Wednesday, September 16, 2015

ውግዘትና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት - ክፍል አምስት


Read in PDF 
በዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
2.   ትምህርተ ሥጋዌን መካድ
     የክርስትና መሠረት የቆመበት ዋናው ዐለት ፤ ሌሎችንም ምስጢራትና ትምህርቶች ደግፎ የያዘው ማዕከላዊው ትምህርት ክርስቶስ ሰው የሆነበት ቅዱስ ምስጢር፤ ትምህርተ ሥጋዌ ነው፡፡ አንድ አባት ስለመናፍቃን የመዳን ትምህርት ስህተት መነሻነት ሲናገሩ፥ “የመናፍቃን ትምህርት አንድ የሚሆኑበትና የሚገናኙበት፤ አንተን የምታድነው አንተ ነህ ማለታቸው ነው፡፡” ይላሉ፡፡
      ስለሰው ውድቀት ስናነሳ የመጀመርያውን ሰው አዳምን ስናነሳ፤ የሰውን ልጅ ትንሳኤና ሕይወትን ስናነሳ ደግሞ ሁለተኛውን አዳም ክርስቶስን ማንሳታችንና ፦
-      በሥጋ የተገለጠ፥
-      በመንፈስ የጸደቀ፥
-      ለመላእክት የታየ፥
-      በአሕዛብ የተሰበከ፥
-      በዓለም የታመነ፥
-      በክብር ያረገ።(1ጢሞ.3፥16)
ብለንም መስበካችን ትልቅ ፍቅሩ ግድ ይለናል፡፡  
     ነገረ ሥጋዌ ማዕከሉ ቅዱሳንን ጨምሮ ሰው በራሱ ጽድቅ መዳን ስላልቻለ (ኢሳ.64፥6) ፣ በህጉ ነቀፌታ ተገኝቶብን ከኃጢአት ወገን ሆነን ስለተከሰስን(ሮሜ.3፥9፤ ገላ.3፥22)፣ ጻድቅ ፤ አስተዋይ ፤ እግዚአብሔርን የሚፈልግ ፤ ቸርነት የሚያደርግ አንድ እንኳ ስለጠፋና በአንድነት የማይጠቅሙ ስለሆኑ (መዝ.13፥2-3 ፤ 52፥2 ፤ ሮሜ.3፥11-13) ፣ ደካሞች ፤ ኃጢአተኞችና ጠላቶች ሆነን ስለተገኘን (ሮሜ.5፥6-10) … ከእግዚአብሔር በቀር እኛን ማዳን የሚቻለው ከሰማይም ከምድርም ፤ ካመኑትም ካላመኑትም ወገን ስለጠፋ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ እኛን ለማዳን መጣ የሚለው ነው፡፡
      የእግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር፤ ክርስቶስ ኢየሱስ መምጣት ያስፈለገበት ዋናው ምክንያት ህዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸው ፣ የዲያብሎስንም ሥራ ያፈርስ ፣ እንዲያው በጸጋው በቤዛነቱ በኩል ከኃጢአት ሁሉ የሰው ልጆችን ያድነንም ፤ ያጸድቀንም እንዲሁም ከሰይጣንና ከኃጢአት ባርነት ፣ ከዘላለም ሞት ፤ ከኩነኔ ፍርድ ከገሃነምም ፍርድ ያድነን ዘንድ ነው፡፡ (ማቴ.1፥21፤ ሉቃ.2፥11፤ 1ዮሐ.3፥8 ፤ ሮሜ.3፥24 ፤ ቲቶ.3፥7 ፤ 1ጴጥ.2፥9 ፤ ሮሜ.8፥1-4፤ ዕብ.2፥14 ፤ ቆላ.1፥13 ፤ ሮሜ.8፥33 ፤ ዮሐ.5፥24)
    ይህን ፍርድና የዘላለም ቁጣ ማምለጥ የምንችለው ደግሞ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ኃጢአተኝነታችንን አውቀን በእውነተኛ ንስሐ ተጸጽተን ከክፉ መንገዳችን ስንመለስና ክፉውን በመጠየፍ ከበጎ ነገር ጋር ስንተባበር (ሉቃ.19፥6-10 ፤ ሐዋ.2፥38 ፤ 3፥19-20 ፤ ሮሜ.3፥11-18 ፤ 23 ፤ 12፥9 )፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ሞታችንን እንደለወጠና በትንሳኤው ደግሞ ህይወትን እንደሰጠን ማመን (ሐዋ.16፥25 ፤ ሮሜ.4፥23-25  ፤ 6፥8-11) ፣ እግዚአብሔር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመናችን የዘላለም ህይወትን እንደሰጠንና ልጆቹ እንዳደረገን ማመን (ዮሐ.1፥12 ፤ 3፥16 ፤ ሮሜ.10፥9) ሲቻለን ነው፡፡

