Thursday, October 29, 2015

ይድረስ ለዲ/ያረጋል የፀረ ተሃድሶ እንቅስቃሴ አባልና አስተባባሪ


Read in PDF
የሰሜን አሜሪካ ኮንፈረንስ ላይ ስለተሐድሶዎች ያቀረብከው መግለጫ ውሸት የተሞላበት ነው ።
የተሃድሶ እንቅሥቃሴ በአስገራሚ ፍጥነት እያደገ መምጣቱ ከተጠበቀው የጊዜ ግምት እጅግ የፈጠነ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ሐሳቡ ከቀሳውስትና ከቤተ ክህነት ሰዎች እጅ አፈትልኮ ወደ ሕዝቡ በመድረሱ ነው። የተሃድሶ እንቅስቃሴ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በባነኑ ካህናት በስውር እና በዝግታ ለረጅም ጊዜ ይካሄድ የነበረ እንቅሥቃሴ ነው። ማህበረ ቅዱሳን ግን ካህናቱን ያገላጥሁ መስሎት ሐሳቡን ለሕዝብ በመግለጡ ሕዝቡ በተቃራኒው ተሐድሶዎችን ፍለጋ ያዘ። እውነት ለመናገር ከሁለት ሺህ አራት ዓ.ም ሕረቱ ውግዘት ወዲህ ለተሀድሶዎች ሥራ በዝቶባቸዋል። ማህበረ ቅዱሳን ለግንዛቤ በማለት በየአዳራሹ እየሰበሰበ ተሃድሶን ለሕዝብ በማስተዋወቁ በርካታ ወጣት ባስፈሪ ሁኔታ ተሀድሶውን ተያይዞታል። ይህ ጉዳይ እንኳን ለማህበረ ቅዱሳን ለተሃድሶ መሪዎችም አሳሳቢ ሆኗል። ከእንቅሥቃሴነት ወደ ማዕበልነት ሊቀየር ይችላል የሚል ሥጋት አለ። ሥጋቱ የተፈጠረው ይህን ማዕበል ባግባቡ መምራት የሚችል ጠንካራ ተቋም ባለመኖሩ ነው። ይህን የተሃድሶ እንቅሥቃሴ ራሱ ቤተ ክህነቱ ቢመራውና አቅጣጫ ቢያስይዘው ለቤተ ክርስቲያን ትልቅ እድል ነበር። ነገር ግን በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል? እንደተባለው ተሃድሶን እንከላከላለን በሚሉ ሞኝ ወንድሞች ምክንያት ቤተ ክርስቲያን እንደተቋም የእንቅሥቃሴው ተጠቃሚ እንዳትሆን እያረጉ ነው።
ይህን ካልኩ በኋላ ወደ አንተ ልመለስ ዲያቆን ያረጋል ለኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ያቀረብከው ሪፖርት ተሃድሶዎች ያላሉትን እንዳሉ አድርገህ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ውሸት ሲገለጥ ሰዎችን እንዲሸሹ ያደርጋል እንጂ አንዳች ፋይዳ አይኖረውም። አሁን የዚህ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ተሃድሶዎችን ቢያገኙና ቢጠይቁ ያረጋል ስለተሃድሶዎች ከተናገርከው ስለሚለይ እንዲህ ዓይነቱን ውሸታም ሰው በቀላሉ ለመሸሽ ምክንያት ይሆን ነበር። እስኪ በራስ መተማመኑ ካለ ከተሃድሶዎች አንዱ በዚህ ኮንፈረንስ ላይ ተጋብዞ ይጠየቅ! አንተ እንደምትከሰው ሆኖ ይገኝ ይሆንን?  ዲያቆን ያረጋል ስለተሃድሶዎች ስትናገር ከሰማሁት ውስጥ ጥቂቶቹ፦

