Wednesday, October 7, 2015

ግብረ ሰዶማዊነትን ለመቃወም ሙጋቤያዊ አቋምም ከመሪዎቻችን ያስፈልጋል!


 Read in PDF

ምንጭ፡-የዲያቆን አቤንኤዘር ተክሉ ገጽ
               እኛ ግብረ ሰዶማውያን አይደለንም!!!” (ሮበርት ሙጋቤ)


    በዘመናችን መንፈሳዊ ማንነታችን ስለተጐሳቆለብን ኃጢአትን በአለም መድረክ የሚቃወሙት አለማውያን መሪዎች፥ ከእኛ ይልቅ በብዙዎች ዘንድ የመደመጥን ዕድል ያገኙ ይመስላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በቅድስና ፍጹም ስትዋብ በአለማውያን መሪዎች ላይ ተጽዕኖ ስለማሳደሯ ምንም ጥርጣሬ የለውም፡፡ ከቤተ ክርስቲያን መለያ ባሕርያት መካከል አንዱ ክርስቶስ በገዛ ደሙ መሥርቷታልና ቅድስት መሆኗ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የቅድስናን ጠባይ ገንዘብ ያደረገችው፥ ከመሠረታትና ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ ከሚሆን ከክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡
     ቤተ ክርስቲያን ከአለማውያን መሪዎች ጋር ያላት ግንኙነት እጅግ ጤናማ መሆን አለበት፡፡ ግንኙነቱ ጤናማ መሆን አለበት ስንል፥ መርሑ ቅድስናና ንጽሕናን ብቻ በተከተለ መንገድ መሆን መቻል አለበት ማለታችን ነው፡፡ ቅድስና በኃጢአተኛው ላይ እጅግ ከፍ ያለ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላል፡፡ በቤተ ክርስቲያን በስደት ዘመን የሰማዕታትን አንገት ይቀሉ የነበሩት ወታደሮች፥ በሚያስደንቅ መንገድ የጌታ ባለሟሎች የሆኑትና ከመግደል ለጌታ እስከመሞት የደረሱት የሰማዕታቱን የቅድስና ጉልበት አንገት በመቁረጥ ፤ በማቃጠልና በብዙ መከራ ማሸነፍ ስላልቻሉ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የክርስቶስ ኢየሱስን ሕይወትና ቃሉን እጅግ በመውደድና በማንበብ ለአገራቸው ሕዝቦች እጅግ ቅን የነበሩትን እንደመሃተመ ጋንዲ ያሉ መሪዎችንም ማንሳትም ይቻላል፡፡

   ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር በመንገዷ ፍጹም በሆነችበት ዘመኗ፥ አለማውያን ቅን መሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን ጨካኝና እጅግ ደንዳና መሪዎችም ላይ ከፍ ያለ ተጽዕኖን ማሳደር ችላለች፡፡ በዚህም ተጽዕኖ መሠረት እንደኮሞዶስ(Comodous)(180-192 ዓ.ም) ሮማዊ ያሉ መሪዎች ከፍጹም ጭካኔያቸው ሲታገሱ ፤ ጌታን አሳልፎ እንደሰጠው ጴንጤናዊ ጲላጦስ አይነቶች ደግሞ ፍጹም ወደጌታ ኢየሱስ ፊታቸውን መልሰው ሰማዕት ሆነዋል፡፡ ለቁጥር የሚታክቱ አመጸኞችና ጨካኞች ፤ ዘፋኞችና አመንዝሮች … ወንጌልን በማንበብ ፣ በመስማት ፣ ከቤተ ክርስቲያን ሕይወት በማየት ፊታቸውን ዘወር ሲያደርጉ በዘመናችንም በጥቂቱ እያየን ነው፡፡
    የኢትዮጲያን መሪዎች ስናነሳ ደግሞ፥ ለአገሪቱ ባስቀመጡት ፍሬያማ የእድገት ቀመር ወይም መሠረት “እጅግ የተተቹ” ቢሆንም፥ ከቤተ ክርስቲያን ጋር “የቅርብ ሽርክና” እንዳላቸው የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን ያላቸው የቅርብ ግንኙነት ያን ያህል የእነርሱን መንፈሳዊ ሕይወት የነካና ተጽዕኖ ያሳደረ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ እንደአፄ ዓምደ ጽዮን ያሉ የአባታቸውን ሚስት ዕቅብት አድርገው ይዘው ፣ እንደአፄ ፋሲል(ፋሲለደስ)ና ሌሎችም በአመንዝራነት እጅግ የታወቁ ሆነው ቤተ ክርስቲያን በማሠራታቸውና ለገዳማት ብዙ አስራት በኩራት በመላካቸው ብቻ ተፈርተው ተቀመጡ እንጂ በተጠጓት ቤተ ክርስቲያን ሕይወታቸው አንዳች አልተለወጠም ማለት ያስደፍራል፡፡ እንዲያውም የተቃወሟቸውን ሰዎች በግልጥ በአደባባይ ያስገርፉ ፤ ያግዙ (ያስሩ) እንደነበር ታሪክ ከነትዝብቱ ይነግረናል፡፡

