Monday, December 14, 2015

ውግዘትና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት - ክፍል ስምንት


Read in PDF 
በዲያቆን ኢሩባኖን ዘኢየሱስ
ካለፈው የቀጠለ
3.  ድህረ ውግዘት ልናደርገው የሚገባን ጥንቃ
3.1.አውግዞ መለየት በቂ አይደለም

“ኤጲስ ቆጶስ ሆይ የበደለውን አውግዘህ ብትለየው በውጭ አትተወው፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን መልሰው እንጂ፡፡ የጠፋውንም ፈልግ፡፡ ስለኃጢአቱ ብዛት እድናለሁብሎ ተስፋ የማያደርገውን በሁሉ ጠፍቶ ይቀር ዘንድ አትተወው፡፡ እንዲህም ኤጲስ ቆጶስ የኃጥኡን ኃጢአት ሊሸከም ይገባዋል፡፡ እርሱም ፈጽሞ እንደበደለ
ያድርግለት፡፡ የበደለውንም “አንተ ተመለስ እኔም ስለእኔና ስለሁሉ በሞተው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምሳል ስለአንተ ሞትን እቀበላለሁ ይበለው፡፡”

(ፍትሐ ነገስት አን.5 ቁ.122)

    ኃጢአትን በግልጥ በመሥራቱና ብዙዎችን ስለማሰናከሉ የተወገዘ ሰው፤ ፈጽሞ ሊጣልና ሊወረውር አይገባውም፡፡ ምንም እንኳ ቃሉ “እንደአረመኔና እንደቀራጭ ይሁንልህ”(ማቴ.18፥17) ቢልም፤ “ለሥጋው ጥፋት ለሰይጣን እንዲሰጥ ቢፈረድም” (1ቆሮ.5፥5) አውግዘን የለየውን “ወንድም” ዳግም ልንፈልገው፤ ከደጅ ወደ ቤቱ ልንመልሰው “የቀጣንህ ቅጣት ይበቃሐልና ፤ ከልክ ባለፈ ሐዘን አትዋጥ ይልቅ ተመለስና ተጽናና … በክርስቶስ ፊት ይቅር ብለንሐል፡፡”(2ቆሮ.2፥6-11)
   ጌታ ኢየሱስ በዱርና በጫካ የጠፋውን፤ የባዘነውን በግ አዳምን ሲፈልገው (ሉቃ 15፥3-7)ብዙ ዋጋ ከፍሎ ነው፡፡ “ኤጲስ ቆጶሳት ሆይ መድኃኒታችንን ንጉሳችንን አምላካችንን ኢየሱስ ክርስቶስን አብነት ልታደርጉት ይገባችኋል፡፡ ጉበኞችም ልትሆኑ ይገባችኋል፡፡ እርሱንም ምሰሉት የምትራሩ ሰላምንም የምትፈልጉ ትሆኑ ዘንድ፡፡ … ኃጥእ ፩ ጊዜ ወይም ፪ ጊዜ ቢበድል ንቀህ ከአንድነት አትለየው፤ በምግብ ጊዜ ከእርሱ ጋር ተባበር አንጂ፡፡ንስሐውንም ተቀበል ፡፡ተጸጽቶ ወደአባቱ በተመለሰው ልጅ አምሳል (ሉቃ.15፥17-24) ልብስ አልብሳቸው፡፡ በጥምቀት ፈንታ እጅ በማኖር ባርካቸው፡፡ ንስሐ የሚገቡ ሰዎች በእጃችን በመባረክ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ያገኛሉና፡፡ ወደ ቀደመ ቦታቸውም መልሳቸው፡፡      (ፍትሐ ነገስት አን.5 ቁ.126፤132)
     እንግዲህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና የቤተ ክርስተያናችን ቀኖና ይህ ነው፡፡ አውግዞ መለየት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ መልሶ ማየትና መፈለግ፤ እድል መስጠት ይህን ሁሉ አድርገን በተመለሰ ጊዜ ይቅር ልንለው ይገባናል፡፡(ሉቃ.17፥3)

