Friday, September 25, 2015

ባለቤት አልባው ደብር


Read in PDF
ቤተ ክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ ይልቅ በብዙ ፈተና ውስጥ የምትገኝበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ከፈተናዎቿ አንዱና ዋናውም ሙስና መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ሙስናውን የሚፈጽሙ ሰዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያዩ መዋቅሮች ውስጥ በሕጋዊም በሕገወጥም መንገድ የተሰገሰጉና ለቤተክርሰቲያን ሳይሆን ለግል ጥቅማቸው የቆሙ ግለሰቦችና ቡድኖች አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደዘገብነው የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን አንዱ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኑ ሕገወጥ አሰራር የሰፈነበት ባለቤት የሌለው ቤት ሆኗል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቤተክርስቲያኑን በባለቤትነት እየመሩ ያሉት ቤተክርስቲያንን መምራት ያለባቸውና ህጋዊ መብቱ ያላቸው ሳይሆኑ በቤተክርስቲያን ሀብትና ንብረት እየነገዱና እያተረፉ ያሉት የሰንበቴ ማኅበራት አመራሮችን ከፊት አሰልፈው ያዘመቱና ከኋላ ሆነው አመራር የሚሰጡ የታገዱ የሰበካ ጉባኤ አባላት ናቸው፡፡
በደብሩ ውስጥ የሚገኙ የሰንበቴ ማህበራት በተለይም የገብርኤል፣ የመድኃኔ ዓለም፣ የማኅበረ በኩር፣ ትልቁና የከበርቴዎቹ የእግዚአብሔር አብ ማኅበር ሰንበቴ ቤቶች ናቸው፡፡ የእነዚህ ሰንበቴ ቤቶች አመራሮች በቤተሰባቸው ቁጥር ልክ የመቀበሪያ ፉካ ያላቸው ሲሆን፣ መሬቱ የቤተክርስቲያን ቢሆንም የአጥቢያው አስተዳደር ፈጽሞ የማይቆጣጠረውና የማይመለከተው ነው፡፡ አንዱ ፉካ እስከ 40 ሺ ብር የሚሸጥ ሲሆን አስከሬን ከውጭ ከመጣ ደግሞ በእጥፍ ይሸጡታል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ከገቢው ለደብሩ በፐርሰንት እንኳ አይከፍሉም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ትግል አድርገው የነበሩት አሁን ኮተቤ ገብርኤልን እያስተዳደሩ ያሉት የቀድሞው አለቃ እያንዳንዱን ፉካ ያለውን የሰንበቴ ማህበር እስከዚያ ጊዜ ድረስ የሸጡትን በማስላት ብር 3 መቶ ሺ (300,000) እንዲከፍሉ አስወስነው ነበር፡፡ ነገር ግን ሆዳቸውን በወደዱ ጥቂት ጥቅመኛ ካህናት ውሳኔው ተቀለበሰ፡፡
 በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት እንደሚባለው ቤተክርስቲያን በገዛ ንብረቷ በሰንበቴ ማህበራት እየተበዘበዘች ነው፡፡ ከዚህ አልፎ የመቃብራችሁ ገቢ ሊወሰድ ነው ተብለው  በህገወጦች የሠበካ ጉባኤ አባላት ተቀስቅሰው ህገ ወጥነታቸው ተረጋግጦ የታገዱት የሰበካ ጉባኤ አባላት ይመለሱልን ሲሉ በሰንበቴያቸው ማህተም ጠይቀዋል፡፡ እነዚህ ዘጠኙ ሰንበቴዎች ካቀረቡት ጥያቄ ውስጥ አስቂኙ አስተዳደሩ ኦዲት ይደረግልን ማለታቸው ነው፡፡ ዋናው የፉካ ነጋዴ ታሸበወርቅ 3 ፎቅ የሰራው ከየት አምጥቶ ነው? ለመሆኑ እየተሠራ ያለው የቤተ ክርስቲያኑ ህንጻ 13 ዓመት ሙሉ ያለ ኦዲት ሲሰራ የት ነበሩ? 310 ካሬ ሜትር ቤት የህንጻ አሰሪ ኮሚቴው ያለጨረታ ሲሸጥ የት ነበሩ? የደሃ ልጆች ከትምህርት ገበታቸው ተባረው መድረሻ ሲያጡ የት ነበሩ? ራሳቸው የመቃብሩ ፉካ ያለ ከልካይ ወይም ያለ ግብርና ፐርሰንት ሲቸበችቡ ማን ኦዲት አደረጋቸው? ቤተክርስቲያንን በቁም እያሉ ሲበዘብዟት ኖረው ሲሞቱ ለመቀበሪያ ብለው ብቻ የተጠጓት እነዚህ የፉካ ነጋዴዎች ገና ለገና ትርፋችን ይቀርብናል ብለው በታገደውና በህገ ወጥ መንገድ ደብሩን እየበጠበጠ ያለው የአቶ ዮናስ ሽፈራው መናጆ ሆነው አለቃውን አናስገባም አሉ፡፡ በምንም ሞራል ጠላ ለመጠጣትና ለመቀበር የተመሰረተ ስብስብ በሀገረ ስብከት የተመደበን አለቃ ማባረር አይችልም፡፡