    ይህን ያህል ለመግቢያ ካነሳሁ ወደዋናው ሃሳቤ ደግሞ ሳመራ፦ የዛሬዎቹ መሪዎቻችንስ ይህን በተመለከተ ምን ይመስላሉ? እራሳቸው ወንጀል ነው ብለው የደነገጉትን ድርጊት እየተስፋፋና ብዙውን ወጣትና ሕጻን እያጠቃ ሲሄድ የመቃወም አቅም አላቸው ወይ? ተፈጥሮን በግልጥ የሚቃወም ድርጊት ሲፈጸም ሲያዩ መቃወም ይችላሉን? ለምንስ መቃወም ተሳናቸው? … የእኛ መንፈሳዊያን መሪዎችስ ለአገራችን መሪዎች እውን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነቡ በድፍረት ይመክሯቸዋልን? ቢያንስ መጽሐፍ ቅዱስን በሥጦታ መልክ እንኳ ለእኒህ መሪዎችስ ይሰጡ ይሆንን? መሪዎቹስ የሥልጣን ባለቤት እግዚአብሔር እንደሆነ አምነው ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነትና ቃሉ ይታዘዛሉን? ጐረቤት አገር ያሉ መሪዎች የሚያደርጉት ተቃውሞ ነገር እነርሱንና ሕዝባቸውን እንደሚመለከትስ ያስባሉን?
     ይህንን ሁሉ እንድጠይቅ ያደረገኝ፥ የዚንባቤው ፕረዘዳንት ሮበርት ሙጋቤ በተባበሩት መንግሥታት መሪዎች ስብሰባ ላይ ግብረ ሰዶማዊነትን በግልጥ በመቃወም በእልህና በቁጣ የተናገሩትን ንግግር ሳደምጥ የእኛ መንፈሳውያንና የአገራችን መሪዎች የት ነው ያሉት? እነርሱስ በዚህ ዙርያ ምን ተናግረዋል? ለመናገርስ ሞራሉ ይኖራቸዋል? እንድል አድርጐኛል፡፡ ምክንያቱም በአገራችን ምንም ልናስተባብል በማንችለው መልኩ ግብረ ሰዶማዊነት ቁጥሩ እጅግ በሚያሰቅቅ መልኩ እየተስፋፋ ነው፡፡ ሕጻናት ፣ ወጣቶች ፣ ጐልማሶች ፤ ሰባክያን ፣ ዘማርያን ፣ መነኮሳት … ፤ ከቀበሌ መስተዳድር እስከ ሚኒስትሮች ጥቂት ብለን በማንሸሸው ቁጥር በዚህ ነውር የተያዙ ፤ እየተያዙም ስለመሆናቸው ሲወራ በግልጥ እንሰማለን ፤ እናያለንም፡፡
    በአንድ ወቅት የሃይማኖት መሪዎች ግብረ ሰዶማዊነትን ለመቃወም የጠሩትን ስብሰባ ፤ በጊዜው የነበሩት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተቃውሞውን ድምጽ እንዳያሰሙ አግባብቶ ከበተነ በኋላ፥ ግብረ ሰዶማዊነትን በዝምታ የሚደግፍ እንጂ በግልጥ የሚቃወም አንዳች መሪ “የሦስት ሺህ ዘመን የሃይማኖት ታሪክ” ካላት አገር ልንሰማ አልታደልንም፡፡
      በእርግጥ አንድ ነገር አምናለሁ ፤ ኃጢአትን፥ ኃጢአት ለማለት መንፈሳዊ ብቃትና ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፈቃድ የሚታዘዝ ልብና መንፈስ ያስፈልጋል፡፡ መሪዎቻችን ያለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ዕርዳታና ዳግመኛ ከእግዚአብሔር መንፈስ ካልተወለዱ በቀር ኃጢአትን ኃጢአት ማለት እንደማይችሉ አምናለሁ ፤ ነገር ግን “እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱት መጠን እግዚአብሔር የማይገባውን ያደርጉ ዘንድ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ እንደሚሰጥ” ደግሞ ቅዱስ ቃሉ ይነግረናል፡፡ (ሮሜ.1፥28)