“ተሃድሶዎች የአርዮስ የንስጥሮስና የግኖስቲኮች ተከታዮች ናቸው” ብለሃል። ይህ አባባል አንድም እውነት የለውም። ተሃድሶዎች በሦስት አካል አንድ አምላክ ብለው እንደ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የነገረ መለኮት ትንታኔ የሚያምኑ በመሆናቸው ወልድ ፍጡር ያለውን አርዮስን ይከተላሉ ማለት ትዝብት ላይ የሚጥል ነው። ማስረጃ ካስፈለገ የዋናውን ተሃድሶ የአለቃ መሠረት ስብሐት ለአብን "ስላሴ በተዋሕዶ” የሚለውን መጽሐፍ ማንበብ በቂ ነው። ስላሴ በተዋሕዶ በቅድስት ሥላሴ እና በኮልፌ በቅዱስ ጳውሎስ ኮሌጆች ላይብራሪ ይገኛል። የነገረ መለኮት አስተማሪዎች ሁሉ ከሥላሴ በተዋህዶ እየቀዱ እንደሚያስተማሩ የታወቀ ነው። ታዲያ የዋናው ተሐድሶ ያለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ መጽሐፍ ዋና መማሪያ ሆኖ እያለ ተሃድሶዎች ያርዮስ ተከታዮች ናቸው እንዴት ትላለህ?
ንስጥሮስ የቃልን ሥጋ መሆን የካደ ነው ተሃድሶዎች ግን ቃል ሥጋ ሆነ ብለው የሚያምኑ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የምሥጢረ ሥጋዌ ትንታኔ መሠረት የሰለጠኑ ናቸው። የጮራ መጽሔት ስለምስጢረ ሥጋዌ የተነተነውን ፈልጎ ማንበብ ብልሕነት ነው።
ግኖስቲኮች መዳን በእውቀት ነው ብለው ያምኑ ነበር። ተሃድሶዎች ግን መዳን በእምነት ነው ብለው ያምናሉ። ስለዚህ ያረጋል ስትቃወም በእውነት ብትቃወም ስላልገባው ነው ይባል ነበር። ግን የተሃድሶዎችን ማንነት እያወቅህ ለጊዜው አላዋቂ የሆኑ ሰዎችን ማደናገርህ ጥሩ ሊመስልህ ይችላል እነዚህ ሰዎች እውነቱን ያወቁ ዕለት ግን ብዙ መዘዝ አለው። ምን ያህል ዘመን ማታለል ይቻላል? ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው።
“ተሃድሶዎች ወዲያው እንዳመንን ወዲያው እንድናለን ከዳንን በኋላም ኃጢአት ብንሠራ ምንም አይደለም ይላሉ” ብለሃል። ወይ ያረጋል ምን ያህል ሰዎችን አታለሃል? ተሃድሶዎች ኃጢአትን በየዌብሳይታቸው እያጋለጡ የሚቃወሙት ኃጢአት ብንሠራ ምንም አይደለም ብለው ስለሚያምኑ ነውን? ተሃድሶ ማለት ከኃጢአት ነጻ መውጣት ማለት ነው። ኃጢአትን ካልተው ምኑን ተሃድሶ ሆኑት ኃጢአትንስ ለምን ይቃወማሉ?።
አዎን ተሃድሶዎች የመዳን ቀን አሁን ነው ብለው ያምናሉ። ያመነ የተጠመቀ ይድናል ስለሚል ቃሉ አምኖ የተጠመቀ ተሃድሶ፣ ድኛለሁ ብሎ ያምናል። ይህ ማለት ድሮ የምሠራውን ኃጢአት አሁን አልሠራውም፣ ድሮ የምናገረውን ውሸት አሁን አልናገረውም አሁን እንደ ድሮው አይደለሁም። ይህን ሕይወት ያገኘሁትም ስለኔ በሞተው በእግዚአብሔር ልጅ በማመኔ ነው ብሎ ያምናል ተሃድሶ። ያረጋል ድኛለሁ እያለ አሁንም ኃጢአትን የሚያደርግ ተሃድሶ ካየህ እርሱ ተሃድሶ አይደለም ምን አልባት የተሃድሶ አጃቢ ሊሆን ግን ይችላል። ለዚህ ነው አንዳንዶችን ተሃድሶ እያላችሁ ስትኮንኑ ያለስማቸው ስም አትስጡ የምንለው። ለነሱ ስም ተቆርቁረን ሳይሆን ይህን የከበረ ስም በባለጌ ሰው ላይ ስትለጥፉ ቅር ስለሚለን ነው። ተሃድሶ ማለት ከኃጢአት ባርነት ነጻ የወጣ ማለት ነው። አንተ በሪፖርትህ ላይ እንዳቀረብከው። በየአብነት ትምህርት ቤቶች፣ በገዳማትና በአድባራት ከጥንቆላ ከድግምት ከበቀለኝነት ከዘረኝነት ነጻ እየወጡ ተሃድሶ የሆኑ ብዙዎች ናቸው። አንተ የምታምነውን ስሕተት ስለማያምኑ ሃይማኖት ቀይረዋል ማለት የለብህም። እነርሱ ክርስቶስን በመረዳት የሕይወት ለውጥ አድርገዋል ይህም በተሃድሶ እንቅሥቃሴ እየተድረገ ያለ ነው።