      ነገር ግን መናፍቃን ይህን የዘላለም እውነት በአንድም በሌላም መንገድ በግልጽ ይክዳሉ፡፡ መናፍቃን ከሚክዷቸው ዋና ዋና የሥጋዌ (የመዳን)  ትምህርቶች ጥቂቶቹን ብናነሳ ፦

1.1. “መዳን የራስን ድርጅት መመሪያና ደንብ መጠበቅ እንጂ በክርስቶስ ደም አይደለም፡፡” ብለው ይክዳሉ፡፡

   የይሖዋ ምስክሮች የድኅነትን ነገር የሚያያይዙት ከመታዘዝ ጋር ነው፡፡ በዓለም ላይ ካሉት ሃይማኖቶች ብቸኛው የሚያድን ሃይማኖት “የይሖዋ ምስክሮች ናቸው ብልን ለመናገር ምንም አናመነታም፡፡ … ይህንን ለማድረግ የሚያስችለው ከሁሉ የተሻለው መንገድ  የይሖዋ ምስክሮች በመንግስት አዳራሽ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው፡፡” ይሉና  ለመዳን ደግሞ “ከሚታየው የአምላክ ድርጅት ጋር ዘወትር ተጠግተህ የምትኖር” እና ልባምና ትጉህ የሆኑትና ከሰማይም የቃሉን መና የሚያወርዱትን ቃላቸውን በፍጹም እምነት መጠበቅ ያድናል ብለው ያምናሉ፡፡ (በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ፡፡(WATCHTOWER BIBLE AND TRACT SOCIETY OF PENNSYLVANIA)፤ 1991፤ አሳታሚ WATCHTOWER BIBLE AND TRACT SOCIETY OF NEWYORK, INC. Brookly, New York, U.S.A.) ገጽ.190 እና 251)
     ለሐዋርያት ቤተ ክርስቲያን (Only Jesus‘s) አማኞች ደግሞ ድኅነት “የድርጅቱ አባል ከሁሉ የሚቀድም ሆኖ በተቀመጠው የጥምቀት ቀመር (ማብራሪያ) በማለፍ የዳነ ሰው ጸጋ ይሰጠዋልና በልሳን የመናገር ግዴታ አለበት” ብለው  ያምናሉ፡፡
     የሞርሞን አማኞች (The Church of Jesus Christ Latterday Saint‘s) አንድ ሰው ንስሐ በገባ ጊዜ እጅ ተጭኖ ከተጸለየበት እንጂ መዳን እንደማይችልና በተጨማሪም “ሞሪና” የተባለው መልዐክ ለሞርሞን የገለጠለትን መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም ሳይጠራጠር መቀበልና ማመን ሲችል እንደሚድን በግልጥ ያስተምራሉ፡፡

1.2.            “በክርስቶስ ደም የሚገኝ የኃጢአት ሥርየት የለም” ብለው ይክዳሉ፡፡


    ብዙውን ጊዜ መናፍቃን የኃጢአት ሥርየት በክርስቶስ በኩል መሆኑን የማይቀበሉት ስለሁለት ነገር ነው ብንል አንደኛው የክርስቶስ ፍጹም አዳኝነትና አምላክነት ላለመቀበልና ለራሳቸው ሥራ (ጽድቅ) ዕውቅና ለማሰጠት ነው፡፡ ከነዚህ መካከል ብንጠቅስ፦