      የኬንያው ፕረዘዳንት ኡሩቱ ኬንያታና ያለምንም ማቅማማት የተቃወሙት የዚንባቤው ፕረዘዳንት የሃይማኖት መሪ አይደሉም ፤ ወይም የነገረ መለኰት ተማሪ መሆናቸውን አልነገሩንም፡፡ ነገር ግን በድፍረት ሲቃወሙ አየን፡፡ እግዚአብሔር ለአህዛብ እንኳ የሕሊና ሕግን ሰጥቷል፡፡ ከነቢያት ሕግ በፊት የነበሩት አበው ቅዱሳን፥ በሕገ ልቦና ሲመሩ ነበር፡፡ አህዛብ እንኳ ከፍርድ የማያመልጡበት አንዱ ነገር መልካምንና ክፉን የሚለዩበት ሕግ፦ “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ ከባሕርያቸው የሕግን ትእዛዝ ሲያደርጉ፥ እነዚያ ሕግ ባይኖራቸው እንኳ ለራሳቸው ሕግ ናቸውና ፤ እነርሱም ሕሊናቸው ሲመሰክርላቸው፥ አሳባቸውም እርስ በርሳቸው ሲካሰስ ወይም ሲያመካኝ በልባቸው የተጻፈውን የሕግ ሥራ ያሳያሉ።” እንዲል ተሰጥቷቸዋል፡፡ (ሮሜ.2፥14-15) ይህ ሕግ የሙሴን ሕግ አያመለክትም ፤ በተፈጥሮ የተሰጠውን የሕሊና ሕግ እንጂ፡፡ እጅግ የሚገርመውና ይህን እውነት የሚያስረግጠው ነገር፥ ጌታ ከአይሁድ የተሻለ ታላቅ እምነት የነበራቸውን ከአህዛብ መካከል አጊኝቷል፡፡ (ማቴ.15፥28 ፤ ሉቃ.7፥9)
     አስተውሉ! አህዛብ ሕግ ካላቸው አይሁድ የሚበልጥ እምነትን ይዘው በመገኘታቸው በሙሴ ሕግ እውቀት የላቀ ደረጃ የነበሩትን አይሁድ በዝምታ ኰንነዋል፡፡ እንግዲህ እንደኬንያውና እንደዚንባቤው መሪዎች ግብረ ሰዶማዊነትን ለመቃወም የሕሊና ሕግ በቂ ነው፡፡ መሪዎቻችን ግብረ ሰዶማዊነትን ለመቃወም መጽሐፍ ቅዱስን አላጠናንም ወይም የነገረ መለኰት ትምህርት ቤት አልገባንም ማለት አይረባቸውም ፤ ተፈጥሮን የሚቃረንና ነፍስን የሚያረክስ ነገርን በአዕምሮ ዕውቀት ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም ማወቅ ይቻላልና፡፡
      እንኪያስ፦ ሙጋቤና ኡሩቱ የተመለከቱት የእኛ መሪዎች ምን ይሆን የተማሩት? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃጢአትን በሸንጎ አጽድቆ በአፈኛ መሪዎች አንደበት “ወደድኃ” አገሮች ሲልክ የድኃ አገር መሪዎች ድህነታቸውንም ፤ ኃጢአቱንም ከእርዳታው እህል ጋር ተሻምቶ ከመቀበል፥ አብሮ በሚያሠራው ተስማምተው በሌላው ግን ለመቃወም  እውን ሞራልና አቅሙ አላቸውን? የእኛ መሪዎችስ በእልፍ አዕላፍ ሰባክያንና ዘማርያን ፤ ጳጳሳትና ቆሞሳት ፤ ገዳማትና አድባራት መካከል ተቀምጠው እውን ለእግዚአብሔር ቃልና እውነት እንግዳ ናቸውን? ምነው ሕጻናትንና ወጣቶችን እያረገፈ ስላለውና በወንጀል ሕጉም ወንጀል ተብሎ ስለተደነገገው ነውር አንድ መሪ እንኳ ድምጽ አላሰማ አለ?! ኢትዮጲያ ሆይ መሪዎችሽ ወዴት ናቸው!? በእውኑ ሕመሙና ርኩሰቱ ሳይሰማን ቀርቶ ነው ወይም ሊመጣ ላለው ፍርድ እየሰባን ይሆን?!

አቤቱ ሕዝብህን አድን ፤ ርስትህን ባርክ፡፡ አሜን፡፡

2 comments:

  1. Atsea Fasil ke- ne amenzeranetachew endiqexelu bezemeta yalefu ye beate krstiyan abatoch telequn ye tebabarinetun dersha wesdewal. Zarem ke papasu eske kahenu le beatekrstiyan keber sayhon lehodachew ena lerasachew keber yeminoru selehonu beatekrstiyan erasuwa ande about yasfelegatal.

    ReplyDelete