Friday, November 6, 2015

ወገን እማማ ኢትዮጵያ ተርባለች … የድረሱልኝ ጥሪዋንም እያሰማች ነው?! የ፲፱፻፷፮ቱ እና የ፸፯ቱ ዓይነት የረሃብ እልቂት ከመድረሱ በፊት ለወገኖቻችን እንድረስላቸው! ከፍል- ፩በዲ/ን ኒቆዲሞስ      (ምንጭ- ከሰንደቅ ጋዜጣ መጠነኛ ማስተካከያ ተደርጎበት የተወሰደ፡፡)
እኛ ኢትዮጵያውያን ለረሃብ ክሥተት በፍጹም እንግዶች አይደለንም፡፡ ጠኔ-ችጋር ደግሞ ደጋግሞ የጎበኘን፣ ረሃብ ስማችንን ያጎደፈብን፣ በሃፍረት አንገታችንን ያስደፋን፣ ቅስማችንን የሰበረን፣ ታሪካችንን ያጠለሸብን፣ የእልቂት፣ የፍጅት፣ የደም ምድር- ‹‹አኬል ዳማ›› በሚል የሚያሰቅቅ ስያሜ የተጠራን፣ መላው ዓለም በኀዘን ከንፈሩን የመጠጠልንና እንባ የተራጨልን ምስኪን ሕዝቦች ነን፡፡
እስቲ ለዛሬው በዝናም እጥረት ምክንያት በአገራችን በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ሚሊዮኖች ወገኖቻችን ለረሃብ ስለተጋለጡበትና ቤተኛው ስላደረገን የድርቅ/የረሃብ ጉዳይ ላይ አብረን በአንድነት ሆነን ትንሽ እንቆዝም ዘንድ በተከታታይ ላስነብባችሁ ወዳሰብኩት ጽሑፍ የሚያንደረድረኝንና ዛሬም ድረስ ሳስታውስው እጅጉን በሚያሳቅቀኝ አንድ ገጠመኜ ልጀምር፡፡
በደቡብ አፍሪካ የአርትና የባህል ሚ/ር፣ ማንዴላና የትግል ጓዶቻቸው ለ፳፯ ዓመታት በተጋዙበትና በዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ቅርስነት በተመዘገበው በሮቢን ደሴት የነጻነት ሙዚየምና እና በኔልሰን ማንዴላ ፋውንዴሽን ትብብርና የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጠውን ‹‹የአፍሪካ ቅርስና ቱሪዝም ጥናት የድኅረ ምረቃ/የፖስት ግራጁየት የትምህርት ፕሮግራም›› ነጻ የስኮላር ሺፕ ዕድል አግኝቼ ከፍተኛ ትምህርቴን በተከታተልኩባት በኬፕታውን ከተማ በሮቢን ደሴት ሙዚየም የሆነ ገጠመኜ ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲ ትምህርታችንን ከመጀመራችን በፊት የትምህርት ክፍላችን አስተባባሪ የሆነው ናይጄሪያዊው ጎልማሳ ከተለያዩ አገራት የመጣን ተማሪዎችን እርስ በርሳችን እንድንተዋወቅና እንዲሁም ይህን የነጻ የስኮላር ሺፕ ትምህርት ዕድል ለሰጠን ማንዴላና የትግል አጋሮቻቸው ለጥቁር ሕዝብ ነጻነት፣ ለሰው ልጆች መብትና እኩልነት ሲሉ ለበርካታ ዓመታት ቃላት ሊገልጸው የማይችለውን መከራና ግፍ በተቀበሉባት ለሮቢን ደሴት ወኅኒ/ግዞት ቤት ከነጻነት በኋላ ደግሞ ሺህዎች በየዕለቱ የሚጎርፉበት የነጻነት መታሰቢያ ሙዚየም ለመጎብኘትና ምስጋናችንን ለመግለጽ በሚል ነበር በደሴቲቱ የተገኘነው፡፡
ትምህርት ክፍላችን አስተባባሪ ከጉብኝታችንና ከቀኑ ውሎአችን በኋላ በሮቢን ደሴት በሚገኘው መኖሪያው የእራት ግብዣ አድርጎልን ነበር፡፡ ከኬፕታውን ሲ ፓይንት፣ ከኔልሰን ማንዴላ ጌት በመርከብ ለ፵፭ ደቂቃ ያህል ቀዝቃዛውንና ማዕበል የሚንጠውን የአትላንቲክ ውቅያኖስን በማቋረጥ፣ ውብ በሆነችው የደቡብ አፍሪካ እናት ከተማ በኬፕታውን ድንቅ ተፈጥሮ እየተደመምን፣ ከአድማሱ ጋራ የተጋጠመው የሚመስለውን ባለ ልዩ ግርማ ተራሮቿን በርቀት