Friday, September 4, 2015

በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተዘጋጀው የሁለት ቀናት ሥልጠና እየተካሄደ ነው Read in PDF
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥር በሚገኙ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ካህናት ሰባክያን የሀገረ ስብከቱ ተወካዮችና ሌሎችም ከ900 በላይ የሆኑ የተሳተፉበትና በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተዘጋጀው የ2 ቀናት ስልጠና በትናንትናው ዕለት ተጀመረ፡፡ በሥልጠናው ላይ የተገኙት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያምና “በሃይማኖት ተቋማት ያለመግባባት ጉዳዮች መሠረታዊ የመፍትሄ አቅጣጫ” በሚል ርእስ በሚንስትሩ የቀረበውና በውይይት እንዲዳብር የሚጠበቀው ጥናት የተሳታፊዎችን ትኩረት ስቦ እንደነበር ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ የቡድን ውይይቶችም ተካሂደዋል፡፡
በጥናቱ ላይ እንደተመለከተው በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ እየታየ ያለው አለመግባባት መልኩን እየለወጠ መምጣቱን በሚመለከት “ከዚህ ቀደም አልፎ አልፎ እንደሚታየው [በሃይማኖት ተቋማት መካከል ወይም] በመካከላቸው ሳይሆን በውስጣቸው አይሎ የሚታይበት ሂደት እየተስተዋለ መጥቷል፡፡” ለዚህም አንዱ ምክንያት የሃይማኖት ተቋማትን “መንፈሳዊና ሰላማዊ ተልእኮ ለራሳቸው በሚመቻቸው ትርጉም አዛብተው በማቅረብ አንዱን የሃይማኖት ተከታይ በራሱ እምነት ውስጥም ይሁን ከሌሎች ሃይማኖቶችና እምነቶች ጋር ጠላትነትን በማሥረጽ ከተከታዩ ፍላጎት በተቃራኒው ሕዝብና ሕዝብ እንዲጋጭ ለማድረግ የሚጠቀሙ የሃይማኖት አመራሮች የሚታዩበት አጋጣሚ ጥቂት አይደለም፡፡” በማለት ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገ አክራሪነት የሚንጸባረቅ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በእምነት ተቋም ውስጥ አለመግባባት እንዲፈጠር የሚፈልገው ቡድን ስሙን የሚያስጠራበት የእምነት ተቋም ቢፈርስ ግድ እንደሌለውና የእርሱ ፍላጎት የራሱ የሆነውን ድብቅ ዓላማ ማሳካት ነው፡፡ (ከዚህ የሚኒስትሩ ገለጻ ተነሥተን በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሚታየውን እውነታ ካስተዋልን ማኅበረ ቅዱሳን እየተንቀሳቀሰ ያለው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ማኅበሩ ቤተክርስቲያኗን በስሟ ለመነገድ ካልሆነ በስተቀር እንደማይፈልጋት በውስጧ እያፈጠረ ያለውን ትርምስና የራሱን ስም እየተከለ የሄደበትን ሁኔታ መመልከቱ ብቻ ይበቃል፡፡ የማኅበሩ ግልጽና ስውር አመራሮች በዓላማ፣ እውነት መስሏቸው የሚከተሉት የዋሃን ደግሞ ባለማስተዋል ራሳቸውን “ማኅበረ ቅዱሳን” እያሉ መጥራታቸው ከበስተጀርባው ያዘለው ድብቅ አጀንዳ ለመኖሩ አንድ ማሳያ ነው፡፡)