3.2.      አውግዘን ስንለይ ቂም ልንይዝ አይገባም

     ተወጋዡ ተወግዞ ሲለይ በአግባብ ያወገዝነው እንደሆነ ራሱን ለማየትና በንስሐ ለመመለስ ዕድል ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በላይ ካየነው ህግና ቀኖና ውጪ በጥላቻና በንቀት፤ በሐሰትም አውግዘን ከሆነ ግን ሰውየውን(ሴቲቱን) በክፉ በድለነዋልና ንስሐ ልንገባ፤ ይቅርታ ልንለምነውም ይገባናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በቀደመ ዘመን ታሪኳ ጳጳሳቶቿ መጽሐፍ ቅዱስ የያዙ ምዕመናንን “ከጳጳስ ውጪ እናንተ ልታነቡ አይገባችሁም” ብላ ይይዙና ያነቡ ያነቡ የነበሩ ምዕመናንን ታስገድል እንደነበር፤ እንግዳ ትምህርት አጊኝቼባችኋለሁ ያለችውን ደግሞ አፍንጫ ትፎንን ምላስ ታስቆርጥ፤ እስከአንገታቸው ድረስ ጉድጓድ አስቆፍራ አአንገታቸውን ብቻ አስቀርታ ከብት ታስነዳ፤ በሴቶች ብልት የጋለ ብረትና ፍህም ትጨምር፤ ቋንጃ ታስቆርጥ፤ በጋለ የብረት ጉጠት ዓይኖቻቸውን ታስወጣ፤ የእግረና የእጅ ጅማቶቻቸውንና ጆሮዐቸውን … ታስቆርጥ እንደነበር የማይነቅዘው ታሪክ ዛሬ ለአደባባይ አስጥቶታል፡፡ (ደቂቀ እስጢፋኖስና የደብረ ብርሃን ሸንጎ ገጽ 140፤ ደቂቀ እስጢፋኖስ     )
    ነገር ግን የተወገዙ ሰዎች “ቂም አንይዝባችሁም፡፡ አናወግዛችሁም ድኅነት ሊደረግላችሁ እንጥራለን፤ እንተጋለን እንጂ፡፡ …” (ተግሳጽ ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አን.4 ገጽ..51) ሊባሉ ሲገባ ያ ሁሉ መዓትና ቁጣን ማውረድ የቅንጣት ታህል ምንም የቃሉ መሠረት የለንም፡፡ ዛሬም ገና ሳይወገዙና ከተወገዙ በኋላም ሰዎችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የምናስደበድብ፣ የምናስጠቃ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ግፍንና አመጽን ከማብዛት በቀር ምንም አይፈይድላትም፡፡
        የማውገዝ ሥልጣን ያላት ቤተ ክርስቲያን ቂም ለመያዝና ግፍ ለመሥራት ፈጽሞ ከሙሽራዋ የለበሰችው ጠባይዋ አይደለም፡፡ ሙሽራዋ “ኃጢአት አላደረገም፥ ተንኰልም በአፉ አልተገኘበትም፤ ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም ፥ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ የሰጠ …”(2ጴጥ.2፥22-24) ነውና እንዲህ በክብርና በንጽዕና ታጌጥ ዘንድ እርሷም ተጠርታለች፡፡ በእውነትም ከክርስቶስ እውነትን እንጂ ሌላ ፈጽሞ ምንም አልተማረችም፡፡ “እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም፤ በእርግጥ ሰምታችሁታልና፥ እውነትም በኢየሱስ እንዳለ በእርሱ ተምራችኋል” (ኤፌ.4፥20-21)     

3.3.    ለመናፍቃንም ወንጌል መመስከር ይገባናል!