እየቃኘን፣ እንዲሁም በዓለማችን የመርከብ ቴክኖሎጂ ታሪክ ተወዳዳሪና አቻ የሌላት የተባለችውን የእንግሊዟን ታይታኒክ መርከብ ከ1200 ተጓዦቿ ጋር ያሰጠመውን በባለ ግርማ ሞገሱን የአትላንቲክ ውቅያኖስ የመርከብ ላይ ጉዞና የዶልፊኖች የውኃ ላይ ገራሚ ትእይንትና በሮቢን ደሴት ጉብኝታችን የፈጠረብንን ልዩ ደስታና ሐሤት በልባችን እንደያዝን ነበር የትምህርት ክፍላችን አስተባባሪ በሆነው በሮቢን ደሴት መኖሪያ ቤቱ ለእራት የታደምነው፡፡
ታዲያ እራት ተበልቶ አልቆ የደቡብ አፍሪካውያንን ወይን እየተጎነጨን ስንጨዋወት በጨዋታችን መካካል በትምህርት ክፍላችን አስተባባሪ ቤት ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠውን የኔልሰን ማንዴላን የትግል ሕይወት የሚተርከውን መጽሐፍ አንስቼ ሳገላብጥ፣ ማንዴላ ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በነበረበት ጊዜ በወቅቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጠው ፓስፖርት በመጽሐፉ ላይ በአባሪነት መካተቱና የኢትዮጵያ ቆይታውን የሚያትተውን አስደናቂ ትረካውን በማየቴ ደስ አለኝ፡፡
ከአጠገቤም ከዩኔስኮ ተወክላ ከናምቢያ ለመጣችው የክፍል ጓደኛዬ መጽሐፉን እያሳየኋት ማንዴላ ሰለ አገሬ ኢትዮጵያ የሰጠውን ድንቅ ምስክርነት በኩራት ካነብበኩላት በኋላ አገራችን ኢትዮጵያ ለደቡብ አፍሪካው ነጻነት ታጋይ ለኔልሰን ማንዴላና በአጠቃላይ ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግልና ተጋድሎ ደረገችውን አስተዋጽኦ ከአንጸባራቂው ከዓድዋው ድል ጋራ አብሬ በአጭሩ ተረኩላት፡፡
‹‹Oh Really! እኔ ይሄን አላውቅም፣ ብዙዎች አፍሪካውያንም ይሄን የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ ስለ ኢትዮጵያ አብዛኛው የአገሬ ናምቢያ ሕዝብና እኔ የምናውቀው ኹለት ነገሮችን ነው፡፡ አንደኛው በርካታ ተከታይ ያላቸውን ንጉሣችሁን ኃይለ ሥላሴን/ራስ ተፈሪውያንን ሲሆን ኹለተኛው ግን Sorry to say this…! አዝናለሁ… በአገራችሁ ተከስቶ በነበረው አስከፊው ድርቅ/ራብ ያለቁትን ወገኖቻችሁን ነው፡፡ እውነቴን ነው የምልህ እንዲህ ዓይነት ለጥቁር ሕዝቦች ኹሉ ኩራት የሆነ፣ የአፍሪካ ጫፍ በሆነችው ደቡብ አፍሪካ ድረስ የዘለቀ አኩሪ የነጻነት ተጋድሎ ታሪክ ያላችሁ ታላቅ ሕዝቦች መሆናችሁን አላውቅም፡፡
እንደ ቢ.ቢ.ሲ ባሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ስለ አገራችሁ የምናውቀው የራብ፣ የጦርነትና የእልቂት ምድር መሆናችሁን ነው፡፡ እንደውም አለችኝ ይህቺ ናምቢያዊት የክፍል ጓደኛዬ፤ ‹‹እንደውም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአገራችሁ ደርሶ የነበረው ረሃብ ባደረሰባችሁ አሰቃቂ እልቂት ልባቸው ክፉኛ ያዘነባቸው የአገሬ የናምቢያ አዛውንቶች አንዳንድ ሰዎች ምግብ ያለ አግባብ ሲጥሉ ሲያዩ ‹Hey Please Think the Starved People in Ethiopia››› እንደሚሉ ስትነግረኝ የቀኑ ውሎ ደስታዬ በአፍታ ወደ ኀዘን ተቀየረ፡፡ ምነው ይሄን መጽሐፍ ባላነሳሁት-በቀረብኝ በሚል ጥፍሬ ውስጥ የመግባት ያህል ሃፍርትና ውርደት ተሰማኝ፡፡ ከዛች ቅጽበት በኋላ ከዚህች ሴት ጋራ ብዙም ማውራት አልቻልኩም፡፡