እንደሚንስትሩ ገለጻ አክራሪዎች ጽንፈኞችና አሸባሪዎች ከሚታወቁባቸው ነገሮች መካከል ቆመንለታል የሚሉትን የእምነት ተቋም በሚገባ የማያውቁ፣ ወደዚያው የማይሄዱ፣ ያሉትን አባቶች የማያውቁ እና የእምነቱን መመሪያ ጠንቅቀው የማያውቁ መሆናቸው ነው፡፡ 24 ሰዓት ይሠራሉ የቅዱሳት መጻሕፍት ጠበቃም ሆነው ይነሣሉ፡፡ ሕዝቡን በራሳቸው አስተሳሰብ ብቻ ይቀርጻሉ፡፡  እነርሱ በቀረጹት አስተሳሰብ ያልሄደውን ከሃይማኖቱ የወጣ ብለው ይፈርጃሉ፡፡ (በዚህም መሰረት ቤተክርስቲያኒቱን ስንቃኝ በኦርቶዶክስም አክራሪነት እንዲያቆጠቁጥ እያደረጉ ያሉት ቡድኖች በተለይም ማቅ ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ እነዚህን እንደሆነና እነዚህን እንደሚያደርግ የማያውቅ የለም፡፡ እንደውም ሚንስትሩ የአክራሪነትን ባሕርያት ሲያስረዱ ተሰብሳቢው ሁሉ ማቅን እያሰበና ከማቅ ጋር እያገናኘ እንደነበር በፊቱ ላይ የሚታየው ስሜት አፍ አውጥቶ ይናገር ነበር፡፡ አክራሪነት ስለመኖር አለመኖሩ ጥያቄ በቀረበ ጊዜ አብላጫው ሰው በመኖሩ ተስማምቷል፡፡)
ከሁሉም ተሳታፊውን የኮረኮሩትን ያህል ያሳቀው አክራሪነትን እያሰረጹ ያሉት ቡድኖች ተከታዮችን የሚመለምሉበትን ስልት ሚንስትሩ ባብራሩ ጊዜ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሰልት ቀስ ብሎ መጠጋት ሲሆን ከዚያም ቀስ ብሎ ማስታጠቅ በመጨረሻም ማሰማራት ነው፡፡ (ተሳታፊው የሳቀው ከዚህ ቀደም ማቅ እነዚህን ስልቶች በሙሉ እንደተጠቀመባቸው በማስታወስ ነው ተብሎ ተወስዷል፡፡ መብታቸውን አውቀውና መደራጀት እንዳለባቸው አምነው ሳይሆን ማቅ ተጠግቶ የመለመላቸውና የተለያየ ነገር አስታጥቆ ያሰማራቸው የሰንበት ት/ቤት አንድነት ጉባኤ ተብዬዎች፣ ከጥምቀት ተመላሽ ወጣቶች የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ምልምሎች ማቅ የሰጣቸውን ተልእኮ ብቻ ለመፈጸም የሚተጉ ናቸው፡፡)
ሌላው በሚኒስትሩ የተነሣው ነጥብ አክራሪዎች ይሁንታን ለማግኘት ለሃይማኖታችን ነው ተብሎ የተሰበከ ህዝብ ለምን? እንዴት? የት ብሎ አይጠይቅም ብለው ስለሚያስቡ ምእመኑ ላይ እንዲህ ያለ ስራ ይሰራሉ፡፡ ይህም የሚያሳየው ምእመኑን መናቃቸውን ነው ብለዋል፡፡ (በዚህ አቅጣጫም ማቅ እየሰራ እንዳለ መገንዘብ እንችላለን፡፡ በተለይም “ተሐድሶ መናፍቃን” እያለ ለአስተሳሰቡ አደገኛ ናቸው ብሎ የፈረጃቸውን ወገኖች በማሳደድና ሕዝቡንም ባገኘው አጋጣሚ ቤተክርስቲያንን እናድሳለን እያሉ እነ እገሌ ሊያፈርሱልህ ነው ተነሥ እያለ በሃይማኖት ሽፋን ዓላማውን ለማሳካት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ እርሱ ተሐድሶ መናፍቃን የሚላቸው ወገኖች በአብዛኛው የእርሱን ፍላጎት አንቀበል ያሉት እንጂ መናፍቃን ሆነው አይደለም፡፡)
ሌላው ሚኒስትሩ የጠቆሙት በማኅበራት አደረጃጀት ውስጥ የሚስተዋለውን ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ችግሩ አደረጃጀቱ ሳይሆን ማኅበሩን ተንተርሰው የሚፈልጉትን ማስፋፋታቸው ነው፡፡ በማኅበራዊ ትስስር ውስጥም እስከ እድር ሳይቀር ዓላማቸውን ለማስፋፋት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ (በዚህ ላይ ማቅ ምን ይመስላል የሚለውን ስንቃኝ ይህን መንገድ የሚጠቀም ሆኖ ነው የምናገኘው፡፡ ከላይም እንደ ጠቆምነው ማቅ ወደተደራጁት ሰርጎ በመግባት ወይም በተለያዩ ስሞች አደረጃጀቶችን በመፍጠር ስውር ዓላማውን ለማሳከት ሌተቀን እየሠራ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የሰንበት ት/ቤት አንድነት ጉባኤ ማቅ ምን እየሰራ እንደሆነ መጥቀሱ ብቻ እንኳን ከበቂ በላይ ነው፡፡ በቅርቡ በእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የሰንበቴ ቤቶችና የእድር አመራሮችን ለአመፅ ማነሳሳቱ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡)