1.2.1.      የይሖዋ ምስክሮች የክርስቶስን ስለሰው ልጆች ኃጢአት መሞትና በሞቱ ሕይወትን መስጠት ስለሁለት ነገር አይቀበሉትም፡፡ ይኸውም፦
1.     አምላክ የሚሞት ከሆነ በመሞቱ ይጠፋል እንጂ አምላክ ሆኖ ሊቀጥልና ሊኖር አይችልም በሚለውና ፤
2.    አምላክ ስለእኛ ኃጢአት የሚሞት ከሆነ ከልኩ አልፎ የሚበዛ ነው ፤ ስለዚህ እርሱ ቢሞትም ፤ የሞተው ፍጹም ሰው ከነበረው ከአዳም ጋር እኩል ሆኖ ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቱንም ሲያብራሩ “በምድር ላይ ከኖሩት ውስጥ ፍጹም የአምላክ ሰብዓዊ ልጅ በመሆን ከአዳም ጋር እኩል የነበረው እርሱ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡” በማለት ምንፍቅናቸውን ያስተምራሉ፡፡ ( ዝኒ ከማሁ ፤ ገጽ 63)

    የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና የትራክት ማህበር (በተለምዶ ይሖዋዎች) “አጋንንት ፣ ሆድ ፣ ገንዘብ ፣ መላዕክት አማልክት ወይም አምላክ ተብለዋልና የክርስቶስ አምላክ መባል አምላክ መሆኑን አይገልጥም እንደሚሉት ያይደለ ፤ መጽሐፍ ቅዱስ በማያሻማ ቃል እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ አምላክ መሆኑን በአምላክነቱም በኩል ብቃት ያለው አዳኝና ቤተ ክርስቲያንንም የዋጀ መሆኑን በግልጥ ሳያሻማ ይናገራል፡፡(ሐዋ.20፥28) አይሁድ ኢየሱስን የተቃወሙበት ትልቁ ምክንያት “እኔ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላል” ብለው ሳይሆን “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” ማለት ራሱ እግዚአብሔርን መሆንና ከእግዚአብሔር ፍጹም መተካከል መሆኑን ስለሚያውቁ ነው ፈጽመው የተቃወሙት፡፡ (ዮሐ.5፥17 ፤ 10፥36) ብሉዩን የጨበጡቱ ኦሪታውያኑ አይሁድ እውነቱ ገብቷቸው ሲቆጡ ፤ መጽሐፍ ቅዱስ የጨበጡቱ  “ሐዲሳውያን” ይህ እውነት ከእነርሱ መሰወሩና ልባቸውም ስለዚህ እውነት መደንዘዙ እጅጉን የሚደንቅ ፤ የሚያሳዝንም ነው፡፡
2.2.2.    የይሖዋ ምስክሮች የክርስቶስን አዳኝነትና በደሙ የሚገኘውን የኃጢአት ሥርየት ተቃውመው ፥ በዚህ ፈንታ ያስገቡት የራሳቸውን ሰዋዊ ብልሃት ነው፡፡ ይኸውም “አንድ ሰው መዳን የሚችለው በማመኑ ሳይሆን ለመጠበቂያ ግንብ አስተምህሮዎች ፤ ይህንንም በተመለከተ በሚደረጉ ፕሮግራሞች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግና በመንግሥት አዳራሽ (ማለትም ፕሮግራማቸው በሚደገረግበት ሥፍራ) ሲገኝ ብቻ ነው” ይላሉ፡፡ ባለንበት ቦታ መዳን አንችልም ብለውም ያክሉበታል፡፡
2.2.3.    የሐዋርያት “ቤተ ክርስቲያን አማኞች” ደግሞ ድኅነት የሚገኘው በቀዳሚነት የድርጅቱ አባል መሆን ሲቻል ፤ ከዚያም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ሳይሆን በኢየሱስ ስም ብቻ ተጠምቆ ልሳን መናገር አለበት ይላሉ፡፡
2.2.4.    ሞርሞናውያን ደግሞ የሞርሞንን መጽሐፍ ቅዱስ ያለምንም ጥርጥር ማመንና መቀበል እንዲሁም ንስሐ ልክ እንደገባ እጅ ተጭኖ በተጸለየበት ጊዜ የመንፈስ ቅዱስን ሥጦታ ሲቀበል ነው የሚድነው በማለት ያስተምራሉ፡፡

