Wednesday, September 23, 2015

በእንተ ዝንቱ ዐለዉ ሕገከ ወኢይወፅእ ፍትሐ ጽድቅ...

“በእንተ ዝንቱ ዐለዉ ሕገከ ወኢይወፅእ ፍትሐ ጽድቅ፥  እስመ ኃጥእ ይትዔገሎ ለጻድቅ በእንተ ዝንቱ ይወፅእ ፍትሕ ግፍቱዕ፡፡” ትርጉም፡- “ስለዚህ ሕግ ላልቶአል፥ ፍርድም ድል ነሥቶ አይወጣም ኃጢአተኛ ጻድቅን ይከብባልና ስለዚህ ፍርድ ጠማማ ሆኖ ይወጣል።” ትንቢተ ዕንባቆም ምዕራፍ 1 ቁጥር 4

አለበል ከአሰላ
ይድረስ ከአባ ሰላማ ድረ ገጽ ይህን ጽሑፍ እንደምታወጡልኝ በመተማመን ልኬላችኋለሁ፡፡
ከላይ በርእሱ የተጠቀሰውን የነቢዩን የዕንባቆም ጩኸት የሚጮህ ሰው ዛሬም አይጠፋም፡፡ በነቢዩ ዘመን እንደ ነበረው ዛሬም ሕግ ላልቶ ይታያል፣ ፍርድም ድል ነስቶ አይወጣም ኃጢአተኛ ጻድቅን የመክበቡ ነገር ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ፍርድም እየተጣመመ ነው፡፡ ይህን ከምናይባቸው ሀገረ ስብከቶች መካከል የአርሲ ሀገረ ስብከት አንዱ ነው፡፡ በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ውስጥ አለቦታቸው የተቀመጡና ጊዜ የሰጣቸው ሙሰኞች ወንጀላቸው ተከድኖ እንዲቀርና በአልጠግብ ባይነት የግል ጥቅማቸውን ለማሳደድ እንዲረዳቸው የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ በተለይም እውነተኞችን አለስማቸው ስም ሰጥተው ማሳደድ አድማ መምታትና በአድማ ቃለ ጉባኤ ተፈራርመው ጭምር አላስበላ ያላቸውን እውነተኛ ሰው ማሳደድ እስከ በላይ ድረስ በሐሰት አቤት ማለት የዕለት ተዕለት ስራቸው ነው፡፡  
እንደዚህ ያልኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ በቅርቡ በሀገረ ስብከታችን ውስጥ የሀገረ ስብከቱ ዋና ፀሐፊ እና ዋና ሥራ አስኪያጅ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባትና ምክንያቱን ለማንሳት ነው፡፡ ጉዳዩን ከማንሳቴ በፊት ትንሽ የግለሰቡን ሕይወት ታሪክ ወይም መንፈሳዊ ህይወትን እና መንፈሳዊ ዕውቀትን ላንሳ፡፡
የሀገረ ስብከቱ ዋና ፀሐፊ አቶ ታምራት ይባላሉ የተወለዱትና ያደጉትም በዚያው ከተማ ሲሆን በቅጡም ባይሆን በዚያው ከተማ በሚገኘው በአሰላ መድኃኔ ዓለም ቤ/ክ ሰንበት ትምህርት ቤት ውስጥ አባል ነበሩ፡፡ በሰንበት ትምህርት ቤቱ ውስጥም ከበሮ ሲደለቅ ከማጨብጨብ በቀር የተማሩት ትምህርት የለም፡፡ ምንም ዓይነት የቤተ ክርስቲያን ክህነትና ትምህርት እንደሌላቸውም ይነገራል፡፡