       የእግዚአብሔር ቃል በአዳኝነቱ ድንበር የለሽ ነው ፤ የትኛውንም ከድንጋይ የሚጠነክርን ልብ እንደሥጋ  የማለስለስ ልማድ አለው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል በየትኛውም ዘመን ኃጢአተኞችን ሲጠራ ፤ የረከሱን ሲያነጻ ፤ የወደቁትን ሲያነሣ ፤ መናፍቃንን ሲለይ ፤ ከሃድያንን ሲያሳፍር ፤ ዓለማውያንን ሲገስጽ በዘመን የእኒህ ሁሉ ዕደፈትና ነውር አላገኘውም፡፡ ፀሐይ በንጹሕ ቦታም ሆነ በቆሻሻ ቦታ ብትወጣ ዕድፈት እንደማያገኛት ነገር ግን ፀሐይ ፤ ፀሐይ ብቻ ሆና እንደምትቀጥል ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ባሕርይ ቅድስናውን ሳይለቅ ሁሉን ያለዕድፈት ያጠራል ፤ ይሠራል ፤ ያከናውናል ፤ ይመረምራል ፤ ይፈትናልም፡፡ (መዝ. 18፥30 ፤ 105፥19 ፤ ምሳ.30፥5)
     የእግዚአብሔር ቃል ለመናፍቃንም መነገር አለበት ስንል፥ መናፍቅነታቸውን ተቀብለን በማጽደቅ አይደለም ፤ ስህተታቸውን ማየት እንዲችሉ ፣ ከእግዚአብሔር ቃልና ፈቃድ የተለዩ መሆናቸውን ፣ ይህ የአለማመን አካሄዳቸውም ለሁለተኛው ሞት የሚያበቃቸው (ራዕ.21፥8) መሆኑን፥ መመለሳቸውን በመመኘት የያዝነውን እውነት በፍቅር (ኤፌ.4፥15) ልንገልጥላቸው ይገባናል፡፡ መናፍቅነት የሥጋ ሥራ ከሆነ (ገላ.5፥21) ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለውን፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ የሚዋጋውን፥ የልብንም ስሜትና አሳብ የሚመረምረውን” (ዕብ.4፥12) ቃል ባለመወሰን ልንሰብከው ይገባናል፡፡
      ጌታችን በወንጌል “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ.28፥19) ያለን መንቀሳቀስ እንዳለብንና ለሰው ሁሉ ወንጌልን መስበክ እንዳለብን ሲያሳስበን ነው እንጂ መናፍቃንን መለየትና መተው እንዳለብን አያሳስበንም፡፡ ደግሜ እላለሁ ፤ ከመናፍቃን ጋር በምንም ምን አንደራደርም ፤ ዳሩ ቢሳሳቱም ሰው ናቸውና በሕይወት በዚህ ምድር እስካሉ ድረስ በንስሐ እንዲመለሱ የተቻለንን ሁሉ በቅን ልብ ልናደርግ ይገባናል፡፡
     ብዙ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን አከባቢ ከምናያቸው ዋና ችግሮች አንዱ መናፍቃን የተባሉትን አካላት ማውገዝ እንጂ ማስተማር ፤ ወንጌል ለእነርሱም እንደሚገባቸው መዘንጋቱ ነው፡፡ የወንጌል ምስክርነት ጣዖት ለሚያመልኩ ፣ ለዘፋኞች ፣ ለአመንዝሮች ፣ ግራና ቀኛቸውን ለማይለዩ አህዛብና ለሌሎችም ካስፈለገ ለመናፍቃንም እንደሚያስፈልጋቸው አምነን ልንዘጋጅበት ፤ የጸሎታችንም ርዕስ አድርገን በጌታ ፊት በትጋት ልናቀርበው ይገባናል፡፡

3.4.     ከተወጋዡ ፍጹም መራቅ ይገባል
                   
“ለሚወጣ ሁሉ በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤  በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት። ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ  ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤”(2ዮሐ.10)

       ይህንን ርዕስ ሳነሳ አንድ ጥያቄ በውስጤ ይነሳል፡፡ ይኸውም፦ ማስተማር አለብን እያልን ደግሞስ እንዴት ነው መራቅ ያለብን? እንደአገልጋይነታችን መናፍቃንንም ሆነ የሰውን ዘር ሁሉ ወንጌልን የመመስከርና የማስታማር ግዴታ ሲኖርብን ፥ እንደአማኝ ደግሞ አብሮ አምልኮአችንን አንፈጽምምና ልንርቃቸው ይገባናል፡፡ ወንድሞች በሕብረት ሊቀመጡ የሚገባቸውና ያማረም የሚሆነው (መዝ.133፥1) ፤ “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና።” (ማቴ.18፥20) የተባለው አምነው በስሙ አንድ ሆነው ለተሰባሰቡት ብቻ ነው፡፡ ይህን ስናስብ ከየትኛውም መናፍቅ እንርቃለን፡፡
      ቅዱስ ዮሐንስ በዚህ ጉዳይ ሲደራደር እናያለን ፤ በቤታችንም መቀበል እንደማይገባን ፤ ልንቀበልም እንደማይገባን በግልጥ ይናገረናል ፤ ይህም መጠለያን ፣ ምግብን ፣ ልብስን ሰጠናቸው ፣ በገንዘብ ረዳናቸው ማለት የክፋት ትምህርታቸውን ተባበርን ፤ ሐሳባቸውን ደገፍን ፤ ለትምህርታቸው እውቅና ሰጠን ማለት ነው፡፡ ስለዚህም  በምንም በምን እነርሱንና ትምህርታቸውን መደገፍ በሚችል መልኩ የምናደርገው ነገር አይኖረንምና ልንርቃቸው ይገባናል፡፡ ለምን?