      ይህንን የመናፍቃንን ትምህርት በደንብ ያጠኑ አንድ የነገረ መለኮት ታላቅ አባት ሲጠቀልሉት “የመናፍቃን ትምህርት አንድ የሚሆኑበትና የሚገናኙበት ፥ አንተን የምታድነው አንተ ነህ ይላሉ” በማለት ያስቀምጣሉ፡፡
       በእርግጥም መጽሐፍ ፦ “ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። (ሮሜ.5፥6 ፤ 8) ነገር ግን እግዚአብሔር በምሕረቱ ባለ ጠጋ ስለ ሆነ ፥ ከወደደን ከትልቅ ፍቅሩ የተነሣ በበደላችን ሙታን እንኳ በሆንን ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ሕይወት ሰጠን፥ በጸጋ ድናችኋልና … (ኤፌ.2፥4) እንዲሁም “እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፥ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ … ” (ሮሜ.916) “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።” (ኤፌ.2፥8-9) “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤” (ቲቶ.3፥5)  ይላልና እንደእኛ ወይም ከእኛ ሥራ የሆነ ምንም የሆነ ነገር የለም፡፡
2.3.    ክርስቶስ የሞተው ለሁሉም ኃጢአት ሳይሆን ለጥቃቅን ኃጢአት ብቻ ነው

3.  የአካል ትንሣኤን ይክዳሉ
   
     ቤተ ክርስቲያን የምትጠብቀው ትልቁ ተስፋና ናፍቆቷ ማራናታ የምትለው ጌታዋ ዳግመኛ በሙታን ትንሳኤ ሊቀበላት እንዳለ እንደሆነ ቅዱሳት መጻህፍት በአንድ ቃል ተስማምተው ይመሰክራሉ፡፡ ትንሳኤ ሙታን የክርስትና ዋናና ማዕከላዊ ትምህርት ነው፡፡ የትንሳኤ ሙታንን ትምህርት መካድ ሙሉ የክርስትና ትምህርትን እንደመካድ ያስቆጥራል፡፡ (1ቆሮ.15፥13-19) ይህን ግን በተለያየ መንገድ የሚክዱ መናፍቃን አሉ፡፡ ለምሳሌ፦

3.1. የመጠበቂያ ግንብ አማኞች (የይሖዋ ምስክሮች)

     በደፈናው “የኢየሱስን ከሙታን መካከል መነሳትን ፥ አልተነሳም” በማለት አይክዱም፡፡ ነገር ግን ትንሳኤውን  ሲያብራሩ በአካሉ የተነሳ አይደለም ፤ አካሉን በመቃብር ውስጥ በመተው የተነሳ ነው እንጂ በማለት ፤ ሲቀጥሉም ከሙታን መካከል የተነሳው እርሱም ኢየሱስ ሳይሆን ሊቀ መላዕክት ሚካኤል ነው በማለት ያስተምራሉ፡፡ ስለዚህም “ኢየሱስ መንፈስ ሆኖ ተነስቷል ፤ ለእግዚአብሔርም ፍቅር መታሰቢያ እንዲሆን ታስቦ በአንድ ቦታ ተጠብቆ ይኖራል እንጂ እርሱ በአካሉ በሰብአዊነት አካሉ (ማንነቱ) ከሙታን መካከል አልተነሳም” በማለት የአካልን ትንሳኤን ሙሉ ለሙሉ ሲክዱ ይስተዋላል፡፡
3.2.  የአዲሱ ዘመን እንቅስቃሴ አማኞች (New age Movement’s)

       የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ አንድ የዚህን እምነት ከሚያስተምሩ “ዋና መምህራን” መካከል ሁለቱን አጊኝቶ የመወያየት ዕድሉን አጊኝቶ ባደረገው ውይይት ከመጠበቂያ ግንብ አማኞች ይዘታቸው ብዙም ባይለይም በግልጥ ቃል እንዲህ ብለዋል ፦ “ኢየሱስማ አፈር ከራሱ ላይ አራግፎ አልተነሳም ፤ እርሱ የተነሳው በመንፈሳዊ ማንነቱ እንጂ በሰብዐዊ ማንነቱ አይደለም” በማለት እንደእምነቷ መሥራች እናታቸው ወይዘሮ ሜሪይ ቤከር ኤዲይ ሃሳባቸውን ያራምዳሉ፡፡ ይህ የእምነት ድርጅት አንዳንዴ “ክርስቲያን ሳይንስ” በማለትም ይጠራል፡፡
    ነገር ግን ታላቁ መጽሐፍ የክርስቶስን ከሙታን መካከል መነሳቱንና እኛም የሙታን ትንሳኤ በአካል የምንነሳ መሆኑን በግልጥ ያስረዳል፡፡ ክርስቶስ ጌታችን ኢየሱስ “ … የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀምጧል” (ዕብ.1፥3 ፤ ማር.16፥19 ፤ ሐዋ.7፥56 ፤ ዕብ.12፥2) ፤ እንዲሁ እንደትንሳኤው በኩራችን ክርስቶስ ኢየሱስ (ቈላ.1፥18) እኛም የዚህን ዓለም የሚበሰብስ አካልን ፣ የተዋረደ ፣ ደካማ ፣ ፍጥረታዊ አካል ፣ የሚጠፋ ፣ የሚሞት አካልን ያይደለ የማይበሰብስ አካልን ፣ የከበረ ፣ ኃያል ፣ መንፈሳዊ አካል ፣ የማይጠፋ የማይሞት አካልል በመልበስ በትንሳኤው ኃይል እንነሳለን፡፡ (1ቆሮ.15፥42-53)

