Wednesday, September 30, 2015

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በጎ ጅምሮችና ቀሪ የቤት ሥራዎችየአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መስከረም 13/01/08 በቤተ ክህነት ትልቅ ግብዣ አደረገ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባል በሚችል መልኩ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎችን ምክትል ሊቃነ መናብርትን ጸሐፊዎችን ሂሳብ ሹሞችን በመጥራት ከዱባይ ዘመናዊ መኪናዎች ከቀረጥ ነፃ በማድረግና 12 ሚሊዮን በላይ በማዳን እንዲገቡ ጥረት ያደረጉት ለሊቀ ጠበብት ኤልያስ እና ለሊቀ ትጉሃን ታጋይ ባደረጉት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ልዩ የወርቅ ተሸላሚዎች ሆነዋል፡፡ ባጠቃላይ መልኩ ዘርፈ ብዙ የሆነ ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን ፐርሰንት ለከፈሉ አድባራት ሽልማት፣ ሊቀጠበብት ኤልያስ ላሰለጠናቸው የአድባራት የሂሳብ አያያዝ ደብል ኢንትሪ ሥልጠና ወስደው የተመረቁ ሠራተኞች የሰርተፍኬት ሽልማት ፕሮግራም የተካተተበት ዝግጅት ነበር፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የሃገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ለተገዙት ዘመናዊ መኪናዎች የአድባራት አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ እውቅናና ክብር በመስጠት ባደረጉት ንግግር በእድምተኛው ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትና አድናቆትን አግኝተዋል፡፡ በዝግጅቱ ላይ የላመና የጣፈጠ ምግብ ቢቀርብም በተሰብሳቢዎች ዘንድ ግን ልዩ ትርጉም ያገኘው ገንዘብ አምጡ ከማለት አልፎ ምንም ብሎ የማያውቀው ሀገረ ስብከት አሁን “የተገኘው ሃብትና ንብረት በእናንተ ምክንያት የተገኘ በመሆኑ እውቅናውም ክብሩም ለእናንተ ይገባል” ብሎ ባልተለመደ መልኩ የአድባራት ሠራተኞችን፣ ምክትል ሊቃነ መናብርትና ሂሳብ ሹሞችን ጠርቶ ኑ ዕውቅና እንስጣችሁ ተጋበዙ ደስ ይበላችሁ የእናንተ ውጤት ነው ማለቱ የመጀመሪያ በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡

Friday, September 25, 2015

ባለቤት አልባው ደብር


Read in PDF
ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በብዙ ፈተና ውስጥ የምትገኝበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ከፈተናዎቿ አንዱና ዋናውም ሙስና መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ሙስናውን የሚፈጽሙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ በሕጋዊም በሕገወጥም መንገድ የተሰገሰጉና ለቤተክርሰቲያን ሳይሆን ለግል ጥቅማቸው የቆሙ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደዘገብነው የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን አንዱ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑ ሕገወጥ አሰራር የሰፈነበት ባለቤት የሌለው ቤት ሆኗል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቤተክርስቲያኑን በባለቤትነት እየመሩ ያሉት ቤተክርስቲያንን መምራት ያለባቸውና ህጋዊ መብቱ ያላቸው ሳይሆኑ በቤተክርስቲያን ሀብትና ንብረት እየነገዱና እያተረፉ ያሉት የሰንበቴ ማኅበራት አመራሮችን ከፊት አሰልፈው ያዘመቱና ከኋላ ሆነው አመራር የሚሰጡ የታገዱ የሰበካ ጉባኤ አባላት ናቸው፡፡
በደብሩ ውስጥ የሚገኙ የሰንበቴ ማህበራት በተለይም የገብርኤል፣ የመድኃኔ ዓለም፣ የማኅበረ በኩር፣ ትልቁና የከበርቴዎቹ የእግዚአብሔር አብ ማኅበር ሰንበቴ ቤቶች ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰንበቴ ቤቶች አመራሮች በቤተሰባቸው ቁጥር ልክ የመቀበሪያ ፉካ ያላቸው ሲሆን፣ መሬቱ የቤተክርስቲያን ቢሆንም የአጥቢያው አስተዳደር ፈጽሞ የማይቆጣጠረውና የማይመለከተው ነው፡፡ አንዱ ፉካ እስከ 40 ሺ ብር የሚሸጥ ሲሆን አስከሬን ከውጭ ከመጣ ደግሞ በእጥፍ ይሸጡታል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ከገቢው ለደብሩ በፐርሰንት እንኳ አይከፍሉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ትግል አድርገው የነበሩት አሁን ኮተቤ ገብርኤልን እያስተዳደሩ ያሉት የቀድሞው አለቃ እያንዳንዱን ፉካ ያለውን የሰንበቴ ማህበር እስከዚያ ጊዜ ድረስ የሸጡትን በማስላት ብር 3 መቶ ሺ (300,000) እንዲከፍሉ አስወስነው ነበር፡፡ ነገር ግን ሆዳቸውን በወደዱ ጥቂት ጥቅመኛ ካህናት ውሳኔው ተቀለበሰ፡፡