አንድ ገጠመኝ ልንገርህ በጎጃም እርባብ በሚባለው አካባቢ በተደረገው የተሃድሶ እንቅሥቃሴ በርካታ መርጌቶች ንስሐ ገብተው አንዳንዶች የጥንቆላ መጽሐፋቸውን አቃጥለው መጽሐፍ ቅዱስን አነሱ። በዚህ ጊዜ ሌሎች ሥልጠናውን ያልወሰዱ ቀሳውስት መናፍቅ ሆነዋል ብለው አሳደሙባቸውና የሕዝብ ስብሰባ ተደረገ፣ ክስ ሆኖ የቀረበው "መድገም ተትዋል” የሚል ነው። ከተከሰሱት አንዱ ብድግ ብለው ድሮ እየጠነቆሉ በሕዝባቸው ላይ የፈጸሙትን በደል ከተናዘዙ በኋላ አሁን ግን በክርስቶስ ከዚህ ክፉ ነገር መዳናቸውን አወጁ። ድሮ በጥንቆላ ስኖር ወዳጆቼ ነበራችሁ አሁን ንስሐ ገብቼ ወደ እግዚአብሔር ስመለስ እንዴት ጠላት ትሆኑኛላችሁ? ብጠነቁል ይሻላችኋል? ሲሉ ሕዝቡን ጠየቁ። ከሕዝቡ ሽማግሌዎች እየተነሱም ይህን እርምጃቸውን ደገፉላቸው እባካችሁ ሌሎች ተንቋዮችንም እናንተ ከሄዳችሁበት ውሰዱልን በማለት ሕዝቡ ክሱን ውድቅ አደረገው። ተሃድሶ ማለት ተስፋ ያለው እንቅስቃሴ ነው የምንለው እየተሠራ ያለውን አስደናቂ ነገር ስለምናውቅ ነው። ለኢትዮጵያ መንፈሳዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትንሣኤ ተሃድሶ ወደር የማይገኝለት ተስፋ ነው። ይህ መፈጸሙ ላይቀር ብዙ ባትደክም ይሻልሃል።
ተሃድሶዎችም ድነናል የሚሉት ከእንደዚህ ዓይነቱ አስከፊ ሕይወት በትክክል ስለዳኑ ነው። አንተ መዳን የምትለው ምኑን ነው? መዳንኮ ከኃጢአት ነው ወንድሜ። አሁን እኒህ ጠንቋይ መርጌታ አልዳኑም ብለህ ልተከሳቸው ነው? ወይስ "እርሱ ከጨለማው ሥልጣን አዳነን ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ሥርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን” ከቶ ለማን ብሏል? ቆላ. 1፥13። ብዙዎች ከኃጢአታቸው እየዳኑ መልካም ሰዎች እየሆኑ ነው። እግዚአብሔርን መፍራት ጀምረዋል። እንዴት ይህን በጎ ጅምር ትቃወማለህ? እኔ ያንተ ተቃውሞ ተሃድሶን ያስቆማል ብዬ ቅንጣት ያህል እንኳ አልደነግጥም እየሆነ ያለውን ታምር እማውቀው ስለሆነ ለሚሰማ ሁሉ ምክር እንዲሆን ነው እዚህ የምጽፈው።
ከዳንን በኋላ ምንም መልካም ነገር አያስፈልገንም ይላሉ ያልከው ከንቱ ክስ ነው። አንተ እነሱን ለመክሰስ "በፍርሐትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ” የሚለውን ቃል ከፊልጵስዩስ 2፥12 ላይ ጠቅሰሃል። ተሃድሶዎች በዚህ ቃል ያምናሉ። ምክንያቱም መዳናቸውን ለመፈጸም እየታገሉ ነው ያሉት። የምንፈጽመው ምኑን ነው? መልሱ የጀመርነውን ነው። ተሃድሶዎች ድነናል አሉ እንጂ ፈጽመናል አላሉም። አንተ አልዳንሁም ብለህ የምታምን ከሆነ ታዲያ ምኑን ነው የምትጨርሰው? እድሜህን ነውን? መዳንን መፈጸም ማለት በክርስቶስ ላይ ባለህ እምነት እስከመጨረሻው መጽናት ማለት ነው። ድንገት በክርስቶስ አዳኝነት ላይ ያለህን እምነት ብትክድ ግን መዳንህን አልጨረስህም ማለት ነው። ወይም ወደቀደመ ኃጢአትህ ብትመለስ ተመልሰህ የኃጢአት ባሪያ ሆንህ ማለት ነው። ስለዚህ ተሃድሶዎች በክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት ጸንተው ለመኖር እየተጉ ናቸው። ይህ ስደት እና መከራ ተጋድሎ አይደለምን? ወይስ ወይስ በገደልና በተራራ ኃጢአት ለማስተስረይ መዞር አለብን? በሥጋ ኃይል ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ከኃጢአት ርቀን እንኖራለን ብለው ያምናሉ ተሃድሶዎች። ከኃጢአት የምንርቀው ሁልጊዜ በመንፈስ ስንመላለስ እንጂ በግሸን ተራራ ላይ በያመቱ ስንመላለስ አይደለም ብለው ያምናሉ። ምክንያቱም የኃጢአት ሥርዬት በክርስቶስ ደም እንጂ በጉልበት አይደለም። ከዚህ እምነትም ሳይጨረሱ አያፈገፍጉም።
 ተሃድሶዎች የቅዱሳንን አማላጅነት ይክዳሉ። ለዚህም ቅዱስ ጵውሎስ በመልእክቶቹ ጸልዩልኝ እያለ የጻፈውን በመጥቀስ እኛም እንደርሱ ጸልዩልን እንላለን እንጂ ቅዱሳንን አላመለክም ብለሃል። አንድ ጥያቄ መልስልኝ ቅዱስ ጳውሎስ ጸልዩልኝ ብሎ መልእክቱን የላከው ወደ አረፉ ቅዱሳን ነው ወይስ በሕይወት ወዳሉ የወቅቱ ክርስቲያኖች? ጳውሎስ ከእርሱ በፊት ወደ አረፉ ቅዱሳን ጸልዩልኝ እያለ ጸልዮ ነበር ወይም መልእክት ልኳል እያልክ ነው?
ወንድሜ አንተና ጳውሎስ የተግባባችሁ አልመስለኝም አንተ እየጸለይክ ያለከው ወደ አረፉ ቅዱሳን ነው እነርሱ አምላክ አይደሉምና ሊያውቁህ አይችሉም፤ ጳውሎስ ግን በአገልግሎቱ ዘመን በጸሎት ያግዙት ለነበሩ ቅዱሳን እንዲያማልዱት ጠይቋል። አሁን በምድር ላይ ያሉ ቅዱሳን አሉ በገዳምም በደብርም በመንደርም እነርሱን ጸልዩልኝ ብትል ትክክል ነህ። ተሃድሶዎችም በዚህ ያምናሉ ስለሚድኑ ሰዎችም ይጸልያሉ ተሃድሶዎች ወንጌል ሊነግሩት ያሰቡትን ሰው መጀመሪያ እንደሚጸልዩለት አውቃለሁ ስለነርሱም የሌሎችን ጸሎት ሲፈልጉ አይቻለሁ። ወደ ሞቱ ቅዱሳን ግን አይጸልዩም። ይህን የሚያምነው ደግሞ ተሃድሶዎች ብቻ ሳይሆኑ ውዳሴ ማርያም አንድምታ የተማሩ ሁሉ የሚያምኑት ነው። ሰአሊ ለነ ቅድስት የሚለው ቃል ሲተረጎም "ልመናስ ስንኳን በርሷ በሌሎችም የለባቸውም በቀደመ ልመናዋ የምታስምር ስለሆነ እንዲህ አለ እንጂ” ይላል። ያረጋል የተሃድሶዎች ስር የሰደደ ጥላቻ ስላለብህ ይህን የቤተ ክርስቲያኒቱን እውነት ክደህ የተሃድሶዎች መወንጀያ ማድረግህ በእግዚአብሔር ዘንድ ያስጠይቀሃል።
“አይጸልዩም አይጾሙም” ያልከውም ውሸት ነው። በእርግጥ ድርሳነ ሚካኤል የሰኔ ጎልጎታ ምናምን አይደግሙም። አለመድገም ግን አለመጸለይ አይደለም። ጸሎት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር እንጂ ለእግዚአብሔር መድገም አይደለምና። አንተ ግን ድርሳነ ሚካኤል ስትደግም ከሚካኤል ጋር፤ የሰኔ ጎልጎታ ስትደግም ከማርያም ጋር እየተነጋገርህ ነው። ስለዚህ ጸሎት ማለት ከሚካኤል ጋር መነጋገር ነው ብለህ ተርጉም ከሚካኤል ጋር እየተነጋገርህ፤ ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋርሁ ነው ብለህ አትዋሽ። ተሃድሶዎች ወደ እግዚአብሔር ብቻ ይጸልያሉ ሲጸልዩም ከልብ የልባቸውን ነገር እያወጡ በመናዘዝና እግዚአብሔርን በግልጽ በመጠየቅ እንጂ በማይገባቸው ቋንቋ በመድገም አይደለም። ስለዚህ ለሚካኤልና ለገብርኤል ያልደገመ እየጸለየ አይደለም ብለህ ያቀረብከው ክስ ዋጋ ዘቢሎ ነው። ያረጋል አንተም አንድ ቀን ጊዜህ ሲደርስ የሕይወት ተሃድሶ እንድታገኝ እየጸለይሁልህ በክርስቶስ ሰላምን እመኝልሃለሁ።
የስብሰባህ ተሳታፊ ነኝ   