ሺህ ዘመናትን ካስቆጠረው ታሪካችን፣ ቅርሳችንና ሥልጣኔያችን፣ በእጅጉ ከምንኮራበት የነጻነት ተጋድሎ ታሪካችን፣ ከአምላክ ከተቸረን የተፈጥሮ ጸጋችንና ውበታችን ይልቅ ክፉ ክፉው ታሪካችን እንዲህ ከጫፍ እጫፍ መሰማቱና መናኘቱ፣ መተረቻና መጠቋቆሚያ፣ የረሃብ መዝገብ ቃላት ፍቺ ማድመቂያ፣ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ፍጅትና እልቂት የደም-ምድር ‹‹አኬል-ዳማ›› መገለጫ ሕዝቦች መሆናችን ግራ አጋባኝ፡፡ እናም ከዚህች ሴት ጋራ በነበረኝ ቆይታዬ ክፉኛ ኀዘን ተሰማኝ፡፡
ይህ ዓይነቱ ገጠመኝ የእኔ ብቻ ገጠመኝ ነው ብዬ አላስብም፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሔዱበት አገርና ምድር ኹሉ ተመሳሳይ የሆነ አንገታቸውን ክፉኛ ያስደፋና ያሳቀቃቸው ገጠመኝ አላቸው፡፡ በዛው በደቡብ አፍሪካ የነጻ ትምህርት ዕድል አግኝቶ ከሔደ ጓደኞቻችን መካከል ከሌሎቻችን ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ወፍር ያለና የሌሎች አፍሪካውያን ዓይነት በስፖርትና በምግብ የዳበረ ሰውነት ያለውን ጓደኛችንን አንዲት ደቡብ አፍሪካዊት የክፍሉ ተማሪ፣ ‹‹አንተ ረሃብ ከሌለበት የኢትዮጵያ ክፍል የመጣህ መሆን አለብህ …፡፡›› እንዳለችው በቁጭትና በኀዘን ሆኖ አጫውቶናል፡፡
እንደማስታውሰው ከጥቂት ዓመታት በፊትም አንጋፋው አዲስ ዘመን ጋዜጣ አንድ ለትምህርት ወደ ደቡብ ኮሪያ ሄዶ የነበረ ኢትዮጵያዊ ወጣት በዩኒቨርስቲው መምህራንና የክፍል ጓደኞቹ ከረሃብ እልቂትና ጦርነት ተርፎ ለዚህ ዕድል መብቃቱ ኩራት ሊሰማው እንደሚገባው በነጋ ጠባ ሲነግሩትና ሲያስረዱትና እርሱም ቢረዱኝ በማለት ስለ አገሩ ያለውን እውነታ ቢነግራቸው ሊያምኑት ባለመቻላቸው  ባጋጠመው የሥነ-ልቦና ቀውስ፣ ብቸኝነትና ባይተዋርነት እጅጉን ተማሮ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ትምህርቱን ጥሎ ወደ አገሩ እንደተመለሰ የሚተርክ ጽሑፍ እንዳስነበብን ትዝ ይለኛል፡
በሄዱበትና በተሰደዱበት አገር በነጋ ጠባ ስለ ኢትዮጵያ የሚወራው የረሃብ፣ የእርስ በርስ ጦርነትና የእልቂት ታሪክ ቅስማቸውን ሰብሮት በባእድ ምድር ቀና ብለው መራመድ እያቃታቸው በኀዘን፣ ሰቀቀንና በቁጭት አንጀታቸው እያረረ፣ እግዚኦ ኢትዮጵያ አምላክ ሆይ መቼ ነው ስማችንና ታሪካችንን የምትለውጠው!? በሚል ተማሕጽኖ እንባቸውን እያፈሰሱ ከአምላካቸው ጋራ የሚሟገቱ በርካታ ወገኖች ዛሬም ድረስ አሉን፡፡ ስለ አገራቸው፣ ስለ ወገኖቻቸው በቁጭት የሚንገበገቡ፡፡
ይህን ለዘመናት አንገታችንን ያስደፋንን የረሃብ፣ የእርስ በርስ ጦርነት የውርደት ታሪካችንን ለማደስ ጉልበቴ በርታ በርታ እያልንበት ባለንበት ዘመን ረሃብ ደጃችንን ዳግመኛ አንኳኳ፡፡ በዘንድሮው ወርኻ ክረምት የዝናም እጥረት ምክንያት በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ለረሃብ ለተጋለጠው በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝባችንን ከረሃብ፣ ከችጋር እልቂት ይታደጉልን ዘንድም መንግሥታችን ተማኅጽኖ ይዟል፡፡