እውነት ነው አለቃው አባ ገብረ ሚካኤል ከፈጸሟቸው አስነዋሪ ድርጊቶች አንጻር ከዚህ በላይ ቢባሉም የሚገባቸው ሰው ናቸው፡፡ ቢሆንም ሀገረ ስብከት የመደበውን አለቃ በህገ ወጥና ለራስ ጥቅም ሲባል በአድማ አናስገባም ማለት ግን ህገወጥነት ነው፡፡ ይህ ለነገው መጥፎ አርአያ ነውና የሚመለከተው አካል ተገቢውን የማስተካካያ እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ በተለይም ሀገረ ስብከቱ ይህን ተገቢውን እርምት ሰጥቶ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡ የጽንፈኝነትና የአክራሪነት አንዱ ዝንባሌ ይህ ነው፡፡ ደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ከዚህ አልፎ የአሸባሪ ዋሻ እየሆነ መምጣቱ ከአማኑኤልና ከብስራተ ገብርኤል ጋር በሲቪል ሰርቪስ በቅርቡ በተካሄደው ሥልጠና ላይ ተወስቷል፡፡
ሌላው አሁን በዚህ ደብር እየታየ ያለውን የሰንበቴ ማህበራት እንቅስቃሴ እየመሩ ያሉት ቤተክርስቲያንን ተገን አድርገው ያሉ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ እነዚህ ከማቅ ጋር ተጋብተው ያሉ ፖለቲከኞች የመድኃኔ ዓለሙ የፉካ ከበርቴ ወታደር ታሸበወርቅ፣ የገብርኤል ሰንበቴ ቤቱ ሻለቃ ጣሰው ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ሌሎቹ በቦታው ላይ በየዕለቱ ችግር እየፈጠሩ እጅ ከፍንጅ ቢያዙም የሆኑት ነገር የለም፡፡ በዚህ ረገድ ህግን ማስፈጸምና ማስከበር የሚገባቸው የወረዳ ፍትህ ቢሮ እና ጥቂት የፖሊስ አባላት ሊገመገሙ ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም የጠቀስናቸው በአጥቢያው የከበሩ ባለሀብቶች በገንዘብ ይዘናቸዋል እያሉ እያስወሩ ሲሆን፣ በፍትህ አካላቱ በኩል የሚታየው ዳተኝነት ኪራይ ሰብሳቢነት እንዳለ በገሃድ የሚያሳይ ነው፡፡ ለምሳሌ አቶ ዮናስ ሽፈራው በማይመለከተውና ስልጣኑ በማይፈቅድለት ሁኔታ በእጁ ያስገባውን የሙዳየ ምጽዋቱን ቁልፍ እንዲያስረክብ ሀገረ ስብከቱ ለፖሊስ ቢጽፍም ይህን ማስፈጸም አልቻለም ለምን? ከመጠን በላይ የሚዘረፈው ገንዘብ ለእንዲህ ዓይነቱ ፍትህን የማስቀልበስ ስራ ላይ ይውላልና ነው፡፡ በየአጥቢያው ለሚከሰቱ ችግሮች እነዚህ የፍትህ አካላት ተጠያቂዎች መሆናቸው በሲቪል ሰርቪስ በተካሄደው የቡድንና የመድረክ ውይይት ላይ ተጠቅሷል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ታች ፖሊስ ጣቢያ ድረስ ምን እየሰራ እንደሆነ መንግስት ራሱን እንዲፈትሽ ለሚኒስትሩ ተነግሯል፡፡
የደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን ችግር ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ለችግሩ ተጠያቂው መቋጫው ምን ይሆን? የሚለው ያጓጓል፡፡ እያንዳንዱ ችግር በየጊዜው የእርምት እርምጃ ቢወሰድበት ኖሮ ነገሩ እዚህ ደረጃ ላይ አይደርስም ነበር፡፡ ለመጥቀስ ያህል፦
1.     13 ዓመት ሙሉ ያልተመረመረው የሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ሂሳብ ተደብቆ በየዓመቱ የተመረመረው የሰበካ ጉባኤ (የደብሩ ሂሳብ) ይመርመር ብሎ ማደናገር፣
2.    ዛሬ ድረስ የታገደው የሙዳየ ምጽዋት ቁልፍ በታገደው የሰበካ ጉባኤ አባል እጅ መኖሩ፣
3.    310 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ግራውንድ እና ፎቅ ቤት ያምንም የጨረታ ማስታወቂያ ሲሸጥና ገንዘቡ የት እንደደረሰ ሳይታወቅ ተደብቆ መቅረቱና በሙስናው ውስጥ እጃቸው ያለ ሰዎች በደብሩ ውስጥ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸው፣
4.    የማኅበረ ቅዱሳን አባል አዲሱ ሕንጸ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥዕል ያለ ጨረታ እንዲስል የተሰጠው መታገዱ፣
5.    ዋንዛ በተባለ ድርጅት ዮናስ ሽፈራው በሚሰራበት ቦታ የቤተ ክርስቲያኑ የወለል የጣውላ ሥራ ያለምንም ጨረታ በኮሚሽን ሲያሰራ ምንም አለመባሉ፣
6.    ዮናስ ሽፈራው እየጻፈ በሚያቀርበው ደብዳቤ የየሰንበቴ ማኅተም በማድረግ የጥቂት ሕገወጥ ነጋዴዎችን ጥያቄ ሕዝቡ እንደጠየቀ በማስመሰል የአድማ ሥራ መሥራቱ፣
7.    የሰንበት ት/ቤቱ 75 ሺ ብር  ማጥፋቱንና ቴፕና ቴሌቪዥን መሰረቁን አለመጣራቱ፣
8.    የሰንበት ት/ቤቱ የአመራር ለውጥ ተንጠልጥሎ መቆየቱ
9.    ሀገረ ስብከቱ አጣሪ ቢመድብም እስካሁን አለመሰየማቸው ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ችግሮች ደብሩን ለብዙ የከፉ ችግሮች  ምሳሌ የሆነ ደብር አድርጎታል፡፡
እነዚህ ሁሉ በጊዜው መስተካከል ቢችሉ ኖሮ ነገሩ እዚህ ደረጃ ላይ ባለደረሰም ነበር፡፡ ያ ባለመሆኑ ግን ለሙሰኞቹና ተባባሪ ለሆኑት በጥፋታቸው እንዲገፉና ሌላ ሕገወጥ ድርጊት አለቃን እስከ ማገድ አድርሷቸዋል፡፡
በቅርቡ በአክራሪነትና ጽንፈኛነት ዙሪያ የተደረገውን ሥልጠና ተከትሎ ማኅበረ ቅዱሳን በደብረ ሲና እግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን ውስጥ የአሰላለፍ ለውጥ ማድረጉ እየታየ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ወጣቶችን ሲጠቀም የነበረው ማቅ ትግሉን ከወጣቶቹ እጅ አውጥቶ ወደ ሽማግሌዎች (ወደሰንበቴ ማኅበራት አመራሮች) ጉያ ከቶታል፡፡ ይህም የሆነው ሽማግሌዎቹ በአክራሪነት አይፈረጁም ብሎ ነው፡፡ ያልገባው ነገር ግን የፉካ ነጋዴዎቹ የቀድሞ የደርግ ወታደሮችና በምርጫ 97 ፖለቲከኞች የነበሩ መሆናቸው ነው፡፡ አሁንም በሃይማኖት ካባ ውስጥ የተደበቁ ፖለቲከኞች መሆናቸውን የማያውቅ የለም፡፡ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ማራመድ ይችላሉ ነገር ግን ሃይማኖትን ለፖለቲካ መጠቀም አግባብነት የለውም፡፡ ስለዚህ ለባለቤት አልባው ደብር ባለቤት  ያስፈልገዋል፡፡    