24 comments:

 1. We need this kind of post. Orthodox for Christ! Gospel! Gospel! Gospel!

  ReplyDelete
 2. ማህበረ ቅዱሳን ገቢ ከሚያስገባባቸው ጉዳዮች አንዱ ተሐድሶ ነው፡፡ ተሐድሶን ለሕዝቡ አስፈሪ አድርጎ በማቅረብ ለእርሱ ደግሞ ከፍተኛ ገቢ ማሰባሰቢያ አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ በውጪ ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥም አንዳንድ ቦታ ነጋዴዎቾ እየሠበሰበ ስለተሐድሶ ግንዛቤ በማስጨበጥ ስም ገቢ እያሰባሰበ ነው፡፡ በአንድ በኩል አላማው ገንዘብ ነው፡፡ ስለዚህ ዲያስፖራዎች ነቄ በሉ

  ReplyDelete
 3. እንዲህ ነው እንጂ "ተሳታፊ" ይበል ብለናል እግዚብሔር የቤተክርስቲያናችንን ተሐድሶ ያሳየን

  ReplyDelete
 4. ያረጋል እስከመቼ ግንዛቤ አስጨባጭ ሆነህ ትቀጥላለህ? እውነተኛውን ግንዛቤ ሳትጨብጥና የሕይወት ተሐድሶ ሳታገኝ ጀንበርህ እንዳትጠልቅ እባክህን ወደ ክርስቶስ ተመለስ፡፡ የሚያድንህ በክርስቶስ ማመንህ እንጂ ማሕበረ ቅዱሳን ድርጅትህ አይደለም፡፡

  ReplyDelete
 5. Good job brothers, let us connect our life with holy bible. Our brothers accuser is only Satan or devil.we are believe in Lord Jesus Chris is our savior who died on the cross for our sin. Thanks guys. No more foolishness, we all learning bible everyday anytime anywhere.........