ከእንግዲህ ወዲህ የሚሠሩ ወርቅ እጆችን ይዘን ስንዴ ልመና እንዴት ይታሰባል፣ ሕልማችን ሕዝባችንን በቀን ሦስት ጊዜ ማብላት ነው፣ ረሃብን ታሪክ እናደርገዋለን፣ በምግብ እህል ራሳችንን እየቻልን ነው … ዕድገታችንን የኢኮኖሚ ግሥጋሤያችን ዓለም ሁሉ እጁን በአፉ ላይ እንዲጭን እያደረግነው ነው … ወዘተ እንዳልተባልን፣ እንዳለስባልን ዛሬ ግን ይኸው ዓይናችንን በጨው አጥበን በምዕራባውያኑ ደጃፍ ምግብ ልመና አኩፋዳችንን ይዘን መሰለፋችን እጅጉን ያሸማቅቃል፣ ያሳፍራልም፡፡
መንግሥት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ ባለፈው ወርኻ ክረምት ወራት የዝናም ስርጭቱ ዝቅተኛና የተጠበቀውያን ያህል ባለመሆኑ የተነሣ ከ፬.፭ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለረሃብ እንደተጋለጠና አስቸኳይ የሆነ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልገው አሳውቆአል፡፡ ለረሃብ የተጋለጡትን ወገኖቻችንን ቁጥር በተመለከተ መንግሥት ይፋ ያደረገው ቁጥር የተዛባ መሆኑን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየገለጹ ነው፡፡ እነዚሁ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የዕርዳታ ድርጅቶች ለረሃብ የተጋለጠው ሕዝባችን ቁጥር ወደ ፲ ሚሊዮን እንደሚጠጋና ይህ ቁጥርም ወደፊት ሊያሻቅብ እንደሚችል እየተናገሩና እያስጠነቀቁ መሆናቸው ሌላኛው በፊታችን የተጋረጠብን እግዚኦ የሚያሰኝ ክፉ ዜና/መርዶ መሆኑ ነው?!
ይቀጥላል፡፡
ሰላም!

1 comment:

 1. ያላችሁት ሁሉ እውነት ነው። እስኪ እኔ ደግሞ ሰሞኑን የገጠመኝን ላጫውታችሁ። ለካ ቁስላችን አልሻረም ፣ አልዳነም ፣ አልደረቀም ፣ አልተረሳም።
  ።።።።።።።።።።።።
  ቁስሌን ነካብኝ በጣምም አመመኝ ፣ያልነካኝ እስኪነካኝ ግን ወዲያው ተሻለኝ።
  ..................★
  ሃተታ ወሬ ሳላበዛ ፣ ወደ ዋናው ጉዳይ እገባለሁ:
  በእርግጥ የአገሬ ቁስል ነው ፣ እኔም የሀገሬ ነኝ ፣ አገርም ነኝ ፣ አገር ያለ ሰው ፣ ሰው ያለ ሀገር ምን ዋጋ አለው?

  የምታውቁ እንደምታውቁት እኔም "እንደሰማሁት" እምዪ እናታለም በ1977 ዓም በደረሰባት ታላቅ ረሃብ በአለም አቀፍ ሚዲያዎች መነጋገሪያ መሆኗ እና እስካሁንም ፣ ብዙ ሃገሮች "ርሃብ" "ችግር" ለሚለው ፣ ምሳሌ:– "ኢትዪጵያ" የሚለው የማያወላዳ ትክክለኛ ምሳሌ እንደሆነ ይታወቃል። አንድ ሀጋር በርሃብ ምሳሌነት በዲክሽነሪ ስትመዘገብ የእኛው ኢትዪጵያ ብቻና ብቻ ናት ብዪ አስባለሁ። ለበለጠ መረጃ: ኦክስፎርድ ዲክሽነሪን መመልከት ይቻላል" Ethiopia ~Hungry...Drought" ይላል።
  ።።።።።።።።።።

  ቁስሌ እንዴት ተነካ? ማን ነካው? ምን አድርጌው ነካብኝ? አከመኝ አፅናናኝ ወይ? ይት ቦታ ነው? ዘራፍ!!!