      በጊዜውም በዚች ዕውቀታቸው ትንሽ ከእሳቸው የተሻሉ፣ ያወቁና የተማሩ ጓደኞቻቸውን ያሳድዱ እንደነበረ ይወሳል፡፡ በተለይ ለደብሩ ስብከተ ወንጌልና በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ነገረ አቀባይ ጆሮ ጠቢ ነበሩ ይባላል፡፡ ይህ ሥራቸው እና ሞያቸው ሳይሆን አይቀርም ምንም ሳይማሩና ሳያውቁ ከሰንበት ትምህርት ቤት ተራ አባልነት አስነስቶ ወደ ሀገረ ስብከት ያስገባቸው፡፡
        ለነገሩ ጊዜውም የሚወደው የተማረ፣ እውነትን የሚናገር፣ መንፈሳዊና ዝምተኛ ሰውን አይደለም፡፡ ይልቅ ያልተማረውን፣ ውሸትን እና ሐሰትን የሚናገር፣ ያልሆነውን ሆነ፣ ያልተደረገውን ተደረገ፣ ያልተባለውን ተባለ፣ እያለ የሚያወራውን ነገር አቀባዩን እና ጆሮ ጠቢውን ነው የሚወደው፡፡ አቶ ታምራት እስከ አሁንም ድረስ ከትውልድ ቦታቸው ወጣ ብለው የአብነት ትምህርት ወይም መጻሕፍት ቤት ሊማሩ ቀርቶ እዚያው የሰንበት ት/ቤት አባል ከነበሩበት ቤተ ክርስቲያን ከሚገኙት መሪጌቶችና ቀሳውስት የተማሩት ለዲቁናና ለንፍቀ ዲቁና ሥልጣን የሚያበቃ ትምህርት የላቸውም፡፡ እንዲያው በደፈናው ጨዋ (ያልተማሩ) ናቸው፡፡ ጨዋነታቸው ለትምህርት እንጂ ለሌላውማ …
        ነገር ግን ከሀገረ ስብከቱ በነበራቸው በመሀይምነት ዕውቀታቸውና ነገረ አቀባይነታቸው ለጳጳሱ በተለይም በሚያደርጉት ጭፍን በሆነ አስተሳሰባቸውና መሰሪነታቸው ሊቃውንትንና ካህናትን ሲያሳድዱ ነው የኖሩት፡፡ በዚሁም ክፋታቸው እና የውሸት የሐሰት ነገር አቀባይነታቸው በጊዜው በነበሩት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በአቡነ ናትናኤል ተሰሚነት እና ተቀባይነት አገኙ፡፡ ከዚያም በገዳም ያደጉትን መነኮሳት፣ በአብነት ትምህርት ቤት ያደጉትን ሊቃውንት፣ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የተማሩትን ቀሳውስትና ዲያቆናትን በማሳደድ፣ ከኮሌጅ ተመርቀው የሚያገለግሉትን በመግፋትና በማባረር ቀደም ብለው ይሰሩት ከነበረው የሥራ ክፍል ተነስተው ከህግ ውጪ የሀገረ ስብከቱ ዋና ፀሐፊና ቁጥጥር ክፍል ሆነው ተሾሙ፡፡ በሌላቸው ማንነትና እውቀትም አለአቅማቸው “ሊቀ ኅሩያን” የተባለ ማእረግም ተሸከሙ፡፡ ይብላኝ ተገቢያቸው ሳይሆን ይህን ማእረግ ላሸከሟቸው ለሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስና ያለሀፍረት ማእረጉን ለተሸከሙት ለአቶ ታምራት፡፡  
        እንኳን ዘንቦብሽ እንዴውም እንደው ነሽ እንዲሉ እንኳን ፀሐፊ ሥራ አስኪያጅ ለምነው እና ጳጳሱን አስፈቅደው ካልሆነ የሀገረ ስብከቱን መኪና በራስ ፈቃድ ማሽከርከር አይቻልም፡፡ እርሳቸው ግን በራሳቸው ፈቃድ እንደፈለጉና ወደ ፈለጉት ሀገረ ለማሽከርከር ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ እስከ አሁንም ድረስ የግል መኪናቸው እንጂ የአንድ ሃይማኖት ተቋም ወይም የሕዝብ ድርጅት ያውም በሊቀ ጳጳስ የሚመራ ባለቤትነት ያለው የሊቀ ጳጳስ መኪና አትመልስም፡፡ የቅርብ ሰዎች ሲያወሩ በዓመት ውስጥ ለመኪናዋ ነዳጅ፣ ለመኪናዋ ጥገና፣ ለመኪናዋ እጥበት ተብሎ የሚወጣው ብቻ አንድ መኪና ይገዛል እያሉ ሲያወሩ ይሰማል፡፡
ለነገሩ ተቆጣጣሪና ተፈሪ ከሌለ ማን ተሰምቶ? ምክንያቱም አብዛኞቹ የሀገረ ስብከቱ ሰራተኞች አብሮ አደጎችና ጓደኛሞች ሲሆኑ በአንድ ደረጃ ላይ ማለትም ዲያቆናትና የሰንበት ተማሪዎች ካልሆኑ በቀር በመካከላቸው ሌላ የተቀላቀለ ሰው የለም፡፡ ለዚህ ነው ለመዝረፍና ለመስረቅ የተመቸው፡፡    