4.  የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን ይጋፋሉ ፤

       መጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት አለው፡፡ ሥልጣኑም ከባለቤቱ ይመነጫል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ስንልም እርሱ እግዚአብሔር የተናገረው ማለታችን ነው፡፡ እርሱ እግዚአብሔር ተናግሮታልና እርሱ የተናገረውን ማንም ሊሽረው ፤ ሊያሻሽለው ፈጽሞ ሥልጣን የለውም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር አፍ የወጣ ቅዱስ ቃል መሆኑን “ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል … ” ሲል ጌታችን (ማቴ.4፥4) ቅዱስ ጳውሎስ ደግሞ “የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ” በማለት በግለጥ አስቀምጦታል፡፡ (2ጢሞ.3፥16) ስለዚህ እግዚአብሔር በሥልጣኑ የተናገረው ቃሉ የማያልፍ (ማቴ.24፥35) ፤ ለዘላለምም የሚኖር ነውና (ኢሳ.40፥6 ፤ 1ጴጥ.1፥24) ሰው ይሽረው ፤ ይለውጠው ዘንድ አንዳች ሥልጣን የለውም፡፡
       በመጀመርያ ደረጃ ማወቅ ያለብን እውነት መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር እንጂ በሰው ፈቃድ እንዳልመጣ ነው፡፡ (2ጴጥ.1፥20-21) እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ፦ “ብዙ ሰዎች የመሰከሩለትን ከእኔም የሰማኸውን ሌሎችን ደግሞ ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች አደራ ስጥ።” (2ጢሞ.2፥2) እንደተባለ ባለአደራም አለው፡፡ ይህችም በገዛ ደሙ የተመሠረተችው ቅድስት አካሉ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡
    ለዘመናት የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ቤተ ክርስቲያን የተጠነቀቁት ነገር ቢኖር መጽሐፍ ቅዱስ እርሱ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ  እንደተናገረው እንዲተላለፍ እንጂ የሰዎች ሃሳብ እንዳይቀላቀልበት በመጠንቀቅ ነው፡፡ የቀደመችው ቤተ ክርሰስቲያን ታላላቅ ጉባኤያትን አሰናድታ ፣ ቀኖናትን ቀንና የመጻሕፍትን ቁጥርና ንባባቸውን በጥንቃቄ መርምራ በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት እስከእኛ ድረስ የደረሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን ባለመተላለፍ በማክበርና በመፍራት ነው፡፡
   የመናፍቃን ትልቁ ድፍረትና ነውር ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ መጣስና በቃሉ ላይ የራሳቸውን ሃሳብ ማስገባት እንዲመቻቸው ሥልጣኑን መጋፋትን ይወዳሉ፡፡  የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን የሚጋፉት ያለድንበርና ያለወሰን እንደልባቸው ቃሉን ወደራሳቸው ሃሳብ ጠምዝዘው ለማምጣት እንዲመቻቸውና እንግዳ ትምህርቶችን ለማስፋፋት ነው፡፡ ከእነዚህ መናፍቃን ጥቂቶቹን ብናነሳ ፦
4.1. የይሖዋ ምስክሮች ፦ “መጽሐፍ ቅዱስ አዲስ አለም ትርጉም” በማለት በ2013 ተሻሽሎ ከወጣው የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም እንግሊዘኛ እትም ላይ የተተረጎመ” ብለው ባወጡትና የግል ባሳተሙት መጽሐፍ ቅዱሳቸው ላይ “እግዚአብሔር” የሚለውን ስም ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስደፍር መልኩ አጥፍተውታል፡፡ የራሳቸውንም ትምህርት ማስረጽ እንዲመቻቸው “ይሖዋ ወይም አምላክ” በሚለው ተክተውታል፡፡
       ይህም በራሳቸው ሥልጣን መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ሥልጣን በመጋፋት የተረጎሙት መሆናቸውን ያሳያል፡፡
4.2.    ሞርሞናውያንም ፦ በተለያየ ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ለሦስት ሺህ ዘጠኝ መቶ አሥራ ሦስት ጊዜ አርመውታል፡፡ በተጨማሪም የሞርሞናውያን መሥራች ጆሴፍ ስሚዝ በዘፍጥረት ምዕራፍ 50 ላይ አሥራ አራት ቁጥሮችን በመጨመር ፤ ይህም እግዚአብሔር ተናግሮለት ያደረገው መሆኑን ለማስረገጥ ተጠቅሞበታለን፡፡ በተጨማሪም ሞርሞንም ሆነ ሌሎች የመሪዎቹ ዋና ቅጂዎች የተረጎሟቸው ትርጉሞች በትክክል ከእግዚአብሔር ቃል እኩል ናቸው ብለው ያምናሉ፡፡ ስለዚህም መጽሐፍ ቅዱስና ትርጉሞቹ ቢጋጩ እውቅና መስጠት የሚገባን ለትርጉሞቹ ነው በማለት ያስቀምጣሉ፡፡
     የመናፍቃን ዋና ዋና ክህደቶች እኒህ ብቻ አይደሉም ፤ እኒህ ማሳያዎች ናቸው፡፡ እኒህንና ሌሎችንም የሚክዱ  ግን ዋና መናፍቃን ናቸውና እንዲህ ባለ ነገር ላይ ልንታገስ አይገባም፡፡ ነገር ግን ዋና ትምህርተ ክርስትና ሳይነካ በቀኖናዎችና በሥርዓቶች ላይ በተደረገ ሃሳብ መስጠትና ተቃውሞ እንዲሁም ዋናው ትምህርት መስመሩን ስቶ በፍጡራን ሃሳብ “በተዋጠ” ጊዜ “ወደነበርንበት ወደጥንት የጌታና የሐዋርያት ትምህርትና ትውፊት እንመለስ” ማለት እንደዋና ትምህርት መካድና እንደመናፍቅ ቆጥሮ አማኞችንና አገልጋዮችን ማሳደድ ፤ ማውገዝ በኋላ ሊያጸጽተን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
 ይቀጥላል...

No comments:

Post a Comment