2 comments:

  1. እናንተ ወረኞች ክርስትና የሓሜትና የቧልት ሕይወት አይደለም፡፡ በዓይኖቻችሁ ዉስጥ ያለውን ሞፈር ሳታወጡ የሌሎችን ጉድፍ እንዴት ማጥራት ትችላላችሁ? የናንተ ነገር እኮ ጅብ በማይታወቅበት አገር ሄዶ “ቁርበት አንጥፉልኝ” እንዳለ ዓይነት ነው፡፡የማያውቃችሁና ክርስትና ያልገባው ሰው ለጊዜው ቢወናበድም እርስ በርስ እየተጣረሰና በውሸት የተሞላውን መልክቶቻችሁን እያነበበ በሄደ ቁጥር ጅብነታችሁን እየተረዳ እንደሚሄድ አልጠራጠርም፡፡ የክርስትናና የክርስቲያኖች መንገዳቸው እውነት ብቻ ናት፡፡ እናንተ ግን የተገለጠ ሐሰትን መከተል ስለመረጣችሁ የሐሰት አባት ዲያብሎስ አባታችሁ ነው፡፡ ስለሆነም ጨለማ ከብርሃን ጋር ምንም መጋጠም የለውም፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆችን ከጨለማ ይሰውረን፡፡ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በጨለማ አገዛዝ ውስጥ ያሉትንም ወገኖቻችንም ነጻ እንዲያወጣቸው የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡ የወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡

    ReplyDelete