የሀገረ ስብከቱ ፀሀፊና ቁጥጥር የሆኑት አቶ ታምራት ወልዴ እና ሂሳብ ሹሙ ገንዘብ ያዡና ሾፌሩ አራቱም እያንዳንዳቸው ቦታ ገዝተው እያሰሩት የለው ቤት ከ3 መቶ ሺህ ብር እስከ 4 መቶ ሺህ ብር ይገመታል፡፡ ያውም በአሰላ ቦታና ቤት ርካሽነት፡፡ ይሄ ታዲያ  እንኳን በአንድ የክልል ሀገረ ስብከት ከ1500-2500 የማይበልጥ የሰራተኛ ደመወዝ በአጭር ጊዜ ውስጥ መገንባት ይቻላል?
ይህ ሁሉ አልበቃ ብሏቸው አሁን ደግሞ በቅርቡ ለሀገረ ስብከቱ በግቢው ለሚሠራው ሕንጻ ግራውንድ የሚቆፈረውን አፈር ፀሀፊውና ሒሳብ ሹሙ ተስማምተው ለግል ጥቅማቸው ሲሸጡት ተደረሰባቸው፡፡ አፈሩ ግን ለጥምቀተ ባህሩ ማስፋፊያ እንዲሆን ወደዚያው ሄዶ እንዲገለበጥ በወቅቱ ያሉት ስራ አስኪያጅ አዘው ነበር ይባላል፡፡ እንደሚባለው የአንድ መኪና አፈር ከ1000-1400 ብር ድረስ ይሸጣል፡፡ ታዲያ ይህን ጉድ በቅርብ ርቀት ሆነው ይታዘቡ የነበሩት በቅርቡ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ተመድበው መጥተው የነበሩት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እንደ አባትነታቸውና እንደ ሃላፊነታቸው ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው በማሰብ ከምክርና ከተግሣጽ በተጨማሪ እንዲህ ሲሉ አስጠነቀቋቸው፡፡
1.     የቤተ ክህነቱን አፈር ሸጠው ለግል ጥቅማቸው ያዋሉትን የአፈር ሽያጭ እንዲያመጡ፣
2.    እስካሁን በሀገረ ስብከቱ ስም የዘረፉትን ንብረት እንዲመልሱ
3.    ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ ሀገረ ስብከቱ ድረስ ወደኋላ ተመልሰው እንደገና ኦዲት እንደሚያደርጉ በማስጠንቀቅ ይነግሯቸዋል፡፡
ከዚያ ሙሰኞቹ ታምራትና ግብረአበሮቻቸው ጉዳችን ፈላ ምን ይዋጠን ተባባሉ፡፡ አብረው የበሉ የሸጡና የለወጡ የዘረፉም ተነጋገሩ ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ዋና ጸሀፊው አቶ ታምራትና ሒሳብ ሹሙ ዲ/ን ዘውዱ ጉዳችንን ሳያወጣብን አሉና ያልሰሩትን ሰሩ፣ ያልበደሉትን በደሉ በማለት ኮንነው የታችኛውንም ሰራተኛ በሙሉ አሳድመው እኛ ከእሳቸው ጋር (ከስራ አስኪያጁ ጋር) አንሠራም፣ እርሳቸው አያዙንም ይነሱልን የሚል ደብዳቤ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ናትናኤል አስገቡ፡፡ የሀገረ ስብከቱን ይሁንታ ሲያጡ እንደለመዱት ሌላ ማጥመጃ ዘዴ ፈጠሩ፡፡ ስራ አስኪያጁ ወደቢሮው ጠርቶ ካስገባኝ በኋላ በሽጉጥ አስፈራራኝ እንደአስፈራራኝም ጩኸቴን ሳሰማ ያየ እማኝ ምስክር አለኝ በማለት አቶ ታምራት ለፖሊስ ጣቢያ አመለከቱ፡፡ በዚህም ምክንያት የውሸት ክስ “ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች” እንዲሉ ሥራ አስኪያጁ አንድ ቀን ሙሉ ታስረው ተፈቱ፡፡ይህ አልበቃቸው ብሎ ጥቅማቸው የተነካባቸው ዋና ፀሀፊና ሒሳብ ሹሙ ሊቀ ጳጳሱን በመዝለፍና በማስፈራራት ሰራተኛውን እንደ ገና በማሳደም ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ ሄደው በቅርቡ ወደ ሀገረ ስብከታችን ከመጡት ሥራ አስኪያጅ ጋር አብረን አንሰራም እሳቸው አያዙንም ይነሱልን በማለት ተፈራርመው አመለከቱ፡፡ “ብልህ በልቶ በሞኝ አፍ ያብሳል” እንዲሉ
·        ያልተማሩት እነሱ
·        የዘረፉት እነሱ
·        ክህነት የሌላቸው እነሱ
·        መባረርና መነሳት ያለባቸው እነሱ ሆነው ሳለ
ከዲቁና እስከ ቁምስና፣ ከቆሎ ትምህርት ቤት እስከ ሀገረ ስብከት ስራ አስኪያጅነት፣ ከልጅነት እስከ ምንኩስና በቤተ ክርስቲያን ያደጉትን አባት ይነሱልን በእሳቸው አንታዘዝም ምን ማለት ነው?
ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም እነ ታምራት ያቀረቡትን አቤቱታ ተመልክቶ ከመረመረ በኋላ ጥፋተኞቹ አድመኛው ታምራት ወልዴና ግብር አበሮቹ መሆናቸውንና ጉዳዩ የስልጣን ይገባኛል ጥያቄ ሆኖ ስላገኘው ለአርሲ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት እና ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በላከው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ በዚህ የተበሳጩት እነታምራት አላማቸውን በደንብ ያልተረዱ አንዳንድ ምእመናንን ጭምር በማነሳሳት በአውቶቡስ አሳፍረው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ለክስ በመምጣት በቅርቡ አቤት ያሉ ሲሆን፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በአቋሙ መጽናት ሲገባውና የጻፈውን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ ማድረግ ሲኖርበት ሥልጣን ለተጠሙት ለነታምራት ስራ አስኪያጅነቱን ቢነሳቸውም ከዚህ ቀደም በዘርፊያቸው እንዲነሱ የተደረጉትንና የሀገረ ስብከቱ ዋና ፀሀፊ የነበሩትን ሊቀ ህሩያን ተ/ማርያም አሰማኸኝን ሥራ አስኪያጅ አድርጎ በመሾም ለውጥ ሊያመጡ የተነሱትንና ብዙ ዋጋ የከፈሉትን ስራ አስኪያጅ አንስቷቸዋል፡፡ አሁን የተሾሙት አዲሱ ስራ አስኪያጅ ከዚህ በፊት ዋና ጸሀፊ ሁነዉ ሲሰሩአንድ አዲስ ቤተክርስቲያን ተሰርቶ ቅዳሴ ቤቱን ለማስከበር ብፁእ አባታችን አምጡ ብለዋልብለው ከህዝቡ 10,000 (አስር ሽህ ብር) በልተዋል ተብሎ ለብጹእ አባታችን ተነግሮ ከዚያ ከፊቴ ሂድልኝ ብለዋቸው ነው የሄዱት፡፡ አሁንም የመጡት በፊት የሠሩት ስህተት እንዳይገለጥባቸው ነው ይባላል፡፡ አልያም ቀደም ብለው ያበላሹትን ለማስተካከል ነው የሚሉም አሉ፡፡ እነታምራትም እስካሁን የዘረፉት ብር ኦዲት እንዳይደረግና ተድበስብሶ እንዲቀር በቀጣይም እነሱም አብሮ ለመብላት እንዲመቻቸዉ ለማድረግ ጠቅላይ ቤተክህነት ውስጥ በፈጠሩት የሙስና ሰንሰለት የጠቅላይ ቤተክህነቱን ውሳኔ በማያሳምን ምክንያት አስለውጠው የፈለጉትን ያስደረጉት፡፡
ኧረ ለመሆኑ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አስቀድሞ ውድቅ ያደረገውን የነታምራትን የስልጣን ጥማታቸውን በገሃድ የገለጹበትን ደብዳቤ ማመልክቻ እንዴት ተቀብሎ ነገሩን እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ እንዳስኬደው ለብዙዎች የአሰላ ሕዝበ ክርስቲያን ጥያቄ ሆኗል፡፡ በዚህ መንገድ ፍትህ ከወዴት ይገኛል? በዚህ መንገድ ቤተክርስቲያን ሰላም ታገኛለችን? እውነተኞች እየተገፉ ሌቦችና ዘራፊዎች ተከብረው የሚኖሩት እስከ መቼ ይሆን?

4 comments:

 1. meregaw teamaninet yigolewal

  ReplyDelete
 2. አባ ናትናኤል የዘሩትን እያጨዱ ይመስላል...
  እንዴት ሰው ባልዋለበት ‹‹ሊቀ ኅሩያን›› ይባላል...

  ReplyDelete
 3. Alebel yemitaweraw hulu arisen aywekilem

  ReplyDelete
 4. ‹‹ሊቀ ኅሩያን›› አቶ ታምራት እስከ አሁንም ድረስ ከትውልድ ቦታቸው ወጣ ብለው የአብነት ትምህርት ወይም መጻሕፍት ቤት ሊማሩ ቀርቶ እዚያው የሰንበት ት/ቤት አባል ከነበሩበት ቤተ ክርስቲያን ከሚገኙት መሪጌቶችና ቀሳውስት የተማሩት ለዲቁናና ለንፍቀ ዲቁና ሥልጣን የሚያበቃ ትምህርት የላቸውም፡፡

  ReplyDelete