  ReplyDelete
 6. pure protestant teaching!so what is the deference between THEADSO&PROTESTANT?Are you trying to fool us?We know Ato Meseret Sibhatleab was a teacher within Mekaneyesus church.How he could be a reference for Orthodox Christianity?I think You guys indeed belief talking false in the name of Jesus isn't sin!what an hypocrite u are!Ur teaching only go hand with hand with protestants only!The rest Christian world already rejected u.why trying to mislead others?why not establish ur own church?Let the Almighty open ur heart!

  ReplyDelete
  Replies
  1. Are U Shure ?
   Before to say this kind of trash word first do this : On Mat. 7 "And why beholdest thou the mote that is in thy brother's eye, but considerest not the beam that is in thine own eye?"

   Delete
 7. I knw that our mother church orthodox tewahido teaches us salvation is gained by three things 1. God Grace 2. Faith and 3. Good works (i.e.that is the fruit of the spirit) This is what our fathers teach us.I strongly DISAGREE with you about intercession, our church believes that those who depart from this earthly world knows what is going on this world because our God is the God of living not the God of dead. Why do not you refer the books written by Coptic orthodox church if you are quarreling with the language. You are always accusing people and Mahibere kidusan.

  ReplyDelete
 8. waw be blessed bro

  ReplyDelete
 9. ይገርማል፤፤ በቃ ለየላችሁ ተሐድሶዎች?
  በሉ እንግዲህ ሞክሩት እስቲ ፤፤ ቤተ ክርስቲያን ሁሌም የማትታደስ ናት፡፡

  We confess a church is One, Holy, Universal & Apostolic.
  We shall convey for the coming generation, what we have received from our Lord Jesus Christ, through Holy apostles & Apostolic Fathers until the last time of the world.

  ReplyDelete
 10. አየ ያረገል ኑፋቄህን ነበር ያነበብህዉ ፍጹም ዉሸታም ነህ ተሀድሶዎች የማይሉትን ተናግረሃል እንጸልይልሀለን አንተም ይገባሃል አንድ ቀን

  ReplyDelete
 11. ዎዳጆች እዉነት ብላችኋል........... አንዳንዶች ተሃድሶን ያጋለጡ እየመሰላቸዉ ባዘጋጁት መጽሃፍ ፣ የቪዲዮ እና ሌሎች የኢንተርኔት ድረገጾቻቸዉ ለብዙዎች ተሃድሶን ለማወቅ ምክንያት ሆነዋል ለዚህ ደግሞ አንዱ ምስክር እኔ ነኝ! እንደነ ያረጋል ያሉ የሃይማኖት መምህርን የሚጽፏቸዉን መጽሃፎች አነብ ነበር........ ሰዎች እዉነቱን እንዲያዉቁ በሚል ከመጽሃፉ ያገኘኋቸዉን ነጥቦች በመጠቀም ሰዎችን ለማስረዳት እሞክር ነበር ........ ነገር ግን የገጠመኝ ነገር ቢኖር ከላይ እንደገለጻችሁት የተሳፈዉ እና የተጻፈባቸዉ ሰዎች ሁኔታ የተለያየ ሁኖ ነበር ብዙ ግዜ የማገኘዉ............. በዚህ ምክንያት የተሃድሶ አመለካከትን ደገፍኩ እላችኋለሁ.......... ጌታ ገና በቤተክርስቲያናችን ተሃድሶን አሁን ካለዉ በላይ ያደርጋል........

  ReplyDelete
 12. Read Medlote-tsidk... You might find yourself.

  ReplyDelete
 13. Ye xenquyoch Zemen yibqan. Geata hoy beatehen yemgobegnebet qen zare yihun. Yante keber yeminegerebet enji yesewech keber yeminegerebet endayhon beatehen atseda. Yemenafrebet yeteret Mesay yewedase zemen bemabqat hidet ley newena geata hoy tolo adregew. Amen.

  ReplyDelete
 14. A worth read. Thank you Aba Selama's.

  ReplyDelete
 15. ያረጋል ወንድማችን እድሜና ጤና ይስጥህ፡፡ ምንም እንኳን ጊዜው የአውሬው ዘመን ቢሆን ከአውሬው አፍ ተርፎ እንደዚህ አይነት መልካም ስራ መስራት በእውነት ወንድማችን ኮርቼብሀለሁኝ፡፡ በርታ አውሬው ለምን ይቆጣል????????????????