Wednesday, September 23, 2015

በእንተ ዝንቱ ዐለዉ ሕገከ ወኢይወፅእ ፍትሐ ጽድቅ...

“በእንተ ዝንቱ ዐለዉ ሕገከ ወኢይወፅእ ፍትሐ ጽድቅ፥  እስመ ኃጥእ ይትዔገሎ ለጻድቅ በእንተ ዝንቱ ይወፅእ ፍትሕ ግፍቱዕ፡፡” ትርጉም፡- “ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፥ ፍርድም ድል ነሥቶ አይወጣም ኃጢአተኛ ጻድቅን ይከብባልና ስለዚህ ፍርድ ጠማማ ሆኖ ይወጣል።” ትንቢተ ዕንባቆም ምዕራፍ 1 ቁጥር 4

አለበል ከአሰላ
ይድረስ ከአባ ሰላማ ድረ ገጽ ይህን ጽሑፍ እንደምታወጡልኝ በመተማመን ልኬላችኋለሁ፡፡
ከላይ በርእሱ የተጠቀሰውን የነቢዩን የዕንባቆም ጩኸት የሚጮህ ሰው ዛሬም አይጠፋም፡፡ በነቢዩ ዘመን እንደ ነበረው ዛሬም ሕግ ላልቶ ይታያል፣ ፍርድም ድል ነስቶ አይወጣም ኃጢአተኛ ጻድቅን የመክበቡ ነገር ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ፍርድም እየተጣመመ ነው፡፡ ይህን ከምናይባቸው ሀገረ ስብከቶች መካከል የአርሲ ሀገረ ስብከት አንዱ ነው፡፡ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ውስጥ አለቦታቸው የተቀመጡና ጊዜ የሰጣቸው ሙሰኞች ወንጀላቸው ተከድኖ እንዲቀርና በአልጠግብ ባይነት የግል ጥቅማቸውን ለማሳደድ እንዲረዳቸው የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ በተለይም እውነተኞችን አለስማቸው ስም ሰጥተው ማሳደድ አድማ መምታትና በአድማ ቃለ ጉባኤ ተፈራርመው ጭምር አላስበላ ያላቸውን እውነተኛ ሰው ማሳደድ እስከ በላይ ድረስ በሐሰት አቤት ማለት የዕለት ተዕለት ስራቸው ነው፡፡  
እንደዚህ ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በቅርቡ በሀገረ ስብከታችን ውስጥ የሀገረ ስብከቱ ዋና ፀሐፊ እና ዋና ሥራ አስኪያጅ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባትና ምክንያቱን ለማንሳት ነው፡፡ ጉዳዩን ከማንሳቴ በፊት ትንሽ የግለሰቡን ሕይወት ታሪክ ወይም መንፈሳዊ ህይወትን እና መንፈሳዊ ዕውቀትን ላንሳ፡፡
የሀገረ ስብከቱ ዋና ፀሐፊ አቶ ታምራት ይባላሉ የተወለዱትና ያደጉትም በዚያው ከተማ ሲሆን በቅጡም ባይሆን በዚያው ከተማ በሚገኘው በአሰላ መድኃኔ ዓለም ቤ/ክ ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ አባል ነበሩ፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤቱ ውስጥም ከበሮ ሲደለቅ ከማጨብጨብ በቀር የተማሩት ትምህርት የለም፡፡ ምንም ዓይነት የቤተ ክርስቲያን ክህነትና ትምህርት እንደሌላቸውም ይነገራል፡፡