1.     ሙሉ ደመወዛችንን ስለሚያሳጡን


     ቅዱሱን ወንጌል በማገልገላችን ልንቀበል የሚገባን ትልቅ ሽልማት እንደሚገባን “ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እኅቶችን ወይም አባትን ወይም እናትን ወይም ሚስትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ፥ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን ወንድሞችንና እኅቶችንም እናቶችንም ልጆችንም እርሻንም መቶ እጥፍ፥ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይቀበል ማንም የለም።” (ማር.10፥29-30) የሚል ኪዳንናዊ ታላቅ ተስፋ በወንጌል ተገብቶልናል፡፡
    መናፍቃን ይህን የተሰጠንን ኪዳናዊ ታላቅ ተስፋና የደከምንበትን ሽልማታችንን እንዳንቀበል የሚያደርጉን እነርሱ ናቸው፡፡ “ሙሉ ደመወዝን እንድትቀበሉ እንጂ የሠራችሁትን እንዳታጠፉ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (2ዮሐ.8) እንዲል ከጌታ ልንቀበል ያለውን ዘላለማዊ ደመወዛችንንና ሽልማታችንን ፥ ሙሉ ደመወዛችንን ስለመቀበል ስንል የሚያጠፉትን እኒህን መናፍቃንን ልንርቃቸው ይገባናል፡፡
2.   የክርስቶስን ወንጌል ስለሚያጣምሙ

      “ …የሚያናውጡአችሁ የክርስቶስንም ወንጌል ሊያጣምሙ የሚወዱ አንዳንዶች አሉ እንጂ። ነገር ግን እኛ ብንሆን ወይም ከሰማይ መልአክ፥ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ፥ የተረገመ ይሁን። … ” (ገላ.1፥7-8) ቃሉ በመጀመርያ ከአይሁድ ተመልሰው ያለሙሴና ግዝረት መዳን አትችሉም በማለት ያመኑ ክርስቲያኖችን ያስጨንቁ የነበሩትን የሐሰት ወንድሞች ቢሆንም ፥ መናፍቃንም ይኸንኑ የጥበብ መንገድ ተከትለው ለማሳት ራሳቸውን ሲገልጡ ሌላ ወንጌል የላቸውም ፤ ነገር ግን ያንኑ የክርስቶስን ወንጌል ያጣምማሉ እንጂ፡፡ የክርስቶስን ወንጌል ስለሚያጣምሙም በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት በቅዱስ ጳውሎስ የተረገሙት እርግማን ይደርስባቸዋል ፤ ወይም ደርሶባቸዋል፡፡
   የክርስቶስን ወንጌል የሚያጣምሙ ለክርስቶስ ቃል ባዕለ ሥልጣንነት የማይታዘዙ ናቸው ማለት ነው፡፡ በተለይም ደቀ መዛሙርትን ባለመራራት ለሞት ለማሰናዳት ፥ ወደኋላቸው ለመሳብ እንዲመቻቸው (ሐዋ.20፥29-30) የሚያደርጉት ትልቁ የክፋት ጥበብ ከወንጌሉ እየጠቀሱ የወንጌሉን ቃል የማጣመም ሥራ መሥራት ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ነፍሱን በጎቹን ስለማዳን አኑሮ እንዳዳነና ምርኮ አድርጎ እንዳስከተለ እነርሱም የፍጥረትን ነፍስ ለመማገድና የስህተታቸው ተከታይ ለማድረግ በነፍሳቸው ተወራርደው ያገልግላሉ፡፡ ስለዚህ እኛ በጌታ መንፈስ ቅዱስ ጉልበት ይህን የስህተት አሠራር ለመጣል በዘመናችን ሁሉ ተግተን በጸሎት ጉልበት በመቃወም ስህተታቸውንና የክፋት ጥበባቸውን ልናፈርስ ይገባናል፡፡
3.  የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፥ ሃይማኖትን ይክዳሉና