  ReplyDelete
 16. it is luter s teaching!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!!

  ReplyDelete
 17. 100%እውነተኛ ፕሮቴስታንት እንዲህ ነው ማተራመስ ኦርቶዶክስን።

  ReplyDelete
 18. እኔ ግራ የገባኝ እናንት ተሃድሶዎች ካልሆናችሁ ምነው እንዲህ ተሟጋች ሆናችሁ።ይህ እኮ የሚያሳየው እናንተ ተሃድሶዎች መሆናችሁን ነው። ስላማዎች እንደው በኤትዮጵያ ኦርቶዶክስ ስም ለኤትዮጵያ ህዝብ ተቆርቋሪ መስላችሁ የይሁዳ ስራ እየስራችሁ ምንም በጎ ነገር የላችሁ እንደው ማንን እንስደብ ነው ስራችሁ አንድም የምንማረው በጎ ምግባር የላችሁም።እግዝያብሄ አይነልቦናችሁን ያብራላችሁ እንደው በጨላማ ውስጥ ነው የምትመላለሱትና ያ ደግሞ የክርስቲያን ባህሪ አይደለም ይሰደባል እንጅ አይሳደብም። አሁንም ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን ክእናቱ ከመቤታችን ጋር እያሳደዳችሁ ነው የቆመ የመሰለው ይጠንቀቅ ይላል።ቃሉ

  ReplyDelete
 19. Good job brother I have one quation for every one of u do u think yemariam or yemlaekt mega wod heiwot yadersal bc Jesus is the only severe we have for us so this is our time to think to be saved and

  ReplyDelete
 20. ተቃጠል እንግዲህ ምድረ ግሪሳ ሀራጥቃ ተሃድሶ ሁላ

  ReplyDelete
 21. ተሓድሶ መንገድ ነው እምነት ነው ኣስተሳሰብ ነው ወደ መድራሻውም ግቡም ግን መንግስተ ሰማያት ሳይሆን ፕሮቴስታንቲዝም ነው።
  ይህን የምለው ለቅፅበትም ከነርሱ የሚለያችሁ ነገር ስለሌለ።
  እውነት ነው ቅዱሳን ያማልዳሉ እግዚአብሄር አምላክ የህያዋን ኣምላክ እንጅ የሙታን አምላክ ኣይደለም ቅዱሳን በአፀደ ነፍስ ይሁን በአፀደ ስጋ ይፀልያሉ። በሓዲስ ኪዳን ክርስቶስ ስለ ላይኛው መንግስቱ ሲያስተምር የሌዌ እና የአልአዛር ታሪክ በምሳሌ በመጥቀስ አልኣዛር ከአብርሃም እቅፍ እንደገባ ይናገራል። ሌዊ እና አልአዛር ከስጋ እረፍት በኃላ ያደረጉት ምልልስ እና የለዌ ለወገኖቹ የለመነውን ልመና ኣስተምሯል። ይህን እንዴት አይታችሁት ነው ስለቅዱሳን ክብር እና አማላጅነት ገደል ላይ የከተታችሁት።

  ReplyDelete
  Replies
  1. ያረጋል እስከመቼ ግንዛቤ አስጨባጭ ሆነህ ትቀጥላለህ? እውነተኛውን ግንዛቤ ሳትጨብጥና የሕይወት ተሐድሶ ሳታገኝ ጀንበርህ እንዳትጠልቅ እባክህን ወደ ክርስቶስ ተመለስ፡፡ የሚያድንህ በክርስቶስ ማመንህ እንጂ ማሕበረ ቅዱሳን ድርጅትህ አይደለም፡፡

   Delete
 22. ያረጋል እስከመቼ ግንዛቤ አስጨባጭ ሆነህ ትቀጥላለህ? እውነተኛውን ግንዛቤ ሳትጨብጥና የሕይወት ተሐድሶ ሳታገኝ ጀንበርህ እንዳትጠልቅ እባክህን ወደ ክርስቶስ ተመለስ፡፡ የሚያድንህ በክርስቶስ ማመንህ እንጂ ማሕበረ ቅዱሳን ድርጅትህ አይደለም፡፡

  ReplyDelete