Wednesday, September 16, 2015

ውግዘትና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት - ክፍል አምስት


Read in PDF 
በዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
2.   ትምህርተ ሥጋዌን መካድ
     የክርስትና መሠረት የቆመበት ዋናው ዐለት ፤ ሌሎችንም ምስጢራትና ትምህርቶች ደግፎ የያዘው ማዕከላዊው ትምህርት ክርስቶስ ሰው የሆነበት ቅዱስ ምስጢር፤ ትምህርተ ሥጋዌ ነው፡፡ አንድ አባት ስለመናፍቃን የመዳን ትምህርት ስህተት መነሻነት ሲናገሩ፥ “የመናፍቃን ትምህርት አንድ የሚሆኑበትና የሚገናኙበት፤ አንተን የምታድነው አንተ ነህ ማለታቸው ነው፡፡” ይላሉ፡፡
      ስለሰው ውድቀት ስናነሳ የመጀመርያውን ሰው አዳምን ስናነሳ፤ የሰውን ልጅ ትንሳኤና ሕይወትን ስናነሳ ደግሞ ሁለተኛውን አዳም ክርስቶስን ማንሳታችንና ፦
-      በሥጋ የተገለጠ፥
-      በመንፈስ የጸደቀ፥
-      ለመላእክት የታየ፥
-      በአሕዛብ የተሰበከ፥
-      በዓለም የታመነ፥
-      በክብር ያረገ።(1ጢሞ.3፥16)
ብለንም መስበካችን ትልቅ ፍቅሩ ግድ ይለናል፡፡  
     ነገረ ሥጋዌ ማዕከሉ ቅዱሳንን ጨምሮ ሰው በራሱ ጽድቅ መዳን ስላልቻለ (ኢሳ.64፥6) ፣ በህጉ ነቀፌታ ተገኝቶብን ከኃጢአት ወገን ሆነን ስለተከሰስን(ሮሜ.3፥9፤ ገላ.3፥22)፣ ጻድቅ ፤ አስተዋይ ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ፤ ቸርነት የሚያደርግ አንድ እንኳ ስለጠፋና በአንድነት የማይጠቅሙ ስለሆኑ (መዝ.13፥2-3 ፤ 52፥2 ፤ ሮሜ.3፥11-13) ፣ ደካሞች ፤ ኃጢአተኞችና ጠላቶች ሆነን ስለተገኘን (ሮሜ.5፥6-10) … ከእግዚአብሔር በቀር እኛን ማዳን የሚቻለው ከሰማይም ከምድርም ፤ ካመኑትም ካላመኑትም ወገን ስለጠፋ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ እኛን ለማዳን መጣ የሚለው ነው፡፡
      የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር፤ ክርስቶስ ኢየሱስ መምጣት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ህዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸው ፣ የዲያብሎስንም ሥራ ያፈርስ ፣ እንዲያው በጸጋው በቤዛነቱ በኩል ከኃጢአት ሁሉ የሰው ልጆችን ያድነንም ፤ ያጸድቀንም እንዲሁም ከሰይጣንና ከኃጢአት ባርነት ፣ ከዘላለም ሞት ፤ ከኩነኔ ፍርድ ከገሃነምም ፍርድ ያድነን ዘንድ ነው፡፡ (ማቴ.1፥21፤ ሉቃ.2፥11፤ 1ዮሐ.3፥8 ፤ ሮሜ.3፥24 ፤ ቲቶ.3፥7 ፤ 1ጴጥ.2፥9 ፤ ሮሜ.8፥1-4፤ ዕብ.2፥14 ፤ ቆላ.1፥13 ፤ ሮሜ.8፥33 ፤ ዮሐ.5፥24)
    ይህን ፍርድና የዘላለም ቁጣ ማምለጥ የምንችለው ደግሞ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ኃጢአተኝነታችንን አውቀን በእውነተኛ ንስሐ ተጸጽተን ከክፉ መንገዳችን ስንመለስና ክፉውን በመጠየፍ ከበጎ ነገር ጋር ስንተባበር (ሉቃ.19፥6-10 ፤ ሐዋ.2፥38 ፤ 3፥19-20 ፤ ሮሜ.3፥11-18 ፤ 23 ፤ 12፥9 )፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ሞታችንን እንደለወጠና በትንሳኤው ደግሞ ህይወትን እንደሰጠን ማመን (ሐዋ.16፥25 ፤ ሮሜ.4፥23-25  ፤ 6፥8-11) ፣ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመናችን የዘላለም ህይወትን እንደሰጠንና ልጆቹ እንዳደረገን ማመን (ዮሐ.1፥12 ፤ 3፥16 ፤ ሮሜ.10፥9) ሲቻለን ነው፡፡