ሚንስትሩ አክለው እነዚህ አክራሪዎች የሚበለጽጉበት መንገድ ሲዲና መጽሐፍ በማባዛትና ለገበያ በማቅረብ ነው፡፡ ምእመኑን ግዛ እያሉ ግጭት ይፈጥራሉ፡፡ በአቋራጭ የፖለቲካ ሥልጣንም ለመያዝ ዘወትር ስለሚያልሙ ለዚህም ቤተ ክርስቲያን ክብሯ ሞገሷ ቀንሷል ተገቢው ክብር አልተሰጣትም ይላሉ፡፡ ውስጣቸው ሲፈተሽ ጽንፈኞች ትምክሕተኞች ጠባቦችና ጎጠኞች ናቸው፡፡ (በኦርቶዶክስ ውስጥ አክራሪነትን እያስፋፋ ያለው ማቅ ከእነዚህ ያልፈጸመውና ያልሆነው የለም፡፡ ማቅ በአብዛኛው እያሳተመ የሚሸጠው ሲዲና መጽሐፍ ከቤተክርስቲያኗ ትምህርት ውጪ የሆነ ሁከትና መለያየትን ለመፍጠር ያለመ ነው፡፡ የሰውን ዘር በኃጢአት እንዲሞት ላደረገው ለአዳም ገድል ከማሳተም ጀምሮ ቤተክርስቲያኒቱን ከወንጌል ጉዞዋ ወደኋላ በመመለስ፣ በሌሎች ላይ ስድብና ትችት ያዘሉ መጻህፍትን በማሰራጨት ጠብ ያለሽ በዳቦ አይነት አካሄድን የሚሄድ በዚህ መንገድ ለሰው መንፈሳዊ ርካታን የሚሰጡ ሳይሆን በመንፈሳዊ ሕይወቱ ላይ አዚምና ድንዛዜን የሚረጩ ጠብና ክርክርን የሚያስነሱ ሥራዎችን በመስራት እየነገደ የሚያተርፍና ዓላማውንም ውስጥ ውስጡን ለማሳከት የሚተጋ ቡድን ነው፡፡ ሌሎቹም ሁሉ የእርሱ መገለጫዎች ናቸው)፡፡
ከላይ በጥቂቱሩ የተጠቀሰው የሚንስትሩ ጽሑፍ ሲቀርብ በአዳራሹ የተሰበሰበው ከ900 በላይ ተሳታፊ ጭብጨባ አልተለየውም፡፡ ሚኒስትሩ በዚህና ይህን በመሳሰሉ ነጥቦች ዙሪያ አሳባቸውን ያቀረቡ ሆኖ እያለ የተጻፈውን ገልብጦ በማንበብና ሐሰተኛ ዘገባ ደርሳ በማቅረብ የምትታወቀውና ከዚህ የተነሣ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን “አዋልድ” እየተባለች የምትጠራዋ ሐራ ግን ይህን ሳይሆን ሚኒስትሩ ምኑን ነው የፈራችሁት? የሙዳየ ምጽዋቱን እንደኾነ ሕዝብ ሰምቶታል እንዳሉ፣ አክለውም ለማቅ አስተሳሰብ አለመመቸታቸው ስላልተመቻት “አማሳኞቹ ስለ አክራሪነት እና ጽንፈኝነት በሚደረገው ውይይት እንደለመዱት ማኅበረ ቅዱሳንን ወንጅለው ራሳቸውን በመሸፈን የውይይቱን ሒደት እና የጋራ አቋም ለመቆጣጠር ተዘጋጅተው ከኾነ፣ ጊዜአችኹን አታጥፉብለዋቸዋል፡፡” ስትል በሬ ወለደ ወሬዋን ነዝታለች፡፡ ደስ የሚለው ነገር ግን ሐራ የምትዘግበውን በቀጥታ ሳይሆን ገልብጦ መረዳት እንደሚያስፈልግ ሁሉም እያወቀ መምጣቱ ነው፡፡
           

3 comments:

  1. የማቅ ኑሮ ይለያል ዘንድሮ (2008 ዓ•ም•)

    ReplyDelete
  2. እናንት የእፉኝ ልጆች እንዴትስ በአባ ሰሳማ ስም ተሸሽጋችሁ እውነት መናገር ትችላላሁ? አንድም ነገር ተናግራችሁ እውነት ያልሆነ የእናንተ እንጂ በሀራ ተዋኅዶ የሚቀርበው አይደለም። ስለዚህ እውነት ትከሳለች እንጂ አትሞትም። ሁሉንም እግዚአብሔር ሁሉን ያደርጋል።

    ReplyDelete
  3. በሬ ወለደ ዉንጀላ የምታካሂዱ እናንተ ሳማዎች ናችሁ

    ReplyDelete