  ↓ ↓ ↓ ↓
  የሆነ ነገር ለመግዛት ወደ አንድ ሱቅ ከጓደኛዪ ጋር አቀናሁ ፣ ከዚያም ’እነዚህ ሰዎች’ መቸም ለመጠየቅ አያርፉምና በተለመደው "ወደገደለው" በተባለው እንግሊዝኛው አንድ በአስተሳሰብ በሰል በእድሜ ቃ ጠና ያለ ሰውዪ "ዪ ፍሮም?" ማለት ነዋ! ጓደኛዪም እኔም "አይ አም ፍሮም ኢትዮጵያ" "አይ አም ፍሮም ማይ ቢዪሪፉል ካንትሪ" አለው አልኩትም። ኦ ኦ "She is very poor country in the world" በማለት በሚሰቀጥጥ ሁኔታ ድንገት ቁስሌን ሲነካው ፣ መሄጃ መሮጫ ፈለኩ፣ ወዲያውም "ዪ አር ቶኪንክ ዘ ስታፍ ዪ ዶንት ኖው አት ኦል" አልኩትና ፣ አስከትዪም ፣ ያለውን የተፈጥሮ መስህብና ስላላት ሃብት እንዲሁም በጉብኝት መልክ መጥቶ እንዲመለከት ያለኝን የቱሪዝም ዘገባ ጀመርኩ፣ ከዚያ በኋላ ሰውዪው አተኩሮ ሲመለከተኝና በአፅንኦት ሲያዳምጠኝ የሆነ የተማረ አንባቢ፣ ኪራይ ሳይሆን ኢንፎርሜሽን ሰብሳቢ መሆኑን ስረዳው ፣ እውነቱን አውቄ ማሳተባበያ እየሰጠሁ እንደሆነ እየገባሁ መሆኑ ገባኛና ፣ "ሌት ሚ ቴል ዪ ዘ ሪያሊቲ አልኩት" እህ ሲለኝ ፣ እውነቱን አፍረጥርጨ የማቀውን የሰማሁትንና ያነበብኩትን የተወሰነች ነገር ነገርኩትና ፣ ይሄ ያልከው ነገር ግን በአንተ እድሜ የሆነ ነገርና አሁን ታሪክ የሆነ ነገር ነው ፣ አንተም እንደምትለው አይደለም ፣ አሁንማ መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው አገሮች ልትገባ ትንሽ ነው የቀራት እድገቷም "2 ዲጅት?" ነው ፣ ስለዚህ ያልከው እውነት ቢሆንም በጣም የቆዪና ይህን ያህል የተጋነነ አይነት አልነበረም ፣ "ሺ ኢዝ ኖት ሰች ካይንድ ኦፎ ካንትሪ " እያልኩ እያወራሁት እየዘገብኩለት እያለሁ ፣ ድንገት ጓደኛዪ ዝው ብሎ ገብቶ ስለ "ደብል ዲጅት ፣ መካከለኛ ገቢና ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገበች ያለች መሆኗን የሉሲ መገኛ መሆኗን ቀጠን አድርጎ አቀጣጠነው"፣ ሰውዪውም ይሄኛው ሌላ ኢንፎ መሰለውና ቀዘቀዘ። ወኬ ወኬ "ዛት ኢዝ ናይስ አይ ድድንት ኖው ዚስ ፣ አይ አም ሶሪ አለኝና ፣ ኢትስ ኦኬ ሰር" ብሎት ሸኘነው።

  በጣም ሚገርመው እንዴት ኢትዪጵያን ከርሃብ ጋ እንዳቆራኛት ነው። እግዚአብሔር ሆይ ባክህን የሆነብንን ሊሆንብን ያለም ካለ አስበን። ፊትህ ምህረትህ በእኛ ላይ ይሁን።
  እስከመቼ እንሰደባለን?
  እስከመቼ እንሳቀቃላን ፣
  አንገታችንንስ ስንት ጊዜ እንደፋለን? እባክህን አስበን ፣ አንተ ካሰብከን ተቀባይነት እናገኛለን ፣ መሳቀቅንም እንረሳዋለን ፤ ተዘልለንም እንኖራለን። ተመስገን።

  ReplyDelete