Sunday, September 13, 2015

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ ሰንበት ት/ቤቶች 13ኛ ዓመታዊ አንድነት ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ


Read in PDF 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ ሰንበት ት/ቤቶች 13ኛ ዓመታዊ አንድነት ጉባኤ ከነሐሴ 29 - ጳጉሜ 1/2007 በመካነ ሰላም መድኃኔ ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ካቴድራል ኦክላንድ ካሊፎርኒያ በተሳካ ሁኔታ ተካሄደ፡፡ “ለእግዚአብሔር መቅናት” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው 13ኛው ጉባኤ በተለያዩ መምህራን የተዘጋጁ ትምህርቶች የተሰጡበትና ውይይቶችም የተካሄዱበት ነበር፡፡ ትምህርቶቹ መሪ ቃሉን አጉልተው ያወጡና ለአብዛኞቹ ታዳሚዎች ከፍተኛ መንፈሳዊ መነቃቃትንና በባዶ ሳይሆን በዕውቀት ለእግዚአብሔር መቅናት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከፍተኛ ግንዛቤ የተጨበጠበት ነበር፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ የተገኙትና ጉባኤውን በቡራኬ የከፈተቱት ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ ሲሆኑ ብፁዕነታቸው “በጉባኤው ላይ የተሳተፉት 150 ወጣቶች ቢሆኑም የሰንበት ትምህርት ቤቶቹ ኅብረት ካሳለፈው 13 ዓመት ዕድሜው አንጻር በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በጉባኤው ላይ የታደሙትን የሰንበት ተማሪዎቹንም “እናንተ የቤተ ክርስቲያን ተረካቢዎች ናችሁ” ብለዋል፡፡

Friday, September 11, 2015

“ወትባርክ አክሊለ ዓመተ ምሕረትከ - በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ” (መዝ. 65፡11)         ዓመትን በቸርነቱ የሚያቀዳጅ እግዚአብሔር ነው፡፡ በራሱ ኀይል 2007 ዓ.ም.ን ፈጽሞ ወደ 2008 ዓ.ም. የተሸጋገረ የለም፡፡ ይህን ዓመት ሳያዩ በሞት የተወሰዱ እጅግ በርካቶች ናቸው፡፡ በሕይወት ያለነውም ከእግዚአብሔር ቸርነት የተነሣ እንጂ ስለሚገባን አይደለም፡፡ በክርስቶስ ያመንን እስከሆንን ድረስ ግን ብንኖርም ብንሞትም የጌታ ነን፡፡ እግዚአብሔር ዕድሜ የሚጨምርልን ክርስቶስን በማመን ጸንተን ከእምነት የሚነሣው መታዘዝ በሕይወታችን እንዲገለጥ ነው፡፡  ስለዚህ በአዲሱ ዓመት እንዲህ እንድንሆን ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን፡፡ ዓመቱን በቸርነቱ ያቀዳጀን ጌታም ፈቃዱን መፈጸም የሚያስችለውን ጸጋ እንዲያበዛልን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን፡፡ 