      በኋለኛው ዘመን (1ጢሞ.4፥1) የተባለው ከጌታ በምድር ከመገለጥ ጀምሮ እስከዳግም ምጽአቱ ያለው መላውን ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህም መናፍቃን በሐዋርያት ዘመን ብቻ ያሉና የተነሱ ሳይሆን እስከፍጻሜ ዘመን ሊነሱ እንዳለ ነው የሚያሳየን፡፡ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችም ጊዜውን በተመለከተ ይኸንኑ ነው የሚያጸኑት፡፡ (ዕብ.1፥1 ፤ ራዕ.1፥1-3) መናፍቃን ልዩ ባሕርያቸው አጋንንነትን ትምህርት ማድመጥና ሃይማኖትን መካድ እንደሆነ ቃሉ ይነግረናል፡፡
      ለእኛ ግን እንድናደምጥና እንድንሠማ የታዘዝነው የጌታን ቃል ብቻ ነው፡፡ “ … እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው።” (ሮሜ.10፥17) እንደተባለ ልንሰማ የሚገባን የክርስቶስን ቃል ወይም መልዕክቱን ይዘው የሚመጡትን ብቻ ሊሆን ይገባናል፡፡ መናፍቃን ግን ከዚህ በተለየ መንገድ ነውና የሚሄዱት ፈጽሞ ልንርቃቸው ይገባል፡፡ 


ማጠቃለያ
 ትምህርተ ውግዘት ከበጣም ብዙ በጥቂቱ ይህን ይመስላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ውግዘትን ስታስብ እንደየመጨረሻ እርምጃ እንጂ እንደየመጀመርያ ወይም እንደበመቀያ ወይም እንደማስፈራርያ መንገድ ልትጠቀምበት አይገባትም፡፡ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ውግዘት ንጹሐንን አድብቶ ለመምታትና ስማቸውን ለማጠልሸት ፤ ለመደቆስም ጥቂት ማህበራት ወይም ቡድኖች እየተጠቀሙበት ያለ መሆኑን እያየን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሐሰተኞች በመካከላችን እንዲፋንኑ መተባበራችንን ያሳያል፡፡
    ቤተ ክርስቲያን አንድም ጌታ የሞተለት ወንድምም ሆነ እህት አላግባብ በሆነ በውግዘት በትር በመምታት እንዳታሳዝንና እንዳትበድል በብርቱ ልትጠነቀቅ ይገባል፡፡ ውግዘትንም ከዓላማው ውጭ ለሌላ ተግባር ማለትም ለማስፈራሪያነት ፤ ሌሎች ሃሳባቸውን እንዳይገልጡ ለማድረግ ፤ ጤናማ የሆነንና ምርምራዊ ትችትና ጥናትን የሚያቀርቡትን ለመቃወምና ለማጥቃት እንዳይውልም ከልብ መጨነቁም አስተዋይነት እንጂ መሸነፍና መበለጥም አይደለም፡፡ ጌታ ለመሪውም ለተመሪውም ጸጋንና ማስተዋልን እንዲያበዛ በመማለድ በጌታ ፊት እንጸልያለን፡፡ ምስጋና ይሁን፡፡ አንድ አምላክ ለሚሆን ለአብ ፣ ለወልድ ፣ ለመንፈስ ቅዱስ፡፡ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡ 

