Friday, October 30, 2015

አባ ሳሙኤል በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ በርካታ ችግሮችን እየፈጠሩ ነውበጥቅምቱ ሲኖዶስ ስብሰባ ዋዜማ ላይ በድርሰት ስርቆት እስከተጋለጡበት “ግብረ መንፈስ ቅዱስ” መጽሐፍ ድረስ በሰው መጽሐፍ ራሳቸውን ጸሀፊ ለማሰኘትና የሌላቸውን ማንነት ለመገንባት ያልተሳካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የቆዩት አባ ሳሙኤል በግብረ መንፈስ ቅዱስ መጽሐፍ ግን የፈጸሙት አሳፋሪ ድርጊት መጋለጡን ተከትሎ ሌሎች መሰሪና አሳፋሪ ሥራዎቻቸው መጋለጥ ቀጥለዋል፡፡ ከግብረ መንፈስ ቅዱስ መጽሐፍ ጋር ጋር በተያያዘ ለማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች ጥያቄ የቀረበ ሲሆን ከማኅበሩ ግልጽ አመራሮች መካከል አንዱ ቀርቦ የተጠየቀ ሲሆን ስለ መጽሐፉ በአባ ሰላማ ድረገጽ የቀረበው ትክክል መሆኑን አምኗል፡፡ መጽሐፉን እነርሱም ሽጡ ተብለው እንደተረከቡና መጽሐፉ ችግሮች ስላሉበት ሳንሸጥ መጋዘን በማስገባት ክፍያውን ግን ፈጽመንላቸዋል ብሏል፡፡
ይህም የሚያሳየው ማቅ ለሃይማኖት ሳይሆን ለግል ጥቅሙ የቆመ ድርጅት መሆኑን ነው፡፡ ምክንያቱም ለሃይማኖቱ ተቆርቋሪ ቢሆን ኖሮ አባ ሰላማ እስኪያጋልጥ ድረስ የአባ ሳሙኤልን ሃይማኖታዊ ሕጸጽና ቅስጣ ድርሰት በቸልታ ማየት እንዳልነበረበትና ጉዳዩን ለሚመለከተው የቤተክርስቲያን አካል አቤት ማለት እንደነበረበት ማንም የሚናገረው እውነት ነው፡፡ ማቅ ግን ለፖለቲካው ሲል እንዲህ አላደረገም፡፡ ለዚህም እንዲህ ባደርግ በአባ ሳሙኤል በኩል የሚፈጸምልኝ ጉዳይ ሊበላሽ ይችላል ብሎ ቅድሚያ ለዚያ ሰጥቶም እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ ሌላውን አለስሙ ስም ለመስጠት አለቅጥ የሚጣደፈውና ማንም የማይቀድመው ማቅ በዚህ ጉዳይ ላይ ያሳየው ዳተኛነትና ቸልተኛነት ሰዎች እንዲወገዙ ጥያቄ የሚያቀርበው በሃይማኖታቸው ላይ ሕጸጽ ስለተገኘ ሳይሆን ለእርሱ አልመች ስላሉትና ስለተቀናቀኑት ነው ለሚለው የብዙዎች እምነት ትልቅ ማጠናከሪያ ሆኗል፡፡ 