                 እንኳን ለ2008 ዓ.ም. በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ!!

Wednesday, September 9, 2015

የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው ወገኖቻችን ትኩረት ሊያገኙ ይገባል!በዲ/ን ኒቆዲሞስ
ከወር በፊት የኢትዮጵያ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማኅበር/Ethiopian National Association on Intellectual Disabilities ‹‹እኛም እንችላለን!›› በሚል መሪ ቃል በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ ባደረገው ዓመታዊ በዓል ላይ ተግኝቼ ነበር፡፡ በዚህ ዝግጅት ላይም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ተወካዮች፣ የኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው ልጆችና ቤተሰዎቻቸው፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለ ሙያዎችና የጥበብ ሰዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶችም ተገኝተው ነበር፡፡
በዚህ በዛሬው አጠር ያለች ትዝብት አከል ጽሑፌ በዕለቱ የኢትዮጵያ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው ብሔራዊ ማኅበር በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ አከናውኖት በነበረው ዓመታዊ በዓልና በአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ባለባቸው ወገኖቻችን ዙርያ ጥቂት አሳቦችን ለማንሳት ወደድኹ፡፡
ጽሑፌን ካነሣሁት ርዕሰ ጉዳይ ጋር በቀጥታ ተያያዥነት ባለው አንድ ገጠመኜ ልጀምር፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት የጠበል ሥፍራ አንድ ዕድሜው በሠላሳዎች አጋማሽ አካባቢ ከሚገኝ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ካለበት ትሑት ወጣት ጋራ ተዋውቄ ነበር፡፡ ታዲያ የዚህ ወጣት የኑሮ ኹናቴ ውስጤ ጥያቄ ፈጠረብኝና ላነጋግረው ወሰንኩ፡፡ ምንም እንኳን ይህ ወጣት እምብዛም ለመነጋገር ባይችልም ቤተሰብ እንዳለውና ቤተሰቡም ቦሌ አካባቢ የሚኖሩ ባለጠጋዎች እንደሆኑና ወደዚህ ከመጣም አምስት ዓመታትን ያህል እንዳስቆጠረ እየተኮላተፈ ነገረኝ፡፡
ወጣቱ በጥሩ ምቾት የተያዘ እንደሆነ ተክለ ሰውነቱና ገጹ ይመሰክራል፡፡ ቤተሰዎቹ አንድ ሙሉ ግቢ ተከራይተውለት በዛ ባማረ ግቢ ውስጥ ከሚንከባበከበው የአንድ የገጠር ሰው ከሆነ ጎልማሳ ጋራ ነው አብሮ የሚኖረው፡፡ ከዚህ ወጣት ጋራ የነበረኝን ጨዋታ ለአፍታ ገታ አድርጌ በቂ ሆነ መረጃ ለማግኘት በማሰብ እንክብካቤ የሚያደርግለትን ጎልማሳ አነጋገርኩት፡፡ እርሱም የወጣቱ ቤተሰዎች የቅርብ ዘመድ እንደሆነና ለእርሱም ዘመዱና ወገኑ የሆነውን ይህን ወጣት ለመንከባከብ በደመወዝ የተቀጠረ እንደሆነ አጫወተኝ፡፡ ምግብ ከማብሰል ጀምሮ ሁሉንም እንክብካቤ ለዚህ ወጣት የሚያደርግለት ይህ ሰው ነው፡፡

