዎች ናቸው፡፡ በደፈናው ይክዳሉ ከማለት እንዴት በሥላሴ እንደሚያምኑ ማብራሪያ ስንጠይቃቸው በአብዛኛው ከመናፍቅነት ባህርይ አንዱ ትምህርተ ሥላሴን ሲክዱ እናያቸዋለን፡፡

.....ይቀጥላል

1 comment:

 1. ወንድማችን ዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ! ያቀርብከው ጽሑፍ በጣም ትምህርታዊ ነው። ነገር ግን ይህ ሁሉ ትምህርት አንድ ሰው ይህንን ተምሮ ሕይወት የሚያገኝበት ትምህርት አይደለም። ምክንያቱም ሰዎች በዘመናችን ሆነ ባለፈውም ዘመን በራሳቸው ጥበብ የሚመሩበት ከንቱ የሆነ ትምህርትና እግዚአብሔር ልናገኝበት የማንችልበት የተወሳሰበ የሃይማኖት ትምህርት ነው። እግዚአብሔር ሰዎች በቀላሉ እርሱን ተረድተው ቃሉን ሰምተው ሕይወት እንዲያገኙ የተቀደሰውን ቃሉን በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ ለሁላችንም በሚገባን መልኩ ቃሉን መዝግቦ ያስተምረናል። ሰለዚህ ሕይወት የሚሰጠን የእርሱ ቃል ብቻ መሆኑን ተረድተን ሁላችንም ከተለያዩ የሰዎች ትምህርት ብንወጣ መልካም ነው። ስለ እግዚአብሔር ሶስትነት ወይም ሊሎቹ እንደሚሉት ሁለትነትና አንድነት በመከራከርና በመወጋገዝ ሕይወት ይገኛል???? መጽሀፉስ ምን ያስተምረናል?
  " 11 እኔ በአብ እንዳለሁ አብም በእኔ እንዳለ እመኑኝ፤ ባይሆንስ ስለ ራሱ ስለ ሥራው እመኑኝ።" (ዩሐ. ም14)። ይላል። በመቀጠልም አባታችን አምላካችን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚያስተምረን "15-16 ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤17 እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።" (ዩሐ. ም14)፡ ይላል። በቀላሉ አድርጎ በግልጽ እግዚአብሔር እንዲህ ያስተምረናል። ለምንድን ነው የማይረዱት የምይገባ የተወሳሰበ ነገር እርሳችንን የምናገባው??? ስለዚህ ይህንን የበለጠ እንድንረዳ ቅዱስ አባቶቻችን ሐዋርያት እንዲህ ሲሉ ይመክሩናል።
  " 22 ክርስቶስ አይደለም ብሎ ኢየሱስን ከሚክድ በቀር ውሸተኛው ማን ነው? አብንና ወልድን የሚክድ ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ነው።23 ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው።24 እናንተስ ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ጸንቶ ይኑር። ከመጀመሪያ የሰማችሁት በእናንተ ቢኖር፥ እናንተ ደግሞ በወልድና በአብ ትኖራላችሁ።25 እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው።26 ስለሚያስቱአችሁ ሰዎች ይህን ጽፌላችኋለሁ።27 እናንተስ ከእርሱ የተቀበላችሁት ቅባት በእናንተ ይኖራል፥ ማንም ሊያስተምራችሁ አያስፈልጋችሁም፤ ነገር ግን የእርሱ ቅባት ስለ ሁሉ እንደሚያስተምራችሁ፥ እውነተኛም እንደ ሆነ ውሸትም እንዳልሆነ፥ እናንተንም እንዳስተማራችሁ፥ በእርሱ ኑሩ።28 አሁንም፥ ልጆች ሆይ፥ በሚገለጥበት ጊዜ እምነት እንዲሆንልን በመምጣቱም በእርሱ ፊት እንዳናፍር በእርሱ ኑሩ።29 ጻድቅ እንደ ሆነ ካወቃችሁ ጽድቅን የሚያደርግ ሁሉ ከእርሱ እንደ ተወለደ እወቁ።" (1ኛ ዩሐ. ም2)። ይላል። ስለዚህ ይህ ከላይ አንድ ነው ሁለት ነው ሶስት ነው የሚለው ነገር ሳይምታታን የእግዚአብሔር ቃል እንደሚመክረን
  "12 ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም።" ስላለን የእግዚአብሔርን ቃል በመማር ልጁን በልቦናችን ማድረግ ይገባናል። ልጁም ካለን ደግሞ ሊላውም ነገር ሁሉ ከእኛ ጋር ይሆናል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል የተጻፈው እኛ ሁሉ እምነታችን በልጁ በክርስቶስ አምነን ሕይወት እንድናገኝ የተሰጠን ጸጋ መሆኑን ያስተምረናል።
  " 31 ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል።" (ዩሐ. ም20)። ይላል። አለበለዚያ ዝም ብለን በራሳችን ጥበብ ሶስት ነው ሁለት ነው አንድ ነው እያልን የምንወዛግብ ከሆን ከእግዚአብሔር ቃል በመራቅ የእግዚአብሔርን ጸጋ እናጣለን። በዚህም ክርስቶስ ኢየሱስ ወገኖቹን አይሁዳውያን በሚወቅስበት ወቅት እንደተናገረው።" 43 እኔ በአባቴ ስም መጥቻለሁ አልተቀበላችሁኝምም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እርሱን ትቀበሉታላችሁ።44 እናንተ እርስ በርሳችሁ ክብር የምትቀባበሉ ከአንዱም ከእግዚአብሔር ያለውን ክብር የማትፈልጉ፥ እንዴት ልታምኑ ትችላላችሁ?45 እኔ በአብ ዘንድ የምከሳችሁ አይምሰላችሁ፤ የሚከሳችሁ አለ፤ እርሱም ተስፋ የምታደርጉት ሙሴ ነው።46 ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና።47 መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?" (ዩሐ. ም5)። ይላል። ስለዚህ ዝም ብለን የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበትን መጽሀፍ አንብበን ስለ አምላካችን መረዳትና ሕይወት ማግኘት ያስፈልገናል። ሌላውን ለተመራማሪዎች ቦታውን መልቀቅ ይገባናል። እኛ ሕይወት የሚሰጠውን ኢየሱስ ክርስቶስን መመገብና ከእርሱ ጋር ተጣብቆ መኖር ያስፈልገናል። ምክንያቱም ልጁ ያለው ሕይወት አለው፤ የእግዚአብሔር ልጅ የሌለው ሕይወት የለውም ብሎ መጽሀፉ ያስተምረናል። አመሰግናለሁ!

  ReplyDelete