ከአጥማቂው ግርማ ጋር በተያያዘም የአባ ሳሙኤል ስም እየተነሳ ነው፡፡ አጥማቂው ግርማ ቀደም ሲል በፈጸመው ወንጀል ሰሞኑን በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋሉን ተከትሎ ከወንጀሉ በተጨማሪ በሕይወቱና በአጥማቂነቱ ብዙ የጥያቄዎች ያሉበት ሰው እንደመሆኑ ለዚህ ሰው ሥልጣነ ክህነትን የሠጠው ማነው? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡ እንደ ምንጮቻችን ከሆነ ግን ቅስና የሰጡት አባ ሳሙኤል መሆናቸው ታውቋል፡፡ በ2004 ዓ.ም ለአጥማቂ ግርማ በልክ የተሰፋና ሥልጣነ ክህነት የሌለው ሰው እንዳያጠምቅ የሚል መመሪያ ወጥቶ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ አጥማቂ ግርማ ብዙ ተከታዮች ስላሉት ያንን በማስላት አባ ሳሙኤል በዚያው ዓመት ቅስና የሠጡት ሲሆን በካርዱ ላይ ግን 2001 ተብሎ መሞላቱን ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡ አባ ሳሙኤልም ሥልጣነ ክህነቱን ስለሰጡት አጥማቂው ግርማ ብር 200 ሺህ ከፍሏቸዋል ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዋጋው ውድ የሆነ እጅግ ዘመናዊ ሞባይልም ከውጭ አስመጥቶ አበርክቶላቸዋል፡፡ እንደ አባ ሳሙኤል ሥልጣነ ክህነትን በብር የሚሸጡ ሌሎች ጳጳሳትም እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥቅመኛው አባ ማርቆስ አንዱና ዋናው ናቸው፡፡
አባ ሳሙኤል በአሁኑ የሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የማቅን በርካታ የቤተ ሥራዎች ለመሥራት ተስማምተውና “ቢጠብቁን እንጠብቅዎታለን” በመባባል ፍቅራቸውን አድሰው እንደነበር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እየተናገሩ ነው፡፡ ምንም እንኳን በድርሰት ስርቆት መጋለጣቸው ትልቅ ጥላ ማጥላቱ ባይቀርም በተለይም የሁለቱም (የማቅም የአባ ሳሙኤልም) ጥቅምና ፍላጎት የሆነውን የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫን በተመለከተ ተመሳሳይ ዐቋም ይዘው እየተንቀሳቀሱ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ማቅም ከእርሱ ቁጥጥር ሊወጡ የማይችሉና በየገዳማቱ ለዚሁ ጊዜ የመለመላቸውና ያስቀመጣቸው መነኮሳት ስላሉ ከአዲስ  አድባራትና ገዳማት የደብር አለቆች እንዳይሆኑ ለማድረግ መስፈርቱን በእርሱው ቅኝት እንዲሄድለት የሚፈልግ ሲሆን አባ ሳሙኤልም ከአዲስ አበባ የሆኑቱ ሊቀናቀኗቸው ስለሚችሉና እንዳሻቸው ሊያደርጓቸው ስለማይችሉ በማቅ በኩል የተያዘው መስመር አባ ሳሙኤልም ምቹ ሆኖ አግኝተውታል፡፡
በሌላም በኩል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ከሚሰራው አፍራሽ ሥራ በስተጀርባ የአባ ሳሙኤል እጅ መኖሩን የሚናገሩት ምንጮች ይህን የሚያደርጉትም ሀገረ ስብከቱ ከእርሳቸው በኋላ እንደ ተበላሸና ሊስተካከል እንዳልቻለ ለማሳየት ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህ በሀገረ ስብከቱ መልካም አስተዳደር ሊሰፍን ሲጀምር አፍራሽ ተግባራትን ማከናወን ይጀምራሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የትኛውንም አጀንዳ ይዘው የሚመጡ ሰዎችንና አጀንዳቸውን ሀገረ ስብከቱ እንዳይረጋጋ ለማድረግ ይጠቀሙበታል፡፡ በቅርቡ እነደረጀ ዘወይንዬ አንቅስቃሴ በስተጀርባ የአባ ሳሙኤልም እጅ እንደነበረበት ምንጮች ይጠቁሟሉ፡፡ በሌላም በኩል ከማኅበሩና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ከሚንቀሳቀሱ ጳጳሳት ጎን ተሰልፈው የተለመደ የማወክ ሥራቸውን ሲሰሩ በሌላ በኩል ደግሞ ሊቀ ማእምራን የማነን ወዳጅ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ በአጥቢያ ላይ ሊ/ማ የማንን ተጠቅመው 6 መነኮሳትን ያስቀጠሩ ሲሆን ከዚህ የተነሣ አባ ሳሙኤል ለየማነ መመሪያ እየሰጡ ነው እየተባለ እየተወራ ነውና ሊቀ ማእምራን የማነ ሊጠነቀቅ ይገባል የሚሉ ወገኖች በርካቶች ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ሲታይ አባ ሳሙኤል ሊቀጳጳስና የሃይማኖት መሪ ሳይሆኑ የሴራ ፖለቲካ አራማጅ ነው የሚመስሉት፡፡
በዚህ የሲኖዶስ ስብሰባ ሀገረ ስብከቱ ያለ ሊቀጳጳስ በሥራ አስኪያጆቹ እንዲቀጥል መወሰኑ ለማቅ ትልቅ ሽንፈትና ራስምታት ሆኗል፡፡ በማቅ ምክር አብሬ አልሰራም ብለው ቦታቸውን በፈቃዳቸው የለቀቁት አባ ቀሌምንጦስም ወደቦታዬ መልሱኝ ሲሉ ለሲኖዶስ አባላት አቤት ቢሉም ከአንድ ሊቀጳጳስ “ወታደር ምሽጉን ከለቀቀ በኋላ ምንም ማደረግ አይችልም፤ መዋጋት ያለበት በምሽጉ ሆኖ ነው፡፡ እርስዎም በፈቃድዎ በፈቃድዎ የለቀቁት ስለሆነ አሁን መልሱኝ የሚለው አይሠራም” ብለዋቸዋል ተብሏል፡፡  በዚህ ሁሉ ማቅ ትልቅ ኪሳራ እንደደረሰበትና ቅዱስ ፓትርያርኩ በልዩ ሀገረ ስብከታቸው ላይ ማንም ጣልቃ ሊገባ እንደማይችል በተግባር ያሳዩበት ውሳኔ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
እንደዚህ ዓይነት ውሳኔዎችም የተወሰኑበት የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የተጠናቀቀ ሲሆን መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

No comments:

Post a Comment