Sunday, September 6, 2015

አክራሪነት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መኖሩን የቤተክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ገለጹ


 Read in PDF

አክራሪው ሃይልም ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑን ማሳያዎቹ ጠቁመዋል
በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች በተዘጋጀው ሥልጠና ላይ በተደረገው ውይይት ሁሉም ተወካዮች በሚያሰኝ ሁኔታ አክራሪነት መኖሩን ገለጹ፡፡ ከ900 መቶ በላይ ተሳታፊዎች በ10 ቡድን ተከፍለው በአክራሪነት መንስኤዎች መገለጫዎችና በመፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ባደረጉት ውይይት ያለው ተጨባጭ ሁኔታ አክራሪነት መኖሩን እንደሚያሳይ በውይይቶቹ የተደረሰባቸው ድምዳሜዎች አመልክተዋል፡፡ በቡድን አወያዮች የቀረቡት ሪፖርቶች ስም አይጥቀሱ እንጂ አክራሪው ቡድን ማቅና ከእርሱ ጋር ንክኪ ያላቸው ክፍሎች መሆናቸውን እንደሚያሳይ ብዙዎች ተስማምተዋል፡፡
በቡድን 1 በአራዳና ጉለሌ ክ/ከ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች
1.     ቃለ አዋዲውን  አንቀበልም ቅዱስ ፓትርያርኩ የሾሟአቸውንም አንቀበልም ብሎ ሁከት መፍጠር
2.    በዐውደ ምህረት ድምፅ ማጉያ እስከመንጠቅ የደረሰ የሀይል እርምጃ መውሰድ
3.    የሥም ማጥፋትና የሀይል እርምጃ ለመውሰድ ማስፈራራት
4.    አሳሳች መልእክቶችን መጠቀም ለምሳሌ የሃይማኖት ጥያቄ አልተመለሰልንም በማለት ሌላ ቅስቀሳና አድማ ማድረግ
5.    ህግን ለማስከበርና የቤተ ክርስቲያንን ሰላም ለማስከበር የሚንቀሳቀሱትን የቤተክርስቲያን ኃላፊዎች ፖለቲከኛ (ወያኔ) በማለት ማስወራት
6.    በቤተ ክርስቲያን ሞዴላ ሞዴል አለመጠቀምና ለህገ ቤተ ክርስቲያን ተገዢ አለመሆን
እንደ መፍትሔ የቀረበው አንዱ ሐሳብ ወጣቶች ለሕግ እንዲገዙ አበክረን ማስተማር አለብን የሚል ነው፡፡

Friday, September 4, 2015

በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተዘጋጀው የሁለት ቀናት ሥልጠና እየተካሄደ ነው Read in PDF
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር በሚገኙ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ካህናት ሰባክያን የሀገረ ስብከቱ ተወካዮችና ሌሎችም ከ900 በላይ የሆኑ የተሳተፉበትና በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተዘጋጀው የ2 ቀናት ስልጠና በትናንትናው ዕለት ተጀመረ፡፡ በሥልጠናው ላይ የተገኙት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያምና “በሃይማኖት ተቋማት ያለመግባባት ጉዳዮች መሠረታዊ የመፍትሄ አቅጣጫ” በሚል ርእስ በሚንስትሩ የቀረበውና በውይይት እንዲዳብር የሚጠበቀው ጥናት የተሳታፊዎችን ትኩረት ስቦ እንደነበር ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ የቡድን ውይይቶችም ተካሂደዋል፡፡
በጥናቱ ላይ እንደተመለከተው በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ እየታየ ያለው አለመግባባት መልኩን እየለወጠ መምጣቱን በሚመለከት “ከዚህ ቀደም አልፎ አልፎ እንደሚታየው [በሃይማኖት ተቋማት መካከል ወይም] በመካከላቸው ሳይሆን በውስጣቸው አይሎ የሚታይበት ሂደት እየተስተዋለ መጥቷል፡፡” ለዚህም አንዱ ምክንያት የሃይማኖት ተቋማትን “መንፈሳዊና ሰላማዊ ተልእኮ ለራሳቸው በሚመቻቸው ትርጉም አዛብተው በማቅረብ አንዱን የሃይማኖት ተከታይ በራሱ እምነት ውስጥም ይሁን ከሌሎች ሃይማኖቶችና እምነቶች ጋር ጠላትነትን በማሥረጽ ከተከታዩ ፍላጎት በተቃራኒው ሕዝብና ሕዝብ እንዲጋጭ ለማድረግ የሚጠቀሙ የሃይማኖት አመራሮች የሚታዩበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም፡፡” በማለት ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ አክራሪነት የሚንጸባረቅ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