ተፈጸመ


ዋቢ መጻህፍት
       የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር መጽሐፍ  ቅዱስ፡፡ 1962 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፣ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት፡፡
       የጥንት አባቶቻችን  ሃይማኖት ፤ ሃይማኖተ አበው፡፡ 1982 ዓ.ም አዲስ አበባ ፤ ተስፋ ማተሚያ ቤት፡፡
       ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ ዘአፈወርቅ ፡፡ 1987 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ ተስፋ ማተሚያ ቤት፡፡
       መጽሐፈ ቅዳሴ ትርጓሜ
       ፍትሐ ነገሥት ሥጋዊ ወመንፈሳዊ የሕግ ምንጭ በግዕዝና በአማርኛ፡፡ 1992 ፤ አዲስ አበባ ፤ ተስፋ ማተሚያ ድርጅት፡፡ 
       አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ አባ)፡፡ ትምህርተ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ  ህይወት ፡፡ 1996 ፤ አዲስ አበባ፡፡ንግድ ማተሚያ ድርጅት(ማህበረ ቅዱሳን)፡፡
       ኪዳነ ወልድ ክፍሌ/አለቃ/፤ መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ፡፡ 1948 ዓ.ም፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡
       ኪዳነ ወልድ ክፍሌ(አለቃ)፡፡ ሃይማኖተ አበው ቀደምት ወፍልጠተ ውሉድ ደኃርት ፤ ያልታተመ፡፡
       የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ፤  የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9ኛ እትም ፣ 2002 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ፡፡ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡
       ከሳቴ ብርሃን ተሠማ ፤ የዐማርኛ መዝገበ ቃላት ፤ 1962 ፤ አዲስ አበባ ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፡፡
       ሞገስ ዕቁበ ጊዮርጊስ (ሊቀ መዘምራን)መርሐ - ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት 1989 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ፡፡ አሳታሚ ገ/ሥላሴ ብርሃኑ፡፡
       መልከ ጼዴቅ (አባ)፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ሁለተኛ ዕትም፡፡ 1996 ዓ.ም፡፡ አዲስ አበባ፡፡ ንግድ ማተሚያ ድርጅት፡፡
       አባ ጎርጎርዮስ (ሊቀጳጳስ) ፡፡ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ 2ኛ ዕትም ፣ 1986 ዓ.ም ፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ድርጅት፡፡
       አባ ጎርጎርዮስ (ጳጳስ) ፤ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በአለም መድረክ ፤ 1978፤ አዲስ አበባ ፤ አሳታሚ ያልታወቀ
       ብሩክ ገብረ ሊባኖስ (መምህር) ፤ የሰው ያለህ ፤ 2005 ዓ.ም ፤ ሜልበርን ፣ አውስተረሊያ ፤ ማተሚያ ቤቱ ያልተጠቀሰ፡፡
       ቄስ ኮሊን ማንሰል ፤ ትምህርተ ክርስቶስ ፤ 2003 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት የታተመ፡፡
       ቄስ ኮሊን ማንሰል ፤ ትምህርተ መንፈስ ቅዱስ ፤ 1999 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ በንግድ ማተሚያ ድርጅት የታተመ፡፡
       ካህሳይ ገ/እግዚአብሔር፡፡ ምንኩስና በኢትዮጲያ ዛሬና ትናንትና፤ 2000 ዓ.ም ፤ አሳታሚ አልተጠቀሰም፤
       ቤተ ክርስቲያንህን ዕወቅ ፤ 1988 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ብራና ማተሚያ ቤት፡፡
       አንዱዓለም ዳግማዊ (ዲያቆን) ፤ ሰዎች የሰውን ልጅ ማን  ይሉታል? ፤ ሐምሌ 1993 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት የታተመ፡፡
       (ጌታቸው ኃይሌ (ፕ/ር) ፤ ደቂቀ እስጢፋኖስ ፤ 2002 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ፕሬስ
       ኤልያስ ግርማ (መሪጌታ) ፤ ደቂቀ እስጢፋኖስና የደብረ ብርሃን ሸንጎ ፤ 2000 ዓ.ም ፤ ማተሚያ ቤቱ ያልጠቀሰ፡፡
       በአቡነ ጳውሎስ የተጻፈ ደብዳቤ
       አቡነ ሺኖዳ 3ኛ (ፓትርያርክ)  ፤ በዲያቆን ወንድወሰን ሶርሳ የተተረጎመ ፤ የይሖዋ ምስክሮች ኑፋቄ 1994 ፤ አዲስ አበባ ፤ ቼምበር ማተሚያ ቤት፡፡
       የኢትዮጲያ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት ሕገ መንግሥት ፤ ነሐሴ 15 ፣ 1987 ፤ አዲስ አበባ፡፡ ማተሚያ ቤቱ ያልተጠቀሰ፡፡
       የኢትዮጲያ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግስት የወንጀል ሕግ  ፤ 1997 ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ፡፡ ማተሚያ ቤቱ ያልተጠቀሰ፡፡
       ህብረት የሺጥላ ፤ ትምህርተ ውግዘት
       በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ ፤ WATCHTOWER BIBLE AND TRACT SOCIETY OF PENNSYLVANIA ፤ 1991፤ አሳታሚ WATCHTOWER BIBLE AND TRACT SOCIETY OF NEWYORK, INC. Brookly, New York, U.S.A.
       ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች ፤ 1995 ፤ አሳታሚዎች ፦ WATCHTOWER BIBLE AND TRACT SOCIETY OF NEW YORK, Inc.Brooklyn, New York, U.S.A
       ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ፤ 2009 ፤ German , አሳታሚዎች፦ Watchtower Bible and tract society of Pennsylvania.


No comments:

Post a Comment