Wednesday, September 2, 2015

“መድሎተ ጽድቅ” በመድሎተ ጽድቅ ሲመዘን - ክፍል አራትምንጭ፡- http://www.chorra.net/
“መድሎተ ጽድቅ” በምዕራፍ አንድ፥ በ1.1 ላይ “የተሐድሶዎች መነሻዎችና መሠረቶች” በሚለው ርእስ ሥር የሚገኘውን ንኡስ ርእስ “1.1.1 በ ‘መሰለኝ’ ማመን” ብሎታል፡፡ በዚህ ንኡስ ርእስ ሥር የቀረበው ሐተታ፥ እኛ ሃይማኖትን ያኽል መሠረታዊና ጥልቅ ጕዳይ “ለእኛ የመሰለንን” እያልን እንደ ስብሰባ አስተያየት እምነታችን ለእኛ የመሰለን ሐሳብ ወይም ግምት እንደ ኾነ አድርገን እንደ ጻፍን በማስመሰል፥ በልል ግስ የተጻፉትንና ማስረጃ የሚላቸውን ከየ መጽሔቱና ከየ መጻሕፍቱ ጠቃቅሷል፡፡ ስለዚህ በዚህ ክፍል ይህን ጕዳይ እንመረምራለን፡፡ በመጀመሪያ የጠቀሰው የሚከተለውን ነው፡፡   
·        ለያንዳንዳችን የመሰለንንና ያመንበትን ከሊቃውንትም የተማርነውን ሐሳብ እውነት መኾኑንና ጠቃሚነቱን ከተቀበልነው ዘንድ ለሌሎች ማስገንዘብ ይገባል በማለት እነሆ  ጮራ’  የተሰኘውን መንፈሳዊ መጽሔት ለማሳተም ተነሥተናል፡፡” (ጮራ ቊጥር 1 ገጽ 3)
በመሠረቱ እምነት በመሰለኝ የሚቆም ነገር አለ መኾኑ ለማንም ግልጥ ነው፡፡ ሰው ከወላጆቹ ከሚወርሰው ሃይማኖት ባሻገር በሃይማኖቱ ውስጥ ሲኖር በራሱ ያወቀውንና የተረዳውን እውነት ያምናል፡፡ ከተገለጠለትና በቃሉ መሠረት ማረጋገጫ ከቀረበለት እውነት ውጪ ያሉትንና ማረጋገጫ ያልተገኘላቸውን ጕዳዮች ለመመርመር ሲሞክር ግን በመሰለኝ ነው እንጂ “ነው” በሚል ርግጠኛነት አይደለም፡፡ ስለዚህ ገለጣው “እንዲህ ሊኾን ይችላል” “እንዲህ ይመስላል” ወዘተ. የሚል ይኾናል፡፡ ለምሳሌ “መድሎተ ጽድቅ” በገጽ 34 ላይ የጠቀሰውና ከጮራ ቊጥር 11 ገጽ 5 ላይ የወሰደውን እንመልከት፡፡ በዚህ ክፍል ስለ ሰብአ ሰገል መምጣትና ስለ ማንነታቸው ተጽፏል፡፡ የሰብአ ሰገል ወደ ቤተ ልሔም መምጣት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመዘገበ እውነት በመኾኑ ርግጠኛ በኾነ ቃል “ጠቢባኑ (ሰብአ ሰገል) ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ” ተብሎ ነው የተገለጠው እንጂ፥ በመሰለኝ “መጥተው ሊኾን ይችላል” ወይም “ሳይመጡ አልቀረም” ወዘተ. ተብሎ በአስተያየት መልክ አይደለም የቀረበው፡፡ ስለ ማንነታቸው ግን መጽሐፍ ቅዱስ “ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም” መምጣታቸውን ብቻ ነው እንጂ አገራቸው የት እንደ ኾነ፥ ከማን ወገን እንደ ኾኑ ወዘተ. ርግጠኛውን ነገር አይናገርም፡፡
ይህን በተመለከተ ልናደርግ የምንችለው የመጀመሪያው ነገር መጽሐፍ ቅዱስ የገለጠውንና “ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ” የሚለውን ብቻ ተቀብሎ ማመንና መጽሐፉ ያልገለጠውን ነገር ለመግለጥ አለ መሞከር ነው፡፡ ኾኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠንን ፍንጭ መነሻ በማድረግ ነገሩን ማጥናትና መላ ምታችንን ማስቀመጥ የምንችልበት ዕድል የተዘጋ አይደለም፡፡ ስለዚህ ኹለተኛውን አማራጭ የምንከተል ከኾነ የደረስንበትን መላ ምት “ነው” በሚል ርግጠኛ ቃል ሳይኾን፥ “ሊኾን ይችላል” በሚል ልል ግስ ነው መግለጥ ያለብን፡፡ በጮራ የተደረገውም ይኸው ነው፡፡ ርግጡንና የታመነውን ነገር “ነው” እንላለን፤ ርግጠኛ ያልተኾነበትንና በእኛ መረዳት የደረስንበትን ጕዳይ ግን “ሊኾን ይችላል” እንላለን፡፡ ይህም እምነታችንን ርግጠኛ ባልኾነና በመሰለን ነገር ላይ እንዳሳረፍን ተደርጎ የሚወሰድና የሚያስወቅሠን ሊኾን አይገባም፡፡
ሊቀ ጠበብት አያሌው ታምሩ “የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት” የተሰኘውን መጽሐፍ ለመጻፍ ካነሣሡአቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የውጪ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች የጻፏቸውን ተርጕመው ያሳተሙና ያሠራጩ ኢትዮጵያውያን ጸሓፊዎች “ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን መኾናቸውንና የትንቢቱ ባለቤቶች መኾናቸውን ክደው የሌላ አገር ሰዎች በድንገት የተጠሩ አረመኔዎች እንደ ነበሩ” መናገራቸው መኾኑን ገልጠው ነበር (1953፣ 17፡ 111)፡፡ እንደ እርሳቸው እምነት ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን ሊኾኑ ይችላሉ ሳይኾን በርግጠኛነት ኢትዮጵያውያን “ናቸው”፡፡ ኢትዮጵያውያን ናቸው ለማለትም በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ከእነርሱ ጋር ተያይዘው ያልተጠቀሱና “ኢትዮጵያ” የሚል ስም ይዘው የተጻፉ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን አስደግፈው ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን መኾናቸውን ለማሳመን ይሞክራሉ፡፡ ይኹን እንጂ ሰብአ ሰገል ወደ ቤተ ልሔም የመጡት ከምሥራቅ መኾኑ ስለ ተገለጠ፥ ከኢየሩሳሌም ወደ ደቡብ 9 ኪሎ ሜትር ርቃ ለምትገኘው ቤተ ልሔም (የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 1972፣ ገጽ 97) ኢትዮጵያ በምሥራቅ ልትገኝ አትችልምና ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን ናቸው የሚለውን መቀበል ያስቸግራል፡፡